የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 12/1 ገጽ 9-14
  • ተስፋ አትቁረጡ!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ተስፋ አትቁረጡ!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሌሎች ቅር ሲያሰኙን
  • ኃጢአት ስንሠራ
  • የሚገባንን ያህል እንዳላደረግን ሲሰማን
  • ብዙ የሚፈለግብን ሲሆን
  • መጨረሻው እስካሁን ባለመምጣቱ
  • ይሖዋ ለደከሙት ኃይል ይሰጣል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • የወደፊቱን ጊዜ “በትኩረት ተመልከት”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020
  • የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኛል—መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ስሜት ለማሸነፍ ሊረዳኝ ይችላል?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
  • የበደለኛነት ስሜት ሁልጊዜ መጥፎ ነው?
    ንቁ!—2002
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 12/1 ገጽ 9-14

ተስፋ አትቁረጡ!

“ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት።”—ገላትያ 6:9

1, 2. (ሀ) አንድ አንበሳ የሚያድነው በምን በምን መንገዶች ነው? (ለ) ሰይጣን በተለይ ለማጥመድ የሚፈልገው ማንን ነው?

አንድ አንበሳ የሚያድንባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉት። አንዳንድ ጊዜ እንስሳቱ ውኃ በሚጠጡበት ቦታ ወይም በሚያልፉ በሚያገድሙበት መንገድ አጠገብ አድፍጦ ይጠብቃል። ይሁንና አንዳንድ ጊዜ ይላል ፖርትሬትስ ኢን ዘ ዋይልድ የተባለው መጽሐፍ “የሜዳ አህያ ውርንጭላ ተኝታ የምትገኝበትን ዓይነት ሌሎች አጋጣሚዎችን ይጠቀማል።”

2 ሐዋርያው ጴጥሮስ ባላጋራችን “ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራል” ሲል ገልጿል። (1 ጴጥሮስ 5:8) ሰይጣን የቀረው ጊዜ አጭር እንደሆነ ስለሚያውቅ ሰዎች አምላክን ከማገልገል ዘወር እንዲሉ ለማድረግ ይህ ነው የማይባል ግፊት እያደረገ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ‘የሚያገሳ አንበሳ’ ዒላማውን በተለይ ያነጣጠረው በአምላክ አገልጋዮች ላይ ነው። (ራእይ 12:12, 17) ለማደን የሚጠቀምበት ዘዴ በአራዊት ዓለም ያለው አንበሳ ከሚጠቀምበት ዘዴ ጋር ተመሳሳይ ነው። እንዴት?

3, 4. (ሀ) ሰይጣን የይሖዋ አገልጋዮችን ለማጥመድ ምን ዘዴዎች ይጠቀማል? (ለ) የምንኖረው በእነዚህ “አስጨናቂ” የሆኑ የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ ስለሆነ ምን ጥያቄዎች ይነሣሉ?

3 ሰይጣን አምላክን ማገልገላችንን እንድናቆም ለማድረግ ሲል ለአምላክ ያለንን ታማኝነት ለማጉደፍ የታቀደ ስደት ወይም ተቃውሞ በማምጣት አድፍጦ ሊያጠምደን የሚሞክርበት ጊዜ አለ። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) ከዚህ ሌላ ደግሞ ልክ እንደ አንበሳው ዲያብሎስም የሚያገኛቸውን አጋጣሚዎች ይጠቀማል። ተስፋ እስክንቆርጥ ወይም እስክንዝል ድረስ ይጠብቅና በተደቆሰው ስሜታችን ተጠቅሞ እጃችንን እንድንሰጥ ለማድረግ ይሞክራል። በቀላሉ በሰይጣን እጅ ውስጥ መውደቅ አይኖርብንም!

4 ይሁንና ዛሬ የምንኖረው በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ከታዩት ጊዜያት ሁሉ ይበልጥ አስቸጋሪ በሆነው ወቅት ላይ ነው። “አስጨናቂ” በሆኑት በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ብዙዎቻችን አልፎ አልፎ ተስፋ ልንቆርጥና በሐዘን ልንዋጥ እንችላለን። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) እንግዲያውስ በቀላሉ በዲያብሎስ እጅ ውስጥ ለመውደቅ የተመቻቸን እስክንሆን ድረስ እንዳንዝል ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? አዎን ሐዋርያው ጳውሎስ “ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት” ሲል በመንፈስ ተገፋፍቶ የሰጠውን ምክር መከተል የምንችለው እንዴት ነው?—ገላትያ 6:9

ሌሎች ቅር ሲያሰኙን

5. ዳዊት እንዲዝል ያደረገው ነገር ምን ነበር? ይሁንና ምን አላደረገም?

