ውሳኔ ለማድረግ ጊዜው አሁን የሆነው ለምንድን ነው?
በ16ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ አምላክ እስራኤላውያንን “ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት . . . የተቀደሰም ሕዝብ” አድርጎ መረጣቸው። (ዘጸአት 19:5, 6) ወዲያው በአካባቢያቸው የሚገኙ ሕዝቦች በሚፈጽሟቸው የጣዖት አምልኮና ምግባረ ብልሹ ልማዶች እንዲበከሉ በመፍቀድ ቅድስናቸውን ይኸውም ሃይማኖታዊ ንጽሕናቸውን አጡ። በዚህ መንገድ “አንገተ ደንዳና ሕዝብ” መሆናቸውን ራሳቸው አሳዩ። (ዘዳግም 9:6, 13፤ 10:16፤ 1 ቆሮንቶስ 10:7–11) ከኢያሱ ሞት ሦስት መቶ ዓመታት በኋላ ባሉት ጊዜያት እስራኤላውያንን ወደ እውነተኛው አምልኮ እንዲመልሱ ይሖዋ ታማኝ መሪዎች የሆኑ መሳፍንት አስነሣ። ነገር ግን ሕዝቡ “የእልከኝነታቸውን መንገድና ሥራቸውን አልተዉም ነበር።”—መሳፍንት 2:17–19
ከዚያም ወደ እውነተኛው አምልኮ እንዲመለሱ ሕዝቡን ለማነሳሳት አምላክ የታመኑ ነገሥታትንና ነቢያትን አስነሳላቸው። ነቢዩ ዓዛርያስ ንጉሥ አሳንና የሀገሩን ሰዎች “ብትፈልጉት ይገኝላችኋል ብትተዉት ግን ይተዋችኋል” በማለት ይሖዋን እንዲፈልጉ አበረታቷቸዋል። አሳ በይሁዳ መንግሥት ውስጥ ሃይማኖታዊ ተሃድሶ አከናውኗል። (2 ዜና መዋዕል 15:1–16) ከጊዜ በኋላም በነቢዩ ኢዩኤል አማካይነት አምላክ ጥሪውን አድሷል። (ኢዩኤል 2:12, 13) ከዚህ በኋላም ቢሆን የይሁዳ ነዋሪዎች ‘እግዚአብሔርን እንዲፈልጉ’ ሶፎንያስ አጥብቆ አሳስቧቸዋል። ወጣቱ ንጉሥ ኢዮስያስም ጣዖት አምልኮንና ምግባረ ብልሹነትን ለማስወገድ ባከናወነው የተሃድሶ ዘመቻ እንዲሁ አድርጓል።—ሶፎንያስ 2:3፤ 2 ዜና መዋዕል 34:3–7
ምንም እንኳ የንስሐ ዝንባሌ ቢያሳዩም የሕዝቡ ሃይማኖታዊ ሁኔታ ይበልጥ አሳሳቢ እየሆነ መጥቶ ነበር። (ኤርምያስ 2:13፤ 44:4, 5) ኤርምያስ በጣዖት አምልኮ የተበከለውን ሃይማኖታዊ ሥርዓት አውግዞ “በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን? በዚያን ጊዜ ክፋትን የለመዳችሁ እናንተ ደግሞ በጎ ለማድረግ ትችላላችሁ” በማለት ሊታደስ እንደማይችል አድርጎ ገልጿታል። (ኤርምያስ 13:23) በዚህም ምክንያት አምላክ በይሁዳ መንግሥት ላይ ከባድ ቅጣት አወረደ። ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሷ በ607 ከዘአበ ተደመሰሱና ከጥፋት የተረፉት ሰዎች 70 ዓመታት ወዳሳለፉበት ባቢሎን ለባርነት ተጋዙ።
ይህ ወቅት ሲያልፍ አምላክ ምሕረቱን አሳያቸው። ቀሪዎቹ ተመልሰው ቤተ መቅደሱን ያድሱ ዘንድ ንጉሥ ቂሮስ እስራኤላውያንን ነጻ እንዲያወጣ አምላክ አነሳሳው። ከዚህ ሁሉ ትምህርት ከመውሰድ ይልቅ አሁንም እንደገና ከእውነተኛው አምልኮ በመራቅ “ወደ እኔ ተመለሱ፣ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ” በማለት ይሖዋ አምላክ ጥሪውን መልሶ እንዲያቀርብ አድርገውታል።—ሚልክያስ 3:7
እስራኤል የተተወበት ምክንያት
