ሌሎች አምላክ የሚፈልግባቸውን እንዲያውቁ መርዳት
“ግድ ደርሶብኝ ነውና፤ ወንጌልንም ባልሰብክ ወዮልኝ።”— 1 ቆሮንቶስ 9:16
1, 2. (ሀ) ይሖዋ እንድንካፈልበት የሚፈልገው ሁለት ገጽታ ያለው ሥራ የትኛው ነው? (ለ) ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የአምላክ መንግሥት ዜጎች መሆን እንዲችሉ ምን ነገር መማር ይኖርባቸዋል?
ይሖዋ የሰው ልጆች እንዲሰሙት የሚፈልገው ምሥራች አለው። እርሱ መንግሥት ያለው ሲሆን በየትም ቦታ የሚኖሩ ሰዎች ስለዚህ መንግሥት እንዲሰሙ ይፈልጋል። ይህን ምሥራች ካወቅን በኋላ ለሌሎች ሰዎች እንድናካፍለው ይጠብቅብናል። ይህ ሁለት ገጽታ ያለው ሥራ ነው። አንደኛ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብን። ኢየሱስ ‘ስለ ነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ’ በተናገረው ትንቢቱ ላይ እንዲህ ብሏል:- “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።”— ማቴዎስ 24:3, 14
2 የዚህ ሥራ ሁለተኛው ገጽታ ለመንግሥቱ መልእክት አዎንታዊ ምላሽ ያሳዩትን ሰዎች ማስተማርን ይጨምራል። ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ ብዙ ሆነው ተሰብስበው ለነበሩት ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴዎስ 28:19, 20) ‘ክርስቶስ እንዲጠብቁ ያዘዛቸው’ ነገር ከራሱ ያመነጨው አልነበረም። ሌሎች ሰዎች የአምላክን ትእዛዛት ወይም ብቃቶች እንዲያከብሩ አስተምሯል። (ዮሐንስ 14:23, 24፤ 15:10) በመሆኑም ‘ክርስቶስ ያዘዛቸውን ነገሮች እንዲጠብቁ’ ሌሎች ሰዎችን ማስተማር አምላክ የሚፈልግባቸው ምን እንደሆነ ማስተማርን የሚጨምር ነው። ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የአምላክ መንግሥት ዜጎች መሆን እንዲችሉ እርሱ የሚፈልግባቸውን ማሟላት ይኖርባቸዋል።
3. የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? የመንግሥቱን መልእክት የምሥራች ያሰኘው መንግሥቱ ወደፊት ምን ነገር ስለሚያከናውን ነው?
3 የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? መልእክቱ የምሥራች የሆነው ይህ መንግሥት ምን ነገር ስለሚያከናውን ነው? የአምላክ መንግሥት ሰማያዊ መስተዳድር ነው። ይሖዋ ስሙን የሚቀድሰውም ሆነ ከደረሰበት ነቀፋ ሁሉ የሚያጠራው በዚህ መንግሥት አማካኝነት ስለሆነ ይህ መንግሥት በእርሱ ዘንድ በጣም የተወደደ ነው። ይሖዋ ፈቃዱ በሰማይ እንደሆነ በምድር ላይ ደግሞ እንዲሆን የሚጠቀምበት መሣሪያ ይህ መንግሥት ነው። ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ እንድንጸልይና በሕይወታችንም ውስጥ ለዚህ መንግሥት ቅድሚያ እንድንሰጥ ያስተማረን በዚህ ምክንያት ነው። (ማቴዎስ 6:9, 10, 33) እንግዲያው ለሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት ማስተማራችን ለይሖዋ እጅግ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ይታያችኋልን?
ትግል ይጠይቃል ግን ከባድ ሸክም አይደለም
4. ምሥራቹን የመስበክ ግዴታችን ከባድ ሸክም እንዳልሆነ እንዴት በምሳሌ ማስረዳት ይቻላል?
4 ታዲያ ይህን ምሥራች መስበክ ከባድ ሸክም ነው? በፍጹም አይደለም! ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት:- አንድ አባት ለቤተሰቡ የሚያስፈልጉትን ቁሳዊ ነገሮች የማቅረብ ግዴታ አለበት። ይህን ሳያደርግ ቢቀር ክርስቲያናዊ እምነቱን እንደካደ ይቆጠራል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል:- “ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፣ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው።” (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ታዲያ ለአንድ ክርስቲያን ወንድ ይህን ግዴታ መፈጸም ከባድ ሸክም ይሆንበታል? ቤተሰቡን የሚወድና የሚያስፈልጋቸውን ለማቅረብ የሚፈልግ ከሆነ ሸክም አይሆንበትም።
5. የመስበኩና ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ግዴታ ቢሆንም በዚህ ሥራ በመካፈላችን ደስ ሊለን የሚገባው ለምንድን ነው?