5 በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ከፍተኛ የታማኝነት አቋም የነበራቸው የይሖዋ አገልጋዮች እንኳ በሐዘን የተዋጡበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። መዝሙራዊው ዳዊት “በጭንቀቴ ደክሜያለሁ፤ ሌሊቱን ሁሉ አልጋዬን አጥባለሁ፣ በዕንባዬም መኝታዬን አርሳለሁ። ዓይኔ ከቁጡ ዕንባ የተነሣ ታወከች” ብሏል። ዳዊት እንደዚህ የተሰማው ለምን ነበር? “ከጠላቶቼ ሁሉ የተነሣ” ነው በማለት ምክንያቱን ገልጿል። ሰዎች የፈጸሙበት ጎጂ ነገር እንባው እንደ ውኃ እስኪፈስ ድረስ ልቡን አቁስሎት ነበር። ይህም ሆኖ ግን ዳዊት ሌሎች ሰዎች ክፉ አደረጉብኝ ብሎ ከይሖዋ አልራቀም።—መዝሙር 6:6–9

6. (ሀ) ሌሎች የሚናገሩት ወይም የሚያደርጉት ነገር ሊነካን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) አንዳንዶች በሰይጣን ወጥመድ በቀላሉ ለመያዝ ራሳቸውን ያመቻቹት እንዴት ነው?

6 በተመሳሳይም ሌሎች የሚናገሩት ወይም የሚያደርጉት ነገር ልባችንን ሊያቆስለንና እንድንዝል ምክንያት ሊሆን ይችላል። ምሳሌ 12:18 [የ1980 ትርጉም] “ያለ ጥንቃቄ የተነገረ ቃል እንደ ሰይፍ ያቆስላል” ይላል። ይህ አሳቢነት የጎደለው ሰው ክርስቲያን ወንድም ወይም እህት ከሆነ ደግሞ ‘ቁስሉ’ ይበልጥ ጥልቅ ሊሆን ይችላል። ሰዎች እንደመሆናችን መቆጣት ምናልባትም ቂም መያዝ ይቀናን ይሆናል። በተለይ ደግሞ ደግነት ወይም ፍትሕ የጎደለው ነገር እንደተፈጸመብን ከተሰማን ይህን ማድረግ ይቀናን ይሆናል። ያስቀየመንን ሰው ማነጋገር በጣም ሊከብደን ይችላል፤ ሆነ ብለን ከእርሱ ወይም ከእርሷ ለመራቅ እንጥር ይሆናል። አንዳንዶች ኃይለኛ ቅሬታ ስላደረባቸው ተስፋ ቆርጠው ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መምጣት አቁመዋል። በዚህ መንገድ ሰይጣን በቀላሉ እንዲያጠምዳቸው ‘ፈንታ መስጠታቸው’ የሚያሳዝን ነው።—ኤፌሶን 4:27

7. (ሀ) ሌሎች ቅር ሲያሰኙን ወይም በደል ሲፈጽሙብን በሰይጣን እጅ የምንወድቅበትን መንገድ ከማመቻቸት መቆጠብ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ቂም መያዝ የማይገባን ለምንድን ነው?

7 ሌሎች ሰዎች ቅር ሲያሰኙን ወይም ሲበድሉን በሰይጣን እጅ ከመውደቅ መራቅ የምንችለው እንዴት ነው? ቂም ላለመያዝ መጣር ይኖርብናል። ከዚህ ይልቅ ግን በተቻለ ፍጥነት ሰላም ለመፍጠር ወይም ችግሮቹን ለመፍታት ቀዳሚዎች ሁኑ። (ኤፌሶን 4:26) ቆላስይስ 3:13 [አዓት] “ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው . . . በነጻ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ” በማለት ይመክረናል። በተለይ ደግሞ በደሉን የፈጸመው ሰው ጥፋቱን አምኖ ከልቡ ከተጸጸተ ይቅር ማለታችን ተገቢ ነው። (ከመዝሙር 32:3–5 እና ከምሳሌ 28:13 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ አንድን ሰው ይቅር ማለት የፈጸመብንን በደል ችላ ብሎ ማለፍ ወይም የጥፋቱን ክብደት ማቃለል ማለት እንዳልሆነ ማስታወሳችን ይረዳናል። ይቅር ማለት ቂም አለመያዝን ይጨምራል። ቂም ከባድ ሸክም ነው። ሐሳባችንን ሁሉ ሊቆጣጠርና ደስታችንን ሊያሳጣን ይችላል። ጤንነታችንን እንኳ ሳይቀር ሊያቃውስ ይችላል። ነገር ግን በተገቢው ጊዜ ይቅር ባይ መሆን ጥቅሙ ለእኛም ጭምር ነው። ሰዎች እንዲህ አሉኝ ወይም እንዲህ አደረጉብኝ ብለን ተስፋ መቁረጥና ከይሖዋ መራቅ አይኖርብንም፤ ከዚህ ይልቅ ዳዊትን ልንመስለው ይገባል።

