የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 10/15 ገጽ 29-31
  • ራሳችሁን ከማጽደቅ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ራሳችሁን ከማጽደቅ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ራስን ከፍ ከፍ የማድረግ ዝንባሌ
  • “አትፍረዱ”
  • የተሳሳተ ቅንዓት
  • አምላክ ለትሑቶች ሞገስ ይሰጣል
  • ‘ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠንቀቁ’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • ‘ከእኔ ተማሩ’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • ከሁሉ አስቀድማችሁ ‘የአምላክን ጽድቅ’ መፈለጋችሁን ቀጥሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
  • ሁለት አስፈላጊ ነገሮች—ጸሎትና ትሕትና
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 10/15 ገጽ 29-31

ራሳችሁን ከማጽደቅ ተጠበቁ!

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ፈሪሳውያን ጻድቅ የአምላክ አገልጋዮች የሚል መልካም ስም አግኝተው ነበር። ቅዱሳን ጽሑፎችን በትጋት ያጠኑና ሁልጊዜ ይጸልዩ ነበር። አንዳንድ ሰዎች ደግና ምክንያታዊ እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸው ነበር። የአይሁድ ታሪክ ጸሐፊ የነበረው ጆሴፈስ “ፈሪሳውያን እርስ በርስ ከመፈቃቀራቸውም በላይ ከማኅበረሰቡ ጋር ተስማምቶ የመኖር ባሕል አዳብረው ነበር” በማለት ጽፏል። ምናልባትም በጊዜው በነበረው የአይሁድ ማኅበረሰብ ውስጥ በጣም የተከበሩና ከፍ ተደርገው ይታዩ የነበሩ ግለሰቦች መሆናቸው አያስገ ርምም!

በዛሬው ጊዜ ግን “ፈሪሳዊ” የሚለውና ከእርሱ ጋር የሚዛመዱ ቃላት ሌሎችን የሚያጣጥል የሚል ፍቺ ያላቸው ሲሆን ሃይማኖተኛ ለመምሰል የሚጥር፣ ራሱን የሚያጸድቅ፣ ያለእኔ ሃይማኖተኛ የለም የሚል፣ ከመጠን በላይ ለሃይማኖቱ የሚቀና እና የተናገረውን በተግባር የማያውል ከሚሉት አባባሎች ጋር ይመሳሰላሉ። ፈሪሳውያን ስማቸው የጎደፈው ለምንድን ነው?

ይህ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ አብዛኞቹ አይሁዶች በፈሪሳውያን ውጪያዊ አቋም ስላልተታለለ ነው። ‘በውጭ አምረው ከሚታዩ በውስጥ ግን የሙታን አጥንትና ርኩሰት ከተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮች’ ጋር አመሳስሏቸዋል።—ማቴዎስ 23:27

በአደባባይ ቆመው ለረጅም ሰዓታት ቢጸልዩም ይህን የሚያደርጉት ኢየሱስ እንዳለው ለሰዎች ለመታየት ብለው ነው። አምልኳቸው ማስመሰያ ብቻ ነበር። በምሳ በከበሬታ ቦታዎች፣ በምኩራቦች ደግሞ ፊት በሚገኙ መቀመጫዎች ይቀመጡ ነበር። ምንም እንኳ ሁሉም አይሁዳውያን በልብሳቸው ጫፍ ዘርፍ እንዲያደርጉ ቢታዘዙም ፈሪሳውያን ከመጠን በላይ ረጅም የሆነ ዘርፍ በማድረግ የሰዎችን ትኩረት ይስቡ ነበር። ሰፋፊ አሸንክታቦችን በማንጠልጠል ጉራቸውን ይነዛሉ። (ማቴዎስ 6:5፤ 23:5–8) ግብዝነታቸው፣ ስስታቸውና ትዕቢታቸው በመጨረሻ አዋረዳቸው።

ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት አምላክ ፈሪሳውያንን ውድቅ እንዳደረጋቸው አስታውቋል፦ “እናንተ ግብዞች፣ ኢሳይያስ ስለ እናንተ፦ ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፣ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል።” (ማቴዎስ 15:7–9) በእርግጥም የእነርሱ ጻድቅነት ራስን በማጽደቅ ላይ የተመሠረተ ነበር። ኢየሱስ “ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠበቁ” በማለት ደቀ መዛሙርቱን ማስጠንቀቁ ተገቢ ነበር። (ሉቃስ 12:1) እኛም ራሳችንን የምናጸድቅ ከመሆን ‘መጠበቅ’ ወይም ሃይማኖታዊ ግብዞች ከመሆን መጠንቀቅ አለብን።

