ወግ ከእውነት ጋር በሚጋጭበት ጊዜ
ለመጠጥነት የማያገለግል አደገኛ ውኃ። እንደዚህ ያሉ ማስጠንቀቂያዎችን መመልከቱ የተለመደ ሊሆን ይችላል። በተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች አንዳንድ የውኃ ምንጮች መርዘኛ በሆኑ ኬሚካሎች እየተበከሉ መሆናቸውን ስለሚያውቁ ለሚጠጡት ነገር ይጠነቀቃሉ። ከዚህ ብክለት የተነሳ ውኃ “ሕይወትን ጠብቆ የሚያቆይ” ከመሆን ይልቅ “የበሽታ ተዋህስያንንና . . . መርዘኛ ኬሚካሎችን የሚያዛምት” ሊሆን እንደሚችል አንድ ጥናት አሳይቷል።—ዎተር ፖሉሽን
የእውነትን ውኃዎች መበከል
ከእውነት ጋር የሚጋጩ ወጎች ልክ እንደተበከሉ የውኃ ምንጮች ናቸው። በቅን ልቦና መርዘኛ ኬሚካል በሆኑት በውሸት፣ በሚያሳስቱ ሐሳቦችና በፍልስፍናዎች የተበከሉ ወጎችን ማለትም ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የመጣ እውቀት፣ አስተሳሰብ፣ እምነት ወይም ልማድ አጥብቀን ይዘን ሊሆን ይችላል። የተበከለ ውኃ ጉዳት እንዳለው ሁሉ እነዚህም ወጎች የከፋ ጉዳት ይኸውም መንፈሳዊ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ።
የምንከተላቸው በወግ ላይ የተመሠረቱ ሃይማኖታዊ እምነቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ቢመስለንም እንኳ ሁላችንም ጊዜ ወስደን በጥንቃቄ ልንመረምራቸው ይገባል። ማርቲን ሉተር በጊዜው የነበረውን በወግ ላይ የተመሠረተ እምነት በመከተል ኮፐርኒከስን ሲያወግዝ የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ እንዳለው አድርጎ ያምን እንደነበር አስታውስ። ቢሆንም ሉተር ‘የሰሙት ነገር ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን በመመርመር ረገድ ልበ ሰፊዎች የሆኑት’ የጥንቶቹ የቤሪያ ሰዎች የተዉትን ግሩም ምሳሌ ሳይከተል ቀርቷል።—ሥራ 17:10, 11
በወግ ላይ የተመሠረቱ እምነቶች በኢየሱስ ዘመን በነበሩ አንዳንድ አይሁዶች ላይ ያስከተሉትን ጉዳት አስብ። አይሁዶች ወጎቻቸው እውነት እንደሆኑ አጥብቀው ያምኑ ነበር። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ወግ አይጠብቁም በማለት በተቃወሙ ጊዜ ኢየሱስ “እናንተስ ስለ ወጋችሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለ ምን ትተላለፋላችሁ?” ብሎ በመጠየቅ የተሳሳቱ መሆናቸውን ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 15:1–3) ስህተታቸው ምን ላይ ነበር? ኢየሱስ “የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል [አምላክን]” በማለት ኢሳይያስ የተናገረውን በጠቀሰ ጊዜ ችግሩ ምን እንደነበረ አመልክቷል።—ማቴዎስ 15:9 ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን፤ ኢሳይያስ 29:13
