የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w97 4/15 ገጽ 13-19
  • እውነተኛውን ሰላም ፈልጉ፣ ተከተሉትም!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • እውነተኛውን ሰላም ፈልጉ፣ ተከተሉትም!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሰዎች ሰላማውያን ሊሆኑ ይችላሉ
  • ሰላምን የሚከተሉ ሰዎች
  • ከዚህ የበለጠ ለውጥ
  • የሰላሙ ገዢ አስተዳደር
  • እውነተኛ ሰላም—ከየት ይገኛል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • “የአምላክ ሰላም” ልባችሁን ይጠብቅ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ዘላቂ ሰላም በእርግጥ የሚመጣው መቼ ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች ሆኖ ማገልገል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
w97 4/15 ገጽ 13-19

እውነተኛውን ሰላም ፈልጉ፣ ተከተሉትም!

“ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፣ . . . ከክፉ ፈቀቅ ይበል፣ መልካምንም ያድርግ፣ ሰላምን ይሻ ይከተለውም።” — 1 ጴጥሮስ 3:​10, 11

1. የትኞቹ በስፋት የታወቁ የኢሳይያስ ቃላት በትክክል እንደሚፈጸሙ የተረጋገጠ ነው?

“ሰይፋቸውን ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።” (ኢሳይያስ 2:​4) ይህ የታወቀ ጥቅስ በኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጽሕፈት ቤት አቅራቢያ በግልጽ ተጽፎ የሚታይ ቢሆንም ይህ ዓለም አቀፍ ድርጅት እነዚህን ቃላት ተግባራዊ ማድረግ ፈጽሞ አልቻለም። ይሁን እንጂ ይህ ጥቅስ መሬት ጠብ ከማይለው የይሖዋ አምላክ ቃል የተወሰደ እንደመሆኑ መጠን ፍጻሜውን እንደሚያገኝ የተረጋገጠ ነው።​— ኢሳይያስ 55:​10, 11

2. በኢሳይያስ 2:​2, 3 መሠረት ‘በዘመኑ ፍጻሜ’ ምን ነገር ይከናወናል?

2 በኢሳይያስ 2:​4 ላይ የሚገኙት ቃላት ስለ ሰላም የተነገረ አንድ አስገራሚ ትንቢት ክፍል ሲሆኑ ይህ ትንቢት በእኛ ዘመን ፍጻሜውን እያገኘ ነው። ትንቢቱ ጦርነትም ሆነ የጦር መሣሪያዎች እንደማይኖሩ የሚገልጸውን እጅግ አስደሳች ተስፋ ከመጥቀሱ በፊት እንዲህ ይላል:- “በዘመኑ ፍጻሜ የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፣ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፣ አሕዛብም ሁሉ ወደ እርሱ ይሰበሰባሉ። ሕግ ከጽዮን የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና ብዙዎች አሕዛብ ሄደው:- ኑ፣ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፣ በጎዳናውም እንሄዳለን ይላሉ።”​— ኢሳይያስ 2:​2, 3

ሰዎች ሰላማውያን ሊሆኑ ይችላሉ

3. ጠበኛ የነበረ ሰው ተለውጦ ሰላማዊ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

3 ሰዎች ሰላማዊ ጎዳና መከተል እንዲችሉ ስለ ይሖዋ መንገዶች መማር እንደሚኖርባቸው ልብ በሉ። የይሖዋን ትምህርት በታዛዥነት መከተል የአንድን ሰው አስተሳሰብና ድርጊት ሊለውጠው ስለሚችል ጠበኛ የነበረ ሰው ሰላማዊ ይሆናል። ታዲያ እንዲህ ዓይነቱን ለውጥ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? ሮሜ 12:​2 (የ1980 ትርጉም) እንዲህ ይላል:- “መልካሙንና ደስ የሚያሰኘውን ፍጹም የሆነውንም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወቅ እንድትችሉ፣ አእምሮአችሁ ታድሶ ሕይወታችሁ ይለወጥ እንጂ የዚህን ዓለም ሰዎች ክፉ ጠባይ አትከተሉ።” አእምሮአችንን በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶችና ምክሮች በመሙላት እናድሰዋለን ወይም ከበፊቱ ወደ ተለየ አቅጣጫ እንዲያተኩር እናደርገዋለን። አዘውትረን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችን ይህን ለውጥ እንድናደርግ የሚረዳን ከመሆኑም በላይ ይሖዋ ለእኛ ያለው ፈቃድ ምን እንደሆነ እንድንገነዘብ ስለሚረዳን መንገዳችን ወለል ብሎ ይታየናል።​— መዝሙር 119:​105

