መልሳችሁ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኝ ይሁን
“አምላኬ ሆይ፣ ስለዚህ ደግሞ አስበኝ . . . አምላኬ ሆይ፣ በመልካም አስበኝ።”—ነህምያ 13:22, 31
1. ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ሰዎች ለይሖዋ ጥሩ መልስ መስጠት እንዲችሉ የሚረዳቸው ነገር ምንድን ነው?
የይሖዋ አገልጋዮች ለአምላክ ጥሩ መልስ መስጠት እንዲችሉ አስፈላጊው እርዳታ ሁሉ ይደረግላቸዋል። ለምን? ምክንያቱም የምድራዊ ድርጅቱ አካል በመሆን ከአምላክ ጋር የተቀራረበ ዝምድና ስላላቸው ነው። ዓላማዎቹን ገልጾላቸዋል፤ በተጨማሪም በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ድጋፍና መንፈሳዊ ማስተዋል ሰጥቷቸዋል። (መዝሙር 51:11፤ 119:105፤ 1 ቆሮንቶስ 2:10-13) እነዚህን ልዩ ሁኔታዎች ግምት ውስጥ በማስገባት ይሖዋ ምድራዊ አገልጋዮቹ ስለ ራሳቸው እንዲሁም እርሱ በሚሰጣቸው ብርታትና ቅዱስ መንፈሱ በሚሰጣቸው እርዳታ ስላከናወኑት ነገር መልስ እንዲሰጡት ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ይጠይቃል።
2. (ሀ) ነህምያ ስለ ራሱ ለአምላክ ጥሩ መልስ የሰጠው በምን መንገዶች ነው? (ለ) ነህምያ በስሙ የተጻፈውንና የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን መጽሐፍ የቋጨው በየትኛው የልመና ቃል ነው?
2 የፋርሱ ንጉሥ የአርጤክስስ (ሎንጊማነስ) ጠጅ አሳላፊ የነበረው ነህምያ ስለ ራሱ ለአምላክ ጥሩ መልስ የሰጠ ሰው ነበር። (ነህምያ 2:1) ነህምያ የአይሁዶች ገዥ ከሆነ በኋላ ጠላቶችና አደገኛ ሁኔታዎች እያሉ የኢየሩሳሌምን ግንብ እንደገና መገንባት ጀመረ። ለእውነተኛ አምልኮ ቅንዓት በማሳየት የአምላክን ሕግ ከማስፈጸሙም በላይ ለተጨቆኑ ሰዎች አሳቢነት አሳይቷል። (ነህምያ 5:14-19) ነህምያ ሌዋውያን ዘወትር ራሳቸውን እንዲያነጹ፣ በሮቹን እንዲጠብቁና የሰንበትን ቀን እንዲቀድሱ አጥብቆ አሳስቧቸው ነበር። በመሆኑም “አምላኬ ሆይ፣ ስለዚህ ደግሞ አስበኝ፣ እንደ ምሕረትህም ብዛት ራራልኝ” በማለት ሊጸልይ ችሏል። በተጨማሪም ነህምያ በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈውን መጽሐፍ “አምላኬ ሆይ፣ በመልካም አስበኝ” በሚል የልመና ቃል መደምደሙ ተገቢ ነበር።—ነህምያ 13:22, 31
3. (ሀ) መልካም የሚሠራን ሰው እንዴት አድርገህ ትገልጸዋለህ? (ለ) የነህምያን ታሪክ መመርመራችን ራሳችንን ምን ብለን እንድንጠይቅ ሊገፋፋን ይችላል?