አዎን፣ ከአምላክ በመጡ እውነቶች ፋንታ ከሰዎች ከዚያም አልፎ ከአጋንንት የሚመነጩ ሐሳቦችን ተክተዋል። ለምሳሌ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለው መጽሐፍ በጥራዝ 1 ገጽ 506 ላይ እንዲህ ይላል፦ “በዚያን ጊዜ የነበሩት ፈሪሳውያን አንድ ሰው ንብረቱ ‘ቁርባን’ ወይም ለአምላክ የሚሰጥ መባ እንዲሆን አንድ ጊዜ ከወሰነ ወላጆቹ ችግረኞች ቢሆኑም እንኳ የእነርሱን ችግር ለመፍታት ሊጠቀምበት አይችልም፤ ከፈለገ ግን እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ራሱ ሊጠቀምበት ይችላል ብለው ያስተምሩ ነበር።” የእውነትን ውኃዎች የበከለው የሰው ጥበብ በአይሁዶች መንፈሳዊነት ላይ መጥፎ ተጽዕኖዎች አሳድሮ ነበር። ሌላው ቀርቶ አብዛኞቹ አይሁዶች ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ሲጠበቅ የነበረውን መሲሐቸውን አንቀበልም ብለዋል።
ሕዝበ ክርስትና ለብክለቱ ተጨማሪ አስተዋጽኦ አበርክታለች
ከኢየሱስ ሞት በኋላም ተመሳሳይ መንፈሳዊ ብክለት ደርሷል። የኢየሱስ ተከታዮች እንደሆኑ የሚናገሩ ብዙ ሰዎች አዲሶቹ ትምህርቶች የመጡት በቃል ከተላለፈው ወግ እንደሆነ አድርገው ያስቡ ነበር። በማክሊንቶክ እና ስትሮንግ የተዘጋጀው ሳይክሎፔድያ ኦቭ ቢብሊካል፣ ቲኦሎጂካል ኤንድ ኤክሌዚያስቲካል ሊትሬቸር እንደሚናገረው አንዳንድ ክርስቲያን ተብዬዎች እንደዚህ ያለው ወግ “የመጀመሪያዎቹ ቤተ ክርስቲያኖች ከሐዋርያት አፍ የሰሙት፣ ከሐዋርያት ዘመን የተላለፈና እነርሱ እስከኖሩበት ዘመን ድረስ በንጽሕና ተጠብቆ የቆየ ትምህርት” እንደሆነ ተሰምቷቸዋል።—ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።
ሐቁ ግን ከእነዚህ ወጎች አብዛኞቹ የተሳሳቱ ሐሳቦች የያዙ ቆሻሻ ወጎች ናቸው። ከላይ የተጠቀሰው ሳይክሎፔድያ እንደገለጸው እነዚህ አዳዲስ ፍልስፍናዎች “ከሌሎች ወጎች ጋር ብቻ ሳይሆን በእጃቸው ካሉት ሐዋርያት ከጻፏቸው ጽሑፎች ጋር የሚጋጩ” ነበሩ። ይህ ሁኔታ አያስገርምም። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን እንዲህ በማለት አስጠንቅቆ ነበር፦ “እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፣ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ።”—ቆላስይስ 2:8
በዛሬው ጊዜም የሚገኙት በወግ ላይ የተመሠረቱ አብዛኞቹ እምነቶች ‘ሐዋርያት ከጻፏቸው ጽሑፎች ጋር ይጋጫሉ።’ ሕዝበ ክርስትና እንደ ሥላሴ፣ እሳታማ ሲኦል፣ የሰው ነፍስ አለመሞት፣ ብሔርተኝነትና የጣዖት አምልኮ በመሳሰሉ ስፍር ቁጥር በሌላቸው አጋንንታዊ አስተሳሰቦች የእውነትን ውኃ በክላዋለች።a (1 ጢሞቴዎስ 4:1–3) ራሳቸውን በወግ ላይ ለተመሠረቱት የሕዝበ ክርስትና አጋንንታዊ ትምህርቶች ያጋለጡ ሰዎች መንፈሳዊ በሽታ እንደያዛቸው ታሪክ ይመሠክራል።—ከኢሳይያስ 1:4–7 ጋር አወዳድር።
እንደነዚህ ያሉ እውነትን የመበከል ተግባሮች ሰው ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ቀጥለዋል። ሰይጣን በኤደን ገነት በጀመረው የሰውን አእምሮ በውሸቶችና በማታለያዎች የመመረዝ ተግባሩ ገፍቶበታል። (ዮሐንስ 8:44፤ 2 ቆሮንቶስ 11:3) ከኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ በኋላ የሰው ቤተሰብ በመላው ምድር ሲሰራጭ ሆን ተብሎ በአጋንንታዊ ፍልስፍናዎችና ሐሳቦች የተመረዘው ሰብዓዊ እውቀት በሁሉም ዓይነት ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሷል።
መንፈሳዊ ብክለት የሚያስከትለው ጉዳት
