‘ከመጽናናት ሁሉ አምላክ’ የሚገኝ መጽናኛ
“የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል።”—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4
1, 2. በሐዘን ላይ ያሉ ሰዎች የሚፈልጉት ምን ዓይነት መጽናኛ ነው?
በሐዘን ላይ ያሉ ሰዎች የሚፈልጉት እውነተኛ ማጽናኛ እንጂ ምን ጊዜም የሚጠቀሱ አሰልቺና ምንችክ ያሉ ቃላት አይደለም። ሁላችንም ‘ጊዜ ቁስልን ይፈውሳል’ የሚለውን ብሂል ሰምተናል፤ ሆኖም በመጀመሪያው የሐዘን ደረጃ ላይ ያለ በሐዘን የተደቆሰ ግለሰብ በዚህ ሐሳብ ይጽናናልን? ክርስቲያኖች አምላክ የትንሣኤ ተስፋ እንደሰጠ ቢያውቁም ይህ ተስፋ የሚወዱትን ሰው በድንገት ማጣታቸው የሚያስከትልባቸውን ጥልቅ ሐዘንና ከባድ የስሜት መቃወስ አይከላከልላቸውም። በተጨማሪም ልጅህን በሞት ካጣህ ሌሎች ልጆችህ የዚያ ውድ ልጅ ምትክ እንደማይሆኑ የተረጋገጠ ነው።
2 የምንወደውን ሰው በሞት ስናጣ አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ በተመሠረተ እውነተኛ ማጽናኛ አማካኝነት ብዙ እርዳታ እናገኛለን። ችግራችንን በእኛ ቦታ ሆኖ የሚረዳልን ሰውም እንፈልጋለን። ይህ ለሩዋንዳ ሕዝቦች በተለይም በዚያ ዲያብሎሳዊ የዘር ጭፍጨፋ የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት ላጡት በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክር ቤተሰቦች ያስፈልጋል። በሐዘን ላይ ያሉ ሁሉ ማጽናኛ ማግኘት የሚችሉት ከማን ነው?
የመጽናናት አምላክ የሆነው ይሖዋ
3. ይሖዋ መጽናኛ በመስጠት ረገድ ምሳሌ የተወልን እንዴት ነው?
3 ይሖዋ ለሁላችንም ማጽናኛ በመስጠት ምሳሌ ትቶልናል። ዘላለማዊ መጽናኛና ተስፋ እንድናገኝ አንድያ ልጁ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ምድር ልኮታል። ኢየሱስ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” ሲል አስተምሯል። (ዮሐንስ 3:16) በተጨማሪም “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም” በማለት ለተከታዮቹ ነግሯቸዋል። (ዮሐንስ 15:13) በሌላ ወቅት ደግሞ “የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” ብሎ ነበር። (ማቴዎስ 20:28) በተጨማሪም ጳውሎስ “ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል” ሲል ገልጿል። (ሮሜ 5:8) እነዚህና ሌሎች ብዙ ጥቅሶች አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ያላቸውን ፍቅር እንድንገነዘብ ይረዱናል።
4. በተለይ ሐዋርያው ጳውሎስ የይሖዋ ታላቅ ውለታ የነበረበት ለምን ነበር?
4 በተለይ ሐዋርያው ጳውሎስ ይገባናል ስለማንለው የይሖዋ ደግነት ያውቅ ነበር። በአክራሪነት መንፈስ የክርስቶስ ተከታዮችን ከማሳደድ ተመልሶ ራሱ የሚሰደድ ክርስቲያን ሆኖ ስለ ነበር በመንፈሳዊ ሙት ከነበረበት ሁኔታ ተላቅቆ ነበር። (ኤፌሶን 2:1–5) ተሞክሮውን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፣ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንሁ እኔ ነኝ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም ከሁላቸው ይልቅ ግን ደከምሁ፣ ዳሩ ግን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም።”—1 ቆሮንቶስ 15:9, 10
5. ጳውሎስ ከአምላክ ስለሚገኘው መጽናኛ ምን ብሎ ጽፏል?
5 እንግዲያው ጳውሎስ እንዲህ ብሎ መጻፉ የተገባ ነበር፦ “የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል፣ ስለዚህም እኛ ራሳችን በእግዚአብሔር በምንጽናናበት መጽናናት በመከራ ሁሉ ያሉትን ማጽናናት እንችላለን። የክርስቶስ ሥቃይ በእኛ ላይ እንደ በዛ፣ እንዲሁ መጽናናታችን ደግሞ በክርስቶስ በኩል ይበዛልናልና። ዳሩ ግን መከራ ብንቀበል፣ ስለ መጽናናታችሁና ስለ መዳናችሁ ነው፤ ብንጽናናም፣ እኛ ደግሞ የምንሣቀይበት በዚያ ሥቃይ በመጽናት ስለሚደረግ ስለ መጽናናታችሁ ነው። ተስፋችንም ስለ እናንተ ጽኑ ነው፤ ሥቃያችንን እንደ ተካፈላችሁ እንዲሁም መጽናናታችንን ደግሞ እንድትካፈሉ እናውቃለንና።”—2 ቆሮንቶስ 1:3–7
6. “ማጽናኛ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ምን ትርጉም አለው?
6 እንዴት ያሉ ስሜት ቀስቃሽ ቃላት ናቸው! እዚህ ላይ “ማጽናኛ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል “ከአንድ ሰው ጎን እንዲሆኑ መጠራት” ከሚለው ሐሳብ ጋር ግንኙነት አለው። ስለዚህ “ማጽናናት አንድ ሰው ከባድ ችግር ሲደርስበት እሱን ለማበረታታት ከጎኑ መቆም ማለት ነው።” (ኤ ሊንጉስቲክ ኪ ቱ ዘ ግሪክ ኒው ቴስታመንት) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ቃሉ . . . ምን ጊዜም፣ ከንፈር ከመምጠጥ በጣም የተለየ ነው። . . . ክርስቲያናዊ ማጽናኛ የሚያደፋፍር ማጽናኛ ነው፣ አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ የሚያጋጥሙትን ችግሮች በሙሉ በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት የሚያስችለው ማጽናኛ ነው።” በተጨማሪም ማጽናናት እንደ ሙታን ትንሣኤ ያሉትን በእርግጠኛ ተስፋ ላይ የተመሠረቱ የሚያጽናኑ ሐሳቦች ማካፈልን ይጨምራል።
ርኅሩኅ አጽናኝ የሆኑት ኢየሱስና ጳውሎስ
7. ጳውሎስ ክርስቲያን ወንድሞቹን ያጽናና የነበረው እንዴት ነው?
7 ጳውሎስ በማጽናናት ረገድ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነበር! በተሰሎንቄ ለነበሩት ክርስቲያን ወንድሞች የሚከተለውን ሊጽፍላቸው ችሎ ነበር፦ “ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትከባከብ፣ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን፤ እንዲሁም እያፈቀርናችሁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማካፈል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ እናካፍላችሁ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ነበረ፣ ለእኛ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ነበርና። . . . እየመከርንና እያጸናን እየመሰከርንላችሁም፣ አባት ለልጆቹ እንደሚሆን ለእያንዳንዳችሁ እንደ ሆንን ታውቃላችሁና።” ሁላችንም እንደ አፍቃሪና አሳቢ ወላጆች በመሆን በችግራቸው ወቅት ለሌሎች ፍቅራችንንና አሳቢነታችንን ለማካፈል እንችላለን።—1 ተሰሎንቄ 2:7, 8, 11
8. የኢየሱስ ትምህርት በሐዘን ላይ ለሚገኙ ሰዎች መጽናኛ የሚሆነው ለምንድን ነው?
8 ጳውሎስ እንዲህ ዓይነቱን አሳቢነትና ደግነት ሲያሳይ ታላቅ አርአያው የሆነውን ኢየሱስን መምሰሉ ነበር። በማቴዎስ 11:28–30 ላይ የተመዘገበውን ኢየሱስ ለሰው ሁሉ ያቀረበውን የሚከተለውን ርኅራኄ የተሞላበት ግብዣ አስታውስ፦ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔ አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔም የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ። ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።” አዎን፣ የኢየሱስ ትምህርት ተስፋን ይኸውም የትንሣኤ ተስፋን ያቀፈ ስለሆነ የሚያሳርፍ ነው። ለሰዎች በመስጠት ላይ ያለነው ተስፋ ይህ ነው፤ ለምሳሌ ያህል፣ የምትወዱት ሰው ሲሞት የተባለውን ብሮሹር ስናበረክት ይህን ተስፋ እንሰጣቸዋለን። ይህ ተስፋ ሁላችንንም ሌላው ቀርቶ ለረጅም ጊዜ በሐዘን ላይ የቆየነውንም ጭምር ሊረዳ ይችላል።
ሐዘንተኞችን እንዴት ማጽናናት እንደሚቻል
9. በሐዘን ላይ ካሉ ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ትዕግሥት ልናጣ የማይገባው ለምንድን ነው?