ኃጢአት ስንሠራ

8. (ሀ) አንዳንዶች አልፎ አልፎ ከፍተኛ የጥፋተኝነት ስሜት የሚሰማቸው ለምንድን ነው? (ለ) ራሳችንን እስክንጠላ ድረስ በጥፋተኛነት ስሜት መዋጣችን ምን አደጋ አለው?

8 ያዕቆብ 3:2 “ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለን” ይላል። በዚህ ወቅት የጥፋተኝነት ስሜት ቢሰማን እንግዳ ነገር አይደለም። (መዝሙር 38:3–8) በተለይ ደግሞ ከሥጋ ድካማችን ጋር ትግል ገጥመን ከሆነና አልፎ አልፎ ሥጋችን የሚያሸንፈን ከሆነ የጥፋተኛነት ስሜቱ ይበልጥ ጠንካራ ሊሆን ይችላል።a እንዲህ ዓይነት ትግል የነበረባት አንዲት ክርስቲያን እንዲህ ስትል ገልጻለች፦ “የፈጸምኩት ኃጢአት ይቅርታ የሌለው ይሁን አይሁን ሳላረጋግጥ በሕይወት መቀጠል አልፈለግሁም ነበር። ከእንግዲህ ወዲህ ምንም ዋጋ የለኝም ብዬ ስላሰብኩ በይሖዋ አገልግሎት በትጋት መካፈል የምችል መስሎ አልተሰማኝም።” ራሳችንን እስክንጠላ ድረስ ይህን ያህል በጥፋተኝነት ስሜት ከተዋጥን ለሰይጣን መንገድ እንከፍትለትና ወዲያው ያንን አጋጣሚ ሊጠቀምበት ይችላል! (2 ቆሮንቶስ 2:5–7, 11) በዚህ ወቅት የሚያስፈልገው ስለ ፈጸምነው ጥፋት ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት መያዝ ሊሆን ይችላል።

9. በአምላክ ምሕረት ላይ ትምክህት ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው?

9 ኃጢአት ስንሠራ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ የጥፋተኝነት ስሜት ቢሰማን ተገቢ ነው። ይሁንና አንድ ክርስቲያን በምንም ዓይነት የአምላክ ምሕረት እንደማይገባው አድርጎ ካሰበ ይህ የጥፋተኝነት ስሜት ለረጅም ጊዜ ይዘልቃል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን “ኃጢአታችንን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው” በማለት ጠንካራ ማረጋገጫ ይሰጠናል። (1 ዮሐንስ 1:9) የእኔን ኃጢአት ይቅር አይለኝም ብለን የምናስብበት ምክንያት ይኖራልን? ይሖዋ በቃሉ ውስጥ “ይቅር ለማለት ዝግጁ” መሆኑን እንደተናገረ አትዘንጉ። (መዝሙር 86:5 አዓት፤ 130:3, 4) ሊዋሽ አይችልምና ንስሐ የሚገባ ልብ ይዘን ወደ እርሱ እስከቀረብን ድረስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የገባውን ቃል ይፈጽማል።—ቲቶ 1:2

10. የሥጋን ድካም መዋጋትን አስመልክቶ ቀደም ሲል የወጣ አንድ መጠበቂያ ግንብ ምን አስደሳች ማበረታቻ ሰጥቶ ነበር?