3 መልካም ነገር የሚያደርግ ሰው ጥሩ ሥነ ምግባር ያለው ከመሆኑም በላይ ሌሎችን የሚጠቅሙ ትክክለኛ ሥራዎችን ያከናውናል። ነህምያ እንዲህ ዓይነት ሰው ነበር። ለአምላክ አክብሮታዊ ፍርሃት የነበረውና ለእውነተኛ አምልኮ ከፍተኛ ቅንዓት የነበረው ሰው ነው። ከዚህም በተጨማሪ በአምላክ አገልግሎት ላገኛቸው መብቶች አመስጋኝ የነበረ ሲሆን ስለ ራሱ ለይሖዋ ጥሩ መልስ ሰጥቷል። የእሱን ታሪክ መመርመራችን ‘አምላክ የሰጠኝን መብቶችና ኃላፊነቶች የምመለከታቸው እንዴት ነው? እኔ ስለ ራሴ ለይሖዋ አምላክና ለኢየሱስ ክርስቶስ ምን ዓይነት መልስ እየሰጠሁ ነው?’ ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅ ሊያነሳሳን ይችላል።
እውቀት ተጠያቂ ያደርገናል
4. ኢየሱስ ለተከታዮቹ ምን ተልእኮ ሰጥቷቸዋል? “ለዘላለም ሕይወትም የተዘጋጁ ሁሉ” ምን አድርገዋል?
4 ኢየሱስ ለተከታዮቹ የሚከተለውን ተልእኮ ሰጥቷቸዋል፦ “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።” (ማቴዎስ 28:19, 20) ደቀ መዛሙርት ማድረግ የሚቻለው በማስተማር ነው። ስለዚህ የተማሩትና “ለዘላለም ሕይወትም የተዘጋጁ ሁሉ” ኢየሱስ እንዳደረገው ይጠመቁ ነበር። (ሥራ 13:48፤ ማርቆስ 1:9-11) ያዘዛቸውን ነገር ሁሉ ለመፈጸም የነበራቸው ፍላጎት ከልባቸው የመነጨ ነበር። የአምላክን ቃል ትክክለኛ እውቀት በመቅሰምና በሥራ በመተርጎም ራስን ወደ መወሰን ደረጃ ይደርሱ ነበር።—ዮሐንስ 17:3
5, 6. ያዕቆብ 4:17 እንዴት ልንረዳው ይገባል? ጥቅሱ በምን ዓይነት ሁኔታዎች እንደሚሠራ በምሳሌ አስረዳ።
5 ከቅዱሳን ጽሑፎች ያገኘነው እውቀት ይበልጥ ጥልቀት እያገኘ በሄደ መጠን የእምነታችንም መሠረት የዚያኑ ያህል ጥብቅ እየሆነ ይሄዳል። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ በአምላክ ፊት ያለን ተጠያቂነት ይጨምራል። ያዕቆብ 4:17 “በጎ ለማድረግ አውቆ ለማይሠራው ኃጢአት ነው” ይላል። ይህ ሐሳብ ቀደም ሲል ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ሙሉ በሙሉ በአምላክ ላይ መደገፍ ሲገባቸው በራሳቸው ስለሚመኩ ሰዎች ለተናገረው ነገር ማሰሪያ አድርጎ ያቀረበው ነው። አንድ ሰው ያለ ይሖዋ እርዳታ ዘላቂነት ያለው ምንም ነገር ማከናወን እንደማይችል እያወቀ ከዚያ ጋር የሚስማማ ነገር የማያደርግ ከሆነ ኃጢአት ነው። ሆኖም የያዕቆብ ቃላት አንድን ነገር ሳያደርጉ በመቅረት የሚፈጸሙ ኃጢአቶችንም ያመለክታል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ስለ በጎቹና ፍየሎቹ በተናገረው ምሳሌ ላይ ፍየሎቹ የተወቀሱት መጥፎ ድርጊት በመፈጸማቸው ሳይሆን የክርስቶስን ወንድሞች ባለመርዳታቸው ነው።—ማቴዎስ 25:41-46
6 የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስጠኑት አንድ ሰው ምንም እንኳ ሲጋራ መተው እንዳለበት ያውቅ የነበረ ቢሆንም ሲጋራውን ባለመተዉ ምክንያት ምንም መንፈሳዊ እድገት አላደረገም ነበር። አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ያዕቆብ 4:17ን እንዲያነብ ጠየቀው። ሽማግሌው ጥቅሱ ያዘለውን ትርጉም ካብራራለት በኋላ “ስለዚህ አንተ ምንም እንኳ ያልተጠመቅህ ብትሆንም ተጠያቂነት አለብህ፤ ለምትወስደውም ውሳኔ ሙሉውን ኃላፊነት የምትሸከመው ራስህ ነህ” አለው። የሚያስደስተው ነገር ሰውየው ጥሩ ምላሽ በማሳየት ሲጋራውን ተወ፤ ከዚያም ብዙ ሳይቆይ ራሱን ለይሖዋ አምላክ መወሰኑን በጥምቀት ለማሳየት ብቁ ሆነ።
በአገልግሎታችን ተጠያቂዎች ነን
7. ‘ለአምላክ እውቀት’ ያለንን አድናቆት የምንገልጽበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?
