ከአምላክ የተላከ ምሥራች!
የተባለውን ብሮሹር መጠቀም የሚቻልበት መንገድ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የሚረዳ አዲስ ብሮሹር
1. “ልብህን ጠብቅ!” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ፣ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የሚረዳ የትኛውን አዲስ ብሮሹር አግኝተናል?
1 “ልብህን ጠብቅ!” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ፣ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የሚረዳ አዲስ ብሮሹር በማግኘታችን በጣም ተደስተን ነበር። ከአምላክ የተላከ ምሥራች! የተባለው ብሮሹር አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹር የሚተካ ሲሆን ትምህርቶቹ አጠር ባለ መልኩ የቀረቡ መሆናቸው ሁለቱን ብሮሹሮች ያመሳስላቸዋል። ይህ ደግሞ ብሮሹሩን በር ላይ እንዳለን ጥናት ለማስጀመር እንድንጠቀምበት ይረዳናል። አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለው ብሮሹር ከክርስቲያኖች የሚጠበቁትን ብቃቶች የሚያብራራ ሲሆን አንድ አዲስ ተማሪ እነዚህን ብቃቶች ተግባራዊ ማድረግ ሊከብደው ይችላል፤ አዲሱ ብሮሹር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው ምሥራች ላይ የሚያተኩር ነው።—ሥራ 15:35
2. ምሥራች የተባለው ብሮሹር የተዘጋጀው ለምንድን ነው?
2 ይህ ብሮሹር የተዘጋጀው ለምንድን ነው? በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የተለያዩ ወንድሞች፣ ሰዎችን ወደ እውነት የሚስባቸውና መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት በምንጠቀምበት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ ጥናት እንዲጀምሩ የሚያነሳሳቸው ቀለል ያለ መሣሪያ ማግኘት እንደሚፈልጉ ሲገልጹ ነበር። መጽሐፍ ማንበብ የሚያስፈራቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ በብሮሹር አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፈቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ። በተጨማሪም ብሮሹሮችን በብዙ ቋንቋዎች መተርጎም ይቀላል።
3. ይህ ብሮሹር ከሌሎች የማስጠኛ ጽሑፎች የሚለየው እንዴት ነው?
3 ብሮሹሩ የተዘጋጀበት መንገድ፦ ሰዎችን ለማስጠናት የምንጠቀምባቸው አብዛኞቹ ጽሑፎች የተዘጋጁት አንድ ሰው ጽሑፎቹን በማንበብ ያለ ማንም እገዛ እውነትን እንዲረዳ በሚያስችል መንገድ ነው። ይህ ብሮሹር ግን የተለየ ነው። ብሮሹሩ የተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስን በአስተማሪ እገዛ ለማጥናት በሚያስችል መንገድ ነው። በመሆኑም ጽሑፉን ስናበረክት በአንድ ወይም በሁለት አንቀጾች ላይ አብረን መወያየታችን የተሻለ ነው። አንቀጾቹ አጫጭር በመሆናቸው በር ላይ እንዳለን ወይም በግለሰቡ የሥራ ቦታ ሆነን ልንወያይባቸው እንችላለን። ከትምህርት 1 ጀምረን መወያየታችን ጥሩ ቢሆንም ጥናቱን ከፈለግነው ትምህርት መጀመር እንችላለን።
4. ብሮሹሩ ሰዎችን በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ለማስተማር የሚረዳን እንዴት ነው?
4 በበርካታ ጽሑፎቻችን ላይ ለአንቀጹ ጥያቄ የሚሆነውን መልስ እዚያው አንቀጹ ውስጥ ማግኘት ይቻላል። በዚህ ጽሑፍ ላይ ግን መልሶቹ በዋነኝነት የሚገኙት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። አብዛኞቹ ሰዎች ጽሑፎቻችን ከማጥናት ይልቅ ራሱን መጽሐፍ ቅዱስን ቢማሩ ይመርጣሉ። በመሆኑም በብሮሹሩ ላይ ያሉት አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ምዕራፍና ቁጥራቸው እንጂ ሐሳባቸው አልሰፈረም። እንግዲያው እነዚህን ጥቅሶች ከመጽሐፍ ቅዱስ አውጥቶ ማንበብ ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ ጥናቶቻችን እየተማሩ ያሉት ነገር ከአምላክ የመጣ ትምህርት እንደሆነ እንዲገነዘቡ ያደርጋል።—ኢሳ. 54:13
5. አስጠኚው ጥናት ከመምራቱ በፊት ምንጊዜም በሚገባ መዘጋጀት የሚኖርበት ለምንድን ነው?
