ይሖዋ ምክንያታዊ ነው!
“ላይኛይቱ ጥበብ . . . ምክንያታዊ ናት።”—ያዕቆብ 3:17 አዓት
1. አንዳንዶች አምላክን ምክንያታዊ እንዳልሆነ አድርገው የገለጹት እንዴት ነው? ሰዎች ለአምላክ ያላቸውን እንዲህ ዓይነቱን አመለካከት እንዴት ታየዋለህ?
የምታመልከው ምን ዓይነት አምላክ ነው? ድርቅ ያለ፣ ውልፍት የማያደርግ፣ ጥብቅና የግትርነት ጠባይ ያለው አምላክ ነው ብለህ ታምናለህን? የፕሮቴስታንት ተሃድሶ መሪ የነበረው ጆን ካልቪን አምላክ እንደዚህ ሆኖ ታይቶት መሆን አለበት። ካልቪን አምላክ ስለ እያንዳንዱ ሰው “ዘላለማዊና የማይለወጥ እቅድ” አለው፤ እያንዳንዱን ግለሰብ በተመለከተ ወይ በደስታ ለዘላለም ይኖራል አለዚያም ለዘላለም በእሳታማ ሲኦል ይሠቃያል ብሎ አስቀድሞ ወስኗል ብሏል። እስቲ አስበው፦ ይህ እውነት ቢሆን ኖሮ አንዳችም ነገር ማድረግ አትችልም ነበር። ምንም ያህል ጠንክረህ ብትሠራ ጥረትህ አምላክ ስለ አንተና ስለ ወደፊቱ ዕጣህ ከብዙ ጊዜ በፊት ያወጣውን የማይለወጥ እቅድ ሊሽረው አይችልም ነበር። እንዲህ ዓይነቱን ምክንያታዊ ያልሆነ አምላክ ለመቅረብ ትገፋፋ ነበርን?—ከያዕቆብ 4:8 ጋር አወዳድር።
2, 3. (ሀ) የሰው ልጅ ተቋሞችና ድርጅቶች ምክንያታዊ አለመሆናቸውን በምሳሌ ማስረዳት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ሕዝቅኤል በራእይ ያየው የይሖዋ ሰማያዊ ሰረገላ ይሖዋ አዲስ ክስተቶችን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?
2 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጸው አምላክ ከማንም በላይ ምክንያታዊ መሆኑን ማወቃችን ምንኛ እፎይ የሚያሰኝ ነው! የግትርነትና ድርቅ የማለት ዝንባሌ ያላቸው በራሳቸው አለፍጽምና የተተበተቡት ሰዎች ናቸው እንጂ አምላክ አይደለም። ሰብዓዊ ድርጅቶች የዕቃ ጫኝ ባቡርን ያህል በተፈለገው ቦታና ጊዜ ለመቆጣጠር የሚያስቸግሩ ሊሆኑ ይችላሉ። አንድ ግዙፍ የዕቃ ጫኝ ባቡር በሚጓዝበት ጊዜ በሐዲዱ ላይ መንገድ የዘጋ ነገር ሲያጋጥመው ዞር ብሎ ማለፍ የማይሞከር ነገር ነው። ለማቆምም ቢሆን በጣም አስቸጋሪ ነው። አንዳንድ ባቡሮች ወደፊት በከፍተኛ ፍጥነት የመጓዝ ኃይል ስላላቸው ፍሬናቸው ከተያዘ በኋላም ለመቆም ከአንድ ኪሎ ሜትር በላይ ይጓዛሉ! የነዳጅ ዘይት የምትሸከም ትልቅ መርከብም እንደዚሁ ሞተሮቿ ከጠፉ በኋላ ለመቆም ሌላ 8 ኪሎ ሜትር መሄድ ያስፈልጋታል። የኋላ ማርሽ ቢገባም እንኳ አሁንም 3 ኪሎ ሜትር ያህል ወደፊት ልትጓዝ ትችላለች! አሁን ግን ከእነዚህ ከሁለቱ በጣም የላቀ ኃይል ያለው የአምላክን ድርጅት የሚወክል አንድ ድንቅ ተሽከርካሪ ተመልከት።