5 በተመሳሳይም የስብከቱና ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ግዴታችን ማለትም ልናሟላው የሚገባን አንዱ ብቃት ነው። ሕይወታችንም በዚሁ ላይ የተመካ ነው። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “ወንጌልን ብሰብክ እንኳ የምመካበት የለኝም፤ ግድ ደርሶብኝ ነውና፤ ወንጌልንም ባልሰብክ ወዮልኝ።” (1 ቆሮንቶስ 9:16፤ ከሕዝቅኤል 33:7-9 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ የምንሰብከው በፍቅር ተነሳስተን እንጂ ግዴታችን ስለሆነ ብቻ አይደለም። በአንደኛ ደረጃ አምላክን እንወደዋለን። በተጨማሪም ጎረቤቶቻችንን እንወዳለን፤ ምሥራቹን መስማት ምን ያህል እንደሚያስፈልጋቸውም እናውቃለን። (ማቴዎስ 22:37-39) ስለ ወደፊቱ ሕይወታቸው ተስፋ እንዲኖራቸው አድርጓል። የአምላክ መንግሥት በቅርቡ ፍትሕ እንደሚያሰፍን፣ ጭቆናን በሙሉ እንደሚያጠፋ፣ ሰላምና አንድነት እንደሚያስገኝና በጠቅላላው የጽድቅ አገዛዙን ለሚቀበሉ ሁሉ የዘላለም በረከት እንደሚያመጣ ተገንዝበዋል። እንዲህ ያለውን ምሥራች ለሌሎች በማካፈል ሥራ መሳተፋችን አያስደስተንም?— መዝሙር 110:3 አዓት
6. የስብከቱና ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ትግል የሚጠይቅ የሆነው ለምንድን ነው?
6 ሆኖም ይህን የስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ ለመፈጸም አንድ ትግል የሚጠይቅ ሁኔታ መወጣት አስፈላጊ ሆኗል። የሰዎች ሁኔታ የተለያየ ነው። ሁሉም ሰዎች አንድ ዓይነት ፍላጎት ወይም ችሎታ የላቸውም። አንዳንዶቹ ከፍተኛ ትምህርት የቀሰሙ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ የትምህርት ደረጃቸው በጣም ዝቅተኛ ነው። በአንድ ወቅት ተወዳጅ የጊዜ ማሳለፊያ የነበረው ንባብ ዛሬ አሰልቺ ሥራ እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። በእንግሊዝኛ አሊትሬሲ የሚል መጠሪያ የተሰጠው “ማንበብ እየቻሉ የማንበብ ፍላጎት የማጣት ችግር” ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኅብረተሰቡ ክፍል ተምሯል በሚባልባቸው አገሮች ሳይቀር እየጨመረ የመጣ ችግር ሆኗል። ታዲያ እንዲህ ዓይነት የተለያየ አስተዳደግና ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች አምላክ የሚፈልግባቸውን እንዲማሩ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው?— ከ1 ቆሮንቶስ 9:20-23 ጋር አወዳድር።
ሌሎችን ለመርዳት የሚያስችል ትጥቅ አግኝተናል
7. “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሌሎች ሰዎች አምላክ የሚፈልግባቸውን እንዲያውቁ ለመርዳት እንድንችል ያስታጠቀን እንዴት ነው?
