የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 9/15 ገጽ 10-15
  • ሁሉም ለአምላክ መልስ መስጠት አለበት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሁሉም ለአምላክ መልስ መስጠት አለበት
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መላእክት በአምላክ ፊት ተጠያቂ ናቸው
  • የአምላክ ልጅም ተጠያቂ ነው
  • በብሔር ደረጃ ተጠያቂ መሆን
  • በግለሰብ ደረጃ ያለውን ተጠያቂነት የሚያሳዩ ምሳሌዎች
  • በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያለ ተጠያቂነት
  • መልሳችሁ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኝ ይሁን
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • የአንባቢያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
  • ክርስቲያኖች እርስ በርስ መደጋገፍ አለባቸው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
  • ብሔራት “እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ”
    የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መልሶ ተቋቋመ!
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 9/15 ገጽ 10-15

ሁሉም ለአምላክ መልስ መስጠት አለበት

“እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን።”—ሮሜ 14:12

1. አዳምና ሔዋን የነበራቸው ነፃነት ምን ገደብ ነበረው?

ይሖዋ አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወላጆቻችንን ማለትም አዳምንና ሔዋንን ሲፈጥር የራሳቸውን ምርጫ የማድረግ ነፃነት ሰጥቷቸው ነበር። ከመላእክት ያነሱ ቢሆኑም እንኳ ጥበብ ያለበት ውሳኔ ማድረግ የሚችሉ ጥሩ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት ነበሩ። (መዝሙር 8:4, 5) ሆኖም ይህ አምላክ የሰጣቸው ነፃነት መልካምና ክፉ የሆነውን ነገር ራሳቸው እንዲወስኑ የሚፈቅድላቸው አልነበረም። በፈጣሪያቸው ፊት ተጠያቂዎች ነበሩ፤ ይህ ተጠያቂነት ደግሞ ለዘሮቻቸው ሁሉ ተላልፏል።

2. ይሖዋ በቅርቡ ምንን በተመለከተ ፍርድ ይሰጣል? ለምንስ?

2 አሁን ይህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ወደሚያከትምበት ጊዜ እየተቃረብን በመሆኑ ይሖዋ ምድርን በተመለከተ ፍርድ ይሰጣል። (ከሮሜ 9:28 የ1980 ትርጉም ጋር አወዳድር።) ለአምላክ አክብሮት የሌላቸው ሰዎች የምድርን የተፈጥሮ ሀብት በማራቆት፣ የሰውን ሕይወት በማጥፋትና በተለይ ደግሞ በአምላክ አገልጋዮች ላይ ስደት በማድረስ ለፈጸሙት ድርጊት በቅርቡ በይሖዋ አምላክ ፊት መልስ ይሰጣሉ።—ራእይ 6:10፤ 11:18

3. የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

3 ከፊታችን ይህን የመሰለ አሳሳቢ ሁኔታ የተደቀነ በመሆኑ ይሖዋ ባለፉት ዘመናት ከፍጥረታቱ ጋር ያደረገውን ፍትሃዊ የሆነ ግንኙነት መመልከቱ ጠቃሚ ነው። በግለሰብ ደረጃ ለፈጣሪያችን ተቀባይነት ያለው መልስ መስጠት እንድንችል ቅዱሳን ጽሑፎች ሊረዱን የሚችሉት እንዴት ነው? የትኞቹ ምሳሌዎች ሊረዱን ይችላሉ? ልንመስላቸው የማይገቡን ምሳሌዎችስ የትኞቹ ናቸው?

መላእክት በአምላክ ፊት ተጠያቂ ናቸው

4. መላእክት ለሚፈጽሟቸው ድርጊቶች በአምላክ ፊት ተጠያቂ እንደሆኑ እንዴት እናውቃለን?