ይህን ለማድረግ ራስን የማጽደቅ ዝንባሌ በቅጽበት የሚፈጠር ነገር አለመሆኑን መገንዘብ አለብን። ከዚህ ይልቅ ይህ ዝንባሌ በጊዜ ሂደት የሚፈጠር ነው። እንዲያውም አንድ ሰው ሳይታወቀው አስፈላጊ ያልሆነውን የፈሪሳውያን መለያ ባሕርይ ሊወርስ ይችላል።

ራስን ከፍ ከፍ የማድረግ ዝንባሌ

ራሳችንን ‘መጠበቅ’ ያለብን ከየትኞቹ አንዳንድ ባሕርያት ነው? ራሳቸውን የሚያጸድቁ ግለሰቦች አብዛኛውን ጊዜ “ንግግራቸው፣ አቋማቸውና አመለካከታቸው ፈጽሞ ስህተት ሠርተን አናውቅም እንደሚሉ ያሳያል” በማለት ኢንሳይክሎፔዲያ ኦቭ ሪሊጅን ኤንድ ኤቲክስ ይናገራል። በተጨማሪም ራሳቸውን የሚያጸድቁ ሰዎች ጉረኞችና ራሳቸውን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ ናቸው፤ ይህም የፈሪሳውያን ዋንኛ ችግር ነበር።

ኢየሱስ ይህንን የፈሪሳውያን ዝንባሌ እንዲህ በማለት በምሳሌ ገልጾታል፦ “ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ መቅደስ ወጡ፣ አንዱ ፈሪሳዊ ሁለተኛውም ቀራጭ። ፈሪሳዊው ቆሞ በልቡ ይህን ሲጸልይ፦ እግዚአብሔር ሆይ፣ እንደ ሌላ ሰው ሁሉ፣ ቀማኞችና ዓመፀኞች አመንዝሮችም፣ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ፤ በየሳምንቱ ሁለት ጊዜ እጦማለሁ፣ ከማገኘውም ሁሉ አሥራት አወጣለሁ።” ከዚህ በተለየ መንገድ ቀራጩ ስህተቱን በትሕትና በማመን ከጉረኛው ፈሪሳዊ ይልቅ ጻድቅ እንደሆነ አስመሥክሯል። ኢየሱስ ይህንን ምሳሌ የተናገረው “ጻድቃን እንደ ሆኑ በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎቹን ሁሉ በጣም ለሚንቁ” ሰዎች ነው።—ሉቃስ 18:9–14

ፍጽምና የሌለን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን አንዳንድ ጊዜ ባሉን የተፈጥሮ ችሎታዎች ወይም ባሉን የተሻሉ አጋጣሚዎች ከሌሎች የምንልቅ ሆኖ ሊሰማን ይችላል። ነገር ግን ክርስቲያኖች እንዲህ ያሉትን ሐሳቦች ቶሎ ብለው ከአእምሯቸው ማስወገድ አለባቸው። በክርስቲያናዊ ሕይወት ብዙ ዓመታት አሳልፈህ ሊሆን ይችላል። ጥሩ ችሎታ ያለህ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ ትሆን ይሆናል። ምናልባትም በሰማይ ከኢየሱስ ጋር ለመንገሥ እንደተቀባህ ትናገር ይሆናል። በጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንዶች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች፣ ሽማግሌዎች ወይም ዲያቆናት የመሆን ልዩ መብቶች ያገኛሉ። ‘ይሖዋ እንድሠራው የሰጠኝን ሥራ የበላይነት ስሜት እንዲሰማኝ ስጠቀምበት እንዴት ይሰማዋል?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። ይህ እንደማያስደስተው የተረጋገጠ ነው።—ፊልጵስዩስ 2:3, 4

አንድ ክርስቲያን ከአምላክ ባገኛቸው ችሎታዎች፣ መብቶች ወይም ሥልጣን የተነሳ የበላይነት ስሜት የሚያሳይ ከሆነ ለአምላክ ብቻ የሚገባውን ክብርና ዝና እየሰረቀ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ክርስቲያን “ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ” በግልጽ ይመክራል። “እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፣ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ” በማለት አጥብቆ ይመክረናል።—ሮሜ 12:3, 16

“አትፍረዱ”

አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ኢንሳይክሎፔዲያ እንደተናገረው ራሱን የሚያጸድቅ ሰው “የሕጉን መንፈስ ሳይሆን የሕጉን ፊደል ብቻ ስለጠበቀ በሥነ ምግባር ትክክል እንደሆነ ወይም በአምላክ ዘንድ ትክክለኛ አቋም እንደያዘ አድርጎ ራሱን ይመለከታል።” ሌላኛው ጽሑፍ ደግሞ ራሳቸውን የሚያጸድቁ ሰዎች “ጊዜያቸውን በሙሉ በሌሎች ላይ መጥፎ ነገር በመፈለግ የሚያሳልፉ ከመጠን ያለፉ ሃይማኖተኞች” በማለት ይገልጻቸዋል።

