የጊልያድ ተመራቂዎች ‘ከመቀበል ይልቅ በመስጠት የበለጠ ደስታ’ ያገኛሉ
ዕለቱ እሁድ መጋቢት 6, 1994 ነው። የዓለም አቀፉ ዋና መሥሪያ ቤት የይሖዋ ምሥክሮች የቤቴል ቤተሰብና ተጋባዥ እንግዶች ለአንድ አስደሳች በዓል ተሰብስበዋል። ይህም በዓል የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት የ96ኛው ኮርስ ተማሪዎች የምረቃ ሥነ ሥርዓት ነው። በይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል ውስጥ ወደ ሃያ ለሚጠጉ ዓመታት ያገለገለውና የፕሮግራሙ ሊቀ መንበር የነበረው ካርል ኤፍ ክላይን ባቀረበው የመክፈቻ ንግግሩ ላይ ለ46ቱ ተማሪዎች እንደሚከተለው ሲል ተናገረ፦ “ኢየሱስ ከመቀበል ይልቅ በመስጠት የበለጠ ደስታ ይገኛል ብሏል። እናንተም በሚስዮናዊነት ምድባችሁ የሚያጋጥማችሁ ይኸው ነው። ማለትም ይበልጥ በሰጣችሁ በመጠን ይበልጥ ደስተኞች ትሆናላችሁ።”—ሥራ 20:35
የመሰነባበቻ ምክሮች
ከዚያም ለተማሪዎቹ የሚቀርቡት ተከታታይ ንግግሮች ቀጠሉ። “ጽናት ይሖዋን ያስከብረዋል” የሚል መልእክት ያለው ንግግር ያቀረበው የአገልግሎት ክፍል ኮሚቴ አባል የሆነው ሊዮን ዊቨር ነበር። ሁላችንም ፈተናዎች ያጋጥሙናል። (2 ቆሮንቶስ 6:3–5) ወንድም ዊቨር “ተጽዕኖ በሚደርስብን ጊዜ በራሳችን ላይ መታመን ይቀናናል” አለ። ይሁን እንጂ “በሰዎች ላይ ሊደርስ የሚችል ምንም ዓይነት ፈተና ቢደርስባችሁ ይሖዋ የሚደርስባችሁን ፈተና ይመለከታል። ከአቅማችሁ በላይ እንድትፈተኑ በፍጹም አይፈቅድም” ሲል ተማሪዎቹን አሳሰባቸው።—1 ቆሮንቶስ 10:13
ከዚህ በማስከተል የአስተዳደር አካል አባል በሆነው በሌይማን ስዊንግል የቀረበው ንግግር ርዕስ “የተሰጣችሁን የሥራ ምድብ ሁልጊዜ በእንክብካቤ ጠብቁት” የሚል ነበር። እስራኤላውያን የት እንደሚኖሩና ምን እንደሚያደርጉ ሁልጊዜ የሚመርጡት እነሱ አልነበሩም። ለእያንዳንዱ ነገድ መሬት ተከፋፍሎ ተሰጥቷቸው ነበር። ሌዋውያን ደግሞ የተወሰኑ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ ተመድበው ነበር። ዛሬም በተመሳሳይ እንደ ሚስዮናውያንና የቤቴል ቤተሰብ አባላት ያሉት በልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የሚሠሩ የት እንደሚኖሩና ምን እንደሚሠሩ የሚወስኑት ራሳቸው አይደሉም። አንድ ሰው የተሰጠውን የሥራ ምድብ ለመቀበል ቢያወላውልስ? ወንድም ስዊንግል “የእምነታችን ራስ የሆነውን ኢየሱስን በትኩረት ከተመለከታችሁና የእሱን ምሳሌ በቅርበት ከመረመራችሁ በቀላሉ ዝላችሁ አትወድቁም” አለ።—ዕብራውያን 12:2, 3
የመጠበቂያ ግንብ የእርሻ ጣቢያ ኮሚቴ አባል የሆነው ሊዮናርድ ፒርሰን በመቀጠል ያቀረበው ንግግር “ከትኩረት አቅጣጫችሁ ፈቀቅ አትበሉ” የሚል ነበር። እንዲህ አለ፦ “በጣም ጥሩ ካሜራና ፎቶግራፍ የምታነሱት በጣም ውብ የሆነ ቦታ ሊኖራችሁ ይችላል። ነገር ግን የካሜራችሁ ፎከስ (እይታ) ካልተስተካከለ የምታነሱት ፎቶ ግራፍ ጥሩ አይሆንም። ሰፊ ሌንስ እንዳለው ካሜራ የእይታ አድማሳችሁም እየተሠራ ያለውን አጠቃላዩን ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ ለማየት የሚችል መሆን አለበት። በጣም ሰፊ የሆነውን የሥራውን ገጽታ በፍጹም መዘንጋት አይኖርብንም። “ለራሳቸው ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጡ ወንድሞችና እኅቶች በተሰጣቸው ምድብ አይደሰቱም” ሲል ወንድም ፒርሰን ተማሪዎቹን አጥብቆ መከረ። “በይሖዋና እሱ እንዲሠሩት በሰጣቸው ሥራ ላይ የሚያተኩሩ ግን የተሳካ ውጤት ያገኛሉ።”