4. አንድ ሰው ሰላማዊ የሆነውን አዲስ ሰውነት የሚለብሰው እንዴት ነው?

4 የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አስተሳሰባችንን ብቻ ሳይሆን ድርጊታችንንና ሁለንተናዊ ባሕርያችንን ጭምር ይለውጣል። ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠውን ማሳሰቢያ ለመፈጸም ይረዳናል:- “ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፣ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፣ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።” (ኤፌሶን 4:​22-24) አእምሮአችንን የሚያንቀሳቅሰው ኃይል ውስጣዊ ነው። ለይሖዋና ለሕጎቹ ያለን ፍቅር እያደገ ሲሄድ እየታደሰና ኃይል እያገኘ ይሄድና መንፈሳዊና ሰላማውያን ሰዎች ያደርገናል።

5. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው “አዲስ ትእዛዝ” በመካከላቸው ሰላም እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ያደረገው እን​ዴት ነው?

5 የዚህ ዓይነቱ መታደስ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ሰዓት በሰጣቸው ትእ​ዛዝ ላይ በግልጽ ተንጸባርቋል:- “እርስ በርሳችሁ ትዋ​ደዱ ዘንድ፣ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።” (ዮሐንስ 13:​34, 35) ይህ የክርስቶስን የመሰለና ራስ ወዳድነት የሌለበት ፍቅር ደቀ መዛሙርቱን ፍጹም በሆነ የአንድነት ማሠሪያ ያስተሳስራቸዋል። (ቆላስይስ 3:​14 NW) አምላክ ቃል የገባውን ሰላም የሚያገኙት ይህን “አዲስ ትእዛዝ” ለመቀበልና ከእርሱም ጋር ተስማምተው ለመኖር ፈቃደኛ የሚሆኑ ሰዎች ብቻ ናቸው። ዛሬ ይህን የሚያደርጉ ሕዝቦች ይኖራሉን?

6. የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ውስጥ ካሉት ሰዎች በተለየ መልኩ ሰላም ያገኙት ለምንድን ነው?

6 የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነታቸው ፍቅርን ለማንጸባረቅ ይጥራሉ። ከዓለም ብሔራት በሙሉ የተውጣጡ ቢሆኑም በዓለም ግጭቶች ተካፋይ አይሆኑም፤ ይህንን ባለማድረጋቸው የሚደርስባቸውን ከባድ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ተጽዕኖም በጽናት ይቋቋማሉ። አንድነት ያለው ሕዝብ በመሆን ከይሖዋ ተምረዋል፤ በመሆኑም ሰላም አግኝተዋል። (ኢሳይያስ 54:​13) በፖለቲካ ግጭቶች ገለልተኝነታቸውን ይጠብቃሉ፤ በማንኛውም ዓይነት ጦርነትም አይካፈሉም። ከዚህ በፊት ጠበኞች የነበሩ ሰዎች ያን ጠባያቸውን እርግፍ አድርገው ትተዋል። የክርስቶስ ኢየሱስን አርዓያ በመከተል ሰላም ወዳድ ክርስቲያኖች ሆነዋል። ጴጥሮስ የሰጠውንም ምክር በሙሉ ልባቸው ይከተላሉ:- “ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፣ መላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል፤ ከክፉ ፈቀቅ ይበል፣ መልካምንም ያድርግ፣ ሰላምን ይሻ ይከተለውም።”​— 1 ጴጥሮስ 3:​10, 11፤ ኤፌሶን 4:​3