9 ሐዘን የሚወዱት ሰው ከሞተ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወዲያው የሚከስም ነገር አይደለም። አንዳንድ ሰዎች በተለይም ልጆቻቸውን በሞት የተነጠቁ ሰዎች ዕድሜ ልካቸውን በሐዘን ተውጠው ይኖራሉ። በስፔይን የሚገኙ አንድ ታማኝ ክርስቲያን ባልና ሚስት የ11 ዓመት ልጃቸው በ1963 በማጅራት ገትር በሽታ ሞተባቸው። እስካሁን ድረስ ፓኪቶ ስለ ተባለው ልጃቸው ሲያወሩ ያለቅሳሉ። ሟች የሞተበት ቀን፣ ፎቶዎችና ያንን ሁኔታ የሚያስታውሱ ነገሮች አሳዛኝ ትዝታዎችን ሊቀሰቅሱ ይችላሉ። ስለዚህ ትዕግሥት ማጣት ወይም ሌሎች እስካሁን መቆየት የለባቸውም፤ ሐዘናቸውን መርሳት አለባቸው ብለን ማሰብ የለብንም። አንድ የሕክምና ጠበብት “የመንፈስ ጭንቀትና የስሜት መለዋወጥ ለብዙ ዓመታት ሊቆዩ ይችላሉ” ብለዋል። ስለዚህ በአካል ላይ ያለ ጠባሳ ሳይጠፋ ዕድሜ ልክ ከእኛ ጋር አብሮ ሊኖር እንደሚችል ሁሉ ብዙዎቹ የስሜት ጠባሳዎችም እንደዚሁ ከአእምሮ እንደማይጠፉ አትርሳ።
10. በሐዘን ላይ ያሉ ሰዎችን ለመርዳት ምን ማድረግ አለብን?
10 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በሐዘን ላይ ያሉ ሰዎችን ለማጽናናት ልናደርጋቸው የምንችላቸው አንዳንድ ተግባራዊ ነገሮች ምንድን ናቸው? ማጽናኛ ለሚያስፈልገው አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት በቅንነት ተነሳስተን “ልረዳህ የምችለው ነገር ካለ ንገረኝ” ብለን እንናገር ይሆናል። ይሁን እንጂ የሚወዱት ዘመዳቸው ወይም ወዳጃቸው ከሞተባቸው ሰዎች መካከል “አንድ ነገር ልትረዳኝ ትችላለህ ብዬ አሰብኩ” ብለው የሚጠሩን ስንቶቹ ናቸው? በሐዘን ላይ ያሉ ሰዎችን ለማጽናናት የምንፈልግ ከሆነ በራሳችን ተነሳስተን አንድ ነገር ልናደርግላቸው እንደሚገባ ግልጽ ነው። እንግዲያው ጠቃሚ በሆነ መንገድ ምን ልናደርግላቸው እንችላለን? ከዚህ በታች ተግባራዊ የሆኑ ጥቂት ሐሳቦች ቀርበዋል።
11. በጥሞና ማዳመጣችን ሌሎችን ሊያጽናና የሚችለው እንዴት ነው?
