የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w94 3/15 ገጽ 26-28
  • ዊልያም ዊስተን መናፍቅ ወይስ ሐቀኛ ምሁር?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ዊልያም ዊስተን መናፍቅ ወይስ ሐቀኛ ምሁር?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር
  • የተለያየ ባሕርይ የነበራቸው ሰዎች
  • ውግዘት
  • እስከ መጨረሻው አወዛጋቢ ሰው ሆኗል
  • ዊልያም ዊስተን
    ንቁ!—2014
  • ታስታውሳለህን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • የርዕስ ማውጫ
    ንቁ!—2014
  • በምድር ላይ ለዘላለም መኖር—እንደገና የታወቀ ተስፋ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
w94 3/15 ገጽ 26-28

ዊልያም ዊስተን መናፍቅ ወይስ ሐቀኛ ምሁር?

ለእምነትህ ስትል መተዳደሪያ ሙያህን መሥዋዕት ታደርጋለህን? ዊልያም ዊስተን ለእምነቱ ሲል እንዲህ አድርጓል።

ዊስተን በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ላይ ከእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ጋር እንደማይስማማ በመግለጹ በ18ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ገደማ ብዙ ሃይማኖታዊ ተቃውሞ የደረሰበት ሰው ሆነ። ከዚህም የተነሣ ከጊዜ በኋላ እንደ መናፍቅ ተቆጥሮ ተወገዘ። ይህ የወሰደው እርምጃ ነቀፋ ብቻ ሳይሆን አክብሮትም ጭምር አስገኝቶለታል።

ዊልያም ዊስተን ማነው? ምንስ ነገር አከናውኗል?

የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር

ዊልያም ዊስተን በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሰር አይዛክ ኒውተን ጎበዝ የሥራ ባልደረባ ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የአይሁድ ታሪክ ጸሐፊ የሆነውን የፍላቭየስ ጆሴፈስን በእንግሊዝኛ ቋንቋ የታተሙ ጽሑፎች የምታነብ ከሆነ በ1736 በዊስተን የተተረጎመውን መጽሐፍ እያነበብክ ሊሆን እንደሚችል አያጠራጥርም። ሌሎች ትርጉሞች ቢኖሩም ምሁራዊ አተረጓጎሙ፣ ማስታወሻዎቹና ጥናታዊ ጽሑፎቹ እስካሁን ድረስ ተወዳዳሪ አልተገኘላቸውም። እስከ ዛሬ ድረስም መታተማቸው አልቀረም። ብዙዎች ዊስተን ካከናወናቸው ሥራዎች ሁሉ ከፍተኛው ይህ የትርጉም ሥራው እንደሆነ ይገምታሉ።

ይሁን እንጂ ፕሪሚቲቭ ኒው ቴስታመንት የተባለው የዊስተን የግሪክ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። ይህ ትርጉም ለኅትመት የበቃው በዊስተን 78ተኛ ዓመት ዕድሜው በ1745 ነው። ዊስተን አራቱን ወንጌሎችና የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን የተረጎመው ከኮዴክስ ቤዛይ ሲሆን የጳውሎስን ደብዳቤዎች ደግሞ ከክለርሞንት ኮዴክስ እንዲሁም ራእይን ጨምሮ የቀረውን ክፍል ደግሞ ከአሌክሳንድሪን የብራና ጽሑፍ ነው። በ1 ዮሐንስ 5:7 ውስጥ የተጨመረውን የሐሰት ጥቅስ አስቀርቶታል። ዊስተን እነዚህን ሦስት ጥንታዊ የግሪክኛ ጽሑፎች የመረጠው በወቅቱ ከነበሩት ጥንታዊ ጽሑፎች ሁሉ የተሻሉ ስለሆኑ ነው።

ዊስተን ይህን እንዲያደርግ የገፋፋው ለመጽሐፍ ቅዱስ የነበረው ፍቅር ነው። ዊስተን ይኖር በነበረበት ዘመን አይሎ የነበረው አመለካከት በአምላክ ለማመን ምክንያታዊ አስተሳሰብ ብቻ ይበቃል የሚለው የዲይዝም ፍልስፍና ነበር። ዊልያም ዊስተን—ኦነስት ኒውቶኒያን የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው ከሆነ ዊስተን “ምንም ስህተት የማይገኝበት የጥንት ታሪክ ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ነው የሚለውን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ አመለካከት” አጥብቆ ይደግፍ ነበር። እዚህ ላይ የገባው “ኒውቶኒያን” የሚለው ቃል በፕሪንሲፒያ ንድፈ ሐሳብ የታወቀውን አይዛክ ኒውተንን ያመለክታል። ኒውተን በዚህ ስሌት አማካኝነት የአጽናፈ ዓለምን የስበት ሕግ አብራርቷል። የኒውተን አስተሳሰብ በዊልያም ዊስተን ላይ ከባድ ተጽዕኖ አሳድሯል። እንዴት?

