ጡረታ መውጣት ለቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴ በር ይከፍታልን?
ብዙዎች ጡረታ መውጣትን ለረጅም ጊዜ ያሳለፉት የጭንቀትና የብስጭት ዘመን የሚያከትምበት ጊዜ አድርገው ይመለከቱታል። ብዙ ሰዎች አሰልቺ በሆነ ወይም በሚያበሳጭ ሥራ ተወጥረው ከተያዙ በኋላ ጡረታ ወጥተው ለመዝናናትና የግል ነፃነት ለማግኘት የሚችሉበት በር እንዲከፈትላቸው ይጓጓሉ። ብዙውን ጊዜ ግን ይህ በር ወደ ስልቹነትና ልፍስፍስነት ይመራል። መዝናኛና በትርፍ ጊዜ የሚደሰቱበትን ነገሮች መሥራት ከሥራ የሚገኘውን ስለ ራስ ጥሩ ግምት የማሳደር ስሜት ሊያመጣ አይችልም።
ጡረታ ለይሖዋ ምሥክሮች “ሥራ የሞላበት ትልቅ በር” ሊከፍትላቸው ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 16:9) ምንም እንኳ በዕድሜ መግፋት የራሱ የሆኑ ችግሮችና ገደቦች ቢኖሩትም አንዳንድ አረጋውያን በይሖዋ እርዳታ ለእርሱ የሚያቀርቡትን አገልግሎት ከፍ ማድረግ የሚቻል ሆኖ አግኝተውታል። በኔዘርላንድ የሚገኙ የአንዳንድ ክርስቲያን አረጋውያንን ተሞክሮዎች ተመልከቱ። በ1995 የአገልግሎት ዓመት ከ1,223 በላይ ከሆኑት አቅኚዎች (የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች) መካከል 269ኞቹ 50 ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የሆናቸው ነበሩ። ከእነዚህ ውስጥ 81ዱ 65 ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ዕድሜ ያላቸው ነበሩ።
አንዳንዶች በሥራ ላይ በነበሩበት ወቅት የነበራቸውን በሥራ የተጠመደ ሕይወት በመቀጠል በአቅኚነት ለማገልገል ችለዋል። (ከፊልጵስዩስ 3:16 ጋር አወዳድር።) ካረል የተባለ አንድ ጡረታ የወጣ ክርስቲያን እንዲህ በማለት ያስታውሳል፦ “በሥራ ላይ በነበርኩበት ወቅት ሥራ የምጀምረው በ1:30 ነበር። ጡረታ ስወጣ ተመሳሳይ ልማድ ለመከተል ወሰንኩ። ጠዋት ጠዋት በአንድ ሰዓት በባቡር ጣቢያ አጠገብ በመንገድ ላይ በመጽሔቶች አማካኝነት በመመሥከር ቀኑን እጀምራለሁ።”
በጥንቃቄ እቅድ ማውጣትም ለስኬታማነት ቁልፍ ነው። (ምሳሌ 21:5) ለምሳሌ ያህል አንዳንዶች ራሳቸውን ችለው ለማገልገል በቂ ገንዘብ ለማጠራቀም ችለዋል። ሌሎች ደግሞ የግል ወጪዎቻቸውን ለመቀነስና የግማሽ ቀን ሥራ ለማግኘት ወስነዋል። ቴኦዶርንና አንን ተመልከቱ። አቅኚዎች ሆነው ትዳር ከጀመሩ በኋላ በቤተሰብ ግዴታዎች ምክንያት አቅኚነታቸውን ለማቆም እስከተገደዱበት ጊዜ ድረስ በአቅኚነት አገልግሎት ቀጥለው ነበር። ሆኖም የአቅኚነት መንፈሳቸው አልጠፋም! ሴቶች ልጆቻቸው እያደጉ ሲሄዱ በየጊዜው አቅኚዎች እንዲሆኑ ያበረታቷቸው ነበር። ከዚህ የበለጠ ደግሞ ቴኦዶርና አን ብዙ ጊዜ ረዳት አቅኚዎች ሆነው በማገልገል ጥሩ ምሳሌዎች ሆኑ። ሴቶች ልጆቻቸው እያደጉ ሲሄዱ ቴኦዶርና አን በመስክ አገልግሎት ተጨማሪ ጊዜ ለማሳለፍ ሲሉ ዓለማዊ ሥራቸውን ቀነሱ።
