የሃይማኖት ምሁራንን ግራ ያጋባ ጉዳይ
“ነፍስ አትሞትም የሚለው አመለካከትና በሙታን ትንሣኤ ማመን . . . የግድ ከሁለቱ አንዱን መምረጥን የሚጠይቁ ጨርሶ የማይገናኙ ሁለት ጽንሰ ሐሳቦች ናቸው።” እነዚህ የፊሊፕ ሜኑ ቃላት የፕሮቴስታንትና የካቶሊክ የሃይማኖት ምሁራን የሙታንን ሁኔታ በተመለከተ ያጋጠማቸውን ግራ መጋባት በአጭሩ ይገልጻሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “በመጨረሻው ቀን” ስለሚፈጸመው የትንሣኤ ተስፋ ይናገራል። (ዮሐንስ 6:39, 40, 44, 54) ይሁን እንጂ ኪስበርት ክሪሻጌ የተባሉ የሃይማኖት ምሁር ስለ አብዛኞቹ ምእመናን ተስፋ ሲናገሩ “ተስፋቸው የተመሠረተው ሰው ሲሞት ከሥጋው ተለይታ ወደ አምላክ ትመለሳለች፤ ማለትም ነፍስ አትሞትም በሚለው እምነት ላይ ሲሆን የትንሣኤ ተስፋ ግን በአብዛኛው ጠፍቷል” ብለዋል።
በርናርድ ሴቡዋ በዚህ ረገድ “ሙታን በሥጋ ሲሞቱና በመጨረሻው ትንሣኤ እስኪያገኙ ድረስ ‘ባለው ጊዜ’ ውስጥ በምን ሁኔታ ይገኛሉ?” የሚል አስቸጋሪ ጥያቄ እንደሚነሣ ገልጸዋል። ይህ ጥያቄ ላለፉት ጥቂት ዓመታት የሃይማኖት ምሁራንን ሲያከራክር የቆየ ይመስላል። ወደዚህ ሁኔታ የመራው ምንድን ነው? ከዚህ ይበልጥ ደግሞ የሙታን እውነተኛ ተስፋ ምንድን ነው?
ግራ የሚያጋባው ጉዳይ አመጣጥና እድገት
የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ስለ ጉዳዩ ትክክለኛ መረዳት ነበራቸው። የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች “ሕያውን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ . . . አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙም” ስለሚሉ ሙታን ምንም የማይሰማቸው በድን መሆናቸውን ከቅዱሳን ጽሑፎች ተረድተዋል። (መክብብ 9:5, 10) እነዚህ ክርስቲያኖች “በጌታ መገኘት” ወቅት ትንሣኤ እንደሚኖር ተስፋ ያደርጉ ነበር። (1 ተሰሎንቄ 4:13–17 አዓት) ይህን ጊዜ እየተጠባበቁ የሆነ ቦታ ሕያው ሆነው እንደሚኖሩ ተስፋ አላደረጉም። በአሁኑ ወቅት የቫቲካን ጉባኤ ሰብሰቢ የሆኑት ዮዜፍ ራቲሲንገር ስለዚህ መሠረተ ትምህርት ሲናገሩ “የጥንት ቤተ ክርስቲያን በነፍስ አለመሞት እንደምታምን የሚያረጋግጥ አንድም መሠረተ ትምህርታዊ ድጋፍ የለም” ብለዋል።
ሆኖም ኖቮ ዲሲዮናሪዮ ዲ ቲኦሎዢያ የተባለው መጽሐፍ እንደ አውጉስቲን ወይም አምብሮስ ያሉት የቤተ ክርስቲያን አባቶች የጻፏቸውን ጽሑፎች ስናነብ “መጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነቶችን በተመለከተ አንድ አዲስ ነገር እንረዳለን፤ ይህ ነገር ከአይሁድ ክርስቲያኖች እምነት ጋር መሠረታዊ ልዩነት ያለው ስለ ሰው የመጨረሻ ዕጣ የሚናገረው ኢስካቶሎጂ የተባለው የግሪክ ትምህርት ብቅ ማለት ነው።” ይህ አዲስ ትምህርት የተመሠረተው “በነፍስ አለመሞትና ግለሰቦች ወዲያው እንደሞቱ የሚያገኙት ሽልማት ወይም ቅጣት በተናጥል ይፈረድባቸዋል” በሚል እምነት ላይ ነው። ስለዚህም “በሞትና በትንሣኤ መካከል ያለ ሁኔታ” ስለሚባለው ነገር የሚነሣው ጥያቄ ሥጋ ከሞተ በኋላ ነፍስ መኖሩዋን የምትቀጥል ከሆነ እስከ “መጨረሻው ቀን” ትንሣኤ ድረስ ስትጠባበቅ በመካከሉ ምን ይደርስባታል? የሚል ነው። የሃይማኖት ምሁራንን ግራ ያጋባቸው ነገር ይህ ነው።