5 ብሮሹሩ ሁሉንም ጥቅሶች አያብራራም። ለምን? ተማሪው ጥያቄዎች እንዲያነሳና አስተማሪውም የማስተማር ችሎታውን እንዲጠቀም ታስቦ ስለተዘጋጀ ነው። በመሆኑም አስተማሪው ጥናት ከመምራቱ በፊት ምንጊዜም በሚገባ መዘጋጀቱ አስፈላጊ ነው። ይሁንና ብዙ እንዳታወሩ ተጠንቀቁ። እርግጥ ጥቅሶችን ማብራራት እንደሚያስደስተን የታወቀ ነው። ያም ቢሆን ብዙውን ጊዜ ተማሪው ስለ ጥቅሱ ያለውን አመለካከት እንዲገልጽ መጠየቁ የተሻለ ጥቅም ያስገኛል። ጥያቄዎችን በጥሩ ሁኔታ የምንጠቀም ከሆነ እያንዳንዱ ጥቅስ የገባበትን ዓላማ ራሱ እንዲገነዘብ ልንረዳው እንችላለን።—ሥራ 17:2
6. ይህን ብሮሹር፦ (ሀ) በአምላክም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥርጣሬ ያላቸውን ሰዎች ስናነጋግር፣ (ለ) ከቤት ወደ ቤት ስንሰብክ፣ (ሐ) ቀጥተኛ አቀራረብ ተጠቅመን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር እና (መ) ተመላልሶ መጠየቅ ስናደርግ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?
6 በወሩ ውስጥ የሚበረከተው ጽሑፍ ምንም ይሁን ምን እንደማንኛውም የማስጠኛ ጽሑፍ ሁሉ ይህን ብሮሹር በማንኛውም ጊዜ ልናበረክተው እንችላለን። ብዙ አስፋፊዎች ቀጥተኛ አቀራረብ ተጠቅመው በር ላይ እንዳሉ በብሮሹሩ ጥናት ያስጀምራሉ። በተጨማሪም በአውራጃ ስብሰባው ላይ እንደተጠቀሰው ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ለማነጋገር በዚህ ብሮሹር መጠቀም “ተመላልሶ ማድረግ በጣም አስደሳች እንዲሆንልህ ሊያደርግ ይችላል!”—ከገጽ 5 እስከ 7 ላይ የሚገኙትን ሣጥኖች ተመልከት።
7. በብሮሹሩ ተጠቅማችሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት የምትችሉት እንዴት ነው?
7 በብሮሹሩ ጥናት መምራት የሚቻልበት መንገድ፦ ውይይቱን ለመጀመር በተራ ቁጥር የሰፈሩትንና በደማቅ የተጻፉትን ጥያቄዎች ማንበብ እንችላለን። ከዚያም አንቀጹንና በሰያፍ የተጻፉትን ጥቅሶች አንብቡ። የታሰበባቸው ጥያቄዎች በመጠየቅ የምታነጋግሩት ሰው የጥቅሱን ሐሳብ መረዳቱን ማረጋገጥ ትችላላችሁ። ከዚያም ወደሚቀጥለው ክፍል ከማለፋችሁ በፊት ግለሰቡ ነጥቡን አግኝቶት እንደሆነ ለማወቅ በደማቅ የተጻፈውን ጥያቄ አቅርቡለት። መጀመሪያ አካባቢ፣ በደማቅ ከተጻፉት ጥያቄዎች በአንዱ ላይ ብቻ መወያየታችሁ የተሻለ ሊሆን ይችላል። ከጊዜ በኋላ ግን ረዘም ያለ ጊዜ ወስዳችሁ አንድ ትምህርት ላይ ያሉትን ጥያቄዎች በሙሉ ልትወያዩባቸው ትችላላችሁ።
8. ጥቅሶችን ማስተዋወቅ ያለብን እንዴት ነው? ለምንስ?
