የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 4/15 ገጽ 11-15
  • የዓለም ሃይማኖቶች የሚጠፉት ለምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የዓለም ሃይማኖቶች የሚጠፉት ለምንድን ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ታላቂቱ ባቢሎን የወደቀችው እንዴት ነው?
  • መምረጥ አለብህ
  • የሐሰት ሃይማኖት ተከሰሰ
  • የሐሰት ሃይማኖት የሚያንጸባርቀው የቃየን መንፈስ
  • “በጣም የሚያስገርም”
  • የሐሰት ሃይማኖት የሚጠፋበት ጊዜ ቀርቧል!
    የሐሰት ሃይማኖት የሚጠፋበት ጊዜ ቀርቧል!
  • አምላክ ሁሉንም ሃይማኖቶች ይቀበላል?
    ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን መንገድ አግኝተኸዋል?
  • የሐሰት ሃይማኖቶች የአምላክን ስም ያሰደቡት እንዴት ነው?
    ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
  • ማንኛውም ሃይማኖት ጥሩ ነውን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 4/15 ገጽ 11-15

የዓለም ሃይማኖቶች የሚጠፉት ለምንድን ነው?

“ሕዝቤ ሆይ፣ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ።”— ራእይ 18:4

1. (ሀ) ታላቂቱ ባቢሎን የወደቀችው በምን መንገድ ነው? (ለ) ይህ ሁኔታ የይሖዋ ምሥክሮችን የነካቸው እንዴት ነው?

“ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች!” አዎን፣ በይሖዋ መስፈርት መሠረት ዓለም አቀፍ የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ወድቃለች። ይህም የሆነው እዚህ ምድር ላይ የቀሩት የክርስቶስ ወንድሞች በሃይማኖታዊቷ ባቢሎን ውስጥ ጉልህ ስፍራ ካላት ከሕዝበ ክርስትና ተጽዕኖ ከተላቀቁበት ከ1919 ጀምሮ ነው። በዚህ የተነሳ እነዚህ የክርስቶስ ወንድሞች የሐሰት ሃይማኖትን ለማጋለጥና አምላክ በመሲሐዊው መንግሥት አማካኝነት የሚያመጣውን የጽድቅ አገዛዝ ለማወጅ ነፃነት አግኝተው ነበር። ባለንበት መቶ ዘመን የይሖዋ ታማኝ ምሥክሮች ሰይጣን ‘ዓለምን ለማሳት’ በመሣሪያነት የሚጠቀምባቸውን ጥርቅም ሃይማኖቶች አጋልጠዋል።—ራእይ 12:9፤ 14:8፤ 18:2

ታላቂቱ ባቢሎን የወደቀችው እንዴት ነው?

2. አሁን ያለው የዓለም ሃይማኖቶች ሁኔታ ምን ይመስላል?

2 ሆኖም አንድ ሰው ‘በብዙ አገሮች ውስጥ ሃይማኖት እንደ አሸን እየፈላ እናንተ እንዴት ባቢሎን ወደቀች ትላላችሁ?’ ብሎ ሊጠይቅ ይችላል። ካቶሊኮችና እስላሞች እያንዳንዳቸው አንድ ቢልዮን አማኞች እንዳሏቸው ይናገራሉ። በአሜሪካ አገሮች የፕሮቴስታንት እምነት አሁንም እየተስፋፋ ሲሆን በእነዚህ ቦታዎች ያለማቋረጥ አዳዲስ ቤተ ክርስቲያኖችና የጸሎት ቤቶች እየተከፈቱ ነው። በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በቡድሂዝምና በሂንዱኢዝም የአምልኮ ሥርዓቶች ይመራሉ። ሆኖም ይህ ሁሉ ሃይማኖት በሥሩ ባሉ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አኗኗር ላይ ምን ያህል ገንቢ ተጽዕኖ አሳድሯል? በሰሜን አየርላንድ ውስጥ ካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች እርስ በርስ እንዳይጨፋጨፉ አግዷልን? በመካከለኛው ምሥራቅ ለሚገኙ አይሁዶችና እስላሞች እውነተኛ ሰላም አምጥቷልን? ሕንድ ውስጥ የሚገኙትን ሂንዱዎችና እስላሞች ወደ ሰላም መርቷቸዋልን? በቅርቡ እንዳየነውስ ቢሆን የሰርብ ኦርቶዶክሶችን፣ የክሮኤሺያ ካቶሊኮችንና የቦስኒያ ሙስሊሞችን “ከጎሳዊ ምንጠራ፣” ከዝርፊያ፣ አስገድዶ ከመድፈርና እርስ በርስ ከመተራረድ እንዲታቀቡ አድርጓቸዋልን? ሃይማኖት ብዙውን ጊዜ እንዲሁ ለመለያ ብቻ የሚያገለግል ከላይ ሲያዩት ጠንካራ የሚመስል ነገር ግን ትንሽ ጫን ሲሉት እንደሚሰባበር የእንቁላል ቅርፊት ነው።—ገላትያ 5:19-21፤ ከያዕቆብ 2:10, 11 ጋር አወዳድር።

