ስለ ሃይማኖት ግድ የለሽ መሆን የማይገባህ ለምንድን ነው?
በምድር ላይ በየትኛውም አገር የሚኖሩ ሰዎች ለሃይማኖት ስሜት አላቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ስለ ሃይማኖት ምንም ደንታ የለኝም ብለው በግልጽ የሚናገሩ ብዙ ሰዎች አሉ። ግን እነዚህ ሰዎች ከመጀመሪያው ጀምሮ ይህን የመሰለ አቋም ነበራቸውን?
ሰው በቁሳዊ ነገሮች ብቻ ሙሉ በሙሉ እንዲረካ ሆኖ አልተፈጠረም። ሰው መንፈሳዊ አቋም ያስፈልገዋል። ለመኖር አስፈላጊ የሆኑትን ቁሳዊ ነገሮች በማግኘትና አልፎ አልፎ በመዝናናት ላይ ብቻ የተመሠረተ ዕለታዊ ኑሮ የአንድን ሰው ውስጣዊ ፍላጎቶች ሙሉ በሙሉ አያሟላም። ሰዎች ከእንስሳት የተለዩ ናቸው። ‘የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው?’ ‘የተፈጠርነው ብዙ ደስ የሚሉና ያንኑ ያህል ደግሞ ብዙ አስቀያሚ የሆኑ ነገሮች የሞሉበት አጭር ሕይወት ለመኖር ብቻ ነውን?’ ብለው ይጠይቃሉ። አንተስ እንደነዚህ ያሉ ጥያቄዎችን ጠይቀህ አታው ቅምን?
ይሁን እንጂ ዛሬ ያሉ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ያደጉት ለሃይማኖት ምንም ስሜት እንዳይኖራቸው የሚያደርጉ ተስፋ አስቆራጭ ግፊቶች በሞሉባቸው አካባቢዎች ነው። ይህ ዓይነቱ ግፊት ከቤተሰቦቻቸው፣ ከአስተማሪዎቻቸው፣ ከእኩዮቻቸው ወይም ከመንግሥት የመጣ ሊሆን ይችላል።
ስካላብሪኖ የተባለ አልባኒያዊ ወጣት አገሪቱ በኮሚኒስት አገዛዝ ሥር በነበረችበት ወቅት ሕዝቡ አምላክ የለም የሚል ትምህርት ይሰጠው እንደነበረ ገልጿል። በተጨማሪም ስለ ሃይማኖት ማውራት በጣም አደገኛና ሊያሳስርም የሚችል ነገር ነበር። ይሁን እንጂ በ1991 በስዊዘርላንድ ስደተኛ ሆኖ ሲኖር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት አጋጣሚ አገኘ። እርሱም አጋጣሚውን ተቀበለ። ለምን?
አልባኒያ በነበረበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ የሚባል መጽሐፍ አለ እየተባለ ሲነገር ይሰማል፤ ሆኖም ስለ መጽሐፉ ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም። ስለዚህ በመጀመሪያው ላይ ለማጥናት የተነሳሳበት ዋና ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስን ለመመርመር ፍላጎት ስላደረበት ላይሆን ይችላል። ምንም እንኳን ጥናቱን ሲጀምር አምላክ ለሰው ልጆችና ለምድር ስላለው ዓላማ እንደሚያጠና ቢገለጽለትም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቱን የሚኖርበትን አገር ቋንቋ ለማሻሻል እንደሚረዳው አጋጣሚ አድርጎ ተመልክቶት ነበር። ሆኖም እየተማረው ያለው ነገር ውስጥ ውስጡን የነበረውን መንፈሳዊ ናፍቆት እያረካለት እንዳለ ወዲያው ተረዳ። ሰላም የሚሰፍንበት አዲስ ዓለም እንደሚመጣ፣ ያም ዓለም ሰዎች ለመኖር የሚያስፈልጓቸው ነገሮች ሁሉ ተትረፍርፈውላቸው ለዘላለም እየተደሰቱ የሚኖሩበት እንደሚሆን አምላክ የሰጠው ተስፋ ልቡን በጣም አስደሰተው። እሱና ቤተሰቡ በዚያ አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር የሚችሉ መሆናቸውን ሲያውቅ ፍላጎቱ ይበልጥ ጨመረ። ይህን ምሥራች ሰምቶ ዝም ማለት አላስችል ስላለው አልባኒያ ለሚኖሩት ቤተሰቦቹ ደውሎ ነገራቸው።