8 በደማቅ ለተጻፉት ጥያቄዎች ቀጥተኛ መልስ ማግኘት የሚቻለው “አንብብ” ተብሎ በተጻፈባቸው ጥቅሶች ላይ ነው። ጥቅስ ስናስተዋውቅ “ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ጽፏል፣” ወይም ደግሞ “ነቢዩ ኤርምያስ ምን እንዳለ ልብ በል” ብለን አለመናገራችን የተሻለ ነው። አለበለዚያ የምናነጋግረው ሰው የምንጠቅሰው የሰዎችን ሐሳብ ሊመስለው ይችላል። “የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል” አሊያም “በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኝ አንድ ትንቢት ምን እንደሚል ልብ በል” ማለቱ የተሻለ ነው።
9. በጥናቱ ወቅት ሁሉም ጥቅሶች ሊነበቡ ይገባል?
9 በትምህርቶቹ ላይ ያሉት ሁሉም ጥቅሶች ሊነበቡ ይገባል? ወይስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አውጥተን ማንበብ የሚኖርብን “አንብብ” የሚል የተጻፈባቸውን ጥቅሶች ብቻ ነው? ይህ እንደ ሁኔታው የሚወሰን ነው። በትምህርቶቹ ውስጥ ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በሙሉ የተጠቀሱት ያለ ምክንያት አይደለም። እያንዳንዱ ጥቅስ ልትወያዩበት የሚገባ ሐሳብ የያዘ ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን ተማሪው ያለውን ጊዜ፣ ፍላጎቱን ወይም ደግሞ የማንበብ ችሎታውን ግምት ውስጥ በማስገባት “አንብብ” የሚል የተጻፈባቸውን ጥቅሶች ብቻ ለማንበብ ልንወስን እንችላለን።
10. ጥናቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ መቀጠል የሚቻለው መቼ ነው?
10 ጥናቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ መቀጠል፦ ለተወሰነ ጊዜ ካጠናችሁ በኋላ እንዲሁም ጥናታችሁን የምታከናውኑት በቋሚነት ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ማጥናት ልትጀምሩ ትችላላችሁ፤ ወይም ደግሞ ምሥራች የተባለውን ብሮሹር እስከ መጨረሻው ለማጥናት ትመርጡ ይሆናል። አስፋፊዎች ጥናቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ መቀጠል የሚኖርባቸው መቼ እንደሆነ ለመወሰን የማመዛዘን ችሎታቸውን መጠቀም ይኖርባቸዋል። በዚህ መጽሐፍ ለማስጠናት ከወሰንን ከመጀመሪያው ምዕራፍ መጀመር ይኖርብናል? በዚህ ረገድ አንድ ዓይነት ሕግ ማውጣት አይቻልም። ምክንያቱም የእያንዳንዱ ግለሰብ ሁኔታ የተለያየ ነው። ይሁንና አብዛኞቹ ተማሪዎች እነዚያኑ ትምህርቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከተባለው መጽሐፍ ላይ በጥልቀት የሚያጠኑ ከሆነ ጥቅም ያስገኝላቸዋል።
11. ይህን አዲስ ብሮሹር በጥሩ ሁኔታ መጠቀም ያለብን ለምንድን ነው?
11 መልካም ዜና መስማት ብርቅ በሆነበት በዚህ ዓለም ውስጥ ምሥራች የመናገር ታላቅ መብት አግኝተናል፤ የአምላክ መንግሥት እየገዛ እንደሆነና በቅርቡ ጽድቅ የሚሰፍንበት አዲስ ዓለም እንደሚመጣ እናውጃለን። (ማቴ. 24:14፤ 2 ጴጥ. 3:13) ይህን መልእክት የሚሰሙ ሁሉ በመንፈስ መሪነት በተጻፈው በሚከተለው ሐሳብ እንደሚስማሙ እርግጠኞች ነን፦ “በተራሮች ላይ የቆሙ፣ የምሥራች ይዘው የሚመጡ እግሮች፣ ሰላምን የሚናገሩ፣ መልካም ዜና የሚያበስሩ፣ ድነትን የሚያውጁ፣ ጽዮንንም፣ ‘አምላክሽ ነግሦአል’ የሚሉ እንዴት ያማሩ ናቸው።” (ኢሳ. 52:7) ይህን አዲስ ብሮሹር በመጠቀም በክልላችን ውስጥ ለሚገኙ እውነትን ለተጠሙ ሰዎች ከአምላክ የተላከውን ምሥራች እናውጅ!