3 ከ2,600 ዓመታት በፊት ይሖዋ መንፈሳዊ ፍጥረታቱን ያቀፈውን ሰማያዊ ድርጅቱን የሚወክል ራእይ ለነቢዩ ሕዝቅኤል አሳየው። በራእይ የታየው እጅግ አስገራሚ በሆነ መንገድ ሚዛኑን ጠብቆ ወደተፈለገው አቅጣጫ መንቀሳቀስ የሚችል ሰረገላ ነበር። ምን ጊዜም በራሱ ቁጥጥር ሥር ያለ የራሱ የይሖዋ “ተሽከርካሪ” ነበር። ትኩረትን እጅግ የሚስበው ነገር እንቅስቃሴ የሚያደርግበት ሁኔታ ነው። ግዙፎቹ መንኮራኩሮች አራት ጎኖች ያሏቸውና በዓይኖች የተሞሉ ነበሩ። ስለዚህም በየትኛውም አቅጣጫ ማየት ይችላሉ፤ አቅጣጫቸውንም ሳይቆሙ ወይም ሳይዞሩ በቅጽበት መቀየር ይችላሉ። እንዲሁም ይህ ግዙፍ ተሽከርካሪ እንደ ነዳጅ ተሸካሚ መርከብና እንደ ዕቃ ጫኝ ባቡር አይንቀራፈፍም። በመብረቅ ፍጥነት መጓዝ ይችላል። በ90 ዲግሪ መታጠፍ ይችላል! (ሕዝቅኤል 1:1, 14–28) የይሖዋ ሰረገላ ሰው ከሠራቸው መናኛ ተሽከርካሪዎች እንደሚለይ ሁሉ ይሖዋ ራሱም ካልቪን ከሰበከው አምላክ የተለየ ነው። ፍጹም በሆነ መንገድ አዲስ ክስተቶችን እንደ ሁኔታው ያስተናግዳል። ይህንን የይሖዋ ባሕርይ መገንዘባችን እኛም ራሳችንን ከሁኔታዎች ጋር የምናስማማ ሆነን እንደንቀጥልና ምክንያታዊ ያለመሆንን ወጥመድ እንድናስወግድ ሊረዳን ይገባል።
ራሱን ከሁኔታዎች ጋር በማስማማት ረገድ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ወደር የሌለው ይሖዋ
4. (ሀ) የይሖዋ ስም ራሱ አዲስ ክስተቶችን የሚያስተናግድ አምላክ መሆኑን የሚገልጸው በምን መንገድ ነው? (ለ) ይሖዋ አምላክ የሚጠራባቸው አንዳንድ መጠሪያዎች ምንድን ናቸው? ተስማሚ የሆኑትስ ለምንድን ነው?
4 ይሖዋ የሚለው ስሙ አዲስ ክስተቶችን ለማስተናገድ ለውጥ የሚያደርግ መሆኑን ያሳያል። ቃል በቃል ሲተረጎም “ይሖዋ” ማለት “የሚያስሆን” ማለት ነው። ይህ ማለት ራሱን የተስፋ ቃሉ ሁሉ ፈጻሚ የሚያስሆን ማለት እንደሆነ ግልጽ ነው። ሙሴ አምላክን ስሙ ማን እንደሆነ በጠየቀው ጊዜ ይሖዋ በዚህ መንገድ ትርጉሙን ዘርዘር አድርጎ ገልጾታል፦ “መሆን የምፈልገውን መሆን እችላለሁ።” (ዘጸአት 3:14 አዓት) የእንግሊዝኛው የሮተርሃም ትርጉም ደግሞ “መሆን የምሻውን ሁሉ እሆናለሁ” በማለት ቁልጭ አድርጎ ያስቀምጠዋል። ይሖዋ የጽድቅ ዓላማዎቹንና ቃል የገባቸውን ነገሮች ለመፈጸም የሚያስፈልገውን ሁሉ ይሆናል ወይም ለመሆን ይችላል። በመሆኑም ፈጣሪ፣ አባት፣ ሉዓላዊ ጌታ፣ እረኛ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፣ ጸሎት ሰሚ፣ ፈራጅ፣ ታላቅ አስተማሪ፣ የሚቤዥና እነዚህን የመሳሰሉ የተለያዩ ታላላቅ መጠሪያዎች አሉት። ፍቅራዊ ዓላማዎቹን ዳር ለማድረስ ሲል ራሱን እነዚህን ሁሉና ሌሎች ነገሮችንም ያስሆናል።—ኢሳይያስ 8:13፤ 30:20፤ 40:28፤ 41:14፤ መዝሙር 23:1፤ 65:2፤ 73:28፤ 89:26፤ መሳፍንት 11:27፤ በተጨማሪም የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም አፔንዲክስ 1J ተመልከት።
5. ይሖዋ አዲስ ክስተቶችን እንደ ሁኔታው ያስተናግዳል ሲባል ጠባዩንና የአቋም ደረጃዎቹን ይለውጣል ማለት እንደሆነ አድርገን መደምደም የሌለብን ለምንድን ነው?