10 አንድን መጥፎ ልማድ ለማሸነፍ ጥረት እያደረግህ ብትሆንና አልፎ አልፎ በዚህ ልማድ ብትሸነፍ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ተስፋ አትቁረጥ! አንድን የተሳሳተ ድርጊት መልሰህ መፈጸምህ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ያደረግኸውን መሻሻል ሁሉ መና ያስቀረዋል ማለት አይደለም። የዚህ መጽሔት የየካቲት 15, 1954 እትም ከዚህ ቀጥሎ ያለውን አስደሳች ማበረታቻ ሰጥቶ ነበር፦ “ቀደም ሲል እንከተለው በነበረው አኗኗር ካሰብነው በላይ ሥር የሰደደ አንድ መጥፎ ልማድ በተደጋጋሚ እንድንደናቀፍ ወይም እንድንወድቅ ሊያደርገን ይችል [ይሆናል]። . . . ተስፋ አትቁረጡ። ምሕረት የማይገባው ኃጢአት ሠርቻለሁ ብላችሁ አትደምድሙ። ሰይጣን እንዲህ ብላችሁ እንድታስቡ ይፈልጋል። ማዘናችሁና በራሳችሁ መናደዳችሁ ራሱ ልትስተካከሉ የምትችሉ መሆናችሁን የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ከልባችሁ የአምላክን ምሕረት ለማግኘት፣ በፊቱ ንጹሕ ሆናችሁ ለመታየትና እርዳታውን ለማግኘት ፈልጋችሁ በትሕትና ወደ እርሱ ለመቅረብ አትታክቱ። አንድ ልጅ ችግር ሲገጥመው ወደ አባቱ እንደሚሮጥ ሁሉ በአንድ ዓይነት ድክመት የቱንም ያህል በተደጋጋሚ ብትወድቁ ይሖዋ ይገባናል በማንለው ደግነቱ ይረዳችኋልና ወደ እርሱ ቅረቡ። በቅን ልቦና ከቀረባችሁት ንጹሕ ሕሊና እንድታገኙ ይረዳችኋል።”

የሚገባንን ያህል እንዳላደረግን ሲሰማን

11. (ሀ) በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ስለመካፈል ምን ዓይነት ስሜት ሊኖረን ይገባል? (ለ) አንዳንድ ክርስቲያኖች በአገልግሎት መካፈልን በተመለከተ ከምን ዓይነት ስሜቶች ጋር ይታገላሉ?

11 የመንግሥቱ ስብከት ሥራ በአንድ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያለው ከመሆኑም በላይ በዚህ ሥራ የሚደረገው ተሳትፎ ደስታ ያመጣል። (መዝሙር 40:8) ሆኖም አንዳንድ ክርስቲያኖች በአገልግሎቱ አሁን ከሚሠሩት የበለጠ ለመሥራት ባለመቻላቸው ከባድ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማቸዋል። እንዲህ ያለው የጥፋተኝነት ስሜት ይሖዋ የሚገባንን ያህል ፈጽሞ እንዳልሠራን አድርጎ እንደሚያየን እያሰብን ደስታችንን እንድናጣና ተስፋ እንድንቆርጥ ሊያደርገን ይችላል። አንዳንዶች ከምን ዓይነት ስሜቶች ጋር እንደሚታገሉ ተመልከት።

ከባለቤቷ ጋር ሆና ሦስት ልጆችን የምታሳድግ አንዲት ክርስቲያን እህት እንደሚከተለው ስትል ጽፋለች፦ “ድህነት ምን ያህል ጊዜ እንደሚያባክን ታውቃላችሁ? በተቻለኝ አቅም ገንዘብ መቆጠብ ይኖርብኛል። ይህ ደግሞ ያገለገሉ ዕቃዎች መሸጫ ሱቆችን፣ ታላቅ ቅናሽ የሚል ማስታወቂያዎች የተለጠፉባቸውን ቦታዎች ፍለጋ ወይም ልብሶችን በመስፋት እንኳ ሳይቀር ብዙ ጊዜ ማጥፋት ይኖርብኛል ማለት ነው። ምግብ [በቅናሽ የሚገኝባቸውን] ኩፖኖች እየሰበሰብኩ በዓይነት በዓይነታቸው ካስቀመጥኩ በኋላ የማልፈልጋቸውን ኩፖኖች በሌላ ለመለወጥ በየሳምንቱ አንድ ወይም ሁለት ሰዓት አጠፋለሁ። አንዳንዴ ይህን ጊዜ በአገልግሎት ማሳለፍ ነበረብኝ ብዬ ስለማስብ እነዚህን ነገሮች በመሥራቴ የጥፋተኛነት ስሜት ይሰማኛል።”