ሰላምን የሚከተሉ ሰዎች

7, 8. ጦርነትን እርግፍ አድርገው ትተው እውነተኛ ሰላም ፈላጊ የሆኑ ሰዎችን ምሳሌ ጥቀስ። (አንተ የምታውቃቸው ሌሎች ምሳሌዎች ካሉ ጥቀስ።)

7 ለምሳሌ ያህል የአንድ ልዩ የሆነ የፀረ አሸባሪዎች ጓድ አባል የነበረውን ራሚ ኦቬድን እንመልከት። ጠላቶቹን ለመግደል የሚያስችል ሥልጠና ተሰጥቶታል። ረቢዎች የሚወዳት ሴት፣ እስያዊት ማለትም ከአሕዛብ ወገን ስለሆነች ብቻ እንዳያገባ እስከ ከለከሉት ቀን ድረስ በእስራኤላዊነቱ በጥብቅ ያምን ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መፈለግ ጀመረ። ከዚያም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘ። ከምሥክሮቹ ጋር ያደረገው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከእንግዲህ ጭፍን ብሔረተኛ መሆን እንደማይችል አሳመነው። ክርስቲያናዊ ፍቅር ማሳየት ማለት ጦርነትንና የጦር መሣሪያዎችን እርግፍ አድርጎ ጥሎ ሁሉንም ዘሮች መውደድ ማለት ነው። “ውድ ወንድሜ ራሚ”! የሚል የመክፈቻ ቃላት የያዘ ደግነት የሞላበት ደብዳቤ በደረሰው ጊዜ በጣም ተደነቀ። ይህ ደብዳቤ ይህን ያህል ያስደነቀው ለምን ነበር? ደብዳቤውን የጻፈችው አንዲት ፍልስጥኤማዊ ምሥክር ነበረች። “ይህ ፈጽሞ ሊታመን የማይችል ነገር ነው። ፍልስጥኤማውያን ጠላቶቼ ሆነው እያለ እንዴት የእነርሱ ወገን የሆነች ሴት ‘ወንድሜ’ ብላ ትጠራኛለች ብዬ አሰብኩ” ሲል ራሚ ተናግሯል። ዛሬ ራሚና ሚስቱ በአምላክ ጎዳና እውነተኛውን ሰላም በመከተል ላይ ናቸው።

8 ሌላው ምሳሌ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሩስያን ወርሮ በነበረው የጀርመን ሠራዊት ውስጥ ያገለግል የነበረው ገኦርግ ሮይተር ነው። ብዙም ሳይቆይ ሂትለር ያወጣው ዓለምን የመግዛት እቅድ ከንቱ እንደሆነ ተሰማው። ከጦርነቱ ከተመለሰ በኋላ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። እንዲህ በማለት ጽፏል:- “በመጨረሻ ነገሮች ግልጽ እየሆኑልኝ መምጣት ጀመሩ። ለዚህ ሁሉ ደም መፋሰስ በኃላፊነት የሚጠየቀው አምላክ እንዳልሆነ ተገነዘብኩ። . . . ምድር አቀፍ ገነት ለማቋቋምና ታዛዥ ለሆኑ የሰው ዘሮች የዘላለም በረከት ለመስጠት ዓላማ እንዳለው አወቅኩ። . . . ሂትለር ስለ ‘ሺህ ዓመት ግዛቱ’ በጉራ ደንፍቶ ነበር። ይሁን እንጂ የገዛው ለ12 [ዓመታት] ብቻ ነው! ያም ቢሆን በጣም አስከፊ ውጤት አስከትሏል። በምድር ላይ የሺህ ዓመት ግዛት ማቋቋም የሚችለውና የሚያቋቁመው . . . ክርስቶስ እንጂ ሂትለር አይደለም።” ከዚያ ወዲህ ገኦርግ የእውነተኛው ሰላም መልእክተኛ በመሆን 50 ለሚያክሉ ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ሠርቷል።

9. በናዚ ጀርመን በነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ላይ የደረሰው ተሞክሮ ምሥክሮቹ ደፋር የዚያኑ ያክል ደግሞ ሰላማዊ እንደሆኑ የሚያሳየው እንዴት ነው?

