የቀድሞዎቹ አምላካዊ ቤተሰቦች ለዘመናችን ምሳሌ ናቸው
ቤተሰብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት እንዲያገኝ የተባበሩት መንግሥታት ጥረት አድርጓል። እንዴት? 1994ን “ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ዓመት” ብሎ በማወጅ ነው። ምንም እንኳ የዓለም መሪዎች፣ የማኅበራዊ ኑሮ ጠበብትና የቤተሰብ አማካሪዎች ያለ ጋብቻ ስለሚወለዱ ልጆችና በፍጥነት እያሻቀበ ስላለው የፍቺ ቁጥር ለማማረር የፈጠኑ ቢሆኑም ለእነዚህ ችግሮች ሊሠሩ የሚችሉ ትክክለኛ መፍትሄዎችን በማቅረብ በኩል ግን ዘግይተዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ ለቤተሰብ ችግሮች መፍትሄ ሊኖረው ይችላልን? መጽሐፍ ቅዱስ በጊዜያችን ላለው ቤተሰብ እርዳታ ሊያበረክት ይችላል የሚለውን ሐሳብ አንዳንዶች አቅልለው ይመለከቱት ይሆናል። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ባለው ሁኔታና ባሕል ሥር ነው። በአብዛኞቹ የዓለም ክፍሎች ያለው ሕይወት በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ከነበረበት ሁኔታ በጣም ተለውጧል። ያም ሆነ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ሁሉም ቤተሰብ ስም ባገኘበት በይሖዋ አምላክ አነሳሽነት ነው። (ኤፌሶን 3:14, 15፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16) መጽሐፍ ቅዱስ የቤተሰብን ችግሮች በተመለከተ ምን ይላል?
ይሖዋ የቤተሰብን ኑሮ አስደሳችና የሚያረካ ለማድረግ የሚያስፈልገው ምን ነገር እንደሆነ በትክክል ያውቃል። ስለዚህ ቃሉ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቤተሰብ ኑሮ ብዙ የሚናገር ሲሆን አንዳንዶቹ በማስጠንቀቂያነት መልክ ቀርበዋል። ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ አምላካዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በተግባር ያዋሉ ምሳሌ የሚሆኑ ቤተሰቦችን ይዟል። ይህን በማድረጋቸውም እውነተኛ የሆነ ቅርርብና እርካታ አግኝተዋል። እስቲ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ ቤተሰቦችን ቀረብ ብለን እንመርምርና ምን ትምህርት መቅሰም እንደሚቻል እንመልከት።
የራስነት ሥልጣን አስቸጋሪ ነውን?
ለምሳሌ ስለ ቤተሰብ የራስነት ሥልጣን ተመልከት። በዕብራውያን አባቶች ዘመን እንደ አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ያሉ ወንዶች “የቤተሰብ ራሶች” መሆናቸው የማያጠያይቅ ነበር። (ሥራ 7:8, 9 አዓት፤ ዕብራውያን 7:4 አዓት) በራልፍ ጎወር የተጻፈው ዘ ኒው ማነር ኤንድ ከስተምስ ኦቭ ባይብል ታይምስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ቤተሰብ . . . በአባት የሚመራ ‘ትንሽ መንግሥት’ ነበር። አባት በቤተሰቡ ውስጥ ባሉት በሁሉም ላይ ማለትም በሚስት፣ በልጆች፣ በልጅ ልጆችና በአገልጋዩች ላይ ይገዛል።” በእርግጥም የዕብራውያን አባቶች ብዙውን ጊዜ በልጆቻቸውና በቤተሰባቸው ላይ ሥልጣን ነበራቸው።—ከዘፍጥረት 42:37 ጋር አወዳድር።