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአምላክም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥርጣሬ ያላቸውን ሰዎች ስታነጋግሩ፦
● በአንዳንድ አካባቢዎች ሰዎች “አምላክ” ወይም “መጽሐፍ ቅዱስ” የሚሉትን ቃላት ሲሰሙ ውይይቱን ወዲያው ያቋርጣሉ። በእናንተ ክልል ሁኔታው እንዲህ ከሆነ ሰዎች የሚያሳስቧቸውን ጉዳዮች አንስቶ መወያየቱ የተሻለ ሊሆን ይችላል፤ ለምሳሌ ያህል፣ መልካም አገዛዝ እንዲሰፍን ስለሚያደርግ መንግሥት፣ አስደሳች የቤተሰብ ሕይወት ለመምራት የሚረዳ መመሪያ ማግኘት ስለሚቻልበት መንገድ እንዲሁም ስለ ወደፊቱ ጊዜ አንስቶ መወያየት ይቻላል። እንዲህ ዓይነት ሰዎችን ስናገኝ ምሥራች የተባለውን ብሮሹር ከማስተዋወቃችን በፊት አምላክ መኖሩን ስለሚያረጋግጡ ማስረጃዎች እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበት መጽሐፍ ነው የምንለው ለምን እንደሆነ በደንብ ብናወያያቸው የተሻለ ሊሆን ይችላል።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከቤት ወደ ቤት ስትሰብኩ፦
● “ዛሬ የመጣሁት አምላክ ወደፊት ለሰው ልጆች ምን እንዳዘጋጀ ልነግርዎት ነው። አምላክ ከሚደርስብን መከራ ይገላግለናል ብለው አስበው ያውቃሉ? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] ይህ ብሮሹር መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠውን መልስ ማወቅ እንዲችሉ ይረዳዎታል። [ብሮሹሩን ስጠውና በትምህርት 1 ላይ የሚገኘውን የመጀመሪያ አንቀጽ አብራችሁ አንብቡ፤ ከዚያም ኤርምያስ 29:11ን አውጥታችሁ አንብቡ።] ከዚህ ጥቅስ አንጻር አምላክ ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚያመጣ ማመን ምክንያታዊ አይመስልዎትም? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] ማንበብ የሚፈልጉ ከሆነ ይህን ብሮሹር ልሰጥዎት እችላለሁ። በሚቀጥለው ጊዜ ‘ለሰው ልጆች ሥቃይ ምክንያት የሆኑ ነገሮችን በሙሉ የሚያስወግደው እንዴት ነው?’ ለሚለው ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መልስ ከሁለተኛው አንቀጽ ላይ መወያየት እንችላለን።” የቤቱ ባለቤት ጊዜ ካለው ግን በመጀመሪያው ቀን ሁለቱንም አንቀጾችና ሌሎቹን ሦስት ጥቅሶች አንብባችሁ ልትወያዩባቸው ትችላላችሁ። ከዚያም እዚያው ትምህርት ላይ ባለው በሁለተኛው ጥያቄ ላይ ለመወያየት ቀጠሮ ያዙ።
● “ብዙ ሰዎች በተለይ አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ወደ አምላክ ይጸልያሉ። እርስዎስ ይጸልያሉ? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] አምላክ ሁሉንም ጸሎቶች የሚሰማ ይመስልዎታል? ወይስ የማይደሰትባቸው ጸሎቶች አሉ? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ የያዘ ብሮሹር ባሳይዎት ደስ ይለኛል። [ብሮሹሩን ስጠውና በትምህርት 12 በመጀመሪያው አንቀጽ ላይ እና “አንብብ” የሚል በተጻፈባቸው ጥቅሶች ላይ ተወያዩ።] አምላክ እኛን ለመስማት ፈቃደኛ መሆኑ ልብ የሚነካ አይደለም? አምላክ ጸሎታችንን እንዲሰማ ከፈለግን ስለ እሱ በደንብ ማወቅ ይኖርብናል። [ትምህርት 2ን አውጣና ንዑስ ርዕሶቹን አሳየው።] ብሮሹሩን ማንበብ የሚፈልጉ ከሆነ ልሰጥዎት እችላለሁ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ትኩረት የሚስቡ ጥያቄዎች ምን መልስ እንደሚሰጥ ሌላ ጊዜ ተገናኝተን መወያየት እንችላለን።”
