ሰዎች በድህነት ተቆራምደው የሚኖሩት እስከ መቼ ነው?
“ነጻ ኅብረተሰብ በድህነት የተቆራመዱትን ብዙ ሰዎች ሊረዳ ካልቻለ ጥቂቶቹን ሀብታሞችም ሊጠብቅ አይችልም።”—ጆን ኤፍ ኬኔዲ
“የወደፊቱ ጊዜ ለሁሉም ሰው ብሩህ የሆነና ድህነት የማይኖርበት፣ በመኖሪያ ቤት እጦት ማንም ሰው መናፈሻ ውስጥ የማያድርበት ገነት እንዲሆን እመኛለሁ!” ይህን የተናገረው በሳኦ ፓሎ የሚኖር የ12 ዓመት ልጅ ነው። ይሁን እንጂ ድህነትን ማስወገድ ይቻላልን? ድሆች በድህነት ተቆራምደው የሚኖሩት እስከ መቼ ነው?
አንዳንድ ሰዎች የሚፈልጓቸውን ነገሮች መግዛት ስላልቻሉ ራሳቸውን ድሀ አድርገው ይቆጥራሉ። ይሁን እንጂ በድህነት የተቆራመዱ ሰዎች የሚደርስባቸውን አሳዛኝ መከራ እስቲ አስብ። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ያለባቸውን ከልክ ያለፈ ችግርና ሐዘን ልትገምት ትችላለህን? ለምሳሌ አንዳንዶች የሚበሉትን ምግብ ለማግኘት ከአሞራዎችና ከአይጦች ጋር በመሻማት ከቆሻሻ መጣያ ውስጥ ምግብ መፈለግ አለባቸው! እንደዚህ ያለው ድህነት የሰውን ዘር የሚያጠቃው እስከ መቼ ድረስ ነው? የዩኔስኮ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት) ዋና ዲሬክተር የሆኑት ፌደሪኮ ሜየር “በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሲቸገሩ፣ ሲራቡና ሲሠቃዩ እያዩ ዝም ማለት የማይቻል ቢሆንም ይህን ሁኔታ ዝም ብለን እንድንመለከት ያደረገንን እያዩ እንዳላዩ ሆኖ የማለፍ መጥፎ ባሕርይ እናስወግድ” ሲሉ ያቀረቡት ጥሪ ተገቢ ነው።
ለዓለም አቀፋዊ ብልፅግና የሚታለመው ሕልም ይፈጸም ይሆን? በድህነት የሚማቅቁ ሰዎች ምን ተስፋ አላቸው?
በድህነት የሚኖሩ ሰዎች ምን አጋጣሚዎች አሏቸው?
ልበ ቅን የሆኑ መሪዎች ብዙ የሥራ መስኮች ለመክፈት፣ የደሞዝ ጭማሪ ለማድረግ፣ ምንም ገቢ የሌላቸውን ሰዎች ደህንነት ለመጠበቅ የሚያስችሉ የተሻሻሉ ፕሮግራሞችን ለመዘርጋትና መሬትን በተመጣጠነ ሁኔታ ለሕዝብ ለማከፋፈል ያቅዳሉ። እንዲህ በማለት ከተናገሩት ከቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ሐሳብ ጋር ይስማሙ ይሆናል፦ “ነጻ ኅብረተሰብ በድህነት የተቆራመዱትን ብዙ ሰዎች ሊረዳ ካልቻለ ጥቂቶቹን ሀብታሞችም ሊጠብቅ አይችልም።” ይሁን እንጂ በአሳቢነት መንፈስ የቀረቡ ጥሩ ሐሳቦች ድህነትን ለማስወገድ በቂ አይደሉም። ለምሳሌ በኢኮኖሚ የሚደረገው እድገት ድሆችን በጥቅሉ ይረዳልን? ላይረዳ ይችላል። የቀድሞው የህንድ መሪ የነበሩት ነሩ “የካፒታሊስት ኅብረተሰብ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ቁጥጥር ካልተደረገበት ሀብታሞችን የበለጠ ሀብታም ድሆችን ደግሞ የበለጠ ድሀ ሊያደርጋቸው ይችላል” ሲሉ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ከችግርና ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ ነገሮች ከማጣትም በተጨማሪ ምንም ዋጋ የለኝም የሚል ስሜት የድሆችን ሸክም የበለጠ ያከብድባቸዋል። በድህነት የሚኖሩ ሰዎች የሚደርስባቸውን የዋጋ ቢስነትና የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዲያሸንፉ ሰብዓዊ መሪዎች ሊረዷቸው ይችላሉን?
እርግጥ ተስፋ በሚያስቆርጥ ሁኔታ በድህነት የተቆራመዱ ብዙ ሰዎች ድህነትን ለመቋቋምና ከፍተኛ የኑሮ ውድነትንና ሥራ አጥነትን የመሳሰሉ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው የሚሰማቸውን የዝቅተኝነት ስሜት እንዴት ማሸነፍ እንደሚችሉ አውቀዋል። ከዚህም በላይ ረሃብ፣ የመኖሪያ ቤት እጦትና ችግር ያለምንም ጥርጥር ከሥራቸው ተነቅለው ይወገዳሉ። ይህ ነገር የማይሆን መስሎ ይታይሃልን? “በቅርቡ ድህነት ጨርሶ ይወገዳል!” የሚለውን የሚቀጥለውን ርዕስ እንድታነብ እንጋብዝሃለን።