በውድድር በተዋጠ ኅብረተሰብ ውስጥ የአእምሮ ሰላም ማግኘት
ኢየሱስ ክርስቶስ “ሰው ፊተኛ ሊሆን ቢወድ ከሁሉ በኋላ የሁሉም አገልጋይ ይሁን” በማለት ሐዋርያቱን መክሯቸዋል። ሐዋርያቱ ከመካከላቸው ማን የበላይ እንደሚሆን ይከራከሩ ነበር። ኢየሱስ እንደዚህ ዓይነቱን መንፈስ እንደሚጠላ ያውቁ ነበር። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ መንፈሳዊ እድገት እንዲያገኙ እርስ በርሳቸው እንዲፎካከሩ አላደረጋቸውም።—ማርቆስ 9:33–37
ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በፍጥረት ሥራ ስለ ተካፈለ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት እንዴት እንደተሠሩ ያውቅ ነበር። (ቆላስይስ 1:15, 16) የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ከሌሎች ጋር ጥቅም የለሽ በሆነ ፉክክር ውስጥ መግባት ሳያስፈልጋቸው የመሻሻል ችሎታ ነበራቸው። ሰዎች የበላያቸው የሚሆነውን ለመወሰን እርስ በርሳቸው መጣላት አላስፈልጋቸውም ኑሯቸውንም ለማሸነፍ ከእንስሳት ጋር መፎካከር አላስፈልጋቸውም።—ዘፍጥረት 1:26፤ 2:20–24፤ 1 ቆሮንቶስ 11:3
የውድድር መንፈስ ምንጭ
ታዲያ ይህን የመሰለ ከባድ የፉክክር መንፈስ በሰብአዊው ኅብረተሰብ ላይ ሊሠለጥን የቻለው እንዴት ነው? በሰው ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያ የሆነው ግድያ ለዚህ ፍንጭ ይሰጠናል። የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት የመጀመሪያ ልጅ የሆነው ቃየን ያሳየው የፉክክር መንፈስ አሳዛኝ ሁኔታ አስከተለ። የአቤል መሥዋዕት አምላክን ሲያስደስት የቃየን ግን ሳያስደስት በመቅረቱ ቃየን ወንድሙን አቤልን ገደለው። በዚህም ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ ቃየን “ከክፉው እንደ ነበረ ወንድሙንም እንደ ገደለ” ይናገራል።—1 ዮሐንስ 3:12፤ ዘፍጥረት 4:4–8
አዎን፣ የፉክክር መንፈስ ምንጭ እና አስፋፊ ክፉው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። ሰይጣን ከፍተኛ መብቶች የነበሩት የአምላክ መልአካዊ ልጅ የነበረ ቢሆንም ሌላ ተጨማሪ ነገር ለማግኘት ፈለገ። (ከሕዝቅኤል 28:14, 15 ጋር አወዳድር።) ይህም ፍላጎቱ ሔዋንን ባታለላት ጊዜ ተጋለጠ። የተከለከለውን ፍሬ በመብላት “እንደ እግዚአብሔር” ልትሆን እንደምትችል ተናገረ። (ዘፍጥረት 3:4, 5) እንደ እውነቱ ከሆነ ግን እንደ አምላክ ለመሆን የፈለገው የይሖዋ ተፎካካሪ የሆነው ሰይጣን ነበር። የነበረው ከአምላክ ጋር የመፎካከር ወይም የመወዳደር መንፈስ ለዓመፅ ገፋፋው።—ያዕቆብ 1:14, 15
ይህ መንፈስ ከአንዱ ወደ ሌላው የመተላለፍ ችሎታ አለው። አምላክ ለመጀመሪያው ቤተሰብ ሰጥቶት የነበረው ሰላም በሰይጣን ምክንያት ጠፋ። (ዘፍጥረት 3:6, 16) ሰይጣን ዲያብሎስ በአምላክ ላይ ካመፀበት ጊዜ ጀምሮ በሰው ልጆች መካከል የውድድር መንፈስ እንዲስፋፋ በማድረግ፣ እንዲያውም ብዙ ወንዶችና ሴቶች እርስ በርስ በፉክክር መተናነቅ የተሳካ ሕይወት ያስገኛል ብለው እስኪያምኑ ድረስ እንዲሳሳቱ በማድረግ የሰውን ዘር ገዝቷል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ሥራ ሁሉ አሉ” ይላል። (ያዕቆብ 3:14–16) ሰይጣን በዚህ መንገድ የሰው ልጆች ደስታና የአእምሮ ሰላም እንዲያጡ አድርጓል።
አለውድድር የሚገኝ የተሳካ ውጤት