7 ልባዊ ፍላጎታችን ፈጣሪያችንን ማስደሰት መሆን አለበት። ‘ለአምላክ እውቀት’ ያለንን አድናቆት የምንገልጽበት አንዱ መንገድ ሰዎችን የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የተሰጠንን ተልእኮ በመፈጸም ነው። በተጨማሪም ይህ ለአምላክና ለሰዎች ያለንን ፍቅር የምናሳይበት መንገድ ነው። (ምሳሌ 2:1-5፤ ማቴዎስ 22:35-40) አዎን፣ ከአምላክ ያገኘነው እውቀት በእርሱ ዘንድ ተጠያቂዎች ያደርገናል፤ ሌሎች ሰዎችንም ወደፊት ደቀ መዛሙርት ሊሆኑ እንደሚችሉ አድርገን ልንመለከታቸው ይገባል።
8. ጳውሎስ አገልግሎቱን በተመለከተ በአምላክ ፊት ተጠያቂ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር ልንል የምንችለው ለምንድን ነው?
8 ሐዋርያው ጳውሎስ ምሥራቹን በሙሉ ልብ መቀበልና መታዘዝ መዳንን የሚያስገኝ መሆኑንና ምሥራቹን አለመቀበል ግን ጥፋት ሊያስከትል እንደሚችል ያውቅ ነበር። (2 ተሰሎንቄ 1:6-8) በመሆኑም አገልግሎቱን በተመለከተ በይሖዋ ፊት ተጠያቂ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። እንዲያውም ጳውሎስና የአገልግሎት አጋሮቹ ለአገልግሎታቸው ከፍ ያለ ግምት በመስጠታቸው ይህን ሥራ የሚያከናውኑት የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት ነው የሚል አመለካከት በሰዎች ልብ ውስጥ እንዳያድር በጣም ይጠነቀቁ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ “ወንጌልን ብሰብክ እንኳ የምመካበት የለኝም፤ ግድ ደርሶብኝ ነውና፤ ወንጌልንም ባልሰብክ ወዮልኝ” ብሎ እንዲናገር ልቡ ገፋፍቶታል።—1 ቆሮንቶስ 9:11-16
9. ሁሉም ክርስቲያኖች ሊከፍሉት የሚገባው ትልቅ ዕዳ ምንድን ነው?