5 ታዲያ ይህ ማለት የአምላክ ባሕርይ ወይም የአቋም ደረጃዎች ይለዋወጣሉ ማለት ነውን? አይደለም። ያዕቆብ 1:17 (የ1980 ትርጉም) ‘እንደ ጥላ መዘዋወር ወይም መለዋወጥ የሌለበት’ በማለት ነገሩን በትክክል አስቀምጦታል። እዚህ ላይ እርስ በእርሱ የሚጋጭ ነገር አለን? በፍጹም የለም። ለምሳሌ ያህል ለልጆቹ ጥቅም ሲል የሥራ ድርሻዎቹን የማይቀያይር አፍቃሪ ወላጅ ማን ነው? አንድ ወላጅ በአንድ ቀን ውስጥ መካሪ፣ ምግብ አቅራቢ፣ የቤት ውስጥ ሥራዎችን የሚያከናውን፣ አስተማሪ፣ ተግሣጽ የሚሰጥ፣ ወዳጅ፣ መካኒክ፣ ነርስ እና ሌሎች ብዙ ነገሮችንም መሆን ይችላል። አንድ ወላጅ እነዚህን የሥራ ድርሻዎች በሚያከናውንበት ጊዜ ስብዕናውን አይለውጥም፤ እሱም ሆነ እሷ የሚያደርጉት ነገር ቢኖር ወቅታዊ ከሆኑ አስፈላጊ ነገሮች ጋር ራሳቸውን ማስማማት ብቻ ነው። በይሖዋ ዘንድም ሁኔታው ከዚህ የተለየ አይደለም፤ ሆኖም ይሖዋ እንደዚህ የሚያደርገው ከሰው እጅግ በላቀ መልኩ ነው። ለፍጥረታቱ ጥቅም ሲል ራሱ መሆን ለሚችለው ነገር ገደብ የለውም። የጥበቡ ጥልቀት በእርግጥም እጅግ የሚያስደንቅ ነው!—ሮሜ 11:33
ምክንያታዊነት የመለኮታዊ ጥበብ መለያ ባሕርይ ነው
6. ያዕቆብ መለኮታዊ ጥበብን ሲገልጽ የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል ቀጥተኛ ትርጉሙና ቃሉ የሚያመለክታቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?
6 ራሱን ከማንም በላይ ከሁኔታዎች ጋር ማስማማት የሚችለው አምላክ ያለውን ጥበብ ለመግለጽ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ አንድ ጥሩ ቃል ተጠቅሟል። “ላይኛይቱ ጥበብ . . . ምክንያታዊ ናት” ሲል ጽፏል። (ያዕቆብ 3:17 አዓት) እዚህ ላይ የገባው የግሪክኛ ቃል (ኤፒኤኬስ) ለትርጉም አስቸጋሪ ነው። ተርጓሚዎች “ገር፣” “ላላ ያለ፣” “ቻይ” እና “አሳቢ” የሚሉትን የመሰሉ ቃላት ተጠቅመዋል። የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም በግርጌ ማስታወሻው ላይ ቃሉ በቀጥታ ሲተረጎም “እሺ ባይ” ማለት መሆኑን በማመልከት “ምክንያታዊ” በማለት ተርጉሞታል።a በተጨማሪም ቃሉ የሕጉ ፊደል ካልተፈጸመ ብሎ አለማክረርን፣ ከመጠን በላይ ጥብቅ ወይም የማያወላዳ አለመሆንን ያመለክታል። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ዊልያም ባርክሌይ በኒው ቴስታመንት ወርድስ ላይ የሚከተለውን ሐሳብ ሰጥተዋል፦ “ኤፒኤኪያን በተመለከተ ዋናውና መሠረታዊው ነገር ከአምላክ የመነጨ መሆኑ ነው። አምላክ መብቱን ቀጥ አድርጎ ቢያስጠብቅ ኖሮና ውልፍት የማያደርጉ የሕጉን የአቋም ደረጃዎች በእኛ ላይ ቢያውላቸው ኖሮ ምን እንሆን ነበር? አምላክ ኤፒኤኪስ በመሆንና ሌሎችን በኤፒኤኪያ በመያዝ ረገድ ወደር የለውም።”
7. ይሖዋ በኤደን ገነት ውስጥ ምክንያታዊነትን ያሳየው እንዴት ነው?