9 በናዚ ግዛት ዘመን በጀርመን ይኖሩ የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች ያሳዩት የጸና አቋምና ገለልተኝነት አሁን ከ50 ዓመት በኋላ እንኳን ለአምላክና ለሰላም ስላላቸው ፍቅር ምሥክር ሆኖ እያገለገለ ነው። በቅርቡ በዋሽንግተን ዲ ሲ በሚገኘው የሆሎኮስት ቤተ መዘክር የታተመ ንዑስ መጽሐፍ የሚከተለውን አትቷል:- “የይሖዋ ምሥክሮች በናዚ ግዛት ሥር በጣም ከባድ ስደት ተቋቁመዋል። . . . አብዛኞቻቸው የደረሰባቸውን ሥቃይ፣ በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ያጋጠማቸውን መከራና አንዳንድ ጊዜም የሚፈጸምባቸውን ግድያ ችለው [ሃይማኖታቸውን ለመካድ] እምቢተኛ በመሆን ያሳዩት ድፍረት አብረዋቸው የነበሩትን ብዙ ሰዎች አክብሮት አትርፎላቸዋል።” ንዑስ መጽሐፉ በመቀጠል “ካምፖቹ ነጻ በመውጣት ላይ በነበሩበት ጊዜም ሥራቸውን ሳያቆሙ በሕይወት በተረፉት ሰዎች መካከል እየተዘዋወሩ አማኞች እንዲሆኑ ለማድረግ ይጥሩ ነበር” ይላል።

ከዚህ የበለጠ ለውጥ

10. (ሀ) እውነተኛ ሰላም እንዲመጣ ምን ትልቅ ለውጥ መደረግ አለበት? (ለ) ይህስ በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የተገለጸው እንዴት ነው?

10 ታዲያ ይህ ማለት የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎች በሙሉ በክርስቲያናዊ ገለልተኝነት እንዲያምኑ በማድረግ ለዓለም ሰላም እናመጣለን ብለው ያምናሉ ማለት ነውን? አይደለም! ሰላም በመላው ምድር ላይ እንዲሰፍን ከተፈለገ ከዚህ የበለጠ ለውጥ መካሄድ ይኖርበታል። ይህ ለውጥ ምንድን ነው? የሚከፋፍል፣ ጨቋኝና ዓመፀኛ የሆነው የሰው ልጅ አገዛዝ ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲጸልዩለት ባስተማረው የአምላክ መንግሥት ግዛት መተካት ይኖርበታል። (ማቴዎስ 6:​9, 10) ይሁን እንጂ ይህ የሚሆነው እንዴት ነው? ነቢዩ ዳንኤል መለኮታዊ መንፈስ ባሳየው ሕልም በመጨረሻው ቀን የአምላክ መንግሥት ‘የሰው እጅ ሳይነካው እንደተፈነቀለ’ አንድ ትልቅ ድንጋይ በምድር ላይ የተፈራረቁትን የሰው ልጆች ፖለቲካዊ አገዛዞች የሚወክለውን ግዙፍ ምስል መትቶ እንደሚያደቅቅ ተመልክቷል። በመቀጠልም እንዲህ ብሏል:- “በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል። ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል። እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች፣ ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች።”​— ዳንኤል 2:​31-44

11. ይሖዋ ሰላም ለማስፈን የሚያስፈልገውን ለውጥ የሚያመጣው በምን መንገድ ነው?