4 በሰማይ ያሉት የይሖዋ መላእክታዊ ፍጥረታትም ልክ እንደ እኛ ለይሖዋ መልስ ይሰጣሉ። በኖኅ ዘመን ከነበረው የጥፋት ውኃ በፊት የተወሰኑ መላእክት ከሴቶች ጋር የጾታ ግንኙነት ለመፈጸም ሲሉ የአምላክን ትእዛዝ በመጣስ ሥጋ ለበሱ። እነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታት የራሳቸውን ምርጫ የማድረግ ነፃነት ያላቸው አካሎች በመሆናቸው የራሳቸውን ውሳኔ መውሰድ ቢችሉም አምላክ ተጠያቂ አድርጓቸዋል። ዓመፀኞቹ መላእክት ወደ መንፈሳዊው ዓለም ሲመለሱ ይሖዋ የቀድሞውን ቦታቸውን መልሰው እንዲያገኙ አልፈቀደላቸውም። “በዘላለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ” ተጠብቀው እንደሚገኙ ደቀ መዝሙሩ ይሁዳ ይነግረናል።—ይሁዳ 6

5. ሰይጣንና አጋንንቱ ምን ውድቀት ደርሶባቸዋል? ለፈጸሙት ዓመፅ የሚቀርብባቸው ክስ ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው?

5 እነዚህ ዓመፀኛ መላእክት ወይም አጋንንት ሰይጣን ዲያብሎስን መሪያቸው አደረጉ። (ማቴዎስ 12:24-26) ይህ ክፉ መልአክ በፈጣሪው ላይ በማመፅ የይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክለኛ የመሆኑን ጉዳይ አጠያያቂ አደረገው። ሰይጣን የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ኃጢአት እንዲሠሩ አደረጋቸው፤ ይህም በመጨረሻ ሞት አስከተለባቸው። (ዘፍጥረት 3:1-7, 17-19) ምንም እንኳ ከዚያ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ሰይጣን ወደ ሰማይ አደባባዮች መግባት እንዲችል ይሖዋ ፈቅዶለት የነበረ ቢሆንም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የራእይ መጽሐፍ ይህ ክፉ መልአክ አምላክ በወሰነው ጊዜ ወደ ምድር እንደሚጣል አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ በ1914 ንጉሣዊ ሥልጣኑን ከተቀበለ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ይህ ሁኔታ እንደተፈጸመ ማስረጃዎቹ ያሳያሉ። ውሎ አድሮ ደግሞ ዲያብሎስና አጋንንቱ ለዘላለም ይጠፋሉ። ሉዓላዊነትን በተመለከተ የተነሳው አከራካሪ ጉዳይ በመጨረሻ መፍትሔ ያገኝና ለዓመፅ የሚሰጠው ፍርድ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ፍጻሜውን ያገኛል።—ኢዮብ 1:6-12፤ 2:1-7፤ ራእይ 12:7-9፤ 20:10

የአምላክ ልጅም ተጠያቂ ነው

6. ኢየሱስ በአባቱ ፊት ያለበትን የራሱን ተጠያቂነት የሚመለከተው እንዴት ነው?

6 የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በጣም ግሩም የሆነ ምሳሌ ትቶልናል! ከአዳም እኩል ፍጹም ሰው የሆነው ኢየሱስ መለኮታዊውን ፈቃድ ማድረግ ያስደስተው ነበር። በተጨማሪም የይሖዋን ሕግ መጠበቅ የሚያስከትልበትን ኃላፊነት ለመወጣት ሙሉ በሙሉ ፈቃደኛ ነበር። መዝሙራዊው “አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ለማድረግ ወደድሁ፣ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው” በማለት ስለ እሱ ትክክለኛ ትንቢት ተናግሯል።—መዝሙር 40:8፤ ዕብራውያን 10:6-9

7. ኢየሱስ በሞቱ ዋዜማ ላይ ሲጸልይ በዮሐንስ 17:4, 5 ላይ ያሉትን ቃላት ሊናገር የቻለው ለምንድን ነው?

