መከራ የደረሰባቸው ሰዎች እፎይታ ያገኙ ይሆን?
አንተ ብቻ ሳትሆን መላው የሰው ዘር ከሥቃይና መከራ ተገላግሎ ለማየት ትጓጓለህ? እስቲ እነዚህን ምሳሌዎች ተመልከት:-
ሶንያ የደረሰባት መከራ ልትሸከመው ከምትችለው በላይ ነበር።a ኑሮዋ መመሰቃቀል የጀመረው ባሏ ለአሥር ዓመታት ያህል ሲማግጥ እንደኖረ ባወቀች ጊዜ ነበር። ከዚያም ትንሹ ልጅዋ በኤች አይ ቪ ቫይረስ በመለከፉ በኤድስ ሞተ። ከሁለት ዓመታት በኋላ ሌላው ልጅዋ ታምሞ ብዙም ሳይቆይ እርሱም በኤድስ ሞተ። ሶንያ እንዲህ በማለት ታስታውሳለች:- “ሊሞት አካባቢ ጣሩ በዝቶ ነበር። ከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት አደረበት፣ ፀጉሩ ሁሉ ረገፈ፣ በቅጡ ማየትም አቃተው። በጣም የሚያሳዝን ነበር።”
የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነችው ብራዚላዊቷ ፋቢያና ደግሞ በዓለም ውስጥ የሚታየው ማኅበራዊ የፍትሕ መጓደል ያሳስባት ነበር። ከጊዜ በኋላ እሷም በአሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ወደቀች። በመንፈስ ጭንቀት ይሠቃይ የነበረው ወንድሟ ራሱን ገደለ። ፋቢያና ከሥራ በተባረረች ጊዜ አንድ ወዳጅዋ ዕድሏ እንዲህ የጠመመባት አንድ ሰው ቢያስደግምባት ነው ብላ ስላሰበች ፔዴሳንቶ (ጠንቋይ) ዘንድ እንድትሄድ ትመክራታለች! ይሁን እንጂ ፔዴሳንቶው ምንም አልፈየደም። ፋቢያና ትሠቃይ ነበር፤ ከደረሰባት መከራ የተነሣ እንቅልፍ እንኳ አልነበራትም።
የአና መከራ የጀመረው ደግሞ ገና ከሕፃንነቷ ነው። “አንድ ዓመት ሲሞላኝ” ትላለች አና “እናቴ ትታኝ ስለሄደች አያቴ ወስደው አሳደጉኝ።” አና ሦስት ዓመት ሲሞላት አያቷ ሞቱ። አና በሪዮ ዴ ጄኔሮ ወደሚገኝ ጓላሟታ ተወሰደችና እስከ 13 ዓመት ዕድሜዋ ድረስ እዚያው ኖረች። አና እንዲህ ትላለች:- “የሚደረግልን አያያዝ በጣም አስከፊ ስለ ነበር ዓመፀኛ ሆንኩ። እያደግሁ ስመጣ ሥራዬ ሁሉንም ነገር መቃወም ሆነ።”
በዚህም ይሁን በዚያ መከራ ሕይወቱን ያልዳሰሰው ሰው ያለ አይመስልም። በእርግጥም ደግሞ በየዕለቱ ዜና ባየን፣ ባነበብንና በሰማን ቁጥር በሰው ልጆች ላይ የሚደርሱትን አሳዛኝ ነገሮች ማስተዋላችን አይቀርም። ዶክተር ማሪ ሲክስ ዊሌ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የዘመናችን የመገናኛ ብዙሐን እያለ ያለማቋረጥ ከሚዘንብብን የአሳዛኝ ዜናዎች ውርጅብኝ ማምለጥ አይቻልም። ጦርነቶች፣ የተፈጥሮ አደጋዎች፣ የኢንዱስትሪ ውድመት፣ የሰው ሕይወት የሚቀጠፍባቸው የመኪና አደጋዎች፣ ወንጀል፣ ሽብርተኝነት፣ በጾታ ማስነወር፣ የግዳጅ ወሲብ፣ በቤት ውስጥ የሚፈጸም ዓመፅና እነዚህን የመሳሰሉት ነገሮች በ20ኛው መቶ ዘመን የስሜት መቃወስ ዘግናኝና የዕለት ተዕለት መወያያ ወደመሆን ደረጃ እንዲደርስ አድርገውታል።” ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ የሰው ልጅ ስላለበት ሁኔታ ሲናገር “ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለንና” በማለት እውነታውን ጠቅለል አድርጎ ገልጿል።— ሮሜ 8:22
አንተስ? መከራ እየደረሰብህ ነውን? እፎይታ የሚሰጥ ምን ነገር ይኖራል ብለህ ልትጠብቅ ትችላለህ? እውነተኛ ሰላም የምታገኝበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? ሶንያ፣ ፋቢያና እና አና እውነተኛ ማጽናኛና ሰላም አግኝተዋል! በሚቀጥለው ርዕስ ስለዚህ ጉዳይ ልታነብ ትችላለህ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዚህ ርዕስ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።