11 አዳምጥ፦ አንድን ሐዘንተኛ ልትረዱ ከምትችሉባቸው ጠቃሚ ነገሮች አንዱ ሐዘንተኛው የሚናገረውን በማዳመጥ የሐዘኑ ተካፋይ መሆን ነው። “ስለ ሁኔታው ልትነግረኝ ትችላለህ?” ብለህ ልትጠይቅ ትችላለህ። ራሱ ሐዘንተኛው እንዲወስን አድርግ። አንድ ክርስቲያን አባቱ የሞተበትን ጊዜ አስታውሶ ሲናገር “ሌሎች ስለ አሟሟቱ ጠይቀውኝ የምናገረውን ከልብ ሲያዳመጡ ቀለል ይለኝ ነበር” ብሏል። ያዕቆብ እንደመከረው ለማዳመጥ ፈጣን ሁን። (ያዕቆብ 1:19) በትዕግሥትና የሐዘኑ ተካፋይ መሆንህን በሚያሳይ መንገድ አዳምጥ። መጽሐፍ ቅዱስ በሮሜ 12:15 ላይ “ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ” ሲል ይመክራል። ኢየሱስ ከማርታና ከማርያም ጋር እንዳለቀሰ አስታውስ።—ዮሐንስ 11:35
12. በለቅሶ ላይ ላሉ ሰዎች ምን ዓይናት መጽናኛ ልንለግሳቸው እንችላለን?
12 አጽናናቸው፦ በሐዘን ላይ ያለው ሰው መጀመሪያ ላይ የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማው እንደሚችል አትዘንጋ፤ ይህ ዓይነቱ ስሜት የሚሰማው ብዙ ማድረግ እንደነበረበት ስለሚሰማው ሊሆን ይችላል። ሊደረግ የሚችለው ነገር ሁሉ እንደተደረገ አረጋግጥለት (ወይም እውነትና ገንቢ ሆኖ ያገኘኸውን ማንኛውም ነገር ንገረው)። የሚሰማው ስሜት ያልተለመደ ነገር እንዳልሆነ አረጋግጥለት። ተመሳሳይ ሐዘን ደርሶባቸው ከሐዘናቸው መጽናናት የቻሉ የምታውቃቸውን ሰዎች ጥቀስለት። በሌላ አባባል ችግሩ የሚገባህና ሐዘኑ የሚሰማህ ሁን። በደግነት የምናደርገው እርዳታ ብዙ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል! ሰሎሞን “በወቅቱ በትክክል የተነገረ ቃል፣ በብር ላይ እንደፈሰሰ የወርቅ ጌጥ፣ ውበት ይኖረዋል” ሲል ጽፏል።—ምሳሌ 16:24፤ 25:11 የ1980 ትርጉም ፤ 1 ተሰሎንቄ 5:11, 14
13. ከእነሱ አለመለየታችን እንዴት ሊረዳቸው ይችላል?
13 አትለያቸው፦ ብዙ ወዳጆችና ዘመዶች በሚኖሩባቸው በሐዘኑ የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ ከሆነ ሌሎች ወደ ዕለት ተግባራቸው ከተመለሱ በኋላም ለብዙ ወራት አትለያቸው። የሐዘኑ ርዝማኔ እንደ ግለሰቡ ሁኔታ ሊለያይ ይችላል። በማንኛውም የችግር ወቅት ክርስቲያናዊ አሳቢነት ማሳየታችንና የሐዘን ተካፋይ መሆናችን ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ከወንድም አብልጦ የሚጠጋጋ ወዳጅ አለ” ይላል። ስለዚህ “በችግር ወቅት የሚደርስ ጓደኛ እውነተኛ ጓደኛ ነው” የሚለው ብሂል ልንሠራበት የሚገባ እውነተኛ አባባል ነው።—ምሳሌ 18:24፤ ከሥራ 28:15 ጋር አወዳድር።
14. ሐዘንተኞችን ለማጽናናት ምን መናገር እንችላለን?
