የአቅኚነት አገልግሎት የሚያስገኛቸው በረከቶች
“የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች፣ ኀዘንንም ከእርስዋ ጋር አይጨምርም።” —ምሳሌ 10:22
1, 2. (ሀ) አንድ አቅኚ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን በሚመለከት የሚሰማውን ስሜት የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) አቅኚዎች ደቀ መዛሙርት በማድረግ የሚገኘውን ደስታ ይበልጥ በተሟላ መንገድ ለማጣጣም የሚያስችል አጋጣሚ አላቸው የምንለው ለምንድን ነው?
“ታስጠኑት የነበረ ሰው የይሖዋ አወዳሽ ሲሆን ከማየት የበለጠ ደስታ ሊኖር ይችላልን? የአምላክ ቃል ሰዎች ይሖዋን ለማስደሰት ሲሉ በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥ እንዲያደርጉ በማንቀሳቀስ ረገድ ምን ያህል ኃይል እንዳለው መመልከት የሚያስደስትና እምነትን የሚያጠነክር ነገር ነው።” ይህንን የጻፈው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ከ32 ዓመታት በላይ ያሳለፈ አንድ በካናዳ ያለ አቅኚ ነው። የአቅኚነት አገልግሎቱን በሚመለከት እንዲህ ብሏል:- “ሌላ ሥራ ፈጽሞ አይታየኝም። እንዲህ ዓይነት ደስታ የሚያስገኝ ሌላ ሥራ ይኖራል ብዬ በፍጹም አላስብም።”
2 ሰዎችን ወደ ሕይወት በሚወስደው ጎዳና እንዲጓዙ በመርዳቱ ሥራ መካፈል ታላቅ ደስታ ያመጣል በሚለው ሐሳብ ትስማማለህ? እርግጥ ነው፣ እንዲህ ዓይነቱን ደስታ የሚያጣጥሙት አቅኚዎች ብቻ አይደሉም። ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች ‘ሰዎችን ደቀ መዛሙርት የማድረግ’ ተልእኮ የተሰጣቸው ሲሆን ይህንን ተልእኳቸውን ለመፈጸም ይጣጣራሉ። (ማቴዎስ 28:19) ይሁን እንጂ አቅኚዎች በመስክ አገልግሎት ብዙ ሰዓታት ስለሚያሳልፉ ደቀ መዛሙርት በማድረግ የሚገኘውን ደስታ ይበልጥ በተሟላ መንገድ ለማጣጣም የሚያስችል አጋጣሚ አላቸው። አቅኚነት ሌሎች በረከቶችም አሉት። አቅኚዎችን ጠጋ ብለህ አነጋግራቸው፤ አቅኚነት ‘ባለጠጋ የሚያደርገውን የይሖዋ በረከት’ ለማጣጣም የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ እንደሆነ ይነግሩሃል።—ምሳሌ 10:22
3. በይሖዋ አገልግሎት ምን ነገር ይበልጥ ሊያነቃቃን ይችላል?
3 በቅርቡ በተለያዩ የምድር ክፍሎች የሚኖሩ አቅኚዎች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያገኟቸውን በረከቶች እንዲገልጹ ተጠይቀው ነበር። እስቲ ምን እንዳሉ እንመልከት። ነገር ግን በጤና ችግር፣ በዕድሜ መግፋት ወይም በሌሎች ሁኔታዎች የተነሣ አገልግሎትህ ውስን ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። አቅኚም ሆንን አልሆን ዋናው ነገር ይሖዋን በሙሉ ልብ ማገልገላችን እንደሆነ አትዘንጋ። ሆኖም አንዳንድ አቅኚዎች የሰጡትን ሐሳብ መስማትህ ሁኔታህ የሚፈቅድልህ ከሆነ ይህንን የሚክስ ሥራ ለመጀመር ያለህን ፍላጎት ያሳድግልህ ይሆናል።
ጥልቅ የሆነ የእርካታና የደስታ ስሜት
4, 5. (ሀ) ምሥራቹን ለሌሎች ሰዎች ማካፈል ይህን ያህል የሚክስ ሥራ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) አቅኚዎች በአገልግሎት ሙሉ ጊዜ በመካፈላቸው ምን ይሰማቸዋል?
