የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 4/15 ገጽ 28-29
  • የአንባብያን ጥያቄዎች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የአንባብያን ጥያቄዎች
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አምላክ ይቅር ይለኝ ይሆን?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
  • ‘እርስ በርስ በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ከልባችሁ ይቅር በሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ይቅር ባዮች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 4/15 ገጽ 28-29

የአንባብያን ጥያቄዎች

ኢየሱስ “ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል” ብሏል። ታዲያ ይህ ሲባል ክርስቲያኖች ኃጢአት ይቅር ማለት ይችላሉ ማለት ነውን?

ክርስቲያኖች በጠቅላላ፣ ሌላው ቀርቶ በጉባኤዎች ውስጥ የተሾሙ ሽማግሌዎችም እንኳ ቢሆኑ ኃጢአትን ይቅር ለማለት መለኮታዊ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል የሚል መደምደምያ ላይ ለመድረስ የሚያስችል ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ የለም። ሆኖም ከላይ የተጠቀሱት በዮሐንስ 20:23 ላይ የሚገኙት ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የተናገራቸው ቃላት አምላክ በዚህ ረገድ ለሐዋርያት ልዩ ሥልጣን እንደሰጣቸው ያሳያሉ። በተጨማሪም እዚህ ላይ ኢየሱስ የገለጸው ሐሳብ በማቴዎስ 18:18 ላይ ስለ ሰማያዊ ውሳኔዎች ከተናገረው ነገር ጋር ግንኙነት ሊኖረው ይችላል።

ክርስቲያኖች “እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፣ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ” በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን 4:32 ላይ ከሰጠው ምክር ጋር በተያያዘ ሁኔታ አንዳንድ ቅር የተሰኙባቸውን ነገሮች ይቅር ሊሉ ይችላሉ። ጳውሎስ እዚህ ላይ እየተናገረ ያለው በግዴለሽነት አነጋገርና በመሳሰሉት ምክንያቶች የተነሣ በክርስቲያኖች መካከል ስለሚፈጠሩ የግል አለመግባባቶች ነበር። ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው ይቅር በመባባል እነዚህን ችግሮች ለማስወገድ መጣር ይኖርባቸዋል። ኢየሱስ “እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፣ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፣ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፣ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፣ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ” በማለት የተናገራቸውን ቃላት አስታውስ።—ማቴዎስ 5:23, 24፤ 1 ጴጥሮስ 4:8

ሆኖም በዮሐንስ 20:23 ዙሪያ ያለው ሐሳብ ኢየሱስ በጣም ከባድ ስለሆኑ ኃጢአቶች እየተናገረ እንደ ነበር ያሳያል፤ ይህም ለእነዚህ የተወሰኑ አድማጮች በተናገረው ሌላ ነገር ታይቷል። ይህ የሆነው ለምን እንደሆነ እንመልከት።

ኢየሱስ ከሞት በተነሣበት ቀን በኢየሩሳሌም በሚገኝ አንድ የተዘጋ ቤት ውስጥ ለደቀ መዛሙርቱ ታያቸው። ታሪኩ እንዲህ ይላል፦ “ኢየሱስም ዳግመኛ፦ ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው። ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና፦ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው።”—ዮሐንስ 20:21-23

እዚህ ላይ በተለይ የተጠቀሱት ታማኝ ሐዋርያት ሳይሆኑ አይቀሩም። (ከቁጥር 24 ጋር አወዳድር።) ኢየሱስ እፍ ካለባቸው በኋላ “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ” ብሎ በመናገር ከጥቂት ጊዜ በኋላ በተመሳሳይ መንገድ መንፈስ ቅዱስ እንደሚሰጣቸው እንዲገነዘቡ አደረጋቸው። ኢየሱስ በመቀጠል የኃጢአት ይቅርታ ማድረግን በተመለከተ ሥልጣን እንደሚኖራቸው ተናግሯል። እነዚህ ሁለት አረፍተ ነገሮች እርስ በርስ የተያያዙ ናቸው ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው።

ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ ከሃምሳ ቀናት በኋላ በጰንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስን አፈሰሰላቸው። ይህ ምን ውጤት አስገኘ? አንዱ ውጤት መንፈስ ቅዱስ የተቀበሉት ሰዎች ከክርስቶስ ጋር በሰማይ አብሮ የመግዛት ተስፋ ያላቸው የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች ሆነው ዳግም መወለዳቸው ነው። (ዮሐንስ 3:3-5፤ ሮሜ 8:15-17፤ 2 ቆሮንቶስ 1:22) ሆኖም መንፈስ ቅዱስ መፍሰሱ ሌላም ነገር አከናውኗል። መንፈስ ቅዱስ ከተቀበሉት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ተአምራዊ ችሎታዎችን አግኝተዋል። አንዳንዶች በእነዚህ ችሎታዎች ተጠቅመው በማያውቋቸው የውጭ አገር ቋንቋዎች ለመናገር ችለዋል። ሌሎች ደግሞ ትንቢት የመናገር ችሎታ ተሰጥቷቸው ነበር። የታመሙ ሰዎችን መፈወስ ወይም ሙታንን ማስነሣት የሚችሉም ነበሩ።—1 ቆሮንቶስ 12:4-11