7 አንድ ሥራ እንዲያው ትግል የሚጠይቅ ቢሆን እንኳ ለሥራው የሚያስፈልጉ ተስማሚ መሣሪያዎች ከተሟሉ ሥራውን በቀላሉ ማከናወን ይቻላል። የተጠቃሚው ፍላጎት ስለሚለዋወጥ ዛሬ ለአንድ ሥራ ተስማሚ የነበረው መሣሪያ በሚቀጥለው ጊዜ መስተካከል ወይም መለወጥ ያስፈልገዋል። ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን መልእክት እንድናውጅ የተሰጠን ተልእኮም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። ባለፉት በርካታ ዓመታት “ታማኝና ልባም ባሪያ” በወቅቱ የሚያስፈልጉንን መሣሪያዎች ማለትም የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት ታስበው የተዘጋጁ ጽሑፎችን ሲያቀርብልን ቆይቷል። (ማቴዎስ 24:45) በመሆኑም ‘ከሕዝብ፣ ከነገድና ከቋንቋ’ የተውጣጡ ሰዎች አምላክ የሚፈልግባቸውን እንዲማሩ ለመርዳት የሚያስችል ትጥቅ አግኝተናል። (ራእይ 7:9) በየጊዜው የሚለዋወጠውን የመስኩን ፍላጎት ለማሟላት ከጊዜ ወደ ጊዜ አዳዲስ መሣሪያዎች ሲዘጋጁ ቆይተዋል። ጥቂት ምሳሌዎች እንመልከት።
8. (ሀ) “እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን” የተባለው መጽሐፍ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት በማስፋፋት በኩል ምን ድርሻ አበርክቷል? (ለ) በ1968 መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት የሚረዳ ምን ጽሑፍ ተዘጋጅቶ ነበር? ለየት ባለ መንገድ የተዘጋጀውስ እንዴት ነበር? (ሐ) እውነት የተባለው መጽሐፍ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ እገዛ ያበረከተው እንዴት ነው?
8 ከ1946 እስከ 1968 ባሉት ዓመታት “እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን” የተባለው መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር ትልቅ መሣሪያ ሆኖ ያገለገለ ሲሆን በ54 ቋንቋዎች 19,246,710 ቅጂዎች ታትመው ነበር። በ1968 የወጣው ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የተባለው መጽሐፍ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት የሚረዳ ውጤታማ መሣሪያ ሆኖ ለብዙ ዓመታት አገልግሏል። ከዚያ በፊት አንዳንዶች ሳይጠመቁ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ከዓመት ዓመት መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናታቸው የተለመደ ነገር ነበር። ይሁን እንጂ ይህ መጽሐፍ ተማሪው በነገሩ እንዲያስብበት በማድረግ የሚማራቸውን ነገሮች እንዲሠራባቸው ለማበረታታት ታስቦ የተዘጋጀ ነበር። ውጤቱስ ምን ነበር? የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች የተባለው (የእንግሊዝኛ) መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ከመስከረም 1, 1968 እስከ ነሐሴ 31, 1971 ድረስ ባሉት ሦስት የአገልግሎት ዓመታት ውስጥ በድምሩ 434,906 ሰዎች የተጠመቁ ሲሆን ይህ ቁጥር ከዚያ በፊት በነበሩት ሦስት የአገልግሎት ዓመታት ከተጠመቁት ከእጥፍ በላይ ነበር!” እውነት የተባለው መጽሐፍ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ በ117 ቋንቋዎች ከ107,000,000 በሚበልጡ ቅጂዎች በከፍተኛ መጠን ተሠራጭቷል።
9. ለዘላለም መኖር የተባለው መጽሐፍ ያለው ለየት ያለ ገጽታ ምንድን ነው? በመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎቸ ቁጥር ረገድ ምን ለውጥ አምጥቷል?
9 በ1982 በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለው መጽሐፍ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚመራበት ዋነኛ መጽሐፍ ሆነ። ይህ መጽሐፍ ከ150 የሚበልጡ ሥዕላዊ መግለጫዎች ያሉት ሲሆን ከእያንዳንዱ ሥዕል አጠገብ ሊተላለፍ የተፈለገውን ነጥብ የሚገልጽ አጠር ያለ መግለጫ ይገኛል። የጥቅምት 1982 የመንግሥት አገልግሎታችን እንደሚከተለው ብሎ ነበር:- “20 ለሚያክሉ ዓመታት (ከ1946 እስከ 1960ዎቹ አጋማሽ ድረስ) ዋነኛ የማስጠኛ መጽሐፋችን ሆኖ ያገለገለውን ‘እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን’ የተባለውን መጽሐፍ በተጠቀምንባቸው ዓመታት ውስጥ ከ1,000,000 የሚበልጡ አዳዲስ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ተጨምረዋል። ከዚያም በ1968 የወጣው ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የተባለው መጽሐፍ ዋነኛ የማስጠኛ መጽሐፍ ሆኖ ባገለገለገበት ጊዜ ውስጥ 1,000,000 የሚያክሉ ተጨማሪ አስፋፊዎች ተገኝተዋል። በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን አዲሱን የማስጠኛ መጽሐፋችንን ስንጠቀም በመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር በኩል ተመሳሳይ ጭማሪ እናገኝ ይሆን? ይሖዋ ፈቃዱ ከሆነ እንደምናገኝ ምንም ጥርጥር የለውም!” በእርግጥም የይሖዋ ፈቃድ ነበር፤ ምክንያቱም ከ1982 እስከ 1995 ድረስ ከ2,700,000 በላይ የሚሆኑ ተጨማሪ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ተገኝተዋል!