በመቀጠል ሌላው የአስተዳደር አካል አባል ጆን ኢ ባር “አመስጋኝ የምንሆንበት በጣም ብዙ ነገር አለ” የሚል መልእክት ያለው ንግግር አቀረበ። “ለይሖዋ ያላችሁን የአመስጋኝነት ስሜት በፍጹም እንዳታጡ” ሲል ወንድም ባር ተማሪዎቹን አጥብቆ መከራቸው። “ምንም ዓይነት ምድብ ይኑራችሁ የአመስጋኝነት ስሜት አንዱ ትልቁ የደስታ ምንጭ ነው።” ዳዊት የአመስጋኝነት ዝንባሌ ስለነበረው እንደሚከተለው ብሎ እንዲጽፍ ተገዷል፦ “ገመድ ባማረ ስፍራ ወደቀችልኝ፣ ርስቴም ተዋበችልኝ።” (መዝሙር 16:6) ወንድም ባር “እናንተ በዕለታዊ ሕይወታችሁ ከይሖዋ ጋር በጣም እንደተቀራረባችሁ እንዲሰማችሁ የሚያደርግ ይህን የመሰለ ውድ ሀብት አላችሁ” ሲል ተናገረ። “ይህን ሀብት በአመስጋኝነት እንደተዋበ ነገር አድርጋችሁ መያዛችሁን እስከቀጠላችሁ ድረስ ይሖዋ ይህን ከእሱ ጋር ያላችሁን ዝምድና አይነጥቃችሁም።”
“አንደበታችሁን እንዴት ትጠቀሙበታላችሁ?” የሚል ርዕስ ያለውን የሚቀጥለውን ንግግር ያቀረበው የጊልያድ ትምህርት ቤት አስተማሪ የሆነው ጃክ ሬድፎርድ ነበር። ሳያስተውሉ መናገር በጣም ትልቅ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። (ምሳሌ 18:21) አንደበትን መቆጣጠር የሚቻለው እንዴት ነው? “አንደበት በአእምሮና በልብ ውስጥ ያለውን ስለሚያንጸባርቅ በመጀመሪያ አእምሮአችሁን ማሠልጠን አለባችሁ” በማለት ወንድም ሬድፎርድ መልስ ሰጠ። (ማቴዎስ 12:34–37) በዚህ ረገድ ኢየሱስ በጣም ግሩም ምሳሌ ትቷል፤ ኢየሱስ አንደበቱን የይሖዋን ስም ከፍ ከፍ ለማድረግ ተጠቅሞበታል። “ዛሬ የይሖዋን ቃል ለመስማት ከመፈለግ የሚመጣ ረሀብ መኖሩን” ወንድም ሬድፎርድ ለተመራቂዎቹ ተናገረ። “እነዚህን ቃላት ታውቋቸዋላችሁ። እናንተ ‘የተማሩ ሰዎች አንደበት’ አላችሁ። ስለዚህ አንደበታችሁ ሁልጊዜ ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ባደረ አእምሮና ልብ እንዲመራ አድርጉት።”—ኢሳይያስ 50:4
“ይሖዋ አጠገባችሁ እንዳለ አድርጋችሁ እየተመላለሳችሁ ነውን?” በሚለው ንግግር ደግሞ የጸሎት አስፈላጊነት ጠበቅ ተደርጎ ተገልጿል። የትምህርት ቤቱ ሬጂስትራር የሆነው ዩሊሰዝ ግላስ እንዲህ አለ፦ “አንድ አባት ቤተሰቡን ለማስተዳደር ጠንክሮ ቢሠራ፣ ነገር ግን በፍጹም የማያነጋግራቸውና አንዳንድ የፍቅር መግለጫ የሆኑ ቃላትን የማይናገር ከሆነ ቤተሰቡ አባትዬው ያን ያህል በኃይል የሚሠራው በፍቅር ተገፋፍቶ ሳይሆን እንዲያው ግዴታው ስለሆነ ብቻ ነው ብሎ ሊደመድም ይችላል። እኛም ቢሆን እንዲሁ ነው። በአምላክ አገልግሎት በጣም የተወጠርን ልንሆን እንችላለን። ይሁን እንጂ የማንጸልይ ከሆነ አፍቃሪ ለሆነ ሰማያዊ አባት ሳይሆን ለሥራ ብቻ ያደርን እንሆናለን።”
የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ቲኦዶር ጃራዝ “እጅግ ብዙ ሰዎች ከአምላክ ሕዝቦች ጋር እየተባበሩ ያሉት ለምንድን ነው?” በሚል ርዕስ ንግግር አቀረበ። በየዓመቱ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ይሖዋ ድርጅት ይጎርፋሉ። (ዘካርያስ 8:23) የይሖዋ ምሥክሮችን የአምላክ ሕዝብ አድርጎ የሚያሳውቃቸው ምንድን ነው? አንደኛ፣ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን ይቀበላሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ሁለተኛ፣ ከፖለቲካ ገለልተኞች ናቸው። (ዮሐንስ 17:16) ሦስተኛ፣ ስለ አምላክ ስም ይመሠክራሉ። (ዮሐንስ 17:26) አራተኛ፣ ራስን መሥዋዕት እስከማድረግ የሚደርስ ፍቅር ያሳያሉ። (ዮሐንስ 13:35፤ 15:13) በእነዚህ ማስረጃዎች መሠረት ‘ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራንን የእሱን ክብር’ በድፍረት ልናውጅ እንችላለን።—1 ጴጥሮስ 2:9
ከነዚህ ቀስቃሽ ንግግሮች በኋላ 46ቱ ተመራቂዎች ዲፕሎማቸውን ተቀበሉ። በዓለም ዙሪያ በ16 አገሮች ተመደቡ።
የተለያዩ ዝግጅቶችን ያካተተ የከሰዓት በኋላ ፕሮግራም
ከሰዓት በኋላ የቤቴል ኮሚቴ አባል በሆነው በዶናልድ ክሬብስ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት በአጭሩ ተመራ። ከዚያም ተመራቂዎቹ “ጥበብ በጎዳና ትጮኻለች” በሚል ርዕስ አንድ ፕሮግራም አቀረቡ። (ምሳሌ 1:20) ከመንገድ ወደ መንገድና በንግድ አካባቢ በሚደረግ ምሥክርነት ያገኟቸውን አስደሳች ተሞክሮዎች በትዕይንት መልክ አሳዩ። በእርግጥም መደበኛ ባልሆነ መንገድ በድፍረት የሚሰብኩትን ይሖዋ ይባርካቸዋል። አንድ ተመራቂ “እኛ ልክ እያጨዱ ባሉት መላእክት እጅ እንዳሉት ማጭዶች እንደሆንን አድርጌ አስባለሁ” ሲል ተናግሯል። “እንደ ስል ማጭድ ከፍተኛ ችሎታ ካለን እነዚህ መላእክት ይበልጥ ሊጠቀሙብን ይችላሉ” (ከራእይ 14:6 ጋር አወዳድር) በተጨማሪም ተማሪዎቹ ባዘጋጁት ፕሮግራም ላይ ያቀረቡት የስላይድ ፊልም ተመልካቾቹ በቦሊቪያ፣ በማልታና በታይዋን ትምህርታዊ ጉብኝት እንዲያደርጉ አስችሏቸው ነበር። ተመራቂዎቹ ከተላኩባቸው አገሮች መካከል እነዚህ ሦስት አገሮች ይገኙበታል።
ቀጥሎ ለ17 ዓመታት ሚስዮናውያን ሆነው ላገለገሉት ለዋለስና ለጄን ሊቨራስ ቃለ ምልልስ ተደረገላቸው። ጥቅምት 1993 ወደ መጠበቂያ ግንብ የእርሻ ጣቢያ እንዲመጡ ጥሪ ቀረበላቸው። በአሁኑ ጊዜ ወንድም ሊቨራስን የጊልያድ ትምህርት ቤት አስተማሪ ሆኖ ያገለግላል።
“በዕድሜ የገፉትን ማክበር ተገቢ ነው” በሚል ርዕስ ባለ አራት ገቢር ድራማ ቀረበ። ሰዎች እያረጁ ሲሄዱ ምንም የማንጠቅምና የተተውን እንሆናለን የሚል ፍርሃት በራሳቸው ላይ ያላቸውን ትምክህት ሊቀንስባቸው ይችላል። (መዝሙር 71:9) ይህ ቀስቃሽ የሆነ አቀራረብ በጉባኤ ውስጥ ያሉት ሁሉ እንደዚህ ያሉትን ታማኝ አረጋውያን እንዴት ሊረዱ እንደሚችሉ ያስገነዘበ ነበር።