7 የሰው ልጅ በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ ያመፀበትን ጊዜ ወደ ኋላ መለስ ብለህ ተመልከት። ሦስቱን ውለታ ቢስ ዓመፀኞች አዳምን፣ ሔዋንና ሰይጣንን የእጃቸውን እንዲያገኙ በሞት መቅጣት ለአምላክ ምንኛ ቀላል ነበር! እንዲህ በማድረግም ከሚደርስበት ሐዘን ምንኛ በተገላገለ ነበር! እንዲህ ያለ የማያወለዳ የፍትሕ እርምጃ የመውሰድ መብት የለውም ብሎ መከራከር የሚችል ማነው? ሆኖም ይሖዋ ሰማያዊ ሰረገላ መሰል ድርጅቱን ድርቅ ባለና ራሱን ከሁኔታዎች ጋር በማያስማማ የፍትሕ ደንብ መርቶት አያውቅም። ስለዚህ ይህ ሰረገላ ግትር አቋም ይዞ በመጓዝ ሰብዓዊውን ቤተሰብና የሰውን ዘር የወደፊት አስደሳች ተስፋዎች አልደመሰሰም። በተቃራኒው ይሖዋ ሰረገላውን በመብረቅ ፍጥነት አቅጣጫውን እንዲቀይር አድርጎቷል። ዓመፁ እንደተፈጸመ ወዲያውኑ ይሖዋ አምላክ ለአዳም ዘሮች በሙሉ ምሕረትና ተስፋን የዘረጋ የረጅም ጊዜ ዓላማ አወጣ።—ዘፍጥረት 3:15
8. (ሀ) ሕዝበ ክርስትና ለምክንያታዊነት ያላት የተሳሳተ አመለካከት ይሖዋ ካለው እውነተኛ ምክንያታዊነት ጋር ሊነጻጸር የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ያለው ምክንያታዊነት መለኮታዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶቹን እንዲጥስ አያደርገውም ለማለት የምንችለው ለምንድን ነው?
8 ይሖዋ ምክንያታዊ ነው ማለት ግን መለኮታዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶቹን ይጥሳል ማለት አይደለም። በዛሬው ጊዜ የሕዝበ ክርስትና ቤተ ክርስቲያኖች ያሻቸውን በሚያደርጉት ሙልጭልጭ በሚሉ መንጎቻቸው ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት የጾታ ብልግናን በቸልታ ሲያልፉ ምክንያታዊ የሆኑ መስሎ ሊታያቸው ይችላል። (ከ2 ጢሞቴዎስ 4:3 ጋር አወዳድር።) ይሖዋ ሕግጋቱን አያፈርስም፤ ወይም መሠረታዊ ሥርዓቶቹን አይጥስም። ከዚህ ይልቅ ግትር ላለመሆን ማለትም ከሁኔታዎች ጋር ራሱን ለማስማማት ፈቃደኝነቱን አሳይቷል። በዚህ መንገድ መሠረታዊ ሥርዓቶቹ በትክክልና በይቅር ባይነት መንፈስ በሥራ ሊውሉ ይችላሉ። ፍትሑንና ኃይሉን ከፍቅሩና ከምክንያታዊ ጥበቡ ጋር በተመጣጠነ ሁኔታ በሥራ የሚያውልበትን መንገድ ጠንቅቆ ያውቃል። ይሖዋ ምክንያታዊነትን በሥራ ያሳየባቸውን ሦስት መንገዶች እስቲ እንመልከት።
“ይቅር ለማለት ዝግጁ ነህ”
9, 10. (ሀ) ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ መሆን’ ከምክንያታዊነት ጋር ምን ዝምድና አለው? (ለ) ዳዊት ይሖዋ ይቅር ለማለት ዝግጁ በመሆኑ የተጠቀመው እንዴት ነው? ለምንስ?