14 የሟቹን ሰው ጥሩ ጥሩ ባሕርያት እያነሳህ ተናገር፦ በትክክለኛው ጊዜ ላይ ሲቀርብ ከፍተኛ እርዳታ የሚያበረክተው ሌላው ነገር ይህ ነው። ስለ ግለሰቡ የምታስታውሳቸውን ገንቢና ደስ የሚሉ ታሪኮች ተናገር። የሟቹን ስም ለመጠቀም አታመንታ። በሞት የተጠለፈው ተወዳጁ ፈጽሞ በሕይወት ያልነበረ ሰው ወይም ከዚህ ግባ የማይባል እንደነበረ የሚያስመስል አነጋገር አትጠቀም። የሃርቫድ ሜዲካል ስኩል ያዘጋጀው አንድ ጽሑፍ የገለጸው የሚከተለው ቃል የሚያጽናና ነው፦ “በሐዘን ላይ ያለው ሰው ከደረሰበት ሐዘን ሊጽናና የሚችለው ሐዘኑን ተወት አድርጎ ስለ ሟቹ ማሰብ ሲችል ነው። . . . ሐዘንተኛው አዲሱን እውነታ እየተቀበለና እየለመደው ሲሄድ ሐዘኑ ይጠፋና በምትኩ እንደ ውድ ነገር የሚታዩ አስደሳች ትዝታዎች ይመጣሉ።” “አስደሳች ትዝታዎች”ን ማለትም ከሚወዱት ሰው ጋር ያሳለፉትን ውድ ጊዜያት ማስታወስ ምንኛ ያጽናናል! ከጥቂት ዓመታት በፊት አባቱ በሞት የተለዩት አንድ የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ብሎ ነበር፦ “አባባ እውነትን ማጥናት ከጀመረ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አብረን እናደርገው የነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ልዩ ትዝታ ጥሎብኛል። በወንዝ ዳር አጠገብ ተኝተን አንዳንድ ችግሮቼን እያነሳን እንወያይ የነበረበት ጊዜም ለእኔ ልዩ ትዝታ አለው። አባቴን እጠይቀው የነበረው በየሦስት ወይም በየአራት ዓመቱ ብቻ ስለ ነበር እነዚያ ጊዜያት ውድ ነበሩ።”
15. አንድ ሰው በራሱ ተነሳስቶ እርዳታ ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው?
15 አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በራስህ ተነሳስተህ እርዳቸው፦ አንዳንድ ሐዘንተኞች ከሌሎች በተሻለ መንገድ ሐዘናቸውን መቋቋም ይችላሉ። ስለዚህ እንደ ሁኔታው እነሱን ለመርዳት ተግባራዊ እርምጃዎችን ውሰድ። አንዲት ሐዘን የደረሰባት ክርስቲያን ሴት “ብዙ የጉባኤ አባሎች ‘ልረዳሽ የምችለው ነገር ካለ ንገሪኝ’ ይሉኝ ነበር። ይሁን እንጂ አንዲት ክርስቲያን እህት እንዲህ ብላ አልጠየቀችኝም። በቀጥታ ወደ መኝታ ቤት ገባችና የቆሸሹትን የአልጋ ልብሶች ወስዳ አጠበች። ሌላ እህት ደግሞ ውኃ በባልዲ ቀዳችና የጽዳት ዕቃዎችን ካቀረበች በኋላ ባሌ አስመልሶበት የነበረውን ምንጣፍ አጸዳች። እነዚህ እውነተኛ ወዳጆች ናቸው፤ በፍጹም አልረሳቸውም።” እርዳታ እንደሚያስፈልግ በግልጽ ከተገነዘብክ በራስህ ተነሳስተህ እርዳቸው፤ ምናልባት ምግብ በማብሰል፣ በጽዳት ሥራ በመርዳት ወይም በመላላክ አንዳንድ ጠቃሚ አገልግሎቶችን ማከናወን ትችል ይሆናል። እርግጥ ሐዘንተኛው ብቻውን መሆን ሲፈልግ መረበሽ የለብንም። በዚህ መንገድ “እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፣ ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ” የሚሉትን የጳውሎስ ቃላት በሥራ ላይ ለማዋል ከልባችን መጣር ይኖርብናል። ደግነት፣ ትዕግሥትና ፍቅር በፍጹም ከንቱ ሆነው አይቀሩም።—ቆላስይስ 3:12፤ 1 ቆሮንቶስ 13:4–8
16. ደብዳቤ ወይም ፖስት ካርድ ሊያጽናና የሚችለው ለምንድን ነው?
16 ደብዳቤ ጻፍ ወይም የሚያጽናና መልእክት የሰፈረበት ፖስት ካርድ ላክ፦ ብዙውን ጊዜ የሐዘን መግለጫ የሰፈረበት ደብዳቤ ወይም ውብ ፖስት ካርድ የሚሰጠው ጥቅም እምብዛም ትኩረት አይሰጠውም። የፖስት ካርድ ወይም የደብዳቤ ጥቅም ምንድን ነው? በተደጋጋሚ ሊነበብ ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ደብዳቤ ረዥም መሆን የለበትም፤ ይሁን እንጂ የተሰማህን ሐዘን የሚገልጽ መሆን አለበት። መንፈሳዊ መልእክት የሚያስተላልፍ ዓይነት መሆን አለበት፤ ሆኖም የሰበካ መንፈስ ያለው መሆን የለበትም። “አይዞህ፣ ከጎንህ ነን” የሚለው መልእክት ብቻ ሊያጽናና ይችላል።
17. ጸሎት ሊያጽናና የሚችለው እንዴት ነው?