7 ኢየሱስ አስከፊ ተቃውሞ የደረሰበት ቢሆንም እንኳ የአምላክን ፈቃድ ከመፈጸሙም በላይ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ እስኪሞት ድረስ ንጹሕ አቋሙን ጠብቋል። ይህንንም በማድረጉ የሰውን ዘር የአዳም ኃጢአት ካመጣቸው ሞት የሚያስከትሉ መዘዞች የሚቤዠውን የቤዛ ዋጋ ከፍሏል። (ማቴዎስ 20:28) በመሆኑም ኢየሱስ በሞቱ ዋዜማ ላይ እንዲህ በማለት በልበ ሙሉነት ሊጸልይ ችሏል፦ “እኔ፣ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ፤ አሁንም፣ አባት ሆይ፣ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ።” (ዮሐንስ 17:4, 5) ኢየሱስ ያጋጠመውን የተጠያቂነት ፈተና ስኬታማ በሆነ መንገድ በመወጣቱና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱ ከላይ የተጠቀሱትን ቃላት ለሰማያዊ አባቱ መናገር ችሏል።

8. (ሀ) ጳውሎስ ስለ ራሳችን ለይሖዋ አምላክ መልስ መስጠት እንዳለብን የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) በአምላክ ፊት ተቀባይነት እንድናገኝ ምን ሊረዳን ይችላል?

8 እኛ ፍጹም ሰው ከነበረው ከኢየሱስ ክርስቶስ የተለየን ነን፤ ፍጹማን ሰዎች አይደለንም። ሆኖም፣ በአምላክ ፊት ተጠያቂዎች ነን። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “አንተም በወንድምህ ላይ ስለ ምን ትፈርዳለህ? ወይስ አንተ ደግሞ ወንድምህን ስለ ምን ትንቃለህ? ሁላችን በክርስቶስ [“በእግዚአብሔር፣” የ1980 ትርጉም] ፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለንና። እኔ ሕያው ነኝ፣ ይላል ጌታ፣ ጒልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል መላስም ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግናል ተብሎ ተጽፎአልና። እንግዲያስ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን።” (ሮሜ 14:10-12) ይህን ማድረግ እንድንችልና በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንድናገኝ በምንናገረውና በምናደርገው ነገር እኛን ለመምራት ሲል ይሖዋ በፍቅር ተገፋፍቶ ሕሊናና በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ሰጥቶናል። (ሮሜ 2:14, 15፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ይሖዋ ባዘጋጃቸው መንፈሳዊ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ መጠቀማችንና በመጽሐፍ ቅዱስ የሰለጠነውን ሕሊናችንን መከተላችን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንድናገኝ ይረዳናል። (ማቴዎስ 24:45-47) የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይሉ ተጨማሪ ብርታትና መመሪያ ይሰጠናል። ከመንፈሱ አመራርና በመጽሐፍ ቅዱስ የሰለጠነው ሕሊናችን ከሚሰጠን መመሪያ ጋር በሚስማማ መንገድ የምንመላለስ ከሆነ ለሠራናቸው ሥራዎች ሁሉ መልስ የምናቀርብለትን ‘አምላክ እንዳላቃለልን’ እናሳያለን።—1 ተሰሎንቄ 4:3-8፤ 1 ጴጥሮስ 3:16, 21

በብሔር ደረጃ ተጠያቂ መሆን

9. ኤዶማውያን እነማን ነበሩ? በእስራኤላውያን ላይ በፈጸሙት ድርጊት ምክንያት ምን ደረሰባቸው?