3. ሃይማኖት በአምላክ ፊት ለፍርድ የቀረበው ለምንድን ነው?

3 በአምላክ ቦታ ሆነን ብንመለከተው ሃይማኖት የብዙ ሰዎችን ድጋፍ ማግኘቱ ሁሉም ሃይማኖቶች በአምላክ ፊት ለፍርድ የመቅረባቸውን እውነታ አይለውጠውም። ታላቂቱ ባቢሎን ካስመዘገበችው ታሪክ ለመገንዘብ እንደሚቻለው ‘ኃጢአትዋ እስከ ሰማይ በመድረሱ እግዚአብሔር ዓመፃዋን ስላሰበ’ ሊፈረድባት ይገባል። (ራእይ 18:5) ሆሴዕ በትንቢታዊ አነጋገር “ነፋስን ዘርተዋል፣ ዐውሎ ነፋስንም ያጭዳሉ” በማለት ጽፏል። የሰይጣን ንብረት የሆኑት በዓለም ዙሪያ ያሉ የሐሰት ሃይማኖቶች በጠቅላላ አምላክን፣ እርሱ ያሳየውን ፍቅር፣ ስሙንና ልጁን ስለ ካዱ ዋጋቸውን ያገኛሉ።—ሆሴዕ 8:7፤ ገላትያ 6:7፤ 1 ዮሐንስ 2:22, 23

መምረጥ አለብህ

4, 5. (ሀ) በዛሬው ጊዜ የምንኖረው በምን ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ ነው? (ለ) ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ መስጠት አለብን?

4 የምንኖረው “በመጨረሻው ቀን” ማብቂያ ላይ ስለሆነ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ይህንን “የሚያስጨንቅ ዘመን” ለማለፍ እንታገላለን። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) እውነተኛ ክርስቲያኖች የሰይጣን ዓለም ጊዜያዊ ነዋሪዎች ናቸው። ይህ ዓለም የሰይጣንን ብልሹ ባሕርያት ማለትም ነፍሰ ገዳይነትን፣ ውሸትንና ስም አጥፊነትን ያንጸባርቃል። (ዮሐንስ 8:44፤ 1 ጴጥሮስ 2:11, 12፤ ራእይ 12:10) በዓመፅ፣ በአታላይነት፣ በአጭበርባሪነት፣ በሥነ ምግባር ንቅዘትና በጾታ ብልግና ተከበናል። መሠረታዊ ሥርዓቶች ችላ እየተባሉ ነው። በሕይወት ውስጥ ዋንኛው ነገር መደሰት ስለሆነ እንብላ እንጠጣ የሚሉት አባባሎች የጊዜያችን መለያ ሆነዋል። ከዚህም በተጨማሪ ቀሳውስት መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ የሚያወግዛቸውን ግብረ ሰዶምን፣ ዝሙትንና ምንዝርን እንደ ቀላል ነገር አድርገው በመመልከት የሥነ ምግባር ውስልትናን ይፈቅዳሉ። ስለዚህ አሁን የሚነሳው ጥያቄ የሐሰት ሃይማኖትን እየደገፍክ ነው ወይስ በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እያደረግህ? የሚል ነው።—ዘሌዋውያን 18:22፤ 20:13፤ ሮሜ 1:26, 27፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9-11

5 ሚናችንን የምንለይበት ጊዜ አሁን ነው። ስለዚህ በሐሰተኛውና በእውነተኛው አምልኮ መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ ያስፈልገናል። በሕዝበ ክርስትና ሥር ያሉ ሃይማኖቶችን ይበልጥ ተነቃፊ የሚያደርጋቸው ሌላ ምን ነገር ፈጽመዋል?—ሚልክያስ 3:18፤ ዮሐንስ 4:23, 24

የሐሰት ሃይማኖት ተከሰሰ

6. ሕዝበ ክርስትና የአምላክን መንግሥት ችላ ያለችው እንዴት ነው?

