የይሖዋን ፈቃድ ፈጽመዋል
የኢየሱስን የመሰነባበቻ ቃላት በመታዘዝ
ኒሳን 14, 33 እዘአ ምሽት ላይ ኢየሱስ ክርስቶስና 11 ታማኝ ሐዋርያቱ ኢየሩሳሌም ውስጥ ፎቅ ላይ በሚገኝ አንድ ክፍል ውስጥ ገበታ ቀርበው ነበር። ኢየሱስ በቅርቡ እንደሚሞት ስለሚያውቅ ‘ከእናንተ ጋር የምቆየው ለጥቂት ጊዜ ነው’ አላቸው። (ዮሐንስ 13:33) እንዲያውም በዚህ ጊዜ የአስቆሮቱ ይሁዳ ኢየሱስን ለመግደል ከሚፈልጉ መጥፎ ሰዎች ጋር ለማሴር ሄዷል።
በክፍሉ ውስጥ ከነበሩት ሰዎች መካከል የኢየሱስን ያህል የጊዜውን አጣዳፊነት ያስተዋለ ሰው አልነበረም። ከጥቂት ሰዓታት በኋላ መከራ እንደሚደርስበት አሳምሮ አውቋል። በተጨማሪም ሐዋርያቱ በዚያው ምሽት ትተውት እንደሚሄዱ ያውቃል። (ማቴዎስ 26:31፤ ዘካርያስ 13:7) ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የሚነጋገርበት የመጨረሻ አጋጣሚ ይህ ስለነበር የመሰነባበቻ ንግግሩ ከሁሉ ይበልጥ አንገብጋቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
“ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት”
ኢየሱስ ከታማኝ ሐዋርያቱ ጋር ሆኖ የአይሁዶችን የማለፍ በዓል የሚተካ አዲስ በዓል አቋቋመ። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን በዓል “የጌታ እራት” በማለት ጠርቶታል። (1 ቆሮንቶስ 11:20) ኢየሱስ ያልቦካ ቂጣ አነሳና ጸለየ። ከዚያም ቂጣውን ቆራረሰና ለሐዋርያቱ ሰጣቸው። “እንካችሁ፣ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው” አላቸው። ቀጥሎ ወይኑን አነሳና ከጸለየ በኋላ “ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው” በማለት ለሐዋርያቱ ሰጣቸው።—ማቴዎስ 26:26-28
እነዚህ ነገሮች ምን ትርጉም አላቸው? ኢየሱስ እንደተናገረው ቂጣው ኃጢአት የሌለበትን የኢየሱስ ሥጋ ያመለክታል። (ዕብራውያን 7:26፤ 1 ጴጥሮስ 2:22, 24) ወይኑ ደግሞ ከኃጢአት የሚያነጻውን የፈሰሰውን የኢየሱስ ደም ያመለክታል። በተጨማሪም ይሖዋ አምላክና ወደፊት ከኢየሱስ ጋር በሰማይ የሚገዙት 144,000 ሰዎች የገቡትን አዲሱ ቃል ኪዳን የጸናው ኢየሱስ መሥዋዕት አድርጎ ባቀረበው ደም አማካኝነት ነው። (ዕብራውያን 9:14፤ 12:22-24፤ ራእይ 14:1) ኢየሱስ ከዚህ እራት እንዲካፈሉ ሐዋርያቱን በመጋበዝ በሰማያዊው መንግሥት አብረውት እንደሚገዙ አሳይቷል።
ኢየሱስ ለመታሰቢያነት የሚያገለግል ይህንን እራት በተመለከተ “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” በማለት አዝዟል። (ሉቃስ 22:19) አዎን፣ የጌታ እራት ልክ እንደ ማለፍ በዓል በየዓመቱ የሚከበር በዓል ነው። የማለፍ በዓል እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ መውጣታቸውን የሚያስታውስ ሲሆን የጌታ እራት ደግሞ ከዚህ በጣም በሚበልጠው ነፃነት ይኸውም የሰው ዘር ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ለመዋጀት የሚችል መሆኑን የሚያስታውስ ነው። (1 ቆሮንቶስ 5:7፤ ኤፌሶን 1:7) ከዚህም በላይ ከምሳሌያዊው ቂጣና ወይን የሚካፈሉ ሰዎች ወደፊት በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ውስጥ ነገሥታትና ካህናት በመሆን የሚያገኟቸውን መብቶች ያስታውሳቸዋል።—ራእይ 20:6