በዮሐንስ 20:22 ላይ የሚገኙት የኢየሱስ ቃላት የሚገልጹት መንፈስ ቅዱስ በደቀ መዛሙርት ላይ ስለ መፍሰሱ ስለሆነ ከዚህ ጋር አያይዞ ይቅር ስለ ማለት የተናገራቸው ቃላት ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ሰዎችን ይቅር የማለት ወይም ያለማለት ልዩ የሆነ መለኮታዊ ሥልጣን የተሰጣቸው ይመስላል።—መጋቢት 1, 1949 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 78 ተመልከት።

መጽሐፍ ቅዱስ ሐዋርያት በዚህ ሥልጣን የተጠቀሙበትን እያንዳንዱን ታሪክ የማይገልጽልን ከመሆኑም በላይ ተአምራታዊ ስጦታቸውን ተጠቅመው በሌላ ቋንቋ የተናገሩበትን፣ ትንቢት የተናገሩበትን ወይም የፈወሱበትን ጊዜ በሙሉ አይነግረንም።—2 ቆሮንቶስ 12:12፤ ገላትያ 3:5፤ ዕብራውያን 2:4

ኃጢአትን ይቅር የማለት ወይም ያለማለት ሐዋርያዊ ሥልጣን የታየበት አንዱ ሁኔታ መንፈስ ቅዱስን ለማታለል ሞክረው የነበሩትን ሐናንያንና ሰጲራን የሚመለከት ነው። ኢየሱስ በዮሐንስ 20:22, 23 ላይ የምናነበውን ነገር ሲያነጋግረው የሰማው ጴጥሮስ ሐናንያንና ሰጲራን አጋለጣቸው። ጴጥሮስ በመጀመሪያ ሐናንያን ሲያናግረው ሐናንያ ወዲያውኑ ሞተ። ከዚያ በኋላ ሰጲራ መጥታ መዋሸቷን ስትቀጥል ጴጥሮስ እንደ ተፈረደባት ነገራት። ጴጥሮስ ኃጢአቷን ይቅር ሳይል “ባልሽን የቀበሩት ሰዎች እግር በደጅ ነው አንቺንም ያወጡሻል” አላት። እርሷም ወዲያውኑ ሞተች።—ሥራ 5:1-11

በዚህ ጊዜ ሐዋርያው ጴጥሮስ አምላክ ሐናንያንና ሰጲራን ይቅር እንደማይል ባገኘው ተአምራዊ እውቀት ተጠቅሞ ኃጢአትን ይቅር ባለማለት ረገድ ባለው ልዩ ሥልጣን ተጠቅሟል። በተጨማሪም ሐዋርያት በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ይቅር ስለማይባሉ ኃጢአቶች ከሰው በላይ የሆነ እውቀት የነበራቸው ይመስላል። ስለዚህ እነዚያ በመንፈስ ተሞልተው የነበሩ ሐዋርያት ኃጢአትን ይቅር ለማለት ወይም ላለማለት ይችሉ ነበር።a

ይህ በዚያን ጊዜ የነበሩ በመንፈስ የተቀቡ ሽማግሌዎች በሙሉ እንዲህ ዓይነቱ ተአምራዊ ሥልጣን ተሰጥቷቸው ነበር ማለት አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ ከቆሮንቶስ ጉባኤ ስለ ተወገደ ሰው ከተናገረው ነገር ይህን ለመረዳት እንችላለን። ጳውሎስ ‘የዚያን ሰው ኃጢአት ይቅር ብዬአለሁ’ ወይም ደግሞ ‘ሰውዬው በሰማይ ይቅር እንደተባለ ስለማውቅ ተቀበሉት’ አላለም። ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ የጉባኤው አባላት በሙሉ ይህን ከውገዳ የተመለሰ ሰው ይቅር እንዲሉትና ፍቅራቸውን እንዲያሳዩት መክሯቸዋል። ጳውሎስ በዚህ ላይ አክሎ ሲናገር “እናንተ ግን ይቅር የምትሉትን እኔ ደግሞ ይቅር እለዋለሁ” ብሏል።—2 ቆሮንቶስ 2:5-11

ሰውዬው ውገዳው ተነሥቶለት ወደ ጉባኤ ስለ ተመለሰ ቀደም ሲል ባደረገው ነገር ምክንያት ቂም ባለመያዝ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች በሙሉ ይቅር ሊሉት ይችሉ ነበር። ሆኖም በመጀመሪያ ንስሐ ገብቶ ከውገዳ መመለስ ይኖርበታል። ይህ የሚሆነው እንዴት ነው?