4 ኢየሱስ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW] ነው” ብሏል። (ሥራ 20:35) አዎን፣ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ስሜት መስጠት የሚያስገኛቸው በረከቶች አሉ። (ምሳሌ 11:25) በተለይ ደግሞ ይህ አባባል ምሥራቹን ለሌሎች በማካፈል ረገድ እውነት ሆኖ እናገኘዋለን። እንደ እውነቱ ከሆነ ለአንድ ሰው ከአምላክ የሚገኘውን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት ከማካፈል የበለጠ ልንሰጠው የምንችለው ሌላ ምን ታላቅ ስጦታ ይኖራል?—ዮሐንስ 17:3
5 በአገልግሎቱ ሙሉ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉ ወንድሞችና እህቶች ብዙውን ጊዜ ከአገልግሎት ስላገኙት ደስታና ጥልቅ እርካታ መናገራቸው ሊያስደንቀን አይገባም። አንድ የ64 ዓመት ዕድሜ ያለው በብሪታንያ የሚገኝ አቅኚ እንዲህ ብሏል:- “እውነትን ለሌሎች ሰዎች በማካፈል ያገኘሁትን ዓይነት እርካታ ሊሰጠኝ የሚችል ሌላ ሥራ እንደሌለ አውቃለሁ።” አንዲት በዛየር የምትኖር መበለት አቅኚነት ለእርሷ ምን ትርጉም እንዳለው ስትናገር እንዲህ ብላለች:- “ውዱን ባለቤቴን በሞት ካጣሁ በኋላ የአቅኚነት አገልግሎት ለእኔ ትልቅ መጽናኛ ሆኖልኛል። ሌሎች ሰዎችን ለመርዳት ይበልጥ በአገልግሎቴ ላይ ባተኮርኩ መጠን ኀዘኔም የዚያኑ ያክል ይቀንሳል። እምነቴን ይሖዋ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እጥላለሁ፤ አብዛኛውን ጊዜ የማስበውም የማስጠናቸው ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥ እንዲያደርጉ መርዳት ስለምችልበት መንገድ ነው። በያንዳንዱ ዕለት መጨረሻ ጣፋጭ እንቅልፍ እተኛለሁ፤ ልቤም በደስታ ይሞላል።”
6. አንዳንድ አቅኚዎች ምን ልዩ ደስታ አግኝተዋል?
6 በአቅኚነት ብዙ አሥርተ ዓመታት ያሳለፉ አንዳንዶች ራቅ ብለው በሚገኙ አካባቢዎች በማገልገልና ጉባኤዎችን በማቋቋም ልዩ ደስታ አግኝተዋል። ከጊዜ በኋላ እነዚህ ጉባኤዎች አድገው ወረዳዎች ሊገኙ ችለዋል። ለምሳሌ ያህል በአብሺሪ ሆካይዶ (በጃፓን ሰሜናዊ ጫፍ የምትገኝ ደሴት ናት) ለ33 ዓመታት በአቅኚነት ያገለገለች አንዲት እህት ትገኛለች። ለመጀመሪያ ጊዜ የወረዳ ስብሰባ ሲደረግ ከመላዋ ሆካይዶ በስብሰባው ላይ የተገኙት 70 ብቻ እንደነበሩ ታስታውሳለች። አሁንስ? በዚያች ደሴት ላይ በድምሩ ከ12,000 አስፋፊዎች በላይ ያሏቸው 12 ወረዳዎች ይገኛሉ። ይህች እህት በደሴቲቱ ላይ ከሚገኙት እጅግ ብዙ መሰል የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ጋር በወረዳና በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ስትገኝ ልቧ በደስታ እንዴት እንደሚፍለቀለቅ አስበው!