የኢየሱስ ሞት በሰዎች ታሪክ ውስጥ ከሁሉ የላቀ ጉዳይ ነው። ኢየሱስ ያደረገውን ነገር የሚያደንቁ ሰዎች ኢየሱስ “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” በማለት የጌታ እራትን በተመለከተ የሰጠውን ትእዛዝ ያከብራሉ። የይሖዋ ምሥክሮች በየዓመቱ ኒሳን 14 በሚውልበት ቀን የኢየሱስን ሞት ያስባሉ። በ1996 ይህ ቀን የሚውለው ሚያዝያ 2 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ነው። በአካባቢህ ባለው የመንግሥት አዳራሽ እንድትገኝ ሞቅ ያለ ግብዣ እናቀርብልሃልን።
“አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ”
ኢየሱስ የጌታ እራትን ከማቋቋሙም በተጨማሪ ለሐዋርያቱ የመሰነባበቻ ምክር ለግሷቸዋል። እነዚህ ሰዎች ምንም እንኳ ጥሩ ሥልጠና አግኝተው የነበረ ቢሆንም መማር ያለባቸው ብዙ ነገሮች ነበሩ። አምላክ ለኢየሱስ፣ ለእነርሱ ወይም ለወደፊቱ ጊዜ ያለውን ዓላማ ሙሉ በሙሉ አልተረዱም ነበር። ሆኖም ኢየሱስ እነዚህን ሁሉ ጉዳዮች በዚህ ጊዜ ለማብራራት አልሞከረም። (ዮሐንስ 14:26፤ 16:12, 13) ከዚህ ይልቅ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ አንድ ነገር ነገራቸው። “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፣ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ” አላቸው። ከዚያም በመቀጠል “ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” አላቸው።—ዮሐንስ 13:34, 35
ይህ ትእዛዝ “አዲስ” የሆነው በምን መንገድ ነው? የሙሴ ሕግ “ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ” በማለት ያዛል። (ዘሌዋውያን 19:18) ሆኖም ኢየሱስ ተከታዮቹ የራስን ሕይወት ለመሰል ክርስቲያኖች እስከ መስጠት ድረስ የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቅ ፍቅር እንዲያሳዩ አዝዟቸዋል። እርግጥ ነው፣ ‘የፍቅር ሕግ’ በጣም አስቸጋሪ ላልሆኑ ሁኔታዎችም ይሠራል። አንድ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ በመንፈሳዊም ሆነ በሌላ በማንኛውም ሁኔታ ሰዎችን በመርዳት ቀዳሚ በመሆን ፍቅር ያሳያል።—ገላትያ 6:10
ኢየሱስ በዚህ የምድራዊ ሕይወቱ የመጨረሻ ምሽት በፍቅር ተነሳስቶ ደቀ መዛሙርቱን በተመለከተ ወደ ይሖዋ አምላክ ጸለየ። ኢየሱስ በጸሎቱ ከጠቀሰው ነገር መካከል “እነርሱም በዓለም ናቸው፣ እኔም ወደ አንተ እመጣለሁ። ቅዱስ አባት ሆይ፣ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው” የሚለው ይገኝበታል። (ዮሐንስ 17:11) ኢየሱስ ለአባቱ ባቀረበው በዚህ ጸሎት ላይ ተከታዮቹ በፍቅር እንዲተሳሰሩ መጠየቁ ትኩረት የሚስብ ነው። (ዮሐንስ 17:20-23) ‘ኢየሱስ እንደወደዳቸው እነርሱም እርስ በርስ መዋደድ’ አስፈልጓቸው ነበር።—ዮሐንስ 15:12
ታማኞቹ ሐዋርያት የኢየሱስን የመሰነባበቻ ቃላት ታዘዋል። እኛም ብንሆን ይህንን ትእዛዝ መፈጸም አለብን። በእነዚህ አስጨናቂ ‘የመጨረሻ ቀናት’ ከማንኛውም ጊዜ ይበልጥ ይሖዋን በእውነት በሚያመልኩ ሰዎች መካከል ፍቅርና አንድነት ያስፈልጋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) እውነተኛ ክርስቲያኖች የኢየሱስን ትእዛዝ በመከተል የወንድማማች ፍቅር ያሳያሉ። ይህም የጌታ እራትን እንድናከብር የተሰጠንን ትእዛዝ መፈጸምን ያካትታል።