በስድስተኛው መቶ ዘመን እዘአ ይኖሩ የነበሩት ጳጳስ ግሪጎሪ አንደኛ ሰዎች ሲሞቱ ነፍሶቻቸው ወዲያውኑ ወደ ተወሰነላቸው ቦታ ይሄዳሉ በማለት ተከራክረው ነበር። በ14ኛው መቶ ዘመን እዘአ ይኖሩ የነበሩት ጳጳስ ዮሐንስ 22ኛ ሙታን በፍርድ ቀን የመጨረሻ ዋጋቸውን እንደሚቀበሉ ያምኑ ነበር። ሆኖም ጳጳስ ቤንዲክት 12ኛ በፊት በቦታቸው የነበሩትን ሰው ሐሳብ አልተቀበሉም። ቤንዲክተስ ድየስ (1336) በተባለው በጳጳስነታቸው በጻፉት ጽሑፍ ላይ “የሙታን ነፍሳት ወዲያውኑ እንደሞቱ ወደ ተድላና ደስታ [ሰማይ]፣ መንጻት [መንጽሔ] ወይም ኩነኔ [ሲኦል] ይገባሉ፤ በትንሣኤ ከሚነሣው ሥጋቸው ጋር የሚደባለቁት በዓለም መጨረሻ ወቅት ብቻ ነው” ብለዋል።
ምንም እንኳ ነገሩ አወዛጋቢና አከራካሪ የሆነና የፕሮቴስታንትና የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያነት በመንጽሔ የማያምኑ ቢሆንም ይህ ነገር ለብዙ መቶ ዘመናት የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት አቋም ሆኖ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ካለፈው መቶ ዓመት ማብቂያ ጀምሮ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ምሁራን ነፍስ አትሞትም የሚለው እምነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ እንደሌለው ለሕዝብ በማሳወቃቸው ምክንያት “በአሁኑ ወቅት ዘመናዊው ሃይማኖታዊ ትምህርት ሰውን በሞት ጊዜ ጨርሶ የሚወገድ አንድ አካል አድርጎ ይመለከተዋል።” (ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪሊጅን) ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች “በሞትና በትንሣኤ መካከል የመሸጋገሪያ ሁኔታ” እንዳለ የሚያሳምን በቂ ምክንያት ለማቅረብ ተቸግረዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ነገር ይናገራል ወይስ ከዚህ የተለየ ተስፋ ይሰጣል?
ጳውሎስ “በሞትና በትንሣኤ መካከል ባለ የመሸጋገሪያ ሁኔታ” ያምን ነበርን?
ካቴኪዝም ኦቭ ዘ ካቶሊክ ቸርች የተባለው ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦ “ከክርስቶስ ጋር ለመነሣት ከክርስቶስ ጋር መሞት አለብን፤ ማለትም ‘ከሥጋ መለየትና ከጌታ ጋር መሆን አለብን።’ [2 ቆሮንቶስ 5:8] በዚህ ‘መለየት’ ማለትም ሞት ነፍስ ከሥጋ ትለያለች። [ፊልጵስዩስ 1:23] በሙታን ትንሣኤ ወቅት ነፍስ ከሥጋ ጋር እንደገና ትዋሃዳለች።” ይሁን እንጂ እዚህ ላይ በተጠቀሱት ጥቅሶች ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ነፍስ ሥጋ ሲሞት ሳትሞት ከሥጋ ጋር ለመዋሃድ “የመጨረሻውን ፍርድ” ትጠባበቃለች ብሏልን?