እስራኤላውያን በኢየሱስ ዘመን የነበራቸው ሃይማኖታዊ ሁኔታ እንዴት ነበር? ግብዞቹ የሃይማኖት መሪዎች “ሰው ሠራሽ ወግና ሥርዓትን እንደ ሕግ” አድርገው የሚያስተምሩ ‘እውር መሪዎች’ ነበሩ። ‘በወጋቸው ምክንያት የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይተላለፉ ነበር።’ አምላክን ‘በከንፈራቸው’ ቢያከብሩም ልባቸው ግን ከእርሱ በጣም ርቋል። (ማቴዎስ 15:3, 4, 8, 9, 14 የ1980 ትርጉም) አሁንም በብሔር ደረጃ ንስሐ ለመግባት ሌላ አጋጣሚ ይሰጣቸዋልን? አይሰጣቸውም። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች።” በተጨማሪም እንዲህ ብሏል “ቤታችሁ” ማለትም በኢየሩሳሌም ያለው ቤተ መቅደስ “የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል።” (ማቴዎስ 21:43፤ 23:38) ስሕተታቸው በጣም ታላቅ ነበር። ጨቋኙን የሮማ ቄሣር ንጉሣቸው አድርገው በመምረጥ የኢየሱስን መሲሕነት አንቀበልም አሉና ገደሉት።—ማቴዎስ 27:25፤ ዮሐንስ 19:15
እስራኤላውያን ኢየሱስ አገልግሎቱን ያከናወነበት ወቅት የፍርድ ጊዜ መሆኑን ለመረዳት አልፈለጉም። ኢየሱስ ታማኝ ላልሆኑት የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች “የመጎብኘትሽን ዘመን አላወቅሽም” ብሏል።—ሉቃስ 19:44
በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት አምላክ ከሁሉም ነገድና ብሔር በሚመረጡ በመንፈስ የሚቀቡ የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የተገነባ አዲስ ብሔር ወይም ሕዝብ አቋቋመ። (ሥራ 10:34, 35፤ 15:14 የ1980 ትርጉም) የአይሁድ ሃይማኖታዊ ሥርዓት በመጨረሻ ይታደሳል የሚል ተስፋ ነበርን? የሮማው ሠራዊት በ70 እዘአ ኢየሩሳሌምን ዶግ አመድ በማድረግ መልሱን ሰጠ። አምላክ ያንን ሃይማኖታዊ ሥርዓት አንቅሮ ተፍቶት ነበር።—ሉቃስ 21:5, 6
የሕዝበ ክርስትና ታላቅ ክህደት
በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖችም “ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን” መሥርተው ነበር። (1 ጴጥሮስ 2:9፤ ገላትያ 6:16) ነገር ግን የመጀመሪያው የክርስቲያን ጉባኤም እንኳ ሃይማኖታዊ ንጽሕናውን ይዞ አልዘለቀም።
ቅዱሳን ጽሑፎች ታላቅ ክህደት ወይም ከእውነተኛው እምነት ማፈግፈግ እንደሚመጣ አስቀድመው ተናግረው ነበር። በኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ምሳሌያዊ እንክርዳድ ማለትም አስመሳይ ክርስቲያኖች ምሳሌያዊውን ስንዴ ወይም በአምላክ መንፈስ የተቀቡትን እውነተኛ ክርስቲያኖች ለማፈን ይሞክራሉ። ምሳሌው የአምላክ ቀንደኛ ጠላት ዲያብሎስ ያስፋፋው የሐሰት ክርስትና መዛመት “ሰዎቹ ሲተኙ” እንደሚጀምር ያመለክታል። ይህ የሆነው ከክርስቶስ ታማኝ ሐዋርያት ሞት በኋላ መንፈሳዊ እንቅልፍ በተጫጫናቸው ጊዜ ነበር። (ማቴዎስ 13:24–30, 36–43፤ 2 ተሰሎንቄ 2:6–8) አስቀድሞ በሐዋርያት እንደተነገረው አያሌ አስመሳይ ክርስቲያኖች ወደ መንጋው ሾልከው ገብተው ነበር። (ሥራ 20:29, 30፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:1–3፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:16–18፤ 2 ጴጥሮስ 2:1–3) ከሐዋርያት መካከል መጨረሻ የሞተው ዮሐንስ ነው። የሐዋርያት ዘመን ማክተሚያ የሆነው ‘የመጨረሻ ሰዓት’ እንደ ጀመረ ዮሐንስ በ98 እዘአ ገደማ ጽፎ ነበር።—1 ዮሐንስ 2:18, 19
የሃይማኖትና የፖለቲካዊ ኃይል ሕብረት በሮማው ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ ከጸደቀ በኋላ የሕዝበ ክርስትና መንፈሳዊ፣ መሠረተ ትምህርታዊና ሥነ ምግባራዊ ሁኔታ አሽቆለቆለ። አያሌ የታሪክ ሰዎች እንደሚስማሙት “በአራተኛው መቶ ዘመን የነበረው የቤተ ክርስቲያን ድል” በክርስቲያን ዓይን ሲታይ “ጥፋት” ነበር። ምክንያቱም ‘ሕዝበ ክርስትና ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃዋን አጥታለች’ በተጨማሪም “የማርያም አምልኮ” እና “ለቅዱሳን” አምልኮታዊ ክብር መስጠት እንዲሁም የሥላሴን ፅንሰ ሐሳብ የመሰሉ ብዙ ልማዶችንና ፍልስፍናዎችን ከአረማውያን ተቀብላለች።
ካገኘችው የሐሰት ድል በኋላ የሕዝበ ክርስትና ሁኔታ ተበላሸ። ኢንኩዜሽን የተባለው የካቶሊክ መናፍቃን ምንጠራ፣ የመስቀል ጦርነትና በካቶሊኮችና በፕሮቴስታንቶች መካከል የተደረጉ “ቅዱስ” ጦርነቶች ሳይጨመሩ፣ ድንጋጌዎች እንዲሁም በጳጳሳትና በጉባኤዎች የተሰጡ የመሠረተ ትምህርት ፍቺዎች ብቻ ሊታደስ የማይችል ሃይማኖታዊ ሥርዓት አስከትለዋል።
ዊሊያም ማንችስተር ኤ ወርልድ ሊት ኦንሊ ባይ ፋየር በተባለው መጽሐፋቸው “የአሥራ አምስተኛውና የአሥራ ስድስተኛው መቶ ዘመን ጳጳሳት የሮም ንጉሠ ነገሥታትን የመሰለ ኑሮ ነበራቸው። አሉ የተባሉ የዓለማችን ባለጠጎች የነበሩ ሲሆኑ እነርሱና ካርዲናሎቻቸው በቅዱሱ የጸሎት ሥነ ሥርዓት በመነገድ ራሳቸውን አበልጽገዋል” በማለት ጽፈዋል። በታላቁ ክህደት ወቅት አነስተኛ ቡድኖች ወይም አንዳንድ ግለሰቦች የምሳሌያዊውን ስንዴ ዓይነተኛ መለያ በማሳየት እውነተኛውን ክርስትና ለመመለስ ፈልገው ነበር። ለዚህም ብዙ ጊዜ የከፈሉት ዋጋ ቀላል አልነበረም። ይኸው መጽሐፍ እንዲህ አለ፦ “አንዳንዴም የክርስትና ማለትም የፕሮቴስታንትና የካቶሊክ እውነተኛ ቅዱሳን በሰማዕትነት ነደዋል።” ሌሎች እንደ ማርቲን ሉተርና ጆን ካልቪን ያሉ ተሃድሶ አራማጅ ተብዬዎች ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የተለየ ግን ዋነኛ መሠረታዊ ትምህርቶቹን የሚጋራ ዘላቂ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ፈጥረዋል። በፖለቲካ ጉዳዮችም ተውጠው ነበር።
በፕሮቴስታንቱ ዓለም ሃይማኖታዊ ማነቃቂያ የሚሉትን በሥራ ለማዋል ጥሮሽ ተደርጓል። ለምሳሌ ይህ ጥረት በ18ኛውና በ19ኛው መቶ ዘመን በሌሎች አገሮች ጠንካራ ሚስዮናዊ እንቅስቃሴ አስከትሎ ነበር። ነገር ግን ራሳቸው እረኞቹ እንደሚያምኑት የፕሮቴስታንት መንጋ ዛሬ ያለበት መንፈሳዊ ሁኔታ የሚያበረታታ አይደለም። ፕሮቴስታንቱ የሃይማኖት ምሁር ኦስካር ኩልማን “በራሳቸው በቤተ ክርስቲያኖቹ መካከል የእምነት መቃወስ” ያለ መሆኑን አምነው ተቀብለዋል።
በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተሃድሶዎችና ተሃድሶዎችን ለማጨናገፍ የሚወሰዱ እርምጃዎች ይካሄዱ ነበር። ከ11ኛው እስከ 13ኛው መቶ ዘመን ባሉት ጊዜያት ምግባረ ብልሹነትና የቀሳውስቱ ሀብት እየተስፋፋ ቢሄድም የድህነት መሃላውን በጥብቅ የሚከተል የመነኮሳት ማኅበር በዚያኑ ጊዜ ተቋቁሞ ነበር። የቅርብ ክትትል ይደረግባቸው ነበር፤ ምሁራን እንደሚሉትም በቤተ ክርስቲያን ባለ ሥልጣናት ይጨቆኑ ነበር። ከዚያም በ16ኛው መቶ ዘመን የፕሮቴስታንትን ተሃድሶ በመዋጋት ላይ ያነጣጠረ፣ ተሃድሶዎችን የሚያደናቅፍ እርምጃ በትሬንት ጉባኤ ተጠነሰሰ።
በ19ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አጋማሽ በቤተ ክርስቲያን ተሃድሶ ወቅት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሌሎች ላይ የመሠልጠንና የወግ አጥባቂነት አቋም ያዘች። እውነተኛውን ክርስትና መልሶ ለማምጣት ምንም ዓይነት ትክክለኛ ተሃድሶ ተደርጓል ማለት አይቻልም። ከዚህ ይልቅ በዓለም ላይ ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ለውጦች ስላሉ ቀሳውስቱ ሥልጣናቸውን ለማጠናከር ሲሉ ያደረጓቸው ጥረቶች ብቻ ናቸው።
በቅርቡ 1960ዎቹ ውስጥ በተደረገው አብያተ ክርስቲያናትን ባቀፈው ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ታላቅ ለውጥ ለመጀመር የፈለገች ይመስል ነበር። ነገር ግን የቤተ ክርስቲያኑን ተራማጅ አባላት መንፈስ ለመግታት በወቅቱ በነበሩት ጳጳስ አማካኝነት በጉባኤው በተላለፈው የተሃድሶ ውሳኔ ላይ ድንገተኛ እገዳ ተጣለ። አንዳንዶች የቮኢቲዋ ተሃድሶ ብለው የሚጠሩት ይህ አዲስ ምዕራፍ በአንድ የካቶሊክ ቡድን “የቆስጠንጢኖሳዊነት አዲስ መልክ” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። ላ ቺቪልታ ካቶሊካ የተባለው የኢየሱሳውያን መጽሔት ለይቶ እንደጠቀሰው እንደ ሌሎች ሃይማኖቶች ሁሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንም የተጋረጠባት ችግር “መሠረታዊና ዓለም አቀፋዊ ችግር ነው። መሠረታዊ የተባለው የእምነትንና የክርስትና ሕይወትን ሥረ መሠረት ስለሚነካ ሲሆን ዓለም አቀፋዊ የሆነው ደግሞ ሁሉንም የክርስትና ገጽታ ስለሚዳስስ ነው።”
እውነተኛው ክርስትና ተመልሶ የሚመጣው ምሳሌያዊው ስንዴ ወደ አንድ ንጹሕ ጉባኤ በሚሰባሰብበት “በመከሩ” ጊዜ ብቻ ስለሆነ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ተሃድሶ አላደረጉም፣ ሊያደርጉም አይችሉም። (ማቴዎስ 13:30, 39) ክርስቲያን ነን አሉም አላሉ በሃይማኖት ስም የተፈጸመው ረጅሙ የወንጀልና የእኩይ ተግባራት መዝገብ ከሕዝበ ክርስትና እውነተኛ ተሃድሶ መጠበቅ ትክክል ነውን? ብለን እንድንጠይቅ ይገፋፋናል።
ተሃድሶ የማይቻል ነውን?
