የብቸኝነት ስሜት ሕይወትህን እንዲያጨልመው አትፍቀድለት
የብቸኝነት ስሜት በዕድሜ የገፉትንም ሆነ የወጣቶችን ሕይወት ሊያጨልም ይችላል። ጁዲት ቪዮረስት የተባሉ ደራሲ ሬድቡክ በተባለው መጽሔት ላይ እንደሚከተለው ብለዋል፦ “የብቸኝነት ስሜት ልብ ላይ እንደ ድንጋይ ይከብዳል። . . . የብቸኝነት ስሜት ባዶና ተስፋ ቢስ ያደርገናል። የብቸኝነት ስሜት እናት እንደሌለው ልጅ፣ እንደ ባዘነች የበግ ግልገል፣ ምንም እንደማንረባ እንዲሁም ለሌላው ደንታ ቢስ በሆነ ሰፊ ዓለም ውስጥ መውጫ መግቢያው እንደጠፋብን እንዲሰማን ያደርጋል።”—መስከረም 1991
ከጓደኞች መለየት፣ ወዳልለመዱት አካባቢ መሄድ፣ ፍቺ፣ የዘመድ ሞት ወይም የግንኙነት መቋረጥና እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች በሙሉ የብቸኝነት ስሜት እንዲሰማህ ሊያደርጉ ይችላሉ። አንዳንዶች ሌሎች ሰዎች አጠገባቸው እያሉም እንኳ በብቸኝነት ስሜት ይዋጣሉ።
ምን ልታደርግ ትችላለህ?
የብቸኝነት ስሜት ቢይዝህ ምንም መከላከያ የሌለው ተጠቂ በመሆን እጅህን መስጠት አለብህን? የብቸኝነት ስሜት ቀስ በቀስ እንደ ነቀዝ እንዲበላህ ወይም የመኖር ፍላጎትህን እንዳያሟጥጥብህ ለመከላከል ማድረግ የምትችለው ነገር ይኖራልን? በእርግጥ አለ። በጣም ጠቃሚ የሆነ ምክር አለልህ። በመንፈስ አነሣሽነት በተጻፈው የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጣም ጥሩ ምክር ተሰጥቷል። የብቸኝነትን ስሜት ለመዋጋት የሚያስፈልግህ ይህን ዓይነቱን ማበረታቻ ማግኘት ብቻ ሊሆን ይችላል።—ማቴዎስ 11:28, 29
ለምሳሌ ያህል ከ3,000 ዓመታት ገደማ በፊት በመካከለኛው ምሥራቅ ትኖር የነበረችውን የአንዲትን ሩት ተብላ የምትጠራ ወጣት ሴት ታሪክ ማንበብ የሚያበረታታ ሆኖ ታገኘው ይሆናል። ሩት የብቸኝነት ስሜት ሊያጠቃት ይችል እንደነበረ የታወቀ ነው። ባሏ ሲሞትባት ከአማቷ ጋር በመሆን በማታውቀው አካባቢ ለመኖር ወደ እስራኤል ሄደች። (ሩት 2:11) ምንም እንኳን ቤተሰቧንና የቀድሞ ጓደኞቿን ብታጣና በማታውቀው አገር እንግዳ ሆና ብትኖርም የብቸኝነት ስሜት እንዲውጣት እንደፈቀደችለት የሚጠቁም ምንም ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። የእሷን ታሪክ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በሩት መጽሐፍ ውስጥ ማንበብ ትችላለህ።
አንተም እንደ ሩት ብሩህ የሆነ አመለካከት መያዝ ያስፈልግሃል። ስለ አንዳንድ ጉዳዮችና ሁኔታዎች ያለህ አመለካከት የብቸኝነትን ስሜት ሊያባብሰው ይችላል። ቀስ በቀስ የሚያመነምን በሽታ የያዘውን አባቷን ለአራት ዓመት ስታስታምም የነበረችው አን ይህ ሁኔታ ደርሶባታል። አባቷ ሲሞቱ በብቸኝነት ስሜት ተዋጠች። “ሙሉ በሙሉ የተተውኩና ምንም የማልረባ ለማንም ሰው ምንም ጥቅም የማልሰጥ እንደሆንሁ ተሰማኝ” ትላለች። “ይሁን እንጂ አሁን ሕይወቴ ሌላ ገጽታ የያዘ የመሆኑን ሐቅ ፊት ለፊት ተጋፈጥኩት፤ ያለብኝን የብቸኝነት ስሜት ለማሸነፍ አሁን ያለኝን ሁኔታ መቀበልና በዚህ ሁኔታዬ በተሻለ መንገድ መጠቀም እንዳለብኝ ተገነዘብኩ።” አንዳንድ ጊዜ ሁኔታዎችህን መቀየር አትችል ይሆናል፤ ለእነሱ ያለህን አመለካከት ግን ልትለውጥ ትችላለህ።