አራት ልጆችና የማያምን ባል ያላት አንዲት እህት እንደሚከተለው ብላለች፦ “የሚፈለግብኝን ያህል ለይሖዋ ፍቅር እንደሌለኝ ሆኖ ተሰማኝ፤ ስለዚህ ለይሖዋ ከማቀርበው አገልግሎት ጋር ትንቅንቅ ያዝሁ። የተቻለኝን ሁሉ አደረግሁ፤ ይሁን እንጂ በቂ እንደሆነ ፈጽሞ ተሰምቶኝ አያውቅም። ለራሴ ጥሩ ግምት አልነበረኝም ማለት ነው፤ በዚህ ምክንያት ይሖዋ ለእርሱ የማቀርበውን አገልግሎት ይቀበላል ብዬ ለማሰብ እንኳ ተቸግሬ ነበር።”

የሙሉ ጊዜ አገልግሎቷን ማቋረጥ ግድ የሆነባት አንዲት ክርስቲያን እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋን ሙሉ ጊዜ ለማገልገል የገባሁትን ቃል ለመፈጸም አለመቻሌ ሊዋጥልኝ አልቻለም። ምን ያህል ተበሳጭቼ እንደነበር ለመገመት ያስቸግራችኋል! አሁን ትዝ ሲለኝ አለቅሳለሁ።”

12. አንዳንድ ክርስቲያኖች በአገልግሎት የበለጠ ለመሥራት ባለመቻላቸው ከባድ የጥፋተኛነት ስሜት የሚሰማቸው ለምንድን ነው?

12 ሙሉ በሙሉ አቅማችን የፈቀደልንን ያህል ይሖዋን ለማገልገል መፈለጋችን ተገቢ ነው። (መዝሙር 86:12) ይሁንና አንዳንዶች ይበልጥ ለመሥራት ባለመቻላቸው ምክንያት ከባድ የጥፋተኛነት ስሜት የሚሰማቸው ለምንድን ነው? አንዳንዶች እንዲህ ዓይነት ስሜት ያደረባቸው ምናልባት በሕይወታቸው ውስጥ በደረሰባቸው አንድ አሳዛኝ ገጠመኝ ምክንያት ለራሳቸው ጥሩ ግምት ስለሚያጡ ይሆናል። ተገቢ ያልሆነ የጥፋተኛነት ስሜት የሚፈጠርበት ሌላው መንገድ ደግሞ ይሖዋ ስለሚጠብቅብን ነገር ከእውነታው የራቀ አመለካከት መያዝ ሊሆን ይችላል። አንዲት ክርስቲያን “አንድ ሰው ድክም እስኪል ድረስ ካልሠራ ሠርቷል የሚባልም አይመስለኝም ነበር” ስትል ተናግራለች። በዚህ ምክንያት ከአቅሟ በላይ የሆኑ ደንቦችን ለራሷ አወጣች፤ ከዚያ በኋላ ያወጣቻቸውን ደንቦች መፈጸም ሳይሆንላት ሲቀር ደግሞ ከበፊቱ የበለጠ የጥፋተኝነት ስሜት ተሰማት።

13. ይሖዋ ከእኛ የሚጠብቀው ምንድን ነው?

13 ይሖዋ ከእኛ የሚጠብቀው ምንድን ነው? ባጭሩ ይሖዋ ከእኛ የሚጠብቀው ሁኔታችን የሚፈቅድልንን ያህል እያደረግን በሙሉ ልባችን እንድናገለግለው ነው። (ቆላስይስ 3:23) ይሁን እንጂ ልናደርገው በምንፈልገው እና በተጨባጭ ልናደርገው በምንችለው ነገር መካከል ትልቅ ልዩነት ሊኖር ይችላል። ዕድሜ፣ ጤንነት፣ የሰውነት ጥንካሬ ወይም የቤተሰብ ኃላፊነት የመሳሰሉት ነገሮች ሊገድቡን ይችላሉ። የሆነ ሆኖ የምንችለውን ሁሉ ካደረግን ለይሖዋ የሙሉ ልብ አገልግሎት እንዳቀረብን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን፤ ይህ ደግሞ ጤንነታቸውና ሁኔታቸው ፈቅዶላቸው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ የሚገኙት ከሚያቀርቡት የሙሉ ነፍስ አገልግሎት አያንስምም አይበልጥምም።—ማቴዎስ 13:18–23

14. ከራስህ ምክንያታዊ የሆነ ምን ነገር መጠበቅ እንደምትችል ለመወሰን እርዳታ ካስፈለገህ ምን ልታደርግ ትችላለህ?