እንዲህ ያለው መንፈሳዊ ብክለት ምን ጉዳት ሊያስከትል ይችላል? የሚያስከትለውን ጉዳት የተበከለ ውኃ በአካላዊ ጤንነታችን ላይ ከሚያስከትለው ጉዳት ጋር ልናወዳድረው እንችላለን። አንድ ምሁር እንዳሉት፦ “200 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች የተበከለ ውኃ ከቆዳ ጋር ሲነካካ የሚመጣው ሺስቶሶሚያሲስ (ቢልሃርዚያ) [የደም ማነስ፣ የሕመም ስሜት፣ የጤንነት መቃወስ አልፎ ተርፎም ሞት የሚያስከትል በቀንድ አውጣ የሚመጣ በሽታ ነው] የተባለ በሽታ ሰለባ ሆነዋል። አምስት መቶ ሚልዮን ሰዎች ለዓይነ ስውርነት ዋነኛ ምክንያቶች ከሆኑት በሽታዎች መካከል አንዱ በሆነው ትራኮማ ተይዘዋል። ይህ የሆነው በቆሻሻ ውኃ ስለሚታጠቡ ነው። . . . ሁለት ቢልዮን ሰዎች ንጹሕ የመጠጥ ውኃ አያገኙም።” (አወር ካንትሪ፣ ዘ ፕላኔት) በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሐሰተኛ በሆኑ የአጋንንት ትምህርቶች የተበከሉ ወጎችን ስለሚከተሉ በመንፈሳዊ ሁኔታ አቅም አጥተዋል፣ ታውረዋል አልፎ ተርፎም ሞተዋል።—1 ቆሮንቶስ 10:20, 21፤ 2 ቆሮንቶስ 4:3, 4
ለምሳሌ ብዙ ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስና በአባቱ በይሖዋ አምላክ መካከል ያለው ዝምድና ግራ አጋብቷቸዋል ወይም ዝምድናውን እንዳያውቁ ታውረዋል። ክርስቲያን እንደሆኑ የሚናገሩ አንዳንድ ሰዎች ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ቅዱስ ስም በክርስቲያን ግሪክ ጽሑፎች ውስጥ አለማስገባታቸው የተለመደ ሆኗል። ጆርጅ ሀዋርድ ጆርናል ኦቭ ቢብሊካል ሊትሬቸር በተባለው መጽሐፍ ላይ “የይሖዋን ስም የሚያመለክቱትን አራቱን የዕብራይስጥ ፊደላት ማስቀረቱ ከአሕዛብ የመጡት የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በ‘ጌታ አምላክ’ እና ‘በጌታ ክርስቶስ’ መካከል ያለው ዝምድና እንዲደናገርባቸው ያደረገ ይመስለናል” ብለዋል።
የሰው ነፍስ አትሞትም የሚለው ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ወግ ያስከተለውንም ግራ መጋባት፣ አጉል እምነትና ፍርሃት አስብ። (ከመክብብ 9:5ና ከሕዝቅኤል 18:4 ጋር አወዳድር።) በቀድሞ አባቶች አምልኮ የተያዙ ወይም ሙታን ሊጎዱን ይመጣሉ በሚለው የማያቋርጥ ፍርሃት ሥር ያሉ ምን ያህል ሰዎች ናቸው? እንዲያውም ይህ እምነት ሰዎች ራሳቸውንና ሌሎችን እንዲገድሉ አበረታቷቸዋል።
ብዙ ጃፓናውያን ስንሞት ወጥተው የሚሄዱት መንፈሶቻችን ከሞት በኋላ ባለው ሕይወት ይገናኛሉ ብለው ያምናሉ። በዚህም ምክንያት ራሳቸውን ያጠፉ አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውንም መግደል ጥሩ መስሎ ተሰምቷቸዋል። አን ኢንግሊሽ ዲክሽነሪ ኦቭ ጃፓኒዝ ዌይስ ኦቭ ቲንኪንግ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ጃፓን ውስጥ ራስን መግደል ሁልጊዜ አይወገዝም። ከዚህ ይልቅ አንድ ሰው ለሠራው ከባድ ኃጢአት ይቅርታ የሚጠይቅበት ተቀባይነት ያለው መንገድ ተደርጎ ይታያል። . . . እንዲያውም ሰዎች ራሳቸውንና የራሳቸውን ቤተሰብ አባላት በጠቅላላ እንደገደሉ ሲነገር የሚጠቀሙባቸው ቃላት ሁኔታውን የሚደግፉ ናቸው።”
ወጎችን መርምር