መጽሐፍ ቅዱስ ከሰይጣን በተለየ ሁኔታ የውድድር መንፈስ ሳይኖራቸው የተሳካ ውጤት ያገኙ ሰዎችን ምሳሌ ይሰጠናል። በቀደምትነት የሚጠቀሰው ምሳሌ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስ በአምላክ መልክ ይኖር የነበረ ቢሆንም የባሪያን መልክ ይዞ ወደ ምድር መጣ እንጂ ከአምላክ ጋር እኩል የመሆንን ሐሳብ እንኳ ወደ አእምሮው አላገባም። ከዚህም በላይ ራሱን በጣም ዝቅ በማድረግ በመከራ እንጨት ላይ ለመሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። ይህ ከማንኛውም ዓይነት የፉክክር መንፈስ ነፃ የሆነ መለኮታዊ ሞገስ እንዲያገኝ አስቻለው። “በዚህም ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፣ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው።” (ፊልጵስዩስ 2:5–9) ማንኛውም ፍጡር ከዚህ የሚበልጥ ምን የተሳካ ውጤት ሊያገኝ ይችላል? ማንም ሌላ ፍጡር ባላደረገው መጠን አባቱን አስደስቷል። ይህንንም ያደረገው ያለ አንዳች የፉክክር ወይም የውድድር መንፈስ ነው።—ምሳሌ 27:11
ብዙ ቁጥር ያላቸው በሰማይ የሚኖሩ ታማኝ መላእክትም ተመሳሳይ ዝንባሌ አላቸው። የመላእክት ሁሉ የበላይ የሆነው ኢየሱስ ወደ ምድር በመጣበት ጊዜ ከመላእክት በጥቂት አንሶ የነበረ ቢሆንም በሚያስፈልገው ሁሉ በፈቃደኝነት አገልግለውታል። የተፈጠረውን አጋጣሚ ተጠቅመው የሊቀ መላእክትነቱን ቦታ ለመውሰድ አላሰቡም።—ማቴዎስ 4:11፤ 1 ተሰሎንቄ 4:16፤ ዕብራውያን 2:7
መላእክት አምላክ ፍጹም ያልሆኑ አንዳንድ ሰዎች ‘በመላእክት ለመፍረድ’ የሚያስችል ሥልጣንና የማይሞት መንፈሳዊ ሕይወት እንዲያገኙ ላወጣው ዓላማ ያሳዩት ዝንባሌ ለፉክክር መንፈስ ከፍተኛ ጥላቻ እንዳላቸው ያሳያል። (1 ቆሮንቶስ 6:3) መላእክት ይሖዋን በማገልገል ብዙ ተሞክሮና ፍጹም ካልሆኑ ሰዎች የበለጠ መልካም ሥራ የማከናወን ችሎታ አላቸው። ሆኖም ወደፊት በሚቀበሉት ሽልማት ሳይቀኑ በምድር ላይ የሚገኙትን ቅቡዓን በደስታ ያገለግሏቸዋል። (ዕብራውያን 1:14) ከፉክክር ነፃ የሆነው ጥሩ ዝንባሌያቸው በሉዓላዊው ጌታ በይሖዋ ዙፋን ፊት ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ ያስችላቸዋል።
ቀጥሎ በምድር ላይ እንዲኖሩ ከሞት የሚነሡትን የጥንት ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች እንውሰድ። አብርሃም በምሳሌነት የሚጠቀስ እምነት የነበረው ሰው ነበር። በተጨማሪም “ለሚያምኑ ሁሉ አባት” ነው ተብሎ ተጠርቷል። (ሮሜ 4:9, 11) ኢዮብ በጣም ታላቅ የሆነ የጽናት ምሳሌ ትቶልናል። (ያዕቆብ 5:11) “በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው” የነበረው ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ ወደ ነፃነት መርቷል። (ዘኁልቁ 12:3) ፍጹም ካልሆኑ ሰዎች መካከል ከእነዚህ ሰዎች የሚበልጥ እምነት፣ ጽናት እና ትሕትና ያሳየ ሰው ይገኛልን? ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች የሚወርሱት የአምላክን መንግሥት ምድራዊ ግዛት ነው። (ማቴዎስ 25:34፤ ዕብራውያን 11:13–16) እነርሱም እንደ መጥምቁ ዮሐንስ “በመንግሥተ ሰማያት ግን ከሁሉ የሚያንሰው” ይበልጣቸዋል። (ማቴዎስ 11:11) እምነታቸው፣ ጽናታቸው ወይም ትሕትናቸው ሰማያዊ ሕይወት ከተሰጣቸው ሰዎች እንደማያንስ፣ እንዲያውም እንደሚበልጥ በመናገር ለማጉረምረም ያስባሉን? በፍጹም አያደርጉትም! የአምላክ መንግሥት ምድራዊ ተገዢዎች በመሆናቸው ደስ ይላቸዋል።
ዛሬም ቢሆን የውድድር ዝንባሌ ከሌላቸው ሰዎች ጋር መዋል ደስ ያሰኛል። በመጀመሪያው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ያሱዎ ብዙ ወርቅ ገዝቶ ብዙ ትርፍ ለማግኘት በማሰብ ዕዳ ውስጥ ከገባ በኋላ ያለውን ንብረቱን ሁሉ አጣ። “ወዳጆቹ” ሁሉ ከዱት። ሚስቱ ከይሖዋ ምስክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምራ ስለነበረ በቤተሰቡ ላይ ባደረሰው ችግር በመጸጸት ወደ ስብሰባቸው ሄደ። ከጊዜ በኋላ የነበረውን የፉክክር መንፈስ አስወገደና ከይሖዋ ምስክሮች አንዱ ሆነ። በአሁኑ ወቅት ችግር ባጋጠመው ጊዜ ለመርዳት ፈቃደኛ በሆኑ ክርስቲያን ጓደኞች መሀል በመሆኑ ተደስቷል።
የአእምሮ ሰላም እንደያዙ መቆየት የሚቻለው እንዴት ነው?