7, 8. አብዛኞቹ ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ አቅኚዎች ምን ደስታ አግኝተዋል?
7 ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ ሌሎች አቅኚዎች ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተጠምቀው ለተጨማሪ የአገልግሎት መብቶች ሲጣጣሩ በማየት ደስታ አግኝተዋል። ጃፓን ውስጥ ከ1957 ጀምሮ በዘጠኝ የተለያዩ ቦታዎች በአቅኚነት ተመድባ ያገለገለች አንዲት እህት ባንክ ውስጥ ለምትሠራ አንዲት ወጣት ሴት ንቁ! መጽሔት አበርክታ እንደነበር ታስታውሳለች። ይህች ወጣት ሴት በዘጠኝ ወራት ውስጥ ተጠመቀች። ከዚያም ባል አገባችና እርሷና ባሏ ልዩ አቅኚዎች ሆኑ። አቅኚዋ እህት ወደ ሦስተኛው የአገልግሎት ምድቧ በሄደች ጊዜ ጉባኤው በአዲሱ የወረዳ የበላይ ተመልካችና በባለቤቱ ማለትም በቀድሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዋ ሲጎበኝ ስታይ እንዴት ተደስታ ይሆን!
8 የአቅኚነት አገልግሎትን ሙያዬ ብለው የያዙት ወንድሞችና እህቶች፣ አንድ ለ22 ዓመታት አቅኚ ሆኖ ያገለገለ ወንድም እንደገለጸው “በዋጋ ሊተመን የማይችል መብት” እንደሆነ አድርገው መመልከታቸው አያስደንቅም!
ይሖዋ እንደሚንከባከባቸው የሚያሳይ ማስረጃ
9. ይሖዋ ታላቅ ሰጭ በመሆኑ ለአገልጋዮቹ ምን ቃል ገብቷል? ይህስ ለእኛ ምን ትርጉም ይኖረዋል?
9 ታላቁ ሰጪ ይሖዋ አገልጋዮቹን በሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊና ቁሳዊ ነገሮች ረገድ በመንከባከብ እንደሚደግፋቸው ቃል ገብቷል። የጥንቱ ንጉሥ ዳዊት እንደሚከተለው ማለቱ ተገቢ ነበር:- “ጎለመስሁ አረጀሁም፤ ጻድቅ ሲጣል፣ ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም።” (መዝሙር 37:25) እርግጥ ነው፣ ይህ መለኮታዊ ዋስትና የቤተሰባችንን ቁሳዊ ፍላጎት ከማሟላት ግዴታችን ነፃ እንድንሆን ሰበብ አይሆነንም ወይም የክርስቲያን ወንድሞቻችንን ልግስና እየጠበቅን እንድንቀመጥ ፈቃድ አይሰጠንም። (1 ተሰሎንቄ 4:11, 12፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:8) ይሁንና ይሖዋን ይበልጥ በተሟላ መንገድ ለማገልገል ብለን በሕይወታችን ውስጥ መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኛ ከሆንን እርሱ አይተወንም።—ማቴዎስ 6:33
10, 11. ብዙ አቅኚዎች ይሖዋ የሚያስፈልገንን በመስጠት ረገድ ስላለው ችሎታ ከተሞክሮ ምን ተምረዋል?