ፈሪሳውያን እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ነበሩ። ውሎ አድሮ ሰው ሠራሽ ሕጎቻቸው ከአምላክ ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች ይበልጥ አስፈላጊ መስለው ነበር። (ማቴዎስ 23:23፤ ሉቃስ 11:41–44) ራሳቸውን ፈራጆች ከማድረጋቸውም በላይ የራሳቸውን የጽድቅ ሕግጋት በማያሟላ ማንኛውም ሰው ላይ ይፈርዱ ነበር። የበላይ የመሆን ዝንባሌያቸውና ከልክ በላይ በራሳቸው መተማመናቸው ሌሎች ሰዎችን በቁጥጥራቸው ሥር እንዲያደርጉ ገፋፍቷቸዋል። ኢየሱስን በቁጥጥራቸው ሥር ማድረግ አለመቻላቸው ስላስቆጣቸው ሊገድሉት አሴሩ።—ዮሐንስ 11:47–53

ሁልጊዜ አጠገቡ ባለው ሰው ሁሉ ላይ ስህተት በመፈለግ፣ ቀረብ ብሎ በመመርመርና በመቆጣጠር ራሱን ፈራጅ ከሚያደርግ ሰው ጋር አብሮ መሆን ደስ አያሰኝም። በጉባኤ ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው የራሱን አስተሳሰብና ያወጣቸውን ሕግጋት በሌሎች ላይ የመጫን ሥልጣን የለውም። (ሮሜ 14:10–13) ሚዛናዊ የሆኑ ክርስቲያኖች በዕለታዊ ሕይወት የሚያጋጥሙን ብዙ ነገሮች ለግል ውሳኔ የተተዉ እንደሆኑ ያውቃሉ። በተለይ ከሌሎች ፍጽምና የሚጠብቁና በቀላሉ የማይረኩ ሰዎች በሌሎች ላይ ከመፍረድ መራቅ አለባቸው።

እርግጥ የክርስቲያን ጉባኤ የይሖዋ ምድራዊ ድርጅት ያለ ችግር እንዲንቀሳቀስ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ መመሪያዎችን የማውጣት ሥልጣን አለው። (ዕብራውያን 13:17) ቢሆንም አንዳንዶች እነዚህን መመሪያዎች አዛብተዋቸዋል ወይም የራሳቸውን ሕግጋት ጨምረውባቸዋል። በአንድ አካባቢ ሁሉም የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ንግግር ሲያቀርቡ ሙሉ ልብስ መልበስና ኮታቸውን መቆለፍ ነበረባቸው። ይህንን የማያደርግ ተማሪ ወደፊት ክፍል አይሰጠውም ነበር። እንዲህ ያሉ ጥብቅ ሕግጋት ከማውጣት ይልቅ የሚያስፈልገውን መመሪያ ደግነት በተሞላበት ሁኔታ መስጠት ይበልጥ ምክንያታዊነትና የአምላክ ቃል ከያዘው መንፈስ ጋር የሚስማማ አይሆንምን?—ያዕቆብ 3:17

ራሳቸውን የሚያጸድቁ ሰዎች አንድ ክርስቲያን ብዙ የግል ችግሮች ካጋጠሙት መንፈሳዊ ድክመት አለበት የሚለውን አመለካከት ሊያስፋፉ ይችላሉ። በራሳቸው ዓይን ጻድቅ የሆኑት ኤልፋዝ፣ በልዳዶስና ሶፋር ታማኝ ስለሆነው ኢዮብ ያሰቡት ልክ እንደዚሁ ነበር። ኢዮብ ስለደረሰበት ሁኔታ የተሟላ ግንዛቤ ስላልነበራቸው ኢዮብን አጥፍተሃል ብለው መውቀስ አይገባቸውም ነበር። በኢዮብ ላይ ስለደረሰው መከራ የተዛባ መደምደሚያ ላይ ስለደረሱ ይሖዋ ገስጿቸዋል።—ኢዮብ ምዕራፍ 4, 5, 8, 11, 18, 20​ን ተመልከት።