17 አብረሃቸው ጸልይ፦ በሐዘን ላይ ካሉ መሰል ክርስቲያኖች ጋር አብሮ የመጸለይንና ለእነሱ የመጸለይን ጠቀሜታ አቅልለህ አትመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ በያዕቆብ 5:16 (የ1980 ትርጉም) ላይ “የጻድቅ ሰው ጸሎት . . . ታላቅ ኅይል አለው” ይላል። ለምሳሌ ያህል፣ በሐዘን ላይ ያሉ ሰዎች ለእነሱ ስንጸልይላቸው ሲሰሙ የጥፋተኝነት ስሜት የመሳሰሉትን አፍራሽ ስሜቶች በተሳካ ሁኔታ እንዲቋቋሙ ይረዳቸዋል። ደከም ስንልና ተስፋ ስንቆርጥ ሰይጣን በእሱ “መሠሪ ዘዴዎች” ወይም “የተንኮል ድርጊቶች” ሊያዳክመን ይሞክራል። ጳውሎስ “በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ” በማለት እንደገለጸው ማጽናኛና የጸሎት ድጋፍ የሚያስፈልገን በዚህ ጊዜ ነው።—ኤፌሶን 6:11, 18 ኪንግደም ኢንተርሊኒየር፤ ከያዕቆብ 5:13–15 ጋር አወዳድር።
መወገድ ያለባቸው ነገሮች
18, 19. ስናነጋግራቸው ዘዴኛ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
18 አንድ ግለሰብ በሐዘን ላይ እያለ ልናደርጋቸው ወይም ልንናገራቸው የማይገቡን ነገሮችም አሉ። ምሳሌ 12:18 “እንደሚዋጋ ሰይፍ የሚለፈልፍ ሰው አለ፤ የጠቢባን ምላስ ግን ጤና ነው” ሲል ያስጠነቅቃል። አንዳንድ ጊዜ ሳይታወቀን ዘዴኛ ሳንሆን እንቀራለን። ለምሳሌ ያህል፣ “እንዴት እንደሚሰማህ አውቃለሁ” እንል ይሆናል። ይሁን እንጂ ሐቁ ይህ ነውን? አንተም ሰውዬው የሞተበት ዓይነት ሰው ሞቶብሃልን? እንዲሁም ተመሳሳይ ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች የሚሰማቸው ሐዘን የተለያየ ነው። ተመሳሳይ ለሆነ ሐዘን አንተ የሚሰማህ የሐዘን ስሜትና ሐዘንተኛው የሚሰማው ስሜት ላይመሳሰል ይችላል። “ከተወሰነ ጊዜ በፊት የእኔ . . . ሲሞት ተመሳሳይ ሐዘን ደርሶብኝ ስለ ነበር ሐዘንህ በጣም ይሰማኛል” ብትል የሐዘንተኛውን ስሜት ላትጎዳ ትችላለህ።
19 ሟቹ በትንሣኤ ይነሳል ወይም አይነሳም በሚለው ጉዳይ ላይ አስተያየት ከመስጠት መቆጠብም ለሰው ስሜት ማሰብን ያሳያል። አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች በሞት ስለ ተለያቸው የማያምን የትዳር ጓደኛ የወደፊት ዕጣ በተሰጡ አስተያየቶች በጣም ተጎድተዋል። ማን በትንሣኤ እንደሚነሳ ወይም እንደማይነሳ ፈራጆቹ እኛ አይደለንም። ልብን የሚያየው ይሖዋ ከእኛ በጣም በላቀ ሁኔታ ምሕረት ያለው መሆኑ ሊያጽናናን ይችላል።—መዝሙር 86:15፤ ሉቃስ 6:35–37
የሚያጽናኑ ጥቅሶች
20, 21. በሐዘን ላይ ያሉ ሰዎችን ሊያጽናኑ የሚችሉ አንዳንድ ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው?