10 በዓለም ዙሪያ የሚገኙት አቅኚዎች ይሖዋ እርሱ እንደሚንከባከባቸው የሚታመኑ ሰዎችን በሚያስፈልጋቸው ነገር እንደሚደግፋቸው ከተሞክሮ ተምረዋል። የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባት አንዲት ትንሽ ከተማ የተዛወሩትን የአንድ አቅኚ ባልና ሚስት ሁኔታ ተመልከት። ከጥቂት ወራት በኋላ ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ ከመምጣቱም ሌላ የነበራቸው ገንዘብም ተሟጥጦ ነበር። ወዲያው ደግሞ የ81 ዶላር የመኪና ኢንሹራንስ ዕዳ መጣባቸው። ወንድም ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ምንም መክፈል የምንችልበት መንገድ አልነበረም። በዚያ ዕለት ምሽት በብርቱ ጩኸት ወደ ይሖዋ ጸለይን።” በሚቀጥለው ቀን እንደ እነርሱ የኢኮኖሚ ትግል ከገጠመ አንድ ቤተሰብ ካርድ ደረሳቸው። የላኩላቸው ካርድ እንደሚለው ቤተሰቡ ከቀረጥ ክፍያ ተመላሽ የሆነ ገንዘብ አግኝቶ ነበር፤ ተመላሽ የሆነው ገንዘብ መጠን ከጠበቁት በላይ ስለነበር የተወሰነውን ገንዘብ ለእነዚህ አቅኚዎች ለማካፈል ወሰኑ። ከካርዱ ጋር አብሮ የ81 ዶላር ቼክ ነበረ! ይህ አቅኚ ወንድም እንዲህ ብሏል:- “ያችን ቀን ፈጽሞ አልረሳትም፤ ከደስታዬ የተነሣ የማደርገው ጠፍቶኝ ነበር። ይህ ቤተሰብ ያሳየንን ልግስና ከልብ አደነቅን!” ይሖዋ ራሱ አገልጋዮቹ ተመሳሳይ የለጋስነት መንፈስ እንዲያሳዩ የሚያበረታታ በመሆኑ እንዲህ ዓይነቱን ደግነት ያደንቃል።—ምሳሌ 19:17፤ ዕብራውያን 13:16
11 ሌሎች ብዙ አቅኚዎችም ተመሳሳይ ተሞክሮዎችን ሊናገሩ ይችላሉ። ጠይቋቸው፤ ፈጽሞ ‘ተጥለው’ እንደማያውቁ ይነግሯችኋል። አንድ የ72 ዓመት ዕድሜ ያለው አቅኚ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፋቸውን 55 ዓመታት ወደ ኋላ መለስ ብሎ በመመልከት “ይሖዋ ጥሎኝ አያውቅም” ብሏል።—ዕብራውያን 13:5, 6
“ወደ ይሖዋ ለመቅረብ የሚያስችል ግሩም መንገድ”
12. ምሥራቹን የማወጁ ሥራ ይህን ያህል ድንቅ መብት የሆነው ለምንድን ነው?
12 ይሖዋ የመንግሥቱን ምሥራች እንድናውጅ እኛን መጠየቁ ራሱ ትልቅ መብት ነው። ፍጽምና የጎደለን ሰዎች ብንሆንም እንኳ በዚህ ሕይወት አድን በሆነ ሥራ ውስጥ ‘አብረነው እንደምንሠራ’ አድርጎ ቆጥሮናል። (1 ቆሮንቶስ 3:9፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:16) ለሌሎች ስለ አምላክ መንግሥት ስንሰብክ፣ ክፋት እንደሚያበቃ ስናውጅ፣ ቤዛውን በመስጠት ስላሳየን ታላቅ ፍቅር ለሰዎች ስናስረዳ፣ ሕያው የሆነውን ቃሉን ከፍተን ቅን ልብ ላላቸው ሰዎች ክቡር የሆነውን መልእክቱን ስናስተምር ወደ ፈጣሪያችን ወደ ይሖዋ መቅረባችን አይቀርም።—መዝሙር 145:11፤ ዮሐንስ 3:16፤ ዕብራውያን 4:12
13. አንዳንዶች የአቅኚነት አገልግሎት ከይሖዋ ጋር ባላቸው ዝምድና ላይ ያለውን ውጤት በሚመለከት ምን ብለዋል?
