ስለ ጊዜው አጣዳፊነት ያላችሁ ስሜት እንዳይቀዘቅዝ ጠብቁት
ይሖዋን በሙሉ ልባችን በማገልገል ለመቀጠል የሚያስችለን አምላክ የሚቀበለው አንዱ የተረጋገጠ መንገድ ምንድን ነው? እውነተኛ የጥድፊያ ስሜት መያዝ ነው። አምላክን በሙሉ ነፍስ ማገልገል ማለት ባለን ነገር ሁሉ እርሱን ማገልገል ማለት ሲሆን ይህም እንድናደርግ የሚጠይቀንን ማንኛውንም ነገር ያለምንም ማወላወል ከልብ መታዘዝን ይጠይቅብናል።
ነቢዩ ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ “አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ” በማለት ሲያዛቸው የዚህን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። (ዘዳግም 6:5) በብዙ መቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ” በማለት ይህንኑ ትእዛዝ ደግሞታል። (ማቴዎስ 22:37) ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የእግዚአብሔርን ፈቃድ ከልብ እንዲፈጽሙ’ ለኤፌሶን ሰዎች ሲነግራቸውና ‘ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደሚያደርጉት የሚሠሩትን ሁሉ በትጋት እንዲያደርጉት’ ለቆላስይስ ሰዎች ሲያሳስባቸው ይህንኑ አስፈላጊ ነገር በተዘዋዋሪ ጠቅሶታል።—ኤፌሶን 6:6 የ1980 ትርጉም ፤ ቆላስይስ 3:23
ነገር ግን የጊዜው አጣዳፊነት በውስጣችን ከሌለ ወይም ደግሞ ስለጊዜው አጣዳፊነት ከዚህ በፊት የነበረን ስሜት ከቀዘቀዘ ምናልባትም ጨርሶ ከጠፋ አምላክን በሙሉ ልባችንና ነፍሳችን ማገልገል ያስቸግረናል። ዛሬ በሰው ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ አጣዳፊ ጊዜ ውስጥ እንኖራለን።
ጥድፊያ ያስፈለገባቸው ጊዜያት
በቅድመ ክርስትና ዘመናት ጥድፊያ ያስፈለገባቸው ብዙ ጊዜያት ነበሩ። የኖኅ ዘመን እንዲሁም ሰዶምና ገሞራ ከመጥፋታቸው ቀደም ብለው የነበሩት ጊዜያት አጣዳፊ ወቅቶች ነበሩ። (2 ጴጥሮስ 2:5, 6፤ ይሁዳ 7) የጥፋት ውኃ ከመምጣቱ በፊት የነበሩት ዓመታት አጣዳፊ በሆኑ እንቅስቃሴዎች የተያዙ እንደነበሩ አያጠራጥርም። ምንም እንኳ ኖኅና ቤተሰቡ የጥፋቱ ውኃ መቼ እንደሚጀምር በትክክል ባያውቁም ያላቸው ‘አምላካዊ ፍርሃት’ ነገ ዛሬ እያሉ ሥራውን እንዳያጓትቱ ረድቷቸዋል።—ዕብራውያን 11:7
በተመሳሳይም ከሰዶምና ገሞራ ጥፋት በፊት መላእክቶቹ ሎጥን ‘በማስቸኮል’ “ራስህን አድን” ብለውት ነበር። (ዘፍጥረት 19:15, 17) አዎን፣ በዚህን ጊዜም ጥድፊያ የጻድቃንን ሕይወት አድኗል። በመቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ በባቢሎን የነበሩ ምርኮኞች “እልፍ በሉ፣ እልፍ በሉ፣ ከዚያ ውጡ፣ ርኩሱን ነገር አትንኩ፣ ከመካከልዋ ውጡ” ተብለው በጥብቅ ተመክረው ነበር። (ኢሳይያስ 52:11) ይህንን አጣዳፊ ትንቢታዊ ትእዛዝ በመከተል በ537 ከዘአበ 200,000 የሚያህሉ ምርኮኞች ከባቢሎን ወጡ።