ይህ ሥልጣን ወንዶች የሆኑ ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን እንዲጨቁኑ ፈቃድ አይሰጥምን? በፍጹም አይሰጥም። እርግጥ አምላክ ለመጀመሪያዋ ሴት ለሔዋን “ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፣ እርሱም ገዥሽ ይሆናል” ብሏታል። (ዘፍጥረት 3:16) እነዚህ ቃላት በጥቅሉ ያገቡ ሴቶች የሚደርስባቸውን ሁኔታ ይጠቁማሉ እንጂ በአምላክ እውነተኛ አምላኪዎች መካከል ነገሮች እንዴት መሆን እንዳለባቸው የሚገልጹ አይደሉም። አምላክን የሚፈሩ ባሎች የይሖዋን የመጀመሪያ ዓላማ በአእምሯቸው መያዝ ነበረባቸው። ይሖዋ ሴትን የሠራው ወንድን “የተሟላ የምታደርገው ረዳት” እንድትሆንለት እንጂ ባሪያው እንድትሆን አይደለም። (ዘፍጥረት 2:20) የጥንቶቹ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወንዶች ራሳቸው ለአምላክ የሚገዙ መሆናቸውንና በእርሱ ፊት ተጠያቂዎች እንደሆኑ ስለተገነዘቡ በሥልጣናቸው አለአግባብ አልተጠቀሙም። አምላክን የሚፈሩ የዕብራውያን አባቶች ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን እንደ ባሪያዎች ከማየት ይልቅ ልባዊ የሆነና የጠበቀ ፍቅር አሳይተዋቸዋል።
ልጆች ዘወትር ያገኙ ከነበረው የጠበቀ ፍቅር መካከል አንዱ በዘፍጥረት 50:23 ላይ ተገልጿል። እዚያ ላይ ስለ ዮሴፍ ሦስተኛ የልጅ ልጆች ሲናገር “በዮሴፍ ጭን ላይ ተወለዱ” ይላል። እንዲህ መባሉ ልጆቹ የእርሱ የልጅ ልጆች መሆናቸውን ዮሴፍ መቀበሉን የሚያሳይ ቢሆንም ጭኑ ላይ በማስቀመጥ ልጆቹን በፍቅር እንደሚያጫውታቸውም ሊያመለክት ይችላል። በዛሬው ጊዜ ያሉ አባቶችም ለልጆቻቸው እንዲህ ያለ የጠበቀ ፍቅር ቢያሳዩአቸው ጥሩ ነው።
አምላክን የሚፈሩ የዕብራውያን አባቶች የቤተሰብ ራስ እንደመሆናቸው መጠን የቤተሰባቸውን መንፈሳዊ ፍላጎት ያሟሉ ነበር። ኖኅ ከዓለም አቀፉ የጥፋት ውኃ በኋላ ከመርከብ እንደወጣ “ለእግዚአብሔር መሠውያውን ሠራ . . . በመሠዊያውም ላይ መሥዋዕትን አቀረበ።” (ከዘፍጥረት 8:20፤ ከኢዮብ 1:5 ጋር አወዳድር።) ታማኙ የዕብራውያን አባት አብርሃም ለቤተሰቡ አባላት መመሪያዎችን በመስጠት ጥሩ ምሳሌ ትቷል። ‘ጽድቅንና ፍርድን በማድረግ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከእርሱ በኋላ ቤቱን ያዝዝ ነበር።’ (ዘፍጥረት 18:19) በዚህም ምክንያት ፍቅር የተሞላበት የራስነት ሥልጣን ለቤተሰቡ ስሜታዊና መንፈሳዊ ደህንነት የበኩሉን ድርሻ አበርክቶ ነበር።
በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያን ወንዶች ይህንን ምሳሌ ይከተላሉ። ቤተሰቡ አምላክ የሚፈልግበትን እንዲፈጽም በመርዳትና ራሳቸውን ጥሩ ምሳሌ አድርገው በማቅረብ በአምልኮ ጉዳዮች የራስነት ሥልጣናቸውን ይጠቀሙበታል። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ ዕብራውያን 10:24, 25) በተጨማሪም ክርስቲያን ባሎችና አባቶች ልክ እንደ ዕብራውያን አባቶች ለቤተሰባቸው አባሎች ትምህርት የሚሰጡበትን ጊዜ ይመድባሉ።
ቆራጥ እርምጃ መውሰድ