ምንም እንኳ ውጤት ባለው ሥራ መጠመድ የሚረዳ ቢሆንም፣ ይህ ብቻውን የብቸኝነትን ስሜት ለማሸነፍ በቂ ሊሆን አይችልም። ባገባች በስድስት ወሯ ባሏን በሞት ያጣችው አይሪን በራሷ ላይ ከደረሰው ሁኔታ ይህ ነገር እውነት መሆኑን ልትገነዘብ ችላለች። “ብዙውን ጊዜ ብቸኝነት የሚሰማኝ ሥራ በምፈታበት ጊዜ ነው፤ ስለዚህ ሌሎችን በመቅረብና ችግሮቻቸውን እንዲያሸንፉ በመርዳት ላይ አተኮርሁ።” ሌሎችን መርዳት ደስታ ያመጣል፤ ብቸኝነት የሚሰማቸው ክርስቲያኖች የጌታ ሥራ የሚበዛላቸው ሊሆኑ ይችላሉ።—ሥራ 20:35፤ 1 ቆሮንቶስ 15:58
ጓደኞችህ እንዲረዱህ አድርግ
ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ መጽሔት ብቸኝነት የሚሰማቸው ልጆች “ጓደኛ ማጣት ባስከተለባቸው ቁስል” የተጎዱ መሆናቸውን ገልጿል። (ሚያዝያ 28, 1991) ብዙዎቹ ብቸኝነት የሚሰማቸው ሰዎች ወጣቶችም ሆኑ በዕድሜ የገፉ ጓደኛ አልባ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ስለዚህ አሳቢ በሆነው ክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እውነተኛ ጓደኝነት ማግኘቱ ካሉን በረከቶች አንዱ ነው። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያለህን ጓደኝነት ለማስፋት ሞክር፤ እነሱ በሚችሉት መንገድ ሁሉ እንዲረዱህ ፍቀድላቸው። አንዱ የጓደኛ ጥቅም በችግር ጊዜ መርዳት ነው።—ምሳሌ 17:17፤ 18:24
ሆኖም ባለብህ የስሜት ሥቃይ የተነሣ ጓደኞችህ አንተን መርዳቱ አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው እንዳታደርግ ተጠንቀቅ። እንዴት? ጄፍሪ ያንግ የተባሉ ደራሲ እንዲህ በማለት ገልጸዋል፦ “አንዳንድ ብቸኝነት የሚሰማቸው ሰዎች በጨዋታ ጊዜ እኛ ብቻ ካልተናገርን በማለት ወይም ደግሞ ተገቢ ያልሆኑ ወይም ሰውን የሚጎዱ አነጋገሮችን በመጠቀም ጓደኛ ሊሆኗቸው የሚችሉትን ሰዎች ያርቃሉ። በዚያም ሆነ በዚህ ከፍተኛ የብቸኝነት ስሜት ያለባቸው ሰዎች የቅርብ ግንኙነትን ማበላሸት ይቀናቸዋል።”—ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ዎርልድ ሪፖርት መስከረም 17, 1984
አንዳንድ ጊዜ ራስህን ከሌሎች ሰዎች በማግለል ነገሮችን ይበልጥ እንዲባባሱ ልታደርግ ትችላለህ። ፒተር የተባሉ አንድ የ50 ዓመት ሰው እንዲህ አድርገው ነበር። ምንም እንኳን በውስጣቸው እርዳታ የማግኘት ፍላጎት ቢኖራቸውም ባለቤታቸው ከሞቱ በኋላ ራሳቸውን ከሌሎች ሰዎች ማግለል ጀመሩ። “አንዳንድ ቀን ሌሎች ሰዎች በፍጹም አብረውኝ እንዲሆኑ አልፈልግም ነበር፤ ከጊዜ በኋላ ራሴን ከሰዎች እያገለልኩ እንዳለሁ አወቅሁ” በማለት ይናገራሉ። ይህ ደግሞ አደገኛ ሊሆን ይችላል። ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ ለብቻችን የምንሆንባቸው ጊዜያት ጠቃሚ ቢሆኑም ፈጽሞ ራስን ከሰዎች ማግለል ግን ጎጂ ነው። (ምሳሌ 18:1) ፒተር ይህን ተገንዝበው ነበር። “በመጨረሻ ችግሬን ተቋቁሜ ለማሸነፍና በጓደኞቼ እርዳታ እንደገና ሕይወቴን ለመገንባት ቻልኩ” ብለዋል።