በእነዚህ ሁኔታዎች የነበረው የጥድፊያ ስሜት በአጣዳፊ ጊዜ እየኖሩ እንዳሉ የሚሰማቸውና ይህንን እምነታቸውን ሕያው አድርገው የያዙ ሰዎች በሙሉ ነፍሳቸው አምላክን እንዲያገለግሉ አድርጓቸዋል።
በክርስትና ዘመናት የነበረው ጥድፊያ
በክርስቲያን ግሪክ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የጥድፊያ አስፈላጊነት በተደጋጋሚ ተጠቅሷል። “ተጠንቀቁ፣” “ትጉ [“ነቅታችሁ ኑሩ” አዓት]፣” “ተዘጋጅታችሁ ኑሩ” የሚሉት አነጋገሮች ክርስቶስ ኢየሱስ በተከታዮቹ ውስጥ ትክክለኛ የጥድፊያ ስሜት ለመትከል የተጠቀመባቸው አገላለጾች ናቸው። (ማቴዎስ 24:42–44፤ ማርቆስ 13:32–37) በተጨማሪም ስለ አሥሩ ቆነጃጅት፣ ስለ ክፉው ባሪያ፣ ስለ መክሊቶቹና በጎቹን ከፍየሎቹ ስለመለየት የተናገራቸው ምሳሌዎች ተዘጋጅቶ ለመጠበቅ ከማነሳሳታቸውም በላይ የጥድፊያ ስሜት እንዲኖር አድርገዋል።—ማቴዎስ 25:1, 14, 15, 32, 33
ኢየሱስ ስለ ጥድፊያ በመናገር ብቻ ሳይወሰን በጥድፊያ በመሥራት የተናገረውን ነገር እውነተኝነት አረጋግጧል። አንድ ጊዜ ሰዎች ወደ ሌላ ቦታ ከመሄድ ባዘገዩት ጊዜ “ስለዚህ ተልኬአለሁና ለሌሎቹ ከተማዎች ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እሰብክ ዘንድ ይገባኛል” በማለት ነግሯቸዋል። (ሉቃስ 4:42,43) በተጨማሪም ‘መከሩ ብዙ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት’ ስለሆኑ የመከሩ ጌታ ተጨማሪ ሠራተኞችን ወደ መከሩ እንዲልክ እንዲለምኑት ደቀ መዛሙርቱን አበረታቷቸዋል። (ማቴዎስ 9:37, 38) እንዲህ ዓይነቱ በሙሉ ልብ ለአምላክ የሚቀርብ ልመና የጥድፊያ ስሜትን ያሳያል።
ተገቢ ያልሆነ ጥድፊያ ነበርን?
አስቀድሞ የተነገረው “ታላቅ መከራ” በብዙ መቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ የሚመጣ ከሆነ በዚያን ጊዜ የጥድፊያ ስሜት ለምን አስፈለገ? በማለት አንዳንዶች ምክንያታዊ ጥያቄ ያነሱ ይሆናል።—ማቴዎስ 24:21
ይህ ሁኔታ ኢያሱስ ተከታዮቹ በመስበኩና በማስተማሩ ሥራ ተጠምደው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ኢየሱስ የተጠቀመበት ማታለያ እንዳልሆነ እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ክርስቶስ ስለ ጥድፊያ ምክር የሰጠው ለዚህ ሳይሆን ለደቀ መዛሙርቱ ፍቅር ስለነበረውና ይሖዋ ስለ ጊዜ ያለውን አመለካከት ሙሉ በሙሉ ስለሚያውቅ ነው። አዎን፣ በአምላክ ዓላማ መሠረት የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም የጥድፊያ መንፈስ እንደሚያስፈልግ ክርስቶስ ኢየሱስ ያውቃል። ከዚህም በተጨማሪ ደቀ መዛሙርቱ እርሱ ተመልሶ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ የጥድፊያ ስሜት ቢኖራቸው ራሳቸው በመንፈሳዊ እንደሚጠቀሙ ያውቅ ነበር።