9 ይሖዋ ብሔራትን ተጠያቂ ያደርጋቸዋል። (ኤርምያስ 25:12-14፤ ሶፎንያስ 3:6, 7) ከሙት ባሕር በስተ ደቡብና ከአካባ ባሕረ ሰላጤ በስተ ሰሜን ትገኝ የነበረችውን የጥንቷን የኤዶም መንግሥት ተመልከት። ኤዶማውያን ከእስራኤላውያን ጋር የቅርብ ዝምድና የነበራቸው የሴም ዝርያ የሆኑ ሕዝቦች ነበሩ። የኤዶማውያን የቀድሞ አባት የአብርሃም የልጅ ልጅ የሆነው ኤሳው የነበረ ቢሆንም እንኳ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ይጓዙ በነበረበት ጊዜ በኤዶም አድርገው “በንጉሡ ጎዳና” ለማለፍ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አላገኘም። (ዘኁልቁ 20:14-21) ኤዶማውያን በእስራኤላውያን ላይ የነበራቸው ጥላቻ ዘመናት እያለፉ ሲሄዱ በጣም እየከረረ ሄደ። በመጨረሻም ኤዶማውያን በ607 ከዘአበ ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን እንዲያጠፉ በመገፋፋት ለፈጸሙት ሥራ መልስ መስጠት ነበረባቸው። (መዝሙር 137:7) በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በንጉሥ ናቦኒደስ ይመሩ የነበሩት የባቢሎን ወታደሮች ኤዶምን ድል አደረጓትና ይሖዋ በሰጠው ብያኔ መሠረት ባድማ ሆነች።—ኤርምያስ 49:20፤ አብድዩ 9-11

10. ሞዓባውያን በእስራኤላውያን ላይ የፈጸሙት ነገር ምን ነበር? አምላክ በሞዓብ ላይ የፈረደውስ እንዴት ነው?

10 ሞዓብም ተመሳሳይ ዕጣ ደርሶባታል። የሞዓብ ንጉሣዊ ግዛት ይገኝ የነበረው ከኤዶም በስተ ሰሜንና ከሙት ባሕር በስተ ምሥራቅ ነበር። እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው በፊት ሞዓባውያን በእንግድነት አልተቀበሏቸውም፤ ዳቦና ውኃም የሰጧቸው የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ እንደነበረ ግልጽ ነው። (ዘዳግም 23:3, 4) የሞዓብ ንጉሥ የነበረው ባላቅ እስራኤልን እንዲረግምለት ለነቢዩ በለዓም ገንዘብ ሰጥቶታል፤ የሞዓባውያን ሴቶችም እስራኤላውያን ወንዶች የጾታ ብልግናና የጣዖት አምልኮ እንዲፈጽሙ ለማድረግ መሣሪያ ሆነው አገልግለዋል። (ዘኁልቁ 22:2-8፤ 25:1-9) ይሁን እንጂ ይሖዋ ሞዓባውያን ለእስራኤላውያን የነበራቸውን ጥላቻ በቸልታ አላለፈውም። በትንቢት እንደተነገረው ሞዓብ በባቢሎናውያን ጠፍታለች። (ኤርምያስ 9:25, 26፤ ሶፎንያስ 2:8-11) አዎን፣ አምላክ ሞዓብን ተጠያቂ አድርጓታል።

11. ሞዓብና አሞን እንደ የትኞቹ ከተሞች ሆኑ? የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በአሁኑ ጊዜ ስላለው ክፉ የነገሮች ሥርዓት ምን የሚጠቁሙት ነገር አለ?

11 ሞዓብ ብቻ ሳትሆን አሞንም በአምላክ ፊት ተጠያቂ ነበረች። ይሖዋ “ሞዓብ እንደ ሰዶም፣ የአሞንም ልጆች እንደ ገሞራ፣ የሳማ ስፍራና የጨው ጉድጓድ ለዘላለምም ምድረ በዳ ሆነው ይኖራሉ” ሲል አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። (ሶፎንያስ 2:9) አምላክ የሰዶምንና የገሞራን ከተሞች እንዳጠፋ ሁሉ የሞዓብንና የአሞንን ምድርም ባድማ አድርጎታል። የለንደን የጂኦሎጂ ጥናት ማኅበር እንዳለው ከሆነ የጠፉት የሰዶምና ገሞራ ከተሞች ይገኙበት የነበረውን ቦታ በሙት ባሕር ምሥራቃዊ ዳርቻ እንዳገኙት ተመራማሪዎች ይናገራሉ። በዚህ ረገድ ወደፊት ሊገኝ የሚችል ማንኛውም እውነተኛ ማስረጃ በአሁኑ ጊዜ ያለው ክፉ የነገሮች ሥርዓትም በይሖዋ አምላክ ተጠያቂ እንደሚሆን በማመልከት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን የሚደግፍ ነው።—2 ጴጥሮስ 3:6-12

12. ምንም እንኳ እስራኤል ለፈጸመችው ኃጢአት ለአምላክ መልስ መስጠት የነበረባት ቢሆንም ስለ አይሁድ ቀሪዎች ምን ትንቢት ተነግሮ ነበር?

