ለተሳካ ኑሮ ቁልፉ ውድድር ነውን?
“ተወዳድሮ ከማሸነፍ የሚበልጥ ምንም ነገር የለም።” በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ቫንስ ሎምባርዲ የተባሉት አሜሪካዊ የእግር ኳስ አሠልጣኝ የተናገሯቸውን እነዚህን ቃሎች መመሪያቸው አድርገዋል። በአሁኑ ጊዜ ኮምኒስት የነበሩ አገሮች ሕዝቦች ጭምር የውድድርን መሠረታዊ ሥርዓት ከሚያደንቁ ሕዝቦች መካከል ሆነዋል። ብልጽግና ሊገኝ የሚችለው በውድድር በሚመራ የገበያ ሥርዓት እንደሆነ ያምናሉ። በሩቅ ምሥራቅ አገሮች የሚገኙ ወላጆች ልጆቻቸው ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ተወዳድረው እንዲያሸንፉ ይፈልጋሉ። ፈተናዎችን ለማለፍ የሚያስችሉ ዘዴዎችን ወደሚያስተምሩ የግል ትምህርት ቤቶች ይልኳቸዋል። ይህ የውድድር መንፈስ የተጠናወታቸው ወላጆች ልጆቻቸው ወደፊት ሀብታም እንዲሆኑላቸው ወደ ጥሩ ትምህርት ቤት ለማስገባት ይጥራሉ።
ብዙዎች ለተሳካ ሕይወት ቁልፉ ውድድር ነው ብለው ያምናሉ። እንደነሱ እምነት፣ የሰው ልጅ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው እርስ በርሱ በመወዳደር ነው። የጃፓን የኢኮኖሚ ድርጅቶች ፌዴሬሽን ባደረገው ጥናት ከዋናዎቹ የኮርፖሬሽኖች ሥራ አስኪያጆች መካከል 65.9 በመቶ የሚያክሉት “የጃፓናውያን ኮርፖሬሽኖች ኃይል ዋነኛ ምንጭ እድገት ለማግኘት የሚደረገው ፉክክር ነው” ብለዋል። በእርግጥም የጃፓን ኩባንያዎች የተሳካላቸው መስለው ታይተው ነበር። ይሁን እንጂ ለተሳካ ኑሮ ቁልፉ ውድድር ነውን?
ውድድር ጥሩ ውጤት ያስገኛልን?
ከሌሎች ጋር የሚወዳደሩ ሰዎች ለእኔ ብቻ የማለትና የራስ ወዳድነት ዝንባሌ አላቸው። ሌሎች አልሳካ ሲላቸው ለእነርሱ የተሻለ ግምት የሚያሰጣቸው ስለሚመስላቸው ደስ ይላቸዋል። የስስት ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ሌሎችን በሚጎዱ ዘዴዎች ይጠቀሙ ይሆናል። ሌሎችን ተወዳድሮ በመጣል የተሳካ ኑሮ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት ወደምን ያደርሳል? ባለበት ኩባንያ ውስጥ በጣም ትልቅ ሰው ለመሆን በማሰብ የእሽቅድምድም ኑሮ ውስጥ የተነከረው ያሱዎ ያሳለፈውን ሕይወቱን በማስታወስ እንዲህ አለ፦ “በፉክክርና እድገት በመፈለግ ምኞት ተውጬ ነበር። እድገት ሳገኝ ከሌሎች እንደምበልጥ ተሰምቶኝ እደሰታለሁ። እነዚያ የበለጥኳቸው ሰዎች ከእኔ ከፍ ያለ ቦታ ሲሰጣቸው ግን በጣም ተቆጥቼ በኩባንያው አስተዳደር ላይ አጉረመርማለሁ። አንድ እንኳ እውነተኛ ጓደኛ አልነበረኝም።”
የውድድር መንፈስ ያለ ዕድሜ መሞትን ሊያስከትል ይችላል። እንዴት? በጃፓን ውስጥ የሚታተመው ማይኔቺ ዴይሊ ኒውስ የተባለው ጋዜጣ ካሮሼ ወይም ከሥራ ብዛት የተነሣ የሚመጣ ሞት ከታይፕ–ኤ ባሕርይ ጋር ቀጥተኛ ዝምድና እንዳለው ገልጿል። በታይፕ–ኤ ባሕርይ የተያዙ ሰዎች ባላቸው ጊዜ ሁሉ ለመጠቀም የሚጣደፉ፣ ከሌሎች ጋር የመወዳደርና የጥላቻ መንፈስ ያላቸው ሰዎች ናቸው። ፍረድማን ሮዝንማን የተባሉ አሜሪካዊ የልብ ሐኪም ታይፕ–ኤ ባሕርይ ከኮሮናሪ የልብ በሽታ ማለትም ወደ ልብ ጡንቻዎች የሚዘዋወረው ደም መጠን እንዲቀንስ ከሚያደርገው በሽታ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ገልጸዋል። አዎን፣ የፉክክር መንፈስ ለሞት ሊያደርስ ይችላል።
በተጨማሪም በሥራ ቦታ ላይ መፎካከር ሌላ ዓይነት የአካልና የአእምሮ መቃወስ ሊያስከትል ይችላል። ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን በጃፓን ውስጥ መኪና ለሚያሻሽጥ ድርጅት ዋነኛ የሽያጭ ሠራተኛ የነበረው ካኖስክ ነው። ይህ ሰው 1,250 መኪናዎችን በመሸጥ ከፍተኛ ሪኮርድ አስመዝግቧል። ፎቶግራፉ በኩባንያው ዋና መሥሪያ ቤት የዲሬክተሮች ቦርድ መሰብሰቢያ ክፍል ውስጥ ተሰቅሏል። የሥራ ባልደረቦቹን መረማመጃ አድርጎ እድገት ማግኘቱ ቢያስጠላውም ኩባንያው ግን እንዲፎካከር ይገፋፋው ነበር። ከዚህም የተነሣ በአንድ ዓመት ውስጥ የጨጓራና የአንጀት መቁሰል በሽታ ያዘው። በዚያው ዓመት 15 የኩባንያው ከፍተኛ ባለ ሥልጣኖች ታመው ሆስፒታል ሲተኙ አንዱ ደግሞ ራሱን ገድሏል።
ከሥራ ቦታ ውጭ ደግሞ ከማን አንሼ የሚለው አስተሳሰብ ሰዎች ኑሯቸው እንዲታይላቸው በመፈለግ ማለቂያ በሌለው የውድድር ኑሮ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል። (1 ዮሐንስ 2:16) እንደዚህ ያለው ዝንባሌ የሚጠቅመው የንግዱን ዓለም ብቻ ነው። ይህም በምድር ነጋዴዎች እጅ ላይ ብር እንዲፈስ ያደርጋል።—ከራእይ 18:11 ጋር አወዳድር።
የውድድርና የፉክክር መንፈስ በሥራ ቦታ ጥሩ የሥራ ውጤት ሊያስገኝ ቢችልም ንጉሥ ሰሎሞን “ደግሞም የሰውን ድካምና የብልሃት ሥራውን ሁሉ ተመለከትሁ፣ በባልንጀራውም ዘንድ ቅንዓት እንዲያስነሣ አየሁ፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው” ማለቱ ሊያስደንቀን አይገባም። (መክብብ 4:4) ስለዚህ በፉክክር በተዋጠ ኅብረተሰብ ውስጥ እየኖርን የአእምሮ ሰላማችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? የዚህን መልስ ለማግኘት የውድድር መንፈስ በመጀመሪያ ከየት እንደመጣ እንመልከት።