መሠራት ያለበት ዓለም አቀፋዊ የምሥክርነት ሥራ እንደነበረና ይህም ሥራ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ የሚከናወን እንደሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ በግልጽ አመልክቶ ነበር። (ማቴዎስ 24:14፤ ማርቆስ 13:10) የዚህ ሥራ የእድገት ደረጃዎች የሚታዩት ሥራው እየገፋ ሲሄድ ብቻ ነው። ቢሆንም እያንዳንዱን ደረጃ ለማከናወን ጥድፊያ ያስፈልግ ነበር። “በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” በማለት ኢየሱስ በተናገረ ጊዜ የዚህን ሥራ የእድገት ደረጃ አመልክቷል። (ሥራ 1:8) ሥራው እስካለንበት ጊዜ ድረስ እየገፋ የመጣው በዚህ መንገድ ነው። ይህም የአምላክ አገልጋዮች ስለ ጊዜ ባላቸው እውቀት ላይ ማስተካከያዎችን እንዲያደርጉ ስለሚጠይቅ በተለያዩ ጊዜያት አንዳንድ ያላሰቧቸው ነገሮች አጋጥሟቸዋል።
ክርስቲያናዊ የጥድፊያ ስሜት የይሖዋን ዓላማ ለማስፈጸም አገልግሏል። የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ዝንፍ በማይለው የይሖዋ ፕሮግራም መሠረት ሥራቸውን ደረጃ በደረጃ ለማከናወን ረድቷቸዋል። ስለዚህ ያለፉትን ወደ 2,000 የሚጠጉ ዓመታት መለስ ብለን ስንመለከት መለኮታዊውን ፕሮግራም ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ እንረዳለን።
ክርስቲያናዊ ጥድፊያ ለእስራኤላውያን የተሰጣቸው ልዩ ሞገስ ከሚወሰድበት ማለትም ከ36 እዘአ በፊት በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ፣ በሰማርያ ለሚኖሩና ለተበተኑት አይሁዶች ደቀ መዛሙርቱ የተሟላ ምሥክርነት አንዲሰጡ አስችሏቸዋል። (ዳንኤል 9:27፤ ሥራ 2:46, 47) በተመሳሳይም የአይሁዶች ሥርዓት ብዙም ሳይቆይ እንደሚጠፋ የጥንቱ ጉባኤ ለሁሉም አይሁዶች ግልጽ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጥ የረዳው ክርስቲያናዊ ጥድፊያ ነበር። (ሉቃስ 19:43, 44፤ ቆላስይስ 1:5, 6, 23) እንዲሁም የአይሁዶች ሥርዓት በ70 እዘአ ሳይታሰብ ከጠፋ በኋላ የመጀመሪያ መቶ ዘመን የክርስቶስ ምሥክሮች አስቀድሞ የተነገረለት ክህደት አስከፊ የሆነውን መንፈሳዊ ጨለማ ከማምጣቱ በፊት ስለ ሰማያዊው ተስፋ ለብዙ ሰዎች ለማወጅ የረዳቸው ጥድፊያ ነበር። (2 ተሰሎንቄ 2:3፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:2 አዓት) ክርስቶስ ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው በመካከለኛው ዘመን ባሉት መቶ ዓመታት ጥቂት ስንዴ መሰል ክርስቲያኖች የመንግሥቱን ተስፋ ይዘው ነበር። (ማቴዎስ 13:28–30) በመጨረሻም ይሖዋ በወሰነው ጊዜ ጠንካራና ዘመናዊ ጉባኤ አስነሳ፤ ይህ ጉባኤ በዚህ የመጨረሻ ትውልድ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች የሚነገር አጣዳፊ የፍርድ መልእክት ይዟል።—ማቴዎስ 24:34