9 ራሳችንን ለይሖዋ የወሰንን አገልጋዮች እንደ መሆናችን መጠን ‘ምሥራቹን የመስበክ ግዴታ አለብን።’ የመንግሥቱን መልእክት የመስበክ ተልእኮ ተሰጥቶናል። ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን ይህን ኃላፊነት ተቀብለናል። (ከሉቃስ 9:23, 24 ጋር አወዳድር።) በተጨማሪም ልንከፍለው የሚገባን ዕዳ አለብን። ጳውሎስ “ለግሪክ ሰዎችና ላልተማሩም፣ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉም ዕዳ አለብኝ፤ ስለዚህም በሚቻለኝ መጠን በሮሜ ላላችሁ ለእናንተ ደግሞ ወንጌልን ልሰብክ ተዘጋጅቼአለሁ” ብሏል። (ሮሜ 1:14, 15) ጳውሎስ ሰዎች ምሥራቹን ሰምተው እንዲድኑ የመስበክ ግዴታ እንዳለበት ያውቅ ስለነበር ባለ ዕዳ ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 1:12-16፤ 2:3, 4) ስለዚህ ጳውሎስ ተልእኮውን ለመፈጸም ተግቶ ሠርቷል፤ እንዲሁም በሰዎች ላይ የነበረበትን ዕዳ ከፍሏል። እኛም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ልንከፍለው የሚገባን እንዲህ ዓይነት ዕዳ አለብን። በተጨማሪም የመንግሥቱ ስብከት ለአምላክ፣ ለልጁና ለሰዎች ፍቅራችንን የምንገልጽበት ዋነኛ መንገድ ነው።—ሉቃስ 10:25-28
10. አንዳንዶች አገልግሎታቸውን ያሰፉት ምን በማድረግ ነው?
10 በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መልስ መስጠት የምንችልበት አንዱ መንገድ ባሉን ችሎታዎች ተጠቅመን አገልግሎታችንን በማስፋት ነው። በምሳሌ ለማስረዳት፦ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የብዙ አገር ሰዎች ብሪታንያ ውስጥ ገብተዋል። ለእነዚህ ሰዎች ምሥራቹን ለመስበክ ከ800 በላይ የሚሆኑ አቅኚዎችና (የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ ሰባኪዎች) በመቶዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ምሥክሮች የተለያዩ ቋንቋዎችን እየተማሩ ነው። ይህ ለአገልግሎቱ ሥራ ጥሩ ማነቃቂያ ሆኗል። የቻይና ቋንቋ በማስተማር ላይ ያለች አንዲት አቅኚ “በዚህ መንገድ እውነትን ለሌሎች ማካፈል እንዲችሉ የራሴን ቋንቋ ለሌሎች ምሥክሮች አስተምራለሁ ብዬ በፍጹም አስቤ አላውቅም። በጣም የሚያስደስት ነው!” ብላለች። አንተስ አገልግሎትህን በዚህ መንገድ ማስፋት ትችላለህን?
11. አንዲት ክርስቲያን መደበኛ ባልሆነ መንገድ ስትመሰክር ምን ውጤት ተገኘ?
11 ሁላችንም አንድን እየሰመጠ ያለ ሰው ለማዳን የምንችለውን ሁሉ እንደምናደርግ ግልጽ ነው። በተመሳሳይም የይሖዋ አገልጋዮች በማንኛውም አጋጣሚ ለመመስከር ባላቸው ችሎታ ሁሉ ለመጠቀም ዝግጁዎች ናቸው። በቅርቡ አንዲት ምሥክር በአውቶቡስ ስትጓዝ አጠገቧ ተቀምጣ የነበረችውን ሴት ስለ ቅዱሳን ጽሑፎች አነጋገረቻት። ሴትዮዋ በሰማችው ነገር በጣም በመደሰቷ ብዙ ጥያቄዎች አቀረበች። ምስክሯ የምትወርድበት ቦታ ሲደርስ ሴትዮዋ ገና ያልተመለሱላት ብዙ ጥያቄዎች ስላሉ ቤቷ ሄደው እንዲወያዩ ለመነቻት። ምሥክሯ ተስማማች። ውጤቱ ምን ነበር? የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረና ከስድስት ወራት በኋላ ሴትዮዋ ያልተጠመቀች የመንግሥቱ አስፋፊ ሆነች። ብዙም ሳይቆይ ሴትዮዋ ራሷ ስድስት የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መምራት ጀመረች። አንድ ሰው ያሉትን ችሎታዎች በመንግሥቱ አገልግሎት ላይ በመጠቀም የሚያገኘው እንዴት ያለ አስደሳች ዋጋ ነው!