የጉባኤ ሽማግሌዎች ሊመለከቷቸው የሚገቡ እንደ ስርቆት፣ መዋሸት ወይም ከባድ የሥነ ምግባር ብልግና ያሉ ኃጢአቶች አሉ። እንደነዚህ ያሉ ኃጢአተኞችን ንስሐ እንዲገቡ ለማበረታታት ተግሣጽ ሊሰጧቸውና ሊያስተካክሏቸው ይሞክራሉ። ሆኖም አንድ ግለሰብ ንስሐ ሳይገባ ከባድ ኃጢአት መሥራቱን ቢቀጥል እነዚህ ሽማግሌዎች ኃጢአተኛውን ለማስወገድ መለኮታዊ መመሪያ ይከተላሉ። (1 ቆሮንቶስ 5:1-5, 11-13) ኢየሱስ በዮሐንስ 20:23 ላይ የተናገረው በዚህ ረገድ አይሠራም። እነዚህ ሽማግሌዎች በአካል የታመመ ሰውን ለመፈወስ ወይም ሙታንን ለማስነሣት የሚያስችሉት ዓይነት ተአምራዊ የመንፈስ ስጦታዎች የሏቸውም፤ እነዚህ ተአምራዊ ስጦታዎች በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓላማቸውን አከናውነው አቁመዋል። (1 ቆሮንቶስ 13:8-10) ከዚህም በላይ በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎች አንድ ከባድ ኃጢአት የፈጸመ ግለሰብ በይሖዋ ፊት ንጹሕ እንደሆነ በመግለጽ ከባድ ኃጢአትን ይቅር የማለት መለኮታዊ ሥልጣን አልተሰጣቸውም። እንዲህ ዓይነቱ ይቅርታ የሚደረገው በቤዛው መሥዋዕት መሠረት ሲሆን በዚህ መሠረት ይቅር ማለት የሚችለው ደግሞ ይሖዋ ብቻ ነው።—መዝሙር 32:5፤ ማቴዎስ 6:9, 12፤ 1 ዮሐንስ 1:9

በጥንት የቆሮንቶስ ከተማ ውስጥ እንደነበረው ሰው ሁሉ አንድ ከባድ ኃጢአት የሠራ ሰው ንስሐ ካልገባ መወገድ ይኖርበታል። በኋላ ግን ተጸጽቶ ለንስሐ የሚገቡ ፍሬዎች ካሳየ መለኮታዊ ተቀባይነት ሊያገኝ ይችላል። (ሥራ 26:20) በእንዲህ ዓይነቱ ጊዜ ሽማግሌዎች ቅዱሳን ጽሑፎች በሚሰጡት ሐሳብ መሠረት ይሖዋ ኃጢአተኛውን በእርግጥ ይቅር እንዳለው ማወቅ ይችላሉ። ግለሰቡ ውገዳው ተነሥቶለት ከተመለሰ በኋላ ሽማግሌዎች በእምነት እንዲጠነክር መንፈሳዊ እርዳታ ሊያደርጉለት ይችላሉ። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በዚያን ጊዜ የተመለሰውን የተወገደ ሰው ይቅር እንዳሉት ሁሉ በጉባኤው ያሉ ሌሎች ሰዎችም ይቅር ሊሉት ይችላሉ።

ሽማግሌዎች አንዳንድ ጉዳዮችን በዚህ መንገድ ሲይዙ የራሳቸውን የፍርድ መመዘኛዎች አያወጡም። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሥራ ላይ ከማዋላቸውም በላይ ይሖዋ ያወጣቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ሥርዓቶች ይከተላሉ። ስለሆነም ሽማግሌዎች ይቅር ሲሉም ሆነ ሳይሉ ኢየሱስ በማቴዎስ 18:18 “እውነት እላችኋለሁ፣ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፣ በምድርም የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል” በማለት ከተናገረው ጋር የሚስማማ ነገር ያደርጋሉ። የሚወስዷቸው እርምጃዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈረውን የይሖዋን አመለካከት የሚያንጸባርቁ ይሆናሉ።

በዚህ መሠረት ኢየሱስ በዮሐንስ 20:23 ላይ የተናገረው ከሌሎች ቅዱሳን ጽሑፎች ሐሳብ ጋር የሚጋጭ ሳይሆን ሐዋርያት በታዳጊው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በነበራቸው ልዩ ሚና ምክንያት ይቅርታ በማድረግ ረገድ ለየት ያለ ሥልጣን እንደ ተሰጣቸው የሚያሳይ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ኢየሱስ ከመሞቱና ቤዛዊ መሥዋዕት ከማቅረቡ በፊት እንኳ ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን ነበረው።—ማቴዎስ 9:2-6፤ በሰኔ 1, 1995 መጠበቂያ ግንብ ላይ ከወጣው “የአንባብያን ጥያቄዎች” ጋር አወዳድር።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