6 በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የአምላክ መንግሥት እንድትመጣ የሚጠይቀውን የጌታ ጸሎት ዘወትር ቢጸልዩም ይህንን ቲኦክራሲያዊ አገዛዝ ችላ እስኪሉ ድረስ ሁሉንም ዓይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በመደገፍ ተወጥረዋል። በመቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት እንደ ካርዲናል ሪሸሎ፣ ማዛሪን እና ዎልሲ የመሳሰሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን “መሳፍንት” የፖለቲካ ሰው በመሆን ምድራዊ መንግሥት አገልግለዋል።

7. የይሖዋ ምሥክሮች ከ50 ዓመት በፊት የሕዝበ ክርስትናን ቀሳውስት ያጋለጡት እንዴት ነው?

7 የይሖዋ ምሥክሮች ከ50 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ሪሊጅን ሪይፕስ ዘ ወርልዊንድ በተባለው ብሮሹር ውስጥ ሕዝበ ክርስትና በፖለቲካ ውስጥ የምታደርገውን ተሳትፎ አጋልጠዋል።a በዚያን ጊዜ የተነገረው የሚከተለው አባባል በአሁኑ ጊዜም ቢሆን የዚያኑ ያህል ኃይል አለው፦ “በየትኛውም ሃይማኖት ውስጥ ያሉት ሃይማኖታዊ ቀሳውስት ጠባይ በሐቀኝነት ብንመረምር ‘የሕዝበ ክርስትና’ ሃይማኖታዊ መሪዎች በጠቅላላ ‘በዚህ ክፉ ዓለም’ ፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውንና ቀስ በቀስ በዓለማዊ ጉዳዮች ውስጥ መጠላለፋቸውን ያሳያል።” ከዚያን ጊዜ ወዲህ ምሥክሮቹ ፖፕ ፒየስ 12ኛ ከናዚ ሂትለር (1933) እና ከፋሺስቱ ፍራንኮ (1941) ጋር ያደረጉትን ስምምነት እንዲሁም መጋቢት 1942 ማለትም ጃፓን በፐርል ሃርበር ላይ አሰቃቂ ጥቃት ከሰነዘረች ከጥቂት ወራት በኋላ ከዚህች ጠብ አጫሪ አገር ጋር ዲፕሎማሲያዊ ወኪሎች መለዋወጣቸውን ክፉኛ ተችተዋል። ጳጳሱ “አመንዝሮች ሆይ፣ ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል” በማለት ያዕቆብ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ አልተከተሉም።—ያዕቆብ 4:4

8. የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በዛሬው ጊዜ በፖለቲካ ውስጥ እየተሳተፈች ያለችው እንዴት ነው?

8 በዛሬው ጊዜ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል? መንበረ ጵጵስናው አሁንም ቢሆን በቀሳውስቱና በምእመናን ወኪሎቹ አማካኝነት ፖለቲካ ውስጥ ይገባል። በቅርብ የነገሡት ጳጳሳት የተባበሩት መንግሥታት ለዓለም ሰላም ለማምጣት የተቋቋመ ሰው ሠራሽ ድርጅት እንደሆነ በመናገር እውቅና ሰጥተውታል። ሎሴርቫቶሬ ሮማኖ የተባለው የቫቲካን ነጋሪት ጋዜጣ በቅርቡ ባወጣው እትሙ ላይ “የጳጳሱ መቀመጫ በሆነችው ከተማ የተሾሙ” ሰባት አዳዲስ አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤያቸውን “ለአቡኑ” እንዳቀረቡ ገልጿል። ኢየሱስና ጴጥሮስ አሁን ቢኖሩ በእንዲህ ዓይነቱ ዲፕሎማሲያዊ ልውውጥ ውስጥ ይገቡ ነበር ብለን መገመት እንችላለንን? ኢየሱስ አይሁዳውያን ሊያነግሡት በፈለጉ ጊዜ እምቢ ከማለቱም በተጨማሪ መንግሥቱ ከዚህ ዓለም እንዳልሆነ ተናግሯል።—ዮሐንስ 6:15፤ 18:36

9. የፕሮቴስታንት ሃይማኖቶች ከካቶሊክ አቻዎቻቸው አይሻሉም የምንለው ለምንድን ነው?