12. በአገልጋይነት ሥራችን ያሉንን ችሎታዎች በመስክ አገልግሎት ውጤታማ በሆነ መንገድ ልንጠቀምባቸው የምንችለው እንዴት ነው?
12 ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን 192 ገጾች ያሉትን መጽሐፍ በመሳሰሉ ጽሑፎች በመጠቀም በአገልጋይነት ሥራችን ያሉንን ችሎታዎች በመስክ ላይ ውጤታማ በሆነ መንገድ ልንጠቀምባቸው እንችላለን። የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል የጽሑፍ አዘጋጅ ኮሚቴ እስከ ሚያዝያ 1996 ባለው ጊዜ ውስጥ እውቀት የተባለው መጽሐፍ ከ140 በሚበልጡ ቋንቋዎች እንዲተረጎም የፈቀደ ሲሆን እስከዚሁ ጊዜ ድረስ በ111 ቋንቋዎች 30,500,000 የመጽሐፉ ቅጂዎች ታትመዋል። ይህ መጽሐፍ የተጻፈው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ስለ አምላክ ቃልና ስለ ዓላማዎቹ በቂ ትምህርት አግኝተው ራሳቸውን ለይሖዋ እንዲወስኑና እንዲጠመቁ ለመርዳት ታስቦ ነው። የመንግሥቱ አስፋፊዎች ከአንድ ተማሪ ጋር ለብዙ ዓመታት የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስለማያደርጉ ሌሎች ተጨማሪ ሰዎችን ማስጠናት ወይም ደግሞ ከቤት ወደ ቤት በሚካሄደው ሥራና በሌሎች የአገልግሎቱ ዘርፎች መካፈል ይችላሉ። (ሥራ 5:42፤ 20:20, 21) በአምላክ ፊት ተጠያቂ መሆናቸውን በመገንዘብ መለኮታዊ ማስጠንቀቂያዎችን ያሰማሉ። (ሕዝቅኤል 33:7-9) ሆኖም ዋናው ዓላማቸው ይሖዋን ማስከበርና ይህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት በቀረው አጭር ጊዜ ውስጥ በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች ስለ ምሥራቹ እንዲማሩ መርዳት ነው።
በቤተሰብ ደረጃ ጥሩ መልስ ማቅረብ
13. ለአምላክ አክብሮት ያላቸው ቤተሰቦች ቋሚ የሆነ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሊኖራቸው የሚገባው ለምንድን ነው?
13 እውነተኛ ክርስትናን የተቀበለ እያንዳንዱ ግለሰብና ቤተሰብ በአምላክ ፊት ተጠያቂ ስለሆነ ‘ወደ ጉልምስና ማደግ’ እንዲሁም ‘በእምነት መጠንከር’ ይኖርበታል። (ዕብራውያን 6:1-3፤ 1 ጴጥሮስ 5:8, 9) ለምሳሌ ያህል እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ያጠኑና የተጠመቁ ሰዎች ዘወትር በስብሰባዎች ላይ በመገኘት እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስንና ሌሎች ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን በማንበብ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውቀታቸውን ማሳደግ አለባቸው። ለአምላክ አክብሮት ያላቸው ቤተሰቦች ቋሚ የሆነ የቤተሰብ ጥናት ሊኖራቸው ይገባል፤ ምክንያቱም ‘ነቅቶ ለመኖር፣ በእምነት ጸንቶ ለመቆም፣ ደፋሮች ለመሆንና ጠንክሮ ለመቆም’ የሚያስችለው ጠቃሚ መንገድ ይህ ነው። (1 ቆሮንቶስ 16:13) የአንድ ቤተሰብ ራስ ከሆንክ ቤተሰብህ በመንፈሳዊ በሚገባ እንዲመገብ በማድረግ ረገድ በአምላክ ፊት ይበልጥ ተጠያቂነት ያለብህ አንተ ነህ። የተመጣጠነ ሥጋዊ ምግብ ለጤንነት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ሁሉ አንተና ቤተሰብህ ‘በእምነት ጤናሞች’ ሆናችሁ መኖር እንድትችሉ ዘወትር የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ መመገብ ያስፈልጋችኋል።—ቲቶ 1:13
14. በሚገባ የተማረች አንዲት እስራኤላዊት ልጅ የሰጠችው ምሥክርነት ምን ውጤት አስገኘ?