● “ብዙ ሰዎች በዓለማችን ላይ የሚከናወኑትን ነገሮች ሲመለከቱ ስጋት ያድርባቸዋል። በዓለማችን ላይ የሚታዩት ሁኔታዎች እየተሻሻሉ የሚሄዱ ይመስልዎታል? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ተስፋ የሚፈነጥቅ ምሥራች እንደያዘ ሲሰሙ ይደነቃሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ እንደሚሰጥ ላሳይዎት።” ብሮሹሩን ስጠውና በጀርባ ሽፋኑ ላይ ያሉትን ጥያቄዎች አሳየው። ከዚያም እሱ የመረጠው ጥያቄ የሚገኝበትን ትምህርት አውጣና የመጀመሪያውን ጥያቄ በመጠቀም እንዴት ማጥናት እንደምትችሉ አሳየው። በዚያው ትምህርት ውስጥ በሚገኘው ሁለተኛ ጥያቄ ላይ ለመወያየት ቀጠሮ ያዙ።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቀጥተኛ አቀራረብ ተጠቀሙ፦
● “ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር አዲስ ዝግጅት አድርገናል፤ ዛሬ ቤትዎ የመጣሁት ስለዚህ ዝግጅት ልነግርዎት ነው። ይህ ብሮሹር ወሳኝ ለሆኑ ጥያቄዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መልስ ለማግኘት የሚረዱ 15 ትምህርቶችን የያዘ ነው። [የብሮሹሩን የፊትና የጀርባ ሽፋን አሳየው።] መጽሐፍ ቅዱስን ለመመርመር ሞክረው ያውቃሉ? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] መጽሐፍ ቅዱስን በዚህ ብሮሹር ተጠቅሞ መመርመር ምን ያህል ቀላል እንደሆነ ላሳይዎት። [ትምህርት 3ን አውጣና በሦስተኛው ጥያቄ ሥር በሚገኘው የመጀመሪያ አንቀጽ ላይ ተወያዩበት፤ ከዚያም ራእይ 21:4, 5ን አንብብ። ሁኔታው አመቺ ከሆነ በቀጣዩ አንቀጽና “አንብብ” የሚል በተጻፈባቸው ጥቅሶች ላይ ተወያዩ።] ማንበብ የሚፈልጉ ከሆነ ይህን ብሮሹር ልሰጥዎት እችላለሁ። መጽሐፍ ቅዱስን በዚህ መልኩ ማጥናት ምን እንደሚመስል ለማወቅ ቢያንስ አንድ ጊዜ እንዲሞክሩት እንጋብዝዎታለን። ጥናቱን ከወደዱት መቀጠል ይችላሉ። ታዲያ ሌላ ጊዜ ተገናኝተን በመጀመሪያው ትምህርት ላይ ብንወያይ ምን ይመስልዎታል? ይህ ትምህርት ከአንድ ገጽ እንኳ አይበልጥም።”
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርጉ ብሮሹሩን አስተዋውቁ፦
● ፍላጎት ላሳየ ሰው ተመላልሶ መጠየቅ ስናደርግ እንዲህ ማለት እንችላለን፦ “እንደገና ስላገኘሁዎት ደስ ብሎኛል። መጽሐፍ ቅዱስ ትኩረት ለሚስቡ የተለያዩ ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ የያዘ ብሮሹር ይዤልዎት መጥቻለሁ። [ብሮሹሩን ስጠውና የጀርባ ሽፋኑን አሳየው።] በየትኛው ጥያቄ ላይ ብንወያይ ደስ ይልዎታል? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው። ከዚያም እሱ የመረጠውን ትምህርት አውጣ።] ይህን ብሮሹር በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ላሳይዎት።” በአንድ ወይም በሁለት አንቀጾች ላይ እንዲሁም “አንብብ” የሚል በተጻፈባቸው ጥቅሶች ላይ በመወያየት ጥናቱ እንዴት እንደሚመራ አሳየው። እንዲህ በማድረግ በቀላሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አስጀመርክ ማለት ነው! ብሮሹሩን አበርክትለትና ሌላ ጊዜ ለመገናኘት ቀጠሮ ያዙ። በአንድ ትምህርት ላይ ተወያይታችሁ ስትጨርሱ ግለሰቡ በመረጠው ሌላ ትምህርት ላይ አሊያም ከብሮሹሩ መጀመሪያ አንስታችሁ ውይይታችሁን መቀጠል ትችላላችሁ።