ለውድድርና ለፉክክር በሚያነሳሳና አዘኔታ በሌለው ኅብረተሰብ ውስጥ እየኖሩ የአእምሮ ሰላም እንደያዙ መቆየት ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “ጥል፣ ክርክር፣ ቅንዓት፣ ቁጣ፣ አድመኛነት፣ መለያየት፣ መናፍቅነት፣ ምቀኝነት” የሥጋ ሥራዎች እንደሆኑና ሰዎች የአምላክን መንግሥት እንዳይወርሱ የሚያደርጉ ባሕርያት እንደሆኑ በመግለጽ እንደሚያወግዛቸው መገንዘብ ይኖርብናል። እነዚህ ሥራዎች ሁሉ ከፉክክር መንፈስ ጋር የማይነጣጠሉ ናቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ “እርስ በርሳችን እየተነሣሣንና እየተቀናናን በከንቱ አንመካ” በማለት የገላትያ ክርስቲያኖችን ማበረታታቱ ሊያስደንቀን አይገባም።—ገላትያ 5:19–21, 26
በዚህ ጥቅስ ዙሪያ ያለው ሐሳብ እንደሚያሳየው የጳውሎስ ደብዳቤ ራስ ወዳድነት የሞላበትን የፉክክር መንፈስ እንዴት ማስወገድ እንደሚቻል ያመለክታል። “የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ነው። እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም” በማለት ተናግሯል። (ገላትያ 5:22, 23) የመንፈስ ፍሬ አእምሯችንን ከፉክክር እንድናነጻ ይረዳናል። ለምሳሌ የፍቅርን ባሕርይ እንውሰድ። ጳውሎስ “ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፣ አይታበይም፤ የማይገባውንም አያደርግም፣ የራሱንም አይፈልግም፣ አይበሳጭም” በማለት ያብራራል። (1 ቆሮንቶስ 13:4–7) ፍቅርን በመኮትኮት የፉክክር መንፈስ የሚቀሰቅሰውን ቅንዓት ከሥሩ ነቅለን ለማጥፋት እንችላለን። ሌሎቹ የመንፈስ ፍሬዎችም ማንኛውንም የፉክክር መንፈስ ርዝራዥ ከአእምሮአችንና ከልባችን ጠርገን እንድናስወጣ ይረዱናል። ራስን የመግዛት ባሕርይ ከኖረን ማንኛውንም መሥዋዕት ከፍለን ከሌሎች ጋር ተወዳድረን እንድናሸንፍ የሚያነሣሳንን ግፊት ለመቆጣጠር እንችላለን።—ምሳሌ 17:27
ይሁን እንጂ እነዚህን ባሕርያት ለማዳበር የአምላክ መንፈስ በእኛ ላይ እንዲሠራ መፍቀድ ይኖርብናል። በጸሎት በመጽናትና የአምላክ መንፈስ እንዲረዳን በመጠየቅ ይህን የመንፈስ ቅዱስ ጤናማ አሠራር ልናበረታታ እንችላለን። (ሉቃስ 11:13) አምላክ ለጸሎታችን መልስ በመስጠት ምን ያደርግልናል? መጽሐፍ ቅዱስ “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል” በማለት መልስ ይሰጣል።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7
ይህ ነገር በኢየሱስ ሐዋርያት ላይ በግልጽ ታይቷል። ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት የጌታን እራት ካቋቋመ በኋላ እንኳ ከመካከላቸው ማናቸው ትልቅ እንደሚሆን ይከራከሩ ነበር። (ሉቃስ 22:24–27) ኢየሱስ በተለያዩ ጊዜያት አስተሳሰባቸውን እንዲያስተካክሉ ለመርዳት ሞክሮ ነበር። ነገር ግን ይህ የውድድር መንፈስ በውስጣቸው ሥር ሰድዶ ነበር። (ማርቆስ 9:34–37፤ 10:35–45፤ ዮሐንስ 13:12–17) ይሁን እንጂ ይህን ክርክር ካደረጉ ከ50 ቀን በኋላ መንፈስ ቅዱስን ሲቀበሉ አመለካከታቸው ተለወጠ። በጰንጠቆስጤ ዕለት በዙሪያቸው ለተሰበሰበው የማወቅ ጉጉት ላደረበት ሕዝብ እነሱን ወክሎ ስለሚናገረው ሰው ምንም ዓይነት ክርክር አልተነሣም ነበር።—ሥራ 2:14–21