13 አቅኚዎች ስለ ይሖዋ በመማርና በማስተማር በየወሩ ብዙ ሰዓታት የሚያሳልፉበት አጋጣሚ አላቸው። ይህ ነገር ከአምላክ ጋር ባላቸው ዝምድና ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ በሚመለከት ምን ይሰማቸዋል? ከአሥር ለሚበልጡ ዓመታት አቅኚ ሆኖ የቆየ በፈረንሳይ የሚገኝ አንድ ሽማግሌ “አቅኚነት ወደ ይሖዋ ለመቅረብ የሚያስችል ግሩም መንገድ ነው” በማለት መልሷል። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት 18 ዓመት ያሳለፈ በዚያው አገር የሚገኝ ሌላ አቅኚ ደግሞ እንዲህ ብሏል:- “የአቅኚነት አገልግሎት በየዕለቱ ከፈጣሪያችን ጋር ይበልጥ ጠንካራ ዝምድና ለመመሥረት የሚያስችል በመሆኑ ‘ይሖዋ ጥሩ መሆኑን እንድናይና እንድንቀምስ’ ያስችለናል”። (መዝሙር 34:8) ለ30 ዓመታት አቅኚ ሆና ያገለገለች በብሪታንያ የምትኖር አንዲት እህትም የተሰማት እንደዚሁ ነው። እንዲህ ብላለች:- “በአገልግሎቴ መመሪያ ለማግኘት በይሖዋ መንፈስ መደገፌ ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንድቀርብ አድርጎኛል። በብዙ አጋጣሚዎች የይሖዋ መንፈስ በትክክለኛው ጊዜ ወደ ተገቢው ቤት እንደመራኝ ተሰምቶኛል።”—ከሥራ 16:6-10 ጋር አወዳድር።
14. አቅኚዎች በየዕለቱ ሌሎችን ለማስተማር በመጽሐፍ ቅዱስና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ ጽሑፎች በመገልገላቸው የተጠቀሙት እንዴት ነው?
14 ብዙ አቅኚዎች በየዕለቱ ስለ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶች ለማስረዳትና ለማስተማር በመጽሐፍ ቅዱስና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ ጽሑፎች መጠቀማቸው በአምላክ ቃል እውቀት እንዲያድጉ እንደረዳቸው ይናገራሉ። ለ31 ዓመታት በአቅኚነት ያገለገለውና 85 ዓመት የሆነው በስፔይን የሚገኝ አንድ ወንድም እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “አቅኚነት ጥልቀት ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እንዳገኝ አስችሎኛል፤ በዚህም እውቀት ብዙ ሰዎች ይሖዋንና ዓላማውን እንዲያውቁ መርዳት ችያለሁ።” ለ23 ዓመታት በአቅኚነት ያገለገለች በብሪታንያ የምትገኝ አንዲት እህት እንዲህ ብላለች:- “የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመንፈሳዊ ምግብ እውነተኛ ፍላጎት እንድኮተኩት ረድቶኛል።” ‘ስለ ተስፋህ’ ለሌሎች ሰዎች ማስረዳት አንተ ራስህ እንደ ውድ ነገር አድርገህ ለያዝካቸው እምነቶች ያለህን የጸና አቋም ያጠናክርልሃል። (1 ጴጥሮስ 3:15) አንዲት በአውስትራሊያ የምትገኝ አቅኚ “አቅኚነት ያመንኩበትን ነገር ለሌሎች በመናገር እምነቴን እንዳጠናክር ረድቶኛል” ብላለች።
15. አንዳንዶች አቅኚ ሆነው ለማገልገልና በዚያው ለመቀጠል ሲሉ ምን ለማድረግ ፈቃደኛ ሆነዋል? ለምንስ?
15 በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው እነዚህ አቅኚዎች ከይሖዋ ዘንድ ቁጥር ስፍር የሌለው በረከት የሚያስገኝላቸውን የአገልግሎት መስክ እንደመረጡ በሚገባ ተገንዝበዋል። ብዙዎች ወደ አቅኚነት አገልግሎት ለመግባትና በዚያው ለመቀጠል ሲሉ በሕይወታቸው ውስጥ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ለማድረግ አልፎ ተርፎም ሰብዓዊ ሥራንና ቁሳዊ ብልጽግናን መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸው ምንም አያስገርምም!—ምሳሌ 28:20
ልባችሁ ብዙ ለመሥራት ይናፍቃልን?