12 ምንም እንኳ እስራኤል በይሖዋ ዘንድ ከፍተኛ ሞገስ አግኝታ የነበረ ቢሆንም ለፈጸመችው ኃጢአት ለአምላክ መልስ መስጠት ነበረባት። ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እስራኤል ሕዝብ ሲመጣ አብዛኞቹ አልተቀበሉትም። በእሱ ያመኑትና ተከታዮቹ የሆኑት ጥቂት ቀሪዎች ብቻ ነበሩ። ጳውሎስ እንደዚህ ብሎ በጻፈ ጊዜ የተወሰኑ ትንቢቶችን እነዚህን የአይሁድ ቀሪዎች ለማመልከት ተጠቅሞባቸዋል፦ “ኢሳይያስም፦ የእስራኤል ልጆች ቁጥር ምንም እንደ ባሕር አሸዋ ቢሆን ቅሬታው ይድናል፤ ጌታ ነገሩን ፈጽሞና ቈርጦ በምድር ላይ ያደርገዋልና ብሎ ስለ እስራኤል ይጮኻል። ኢሳይያስም እንደዚሁ፦ ጌታ ፀባዖት ዘር ባላስቀረልን እንደ ሰዶም በሆንን ገሞራንም በመሰልን ነበር ብሎ አስቀድሞ ተናገረ።” (ሮሜ 9:27-29፤ ኢሳይያስ 1:9፤ 10:22, 23) ሐዋርያው በኤልያስ ዘመን የነበሩት ለበኣል ያልሰገዱትን 7,000 ሰዎች ምሳሌ ከጠቀሰ በኋላ “እንደዚሁም በአሁን ዘመን ደግሞ በጸጋ የተመረጡ ቅሬታዎች አሉ” ሲል ተናግሯል። (ሮሜ 11:5) እነዚህ ቀሪዎች በግለሰብ ደረጃ በአምላክ ፊት ተጠያቂ የሆኑ ሰዎች ናቸው።

በግለሰብ ደረጃ ያለውን ተጠያቂነት የሚያሳዩ ምሳሌዎች

13. ወንድሙን አቤልን በመግደል ለፈጸመው ድርጊት አምላክ ተጠያቂ ባደረገው ጊዜ ቃየን ምን ደረሰበት?

13 መጽሐፍ ቅዱስ በይሖዋ አምላክ ፊት በግለሰብ ደረጃ ተጠያቂ የሆኑ ብዙ ሰዎችን ይጠቅሳል። ለምሳሌ ያህል የአዳም የበኩር ልጅ የሆነውን ቃየንን እንውሰድ። እሱና ወንድሙ አቤል ለይሖዋ መሥዋዕት አቅርበው ነበር። የአቤል መሥዋዕት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ሲያገኝ የቃየን ግን ተቀባይነት አላገኘም ነበር። ወንድሙን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በመግደሉ አምላክ ላቀረበለት ጥያቄ “የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን?” የሚል አዘኔታ የጎደለው መልስ ሰጥቷል። ቃየን በሰራው ኃጢአት ምክንያት ከሚኖርበት አካባቢ ተባርሮ “ከዔድንም ወደ ምሥራቅ በኖድ ምድር ተቀመጠ።” በተበየነበት ትክክለኛ ቅጣት ከማዘን በስተቀር ለሠራው ወንጀል ልባዊ ጸጸት አላሳየም።—ዘፍጥረት 4:3-16

14. በግለሰብ ደረጃ በአምላክ ፊት ተጠያቂ የመሆን ጉዳይ በሊቀ ካህኑ ዔሊና በልጆቹ ሁኔታ ላይ የታየው እንዴት ነው?