ሴቶች ልጆቻቸው የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀምረው ራሳቸውን ችለው ከቤት ከወጡ በኋላ አን የአቅኚነት አገልግሎት ጀመረች። አንድ ቀን ቴኦዶር ሥራውን እንዲያቆም አበረታታችው። “ሁለታችንም አቅኚ መሆን እንችላለን” ስትል ሐሳብ አቀረበች። ቴኦዶር ሐሳቡን ለአሠሪው ገለጸ። አለቃው “እዚያ [ሰማይ] ላለው አለቃህ ሙሉ ጊዜ ልትሠራ የፈለግህ ይመስለኛል” በማለት የግማሽ ቀን ሥራ በመስጠት ሊረዳው እንደሚፈልግ ሲነግረው ቴኦዶር ተገረመ። በአሁኑ ጊዜ ቴኦዶርና አን አንድ ላይ ሆነው በአቅኚነት በማገልገል ላይ ናቸው።
አንዳንዶች አቅኚነት የጀመሩት በሕይወታቸው ውስጥ ባጋጠሟቸው ሁኔታዎች ምክንያት ነው። ሴት ልጃቸውና የልጅ ልጃቸው በአሳዛኝ ሁኔታ መሞታቸው አንድ አረጋዊ ባልና ሚስት ቀሪውን ሕይወታቸውን የሚጠቀሙበትን መንገድ በቁም ነገር እንዲያስቡበት አድርጓቸዋል። (መክብብ 7:2) በሐዘን ከመዋጥ ይልቅ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ገቡ፤ በአሁኑ ጊዜ በዚህ አገልግሎት ከስምንት ዓመት በላይ ሆኗቸዋል!
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መቆየት ጽኑ ውሳኔ እንደሚጠይቅ እሙን ነው። ለምሳሌ ያህል ኧርነስትና ባለቤቱ ሪክ ልጆቻቸው ከቤት እንደወጡ የአቅኚነት አገልግሎት ጀምረው ነበር። ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የቀድሞው የንግድ ሸሪኩ አትራፊ ሥራ እንዲሠራ ለኧርነስት ሐሳብ አቀረበለት። ኧርነስት “ከማንኛውም አሠሪ የተሻለ አሠሪ አለን፤ የእርሱን ሥራ ለመተው አንፈልግም!” በማለት መለሰለት። ኧርነስትና ባለቤቱ “አሠሪያቸው” የሆነውን ይሖዋን ማገልገላቸውን ስለ ቀጠሉ ሌሎች የአገልግሎት መብቶች ተከፍተውላቸዋል። ከ20 ዓመታት በላይ በወረዳ ሥራ ያገለገሉ ሲሆን እስከ ዛሬ ድረስ በአቅኚነት አገልግሎት ቀጥለዋል። የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ አካሄድ በመከተላቸው ተጸጽተዋልን? እነዚህ ባልና ሚስት ከጥቂት ጊዜ በፊት እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “የይሖዋ ፈቃድ ከሆነ አብዛኛውን ጊዜ የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ተብሎ የሚጠራውን 50ኛ ዓመት የጋብቻ በዓላችንን ከሦስት ወር በኋላ እናከብራለን። ይሁን እንጂ ወርቃማ ዓመቶቻችን የጀመሩት የአቅኚነት አገልግሎት በጀመርንበት ወቅት እንደሆነ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ሆነን እንናገራለን።”