9 ዳዊት “አቤቱ፣ አንተ ጥሩና ይቅር ለማለት ዝግጁ ነህ፤ ፍቅራዊ ደግነትህም ለሚጠሩህ ሁሉ ብዙ ነውና” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 86:5 አዓት) የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ወደ ግሪክኛ ሲተረጎሙ “ይቅር ለማለት ዝግጁ ነህ” የሚለው ሐረግ ኤፒኤኬስ ወይም “ምክንያታዊ” ተብሎ ተተርጉሟል። በእርግጥም ምክንያታዊነትን ለማንጸባረቅ ቁልፉ ይቅር ለማለት ዝግጁ መሆንና ምሕረትን ማሳየት ሳይሆን አይቀርም።
10 ዳዊት ራሱ ይሖዋ በዚህ ረገድ ምን ያህል ምክንያታዊ እንደሆነ አሳምሮ ያውቅ ነበር። ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር በፈጸመበትና ባልዋን ለማስገደል ሁኔታዎችን ባመቻቸበት ጊዜ እሱም ሆነ ቤርሳቤህ የሞት ቅጣት ይገባቸው ነበር። (ዘዳግም 22:22፤ 2 ሳሙኤል 11:2–27) ጉዳዩን በፍርድ የተመለከቱት ግትር ሰብዓዊ ዳኞች ቢሆኑ ኖሮ ሁለቱም ሕይወታቸውን ሊያጡ ይችሉ ነበር። ይሖዋ ግን ምክንያታዊነትን (ኤፒኤኬስ) አሳይቷል። ይህንንም ቫይን ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ቢብሊካል ዎርድስ “‘የአንድን ጉዳይ እውነታዎች በሰብአዊነትና በምክንያታዊነት’ የሚመለከትን አሳቢነት የሚገልጽ” ነው በማለት አስቀምጦታል። ይሖዋን ምሕረት እንዲያደርግ የገፋፉት እውነታዎች የኃጢአተኞቹ ልባዊ ጸጸትና ዳዊት ራሱ ቀደም ሲል ለሌሎች ያደረገው ምሕረት ጭምር ሊሆኑ ይችላሉ። (1 ሳሙኤል 24:4–6፤ 25:32–35፤ 26:7–11፤ ማቴዎስ 5:7፤ ያዕቆብ 2:13) ሆኖም ይሖዋ በዘጸአት 34:4–7 ላይ ስለ ራሱ ከሰጠው መግለጫ ጋር በሚስማማ መንገድ ለዳዊት እርማት መስጠቱ ምክንያታዊ ነበር። ዳዊት የይሖዋን ቃል ማቃለሉን እንዲገነዘብ የሚያደርግ ኃይለኛ መልዕክት አስይዞ ነቢዩ ናታንን ወደ ዳዊት ላከው። ዳዊት በመጸጸቱ በሠራው ኃጢአት አልሞተም።—2 ሳሙኤል 12:1–14
11. ይሖዋ ይቅር ለማለት ዝግጁ መሆኑን በምናሴ ላይ ያሳየው እንዴት ነው?
11 የይሁዳ ንጉሥ የነበረው ምናሴ ከዳዊት ፍጹም በተለየ ሁኔታ ለረጅም ጊዜ እጅግ ክፉ ሆኖ ቆይቶ ስለነበር በዚህ ረገድ ጎላ ብሎ የሚታይ ምሳሌ ያለው ሆኖ እናገኘዋለን። ምናሴ ሰውን መሥዋዕት ማድረግን ጨምሮ አስጸያፊ ሃይማኖታዊ ልማዶችን በአገሩ አስፋፍቷል። ታማኙ ነቢይ ኢሳይያስ ‘በመጋዝ እንዲሰነጠቅ’ ያደረገውም እርሱ ሊሆን ይችላል። (ዕብራውያን 11:37) ይሖዋ ምናሴን ለመቅጣት ወደ ባቢሎን ተማርኮ እንዲወሰድ ፈቅዷል። ሆኖም ምናሴ በወኅኒ ሆኖ ንስሐ ገባ፤ ምሕረት ለማግኘትም ተማፀነ። ይህ ነው የማይባል ከባድ ኃጢአት የሠራ ቢሆንም እንኳ ይህን ልባዊ ንስሐ በማሳየቱ ይሖዋ በምላሹ ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ ነበር።—2 ዜና መዋዕል 33:9–13
አዳዲስ ሁኔታዎች ሲከሰቱ እርምጃን መቀየር
12, 13. (ሀ) ነነዌን በተመለከተ ይሖዋ ሊወስድ ያሰበውን እርምጃ እንዲቀይር የገፋፋው የትኛው ሁኔታ መለወጡ ነው? (ለ) በምክንያታዊነት ረገድ ዮናስ ከይሖዋ አምላክ ያነሰ አቋም ይዞ የተገኘው እንዴት ነው?