14 በግለሰብ ደረጃ በአምላክ ፊት ተጠያቂ የመሆን ጉዳይ የእስራኤል ሊቀ ካህን በነበረው በዔሊ ሁኔታም ላይ ታይቷል። አፍኒንና ፊንሐስ የተባሉት ልጆቹ ዋነኛ ካህናት ሆነው ያገለግሉ የነበረ ቢሆንም “በሰው ላይ ይፈጽሙ በነበረው ግፍ ተጠያቂዎች ነበሩ፤ በተጨማሪም ፈሪሃ አምላክ የጎደላቸውና ከክፋት ሁሉ ያልራቁ ሰዎች ነበሩ” ሲል ታሪክ ጸሐፊው ጆሴፈስ ገልጿል። እነዚህ “ምናምንቴዎች” ይሖዋን አልተቀበሉም፤ የረከሰ ምግባር ይፈጽሙ ነበር፤ በተጨማሪም ከባድ የጾታ ብልግና በመፈጸም ተጠያቂዎች ነበሩ። (1 ሳሙኤል 1:3፤ 2:12-17, 22-25) ዔሊ አባታቸውና የእስራኤል ሊቀ ካህን እንደመሆኑ መጠን እነሱን የመገሰጽ ግዴታ ነበረበት፤ ሆኖም ለዘብ ያለ እርምት በመስጠት አልፏቸዋል። ዔሊ ‘ለልጆቹ ከይሖዋ የበለጠ ክብር ሰጥቷቸዋል።’ (1 ሳሙኤል 2:29) በዚህም ምክንያት በዔሊ ቤት ላይ መዓት ወርዷል። ሁለቱም ልጆች አባታቸው በሞተበት በዚያው ዕለት ሞተዋል፤ ከጊዜ በኋላም በዘር ሐረጋቸው ሲተላለፍ የቆየው በክህነት የማገልገል መብት ሙሉ በሙሉ ተቋረጠ። በዚህ መንገድ ፍርዱ ተፈጸመ።—1 ሳሙ ኤል 3:13, 14፤ 4:11, 17, 18

15. የንጉሥ ሳኦል ልጅ የሆነው ዮናታን የተካሰው ለምንድን ነው?

15 የንጉሥ ሳኦል ልጅ የሆነው ዮናታን የተወው ምሳሌ ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። ዳዊት ጎልያድን ከገደለው በኋላ ብዙም ሳይቆይ “የዮናታን ነፍስ በዳዊት ነፍስ ታሰረች፤” ከዚያም የወዳጅነት ቃል ኪዳን አደረጉ። (1 ሳሙኤል 18:1, 3) ዮናታን የአምላክ መንፈስ ከሳኦል እንደራቀ ሳይገነዘብ አልቀረም፤ ሆኖም እሱ ለእውነተኛ አምልኮ የነበረው ቅንዓት አልጠፋም። (1 ሳሙኤል 16:14) ዮናታን አምላክ ለዳዊት ለሰጠው ስልጣን የነበረው አክብሮት አልቀነሰም። ዮናታን በአምላክ ፊት ያለበትን ተጠያቂነት ተገንዝቦ ነበር፤ ይሖዋም የዘር ሐረጉ ለብዙ ትውልዶች እንዲቀጥል በማድረግ ዮናታን ላሳየው ትክክለኛ ምግባር ክሶታል።—1 ዜና መዋዕል 8:33-40

በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያለ ተጠያቂነት

16. ቲቶ ማን ነበር? ስለ ራሱ ለአምላክ ጥሩ መልስ ሰጥቷል ሊባል የሚቻለውስ ለምንድን ነው?