16, 17. (ሀ) አቅኚ መሆን ስለመቻልህ እያሰብክ ከሆነ ምን ልታደርግ ትችል ይሆናል? (ለ) አንዳንዶች አቅኚ ለመሆን ባለመቻላቸው ምን ይሰማቸዋል?
16 የአቅኚነት አገልግሎት ያለውን በረከት በሚመለከት አቅኚዎች የሰጡትን ሐሳብ ከተመለከትህ በኋላ አንተም አቅኚ መሆን ትችል እንደሆነና እንዳልሆነ እያሰብክ ይሆናል። ከሆነ ለምን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተሳካለትን አንድ አቅኚ ቀረብ ብለህ አታነጋግርም? እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ካሉት ሽማግሌዎች መካከል በደንብ የሚያውቅህን ማለትም ያለህን የጤንነት ሁኔታ፣ ያለብህን የአቅም ገደብ እንዲሁም የቤተሰብ ኃላፊነት ከሚያውቅ ሽማግሌ ጋር መወያየቱንም ጠቃሚ ሆኖ ታገኘዋለህ። (ምሳሌ 15:22) ሌሎች የሚሰጡት ከእውነታው ያልራቀ ሐሳብ አቅኚ መሆን ትችል እንደሆነና እንዳልሆነ በጥንቃቄ ለመገምገም ይረዳሃል። (ከሉቃስ 14:28 ጋር አወዳድር።) አቅኚ መሆን ከቻልክ በእርግጥም የምታገኘው በረከት ታላቅ ይሆናል።—ሚልክያስ 3:10
17 ይሁንና በአገልግሎት ብዙ ለመሥራት ቢጓጉም አቅኚ ለመሆን ሁኔታቸው ስለማይፈቅድላቸው ብዙ የታመኑ የመንግሥቱ አስፋፊዎችስ ምን ለማለት ይቻላል? ለምሳሌ ያህል አራት ልጆቿን ብቻዋን ለማሳደግ የምትታገል አንዲት ክርስቲያን እህት ምን እንደተሰማት ተመልከት። “ከአሁን በፊት የዘወትር አቅኚ ነበርኩ፤ አሁን ግን ካለኝ ሁኔታ አንጻር እንደ በፊቱ ወደ አገልግሎት መውጣት ስለማልችል ስለ ራሴ ጥሩ ስሜት የለኝም።” ይህች እህት ልጆቿን በጣም ትወዳቸዋለች፤ እነርሱን መንከባከብም ትፈልጋለች። በሌላ በኩል ደግሞ በስብከቱ ሥራ ብዙ መሥራት ትፈልጋለች። “አገልግሎት በጣም እወዳለሁ” ስትል ተናግራለች። ለአምላክ ያላቸው ፍቅር እርሱን ‘በሙሉ ልባቸው’ እንዲያገለግሉ የሚገፋፋቸው ለእርሱ ያደሩ ሌሎች ክርስቲያኖችም ተመሳሳይ ነገር ይሰማቸዋል።—መዝሙር 86:12
18. (ሀ) ይሖዋ ከእኛ የሚጠብቀው ምንድን ነው? (ለ) አንዳንድ ሁኔታዎች አቅማችንን ቢገድቡብን ተስፋ መቁረጥ የማይገባን ለምንድን ነው?