ሆኖም ሌሎች አንተን የመርዳት ግዴታ እንዳለባቸው አድርገህ አትገምት። ብዙ ነገር እንዲደረግልህ የምትፈልግ ከመሆን ለመራቅ ጥረት አድርግ። በደግነት የሚደረግልህን ማንኛውንም ነገር በደስታ ተቀበል፤ እንዲሁም ለተደረገልህ ነገር አድናቆትህን ግለጽ። በተጨማሪም በምሳሌ 25:17 ላይ የሚገኘውን “እንዳይሰለችህ እንዳይጠላህም እግርህን ወደ ባልንጀራህ ቤት አታዘውትር” የሚለውን ጥሩ ምክር አስታውስ። ለ35 ዓመታት በትዳር አብረው ከኖሩ በኋላ ባላቸውን በሞት በማጣታቸው በከባድ የብቸኝነት ስሜት ተውጠው የነበሩት ፍራንስስ ይህ ዓይነቱ ማስጠንቀቂያ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማቸዋል። “ሌሎች እንዲያደርጉልህ በምትጠብቀው ነገር ምክንያታዊ ሁን፤ እንዲሁም ከመጠን በላይ እንዲያደርጉልህ አትጠብቅ። እርዳታ በመፈለግ ወደ አንድ ሰው ቤት እግር አታብዛ” ብለዋል።
ይሖዋ ያስብልሃል
ሰብአዊ ጓደኞችህ አንዳንድ ጊዜ ለእርዳታ ባይደርሱልህም እንኳን ይሖዋን እንደ ጓደኛህ አድርገህ ልትይዘው ትችላለህ። ይሖዋ እንደሚያስብልህ እርግጠኛ ሁን። በእሱ ላይ ያለህ ትምክህት ምን ጊዜም ጠንካራ ይሁን፤ እንዲሁም በእርሱ ጥበቃ ስር ከለላ ለማግኘት ዘወትር ጥረት አድርግ። (መዝሙር 27:10፤ 91:1, 2፤ ምሳሌ 3:5, 6) ሞዓባዊቷ ሩት ይህን አድርጋለች፤ ይህን በማድረጓም በጣም ብዙ በረከት አግኝታለች። ሌላው ቀርቶ የኢየሱስ ቅድመ አያት ለመሆን በቅታለች!—ሩት 2:12፤ 4:17፤ ማቴዎስ 1:5, 16
ያለማቋረጥ ወደ ይሖዋ ጸልይ። (መዝሙር 34:4፤ 62:7, 8) ማርግሬት ጸሎት የብቸኝነትን ስሜት ለማሸነፍ ከፍተኛ ኃይል እንደሰጣት ተረድታለች። ባሏ ገና ወጣት ሳለ በሞት እስከተለያት ጊዜ ድረስ አብራው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ትካፈል ነበር። “ድምፄን ከፍ አድርጌ በመጸለይ ፍርሃቴንና ጭንቀቴን ሁሉ ለይሖዋ መንገር ምን ጊዜም ጠቃሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ይህም ብቸኝነት በሚሰማኝ ጊዜ ነገሮችን በትክክል እንድመለከት ረድቶኛል። ይሖዋ ጸሎቶቼን ሲመልስልኝ ማየቴ ትምክህት አሳድሮብኛል” ትላለች። “እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት” የሚለውን የሐዋርያው ጴጥሮስን ምክር በመከተል ብዙ ጥቅም አግኝታለች።—1 ጴጥሮስ 5:6, 7፤ መዝሙር 55:22
ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት ብቸኝነት የሚሰማቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ የሚያጡትን አንድ ነገር እንድታገኝ ይረዳሃል። ይኸውም በራስ መተማመን ነው። ጃኔት ኩፕፈርማን የተባለችው ጋዜጠኛ ባሏ በካንሰር ከሞተ በኋላ ስለተሰማት “በራስ ያለመተማመንና የከንቱነት ስሜት” ጽፋለች። “ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ብዙዎቹን ሴቶች ራስን እስከ መግደል የሚያደርስ የመንፈስ ጭንቀት የሚያመጣባቸው ይህ ዓይነት የከንቱነት ስሜት ነው” ስትል ተናግራለች።