9 የፕሮቴስታንት መሪዎች ከካቶሊክ አቻዎቻቸው የተሻሉ ናቸውን? በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብዙዎቹ ወግ አጥባቂ የፕሮቴስታንት ሃይማኖቶችና ሞርሞኖች የተወሰኑ የፖለቲካ ቡድኖችን ይደግፋሉ። ክርስቺያን ኮዋሊሽን የተባለው ድርጅት በዩናይትድ ስቴትስ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ ያደርጋል። ሌሎች የፕሮቴስታንት ቀሳውስት የተለያዩ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን በግልጽ ይደግፋሉ። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኙት እንደ ፓት ሮበርትሰን እና ጄሲ ጃክሰን እንዲሁም የእንግሊዝ ፓርላማ አባል እንደሆኑት የሰሜን አየርላንዱ ኢያን ፒዝሊ ያሉት ፖለቲከኞች የሃይማኖት ሰዎች እንደሆኑ ወይም እንደነበሩ አንዳንድ ጊዜ ይዘነጋል። እነዚህ ሰዎች ያላቸውን አቋም እንዴት አድርገው ይገልጹት ይሆን?—ሥራ 10:34, 35፤ ገላትያ 2:6

10. በ1944 ምን የማያሻማ መግለጫ ተሰጥቷል?

10 ሪሊጅን ሪይፕስ ዘ ወርልዊንድ የተባለው ብሮሹር በ1944 እንደሚከተለው በማለት ያቀረበውን ጥያቄ ዛሬም እኛ እንጠይቃለን፦ “አንድ ድርጅት ጥቅም ለማግኘትና ከዚህ ዓለም ለመከለል ብሎ ከምድራዊ መንግሥታት ጋር እየተዋዋለና በዚህ ዓለም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ራሱን እያጠላለፈ . . . የአምላክ ቤተ ክርስቲያን ወይም የኢየሱስ ክርስቶስ ምድራዊ ወኪል ሊሆን ይችላልን? . . . ከዚህ ዓለም መንግሥታት ጋር ተመሳሳይ ግብ ያላቸው ሃይማኖተኞች በጠቅላላ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራውን የአምላክ መንግሥት አይወክሉም።”

የሐሰት ሃይማኖት የሚያንጸባርቀው የቃየን መንፈስ

11. የሐሰት ሃይማኖት የቃየንን ምሳሌ የተከተለው እንዴት ነው?

11 የሐሰት ሃይማኖት በሰው ዘር ታሪክ በሙሉ ወንድሙን አቤልን የገደለው ቃየን ያሳየውን መንፈስ ሲያንጸባርቅ ቆይቷል። “የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ የተገለጡ ናቸው፤ ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም። ከመጀመሪያ የሰማችኋት መልእክት፦ እርስ በርሳችን እንዋደድ የምትል ይህች ናትና፤ ከክፉው እንደ ነበረ ወንድሙንም እንደ ገደለ እንደ ቃየል አይደለም፤ ስለ ምንስ ገደለው? የገዛ ሥራው ክፉ፣ የወንድሙም ሥራ ጽድቅ ስለ ነበረ ነው።” የወንድሙ ንጹሕና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አምልኮ ያናደደው ቃየን በወንድሙ ላይ የኃይል እርምጃ ወሰደበት። ይህም ለሚያደርጉት ነገር ምክንያት ማቅረብ የማይችሉ ሰዎች የሚወስዱት የመጨረሻ እርምጃ ነው።—1 ዮሐንስ 3:10-12

12. ሃይማኖት በጦርነቶችና በግጭቶች ውስጥ ጣልቃ እንደገባ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

