ስጦታ የተወሰነ ጊዜ ጠብቆ የሚደረግ ነውን?
ብዙውን ጊዜ ስጦታ የሚሰጠው በባህል አስገዳጅነት እንደሆነ ታውቅ ይሆናል። በአብዛኞቹ ባህሎች ስጦታዎች የሚሰጡባቸው የተወሰኑ ጊዜያት አሉ። እነዚህ ስጦታዎች የአክብሮት ምልክት ወይም የፍቅር መግለጫ እንደሆኑ ተደርገው ሊታዩ ይችላሉ። አብዛኞቹ ስጦታዎች ተቀባዮቹ ፈጽሞ አይገለገሉባቸውም፤ ሌሎቹ ደግሞ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማሟላት የሚያገለግሉና ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ናቸው።
በዴንማርክ አንድ ልጅ ሲወለድ ወዳጅ ዘመድ ለሕፃኑ ይጠቅማል ብለው ያሰቧቸውን ስጦታዎች ይዘው ይሄዳሉ። በሌሎች አገሮች ደግሞ የቤተሰቡ ወዳጆች አንድ ላይ በመሰባሰብ የልጁን መወለድ በናፍቆት እንደሚጠባበቁ ለማሳየት ስጦታዎችን ይዘው ይመጣሉ።
ብዙውን ጊዜ ሰዎች በዓመታዊ በዓላት ወቅት ስጦታ ይሰጠናል ብለው ይጠብቃሉ። ምንም እንኳ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች እንዲህ ያሉ በዓላትን ባያከብሩም እነዚህ በዓላት ክርስቲያን ነን በሚሉና ክርስቲያን ባልሆኑ ሰዎች ዘንድ በጣም የተለመዱ ሆነዋል። በአንዳንድ ባህሎች ልጆች እያደጉ ሲሄዱ በልደት ቀናቸው ይሰጣቸው የነበረው ስጦታ እየቀረ ሊሄድ ይችላል፤ በግሪክ ያለው ልማድ ግን ከዚህ የተለየ ነው። በግሪክ የልደት ቀን ከፍተኛ ቦታ ይሰጠዋል። በተጨማሪም የአንድ ሰው “የስሙ ቀን” ሲደርስ ስጦታዎች ያበረክቱለታል። “የስም ቀን” ምንድን ነው? ሰዎች በሃይማኖታዊ ልማድ የተነሳ እያንዳንዱን ቀን “በቅዱሳን” ስም የሰየሙ ሲሆን ብዙ ሰዎች ደግሞ “በቅዱሳን” ስም ይጠራሉ። በአንድ “ቅዱስ” የተሰየመው ቀን ሲደርስ በዚያ ስም የሚጠሩ ሰዎች ስጦታ ይሰጣቸዋል።
ኮሪያውያን ከልጆቻቸው የልደት በዓል በተጨማሪ የልጆች ቀን የሚባል ብሔራዊ በዓል አላቸው። ይህ በዓል ቤተሰቦች ሽርሽር የሚሄዱበትና የልደት ቀናቸው መቼም ቢሆን ለልጆች ስጦታ የሚሰጥበት ጊዜ ነው። ከዚህም በላይ ልጆች ለወላጆቻቸው ስጦታ የሚሰጡበት የወላጆች ቀን እንዲሁም ተማሪዎች ለአስተማሪዎች ያላቸውን አክብሮት የሚገልጹበትና ለአስተማሪዎቻቸው ስጦታ የሚሰጡበት የአስተማሪዎች ቀን አላቸው። በኮሪያውያን ልማድ መሠረት አንድ ሰው 60 ዓመት ሲሞላው ትልቅ ድግስ ይደገሳል። ቤተሰብና ጓደኞች እዚህ ዕድሜ ላይ ለደረሰው ሰው ረጅም ዕድሜና ደስታ እንዲኖረው ያላቸውን ምኞት ከመግለጻቸውም በላይ ስጦታ ይሰጡታል።
በብዙ ባህሎች ሰዎች ስጦታ የሚጠብቁበት ሌላው አጋጣሚ ሠርግ ነው። በኬንያ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ሲጋቡ የሙሽራው ቤተሰብ ለሙሽሪቷ ቤተሰብ ስጦታ እንዲሰጥ ይጠበቅበታል። እንግዶችም ስጦታ ያመጣሉ። ሙሽሪትና ሙሽራው ባህላዊውን ሥርዓት የሚከተሉ ከሆነ መድረክ ላይ ይቀመጡና እንግዶቹ ስጦታቸውን ያቀርቡላቸዋል። እያንዳንዱ ሰው ስጦታ ሲያበረክት “እከሌ ለሙሽሮቹ ስጦታ አምጥቷል” ተብሎ በማስታወቂያ መልክ ይነገርለታል። አብዛኞቹ ሰዎች ስጦታ አምጥተው ሳይነገርላቸው ከቀረ በጣም ያዝናሉ።
በሊባኖሳውያን ባህል ደግሞ አንድ ሰው ሲያገባ ጓደኞች፣ ጎረቤቶች ሌላው ቀርቶ ሙሽሮቹን በደንብ የማያውቁ ሰዎች ጭምር ከሠርጉ በኋላ ባሉት ቀናት ስጦታ ይዘው ይመጣሉ። ስጦታ መስጠት ልክ ብድርን እንደ መክፈል ራሱን የቻለ ኃላፊነት እንደሆነ ከልጅነታቸው ጀምሮ ይነገራቸዋል። አንድ ሊባኖሳዊ ሰው “እንዲህ ካላደረግህ ቅር ይልሃል። ባህል ነው” ብለዋል።
ይሁን እንጂ በብዙ አገሮች ሰዎች በይበልጥ ስጦታ ይሰጠኛል ብለው የሚጠብቁት ገና ሲደርስ ነው። አንተ በምትኖርበት አካባቢ ያለው ሁኔታ እንደዚህ አይደለምን? በቅርቡ በ1990 በተሰጠው ግምት አሜሪካውያን በየዓመቱ ለገና ስጦታ ከ40 ቢልዮን ዶላር የሚበልጥ ገንዘብ ያወጣሉ። ይህ በዓል ጃፓን ውስጥ በሚገኙ ቡድሂስቶችና የሺንቶ እምነት ተከታዮችም ዘንድ በጋለ ስሜት ይከበራል፤ እንዲሁም በዓሉ በአውሮፓ፣ በደቡብ አሜሪካና በአንዳንድ የአፍሪካ ክፍሎች በተለያዩ መንገዶች ይከበራል።
ሰዎች ገና ደስተኛ የሚሆኑበት ጊዜ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ደስተኛ ለመሆን የሚፈልጉበት ወቅት ነው፤ ቢሆንም ብዙዎቹ ደስተኞች አይሆኑም። ዕቃዎችን ብዙም ሳያስቡት በስሜት ተገፋፍተው ከገዙ በኋላ የስጦታ ዕዳውን ለመክፈል ያለው ጭንቀት ያገኙትን ማንኛውንም ደስታ የሚያሳጣቸው ጥቂቶች አይደሉም።
ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ በመስጠት ደስታ ይገኛል ይላል። አዎን፣ ስጦታ መስጠት ደስ ያሰኛል፤ ሆኖም ስጦታውን ለመስጠት የሚገፋፋው መንፈስ ለዚህ ወሳኝነት አለው።—ሥራ 20:35