የዕብራውያኑ አባት ያዕቆብ ለአማቹ የነበረበትን ከፍተኛ ዕዳ በከፈለ ጊዜ “እኔ ደግሞ ለቤቴ የምሠራው መቼ ነው?” በማለት ጠይቆ ነበር። (ዘፍጥረት 30:30) ያዕቆብ እንደ ማንኛውም አባት የቤተሰቡን ቁሳዊ ፍላጎት ማሟላት እንዳለበት ስለተሰማው ይህንን ለማድረግ ጠንክሮ ሠራ። ዘፍጥረት 30:43 “ያ ሰውም እጅግ ባለ ጠጋ ሆነ፤ ብዙም ከብት ሴቶችም ወንዶችም ባሪያዎች ግመሎችም አህዮችም ሆኑለት” በማለት ይናገራል።
ነገር ግን ያዕቆብ ወደ ከነዓን ምድር ከሄደ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሴት ልጁ ዲና አረማዊ ከሆኑ ከነዓናውያን ጋር ቅርርብ የማድረግ አጉል ጠባይ እንዳመጣች አላወቀም ነበር።a (ዘፍጥረት 34:1) እንዲሁም እቤቱ ውስጥ የአምልኮ ዕቃዎች እንዳሉ በተመለከተ ጊዜ እርምጃ አልወሰደም ነበር። የሆነ ሆኖ አንድ ከነዓናዊ ዲናን አስገድዶ በመድፈር አሳዛኝ ሁኔታ ከፈጸመ በኋላ ቆራጥ እርምጃ ወሰደ። “እንግዶቹን አማልክት ከመካከላችሁ አስወግዱ፣ ንጹሐንም ሁኑ” በማለት አዘዘ።—ዘፍጥረት 35:2–4
ክርስቲያን አባቶች የቤተሰባቸውን መንፈሳዊነት በተመለከተ ንቁዎች መሆን አለባቸው። የብልግና ጽሑፎች ወይም መጥፎ ሙዚቃዎች የመሳሰሉ የቤተሰቡን መንፈሳዊ ደህንነት የሚጎዱ ነገሮች እቤት ውስጥ ካሉ ቆራጥ እርምጃ መውሰድ አለባቸው።
እንደ ሣራ፣ ርብቃና ራሔል ያሉትም እምነት የነበራቸው ሴቶች በቤተሰቡ ውስጥ የጎላ ተጽዕኖ ማሳደራቸው ትኩረት የሚስብ ነው። ለባሎቻቸው የሚገዙ ቢሆኑም እንኳ ተገቢና አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ቀዳሚ በመሆን እርምጃ ከመውሰድ ወደ ኋላ አላሉም። ለምሳሌ ያህል ዘጸአት 4:24–26 ሙሴና ቤተሰቡ ወደ ግብጽ ሲሄዱ “እግዚአብሔር [“የይሖዋ መልአክ” ሴፕቱጀንት] ተገናኘው፣ ሊገድለውም [የሙሴን ልጅ] ፈለገ” በማለት ይነግረናል። ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለው ሙሴ ሳይገርዘው በመቅረቱ ምክንያት የሙሴ ልጅ ሊገደል ነበር። ሲፓራ ፈጣን እርምጃ ወስዳ ልጅዋን ገረዘችው። በዚህም ምክንያት መልአኩ ትቶት ሄደ። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያን ሚስቶችም ተገቢ በሚሆንበት ጊዜ ቀዳሚ ሆነው እርምጃ መውሰድ ይችላሉ።
በሙሴ ሕግ ሥር የነበረው አባታዊ መመሪያ
በ1513 ከዘአበ እስራኤል ራሷን የቻለች ብሔር ስትሆን የዕብራውያን አባቶች ዘመን አበቃ። (ዘጸአት 24:3–8) አባቶች የቤተሰብ ራስ ሆነው ማገልገላቸውን ቀጥለው ነበር። ቢሆንም የቤተሰብ ሕግ አምላክ ለሙሴ በሰጠውና የተሾሙ መሳፍንት ተፈጻሚነቱን ከሚቆጣጠሩት ከብሔሩ ሕግ በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ ሆነ። (ዘጸአት 18:13–26) ሌዋዊው ክህነት መሥዋዕት ማቅረብ የመሳሰለውን የአምልኮ ክፍል ተረከበ። ቢሆንም አባት ጠቃሚ ሚና መጫወቱን ቀጥሏል። ሙሴ እንዲህ በማለት አጥብቆ መክሯል፦ “እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስተምረው፣ በቤትህም ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም፣ ስትነሣም ተጫወተው።”—ዘዳግም 6:6, 7