14 በቤተሰብህ ውስጥ ልጆች ካሉ ለልጆች ጤናማ የሆነ መንፈሳዊ ትምህርት በመስጠትህ በአምላክ ፊት ጥሩ ስም ታተርፋለህ። እንዲህ ዓይነቱ ትምህርት የአምላክ ነቢይ በነበረው በኤልሳዕ ዘመን በሶርያውያን ተማርካ የነበረችውን አንዲት ትንሽ እስራኤላዊት ልጃገረድ እንደጠቀመ ሁሉ እነርሱንም ይጠቅማቸዋል። ይህች ልጃገረድ በሥጋ ደዌ የተለከፈ ንዕማን የሚባል የአንድ የሶርያ ሠራዊት አለቃ ሚስት አገልጋይ ሆነች። ልጅቷ ምንም እንኳ ትንሽ የነበረች ብትሆንም እመቤቷን “ጌታዬ በሰማርያ ካለው ከነቢዩ ፊት ቢደርስ ኖሮ ከለምጹ በፈወሰው ነበር” አለቻት። ይህች ልጅ በሰጠችው ምሥክርነት ንዕማን ወደ እስራኤል ሄዶ ኤልሳዕ ሰባት ጊዜ በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ እንዲታጠብ የሰጠውን መመሪያ በመጨረሻ ከተቀበለ በኋላ ከነበረበት የሥጋ ደዌ ሊነጻ ችሏል። በተጨማሪም ንዕማን የይሖዋ አምላኪ ለመሆን በቅቷል። ይህ ሁኔታ ያችን ትንሽ ልጅ ምንኛ አስደስቷት ይሆን!—2 ነገሥት 5:1-3, 13-19
15. ወላጆች ለልጆቻቸው ጥሩ መንፈሳዊ ማሰልጠኛ መስጠታቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።
15 በሰይጣን ሥልጣን ሥር በወደቀው በዚህ በሥነ ምግባር በተበላሸ ዓለም ውስጥ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ልጆች ማሳደግ ቀላል አይደለም። (1 ዮሐንስ 5:19) ይሁን እንጂ ጢሞቴዎስን አያቱ ሎይድና እናቱ ኤውንቄ ከሕፃንነቱ ጀምሮ በተሳካ ሁኔታ ቅዱሳን ጽሑፎችን አስተምረውታል። (2 ጢሞቴዎስ 1:5፤ 3:14, 15) ከልጆችህ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት፣ ልጆችህን ዘወትር ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መውሰድና ውሎ አድሮ ደግሞ አገልግሎት ይዘሃቸው መሄድ እነርሱን በማሰልጠን ረገድ ለአምላክ መልስ በምትሰጥባቸው ጉዳዮች ውስጥ የሚካተቱ ናቸው። በአሁኑ ጊዜ በ80ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አንዲት በዌልስ የሚኖሩ ክርስቲያን በ1920ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ አባታቸው ከአንድ ተራራ ቀጥሎ በሚገኘው ሸለቆ ውስጥ ባሉ መንደሮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትራክቶችን ለማሰራጨት በተራራው ላይ 10 ኪሎ ሜትር ሲጓዙ (ደርሶ መልስ 20 ኪሎ ሜትር) እሳቸውን ይዘዋቸው ይሄዱ እንደነበር ያስታውሳሉ። “አባቴ እውነትን በልቤ ውስጥ የተከለብኝ ወደዚያ ሥፍራ እናደርገው በነበረው ጉዞ ወቅት ነበር” ሲሉ ምስጋናን በሚገልጽ ስሜት ተናግረዋል።
ሽማግሌዎች መልስ የሚሰጡት እንዴት ነው?