በ2 ቆሮንቶስ 5:1 ላይ ጳውሎስ ስለ ሞቱ ጠቀሰና ስለ አንድ ‘ምድራዊ መኖሪያ’ ‘መፍረስ’ ተናገረ። የማትሞት ነፍሱ ስለ ተለየችው ሥጋ መናገሩ ነበርን? አልነበረም። ጳውሎስ ሰው ራሱ ነፍስ እንደሆነ እንጂ ነፍስ እንዳለው አያምንም ነበር። (ዘፍጥረት 2:7 አዓት ፤ 1 ቆሮንቶስ 15:45) ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ተስፋቸው ‘በሰማይ እንደ ተዘጋጀላቸው’ ወንድሞቹ ሁሉ በመንፈስ የተቀባ ክርስቲያን ነበር። (ቆላስይስ 1:5፤ ሮሜ 8:14–18) ስለዚህ ‘ልባዊ ፍላጎቱ’ አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ የማይሞት መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ በሰማይ ለመኖር መነሣት ነበር። (2 ቆሮንቶስ 5:2–4) ስለዚህ ተስፋ ሲናገር “የኋለኛው መለከት ሲነፋ . . . እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን” ሲል ጽፏል።—1 ቆሮንቶስ 15:51, 52፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።
ጳውሎስ በ2 ቆሮንቶስ 5:8 ላይ “ከሥጋ ተለይተን በስደት መኖር በጌታም ዘንድ ማደር ደስ ይለናል” ብሏል። አንዳንዶች እነዚህ ቃላት በሞትና በትንሣኤ መካከል ያለውን ነፍሳት እየተጠባበቁ የሚያሳልፉትን ሁኔታ እንደሚያመለክቱ ያምናሉ። በተጨማሪም እንደዚህ ያሉት ሰዎች ኢየሱስ ‘ከእርሱ ጋር እንዲኖሩ’ ስፍራ ሊያዘጋጅላቸው እንደሚሄድ ለታማኝ ተከታዮቹ የገባላቸውን ተስፋ ይጠቅሳሉ። ይሁን እንጂ ይህ ተስፋ የሚፈጸመው መቼ ነው? ክርስቶስ ተስፋው የሚፈጸመው ‘እንደገና በሚመጣበት’ ጊዜ እንደሆነ ተናግሯል። (ዮሐንስ 14:1–3) በተመሳሳይም ጳውሎስ በ2 ቆሮንቶስ 5:1–10 ላይ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ያላቸው የጋራ ተስፋ ሰማያዊ መኖሪያን መውረስ እንደሆነ ተናግሯል። ይህ የሚፈጸመው ነፍስ ስለማትሞት ሳይሆን በክርስቶስ መገኘት ወቅት በሚፈጸም ትንሣኤ ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:23, 42–44) የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኝ የሆኑት ሻርል ማሶን 2 ቆሮንቶስ 5:1–10 “‘በሞትና በትንሣኤ መካከል ስላለ ሁኔታ’ እንደማይናገር በደንብ መረዳት ይቻላል” ሲሉ ደምድመዋል።
ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 1:21, 23 ላይ እንደ 1980 ትርጉም “ለእኔ ሕይወት ማለት፣ በክርስቶስ መኖር ነው፤ ሞትም ማለት፣ ጥቅም የሚገኝበት ነገር ነው። በእነዚህ በሁለቱ አሳቦች መካከል ተይዣለሁ፤ በአንድ በኩል ከዚህ ሕይወት ተለይቼ ከክርስቶስ ጋር መሆን እፈልጋለሁ፤ ምክንያቱም ከክርስቶስ ጋር መሆን ከሁሉ የሚበልጥ ነገር ስለሆነ ነው” ብሏል። ጳውሎስ እዚህ ላይ የጠቀሰው ‘በሞትና በትንሣኤ መካከል ያለውን ሁኔታ’ ነውን? አንዳንዶች እንደዚያ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ ጳውሎስ የተናገረው ሁለት ነገሮች ሊያጋጥሙት ማለትም ሊኖር ወይም ሊሞት እንደሚችል ነው። “በአንድ በኩል ከዚህ ሕይወት ተለይቼ ከክርስቶስ ጋር መሆን እፈልጋለሁ” ሲል በማከል ሦስተኛውን አማራጭ ጠቀሰ። ወዲያውኑ ‘ከዚህ ሕይወት እንደ ተለየ’ ከክርስቶስ ጋር ይሆናል ማለት ነው? ጳውሎስ ታማኝ የሆኑ ቅቡዕ ክርስቲያኖች በክርስቶስ መገኘት ወቅት እንደሚነሡ እንደሚያምን ከዚህ በፊት አይተናል። ስለዚህ በዚያን ወቅት የሚፈጸሙ ነገሮችን መናገሩ መሆን አለበት።