በጥንት ዘመን ይኖር የነበረው ዳንኤል “ምን ታደርጋለህ?” በማለት አምላክን እንዳልጠየቀ ሁሉ ታማኝ የሆኑት ዘመናዊ የአምላክ ምሥክሮችም እንዲህ ብለው ለመጠየቅ አይደፍሩም። (ዳንኤል 4:35) ይሖዋ በፕሮግራሙ መሠረት ሥራውን ሠርቶ ለማጠናቀቅ ምን እንደሚያስፈልግ በትክክል እንደሚያውቅ ሙሉ እምነት አላቸው። ስለዚህ ይሖዋ ነገሮችን በምን አቅጣጫ እንደሚያስኬዳቸው ከመጠየቅ ይልቅ አምላክ በዚህ ታሪካዊ ወቅት ከእርሱ ጋር አብረው የመሥራት አጋጣሚ ስለሰጣቸው ይደሰታሉ።—1 ቆሮንቶስ 3:9
የጥድፊያ ስሜት እንዲኖረን የሚያደርግ ተጨማሪ ማበረታቻ
የጥድፊያ ስሜት እንዲኖረን ያስፈለገበት ሌላው ምክንያት ታላቁ መከራ የሚፈነዳበትን ትክክለኛ ቀንና ሰዓት በትክክል መናገር አለመቻላችን ነው። ክርስቶስ ኢየሱስ ቁርጡ የሚለይበትን አስቀድሞ የተወሰነውን ቀንና ሰዓት በምድር ላይ የሚኖር ማንኛውም ፍጡር እንደማያውቅ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:36) በሌላ ጊዜ ደግሞ ለማወቅ ጓጉተው ለነበሩት ሐዋርያቱ “አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም” በማለት ነግሯቸዋል። (ሥራ 1:7) አዎን፣ የመጨረሻው ውጤት ምን እንደሆነ በግልጽ ተቀምጦልናል፤ ቢሆንም ሁሉንም ዝርዝር ጉዳዮች ማወቅ አያስፈልገንም።
ሐዋርያው ጳውሎስ ጥድፊያን በተመለከተ ትክክለኛ አመለካከት ነበረው። “ወንድሞች ሆይ፣ ስለ ዘመናትና ስለ ወራት ምንም እንዲጻፍላችሁ አያስፈልጋችሁም” በማለት ለተሰሎንቄ ሰዎች ስለ ክርስቶስ መገኘት በጻፈላቸው ጊዜ ምናልባት የኢየሱስን ቃላት በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል። (1 ተሰሎንቄ 5:1) ይህንን ደብዳቤ የጻፈው ኢየሱስ “እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” ብሎ ከተናገረ 17 ከሚያክሉ ዓመታት በኋላ ነው። (ሥራ 1:8) በዚያን ጊዜ ይህን ያህል ብዙ የተገለጠ ነገር ስላልነበረ ብዙ የሚጻፍ ነገር አልነበረም። ቢሆንም ክርስቲያኖች በጥድፊያ እየሰበኩ እያለ የይሖዋ ቀን ‘ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፣ እንዲሁ እንደሚሆን’ እርግጠኞች ሊሆኑ ይችላሉ።—1 ተሰሎንቄ 5:2
የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች እነዚህን ቃላት በአእምሯቸው ስለያዙ የይሖዋ ቀን የሚመጣው በመቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ነው በማለት ያሰቡ አይመስልም። ኢየሱስ ወደ ሩቅ አገር ስለሄደው መኮንንና ወደ ሌላ አገር ስለተጓዘው ሰው የተናገራቸውን ምሳሌዎች ያውቁ እንደነበር የታወቀ ነው። በተጨማሪም ምሳሌዎቹ እንደሚያሳዩት መኮንኑ የሚመጣው “በመጨረሻ” እንደሆነ፤ ተጓዡ ሰው ደግሞ ‘ከብዙ ዘመን በኋላ’ እንደሚመለስ ያውቁ ነበር። ነገር ግን “በመጨረሻ” የተባለው መቼ ነው? ‘ከብዙ ዘመን በኋላ’ ማለትስ? አሥር ዓመት? ሃያ ዓመት? ሃምሳ ዓመት? ወይስ ከዚህ የበለጠ ጊዜ ነው? እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎች ግራ እንዳጋቧቸው አያጠራጥርም። (ሉቃስ 19:12, 15 አዓት ፤ ማቴዎስ 25:14, 19) “እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፣ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣል” የሚሉት የኢየሱስ ቃላት ጆሯቸው ላይ ማቃጨላቸውን ቀጥለው ነበር።