የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
የአምላክ ቃል ሰውን የመለወጥ ኃይል አለው
“የአምላክ ቃል ሕያው ነው፤ ሰውን የመለወጥ ኃይልም አለው።” (ዕብራውያን 4:12 አዓት) በሐሰት ሃይማኖት ተታልለው የነበሩ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ሲያገኙ ለውጥ በማድረጋቸው እነዚህ ቃላት እውነት መሆናቸው በተደጋጋሚ ተረጋግጧል። ከዶሚኒካን ሪፑብሊክ የተገኘው ቀጥሎ ያለው ተሞክሮ እንደሚያሳየው መጽሐፍ ቅዱስ ያለው ኃይል የሰዎችን ሕይወት ሊለውጥና ተስፋ ሊሰጥ ይችላል።
የይሖዋ ምሥክሮች ሁለት ትንንሽ ልጆቿን በቅርብ ጊዜ በሞት ያጣች አንዲት አጥባቂ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ሴት ያነጋግራሉ። በከባድ ሐዘን ተውጣ ነበር፤ የደረሰባትንም አሳዛኝ አደጋ በየቀኑ በምሬት ትናገራለች። ምሥክሮቹ መጽሐፍ ቅዱስ በዮሐንስ 5:28, 29 ላይ ስለ ትንሣኤ ተስፋ ምን እንደሚል አሳዩአት። ከምሥክሮቹ ጋር ተጨማሪ ውይይቶችን ካደረገች በኋላ በትንሣኤ ተስፋ ከመጽናናቷም በላይ የካቶሊክ ሃይማኖት መሪዎቿ አታልለዋት እንደነበረ ተገነዘበች።
ምንም ጊዜ ሳታባክን ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ወጣችና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንድታደርግ የቀረበላትን ግብዣ ተቀበለች። ይሁን እንጂ ባሏ በእሷ እርምጃ አልተስማማም ነበር። እሱም አጥባቂ ካቶሊክ ስለነበረ ሚስቱ የጀመረችውን አቅጣጫ እንድትተው እንዲመክሯትና ወደዚያው ወደ ካቶሊክነቷ እንድትመለስ እንዲያግባቧት የታወቁ የፖለቲካና የሃይማኖት ጓደኞቹ እንዲያነጋግሯት ዝግጅት አደረገ። ከዚያም በኋላ እፈታሻለሁ ብሎ ዛተ። እንዲያውም ልንፋታ ነው በማለት ለቤተ ክርስቲያኑ አባላት እስከመናገር ደርሶ ነበር።
ይሁን እንጂ የተጠቀመበት ዘዴ አልተሳካለትም። እንዲያውም እሷ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቷን ለመቀጠል የበለጠ ቆረጠች። መንፈሳዊ እድገት በማድረጓና ጥሩ የሆኑ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን በማዳበሯ ከመፍታት ይልቅ ከእሷ ጋር ለመቀጠል ወሰነ። አልፎ ተርፎም አንድ ቀን እሷ የምታጠናቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ማስተማሪያ መጻሕፍት ለመመርመር ተስማማ። ይሁን እንጂ እነዚህን መጻሕፍት መመርመር የሚፈልገው የካቶሊክ ትርጉም የሆነውን የራሱን መጽሐፍ ቅዱስ በመጠቀም ብቻ መሆኑን ገለጸ።
የይሖዋ ምሥክሮች ባዘጋጁአቸው ጽሑፎች አማካኝነት በቀጥታ ከራሱ መጽሐፍ ቅዱስ አዳዲስ ነገሮችን ሲማር በጣም ተገረመ። ሚስቱ ትክክለኛውን መንገድ መርጣ እንደነበረ ተገነዘበ፤ የእሷንም ምሳሌ ለመከተል ወዲያው ዝግጁ ሆነ። በራሱ ሕይወት ላይ ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልገውም ተገንዝቧል። አንዱ አስቸጋሪ የሆነው ፈተና ሲጋራ የማጨስ ልማዱን መተው ነበር። “በገንዘብ የሚገዛ ሞት፤ ሲጋራ ማጨስን ለማቆም የሚረዱ አሥር መንገዶች” በሚል የሽፋን ርዕስ የወጣውን የሐምሌ 8, 1989 የእንግሊዝኛ ንቁ! መጽሔት ካነበበ በኋላ ይህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ልማድ ለማቆም ቁርጥ ውሳኔ አደረገ። በተለመዱት የሲጋራ ፓኬቶች ፋንታ ይህንን የንቁ! መጽሔት እትም በኪሱ ይይዝ ጀመር። እንዲያጨስ የሚገፋፋ ስሜት በመጣበት ቁጥር ስለ ማጨስ የሚናገረውን ርዕስ ያነባል። የተጠቀመበት ዘዴ ሠራለት! በዚህ ርዕስ የወጣውን ሐሳብ ብዙ ጊዜ ደጋግሞ ካነበበ በኋላ ሲጋራ ማጨሱን ሊያቆም ቻለ።
በአሁኑ ጊዜ ባልና ሚስቱ ተጠምቀው ይሖዋን እያገለገሉ ነው። አብዛኛውን ጊዜውን የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመስበኩ ሥራ በማዋል ሁኔታዎቹ በሚፈቅዱለት ጊዜ ሁሉ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ በመሆን ይሠራል። እንዲሁም በአካባቢው በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ዲያቆን በመሆን ያገለግላል። እሱም ሆነ ሚስቱ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ልጆቻቸው ወደ ሕይወት ሲመለሱ ለመቀበል የሚችሉበትን የትንሣኤ ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ። አዎን፣ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ሕያውና ሰውን የመለወጥ ኃይል ያለው ነው!