16, 17. (ሀ) በጥንቷ እስራኤል በመንፈሳዊ የጎለመሱ ሽማግሌዎች ምን መብቶች አግኝተዋል? (ለ) በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር በዛሬው ጊዜ ካሉ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ብዙ የሚፈለገው ለምንድን ነው?
16 ጠቢቡ ሰሎሞን “የሸበተ ጠጉር በጽድቅ መንገድ ሲገኝ የውበት ዘውድ ነው” ሲል ተናግሯል። (ምሳሌ 16:31 አዓት) ሆኖም በአምላክ ሕዝብ ጉባኤ ውስጥ አንድን ሰው ለኃላፊነት ብቁ የሚያደርገው እንዲያው ዕድሜ ብቻ አይደለም። በጥንቷ እስራኤል ውስጥ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ሽማግሌዎች ፍትሕን ለማስፈጸም እንዲሁም ሰላም፣ ሥርዓትና መንፈሳዊ ጤንነት እንዲኖር ለማድረግ ፈራጆችና አለቆች ሆነው አገልግለዋል። (ዘዳግም 16:18-20) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥም ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ቢሆንም እንኳ የዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ እየቀረበ ሲሄድ ከሽማግሌዎች ይበልጥ የሚፈለግ ነገር ይኖራል። ለምን?
17 እስራኤላውያን አምላክ ከጥንቷ ግብጽ ነጻ ያወጣቸው ‘የተመረጡ ሕዝቦች’ ነበሩ። ሕጉን የተቀበሉት መካከለኛቸው በነበረው በሙሴ በኩል ስለነበር ዝርያዎቻቸው የተወለዱት ራሱን ለአምላክ በወሰነ ሕዝብ መካከል ሲሆን የይሖዋን መመሪያዎችም በሚገባ ያውቁ ነበር። (ዘዳግም 7:6, 11) ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ ራሱን ለአምላክ በወሰነ ሕዝብ መካከል በመወለድ ብቻ የዚህ ሕዝብ አካል መሆን አይቻልም፤ ለአምላክ አክብሮት ባላቸው ቤተሰቦች ውስጥ ቅዱስ ጽሑፋዊውን እውነት በሚገባ ተምረው የሚያድጉት ልጆች ቁጥር በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በጣም አነስተኛ ነው። በተለይ በቅርቡ ‘በእውነት መንገድ መጓዝ’ የጀመሩት ሰዎች ከቅዱስ ጽሑፋዊ ሥርዓቶች ጋር እንዴት ተስማምተው መኖር እንደሚችሉ ትምህርት ሊሰጣቸው ይገባል። (3 ዮሐንስ 4) ስለዚህ ታማኝ ሽማግሌዎች ‘የጤናማውን ቃል ምሳሌ በመያዝ’ የይሖዋን ሕዝብ በሚረዱበት ጊዜ ከባድ ኃላፊነት አለባቸው።—2 ጢሞቴዎስ 1:13, 14
18. የጉባኤ ሽማግሌዎች ምን ዓይነት እርዳታ ለመስጠት ዝግጁዎች መሆን አለባቸው? ለምንስ?