—ሉቃስ 12:40
ጥድፊያ የሚያስገኘው መልካም ውጤት
አዎን፣ አምላካዊ የሆነ ሰው ሊያድርበት የሚገባው የጥድፊያ ስሜት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችን ከፍተኛ ቦታ በሚሰጣቸው በመስበኩና በማስተማሩ ሥራ እንዲጠመዱ በማድረግ በሚያስገርም ሁኔታ አበረታቷቸዋል። በዛሬው ጊዜም በብዙ መንገዶች ያበረታታናል። እስከዛሬ በሠራነው ሥራ ከመርካት ወይም ‘መልካም ሥራን ለመሥራት ከመታከት’ ይጠብቀናል። (ገላትያ 6:9) በዓለምና ዓለም በሚያቀርባቸው አታላይ የሆኑ ቁሳዊ ነገሮች ከመጠን በላይ እንዳንጠላለፍ ይጠብቀናል። አእምሯችን ‘በእውነተኛው ሕይወት’ ላይ እንዲያተኩር ያስችለናል። (1 ጢሞቴዎስ 6:19) ጌታ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ‘በተኩላዎች መካከል እንዳሉ በጎች’ እንደሆኑ ስለተናገረ ዓለምን ለመዋጋት ያለንን ቁርጥ ውሳኔ እንደያዝን የመቀጠሉን አስፈላጊነት ያውቅ ነበር። አዎን፣ በክርስቲያናዊ የጥድፊያ ስሜታችን በመጠለል ከአደጋ እንጠበቃለን።—ማቴዎስ 10:16
ይሖዋ አምላክ ወደር በሌለው ጥበቡ አማካኝነት አገልጋዮቹ የጥድፊያ ስሜታቸውን እንደያዙ ለመቀጠል የሚያስችላቸውን በቂ መረጃ ሁልጊዜ ይሰጣቸዋል። በዚህ በተበላሸ የነገሮች ሥርዓት ‘የመጨረሻ ቀናት’ ላይ አንደምንገኝ አጥብቆ ያረጋግጥልናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ያለንበት ትውልድ የታላቁ መከራ መደምደሚያ በሆነው አርማጌዶን ከመጥፋቱ በፊት በዓለም ውስጥ ብርሃን አብሪዎች መሆን እንዳለብን ያለማቋረጥ ማሳሰቢያ ይሰጠናል።—ፊልጵስዩስ 2:15፤ ራእይ 7:14፤ 16:14, 16
አዎን፣ አምላካዊ የሆነ ሰው ሊያድርበት የሚገባው የጥድፊያ ስሜት በሙሉ ነፍስ ለይሖዋ የምናቀርበው አገልግሎት ዋነኛ ክፍል ነው። የጥድፊያ ስሜት የአምላክ አገልጋዮች ‘በነፍሳቸው ዝለው እንዲደክሙ’ ዲያብሎስ የሚያደርገውን ሙከራ ከመከላከሉም በላይ ሙከራውን ለማጨናገፍ ይረዳል። (ዕብራውያን 12:3) በማንኛውም ጊዜ በሙሉ ነፍስ የሚቀርብ አምልኮ ማቅረብ የይሖዋ አገልጋዮች እርሱን እንዲታዘዙት ያስችላቸዋል፤ ባለንባቸው የአርማጌዶን ዋዜማ ቀናት ጥልቅ የሆነ ልባዊ የጥድፊያ ስሜት ማሳየት ግን በሙሉ ነፍስ ከሚቀርበው አምልኮ ዋነኛ ክፍል ነው።
“አሜን፣ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ ና” የሚሉትን የሐዋርያው ዮሐንስን ቃላት ማስተጋባታችንን በመቀጠል የጥድፊያ ስሜታችንን እንደያዝን እንድንኖር ይሖዋ አምላካችን ሁላችንንም ይርዳን።—ራእይ 22:20