ሕጉ እንደ ማለፍ የመሳሰሉ ቀጥተኛ በሆነና ባልሆነ መንገድ ትምህርት ሊሰጥባቸው የሚችሉ አንዳንድ በዓላት እንዲከበሩ ያዝዝ ነበር። የማለፍ በዓል ቀን ማለትም ኒሳን 14 ሲቃረብ አይሁዳውያን ቤተሰቦች ወደ ኢየሩሳሌም ለሚያደርጉት የተለመደ ጉዞ መዘጋጀት ይጀምሩ ነበር። (ዘዳግም 16:16፤ ከሉቃስ 2:41 ጋር አወዳድር።) እንደነዚህ ባሉ ዝግጅቶች የማይደሰት የትኛው ልጅ ነው? ጉዞው ራሱ በጣም ያስደስታቸው ነበር። ጉዞው የሚደረግበት ጊዜ የክረምቱ ወቅት አብቅቶ የፀደይ ፀሐይ የክረምቱን ብርድ ማስወገድ የምትጀምርበት ጊዜ ነበር። በአርሞንዔም ተራራ ላይ ያለው በረዶ ስለሚቀልጥ የዮርዳኖስ ወንዝ ሞልቶ ይፈስ ነበር።
በመንገዳቸው ላይ ሳሉ አባቶች የመሬታቸውን መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ብቻ ሳይሆን እየተጓዙበት ካለው ቦታ ጋር የተያያዙ ብዙ ታሪኮችን ለልጆቻቸው ማስተማር ይችሉ ነበር። ይህም የሕጉ በረከትና መርገም ተነቦባቸው የነበሩትን የጌባልንና የገሪዛንን ተራሮች ያካትታል። ያዕቆብ ስለ ሰማይ መሰላል ራእይ አይቶበት በነበረው ቤቴልም ያልፉ ይሆናል። በዚህ አማካኝነት የሚያስደስት ውይይት ይከፈታል። ብዙ እየተጓዙ ሲሄዱ ከሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ ተጓዦች ከቤተሰቡ ጋር ሲቀላቀሉ ሁሉም በዚህ የሚያንጽ ጓደኝነት ይደሰቱ ነበር።
በመጨረሻም ቤተሰቡ “በውበትዋ ፍጹም” ወደ ሆነችው ኢየሩሳሌም ይገባል። (መዝሙር 50:2 የ1980 ትርጉም) አልፍሬድ ኤደርሺይም የተባሉት ምሁር እንዲህ ብለዋል፦ “ሃይማኖታዊ ሥርዓት ለማከናወን ከሚጓዙት ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ አብዛኞቹ ከከተማዋ ቅጥር ውጪ መስፈር ነበረባቸው። ከተማዋ ውስጥ ያረፉት ሰዎች ያለምንም ወጪ ይስተናገዱ ነበር።” አዎን፣ ዕብራውያን ልጆች ወንድማማቻዊ ፍቅርና እንግዳ ተቀባይነትን በተመለከተ በዓይናቸው በማየት ትምህርት ያገኙ ነበር። በዛሬው ጊዜ በየዓመቱ የሚደረጉት የይሖዋ ምሥክሮች ትልልቅ ስብሰባዎች የሚያገለግሉት ለዚሁ ዓይነት ዓላማ ነው።
በመጨረሻ ኒሳን 14 ይደርሳል። ለማለፍ በዓል የተዘጋጀው እንስሳ ይታረድና ለረዥም ሰዓታት ይጠበሳል። እኩለ ሌሊት ገደማ ቤተሰቡ ጠቦቱን፣ ያልቦካውን ቂጣና መራራውን ቅጠል ይበላል። በልማዱ መሠረት አንድ ወንድ ልጅ ‘ይህ የምታከናውኑት የአምልኮ ሥርዓት ምንድን ነው?’ ብሎ ይጠይቃል። አባቶች ደግሞ “በግብፅ አገር በእስራኤል ልጆች ቤቶች ላይ አልፎ ግብፃውያንን በመታ ጊዜ፣ ቤቶቻችንን ያዳነ የእግዚአብሔር የማለፉ መሥዋዕት ይህች ናት” በማለት ቀጥተኛ የሆነ ትምህርት ይሰጣሉ።—ዘጸአት 12:26, 27፤ 13:8
የእስራኤሉ ንጉሥ ሰሎሞን ‘ለመሳቅ ጊዜ አለው ለመዝፈንም ጊዜ አለው’ ብሏል። (መክብብ 3:4) እስራኤላውያን ልጆች የመዝናኛ ጊዜ ይመደብላቸው ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ልጆች በገበያ ቦታዎች ሲጫወቱ ተመልክቶ ነበር። (ዘካርያስ 8:5፤ ማቴዎስ 11:16) በተጨማሪም ዐቅሙ የሚፈቅድላቸው ወላጆች ዘፈን፣ ጭፈራና የተትረፈረፈ መብልና መጠጥ ያሉባቸው የተለያዩ ቤተሰቦች አንድ ላይ ተሰባስበው በመጫወት የሚደሰቱባቸውን ዝግጅቶች ማድረግ የተለመደ ነበር። (ሉቃስ 15:25) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉ ወላጆችም በራሳቸው አነሳሽነት ጤናማ የሆኑ መዝናኛዎችንና ከልጆቻቸው ጋር አብረው የሚያሳልፉበትን ጊዜ ያመ ቻቻሉ።
በአይሁድ ኅብረተሰብ ውስጥ የሚገኙ እናቶችና ልጆች