14 እንግዲያውስ ከራስህ ልትጠብቀው የምትችለው ምክንያታዊ የሆነ ነገር ምን እንደሆነ እንዴት ልትወስን ትችላለህ? ይህን በተመለከተ የአንተን ችሎታና ያሉብህን የአቅም ገደቦች እንዲሁም የቤተሰብ ኃላፊነቶች ከሚያውቅ የታመነና የጎለመሰ ክርስቲያን ጓደኛህ አለዚያም ከአንድ ሽማግሌ ወይም ተሞክሮ ያላት እህት ጋር ለመወያየት ትመርጥ ይሆናል። (ምሳሌ 15:22) በአምላክ ፊት ያለህ ዋጋ በመስክ አገልግሎት በምትሠራው ሥራ መጠን እንደማይለካ አስታውስ። ሁሉም አገልጋዮቹ ለይሖዋ ውድ ናቸው። (ሐጌ 2:7፤ ሚልክያስ 3:16, 17) በስብከቱ ሥራ የምታደርገው ተሳትፎ ከሌሎች ሊበልጥ ወይም ሊያንስ ይችላል፤ ይሁን እንጂ ምርጥህን እስከ ሰጠህ ድረስ ይሖዋም ይደሰታል፣ አንተም የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማህ አይገባም።—ገላትያ 6:4

ብዙ የሚፈለግብን ሲሆን

15. ከጉባኤ ሽማግሌዎች ብዙ የሚጠበቀው በምን መንገዶች ነው?

15 ኢየሱስ “ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል” ብሏል። (ሉቃስ 12:48) በእርግጥም የጉባኤ ሽማግሌ ሆነው ከሚያገለግሉት ‘ብዙ ይፈለግባቸዋል።’ እንደ ጳውሎስ እነርሱም ጉባኤዎችን ለማገልገል ራሳቸውን ያቀርባሉ። (2 ቆሮንቶስ 12:15) ንግግር ለመስጠት ዝግጅት ይጠይቅባቸዋል፣ የእረኝነት ጉብኝት ያደርጋሉ፣ የፍርድ ጉዳዮችን ይመለከታሉ፤ ይህን ሁሉ ደግሞ የሚያደርጉት የቤተሰብ ኃላፊነቶቻቸውን ችላ ሳይሉ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 3:4, 5) አንዳንድ ሽማግሌዎች ደግሞ የመንግሥት አዳራሾች ሲገነቡ በመርዳት፣ በሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች ውስጥ በመሥራት እንዲሁም በወረዳና በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ በፈቃደኛነት በማገልገል በሥራ ይጠመዳሉ። እነዚህ ለሥራቸው ፍቅር ያላቸው ታታሪ ሠራተኞች ይህን ሁሉ ኃላፊነት ተሸክመው ሳይዝሉ መቀጠል የሚችሉት እንዴት ነው?

16. (ሀ) ዮቶር ለሙሴ የሰጠው ምን ዓይነት ተግባራዊ የሆነ መፍትሔ ነበር? (ለ) አንድ ሽማግሌ አንዳንድ ኃላፊነቶችን ለሌሎች እንዲያጋራ የሚያስችለው ምን ዓይነት ባሕርይ ነው?

16 ትሑትና አቅሙን የሚያውቅ ሰው የነበረው ሙሴ የሌሎችን ችግር ለመፍታት ደፋ ቀና ሲል በደከመ ጊዜ አማቱ ዮቶር ኃላፊነቶቹን ብቃት ላላቸው ወንዶች እንዲያካፍል ጠቃሚ ምክር ሰጥቶታል። (ዘጸአት 18:17–26፤ ዘኁልቁ 12:3) ምሳሌ 11:2 ‘በትሑታን [አቅምና ቦታቸውን በሚያውቁ] ዘንድ ጥበብ ትገኛለች’ ይላል። እዚህ ላይ የገባው “ሞደስት” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ያሉብንን የአቅም ገደቦች መገንዘብና አምኖ መቀበል የሚል ትርጉም አለው። አቅሙንና ቦታውን የሚያውቅ ሰው ለሌሎች ኃላፊነት ለማጋራት አያመነታም ወይም ብቃት ላላቸው ሌሎች ወንዶች ተገቢውን ኃላፊነት በማካፈሉ ምናልባት ያለኝን ቦታ አጣለሁ ብሎ አይሰጋም።b (ዘኁልቁ 11:16, 17, 26–29) እንዲያውም እድገት እንዲያደርጉ ለመርዳት ዝግጁ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 4:15