18 ይሖዋ በሙሉ ነፍሳችን እንድናገለግለው እንደሚጠብቅብን አስታውስ። የሙሉ ነፍስ አገልግሎት መጠኑ ደግሞ ከነፍስ ወደ ነፍስ ይለያያል። አንዳንዶች የዘወትር አቅኚ ሆነው ለማገልገል ሁኔታቸውን ማስተካከል ችለዋል። ሌሎች ብዙዎች ደግሞ በየወሩ በአገልግሎት 60 ሰዓት በማሳለፍ አልፎ አልፎ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ረዳት አቅኚ ሆነው ለማገልገል ይመዘገባሉ። ይሁን እንጂ ከይሖዋ ሕዝቦች መካከል አብዛኛዎቹ ለስብከቱና ለማስተማሩ ሥራ በሙሉ ነፍሳቸው ያደሩ የጉባኤ አስፋፊዎች ናቸው። በእርግጥ የጤና ችግር፣ የዕድሜ መግፋት፣ የቤተሰብ ኃላፊነቶች ወይም ሌሎች ሁኔታዎች አቅምህን የሚገድቡብህ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። ምርጥህን እስከሰጠህ ድረስ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከተሠማሩት ባልተለየ መንገድ የአንተም አገልግሎት በአምላክ ፊት ዋጋው እጅግ ከፍ ያለ ነው!
ሁላችንም የአቅኚነት መንፈስ ማሳየት እንችላለን
19. የአቅኚነት መንፈስ ምንድን ነው?
19 አቅኚ ሆነህ ማገልገል ባትችልም እንኳ የአቅኚነት መንፈስ ማሳየት ትችላለህ። የአቅኚነት መንፈስ ምንድን ነው? የሐምሌ 1988 የመንግሥት አገልግሎታችን እንዲህ ብሎ ነበር:- “እንድንሰብክና ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ ለተሰጠን ትእዛዝ አዎንታዊ አመለካከት መያዝ፣ ለሰዎች ፍቅርና አሳቢነት ለማሳየት ዝግጁ መሆን፣ የራስን ጥቅም የሚሰዉ መሆን፣ የጌታን ፈለግ በቅርብ በመከተል እንዲሁም በቁሳዊ ነገሮች ሳይሆን በመንፈሳዊ ነገሮች መደሰት የሚል ፍቺ ሊሰጠው ይችላል።” ታዲያ የአቅኚነት መንፈስ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?
20. ወላጆች የአቅኚነት መንፈስ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?
20 ወጣት ልጆች ያሏችሁ ወላጆች ከሆናችሁ አቅኚነትን ሙያቸው አድርገው መያዝን እንዲያስቡበት ለማድረግ ከልባችሁ ልትጥሩ ትችላላችሁ። እናንተ ለአገልግሎት ያላችሁ አዎንታዊ አመለካከት ለይሖዋ አገልግሎት በሕይወታቸው ውስጥ ቀዳሚውን ቦታ የመስጠቱ አስፈላጊነት በአእምሮአቸው ውስጥ እንዲቀረጽ ሊያደርግ ይችላል። ልጆቻችሁ ከእነርሱ ምሳሌ ሊጠቀሙ ይችሉ ዘንድ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ደስታ ያገኙ አቅኚዎችን እንዲሁም ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችንና ሚስቶቻቸውን ቤታችሁ መጋበዝ ትችሉ ይሆናል። (ከዕብራውያን 13:7 ጋር አወዳድር።) በሃይማኖት በተከፋፈሉ ቤቶች ውስጥ እንኳ ሳይቀር የሚያምኑት ወላጆች በቃልና ምሳሌ በመሆን ልጆቻቸው የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን የሕይወት ግባቸው እንዲያደርጉት ሊረዷቸው ይችላሉ።—2 ጢሞቴዎስ 1:5፤ 3:15
21. (ሀ) ሁላችንም አቅኚ ሆነው ለሚያገለግሉት ድጋፍ መስጠት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ሽማግሌዎች አቅኚዎችን ለማበረታታት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