በወግ ላይ የተመሠረቱ እምነቶችንና ልማዶችን በጭፍንነት መከተሉ የሚያስከትለውን አደጋ ግምት ውስጥ በማስገባት ምን ማድረግ አለብን? ሐዋርያው ዮሐንስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ማብቂያ አካባቢ እንደ እርሱ ላሉ ክርስቲያኖች የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል፦ “ወዳጆች ሆይ፣ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፣ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ [ልክ ውኃ ንጹሕ ወይም የተበከለ መሆኑን እንደምትመረምሩ፤] ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና።” (1 ዮሐንስ 4:1፤ በተጨማሪም 1 ተሰሎንቄ 5:21ን ተመልከት።) አንድ ወግ መጥፎ መሆኑንና አለመሆኑን እንዴት ታውቃለህ? ምን ማመን እንዳለብህ ለመፈተን እውነተኛ የሆነ የንጽሕና መለኪያ ያስፈልግሃል።
መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ መጽሐፍ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ “በእውነትህ ቀድሳቸው ቃልህ እውነት ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 17:17) በተጨማሪም “በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 4:23) የአምላክን ቃል በመጠቀም የተበከሉ ውኃዎች በሆኑት የሰዎችና የአጋንንት ፍልስፍናዎች ፋንታ የእውነትን ንጹሕ ውኃዎች ታገኛለህ።—ዮሐንስ 8:31, 32፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16
መጠኑ ትንሽ የሆነ መርዘኛ ነገር የከፋ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል አትርሳ። አንዳንድ ጊዜ መርዙ የሚያስከትላቸው ውጤቶች ከመገለጣቸው በፊት ዓመታት ይፈጃል። የቀድሞው የዓለም የአካባቢ ጥበቃ ማኅበር ፕሬዚዳንት የሆኑት ሽሬዴዝ ራምፋል “ቆሻሻ ውኃ የዓለማችን ከፍተኛ ገዳይ ሆኗል። በቆሻሻ ውኃ በመጠቀማቸው የተነሳ በየዕለቱ ቢያንስ 25 ሺህ ሰዎች ይሞታሉ” ብለዋል። በመንፈሳዊ ሁኔታም የተበከሉ ወጎች ከዚህ ይበልጥ አደገኞች ናቸው።
ለብዙ ዓመታት የተከተልካቸው በወግ ላይ የተመሠረቱ እምነቶች ከእውነት ጋር እንደሚጋጩ ብታውቅ እነዚህን እምነቶች ለመተው ድፍረቱ አለህን? የሚሰጡትን ማስጠንቀቂያዎች ሰምተህ እርምጃ ውሰድ። የያዝካቸው ወጎች ንጹሕ ከሆነው የአምላክ የእውነት ቃል ጋር የሚስማማ መሆኑን በማረጋገጥ ራስህንና ቤተሰብህን ከአደጋ ጠብቅ።—መዝሙር 19:8–11፤ ምሳሌ 14:15፤ ሥራ 17:11
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እነዚህ ትምህርቶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት እንደሌላቸው ለማረጋገጥ ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት። ይህ መጽሐፍ ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀ ነው።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክ የእውነት ቃል ኩልል ያለ ንጹሕ ውኃ እንደሚወርድበት ወንዝ ነው