12 የይሖዋ ምክንያታዊነት አንድን እርምጃ ሊወስድ አስቦ ሳለ አዳዲስ ሁኔታዎች ሲከሰቱ እርምጃውን ለመቀየር ፈቃደኛ በመሆኑም ይታያል። ለምሳሌ ያህል ነቢዩ ዮናስ በጥንቷ ነነዌ ጎዳናዎች ላይ እየተመላለሰ በመንፈስ አነሣሽነት የተናገረው መልዕክት የማያሻማ ነበር፦ ታላቂቱ ከተማ በ40 ቀናት ውስጥ ትጠፋለች አለ። ይሁን እንጂ ሁኔታዎቹ በድንገት ተለወጡ! የነነዌ ሰዎች ንስሐ ገቡ።—ዮናስ ምዕራፍ 3 (የ1980 ትርጉም)
13 እነዚህ ሁኔታዎች ሲለወጡ ይሖዋና ዮናስ የሰጡትን ምላሽ ማነጻጸሩ ጥሩ እውቀት ይሰጣል። ይሖዋ ሰማያዊ ሰረገላው አቅጣጫውን እንዲቀይር አደረገ። በዚህ ወቅት ራሱን “ተዋጊ” ከማድረግ ይልቅ የኃጢአት ይቅር ባይ በመሆን አዲስ የተፈጠሩትን ሁኔታዎች ለማስተናገድ ፈቃደኛ ሆነ። (ዘጸአት 15:3) በሌላ በኩል ዮናስ ግትር ሆኖ ነበር። ከይሖዋ ሰረገላ ጋር እኩል ከመራመድ ይልቅ ቀደም ሲል እንደተጠቀሱት እንደ ዕቃ ጫኝ ባቡሩ ወይም እንደ ነዳጅ ተሸካሚዋ መርከብ ያለ ሁኔታ ፈጸመ። ጥፋት ይመጣል ብሎ አውጆአል፤ ስለዚህ ጥፋት መምጣት አለበት! ምናልባት ሊወሰድ በታሰበው እርምጃ ላይ ለውጥ መደረጉ የነነዌ ሰዎች እንዲያቃልሉኝ ያደርጋቸዋል የሚል ስሜት ተሰምቶት ይሆናል። ይሖዋ ግን ታጋሽ በመሆን በአቋሙ ድርቅ ብሎ የነበረውን ነቢዩን በምክንያታዊነትና በመሐሪነት የማይረሳ ትምህርት አስተማረው።—ዮናስ ምዕራፍ 4
14. ነቢዩን ሕዝቅኤልን በተመለከተ ይሖዋ ሊያደርግ ያሰበውን ነገር የለወጠው ለምን ነበር?
14 ይሖዋ በሌሎች ወቅቶችም አነስተኛ በሆኑ ጉዳዮች ረገድም እንኳ ሊወስድ ያሰበውን እርምጃ ለውጧል። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ ነቢዩ ሕዝቅኤልን ትንቢታዊ ድራማ እንዲሠራ ባዘዘው ጊዜ በሰው እዳሪ በሚነድ እሳት ምግቡን እንዲያበስል መመሪያ ሰጥቶት ነበር። “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፣ ወዮ!” በማለት ለጮኸውና በጣም የቀፈፈውን ይህን ድርጊት ላለማድረግ ለተማጸነው ነቢይ ይህ ከአቅሙ በላይ የሆነ ነገር ነበር። ይሖዋ የነቢዩን ስሜት መሠረተ ቢስ እንደሆነ አድርጎ በመቁጠር ውድቅ አላደረገውም፤ ከዚህ ይልቅ እስከ ጊዜያችንም ድረስ በብዙ አገሮች ውስጥ የተለመደውን ሰዎች እሳት ለማንደድ የሚጠቀሙበትን ኩበት እንዲጠቀም ፈቀደለት።—ሕዝቅኤል 4:12–15
15. (ሀ) ይሖዋ የሰው ልጆችን ለመስማትና ለሁኔታቸው የሚስማማ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ እንደነበረ የሚያሳዩት የትኞቹ ምሳሌዎች ናቸው? (ለ) ይህስ ምን ትምህርት ሊሰጠን ይችላል?
15 ስለ ይሖዋ አምላካችን ትሕትና ማሰቡ ልብን በደስታ ሞቅ የሚያደርግ አይደለምን? (መዝሙር 18:35) እኛ በእርሱ ዘንድ ኢምንት ነን፤ ያም ሆኖ ግን ፍጹም ያልሆኑትን የሰው ልጆች በትዕግሥት ያዳምጣል፤ አልፎ ተርፎም አንዳንድ ጊዜ እርምጃውን እንደ ሁኔታው ይቀይራል። አብርሃም የሰዶምንና የገሞራን ጥፋት አስመልክቶ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲሞግተው ፈቅዶለታል። (ዘፍጥረት 18:23–33) ዓመፀኞቹን እስራኤላውያንን ለማጥፋትና በምትኩ ሙሴን ታላቅ ሕዝብ ለማድረግ ባሰበ ጊዜ ሙሴ ያቀረበውን ተቃውሞ ይሖዋ ተቀብሎታል። (ዘጸአት 32:7–14፤ ዘዳግም 9:14, 19፤ ከአሞጽ 7:1–6 ጋር አወዳድር።) እግረ መንገዱንም ምክንያታዊና የሚቻል እስከሆነ ድረስ ሌሎችን ለመስማት ይህን የመሰለ ዝግጁነት ማሳየት ለሚኖርባቸው ሰብዓዊ አገልጋዮቹ ፍጹም ምሳሌ ትቶላቸዋል።—ከያዕቆብ 1:19 ጋር አወዳድር።
በሥልጣን አጠቃቀም ረገድ ምክንያታዊነትን ማሳየት
16. ይሖዋ በሥልጣን አጠቃቀም ረገድ ከብዙዎቹ ሰዎች የሚለየው እንዴት ነው?