የራእይ መጽሐፍ ወይም አፖካሊፕስ “ታላቂቱ ባቢሎን” የሚል ምሥጢራዊ ስም ስለያዘች ምሳሌያዊት ታላቅ ጋለሞታ ይናገራል። (ራእይ 17:1, 5) ለብዙ መቶ ዘመናት የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች ይህ የሚያመለክተውን ምሥጢር ለማብራራት ሞክረዋል። ብዙዎቹ በቀሳውስት ሀብትና ምግባረ ብልሹነት ተከፍተው ነበር። አንዳንዶች ታላቂቱ ባቢሎን የቤተ ክርስቲያንን ባለ ሥልጣናትን ትወክላለች ብለው አሰቡ። ከእነሱም መካከል በ1415 እዘአ ከነሕይወቱ የተቃጠለው የቦሒሚያው ካቶሊክ ካህን ያን ሁስ እና በ1570 ተሰቅሎ የተቃጠለው የጥንቱ ሰብዓዊ ባህል ይሻላል ብሎ ይሟገት የነበረው ኢጣሊያዊው ፈላስፋ አኦንዮ ፓሌሪዮ ይገኙበታል። ሁለቱም “ጥንት የነበራትን ማዕረግ” መልሳ ታገኛለች በሚል ተስፋ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ለማደስ ያለ ውጤት ደክመዋል።
ከዚህ በተቃራኒ የራእይ መጽሐፍ 17ኛውና 18ኛው ምዕራፍ “ታላቂቱ ባቢሎን” መላውን የሐሰት ሃይማኖቶች ዓለም አቀፍ ግዛት እንደምታመለክት ያሳያል።a ይህች ብዙ ሃይማኖቶችን አቅፋ የያዘች ‘ታላቂቱ ጋለሞታ’ ልትታደስ አትችልም ምክንያቱም ‘ኃጢአትዋ እስከ ሰማይ ደርሶአል።’ እንዲያውም በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ሕዝበ ክርስትና ብቻ ሳትሆን ሁሉም ሃይማኖቶች ብዙ ደም እያፈሰሱ ላሉት ጦርነቶችና የሰውን ዘር ላጥለቀለቀው የሥነ ምግባር ውድቀት ተጠያቂ ናቸው። በዚህ ምክንያት አምላክ “ባቢሎን” እንድትጠፋ ደንግጓል።—ራእይ 18:5, 8
‘ከእርስዋ ለመውጣት’ ጊዜው አሁን ነው
የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ እንደሚያሳየው ጊዜያችን ከዚህ ክፉ “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ጋር ይመሳሰላል። (ማቴዎስ 24:3 አዓት) አምላክን ከልብ ለማምለክ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው የራሱን አስተሳሰብና ምርጫ አይከተልም። በኢየሱስ አስቀድሞ የተነገረው “ታላቁ መከራ” በጣም ስለቀረበ አሁኑኑ ‘ይሖዋን በሚገኝበት ጊዜ መፈለግ’ አለበት። (ኢሳይያስ 55:6፤ ማቴዎስ 24:21) በእስራኤል ሕዝብ ላይ እንደደረሰው ሁሉ አምላክ አንድ ሃይማኖት በጥንታዊነቱ ምክንያት ስለሚኮራ ብቻ ምግባረ ብልሹ ሆኖ እንዲቀጥል አይፈቅድም። ከመስጠም የማይተርፈውን መርከብ ለመጠገን ደፋ ቀና ከማለት ይልቅ በአምላክ ፊት ተቀባይነትን ማግኘትንና መዳንን የሚፈልጉ ሁሉ በራእይ 18:4 ላይ በመንፈስ መሪነት የተሰጠውን “ሕዝቤ ሆይ፣ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ [ከታላቂቱ ባቢሎን] ዘንድ ውጡ” የሚለውን መመሪያ ዛሬ ነገ ሳይሉ መታዘዝ ይኖርባቸዋል።
ነገር ግን ‘ወጥቶ’ ወዴት ለመሄድ? መዳን ሌላ የት ይገኛል? ትክክለኛ ባልሆነ ስፍራ መጠለል አደጋ የለውምን? አምላክ የሚቀበለው ብቸኛ ሃይማኖት እንዴት ሊታወቅ ይችላል? እምነት የሚጣልባቸው ብቸኛ መልሶች ከአምላክ ቃል ሊገኙ ይችላሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ ጠለቅ ብለህ እንድትመረምረው ይጋብዙሃል። አምላክ እየቀረበ ካለው የቁጣው ቀን የሚጠብቃቸው ‘ለስሙ የሚሆን ሕዝብ’ አድርጎ የመረጣቸው እነማን እንደሆኑ በሚገባ ልትረዳ ትችላለህ።—ሥራ 15:14፤ ሶፎንያስ 2:3፤ ራእይ 16:14–16
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ምሳሌያዊቷን ታላቂቱ ባቢሎን ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ባለው ትክክለኛ መንገድ ለመለየት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በ1988 የታተመውን ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለውን መጽሐፍ ከምዕራፍ 33 እስከ 37 ተመልከት።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ያለህበት ሃይማኖታዊ መርከብ እየሰጠመ ከሆነ ሕይወት አድን ወደ ሆነው እውነተኛ የክርስትና መርከብ ፊትህን አዙር