20 በትክክለኛው ጊዜ ሲቀርብላቸው በሐዘን ላይ ያሉ ሰዎች መጽናኛ ከሚያገኙባቸው ከሁሉ የላቁ ነገሮች አንዱ ይሖዋ ስለ ሙታን የሰጠውን ተስፋ መመልከት ነው። በሐዘን ላይ ያለው ግለሰብ የይሖዋ ምሥክርም ይሁን በአገልግሎት ወቅት ያገኘነው ሰው እነዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳቦች ጠቃሚ ናቸው። ከእነዚህ ጥቅሶች አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው? ይሖዋ “የማጽናናችሁ እኔ ነኝ፣ እኔ ነኝ” በማለት ስለተናገረ የመጽናናት ሁሉ አምላክ እንደሆነ እናውቃለን። በተጨማሪም “እናት ልጅዋን እንደምታጽናና እንዲሁ አጽናናችኋለሁ” ብሏል።—ኢሳይያስ 51:12፤ 66:13
21 መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የተስፋ ቃልህ ሕይወቴን ስላደሰልኝ፣ በመከራዬ ጊዜ እንኳ ተጽናንቻለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! መጽናናትን የሚሰጠኝ ስለሆነ፣ ከጥንት ጀምሮ የነበረውን ሕግህን አስታውሳለሁ። ለእኔ ለአገልጋይህ በሰጠኸው የተስፋ ቃል መሠረት ዘላለማዊ ፍቅርህ ያጽናናኝ።” በእነዚህ ምንባቦች ውስጥ ‘መጽናኛ’ የሚለው ቃል በተደጋጋሚ እንደተጠቀሰ አስተውል። አዎን፣ በመከራችን ወቅት ትኩረታችንን ወደ ይሖዋ ቃል በማዞር ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች የሚሆን እውነተኛ መጽናኛ ልናገኝ እንችላለን። ይህ ከወንድሞቻችን ፍቅርና አሳቢነት ጋር ተዳምሮ የምንወደውን ሰው ማጣት ያስከተለብንን ሥቃይ በተሳካ ሁኔታ እንድንቋቋምና ሕይወታችን አስደሳች በሆነው ክርስቲያናዊ አገልግሎት እንደገና እንዲጠመድ ለማድረግ ሊረዳን ይችላል።—መዝሙር 119:50, 52, 76 የ1980 ትርጉም
22. ከፊት ለፊታችን ምን ተስፋ ተዘርግቶልናል?
22 በተጨማሪም በሐዘን የተዋጡ ሌሎች ሰዎችን በመርዳቱ ሥራ ራሳችንን በማስጠመድ ሐዘናችንን በተወሰነ ደረጃ ለመቋቋም እንችላለን። ትኩረታችንን መጽናናት ወደሚያስፈልጋቸው ሰዎች ስናዞር በመንፈሳዊ መንገድ መስጠት የሚያስገኘውን እውነተኛ ደስታም እናገኛለን። (ሥራ 20:35) የሁሉም የቀድሞ ብሔራት ሕዝቦች በየትውልዱ ቅድም ተከተል በአዲስ ዓለም ውስጥ በሞት የተለዩአቸውን የሚወዷቸውን ሰዎች እንደገና የሚቀበሉበትን የትንሣኤ ቀን ዕይታ እንደ እኛ በዓይነ ሕሊናቸው መመልከት እንዲችሉ እናድርግ። እንዴት ያለ ተስፋ ነው! በዚያን ወቅት ይሖዋ “ኀዘንተኞችን የሚያጽናና” አምላክ መሆኑን ስናስታውስ የደስታ እንባ እናነባለን!—2 ቆሮንቶስ 7:6
ታስታውሳለህን?
◻ ይሖዋ “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” የሆነው እንዴት ነው?
◻ ኢየሱስና ጳውሎስ ሐዘንተኞችን ያጽናኑት እንዴት ነበር?
◻ ሐዘንተኞችን ለማጽናናት ልናደርግ የምንችላቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
◻ በሐዘን ላይ ካሉ ሰዎች ጋር በምናደርገው ግንኙነት ምን ነገሮችን ማስወገድ አለብን?
◻ ሰው ሲሞት ከሁሉ ይበልጥ መጽናኛ ይሰጣሉ የምትላቸው ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሐዘን ላይ ያሉ ሰዎችን በራስህ ተነሳስተህ በዘዴ እርዳቸው