ከመዝጊያው መዝሙርና ጸሎት በኋላ በጀርሲ ሲቲ የክልል ስብሰባ አዳራሽና በሌሎች አዳራሾች ውስጥ ሆነው ፕሮግራሙን ይከታተሉ የነበሩት 6,220 ተሰብሳቢዎች በሙሉ በጣም ደስ አላቸው። ተመራቂዎቹ በአዲሱ ምድባቸው ባላቸው ሥራ እንዲበረቱ እንጸልይላቸዋለን። ከመስጠት የሚገኘውን ትልቅ ደስታ ለማየት ያብቃቸው።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ስለተመራቂዎቹ የቀረበ አኃዛዊ መረጃ
ሚስዮናውያኑ የመጡባቸው አገሮች፦ 9
የተመደቡባቸው አገሮች፦ 16
የተማሪዎች ጠቅላላ ቁጥር፦ 46
አማካይ ዕድሜ፦ 33.85
በእውነት ውስጥ የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ፦ 16. 6
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ፦ 12.2
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ለማልታ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል
ሕዝበ ክርስትና በማልታ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንዳይነገር ለብዙ ዓመታት ስታፍን ቆይታለች። ለመጨረሻ ጊዜ ወደዚያ የተላኩት የጊልያድ ሚስዮናውያን በ1947 የስምንተኛው ኮርስ ተመራቂዎች የሆኑት ፍሬድሪክ ስሚድሌይና ፒተር ብራይድል ነበሩ። ይሁን እንጂ ማልታ ደርሰው ብዙም ሳይቆዩ ተያዙና ከአገሪቱ ተባረሩ። የ1948 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ እንደሚከተለው ሲል ይገልጻል፦ “እነዚህ ሁለት ሚሲዮናውያን በሮማ ካቶሊክ ቄሶች ተቃውሞ የተነሣ በፍርድ ቤትና ከአገሪቱ ባለ ሥልጣኖች ጋር በመሟገት አገልግሎታቸውን በማከናወን ካሳለፉት ጊዜ ያላነሰ አጥፍተዋል። ቄሶቹ ማልታ የካቶሊኮች ስለሆነች ማንኛውም ሌላ ሃይማኖት መውጣት አለበት ባዮች ናቸው።” አሁን ከ45 ዓመታት ገደማ በኋላ ከ96ኛው የጊልያድ ኮርስ የተመረቁ አራት ሚስዮናውያን በማልታ ተመድበዋል።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት የ96ኛው ኮርስ ተመራቂዎች
ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር የረድፍ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደ ኋላ ሲሆን የእያንዳንዱ ረድፍ የስም ዝርዝር የተጻፈው ከግራ ወደ ቀኝ ነው።
(1) ኤለርስ ፒ፤ ጊዝ ኤም፤ ዜልማን ኤስ፤ ሱስፐርጉ ጄ፤ ሮው ኤስ፤ ጃክሰን ኬ፤ ስኮት ቲ። (2) ሊየር ቲ፤ ጋርሲያ አይ፤ ጋርሲያ ጄ፤ ፈርናንዴዝ ኤ፤ ዴቪድሰን ኤል፤ ሊዳማን ፒ፤ ጊብሰን ኤል፤ ሀዋሬስ ሲ። (3) ፎውትስ ሲ፤ ፓስተራነ ጂ፤ ክሎሰን ዲ፤ ፈርናንዴዝ ኤል፤ ዎልስ ኤም፤ ድሬስን ኤም፤ ፓስትራና ኤፍ፤ በርክስ ጄ። (4) በርክስ ዲ፤ ስኮት ኤስ፤ ጃክሰን ኤም፤ ሞሪ ኤች፤ ጃረዝ ኤል፤ ሱስፐርጊ ኤ፤ ብሩሾን ሲ፤ ሮው ሲ። (5) ሴልማን ኬ፤ ሊድማን ፒ፤ ዴቪድሰን ሲ፤ ሞሪ ኤስ፤ ዎልስ ዲ፤ ድሬስን ዲ፤ ስካፍስማ ጂ፤ ሊየር ኤስ። (6) ክሎሰን ቲ፤ ጊብሰን ቲ፤ ጊይዝ ሲ፤ ኤለርስ ዲ፤ ፎትስ አር፤ ስካፍስማ ኤስ፤ ብሩሾን ኤል።