በሩስያ የሚኖረው አሌክሲም ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኘው ትክክለኛ እውቀት የሰውን ሕይወት ምን ያህል ሊለውጥ እንደሚችል በማየቱ በጣም ተገርሟል። በችግሮች ማጥ ስለተዋጠና የሕይወት ዓላማ ምን ስለመሆኑ የሚያረካ ማብራሪያ ሊያገኝ ስላልቻለ ራሱን ሊገድል አሰበ። በመጀመሪያ ግን ጓደኛውን ለመጠየቅ ወደ ፊንላንድ ሄደ። በባቡር እየተጓዘ ሳለ አብረውት ከተሳፈሩት መንገደኞች ለአንዳንዶቹ ስላለበት ችግር ነገራቸው። ችግሩን ካዋያቸው መንገደኞች መሀል አንዲት የይሖዋ ምሥክር ነበረች። እሷም መጽሐፍ ቅዱስ ለእንደነዚህ ዓይነት ችግሮች መፍትሔ ስለሚሰጥ መጽሐፍ ቅዱስ ቢያጠና ጥሩ እንደሆነ አጥብቃ መከረችው። እሱ ግን የነገረችውን ከቁም ነገር አልቆጠረውም። ሲመለስም እንዲሁ ዓይነት ነገር አጋጠመው። በዚህ ጊዜ ያነጋገረችው እህት እሷም እንዲህ ዓይነት ችግሮች እንደነበሩባትና መጽሐፍ ቅዱስ ችግሮቿን እንድታሸንፍ እንደረዳት ገለጸችለት። እሷም መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና አበረታታችው። እቤቱ ሲደርስ ስልክ ተደወለ። ስልክ የደወለችለት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት በመጀመሯ በጣም የተደሰተችው ሌላ ጓደኛው ነበረች። ሰውዬው መጽሐፍ ቅዱስ የጎደለኝን ነገር ሊያሟላልኝ ይችል ይሆናል የሚል አመለካከት እየያዘ መጣ። ይሁን እንጂ የሚረዳው ሰው ካላገኘ መጽሐፍ ቅዱስ ሊገባው እንደማይችል አወቀ። ስለዚህ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ቋሚ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ተስማማ። በስብሰባዎቻቸውም ላይ መገኘት ጀመረ። በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች መሠረት ሕይወታቸውን አስተካክለው የሚኖሩ ሰዎች ምንም እንኳን ሰው ሁሉ የሚደርስበት ችግር በነሱም ላይ የሚደርስ ቢሆንም ደስተኞች ሊሆኑ የቻሉበት ምክንያት ምን እንደሆነ ለመረዳት ጊዜ አልፈጀበትም።
ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን አፈጣጠር ጠለቅ ብሎ ስለሚያውቅ “ሰው በእንጀራ ብቻ ሊኖር አይችልም” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 4:4 ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) እንዲሁም “ለሚያስፈልጓቸው መንፈሣዊ ነገሮች ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው” ብሏል። (ማቴዎስ 5:3 አዓት) ደስተኞች የሚሆኑት የጐደላቸውን ነገር በደንብ ስለሚገነዘቡ፣ ይህንን ለማሟላት አስፈላጊ እርምጃዎችን ስለሚወስዱና በዚህም ምክንያት የአምላክን በረከት ስለሚያገኙ ነው። ይሁን እንጂ የአንድ ቤተ ክርስቲያን አባል ስለሆንን ወይም ቤተ ክርስቲያን ሄደን ስላስቀደስን ብቻ በመንፈሳዊ የጎደለንን ነገር ሊሟላልን አይችልም። ብዙ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች የሚከናወኑበት ሃይማኖት ይማርከን ይሆናል፤ ነገር ግን በሕይወታችን ውስጥ ለሚያጋጥሙን ችግሮች ከእውነታው ያልራቀ መፍትሔ ይሰጠናልን? ምንም እንኳን አንድ ሃይማኖት አንዳንድ ትክክለኛ የሆኑ መሠረታዊ መመሪያዎችን የሚሰብክ ቢሆንም የሕይወትን እውነተኛ ዓላማ የሚያሳውቅ ካልሆነ የሚያስፈልግህን መንፈሳዊ ነገር ሊያሟላልህ ይችላልን? ከዚህም ይበልጥ የሚያሳስበው ደግሞ እንዲህ ዓይነቱን ሃይማኖት መከተል ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖርህ ይረዳሃልን? ይህ ካልሆነ እውነተኛ እርካታ ሊያስገኝ አይችልም።
በዚህ ረገድ ብዙ ሰዎች ከዚህ በፊት ያላገኙትን አንድ ነገር ለማግኘት ፍለጋ ጀምረዋል።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአንድ ቤተ ክርስቲያን አባል መሆንህ ብቻ የጐደለህን መንፈሳዊ ነገር ያሟላልሃልን?
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስ እየገባቸው ሲሄድ ሕይወታቸው ትርጉም ያለው ሆኖላቸዋል