የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 1/15 ገጽ 29-31
  • መለኮታዊ መመሪያን ተቀብሏል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መለኮታዊ መመሪያን ተቀብሏል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ችግሮች ያጋጠሙት ጻድቅ ሰው
  • መንፈሳዊ ሰው
  • የዮሴፍ ተስፋ
  • ቤተሰቡን ጠብቋል፣ ተንከባክቧል፣ ኃላፊነቱን ተወጥቷል
    በእምነታቸው ምሰሏቸው
  • ቤተሰቡን ጠብቋል፣ ተንከባክቧል፣ ኃላፊነቱን ተወጥቷል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • ማርያም ሳታገባ ፀነሰች
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
  • ከኢየሱስ ቤተሰቦች ምን እንማራለን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 1/15 ገጽ 29-31

መለኮታዊ መመሪያን ተቀብሏል

በደንብ ተንከባክበህ እንድታሳድገው ተብሎ አንድ ፍጹም ልጅ ተሰጥቶሃል እንበል። እንዴት ያለ ከባድ ሥራ ነው! ማንኛውም ፍጹም ያልሆነ ሰው እንዴት ይህን ሊያደርግ ይችላል? መለኮታዊ መመሪያን በመቀበልና በዕለታዊ ሕይወቱ በመተግበር ብቻ ነው።

የኢየሱስ አሳዳጊ አባት ዮሴፍ ያደረገው ይህንኑ ነበር። ስለ ዮሴፍ ዝርዝር ታሪኮችን ከሚተርኩት ተአማኒነት ከሌላቸው ወጎች በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስ እሱ በኢየሱስ የልጅነት ሕይወት ውስጥ ስለ ተጫወተው ሚና የሚናገረው ጥቂት ነው። ዮሴፍና ሚስቱ ማርያም ኢየሱስን፣ ሌሎች አራት ወንዶች ልጆችንና ሴቶች ልጆችን እንዳሳደጉ እናውቃለን።—ማርቆስ 6:3

ዮሴፍ በሰሎሞን በኩል የእስራኤሉ ንጉሥ የዳዊት ዝርያ ነው። የያዕቆብ ልጅ ሲሆን የኤሊ ደግሞ አማች ነበር። (ማቴዎስ 1:16፤ ሉቃስ 3:23) በገሊላ ውስጥ በነበረች ናዝሬት በምትባል ከተማ ውስጥ የነበረ አናጢ እንደመሆኑ መጠን ድሃ ነበር። (ማቴዎስ 13:55፤ ሉቃስ 2:4, 24፤ ከዘሌዋውያን 12:8 ጋር አወዳድር።) በመንፈሳዊ ግን ሀብታም ነበር። (ምሳሌ 10:22) ይህ የሆነው መለኮታዊ መመሪያዎችን ይቀበል ስለነበር እንደሆነ እሙን ነው።

ዮሴፍ በአምላክ ላይ እምነት የነበረውና ትክክል የሆነውን ለማድረግ የሚፈልግ የዋህና ትሑት አይሁዳዊ እንደነበር አያጠራጥርም። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ስለ እሱ ሕይወት የተመዘገቡት ጥቂት ገጠመኞች የይሖዋን ትእዛዞች ሁልጊዜ ያከብር እንደነበር ያሳያሉ። ይህን ያደረገውም በሕጉ የታቀፉትንም ሆነ ራሱ ዮሴፍ በቀጥታ በመላእክት በኩል የተቀበላቸውን መልእክቶች ጭምር በመታዘዝ ነው።

ችግሮች ያጋጠሙት ጻድቅ ሰው

አንድ አምላካዊ ሰው ከባድ ችግሮች ሲገጥሙት ምን ማድረግ አለበት? ‘ሸክሙን በይሖዋ ላይ ጥሎ’ መለኮታዊ መመሪያን መከተል ነዋ! (መዝሙር 55:22) ዮሴፍ ያደረገው ይህንኑ ነው። ማርያምን ባጨበት ወቅት “ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች።” ዮሴፍ ‘ጻድቅ ስለነበርና በሕዝብ ፊት ሊያጋልጣት ስላልፈለገ በስውር ሊተዋት አሰበ።’ ዮሴፍ በነገሩ ላይ በጥሞና ካሰበበት በኋላ የይሖዋ መልአክ በሕልም “የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፣ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ” አለው። ከእንቅልፉ ሲነቃ ዮሴፍ “የጌታ መልአክ እንዳዘዘው አደረገ፤ እጮኛውንም ወሰደ፤ የበኩር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፤ ስሙንም ኢየሱስ አለው።” (ማቴዎስ 1:18–25) ዮሴፍ መለኮታዊ መመሪያ ተቀብሏል።

አውግስጦስ ቄሣር ሰዎች በየከተሞቻቸው እንዲቆጠሩ አዘዘ። ዮሴፍና ማርያም በታዛዥነት በይሁዳ ወደምትገኘው ቤተ ልሔም ሄዱ። እዚያም ማርያም ኢየሱስን ወለደችና ሌላ የእንግዳ ማረፊያ ስላልተገኘ በግርግም አኖረችው። በዚያች ሌሊት የዚህን ልዩ ልጅ መወለድ ከመላእክት የሰሙት እረኞች ሕፃኑን ለማየት መጡ። ከ40 ቀናት በኋላ ዮሴፍና ማርያም ኢየሱስን ከመሥዋዕት ጋር በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ በማቅረብ ሕጉን ፈጸሙ። በዕድሜ የገፋው ስምዖን ኢየሱስ ስለሚያደርጋቸው ታላላቅ ነገሮች ትንቢት ሲናገር ሲሰሙ ሁለቱም ተገረሙ።—ሉቃስ 2:1–33፤ ከዘሌዋውያን 12:2–4, 6–8 ጋር አወዳድር።