ብዙዎች ይህን በር ወደ ተጨማሪ ሥራ ብቻ ሳይሆን ወደ ላቀ ደስታም ጭምር የሚመራ ሆኖ አግኝተውታል! 65 ዓመት ከሆነው ከሁለት ሳምንታት በኋላ የአቅኚነት አገልግሎት የጀመረ አንድ ወንድም “ባለፉት አሥር ዓመታት በአቅኚነት አገልግሎት ባሳለፍኩበት ወቅት ያገኘኋቸውን የተትረፈረፉ በረከቶች ያህል በሕይወቴ ፈጽሞ አጋጥሞኝ እንደማያውቅ ለመግለጽ እገደዳለሁ” ብሏል። ከሰባት ዓመታት በላይ በአቅኚነት ያገለገሉ አንድ ባልና ሚስት እንዲህ ብለዋል፦ “በእኛ ዕድሜና እኛ ባለንባቸው ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ ባልና ሚስት ከዚህ የተሻለ ምን ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ? ብዙውን ጊዜ በክልሉ ውስጥ በእኛው ዓይነት ሁኔታ ሥር የሚገኙ ሰዎች በተመቻቸ አኳኋን ቤታቸው ተቀምጠው እየወፈሩ፣ እያረጁና ሰውነታቸው እየተዳከመ ሲሄድ እንመለከታለን። ይህ አገልግሎት በአእምሮና በአካል ጤናሞች ሆነን እንድንቀጥል አድርጎናል። ሁልጊዜ አንድ ላይ እንሆናለን። ብዙ እንስቃለን፤ በሕይወታችንም ደስተኞች ነን።”
እርግጥ አረጋውያን ሁሉ አቅኚ ለመሆን የሚያስችል ሁኔታ አላቸው ማለት አይደለም። ይሖዋ እነዚህ ክርስቲያኖች እርሱን ለማገልገል የሚያደርጉትን ማንኛውንም ጥረት እንደሚያደንቅ እርግጠኞች ሊሆኑ ይችላሉ። (ከማርቆስ 12:41-44 ጋር አወዳድር።) ለምሳሌ ያህል አንዲት የአካል ጉዳተኛ እህት በአቅመ ደካሞች መንከባከቢያ ተቋም ውስጥ ትኖራለች። ሆኖም የሥራ በር ተከፍቶላታል! አንድ ዶክተር ያላትን በርካታ ጊዜ እንዴት እንደምታሳልፍ ጠየቃት። እንዲህ ትላለች፦ “ዘወትር ጊዜ እንደሚያጥረኝ ነገርኩት። ምን ማለቴ እንደሆነ ሊገባው አልቻለም። ይህ የሆነው ጊዜዬን አስደሳች የሆኑ ሥራዎችን ለመሥራት ስለምጠቀምበት እንደሆነ ነገርኩት። ብቸኛ አይደለሁም፤ ሆኖም ብቸኛ የሆኑ ሌሎች ሰዎችን ፈልጌ አምላክ ለሰው ልጆች ያዘጋጀላቸውን ልነግራቸው እሞክራለሁ።” እንዲህ በማለት ጉዳዩን አጠቃልላለች፦ “80 ዓመት ያህል ከሞላው ሰው ማንም ብዙ አይጠብቅም። ብዙ ሰዎችን ወደ ይሖዋ ለማምጣት እንድችል ጸልዩልኝ።”
በጡረታ ዕድሜ ላይ ትገኛለህን? ከሥራ ነፃ መሆን በሚቻልበት በር መግባት በጣም የሚያጓጓ ሊሆን ቢችልም ይህ በር መንፈሳዊ በረከት አያስገኝም። ያለህበትን ሁኔታ በጸሎት አስብበት። በይሖዋ አገልግሎት የበለጠ ተሳትፎ ለማድረግ በሚያስችለው በር ልትጠቀም ትችል ይሆናል።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጡረታ መውጣት በአገልግሎት ከፍ ያለ እንቅስቃሴ ለማድረግ አጋጣሚ ሊፈጥር ይችላል