10. በ1995 የተዘጋጀው አዲስ ጽሑፍ ምንድን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችስ ፈጠን ያለ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ሊረዳቸው ይገባል የምንለው ለምንድን ነው?
10 ኢየሱስ “መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው” ብሏል። (ማቴዎስ 9:37) በእርግጥም መከሩ ብዙ ነው። መሠራት ያለበት ገና ብዙ ሥራ አለ። በአንዳንድ አገሮች ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀመርላቸው ተመዝግበው ተራ እስኪደርሳቸው ለመጠበቅ ተገደዋል። በመሆኑም አምላክ የሚሰጠውን እውቀት በበለጠ ፍጥነት ለማሠራጨት ሲባል “ታማኝና ልባም ባሪያ” በ1995 ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለ ባለ 192 ገጽ አዲስ ጽሑፍ አውጥቷል። ይህ ግሩም መጽሐፍ የሐሰት መሠረተ ትምህርቶችን በማፍረስ ላይ አያተኩርም። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አዎንታዊ በሆነ መንገድ ያቀርባል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ፈጠን ያለ መንፈሳዊ እድገት እንዲያሳዩ ይረዳቸዋል ተብሎ ይታመናል። እውቀት የተባለው መጽሐፍ በ125 ቋንቋዎች 45,500,000 በሚያክሉ ቅጂዎች ተሠራጭቶ በመስኩ ውስጥ ሥራውን የጀመረ ሲሆን ወደ ተጨማሪ 21 ቋንቋዎች በመተርጎም ላይ ነው።
11. ያልተማሩትን ወይም ዝቅተኛ የማንበብ ችሎታ ያላቸውን ሰዎች ለመርዳት ምን ውጤታማ ጽሑፍ ተዘጋጅቶ ነበር? በዓለም አቀፉ የትምህርት መርሐ ግብር ውስጥ ምን ትልቅ ሚና ተጫውቷል?
11 ‘ታማኙ ባሪያ’ የተወሰኑ ሰዎችን ለመርዳት ታስበው የተዘጋጁ ጽሑፎችን በየጊዜው ሲያወጣ ቆይቷል። ለምሳሌ ያህል ካደጉበት ባሕል ወይም ሃይማኖት አንጻር ለየት ያለ እርዳታ ስለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ምን ማለት ይቻላል? አምላክ ምን እንደሚፈልግባቸው እንዲያውቁ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው? በ1982 በወቅቱ በጣም አስፈላጊ የነበረውን በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለ ባለ 32 ገጽ ብሮሹር አግኝተናል። በበርካታ ሥዕሎች የተዋበው ይህ ብሮሹር ያልተማሩትን ወይም ዝቅተኛ የማንበብ ችሎታ ያላቸውን ሰዎች በመርዳት ረገድ ውጤታማ ሆኖ ተገኝቷል። መሠረታዊ የሆኑትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርቶች በጣም ቀላልና ለመረዳት አመቺ በሆነ መንገድ ያቀርባል። በደስታ ኑር! የተባለው ብሮሹር ከወጣበት ጊዜ አንስቶ በምድር አቀፉ የማስተማር መርሐ ግብር ውስጥ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። በ239 ቋንቋዎች ከ105,100,000 በሚበልጡ ቅጂዎች በመታተሙ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር እስከ ዛሬ ድርስ ካወጣቸው ጽሑፎች ሁሉ በብዙ ቋንቋዎች በመተርጎም ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው ጽሑፍ ሆኗል!
12, 13. (ሀ) ‘ታማኙ ባሪያ’ ከ1990 ጀምሮ የብዙኀኑን ልብ ለመንካት የሚያስችል ምን አዲስ መንገድ አዘጋጅቷል? (ለ) የማኅበሩን የቪዲዮ ካሴቶች በመስክ አገልግሎታችን ልንጠቀምባቸው የምንችለው እንዴት ነው? (ሐ) በቅርቡ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የሚረዳ ምን አዲስ ጽሑፍ አግኝተናል?