17. (ሀ) የጉባኤ አባላት የሽማግሌዎችን ሸክም ሊያቀሉላቸው የሚችሉት እንዴት ሊሆን ይችላል? (ለ) የሽማግሌዎች ሚስቶች ምን ዓይነት መሥዋዕትነት ይከፍላሉ? ይህንንስ እንደ ቀላል ነገር እንደማንመለከተው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

17 የሽማግሌዎችን ሸክም በማቃለል ረገድ የጉባኤው አባላት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ። ሽማግሌዎች የሚያስተዳድሩት ቤተሰብ እንዳላቸው ስለሚገነዘቡ ሌሎች ሳያስፈልግ የሽማግሌዎችን ጊዜና ትኩረት አይሻሙም። የሽማግሌዎች ሚስቶች ባሎቻቸው ጉባኤውን በማገልገል ብዙ ሰዓታት እንዲያሳልፉ ሲሉ በፈቃደኛነት የሚከፍሉትን መሥዋዕትነት እንደ ቀላል ነገር አይመለከቱትም። ባሏ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግል አንዲት የሦስት ልጆች እናት እንዲህ ብላለች፦ “ባሌ ሽማግሌ ሆኖ እንዲያገለግል ስል በፈቃደኛነት ስለተሸከምኳቸው ተጨማሪ የቤት ውስጥ ኃላፊነቶች አማርሬ አላውቅም። የእርሱ አገልግሎት ለቤታችን የይሖዋን የተትረፈረፈ በረከት እንዳስገኘልን አውቃለሁ፤ በዚህ የሚያጠፋው ጊዜና ጉልበት አስቆጭቶኝ አያውቅም። ባለቤቴ ሥራ ስለሚበዛበት ብዙውን ጊዜ ጓሯችንን የምንከባከበውና ለልጆቻችን ምክርና ተግሣጽ የመስጠቱን ተግባር በአብዛኛው የማከናውነው እኔ ነኝ።” የሚያሳዝነው ግን ይህች እህት የተሸከመችውን ተጨማሪ ሸክም ከማድነቅ ይልቅ “አቅኚ የማትሆኚው ለምንድን ነው?” የሚሉትን የመሳሰሉ አሳቢነት የጎደላቸው አስተያየቶች የሚሠነዝሩ አጋጥመዋታል። (ምሳሌ 12:18) ሌሎችን ሊያደርጉት በማይችሉት ነገር ከመኮነን ይልቅ እያደረጉ ስላሉት ነገር ማመስገን እንዴት ይበልጥ የተሻለ ይሆናል!—ምሳሌ 16:24፤ 25:11

መጨረሻው እስካሁን ባለመምጣቱ

18, 19. (ሀ) ዛሬ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የምናደርገውን ሩጫ የምናቆምበት ጊዜ ያልሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ሐዋርያው ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ለነበሩት ክርስቲያኖች ምን ወቅታዊ ምክር ሰጥቷቸው ነበር?

18 አንድ ሯጭ ረጅም ርቀት ከሮጠ በኋላ ወደ መጨረሻው እንደቀረበ ካወቀ የቀረውን ርቀት ለመጨረስ አይታክትም። ምናልባት ሰውነቱ ዝሎ፣ በጣም ሞቆት፣ በውስጡ ያለው ፈሳሽ ተንጠፍጥፎ አልቆ ጉልበቱ ሁሉ ተሟጦ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ይህን ያህል ወደ መጨረሻው ከቀረበ በኋላ ሩጫውን አያቆምም። በተመሳሳይም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን የሕይወትን ሽልማት ለማግኘት በሚደረግ ሩጫ ላይ ከመሆናችንም በላይ ሩጫችንን ወደምንጨርስበት መስመር በጣም ተቃርበናል። አሁን ሩጫችንን የምናቆምበት ጊዜ አይደለም!—ከ1 ቆሮንቶስ 9:24​ና ከፊልጵስዩስ 2:16፤ 3:13, 14 ጋር አወዳድር።