ይሖዋ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከትህ አስታውስ። የማትረባ እንደሆንክ አድርጎ አያስብም። (ዮሐንስ 3:16) አምላክ ባለፉት ዘመናት ሕዝቦቹ የነበሩትን እስራኤላውያንን እንደረዳቸው ሁሉ አንተንም ይረዳሃል። እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “አንተ ባሪያዬ ነህ፣ መርጬሃለሁ አልጥልህም ያልሁህ ሆይ፣ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፣ እረዳህማለሁ፣ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ።”—ኢሳይያስ 41:9, 10
በአምላክ ላይ አታማር
ከሁሉም በላይ ደግሞ ላለብህ የብቸኝነት ስሜት በአምላክ ላይ አታማር። ለዚህ ተጠያቂው ይሖዋ አይደለም። የእሱ ዓላማ አንተም ሆንክ ባጠቃላይ የሰው ዘር በጥሩና በሚያረካ ጓደኝነት ሁልጊዜ እንድትደሰቱ ነው። አምላክ አዳምን ሲፈጥር “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም። የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት” ብሎ ነበር። (ዘፍጥረት 2:18) አምላክ የመጀመሪያዋን ሴት ሔዋንን በፈጠረ ጊዜ ያደረገው ነገር ይህን ነበር። ሰይጣን ባያምፅ ኖሮ አዳምና ሔዋንም ሆኑ እነሱ የሚያፈሯቸው ቤተሰቦች የብቸኝነት ስሜት አይመጣባቸውም ነበር።
እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ክፋት ለጊዜው እንዲቀጥል መፍቀዱ የብቸኝነት ስሜት እንዲጨምርና ሌሎች ሥቃዮችም እንዲከሰቱ አድርጓል። ሆኖም ይህ ጊዜያዊ ብቻ መሆኑን ፈጽሞ አትርሳ። በመጪው አዲስ ዓለም ውስጥ አምላክ ከሚያደርግልህ ነገር አንፃር ሲታይ የብቸኝነት ስሜት የሚያመጣቸው መከራዎች ይህን ያህል ለመሸከም አዳጋች አይደሉም። እስከዚያ ጊዜ ድረስም ቢሆን አምላክ ይደግፍሃል፣ ያጽናናሃል።—መዝሙር 18:2፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7
ይህን ማወቅህ ብርታት ሊሰጥህ ይችላል። ፍራንስስ (ቀደም ሲል የተገለጸችው) ባሏ ከሞተባት በኋላ በመዝሙር 4:8 ላይ በሚገኙት ቃላት በጣም ተጽናንታለች፤ በተለይ ደግሞ እነዚህ ቃላት ሌሊት ያጽናኗት ነበር። “በሰላም እተኛለሁ አንቀላፋለሁም፤ አቤቱ፣ አንተ ብቻህን በእምነት አሳድረኸኛልና።” በመዝሙር መጽሐፍ ላይ እንደሚገኙት ባሉ ስሜትን በሚነኩ ቃላት ላይ አሰላስል። እንደ መዝሙር 23:1–3 ባሉት ጥቅሶች ላይ በተገለጸው መሠረት አምላክ እንዴት አድርጎ እንደሚንከባከብህ አሰላስል።
ብቸኝነት የሚሰማውን ሰው መርዳት የሚቻለው እንዴት ነው?
ብቸኝነት የሚሰማውን ሰው ለመርዳት የመጀመሪያው ዘዴ ፍቅር ማሳየት ነው። የአምላክ ሕዝቦች እርስ በርሳቸው ፍቅር እንዲያሳዩ መጽሐፍ ቅዱስ ደጋግሞ ያበረታታቸዋል። በተለይ ደግሞ በመከራ ጊዜ እንዲህ እንዲያደርጉ ያበረታታል። ሐዋርያው ጳውሎስ “በወንድማማች መዋደድ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 12:10) እንዲያውም በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል “ፍቅር አይወድቅም” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 13:8) ብቸኝነት ለሚሰማቸው ሰዎች ፍቅር ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?