የተለያየ ባሕርይ የነበራቸው ሰዎች

ዊልያም ዊስተን የተወለደው በ1667 ሲሆን አባቱ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ቄስ ነበር። በ1693 የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ቄስ ሆኖ ከተሾመ በኋላ የሒሳብ ትምህርት ለማጥናትና የኒውተን ረዳት ለመሆን ወደ ካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ተመለሰ። በኒውተንና በዊስተን መካከል በጣም የጠበቀ ግንኙነት ተመሠረተ። ኒውተን ከሦስት ዓመት ገደማ በኋላ የነበረውን የሉካዚያን ማለትም የሒሳብ ፕሮፌሰርነት ማዕረጉን ሲለቅ ዊስተን በእሱ ምትክ እንዲሾም አድርጓል። ዊስተን የከዋክብት ጥናትና የሒሳብ ትምህርት አስተማሪ በመሆን ሥራውን ቀጠለ። ይሁን እንጂ የኒውተን ተጽዕኖ ለመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን አቆጣጠርና ሃይማኖታዊ ትምህርት ጥልቅ ፍላጎት እንዲኖረው ገፋፍቶታል።

ኒውተን የሃይማኖት ሰው ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጠቀሰው የሺህ ዓመት ግዛት ጠንካራ እምነት ስለነበረው ስለ ዳንኤል ትንቢቶችና ስለ ራእይ መጽሐፍ በሰፊው ጽፏል። ይሁን እንጂ ከእነዚህ ጽሑፎች ውስጥ አንዱም ኒውተን በሕይወት በነበረበት ወቅት ለኅትመት አልበቃም። የሥላሴን ትምህርት አይቀበልም ነበር። ይሁን እንጂ “ኒውተን የያዘው ፀረ ሥላሴ አመለካከት እንዳይታወቅበት በመፍራት” ሥላሴን የሚቃወመውን ማስረጃውን ከማሳተም ወደኋላ እንዳለ ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ጠቅሷል። ኤፍ ኢ ማኑኤል አይዛክ ኒውተን ሂስቶሪያን በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንደሚከተለው በማለት ገልጸዋል፦ “የኒውተን ቡድን ሐሳባቸውን በምሥጢር የሚይዙ ወይም ስሜታቸውን አምቀው የሚያስቀሩ ነበሩ።  . . ኒውተን ነገሮችን በሆዱ የሚይዝ ሰው ሲሆን ዊስተን ግን ሐሳቡን በአደባባይ የሚገልጽ ሰው ነበር።” ስለዚህ ሁለቱ ሰዎች የተለያዩ ባሕርያት ነበሯቸው።

ውግዘት

ዊስተን በሐምሌ 1708 የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን በአትናቴዎስ ድንጋጌ የተገለጸውን የሥላሴን የሐሰት ሃይማኖታዊ ትምህርት በተመለከተ ማሻሻያ እንዲያደርግ አጥብቆ በማሳሰብ ለካንተርበሪ እና ለዮርክ ሊቀ ጳጳሳት ደብዳቤ ጽፎ ነበር። ከዚያም አርፎ ቢቀመጥ እንደሚሻለው ማስጠንቀቂያ ሳይሰጠው እንዳልቀረ መረዳት ይቻላል። ይሁን እንጂ ዊስተን በአቋሙ ጸና። “እኔ እነዚህን ነጥቦች ከሥረ መሠረታቸው አጥንቻቸዋለሁ። ሙሉ በሙሉ አምኜባቸዋለሁ፣ ቤተ ክርስቲያን በእነዚህ ነጥቦች ላይ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በጣም ስትሳሳት ቆይታለች፤ ከአሁን በኋላ በአምላክ በረከት የሚቻለኝ ከሆነ ቤተ ክርስቲያን ከእንግዲህ ወዲህ በእነዚህ ነጥቦች እንዳትታለል አደርጋለሁ” ብሏል።

ኒውተን በማኅበራዊ ኑሮም ሆነ በትምህርት ደረጃው የነበረው ክብር እንዳይነካ ይፈራ ነበር። ዊስተ ግን ምንም ዓይነት ፍርሃት አልነበረውም። ዊስተን ፀረ ሥላሴ የሆነ እምነቱን ካጠናቀረ በኋላ አመለካከቱን የምታብራራ አንዲት በራሪ ጽሑፍ አዘጋጀ። ይሁን እንጂ ጽሑፉ ከተለመደው አመለካከት ጋር የማይስማማ ነው ተብሎ ስለታሰበ በነሐሴ 1708 ይህችን ጽሑፍ ለማሳተም የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ፈቃድ ከለከለው።