16 ግለሰቦች ከፍ ያለ ሥልጣን ባገኙ መጠን ብዙዎቹ ምክንያታዊነታቸው እየቀነሰ እንደሚሄድ አስተውለሃልን? በአንጻሩ ይሖዋ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከፍተኛውን የሥልጣን ቦታ የያዘ ቢሆንም እንኳ ምክንያታዊ በመሆን ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ነው። ሥልጣኑን ምን ጊዜም ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ይጠቀምበታል። ይሖዋ እንደ ሰዎች ለሥልጣኑ አይሰጋም። ስለዚህም የተወሰነ የሥልጣን ደረጃን ለሌሎች መስጠት ሥልጣኔን በሆነ መንገድ አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል ብሎ በማሰብ ለሥልጣኑ የቀናተኝነት ጥበቃ ማድረግ እንዳለበት ሆኖ አይሰማውም። እንዲያውም በአጽናፈ ዓለም ውስጥ አንድ ሌላ አካል ብቻ በነበረበት ጊዜ ይሖዋ ለዚህ አካል ትልቅ ሥልጣን ሰጥቶታል። ሎጎስን “ዋና ሠራተኛ” አደረገው፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሁሉንም ነገሮች ወደ መኖር ያመጣው በተወዳጅ ልጁ አማካኝነት ነው። (ምሳሌ 8:22, 29–31፤ ዮሐንስ 1:1–3, 14፤ ቆላስይስ 1:15–17) በኋላም ‘በሰማይና በምድር ያለውን ሥልጣን ሁሉ በውክልና ሰጠው።’—ማቴዎስ 28:18፤ ዮሐንስ 5:22
17, 18. (ሀ) ይሖዋ ወደ ሰዶምና ገሞራ መላእክትን የላከው ለምንድን ነው? (ለ) አክአብን እንዴት ማሳሳት እንደሚቻል ሐሳብ እንዲሰጡ ይሖዋ መላእክትን የጠየቀው ለምንድን ነው?
17 በተመሳሳይም ይሖዋ ራሱ በተሻለ ሁኔታ ሊያከናውናቸው የሚችላቸውን ሥራዎች ለብዙዎቹ ፍጥረታቱ ሰጥቷል። ለምሳሌ ያህል አብርሃምን “እንግዲህስ ወደ እኔ እንደ መጣች እንደ ጩኸትዋ አድርገው እንደ ሆነ [ወደ ሰዶምና ገሞራ] ወርጄ አያለሁ” ባለው ጊዜ በአካል ወደዚያ እሄዳለሁ ማለቱ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ እንዲህ ዓይነቱን መረጃ አጠናቅረው እንዲመጡ መላእክትን በመሾም ሥልጣኑን በውክልና መስጠትን መረጠ። ይህን መረጃ ለማግኘት የሚያስችል ተልእኮ እንዲያከናውኑና ወደ እርሱ ተመልሰው ሪፖርት እንዲያደርጉ ሥልጣን ሰጣቸው።—ዘፍጥረት 18:1–3, 20–22
18 በሌላ ወቅት ላይ ይሖዋ ክፉውን ንጉሥ አክአብን በሞት ለመቅጣት በወሰነበት ጊዜ ከሐዲው ንጉሥ ሕይወቱን ለሕልፈት ወደሚዳርገው ውጊያ እንዲገባ እንዴት ‘ማሳሳት’ እንደሚቻል ሐሳብ እንዲሰጡ መላእክትን በሰማይ ሰብስቧቸው ነበር። የጥበብ ሁሉ መፍለቂያ የሆነው ይሖዋ ከሁሉ የተሻለውን እርምጃ ለመውሰድ እርዳታ እንደማያስፈልገው ምንም አያጠራጥርም! ሆኖም የመፍትሔ ሐሳቦችን እንዲያቀርቡ መብት በመስጠትና ድርጊቱ እንዲፈጸምበት ባሰበው ሰው ላይ ሥልጣን እንዲኖራቸው በማድረግ መላእክቱን ከፍ ከፍ አድርጓቸዋል።—1 ነገሥት 22:19–22
19. (ሀ) ይሖዋ የሚያወጣቸውን ሕጎች ቁጥር የሚገድበው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ከእኛ የሚጠብቀውን ነገር በተመለከተ ምክንያታዊ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