21 በጉባኤ ውስጥ ሁላችንም በአቅኚነት ለማገልገል ሁኔታቸው የፈቀደላቸውን በሙሉ ልባችን ልንደግፋቸው እንችላለን። ለምሳሌ ያህል ከአንድ አቅኚ ጋር ለማገልገል ምናልባትም አብሮት የሚያገለግል ሰው በማይኖርበት ጊዜ አብረኸው ለመሥራት ለየት ያለ ጥረት ልታደርግ ትችላለህን? ይህ ‘እርስ በርስ ለመበረታታት የሚያስችል’ አጋጣሚም ሆኖ ታገኘዋለህ። (ሮሜ 1:11, 12) ሽማግሌ ከሆንህ አቅኚዎችን ለማበረታታት ከዚህ የበለጠ ነገርም ማድረግ ትችላለህ። የሽማግሌዎች አካል ስብሰባ በሚያደርግበት ጊዜ በየጊዜው አቅኚዎች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በሚመለከት ሊወያዩ ይገባል። አንድ አቅኚ ተስፋ በሚቆርጥበት ወይም አንዳንድ ችግሮች በሚገጥሙት ጊዜ አቅኚነቱን እንዲያቆም ለማድረግ አትቸኩሉ። አንዳንድ ጊዜ እንደዚያ ማድረጉ አስፈላጊ ሊሆን ቢችልም አቅኚነት የሙሉ ጊዜ አገልጋዩ ከልቡ የሚንከባከበው ውድ መብት መሆኑን አትዘንጉ። የሚያስፈልገው ጥቂት ማበረታቻና አንዳንድ ተግባራዊ ምክር ወይም ድጋፍ ብቻ ሊሆን ይችላል። በስፔይን የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሽማግሌዎች አቅኚነትን ሲያበረታቱ፣ በመስክ አገልግሎት አቅኚዎችን ሲደግፏቸውና አዘውትረው የእረኝነት ጉብኝት ሲያደርጉላቸው አቅኚዎች ደስታቸው ይጨምራል፣ ጠቃሚ እንደሆኑ ይሰማቸዋል እንዲሁም እንቅፋቶች ቢያጋጥሟቸውም ለመቀጠል ይጣጣራሉ።”
22. በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ አስቸጋሪ በሆነው በአሁኑ ጊዜ ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ለማድረግ መሆን ይገባዋል?
22 የምንኖረው በሰው ዘር ታሪክ እጅግ አስጨናቂ በሆነው ወቅት ላይ ነው። ይሖዋ ሕይወት አድን ሥራ ሰጥቶናል። (ሮሜ 10:13, 14) አቅኚ በመሆን በዚህ ሥራ ሙሉ ጊዜ መካፈል ቻልንም አልቻልን የአቅኚነትን መንፈስ እናሳይ። የጥድፊያና የራስን ጥቅም የመሠዋት ስሜት ይኑረን። ይሖዋ ከእኛ የሚጠይቀውን የሙሉ ነፍስ አገልግሎት ለመስጠት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። የምንሰጠው ነገር የሚመሳሰለው ከመበለቲቱ ትናንሽ ሳንቲሞች ጋርም ሆነ ከማርያም ውድ ሽቱ ጋር፣ መስጠት የምንችለውን ያህል ከሰጠን አገልግሎታችን በሙሉ ነፍስ የቀረበ እንደሆነና ይሖዋም ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው እናስታውስ!
ታስታውሳለህን?
◻ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የእርካታና የደስታ ስሜት የሚያመጣው ለምንድን ነው?
◻ ብዙ አቅኚዎች ይሖዋ የሚያስፈልገንን በመስጠት ረገድ ስላለው ችሎታ ከተሞክሮ ምን ተምረዋል?
◻ አቅኚዎች አገልግሎታቸው ከይሖዋ ጋር ባላቸው ዝምድና ላይ ምን ውጤት እንዳለው ይሰማቸዋል?
◻ የአቅኚነት መንፈስ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አቅኚዎች ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ታላቅ ደስታ ያገኛሉ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ልጆቻችሁ ከሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ጋር መቀራረባቸው ሊጠቅማቸው ይችላል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሽማግሌዎች አቅኚዎችን በመስክ አገልግሎት ሊያበረታቷቸው ይችላሉ