የአንባብያን ጥያቄዎች
ከመታሰቢያው ቂጣና ወይን ጠጅ የሚካፈሉት ሰዎች ቁጥር በትንሹ እንደጨመረ የተወሰኑ ዓመታት ሪፖርቶች ያሳያሉ። ታዲያ ይህ ብዙ ቁጥር ያላቸው አዳዲስ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ እየተቀቡ እንዳሉ ያመለክታልን?
የ144,000 ቅቡዓን ክርስቲያኖች ቁጥር ከአሥርተ ዓመታት በፊት እንደሞላ የሚያሳምኑ ማስረጃዎች አሉ።
የተወሰነ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ያቀፈው የዚህ ቡድን የመጀመሪያ አባላት ስለሆኑት ሰዎች ሥራ 2:1-4 ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “በዓለ ኀምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ፣ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፣ ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፣ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው። እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው። በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፣ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር።”
ከዚህ በኋላ ይሖዋ ሌሎች ሰዎችንም መርጦ በመንፈስ ቅዱሱ ቀብቷቸዋል። ክርስትና ባቆጠቆጠበት በመጀመሪያዎቹ ዓመታት በሺህ የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ተጨምረዋል። በጊዜያችን በሚከበረው የመታሰቢያ በዓል ላይ ተናጋሪው ቅቡዓን “የልጅነት መንፈስ” እንደተቀበሉ የሚገልጸውን ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 8:15-17 ላይ የተናገራቸውን ቃላት በተደጋጋሚ ይጠቅሳል። የተቀበሉት መንፈስ ‘የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውንና ከክርስቶስ ጋር አብረው ወራሾች እንደሆኑ ከመንፈሳቸው ጋር ይመሰክራል’ በማለት ጳውሎስ ጨምሮ ተናግሯል። በዚህ መንፈስ የተቀቡ ሁሉ መቀባታቸውን በሚገባ ያውቃሉ። ይህ እንዲሁ የምኞት ጉዳይ ወይም ደግሞ ከስሜታዊነትና ስለ ራሳቸው ከሚኖራቸው የተሳሳተ ግምት የሚመነጭ አይደለም።
ምንም እንኳ የጨለማ ዘመን ተብሎ በሚታወቀው ዘመን የቅቡዓኑ ቁጥር በጣም ጥቂት የሆነበት ጊዜ የነበረ ቢሆንም ይህ ሰማያዊ ጥሪ ለብዙ መቶ ዓመታት የቀጠለ እንደሆነ እናውቃለን።a እውነተኛ ክርስትና እንደገና ባንሰራራበት ባለፈው መቶ ዘመን ማብቂያ አካባቢ ተጨማሪ ሰዎች ጥሪው ቀርቦላቸው ተመርጠዋል። ይሁን እንጂ በ1930ዎች አጋማሽ ላይ የ144,000 ጠቅላላ ቁጥር የተሟላ ይመስላል። ስለዚህም ምድራዊ ተስፋ ያላቸውን ሰዎች ያቀፈ አንድ የታማኝ ክርስቲያኖች ቡድን ብቅ ማለት ጀመረ። ከቅቡዓን ጋር በአምልኮ በመተባበር ከእነርሱ ጋር አንድ መንጋ የሚሆኑትን እነዚህን ሰዎች ኢየሱስ “ሌሎች በጎች” በማለት ጠርቷቸዋል።—ዮሐንስ 10:14-16