12 ‘ታማኙ ባሪያ’ ከ1990 ወዲህ ከጽሑፎች በተጨማሪ ለብዙኀኑ ለማዳረስ የሚያስችል አዲስ ማስተማሪያ ዘዴ አዘጋጅቶልናል። ይህም የቪዲዮ ካሴት ነው። በማኅበሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1990 ጥቅምት ወር “የይሖዋ ምሥክሮች — ከስሙ በስተጀርባ ያለው ድርጅት” የተባለ 55 ደቂቃ የሚፈጅ የቪዲዮ ካሴት ወጣ። 35 በሚደርሱ ቋንቋዎች የሚገኘው ይህ ውብና ትምህርት ሰጪ አቀራረብ ያለው የቪዲዮ ካሴት የይሖዋ ሕዝቦች ዓለም አቀፍ ድርጅት ኢየሱስ የሰጠውን ምሥራቹን በምድር ዙሪያ የማወጅ ትእዛዝ ሲፈጽም የሚያሳይ ነው። ይህ የቪዲዮ ካሴት የተዘጋጀው በተለይ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ለመደገፍ ሲባል ነው። የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይህንን መሣሪያ በመስክ አገልግሎታቸው ለመጠቀም ጊዜ አላጠፉም። አንዳንዶቹ ከቦርሳቸው ስለማይለዩት ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ሁሉ ለማሳየት ወይም ለማዋስ ችለዋል። ይህ የቪዲዮ ካሴት ከወጣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የቪዲዮ ካሴቶች በ21ኛው መቶ ዘመን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን አእምሮና ልብ ለመንካት የሚያስችሉ ዘዴዎች ሆነው ብቅ ብለዋል። በመሆኑም ማኅበሩ ዓለም አቀፉን የመንግሥቱን ሥራ ለማስፋፋት በተከታታይ ሌሎች የቪዲዮ ካሴቶች ያወጣል ብለን እናምናለን።” በእርግጥም ሦስት ተከታታይ ካሴቶች ያሉት ሐቀኛ ታሪኮችና ትንቢቶች የያዘው መጽሐፍ ቅዱስ የተባለውና የይሖዋ ምሥክሮች የናዚን ጥቃት በጽናት ተወጡት የሚለውን ጨምሮ ሌሎች ካሴቶች ወጥተዋል። የማኅበሩ የቪዲዮ ካሴቶች በቋንቋችሁ የሚገኙ ከሆነ በመስክ አገልግሎታችሁ ተጠቅማችሁባቸው ታውቃላችሁን?a
13 በቅርቡ ደግሞ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የሚያግዘን አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለ አዲስ ብሮሹር አግኝተናል። ይህ ብሮሹር የተዘጋጀበት ዓላማ ምንድን ነው? እንዴትስ ልንጠቀምበት እንችላለን?
አዲሱን መሣሪያ መመርመር
14, 15. አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለው ብሮሹር እነማንን ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው? በውስጡስ ምን ይዟል?