ይህንንም በፊልጵስዩስ 3:20, 21 እና በ1 ተሰሎንቄ 4:16 ላይ ከሚገኙት ከራሱ ቃላት ማየት ይቻላል። በክርስቶስ መገኘት ወቅት የሚፈጸመው ይህ “ከዚህ ሕይወት መለየት” ጳውሎስ አምላክ ያዘጋጀለትን ሽልማት እንዲቀበል ያስችለዋል። ይህን ተስፋ እንደሚያደርግ ለወጣቱ ጢሞቴዎስ ከጻፈለት ከሚከተሉት ቃላት መረዳት ይቻላል፦ “ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፣ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፣ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም።”—2 ጢሞቴዎስ 4:8
አስደናቂ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የሆነው ትንሣኤ
የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ትንሣኤ በክርስቶስ መገኘት ወቅት እንደሚጀምር ያስቡ ነበር፤ ከዚህ አስደናቂ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ከፍተኛ ብርታትና መጽናናት አግኝተዋል። (ማቴዎስ 24:3፤ ዮሐንስ 5:28, 29፤ 11:24, 25፤ 1 ቆሮንቶስ 15:19, 20፤ 1 ተሰሎንቄ 4:13) ስለ ነፍስ አለመሞት የሚናገሩትን የክህደት ትምህርቶች ባለመቀበል ወደፊት የሚያገኙትን ደስታ በታማኝነት ይጠባበቁ ነበር።—ሥራ 20:28–30፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:3, 4፤ 2 ጴጥሮስ 2:1–3
እርግጥ ትንሣኤ የሚያገኙት ሰማያዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች ብቻ አይደሉም። (1 ጴጥሮስ 1:3–5) የዕብራውያን አባቶችና ሌሎች የጥንት የአምላክ አገልጋዮች ይሖዋ ሙታንን ወደ ሕይወት ለማምጣት ባለው ችሎታ አምነዋል። (ኢዮብ 14:14, 15፤ ዳንኤል 12:2፤ ሉቃስ 20:37, 38፤ ዕብራውያን 11:19, 35) ‘ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ስለሚነሡ’ ባለፉት መቶ ዘመናት አምላክን በጭራሽ ሳያውቁ የሞቱ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንኳ በምድራዊት ገነት ውስጥ እንደገና በሕይወት የመኖር ዕድል ያገኛሉ። (ሥራ 24:15፤ ሉቃስ 23:42, 43) ይህ የሚያስፈነድቅ ተስፋ አይደለምን?
ይሖዋ መከራና ሞት ሁልጊዜ እንደሚኖሩ እንድናምን ከማድረግ ይልቅ ‘የኋለኛው ጠላት ማለትም ሞት’ ለዘላለም ወደሚጠፋበትና ታማኝ የሰው ልጆች ዝንተ ዓለም ወደሚኖሩባት ተመልሳ ወደምትመጣው ገነት ትኩረታችንን ያዞራል። (1 ቆሮንቶስ 15:26፤ ዮሐንስ 3:16፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) እንደገና ወደ ሕይወት የሚመጡትን የምንወዳቸውን ሰዎች ማየት ምንኛ አስደናቂ ይሆናል! ይህ እርግጠኛ ተስፋ በአምላክ ቃል ላይ ሳይሆን በግሪክ ፍልስፍና ላይ ከተመሠረተው የሰው ነፍስ አትሞትም ከሚለው መላ ምታዊ መሠረተ ትምህርት ምንኛ የተሻለ ነው! ተስፋህን በአምላክ እርግጠኛ የተስፋ ቃል ላይ ከመሠረትህ አንተም በቅርቡ ‘ሞት የማይኖርበትን’ ዓለም ልታይ ትችላለህ!—ራእይ 21:3–5
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ትንሣኤ አስደናቂ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ነው