19 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖችም ተመሳሳይ ሁኔታ ገጥሟቸው ነበር። በ61 እዘአ ገደማ ሐዋርያው ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ለሚገኙት ክርስቲያኖች ጽፎላቸው ነበር። ጊዜው እየተሟጠጠ ነበር፤ ክፉው “ትውልድ” ማለትም የከሃዲዎቹ አይሁዳውያን የነገሮች ሥርዓት ‘ሊያልፍ’ የቀረው ጊዜ ጥቂት ነበር። በተለይ በኢየሩሳሌም የነበሩት ክርስቲያኖች ንቁዎችና ታማኞች ሆነው መገኘት ነበረባቸው፤ ዙሪያቸውን በወታደር ተከብበው ሲያዩ ከተማዋን ጥለው መውጣት ያስፈልጋቸው ነበር። (ሉቃስ 21:20–24, 32) በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ “በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ” ሲል የሰጠው ምክር ለጊዜው የሚስማማ ነበር። (ዕብራውያን 12:3) ሐዋርያው ጳውሎስ እዚህ ላይ ‘መድከም’ (ካምኖ) እና ‘መዛል’ (ኤክሊዮማይ) የሚል ትርጉም ያላቸውን ሁለት ግሶች ተጠቅሟል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንዳሉት ከሆነ “ሩጫቸውን ጨርሰው ከገቡ በኋላ ተጥመልምለው መሬት ላይ የሚወድቁትን ሯጮች ለማመልከት አርስቶትል እነዚህን የግሪክኛ ቃላት ተጠቅሟል። [የጳውሎስ ደብዳቤ] አንባቢዎች በዚያን ወቅት ገና በሩጫ ላይ ነበሩ። የመጨረሻ ግባቸው ላይ ሳይደርሱ ተስፋ መቁረጥ አይኖርባቸውም። ሰውነታቸው ዝሎና ተዝለፍልፈው እንዲወድቁ መፍቀድ አልነበረባቸውም። መከራዎችን ተጋፍጦ የመጽናቱ አስፈላጊነት ዛሬም እንደተጠበቀ ነው።”

20. የጳውሎስ ምክር ዛሬ ላለነው ሰዎች ወቅታዊ የሆነው ለምንድን ነው?

20 የጳውሎስ ምክር ዛሬ ላለነው ክርስቲያኖች እንዴት ወቅታዊ ነው! ችግሮች ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመሩ በሚሄዱበት በአሁኑ ጊዜ እግሮቹ ተሽመድምደው ሊወድቅ እንደደረሰ ሯጭ የምንሆንባቸው ጊዜያት ይኖሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ ወደ መጨረሻው መሥመር ይህን ያህል ከተቃረብን በኋላ መታከት አይኖርብንም! (2 ዜና መዋዕል 29:11) ‘እንደሚያገሳ አንበሳ’ የሆነው ባላጋራችን የሚፈልገውም ይህንኑ ነው። ይሖዋ ‘ለደከሙት ኃይል’ የሚሰጥባቸው ዝግጅቶች በማድረጉ አመስጋኞች ነን። (ኢሳይያስ 40:29) ስለ እነዚህ ዝግጅቶች ምንነትና እኛ እንዴት ልንጠቀምባቸው እንደምንችል በሚቀጥለው ርዕስ ይብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ለምሳሌ ያህል አንዳንዶች እንደ ግልፍተኝነት ከመሳሰለው በውስጣቸው ሥር የሰደደ የግል ባሕርያቸው ጋር ወይም ደግሞ እንደ ማስተርቤሽን ያሉትን ችግሮች ለማሸነፍ ትግል ይኖርባቸው ይሆናል።—በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተሙትን የእንግሊዝኛ ንቁ! ግንቦት 22, 1988 ገጽ 19–21፤ ኅዳር 8, 1981 ገጽ 16–20 እንዲሁም ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 198–211 ተመልከት።

b በጥቅምት 15, 1992 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 20–3 ላይ የወጣውን “ሽማግሌዎች ኃላፊነታችሁን ለሌሎችም አካፍሉ!” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

◻ ሌሎች ቅር ሲያሰኙን ወይም አንድ ዓይነት በደል ሲፈጽሙብን ተስፋ ሳንቆርጥ መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?

◻ ተስፋ እንዳንቆርጥ የሚረዳን ስለ ፈጸምነው ጥፋት ምን ዓይነት ሚዛናዊ አመለካከት መያዛችን ነው?

◻ ይሖዋ ከእኛ የሚጠብቅብን ምንድን ነው?

◻ አቅምንና ቦታን ማወቅ ሽማግሌዎችን ከመዛል ሊጠብቃቸው የሚችለው እንዴት ነው?

◻ ጳውሎስ በዕብራውያን 12:3 ላይ የሰጠው ምክር ዛሬ ለእኛ ወቅታዊ የሆነው ለምንድን ነው?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