ሉቃስ 2:39 ዮሴፍና ማርያም ኢየሱስን በቤተ መቅደስ ካቀረቡ በኋላ ወደ ናዝሬት እንደሄዱ ቢናገርም ይህ ጥቅስ ባጭሩ ከተገለጸው ዘገባ ክፍል አንዱ ነው። ምሥራቃውያን ኮኮብ ቆጣሪዎች (ሰብአ ሰገል) ማርያምና ኢየሱስን በቤተ ልሔም ውስጥ በነበረ አንድ ቤት ውስጥ የጠየቋቸው ኢየሱስ ቤተ መቅደስ ከቀረበ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ይመስላል። መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ይህ ጥየቃ በኢየሱስ ላይ ሞት እንዳያስከትል አገደ። ሰብአ ሰገል ከሄዱ በኋላ የይሖዋ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገለጠለትና ‘ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋል’ ሲል ነገረው። እንደተለመደው ዮሴፍ መለኮታዊ መመሪያ በመከተል ቤተሰቡን ይዞ ወደ ግብፅ ሄደ።—ማቴዎስ 2:1–14

ሄሮድስ ሲሞት በግብፅ ውስጥ መልአኩ በሕልም ወደ ዮሴፍ ቀርቦ “ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል አገር ሂድ” አለው። በአባቱ በሄሮድስ ቦታ አርኬላዎስ እየገዛ መሆኑን ሰምቶ ዮሴፍ ወደ ይሁዳ መመለስ ፈራ። በሕልም የተሰጠውን መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ በመታዘዝ ወደ ገሊላ ክፍለ ሀገር ወጣና በናዝሬት ከተማ ኖረ።—ማቴዎስ 2:15–23

መንፈሳዊ ሰው

ዮሴፍ ቤተሰቡ መለኮታዊ ሕግን መታዘዝና በመንፈሳዊ በደንብ የተመገቡ መሆን በሚችሉበት መንገድ ነገሮችን ይመራ ነበር። በየዓመቱ የሚደረገውን የማለፍ በዓል እንዲያከብሩ ጠቅላላ ቤተሰቡን ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ነበር። እንዲህ ባለ አንድ ወቅት ላይ ዮሴፍና ማርያም ወደ ናዝሬት ተመልሰው የአንድ ቀን መንገድ የሚያህል ከሄዱ በኋላ የ12 ዓመቱ ልጃቸው ኢየሱስ ከእነሱ ጋር እንደሌለ ተገነዘቡ። ተመልሰው በደንብ ከፈለጉት በኋላ መጨረሻ ላይ በቤተ መቅደስ ውስጥ እዚያ ያሉትን መምህራን ሲያደምጣቸውና ሲጠይቃቸው አገኙት።—ሉቃስ 2:41–50

ዮሴፍ ሚስቱ በአንዳንድ ነገሮች ቀዳሚ እንድትሆን ያደርግ የነበረ ይመስላል። ለምሳሌ ያህል ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ኢየሱስን በቤተ መቅደስ ውስጥ ሲያገኙት ወጣት ልጅዋን ስለ ጉዳዩ ያነጋገረችው ማርያም ነበረች። (ሉቃስ 2:48, 49) ኢየሱስ “የጸራቢ ልጅ” ሆኖ ሲያድግ መንፈሳዊ መመሪያ አግኝቷል። ኢየሱስ “ጸራቢው የማርያም ልጅ” ተብሎ ስለተጠራ ዮሴፍ አናጺነትም አስተምሮታል። (ማቴዎስ 13:55፤ ማርቆስ 6:3) በአሁኑ ወቅት ያሉትም አምላካዊ ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስተማር በተለይም ደግሞ በመንፈሳዊ ለማሠልጠን ያሏቸውን ተመሳሳይ አጋጣሚዎች ሙሉ በሙሉ መጠቀም አለባቸው።—ኤፌሶን 6:4፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:5፤ 3:14–16

የዮሴፍ ተስፋ

ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ ዮሴፍ አሟሟት የሚናገሩት ነገር የለም። ይሁን እንጂ በማርቆስ 6:3 ላይ ኢየሱስ የዮሴፍ ሳይሆን “የማርያም ልጅ” መባሉ ሊስተዋል ይገባል። ይህ ዮሴፍ በዚያ ወቅት ሞቶ እንደነበር ያሳያል። በተጨማሪም ዮሴፍ እስከ 33 እዘአ ድረስ ቢኖር ኖሮ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ የነበረው ኢየሱስ ማርያምን ለሐዋርያው ዮሐንስ በአደራ እንደማይሰጣት የታወቀ ነው።—ዮሐንስ 19:26, 27

በዚህ ምክንያት ዮሴፍ የሰውን ልጅ ድምፅ ሰምተው በትንሣኤ ከሚነሡት የሞቱ ሰዎች መካከል ይሆናል ማለት ነው። (ዮሐንስ 5:28, 29) ዮሴፍ ከ1,900 ዓመታት በፊት መለኮታዊ መመሪያን እንደታዘዘ ሁሉ ይሖዋ የዘላለም ሕይወት ለመስጠት ያዘጋጀውን ዝግጅት ተምሮ በደስታ እንደሚጠቀምበትና የታላቁ ሰማያዊ ንጉሥ የኢየሱስ ክርስቶስ ታዛዥ ተገዢ እንደሚሆን አያጠራጥርም።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዮሴፍ ለኢየሱስ መንፈሳዊ መመሪያ ሰጥቶታል እንዲሁም የአናጺነት ሙያም አስተምሮታል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