16 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ ራሳቸው ጥሩ መልስ ስለሰጡ ብዙ ወንዶችና ሴቶች መልካም ምግባር ይናገራሉ። ግሪካዊውን ክርስቲያን ቲቶን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ቲቶ ክርስቲያን የሆነው ጳውሎስ በመጀመሪያው ሚስዮናዊ ጉዞው ወደ ቆጵሮስ በሄደበት ጊዜ እንደነበረ ይገመታል። በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ከቆጵሮስ የመጡ አይሁዳውያንና ወደ አይሁድ እምነት የተለወጡ ሰዎች ተገኝተው ሊሆን ስለሚችል ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ክርስትና ወደዚያች ደሴት ደርሶ ሊሆን ይችላል። (ሥራ 11:19) ያም ሆነ ይህ ቲቶ ከጳውሎስ ታማኝ የሥራ አጋሮች አንዱ ሆኗል። ግዝረትን በተመለከተ ተነስቶ የነበረው አከራካሪ ጉዳይ እልባት ባገኘበት ወቅት ማለትም በ49 እዘአ ገደማ ጳውሎስና በርናባስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዙ አብሯቸው ሄዷል። ቲቶ ያልተገረዘ መሆኑ ጳውሎስ ወደ ክርስትና የተለወጡ አሕዛብ በሙሴ ሕግ ሥር መሆን የለባቸውም ለሚለው የመከራከሪያ ሐሳቡ ጥሩ ማጠናከሪያ ሆኖለታል። (ገላትያ 2:1-3) ቲቶ ያከናወነው መልካም አገልግሎት በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተገልጿል፤ እንዲያውም ጳውሎስ በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ደብዳቤ ልኮለታል። (2 ቆሮንቶስ 7:6፤ ቲቶ 1:1-4) በምድራዊ ሕይወቱ መገባደጃ ላይም ቲቶ ስለ ራሱ ለአምላክ መልካም መልስ መስጠቱን እንደቀጠለ በግልጽ መረዳት ይቻላል።

17. ጢሞቴዎስ ስለ ራሱ ምን መልስ ሰጥቷል? ይህ ምሳሌ እኛን ሊነካን የሚችለውስ እንዴት ነው?

17 ጢሞቴዎስ ስለ ራሱ በይሖዋ አምላክ ፊት ተቀባይነት ያለው መልስ ያቀረበ ሌላው ቀናተኛ ሰው ነው። ምንም እንኳ ጢሞቴዎስ አንዳንድ የጤና ችግሮች የነበሩት ቢሆንም ‘ግብዝነት የሌለበት እምነት’ ከማሳየቱም በላይ ‘ምሥራቹን በማስፋፋቱ ሥራ ከጳውሎስ ጋር አገልግሏል።’ በመሆኑም ሐዋርያው በፊልጵስዩስ ለሚገኙት መሰል ክርስቲያኖች “እንደ [ጢሞቴዎስ] ያለ፣ ስለ ኑሮአችሁ በቅንነት የሚጨነቅ፣ ማንም የለኝም” ሊላቸው ችሏል። (2 ጢሞቴዎስ 1:5፤ ፊልጵስዩስ 2:20, 22፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:23) እኛም ሰብዓዊ ድክመቶችና ሌሎች ፈተናዎች ያሉብን ቢሆንም እንኳ ግብዝነት የሌለበት እምነት መያዝና ስለ ራሳችን ለአምላክ ተቀባይነት ያለው መልስ መስጠት እንችላለን።

18. ልድያ ማን ነበረች? ምን ዓይነት መንፈስስ አሳይታለች?

18 ልድያ ስለ ራሷ ለአምላክ ጥሩ መልስ ያቀረበች አምላካዊ አክብሮት የነበራት ሴት ነበረች። እሷና ቤተሰቧ ጳውሎስ በ50 እዘአ ገደማ በፊልጵስዩስ ውስጥ ባደረገው እንቅስቃሴ ምክንያት በአውሮፓ ውስጥ ክርስትናን ከተቀበሉት የመጀመሪያ ሰዎች መካከል የሚገኙ ናቸው። የትያጥሮን ተወላጅ የሆነችው ልድያ ወደ አይሁድ እምነት የተለወጠች ሴት ሳትሆን አትቀርም፤ ሆኖም በፊልጵስዩስ ውስጥ የነበሩት አይሁዶች በጣም ጥቂቶች ሊሆኑ ይችላሉ፤ በተጨማሪም በፊልጵስዩስ ውስጥ አንድም ምኩራብ አልነበረም። ጳውሎስ ባነጋገራቸው ጊዜ እሷና ለአምላክ ያደሩ ሌሎች ሴቶች በአንድ ወንዝ አጠገብ ተሰብስበው ነበር። በውጤቱም ልድያ ክርስቲያን ሆነች፤ እንዲሁም ጳውሎስና አብረውት የነበሩት ሰዎች እሷ ቤት እንዲያርፉ አደረገች። (ሥራ 16:12-15) ልድያ ያሳየችው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እውነተኛ ክርስቲያኖች ተለይተው የሚታወቁበት ባሕርይ ሆኖ ኖሯል።