በሙሴ ሕግ ሥር እናቶች ምን ሚና ይጫወቱ ነበር? ምሳሌ 1:8 “ልጄ ሆይ፣ የአባትህን ምክር ስማ፣ የእናትህንም ሕግ አትተው” በማለት ትእዛዝ ይሰጣል። አንዲት አይሁዳዊት ሚስት በባሏ ሥልጣን ሥር በመሆን አምላክ ያወጣቸው ደንቦች በሥራ ላይ እንዲውሉ ታደርጋለች። ካረጀች በኋላ እንኳ ልጆችዋ ሊያከብሯት ይገባ ነበር።—ምሳሌ 23:22
እናት ልጆቿን በማሰልጠን በኩልም ከፍተኛ ድርሻ ነበራት። ሕፃኑ ጡት እስከሚጥልበት ጊዜ ድረስ ሙሉ በሙሉ ትንከባከበዋለች፤ ይህም የቀረበ የእናትና የልጅ ትስስር እንደሚፈጥር አያጠራጥርም። (ኢሳይያስ 49:15) አባት ወንዶች ልጆቹን አንድ ዓይነት ሥራ ሲያሰለጥናቸው እናት ደግሞ ሴቶች ልጆችዋን የቤት ውስጥ ሙያዎችን ታስተምራቸው ነበር። በተጨማሪም እናቶች በወንዶች ልጆቻቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድሩ ነበር። ለምሳሌ ያህል ንጉሡ ልሙኤል “እናቱ ከሰጠችው ቁም ነገር ያዘለ ምክር” ጥቅም አግኝቶ ነበር።—ምሳሌ 31:1 አዓት
በተጨማሪም አንዲት ባለሙያ አይሁዳዊት ሚስት ‘ቤተሰብዋን በመንከባከብ’ በኩል ከፍተኛ ቦታ አላት። ምሳሌ 31:10–31 እንደሚናገረው የቤት ቀለብ መሸመት፣ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን መግዛትና ሌላው ቀርቶ አነስተኛ የንግድ ሥራ ማካሄድ ትችላለች። ለአድናቂ ባል ሚስት ያላት ዋጋ “ከቀይ ዕንቁ እጅግ ይበልጣል።”
ለዘመናችን የሚሆን ምሳሌ
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመናት የነበረው የቤተሰብ ዝግጅት ለሁሉም የቤተሰቡ አባላት ስሜታዊና መንፈሳዊ እድገት አገልግሎ ነበር። አባቶች ቤተሰባቸውን ለመጥቀም ከፈለጉ ባላቸው ሥልጣን በፍቅር መጠቀም ነበረባቸው። በአምልኮ ቀዳሚ መሆን ነበረባቸው። አባቶችም ሆኑ እናቶች ልጆቻቸውን በማስተማርና በማሰልጠን፣ አምልኳቸውን ከእነርሱ ጋር ሆነው በማከናወንና መዝናኛዎችን በማዘጋጀት ለልጆቻቸው ያላቸውን ፍቅር ያሳያሉ። አምላካዊ እናቶች ቀዳሚ በመሆን ለቤተሰባቸው የሚጠቅሙ እርምጃዎችን በሚወስዱበት ጊዜ የባሎቻቸውን የራስነት ሥልጣን በማክበር ዋጋ ያላቸው ረዳቶች መሆናቸው ታይቷል። ታዛዥ ልጆች ወላጆቻቸውንና ይሖዋን አስደስተዋል። በእርግጥም በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበረው አምላክን የሚፈራ ቤተሰብ ለዘመናችን በጣም ጥሩ ምሳሌ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ያዕቆብ ቤተሰቡን ከከነዓናውያን ተጽዕኖ ለመጠበቅ ሲል ከዚህ በፊት ጥብቅ እርምጃዎችን እንደወሰደ ሊታወቅ ይገባል። መሠዊያ ሠርቷል፤ ይህ መሠዊያ ከከነዓናውያን ጎረቤቶቹ የሚለየው ዓይነት አሠራር እንዳለው አያጠራጥርም። (ዘፍጥረት 33:20፤ ዘጸአት 20:24, 25) በተጨማሪም ከሴኬም ከተማ ውጪ የሰፈረ ከመሆኑም በላይ የራሱን የውኃ ጉድጓድ ቆፍሮ ነበር። (ዘፍጥረት 33:18፤ ዮሐንስ 4:6, 12) በዚህ የተነሳ ያዕቆብ ከከነዓናውያን ጋር ቅርርብ እንድትመሠርት እንደማይፈልግ ዲና አሳምራ ታውቅ ነበር።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቤተሰብህ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይሖዋን ያመልኩ እንደነበሩት ቤተሰቦች ደስተኛ ሊሆን ይችላል