ባለፉት አሥርተ ዓመታት የተፈጸሙት እውነታዎች የቅቡዓን ጥሪ ማብቃቱንና ይሖዋ “ከታላቁ መከራ” በሕይወት ለማለፍ ተስፋ የሚያደርጉትንና በቁጥር እየጨመሩ የሚሄዱትን “እጅግ ብዙ ሰዎች” እንደባረካቸው ያረጋግጣሉ። (ራእይ 7:9, 14) ለምሳሌ ያህል በ1935 በተከበረው የመታሰቢያው በዓል ላይ 63,146 ሰዎች ሲገኙ ከምሳሌያዊው ቂጣና ወይን ጠጅ በመካፈል እንደተቀቡ በግልጽ ያስመሰከሩት ሰዎች ቁጥር 52,465 ነበር። ከሠላሳ ዓመት በኋላ ወይም በ1965 በበዓሉ ላይ 1,933,089 ሰዎች ሲገኙ የተካፋዮቹ ቁጥር በማሽቆልቆል 11,550 ደረሰ። ከ30 ዓመት በኋላ ማለትም በ1995 የተሰብሳቢዎች ቁጥር ወደ 13,147,201 ሲደርስ ከቂጣውና ከወይኑ የተካፈሉት 8,645 ብቻ ነበሩ። (1 ቆሮንቶስ 11:23-26) በግልጽ ማየት እንደምንችለው ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ከቀሪዎች ክፍል እንደሆኑ የሚናገሩት ሰዎች ቁጥር በጣም እየቀነሰ ሄዷል። በ1935 52,400፤ በ1965 11,500፤ በ1995 8,600 ያህል ነበሩ። በአንጻሩ ደግሞ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ተባርከዋል እንዲሁም ቁጥራቸው በጣም ጨምሯል።
በቅርቡ የተመዘገበው የ1995 ሪፖርት እንደሚያሳየው ከቂጣውና ከወይኑ የተካፈሉት ሰዎች ቁጥር በስብሰባው ላይ ከተገኙት ሰዎች በሬሾ ደረጃ ሲታይ በጣም ያነሰ ነበር፤ ቢሆንም በ1995 በተከበረው በዓል ላይ ከወይኑና ከቂጣው የተካፈሉት ሰዎች ቁጥር ከፊተኛው ዓመት በ28 ጨምሯል። ጥቂት ተጨማሪ ሰዎች ከቂጣውና ከወይኑ መካፈል መጀመራቸው እኛን ሊያሳስበን አይገባም። ባለፉት ዓመታት የተጠመቁ አንዳንድ አዳዲስ ሰዎች እንኳን ሳይቀሩ ከቂጣውና ከወይኑ በድንገት መካፈል ጀምረዋል። ከጊዜ በኋላ ግን ብዙዎቹ እንዲህ ማድረጋቸው ትክክል እንዳልነበረ አምነው ተቀብለዋል። አንዳንዶቹ በአካላቸው ወይም በአእምሯቸው ውስጥ በተፈጠረው ውጥረት ምክንያት ሊሆን ይችላል በስሜት ተነሳስተው እንደተካፈሉ ተናግረዋል። ለሰማያዊው ሕይወት በእርግጥ እንዳልተጠሩም ተገንዝበዋል። አምላክ ሁኔታዎቹን ተረድቶ እንዲምራቸው ጠይቀዋል። በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ይዘው ንጹሕና ታማኝ ክርስቲያን ሆነው እርሱን ማገልገል ቀጥለዋል።
አንድ ሰው ከቂጣውና ከወይኑ መካፈል ቢጀምር ወይም ቢያቆም ሁኔታው እኛን ሊያሳስበን አይገባም። አንድ ግለሰብ በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቶ ለሰማያዊው ጥሪ መጠራቱ ወይም አለመጠራቱ እኛን የሚመለከት ጉዳይ አይደለም። ‘መልካሙ እረኛ እኔ ነኝ። በጎቼንም አውቃቸዋለሁ’ በማለት ኢየሱስ የሰጠውን ጠንካራ ማረጋገጫ አስታውስ። እንደሚታወቀው ይሖዋ መንፈሳዊ ልጆች አድርጎ የመረጣቸውን ለይቶ እንደሚያውቅ ምንም አያጠራጥርም። የዕድሜ መግፋትና የተለያዩ ድንገተኛ አደጋዎች ምድራዊ ሕይወታቸውን እንዲጨርሱ ስለሚያደርጓቸው የቅቡዓን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ እንደሚሄድ ለማመን የሚያስችል በቂ ምክንያት አለ። ሆኖም እነዚህ እውነተኛ ቅቡዓን እስከ ሞት ድረስ ታማኝነታቸውን በመጠበቅ የሕይወት ሽልማት የሚቀበሉበትን ጊዜ በጉጉት እንደሚጠባበቁ ሁሉ ልብሳቸውን በበጉ ደም ያጠቡት ሌሎች በጎችም እየቀረበ ካለው ታላቅ መከራ በሕይወት የሚተርፉበትን ጊዜ በጉጉት ሊጠባበቁ ይችላሉ።—2 ጢሞቴዎስ 4:6-8፤ ራእይ 2:10
[የግርጌ ማስታወሻ]