ማንም ሰው በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የበላይ ገዥ የሚሆንበት ምንም ዓይነት ምክንያት አልነበረም። ስለ መገረዝ ጉዳይ ክርክር ተነሥቶ በሚነጋገሩበት በዚህ ከፍተኛ ግምት በሚሰጠው ስብሰባ ሊቀ መንበር የነበረው ኢየሱስ በሞተበት ወቅት ደቀ መዝሙር ያልነበረው ያዕቆብ ነበር። የክርስቲያን ጉባኤ የአስተዳደር አካል ያደረገውን ይህን ስብሰባ ማን ይምራ የሚል ክርክር ፈጽሞ አልተነሣም። ሐዋርያቱ በፉክክር መንፈስ ተበክለው ከነበሩበት ጊዜ በጣም ከፍተኛ የሆነ ለውጥ አድርገዋል። በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ የኢየሱስን ትምህርቶች ለማስታወስና በትምህርቶቹ ለማስተላለፍ የፈለጋቸውን ቁምነገሮች ለማስተዋል ችለዋል።—ዮሐንስ 14:26
የእኛም ሁኔታ ከዚህ ያልተለየ ሊሆን ይችላል። በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ በሌሎች ላይ ተረማምደን እድገት ለማግኘት እንድንጥር የሚያነሣሳንን የውድድር መንፈስ ልናሸንፍ እንችላለን። ከዚህ ይልቅ ከማንኛውም ሐሳብ የሚልቀውን የአእምሮ ሰላም እናገኛለን። መጽሐፍ ቅዱስ በጣም ኃይለኛ የሆነው የውድድር መንፈስ ምንጭ የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ በቅርቡ እንደሚታሰር ያረጋግጥልናል። (ራእይ 20:1–3) ከዚያ በኋላ በጎረቤቶች መካከል የሚፈጠር ፉክክር አይኖርም። ታዲያ ከዚህ የተነሳ የሚኖረው ኅብረተሰብ ምንም መሻሻል የማይታይበት ይሆናል ማለት ነውን? በጭራሽ! ሰዎች ወደ ፍጽምና የሚደርሱት በመካከላቸው በሚኖረው ፉክክር ሳይሆን ቤዛ ሆኖ በቀረበላቸው የኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት ነው።—1 ዮሐንስ 2:1, 2
ቀደም ሲል የተጠቀሰው ብዙ መኪናዎችን በመሸጥ በዚህ ዓለም ከፍተኛ ክብር የሚያስገኝ ሥራ ያከናወነው ካኖስክ አእምሮውንም አካሉንም ብዙ ካደከመ በኋላ በመጨረሻ ሥራውን ተወ። “አሁን ሕይወቴ በእውነተኛ ደስታ የተሞላ ነው” ይላል። አሁን የኢየሱስ ሕይወት በጣም የተሳካ የሆነበትን ምክንያት ለማስተዋል ችሏል። በአምላክ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ውስጥ ከሚሠራቸው ሥራዎች እውነተኛ እርካታ አግኝቷል። በዚህም መንገድ ከፉክክር ነፃ ለሚሆነው ለአዲሱ ዓለም በመዘጋጀት ላይ ይገኛል። አንተም ብትሆን በአካባቢህ ወደሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ ብትሄድና ከይሖዋ ምስክሮች ጋር ብትገናኝ ይህ አዲስ ዓለም ምን ሊመስል እንደሚችል ለማየት ትችላለህ።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአምላክ አዲስ ዓለም በሚኖረው ሰብአዊ ኅብረተሰብ ውስጥ ሰላምና ኅብረት ይሰፍናል