12 በሐሰት ሃይማኖት ላይ የቀረበው ይህ ክስ እውነት መሆኑን ያሉት እውነታዎች ያረጋግጣሉን? አንድ ደራሲ ፕሪቸርስ ፕሬዘንት አርምስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “በሥልጣኔ ታሪክ ውስጥ . . . ሁለት ኃይሎች ሁልጊዜ ተባብረውና ተቀናጅተው እናገኛለን። እነዚህ ኃይሎች ጦርነትና ሃይማኖት ናቸው። በዓለማችን ላይ ካሉት ታላላቅ ሃይማኖቶች ውስጥ . . . [የሕዝበ ክርስትናን] ያህል ራሱን [ለጦርነት] ያሰለፈ ሃይማኖት የለም።” ከጥቂት ዓመታት በፊት ዘ ሰን የተባለ የቫንኩቨር ካናዳ ጋዜጣ “ቤተ ክርስቲያን የባንዲራ ተከታይ መሆኗ የሁሉም የተደራጁ ሃይማኖቶች ደካማ ጎን ሳይሆን አይቀርም . . . አምላክ በሁለቱም ተቃራኒ ጎራዎች ጎን እንደተሰለፈ ያልተነገረበት ጦርነት አለን?” ብሏል። የዚህን እውነተኝነት በአካባቢህ በሚገኙ አንዳንድ ቤተ ክርስቲያኖች ውስጥ ተመልክተህ ሊሆን ይችላል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ የአምልኮ ሥርዓት የሚፈጸምባቸውን ቦታዎች በብሔራዊ ባንዲራ እንዲያሸበርቁ ማድረግ የተለመደ ነው። ኢየሱስ የትኛውን ባንዲራ አንግቦ ይዘምት ነበር ብለህ ታስባለህ? “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም” የሚሉት የኢየሱስ ቃላት ባለፉት መቶ ዘመናት በሙሉ ሲያስተጋቡ ቆይተዋል!—ዮሐንስ 18:36

13. (ሀ) የሐሰት ሃይማኖት አፍሪካ ውስጥ ያልተሳካለት እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ የሰጠው የክርስትና መለያ ምልክት ምንድን ነው?

13 በሕዝበ ክርስትና ሥር ያሉ ሃይማኖቶች ስለ እውነተኛው የወንድማማች ፍቅር የሚናገረውን እውነት ለመንጎቻቸው አላስተማሩም። ከዚህ ይልቅ አባሎቻቸው በብሔር፣ በጎሣና በዘር እንዲከፋፈሉ አድርገዋል። የካቶሊክና የአንግሊካን ቀሳውስት በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ባስከተለው ክፍፍል ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ የተለያዩ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንዲህ በማለት ሪፖርት አድርጓል፦ “በሩዋንዳ ይኖሩ የነበሩ ብዙ የሮማ ካቶሊኮች በዚህች አገር በተፈጸመው እልቂት ምክንያት የቤተ ክርስቲያን ባለሥልጣኖች ፈጽሞ እንደጣሏቸው ተሰምቷቸዋል። ቤተ ክርስቲያኒቱ በሁቱና በቱትሲ ጎሣዎች የተከፈለች ናት።” ይኸው ጋዜጣ አንድ የሜሪኖል ቄስ የተናገሩትን ነገር እንዲህ በማለት ጠቅሷል፦ “በ1994 ቤተ ክርስቲያኗ በሩዋንዳ ከባድ ውድቀት ደርሶባታል። አብዛኞቹ ሩዋንዳውያን ቤተ ክርስቲያኗን ችላ እያሏት ነው። ተሰሚነት አጥታለች።” ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” በማለት ከተናገረው ምንኛ የተለየ ነው።—ዮሐንስ 13:35

14. ክርስቲያን ያልሆኑ ዋና ዋና ሃይማኖቶች ምን ታሪክ አስመዝግበዋል?

14 በታላቂቱ ባቢሎን ሥር ያሉ ሌሎቹ ታላላቅ ሃይማኖቶችም ቢሆኑ በጥሩነታቸው የሚጠቀሱ አይደሉም። በ1947 ሕንድ ስትከፈል የደረሰው አሳዛኝ እልቂት እዚያ ያሉት ዋና ዋና ሃይማኖቶች እርስ በርስ የመቻቻልን ባሕርይ እንዳላፈሩ ያሳያል። ከዚያም በኋላ ሕንድ ውስጥ የቀጠለው ዓመፅ አብዛኛው ሰው እንዳልተለወጠ ያረጋግጣል። ኢንዲያ ቱዴይ የተባለው መጽሔት እንደሚከተለው በማለት መደምደሙ አያስደንቅም፦ “ሃይማኖት ከሁሉ የከፋ ዓመፅ የሚፈጸምበት ቡድን ነው። . . . ሃይማኖት ይህ ነው የማይባል ዓመፅ ከማስከተሉም በተጨማሪ በጣም ጎጂ ነው።”

“በጣም የሚያስገርም”

15. በምዕራቡ ዓለም ሃይማኖት በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ይገኛል?