14 አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለው አዲስ ጽሑፍ በአምላክ የሚያምኑና ለመጽሐፍ ቅዱስም አክብሮት ያላቸውን ሰዎች ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና በታዳጊ አገሮች ውስጥ የሚያገለግሉ የብዙ ዓመት ተሞክሮ ያላቸው የጊልያድ ሚስዮናውያን በብሮሹሩ ዝግጅት ተካፍለዋል። መሠረታዊ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች የሚያቅፍና ሰፋ ያለ ይዘት ያለው የማስጠኛ ጽሑፍ ነው። የሚጠቀምባቸው ቃላት ፍቅራዊ ስሜት የተንጸባረቀባቸው፣ ቀላልና ቀጥተኛ ናቸው። ይሁን እንጂ ከመጠን በላይ ቀላል የሆነ ጽሑፍ አይደለም። “ወተት” ብቻ ሳይሆን አብዛኞቹ ሰዎች ሊረዱት በሚችሉት መልክ የቀረበና ከአምላክ ቃል የተገኘ ‘ጠንካራ ምግብ’ ይዟል።— ዕብራውያን 5:12-14
15 በቅርብ ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የመንግሥቱ አስፋፊዎች እንዲህ ዓይነት ጽሑፍ እንዲዘጋጅላቸው ጠይቀው ነበር። ለምሳሌ ያህል በፓፑዋ ኒው ጊኒ የሚገኘው የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሰዎች እርስ በርሳቸው በሚጋጩ ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ግራ ተጋብተዋል። ከራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ አውጥተው በሚመለከቷቸው ጥቂት ጥቅሶች የተደገፈና እጥር ምጥን ብሎ የቀረበ የእውነት ማብራሪያ ያስፈልጋቸዋል። አምላክ ከእውነተኛ ክርስቲያኖች ምን እንደሚፈልግ እንዲሁም የትኞቹ ልማዶችና ድርጊቶች በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌላቸው ግልጽና ቀጥተኛ በሆነ መንገድ የሚገልጽ ጽሑፍ ያስፈልጋቸዋል።” አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የሚለው ብሮሹር እንደነዚህ ያሉ ሰዎች አምላክ ምን እንደሚፈልግባቸው እንዲማሩ ለመርዳት የሚያስችል ተስማሚ ጽሑፍ ነው።
16. (ሀ) በአዲሱ ብሮሹር ውስጥ ከሚገኘው ቀለል ያለ ማብራሪያ በተለይ እነማን ሊጠቀሙ ይችላሉ? (ለ) በእናንተ የአገልግሎት ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎች አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? ከተባለው ብሮሹር ሊጠቀሙ የሚችሉት እንዴት ነው?
16 ይህንን አዲስ መሣሪያ እንዴት ልትጠቀሙበት ትችላላችሁ? በአንደኛ ደረጃ ማንበብ የማይችሉ ወይም የማንበብ ልማዱ የሌላቸው ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት ልንጠቀምበት እንችላለን።b እንደነዚህ ያሉት ሰዎች ቀለል ካለው የብሮሹሩ ማብራሪያ ሊጠቀሙ ይችላሉ። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮዎች የጽሑፉን ቅድመ ዝግጅት ከተመለከቱ በኋላ እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈዋል:- “ብሮሹሩ ብዙ የማንበብ ልማድ የሌላቸው ሰዎች በሚገኙባቸው በአብዛኞቹ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ትልቅ ሚና ይጫወታል።” (ብራዚል) “የትውልድ አገር ቋንቋቸውን ማንበብ የማይችሉና ፈረንሳይኛም ቢሆን ለማንበብ የሚቸገሩ በርካታ ስደተኞች አሉ። ይህ ብሮሹር እነዚህን ሰዎች ለማስጠናት ሊያገለግል ይችላል።” (ፈረንሳይ) በእናንተ የአገልግሎት ክልልስ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? ከሚለው ብሮሹር ሊጠቀሙ የሚችሉ ሰዎች ይኖራሉ?
17. ይህ ብሮሹር በብዙ አገሮች ውስጥ ጠቃሚ ሊሆን የሚችልባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው? ለምንስ?
17 በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በብዙ አገሮች የሚገኙ የትምህርት ደረጃቸው ምንም ይሁን ምን አምላካዊ ፍርሃት ያላቸውን ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር በጣም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። እርግጥ ነው፣ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት በተባለውም መጽሐፍ ጥናት ለማስጀመር ጥረት ሊደረግ ይገባል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ በብሮሹር ጥናት ማስጀመሩ ይበልጥ ቀላል ሊሆን ይችላል። ከዚያ በኋላ ጥናቱን በተገቢው ጊዜ ላይ ዋነኛ የማስጠኛ መጽሐፍ አድርገን ወደምንመርጠው ወደ እውቀት መጽሐፍ ሊዛወር ይገባል። አምለክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለው ብሮሹር በዚህ በኩል የሚያበረክተውን ድርሻ በተመለከተ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮዎች እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል:- “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር አስቸጋሪ ነው፤ ሆኖም አስፋፊዎች በብሮሹር ሲጠቀሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የማስጀመር ሰፊ አጋጣሚ ያለ ይመስላል።” (ጀርመን) “እንዲህ ዓይነቱ ብሮሹር አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በማስጀመር በኩል በጣም ውጤታማ ይሆናል። ከዚያ በኋላ ጥናቱን ወደ እውቀት መጽሐፍ ማዛወር ይቻላል።” (ኢጣሊያ) “ጃፓናውያን የትምህርት ደረጃቸው ከፍተኛ ቢሆንም አብዛኞቹ ስለ መጽሐፍ ቅዱስና በውስጡ ስላሉት መሠረታዊ ትምህርቶች ያላቸው እውቀት በጣም ውስን ነው። ይህ ብሮሹር እውቀት ወደተባለው መጽሐፍ ጥሩ የመሸጋገሪያ ድልድይ ይሆንላቸዋል።”— ጃፓን
18. አምላክ የሚፈልግብንን ነገሮች በማሟላት ረገድ ልንዘነጋው የማይገባ ነገር ምንድን ነው?