18 መራመድ እየተለማመደ ያለ ሕፃን ሊደናቀፍና ሊወድቅ ይችላል። ፍርሃት ስለሚሰማው የወላጅ እርዳታና ማበረታቻ ያስፈልገዋል። ራሱን ለይሖዋ የወሰነ አንድ ግለሰብም እንደዚሁ በመንፈሳዊ ሊደናቀፍ ወይም ሊወድቅ ይችላል። ሌላው ቀርቶ ሐዋርያው ጳውሎስ እንኳ በአምላክ ፊት ትክክል ወይም መልካም የሆነውን ነገር ለማድረግ ትግል ማድረግ አስፈልጎት ነበር። (ሮሜ 7:21-25) የአምላክ መንጋ እረኞች ስህተት ፈጽመው ከልባቸው ንስሐ የገቡ ክርስቲያኖችን ፍቅራዊ እርዳታ ሊያደርጉላቸው ይገባል። ሽማግሌዎች ከባድ ስህተት የፈጸመችን አንዲት ራስዋን የወሰነች ሴት ባነጋገሩበት ጊዜ ራሱን ለአምላክ የወሰነው ባልዋ ባለበት “እንደምታስወግዱኝ አውቃለሁ!” ብላቸው ነበር። ሆኖም ሽማግሌዎቹ ቤተሰቡን በመንፈሳዊ እንደገና በሁለት እግሩ ለማቆም ምን እርዳታ እንደሚያስፈልግ ማወቅ እንደሚፈልጉ በነገሯት ጊዜ እንባዋን መቆጣጠር አልቻለችም። ሽማግሌዎቹ ለአምላክ መልስ እንደሚሰጡ በመገንዘብ ንስሐ የገባን መሰል አማኝ ለመርዳት ዝግጁዎች ነበሩ።—ዕብራውያን 13:17
ጥሩ መልስ መስጠታችሁን ቀጥሉ
19. ስለ ራሳችን ለአምላክ ጥሩ መልስ መስጠታችንን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?
19 የጉባኤ ሽማግሌዎችም ሆኑ ሌሎች የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ ስለ ራሳቸው ለይሖዋ ጥሩ መልስ መስጠታቸውን መቀጠል አለባቸው። ይህን ማድረግ የሚቻለው የአምላክን ቃል የምንጠብቅና ፈቃዱን የምናደርግ ከሆነ ነው። (ምሳሌ 3:5, 6፤ ሮሜ 12:1, 2, 9) በተለይ በእምነት ለሚዛመዱን ሰዎች መልካም ነገር ማድረግ ይኖርብናል። (ገላትያ 6:10) ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን መከሩ ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂቶች ናቸው። (ማቴዎስ 9:37, 38) እንግዲያው የመንግሥቱን መልእክት በትጋት በማወጅ ለሌሎች መልካም እናድርግ። ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን የገባነውን ቃል ከፈጸምን፣ ፈቃዱን ካደረግንና ምሥራቹን በታማኝነት ካወጅን ይሖዋ ላቀረብነው መልስ ጥሩ ምላሽ ይሰጠናል።
20. የነህምያን ታሪክ በመመርመር ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
20 እንግዲያው ዘወትር የጌታ ሥራ የበዛልን እንሁን። (1 ቆሮንቶስ 15:58) የኢየሩሳሌምን ግንብ መልሶ የገነባውን፣ የአምላክን ሕግ ያስፈጸመውንና እውነተኛ አምልኮን በቅንዓት ያስፋፋውን ነህምያን ማሰብ አለብን። ይሖዋ አምላክ በሠራው መልካም ሥራ እንዲያስበው ጸልዮአል። ለይሖዋ ያደራችሁ ሆናችሁ ለመገኘት ያብቃችሁ፤ ይሖዋም ለምታቀርቡት መልስ ሞገሱን ይስጣችሁ።
መልሶችህ ምንድን ናቸው?
◻ ነህምያ ምን ምሳሌ ትቷል?
◻ እውቀት በአምላክ ፊት ተጠያቂዎች እንድንሆን የሚያደርገን ለምንድን ነው?
◻ በአገልግሎታችን ለይሖዋ ተቀባይነት ያለው መልስ መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?
◻ ቤተሰቦች ለአምላክ ጥሩ መልስ ለመስጠት ምን ማድረግ ይችላሉ?
◻ ክርስቲያን ሽማግሌዎች መልስ የሚሰጡት እንዴት ነው?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ልክ እንደ ጳውሎስ እኛም የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሆነን በምናከናውነው ሥራ ለአምላክ ጥሩ መልስ ማቅረብ እንችላለን
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ልጆቻችሁ በንዕማን ቤት ውስጥ ትኖር እንደነበረችው ትንሽ እስራኤላዊት ልጅ በእምነት ጠንካሮች ናቸውን?