የተሳሳተ ቅንዓት

ራስን ማጽደቅና ቅንዓት ብዙውን ጊዜ ይዛመዳሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ ሃይማኖታዊ ዝንባሌ ስላላቸው አይሁዶች እንዲህ ብሏል፦ “በእውቀት አይቅኑ እንጂ ለእግዚአብሔር እንዲቀኑ እመሰክርላቸዋለሁና። የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውንም ጽድቅ ሊያቆሙ ሲፈልጉ፣ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም።” (ሮሜ 10:2, 3) ጳውሎስ ራሱ ቀድሞ ፈሪሳዊ እንደመሆኑ መጠን ከፍተኛ ቅንዓት የነበረው ቢሆንም ቅንዓቱ በይሖዋ ጽድቅ ላይ ስላልተመሠረተ የተሳሳተ ቅንዓት ነበር።—ገላትያ 1:13, 14፤ ፊልጵስዩስ 3:6

መጽሐፍ ቅዱስ “እጅግ ጻድቅ አትሁን፣ እጅግ ጠቢብም አትሁን፣ እንዳትጠፋ” በማለት መምከሩ ተገቢ ነው። (መክብብ 7:16) ጉባኤ ውስጥ አንድ ክርስቲያን ትጉህ መሆን ይጀምር ይሆናል፤ ቢሆንም ትጋቱና ቅንዓቱ ራሱን እንዲያጸድቅ ሊያደርገው ይችላል። ሃይማኖታዊ ቅንዓት ከይሖዋ ጽድቅ ይልቅ በሰብዓዊ ጥበብ የሚመዘን ከሆነ ሌሎችን ሊጎዳ ይችላል። እንዴት?

ለምሳሌ ወላጆች የሌሎችን መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት ሲዋከቡ የራሳቸውን ቤተሰብ ችላ ሊሉ ይችላሉ። ወይም ልጆቻቸው ሊያደርጉት የማይችሉትን እንዲያደርጉ በመጠየቅ ወላጆች ከመጠን በላይ ቅንዓታቸውን ሊያሳዩ ይችላሉ። (ኤፌሶን 6:4፤ ቆላስይስ 3:21) አንዳንድ ልጆች እንዲህ ያሉትን ምክንያታዊ ያልሆኑ ጥያቄዎች ማሟላት ሲያቅታቸው ሁለት ዓይነት ኑሮ በመኖር ችግሩን ይወጡታል። ምክንያታዊ ወላጅ የቤተሰቡን ዓቅም ግምት ውስጥ በማስገባት ተገቢ ማስተካከያዎችን ያደርጋል።—ከዘፍጥረት 33:12–14 ጋር አወዳድር።

ከመጠን ያለፈ ቅንዓት ዘዴኛ፣ በሌላው ቦታ ሆኖ የሰውን ችግር መረዳትና ለስላሳ መሆን የመሳሰሉትን ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት አስፈላጊ የሆኑትን ባሕርያት ሊያሳጣን ይችላል። አንድ ሰው የመንግሥቱን ሥራዎች ለማፋጠን ጠንክሮ ይሠራ ይሆናል። ቢሆንም ያለው ከፍተኛ ቅንዓት እግረ መንገዱን ሰዎችን ሊጎዳ ይችላል። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “ትንቢትም ቢኖረኝ፣ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፣ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፣ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም።”—1 ቆሮንቶስ 13:2, 3

አምላክ ለትሑቶች ሞገስ ይሰጣል

ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን ራስን የማጽደቅ ባሕርይ እንዳለብንና እንደሌለብን ከማደጉ በፊት ለይተን ማወቅ ያስፈልገናል። የበላይ የመሆን ዝንባሌን፣ በሌሎች ላይ የመፍረድን ጠባይና በሰብዓዊ ጥበብ ላይ የተመሠረተ ጭፍን ቅንዓትን ማስወገድ አለብን።

ከፈሪሳውያን አመለካከቶች ‘መጠበቅ’ ስላለብን ራሳቸውን እንደሚያጸድቁ ሰዎች በሌሎች ላይ ከመፍረድ ይልቅ በራሳችን ዝንባሌዎችና ጠባዮች ላይ ማተኮር የተሻለ ነው። እውነት ነው ኢየሱስ በፈሪሳውያን ላይ ከመፍረዱም በላይ ዘላለማዊ ጥፋት የሚገባቸው “የእፉኝት ልጆች” እንደሆኑ በመናገር አውግዟቸዋል። ቢሆንም ኢየሱስ የሰዎችን ልብ ያነብ ነበር። እኛ ግን ይህንን ማድረግ አንችልም።—ማቴዎስ 23:33

የራሳችንን ሳይሆን የአምላክን ጽድቅ እንፈልግ። (ማቴዎስ 6:33) መጽሐፍ ቅዱስ “ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፣ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፣ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” በማለት ሁላችንንም ስለሚመክረን የይሖዋን ሞገስ የምናገኘው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው።—1 ጴጥሮስ 5:5

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