18 በዓለም ዙሪያ የሚገኙት የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ይህን ብሮሹር ለመተርጎም የጠየቁ ሲሆን በ221 ቋንቋዎች እንዲተረጎም ፈቃድ ተሰጥቷል። ይህ አዲስ ጽሑፍ ሰዎች ይሖዋ አምላክ የሚፈልግባቸውን እንዲያውቁ ለመርዳት በምናደርገው ጥረት ጠቃሚ መሣሪያ ሆኖ እንዲገኝ እንመኛለን። እኛም በበኩላችን መስበክንና ደቀ መዛሙርት ማድረግን የሚጠይቀውን ትእዛዝ ጨምሮ አምላክ ከእኛ የሚፈልጋቸውን ብቃቶች ማሟላት ይሖዋን ምን ያህል እንደምንወደው የምናሳይበት ውድ አጋጣሚ እንደሚከፍትልን እናስታውስ። አዎን፣ አምላክ እንድናሟላው የሚፈልገው ነገር ከባድ ሸክም አይደለም። ከሁሉ የተሻለ የአኗኗር መንገድ ነው!— መዝሙር 19:7-11
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች የተባለው (የእንግሊዝኛ) መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “የቪዲዮ ካሴቶች በጽሑፎች አማካኝነት ወይም በግል የሚሰጠውን ምሥክርነት በምንም ዓይነት አይተኩም። ማኅበሩ የሚያወጣቸው ጽሑፎች ምሥራቹን በማዳረስ በኩል ሕይወት አድን ሚና መጫወታቸውን ይቀጥላሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት የሚያደርጉት አገልግሎት ጠንካራ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት ያለው የአገልግሎታቸው ክፍል ሆኖ ይቀጥላል። ይሁን እንጂ የቪዲዮ ካሴቶች ይሖዋ በገባልን ግሩም ተስፋዎች ላይ ያለንን እምነት የሚያጎለብቱና ዛሬ በምድር ላይ እየሠራው ላለው ነገር አድናቆት እንዲያድርብን በማድረግ ተጨማሪ መሣሪያ ሆነው ያገለግላሉ።”
b አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? በተባለው ብሮሹር እንዴት ጥናት መምራት እንደምትችል ማብራሪያ ለማግኘት በገጽ 16-17 ላይ የሚገኘውን “ሰዎች አምላክ የሚፈልግባቸውን እንዲማሩ ለመርዳት የተዘጋጀ አዲስ መሣሪያ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ ይሖዋ አገልጋዮቹ ሁለት ገጽታ ባለው በየትኛው ሥራ እንዲካፈሉ ይፈልጋል?
◻ የመስበክና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ግዴታችን ከባድ ሸክም ያልሆነው ለምንድን ነው?
◻ “ታማኝና ልባም ባሪያ” በስብከትና ደቀ መዛሙርት በማድረግ ሥራችን የምንጠቀምባቸው ምን መሣሪያዎች አዘጋጅቶልናል?
◻ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለው ብሮሹር የተዘጋጀው ማንን ለመርዳት ታስቦ ነው? በአገልግሎታችን እንዴት ልንጠቀምበት እንችላለን?
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የስብከቱና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራችን ከባድ ሸክም አይደለም
[በገጽ 26 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
“እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን” (1946 እንደገና በ1952 ታተመ):- 19,250,000 በ54 ቋንቋዎች
“ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት” (1968):- 107,000,000 በ117 ቋንቋዎች (የፈረንሳይኛው ቅጂ)
“በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ” (1982):- 80,900,000 በ130 ቋንቋዎች (የሩስያኛው ቅጂ)
“ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት” (1995):- 45,500,000 በ125 ቋንቋዎች (የጀርመንኛው ቅጂ)