በ1710 ዊስተን ከእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ተቃራኒ የሆነ የሃይማኖት ትምህርት ያስተምራል የሚል ክስ ቀርቦበት ነበር። ጥፋተኛ ሆኖ ስለተገኘ የፕሮፌሰርነት ማዕረጉን ተገፈፈ፤ እንዲሁም ከካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ተባረረ። ሆኖም ለአምስት ተጨማሪ ዓመታት በፍርድ ቤት ሲታይ የቆየ ክስ ቢመሠረትበትም ዊስተን መናፍቅ ነው የሚል ፍርድ አልተፈረደበትም።

ኒውተን የነበረው ፀረ ሥላሴ አመለካከት ከዊስተን ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም ኒውተን ጓደኛውን የሚደግፍ ምንም ነገር አልተናገረም። እንዲያውም ከጊዜ በኋላ አውግዞታል። ሥላሴን የሚያጋልጠው የኒውተንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥናት የያዘው ጽሑፍ እሱ ከሞተ ከ27 ዓመት በኋላ በ1754 ለኅትመት በቃ። ይሁን እንጂ ከሁለት ዓመት በፊት ለሞተው ለዊስተን ምንም አላደረገለትም።

ዊስተንን ከፍተኛ ክብር ካለው ከሮያል ሶሳይቲ ያስወጣው ኒውተን እንደሆነ ይገመታል። ይሁን እንጂ ዊስተን ተስፋ አልቆረጠም ነበር። ዊስተንና ቤተሰቡ ወደ ለንደን ሄዱ። በዚያም የጥንቱን ክርስትና የሚያስፋፋ አንድ ማኅበር አቋቋመ። ዊስተን ሙሉ ኃይሉን በሥነ ጽሑፍ ሥራ ላይ አዋለ። በዚያ ጊዜ ከጻፋቸው መጻሕፍት ከፍተኛ ግምት የተሰጠው አራት ጥራዞች ላሉት ፕሪሚቲቭ ክርስቲያኒቲ ሪቫይቭድ ለተባለው መጽሐፍ ነበር።

እስከ መጨረሻው አወዛጋቢ ሰው ሆኗል

ዊስተን ሳይንቲስት እንደመሆኑ መጠን መርከበኞች በባሕር ላይ የኬክሮስን መሥመር ለማግኘት የሚያስችላቸውን የተለያዩ ዘዴዎች አጥንቷል። ሐሳቦቹ በጊዜው ሥራ ላይ ባይውሉም ለሥራው ያሳየው ትጋት በመጨረሻ የባሕር ክሮኖሜትር እንዲሠራ አስችሎታል። ምንም እንኳን በጊዜው እንደነበሩት ሰዎች ሁሉ ዊስተን በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ላይ የነበረው አብዛኛዎቹ አመለካከቶች ትክክል ባይሆኑም እውነትን ለመፈለግ ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም። ጅራታም ኮኮቦች ስለሚጓዙበት ምህዋርና በኖኅ ዘመን ደርሶ የነበረው የውኃ ጥፋት ስላስከተለው ውጤት የጻፋቸው ትራክቶች ዊስተን ለሳይንሳዊና ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነቶች ማስረጃ ለማቅረብ ከጻፋቸው ጽሑፎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። ይሁን እንጂ የሥላሴ ትምህርት ቅዱስ ጽሑፋዊ አለመሆኑን የሚያጋልጡት ጽሑፎቹ ሌሎች ጽሑፎቹን በሙሉ የሚያስንቁ ናቸው።

ዊስተን በነበረው የድፍረት አቋም መሠረት በ1747 የእንግሊዝን ቤተ ክርስቲያን ትቶ ወጣ። ቃል በቃልም ሆነ በምሳሌያዊ አባባል ቤተ ክርስቲያኑን ትቶ ወጥቷል። አንድ ቄስ የአትናቴዎስን ድንጋጌ ማንበብ በሚጀምርበት ጊዜ ዊስተን ቤተ ክርስቲያኑን ትቶ ወጣ። ኤ ሪሊጂየስ ኢንሳይክሎፔዲያ ስለ ዊስተን እንደሚከተለው ይላል፦ “ማንም ሰው የዊስተንን ድፍረት የተሞላበት የግልጽነትና የእውነተኝነት ባሕርይ፣ የማያወላውል አቋምና ቀጥተኛ የሆነ ጠባይ ማድነቅ አለበት።”

ዊልያም ዊስተን ከእውነት ሊያፈገፍግ የማይችል ሰው ነበር። በሰዎች ዘንድ ከመወደስና ከመሞገስ ይልቅ በራሱ ጽኑ እምነት መመራትን እንደ ውድ ነገር ይቆጥር ነበር። ዊስተን ብዙ ውዝግብ ያስከተለ ሰው ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን በድፍረት ደግፎ የተከራከረ ሐቀኛ ምሁር ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

[ምንጭ]

Copyright British Museum

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