15 ሃይማኖታዊ ያልሆኑ ተንታኞች እንኳ ሃይማኖት ሌሎችን ማሳመን፣ ትክክለኛውን ሥነ ምግባር ማስተማርና ሰዎች በዓለማዊ አስተሳሰብ እንዳይዋጡ ማድረግ እንዳልቻለ ተገንዝበዋል። የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የጸጥታ አማካሪ ዙቢግኔፍ ብሬዢንስኪ አውት ኦቭ ኮንትሮል በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “‘አምላክ በድን ነው’ የሚለው አመለካከት ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘው ማርክሲዝም በሰፈነባቸው አገሮች ሳይሆን . . . በባህላቸው ሥነ ምግባራዊ ግዴለሽነት በሚያጠቃቸው ብዙ አመለካከቶችን አቅፈው በያዙ ዲሞክራሲያዊ በሆኑ ምዕራባውያን አገሮች መሆኑ በጣም የሚያስገርም ነው። በምዕራባውያን ዘንድ ሃይማኖት በማኅበረሰቡ ላይ ብዙም ተጽዕኖ የለውም።” በመቀጠልም “አውሮፓ ውስጥ ሃይማኖተኛነት እየቀነሰ ሲሆን በዛሬው ጊዜ የአውሮፓ ሕዝብ ከአሜሪካ ሕዝብ ይልቅ ዓለማዊ ኅብረተሰብ ሆኗል” ብለዋል።

16, 17. (ሀ) ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን የሃይማኖት መሪዎች በተመለከተ ምን ምክር ሰጥቷል? (ለ) ኢየሱስ ፍሬን በተመለከተ የትኛውን ግሩም መሠረታዊ ሥርዓት ገልጿል?

16 ኢየሱስ በጊዜው ስለነበሩት የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ምን ብሎ ነበር? “ጻፎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋል [ቶራህን ማለትም ሕጉን ለማስተማር።] ስለዚህ ያዘዙአችሁን ሁሉ አድርጉ ጠብቁትም፣ ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ።” አዎን፣ ሃይማኖታዊ ግብዝነት አዲስ ነገር አይደለም።—ማቴዎስ 23:2, 3

17 የሐሰት ሃይማኖት በጣም መጥፎ መሆኑን ራሱ ያፈራው ፍሬ ያሳያል። ኢየሱስ እንዲህ በማለት የተናገረው መሠረታዊ ሥርዓት ለዚህ ተስማሚ ነው፦ “እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፣ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል። መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት፣ ወይም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ማፍራት አይቻለውም። መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። ስለዚህም ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።”—ማቴዎስ 7:17-20

18. ሕዝበ ክርስትና ራሷን ለማጽዳት ምን እርምጃ መውሰድ ነበረባት?

18 በሕዝበ ክርስትና ሥር ያሉ ሃይማኖቶች አባሎቻቸው እንደሆኑ የሚናገሩ ሰዎች መጥፎ ነገር ሲፈጽሙ በማስወገድ ወይም በማግለል በሁሉም ላይ ክርስቲያናዊ እርምጃ ቢወስዱባቸው ኖሮ ምን ይፈጠር ነበር? ንስሐ የማይገቡ ውሸተኞች፣ ዝሙት ፈጻሚዎች፣ አመንዝራዎች፣ ሰዶማውያን፣ አታላዮች፣ ወንጀለኞች፣ ዕፅ አዘዋዋሪዎችና የዕፅ ሱሰኞች እንዲሁም የቀማኞች ቡድን አባላት ምን ይሆኑ ነበር? ሕዝበ ክርስትና ያፈራችው መጥፎ ፍሬ አምላክ እንዲያጠፋት ራሷን ከማዘጋጀት ሌላ ምንም አላደረገላትም።—1 ቆሮንቶስ 5:9-13፤ 2 ዮሐንስ 10, 11

19. ሃይማኖታዊ መሪዎችን በተመለከተ ተቀባይነት ያገኘው ነገር ምንድን ነው?