19. ዶርቃ ስለ ራሷ ለአምላክ ጥሩ መልስ የሰጠችው የትኞቹን መልካም ነገሮች በመፈጸም ነው?

19 ስለ ራሷ ለይሖዋ አምላክ ጥሩ መልስ የሰጠች ሌላዋ ሴት ዶርቃ ነች። በሞተች ጊዜ ጴጥሮስ በዚያ ይኖሩ የነበሩ ደቀ መዛሙርት ያቀረቡትን ጥያቄ በመቀበል ወደ ኢዮጴ ሄደ። ጴጥሮስን ያገኙት ሁለቱ ሰዎች ወደ “ሰገነት አወጡት፤ መበለቶችም ሁሉ እያለቀሱ ዶርቃ ከእነርሱ ጋር ሳለች ያደረገቻቸውን ቀሚሶችንና ልብሶችን ሁሉ እያሳዩት በፊቱ ቆሙ።” ዶርቃ እንደገና ሕያው ሆነች። ይሁን እንጂ ዶርቃ የምትታወሰው በነበራት የለጋስነት መንፈስ ብቻ ነውን? አይደለም። ዶርቃ “ደቀ መዝሙር” ነበረች፤ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራም እንደተካፈለች ጥርጥር የለውም። በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ክርስቲያን ሴቶች ‘ለጋሶችና ብዙ መልካም ነገሮች የሚያደርጉ’ ናቸው። በተጨማሪም የመንግሥቱን ምሥራች በማወጁና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በትጋት መሳተፍ ያስደስታቸዋል።—ሥራ 9:36-42፤ ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20

20. የትኞቹን ጥያቄዎች ራሳችንን ልንጠይቅ እንችላለን?

20 ብሔራትም ሆኑ ሰዎች ለሉዓላዊው ጌታ ለይሖዋ መልስ መስጠት እንዳለባቸው መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያሳያል። (ሶፎንያስ 1:7) ራሳችንን ለአምላክ የወሰንን ከሆንን ‘አምላክ የሰጠኝን መብቶችና ኃላፊነቶች የምመለከተው እንዴት ነው? ስለ ራሴ ለይሖዋ አምላክና ለኢየሱስ ክርስቶስ ምን ዓይነት መልስ እየሰጠሁ ነው?’ ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ እንችላለን።

መልሶችህ ምንድን ናቸው?

◻ መላእክትና የአምላክ ልጅ በይሖዋ ፊት ተጠያቂ መሆናቸውን እንዴት ልታስረዳ ትችላለህ?

◻ አምላክ ብሔራትን ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው የሚያሳዩት የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ናቸው?

◻ መጽሐፍ ቅዱስ በግለሰብ ደረጃ በአምላክ ፊት ተጠያቂ መሆንን በተመለከተ ምን ይላል?

◻ ለይሖዋ አምላክ ጥሩ መልስ የሰጡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝገበው የሚገኙ አንዳንድ ሰዎች እነማን ናቸው?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ራሱ ለሰማያዊ አባቱ ጥሩ መልስ ሰጥቷል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ሴቶች ልክ እንደ ዶርቃ ስለ ራሳቸው ለይሖዋ አምላክ ጥሩ መልስ ይሰጣሉ

[ምንጭ]

The Death of Abel/The Doré Bible Illustrations/Dover Publications, Inc.

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