ብቸኝነት የሚሰማቸውን ሰዎች እስከ ጭራሹ ከመተው ወይም ችላ ከማለት ይልቅ አሳቢ የሆኑ ሰዎች አመቺ በሆነው ጊዜ ሁሉ በትዕግሥት እነርሱን በመርዳት ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር ሊያሳዩአቸው ይችላሉ። “የድኾችን ጩኸት ሰምቼ እታደጋቸው ነበር፤ ወላጆቻቸው የሞቱባቸውንም ልጆች እረዳቸው ነበር። . . . ባሎቻቸው የሞቱባቸውም ሴቶች ስለምደግፋቸው የደስታ መዝሙር ይዘምሩ ነበር” ሲል እንደተናገረው ኢዮብ እንደተባለው ሰው ሊሆኑ ይችላሉ። (ኢዮብ 29:12, 13 የ1980 ትርጉም) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ የተሾሙ ሽማግሌዎችም ሆኑ ርኅሩኅ የሆኑ ጓደኞች እንደ ስሜትን መረዳት፣ የሞቀ ፍቅርና ማጽናኛ የመሳሰሉትን መሠረታዊ የሰው ፍላጎቶች በመስጠት ተመሳሳይ አሳቢነት ሊያሳዩ ይችላሉ። ራሳቸውን በእነሱ ቦታ በማስቀመጥ ስሜታቸውን መረዳትና የልባቸውን እንዲያጫውቷቸው መፍቀድ ይችላሉ።—1 ጴጥሮስ 3:8
ብዙ ጊዜ ወንድሞች የሚያደርጓቸው ጥቃቅን ነገሮች ብቸኝነት ለሚሰማቸው ሰዎች በጣም ትልቅ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ የእምነት ጓደኛችን የሚያፈቅረው የቤተሰብ አባል ቢሞትበት ከእውነተኛ ጓደኝነት በሚመነጭ የልግስና አድራጎት አማካኝነት ብዙ ጥሩ ነገር ማከናወን እንችላለን። እንደ ራት ወይም ምሳ መጋበዝ፣ በርኅራኄ ማዳመጥ፣ ወይም ማበረታታት የመሳሰሉት ነገሮች እንደ ቀላል መታየት የለባቸውም። እነዚህ ነገሮች አንድ ሰው የብቸኝነትን ስሜት እንዲያሸንፍ በመርዳት ረገድ በጣም ጠቃሚ ናቸው።—ዕብራውያን 13:16
ሁላችንም ብንሆን አልፎ አልፎ ብቸኝነት እንደሚሰማን የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ የብቸኝነት ስሜት እንደ መቅሰፍት ሆኖ እንዲያሠቃየን መፍቀድ የለብንም። ሕይወትህ ትርጉም ባላቸውና ገንቢ በሆኑ ሥራዎች የተሞላ ይሁን። ጓደኞችህ በሚችሉት ሁሉ እንዲረዱህ አድርግ። በይሖዋ አምላክ ላይ ትምክህት ይኑርህ። “የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፣ እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል” የሚለውን በመዝሙር 34:19 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን አበረታች ተስፋ ሁልጊዜ በአእምሮህ ያዝ። ለእርዳታ ወደ ይሖዋ ዘወር በል፤ የብቸኝነት ስሜት ሕይወትህን እንዲያጨልመው አትፍቀድለት።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የብቸኝነትን ስሜት ለመዋጋት የሚረዱ አንዳንድ መንገዶች
▪ ወደ ይሖዋ ተጠግቶ መኖር
▪ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ማጽናኛ ለማግኘት መጣር
▪ ብሩህ የሆነ ክርስቲያናዊ አመለካከት መያዝ
▪ ትርጉም ባላቸው ሥራዎች መጠመድ
▪ የጓደኞችን ቁጥር መጨመር
▪ ጓደኞች እንዲረዱ ሁኔታውን ቀላል ማድረግ
▪ ራስን ከሌሎች አለማግለል፤ ከዚህ ይልቅ ከሁሉም ጋር ተግባቢ የሆነ ፍቅር መኮትኮት
▪ ይሖዋ እንደሚያስብልን ትምክህት ይኑረን
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ብቸኝነት የሚሰማቸውን ሰዎች እንዴት ልትረዳቸው ትችላለህ?
▪ ስሜታቸውን መረዳት፣ ሞቅ ያለ ፍቅራዊ ስሜት ማሳየትና ማጽናናት
▪ የልባቸውን እንዲያጫውቱህ ራስን ማቅረብ
▪ ሊረዷቸው የሚችሉ ጥቃቅን ነገሮችንም ቢሆን ሳታቋርጥ ማድረግ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሩት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟትም እንኳን የብቸኝነት ስሜት ሕይወቷን እንዲያጨልመው እንደፈቀደችለት የሚጠቁም ምንም ነገር የለም