19 ይሖዋ ሥልጣኑን በሌሎች ላይ ከልክ ያለፈ ቁጥጥር ለማድረግ አይጠቀምበትም። በዚህም ረገድ ወደር የለሽ ምክንያታዊነት አሳይቷል። ያወጣቸውን ሕጎች ቁጥር በጥንቃቄ ገደብ አበጅቶላቸዋል፤ እንዲሁም አገልጋዮቹ የራሳቸውን እንደ ሸክም የሚከብዱ ሕጎች እየጨመሩ ‘ከተጻፈው እንዳያልፉ’ አዟል። (1 ቆሮንቶስ 4:6፤ ሥራ 15:28፤ ከማቴዎስ 23:4 ጋር አወዳድር።) ፍጥረታቱ በጭፍን እንዲታዘዙት አይፈልግም፤ ከዚህ ይልቅ ብዙውን ጊዜ እነርሱን ለመምራት በቂ እውቀት ያቀርብላቸዋል። የመታዘዝን ጥቅምና አለመታዘዝ የሚያስከትለውን መዘዝ እንዲያውቁ በማድረግም ምርጫ በፊታቸው ያስቀምጥላቸዋል። (ዘዳግም 30:19, 20) ሰዎች በጥፋተኝነት ስሜት፣ በኃፍረት ወይም በፍርሃት ተሸማቀው ሳይሆን ከልብ ተነሳስተው እንዲታዘዙት ይፈልጋል። ሰዎች ተገደው ሳይሆን ከልባዊ ፍቅር ተነሳስተው እንዲያገለግሉት ይፈልጋል። (2 ቆሮንቶስ 9:7) ይህን የመሰለ በሙሉ ነፍስ የሚደረግ አገልግሎት ሁሉ የይሖዋን ልብ ደስ ያሰኘዋል፤ እርሱን ‘ማስደሰት አለቅጥ አስቸጋሪ’ አይደለም።—1 ጴጥሮስ 2:18 አዓት፤ ምሳሌ 27:11፤ ከሚክያስ 6:8 ጋር አወዳድር።
20. ይሖዋ ምክንያታዊ መሆኑ አንተን እንዴት ይነካሃል?
20 ከማንኛውም ፍጥረት የበለጠ ኃይል ያለው ይሖዋ አምላክ ኃይሉን ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ሌሎችን አስገድዶ እንዲሽቆጠቆጡለት ለማድረግ አለመጠቀሙ የሚያስደንቅ አይደለምን? ከእርሱ ጋር ሲነጻጸሩ ኢምንት የሆኑት የሰው ልጆች ግን አንዱ ሌላውን ሲጨቁን የኖረበትን ዘመን የሚያወሳ ታሪክ አላቸው። (መክብብ 8:9) ምክንያታዊነት ይሖዋን ይበልጥ እንድናፈቅረው የሚያነሳሳ ውድ ባሕርይ እንደሆነ ግልጽ ነው። ይህም በበኩሉ እኛም ይህን ባሕርይ እንድናዳብር ሊያነሳሳን ይችላል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ያብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በ1769 የመዝገበ ቃላት አዘጋጅ የሆኑት ጆን ፓርክኸርስት ቃሉን “እሺ ባይ፣ ረጋ ያለ፣ ገር፣ ታጋሽ” ብለው ተርጉመውታል። ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራንም “እሺ ባይ” ብለው ተርጉመውታል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ የይሖዋ ስምና የሰማያዊ ሰረገላው ራእይ ይሖዋ አዲስ ክስተቶችን እንደ ሁኔታው የሚያስተናግድ መሆኑን ጎላ አድርጎ የሚገልጸው እንዴት ነው?
◻ ምክንያታዊነት ምንድን ነው? የመለኮታዊ ጥበብ አንዱ ምልክት የሆነውስ ለምንድን ነው?
◻ ይሖዋ ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ መሆኑን’ ያሳየው በምን መንገዶች ነው?
◻ ይሖዋ በአንዳንድ ወቅቶች ላይ ሊያደርግ ያሰበውን ነገር ለመለወጥ የመረጠው ለምንድን ነው?
◻ ይሖዋ በሥልጣን አጠቃቀም ረገድ ምክንያታዊነትን ያሳየው እንዴት ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ ክፉውን ንጉሥ ምናሴን ይቅርታ ያደረገለት ለምንድን ነው?