19 በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የፕሪስቢቴሪያን ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ጉባኤ የሚከተለውን አምኗል፦ “በመጠኑም ሆነ በዓይነቱ በጣም ከፍተኛ የሆነ ቀውስ ከፊታችን ተደቅኗል። . . . በዚህች አገር ከሚኖሩ ቀሳውስት መካከል ከ10 እስከ 23 በመቶ የሚደርሱት በሰበካቸው ሥር ካሉ አባሎች፣ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ሊፈጽሙ ከሚሄዱ ሰዎች፣ ከሠራተኞች ወዘተ ጋር ተዳርተዋል አሊያም የጾታ ግንኙነት ፈጽመዋል።” አንድ አሜሪካዊ ነጋዴ “ሃይማኖታዊ ተቋሞች ታሪካዊ እሴቶቻቸውን ማስተላለፍ የተሳናቸው ከመሆኑም በላይ አብዛኛውን ጊዜ እነርሱ ራሳቸው የሥነ ምግባር ችግሩ ክፍል ሆነዋል” በማለት ነጥቡን ጠቅለል አድርገው በጥሩ ሁኔታ ገልጸውታል።

20, 21. (ሀ) ኢየሱስና ጳውሎስ ግብዝነትን ያወገዙት እንዴት ነው? (ለ) የትኞቹ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል?

20 ኢየሱስ ሃይማኖታዊ ግብዝነትን ሲያወግዝ እንደሚከተለው በማለት የተናገረው ነገር እርሱ በምድር ላይ በነበረበት ዘመን ይሠራ እንደነበረ ሁሉ በዘመናችንም ይሠራል፦ “እናንተ ግብዞች፣ ኢሳይያስ ስለ እናንተ፦ ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፣ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ብሎ በእውነት ትንቢት ተናገረ።” (ማቴዎስ 15:7-9) በተጨማሪም ጳውሎስ ለቲቶ እንደሚከተለው በማለት የጻፈለት መልእክት በዘመናችን ያለውን ሁኔታ ይገልጻል፦ “እግዚአብሔርን እንዲያውቁ በግልጥ ይናገራሉ፣ ዳሩ ግን የሚያስጸይፉና የማይታዘዙ ለበጎ ሥራም ሁሉ የማይበቁ ስለ ሆኑ፣ በሥራቸው ይክዱታል።”—ቲቶ 1:16

21 ኢየሱስ ዕውርን የሚመራው ዕውር ከሆነ ሁለቱም ጉድጓድ ውስጥ እንደሚገቡ ተናግሯል። (ማቴዎስ 15:14) ከታላቂቱ ባቢሎን ጋር መጥፋት ትፈልጋለህን? ወይስ ዓይኖችህን ገልጠህ የይሖዋን በረከት እያገኘህ ቀና በሆነ መንገድ ላይ መጓዝ ትፈልጋለህ? አሁን ከፊታችን የሚደቀኑት ጥያቄዎች የሚከተሉት ናቸው፦ አምላካዊ ፍሬ የሚያፈራው የትኛው ሃይማኖት ነው? በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን እውነተኛ አምልኮ እንዴት ለይተን ማወቅ እንችላለን?—መዝሙር 119:105

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በ1944 የታተመ ብሮሹር ሲሆን በአሁኑ ጊዜ መታተም አቁሟል።

ታስታውሳለህን?

◻ ታላቂቱ ባቢሎን በአሁኑ ጊዜ በአምላክ ፊት ያላት አቋም ምንድን ነው?

◻ የሐሰት ሃይማኖት የተከሰሰው በምን መሠረት ነው?

◻ የሐሰት ሃይማኖት የቃየንን መንፈስ ያንጸባረቀው እንዴት ነው?

◻ ኢየሱስ ማንኛውንም ሃይማኖት ለመገምገም የሚያስችል ምን መሠረታዊ ሥርዓት ሰጥቷል?

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በታሪክ ዘመናት ሁሉ ሃይማኖታዊ መሪዎች እጃቸውን ፖለቲካ ውስጥ ሲያስገቡ ቆይተዋል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

እነዚህ ሰዎች የሃይማኖት መሪዎች ከመሆናቸውም በተጨማሪ ከፍተኛ የፖለቲካ ሰዎች ነበሩ

ካርዲናል ማዛሪን

ካርዲናል ሪሸሎ

ካርዲናል ዎልሲ

[ምንጭ]

ካርዲናል ማዛሪን እና ካርዲናል ሪሸሎ፦ From the book Ridpath’s History of the World (Vol. VI and Vol. V respectively). ካርዲናል ዎልሲ፦ From the book The History of Protestantism (Vol. I).

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