11 በዓለም ሁኔታ ላይ ይህን የመሰለ ሥር ነቀል ለውጥ የሚካሄደው ለምንድን ነው? ይሖዋ ምድርን ከሚያቆሽሿትና ከሚያበላሿት ሁሉ እንደሚያጸዳ ቃል ስለገባ ነው። (ራእይ 11:​18) ይህ የተሐድሶ ለውጥ የሚደረገው ይሖዋ በሰይጣንና በእርሱ ክፉ ዓለም ላይ በሚያካሂደው የጽድቅ ጦርነት ነው። ራእይ 16:​14, 16 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “ምልክት እያደረጉ የአጋንንት መናፍስት ናቸውና፣ በታላቁም ሁሉን በሚገዛ በእግዚአብሔር ቀን ወደሚሆነው ጦር እንዲያስከትቱአቸው ወደ ዓለም ሁሉ ነገሥታት [ወደ ፖለቲካዊ ገዢዎች] ይወጣሉ። በዕብራይስጥም አርማጌዶን ወደሚባል ስፍራ አስከተቱአቸው።”

12. አርማጌዶን ምን መልክ ይኖረዋል?

12 አርማጌዶን ምን ይመስል ይሆን? የኑክሌር እልቂት ወይም በሰው ልጅ ጥፋት የሚከሰት አደጋ አይሆንም። የለም፣ አርማጌዶን ጦርነትንና ጦርነቶቹን የሚያራምዱትን ሰዎች ጨርሶ የሚያወድም የአምላክ ጦርነት ነው። ሰላም ወዳድ ለሆኑ ሁሉ እውነተኛ ሰላም ለማምጣት የሚደረግ የአምላክ ጦርነት ነው። አዎን፣ አርማጌዶን አምላክ ባቀደለት ጊዜ ይመጣል። አይዘገይም። ነቢዩ ዕንባቆም በመንፈስ ተገፋፍቶ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “ራእዩ ገና እስከ ተወሰነው ጊዜ ነው፣ ወደ ፍጻሜውም ይቸኩላል፣ እርሱም አይዋሽም፣ ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው፣ እርሱ አይዘገይም።” (ዕንባቆም 2:​3) በሰብዓዊ አመለካከት ቀኑ የዘገየ መስሎ ሊሰማን ይችላል፤ ይሖዋ ግን ፕሮግራሙን አያዛንፍም። አርማጌዶን ይሖዋ አስቀድሞ በቀጠረው ቀን ይጀምራል።

13. አምላክ በቀንደኛው ወንጀለኛ በሰይጣን ዲያብሎስ ላይ ምን እርምጃ ይወስዳል?

13 ይህ ቁርጠኛ እርምጃ እውነተኛ ሰላም የሚመጣበትን ጥርጊያ መንገድ ይከፍታል! ይሁን እንጂ እውነተኛ ሰላም በጽኑ መሠረት ላይ እንዲጣል ሌላም ነገር ያስፈልጋል፤ ይኸውም መከፋፈል፣ ጥላቻና ግጭት እንዲፈጠር ምክንያት የሆነው አካል መወገድ ይኖርበታል። መጽሐፍ ቅዱስ ቀጥሎ እንደሚከናወን የሚተነብየውም ይህንኑ ነው። በቅርቡ ጦርነት ጠንሳሽና የሐሰት አባት የሆነው ሰይጣን በጥልቅ ውስጥ እንደሚታሠር ይገልጻል። ሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ 20:​1-3 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ይህን ክንውን በትንቢታዊ ራእይ ተመልክቶ ነበር:- “የጥልቁንም መክፈቻና ታላቁን ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ። የቀደመውንም እባብ ዘንዶውንም እርሱም ዲያብሎስና ሰይጣን የተባለውን ያዘው፣ ሺህ ዓመትም አሰረው፣ ወደ ጥልቅም ጣለው አሕዛብንም ወደፊት እንዳያስት ሺህ ዓመትም እስኪፈጸም ድረስ በእርሱ ላይ ዘግቶ ማኅተም አደረገበት።”

14. ይሖዋ በሰይጣን ላይ የሚወስደው የድል አድራጊነት እርምጃ እንዴት ሊገለጽ ይችላል?

14 ይህ ሊሆን የማይችል ቅዠት አይደለም። አምላክ ቃል የገባው ጉዳይ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ‘እግዚአብሔር ሊዋሽ አይችልም’ ይላል። (ዕብራውያን 6:​18) በዚህ ምክንያት ይሖዋ በነቢዩ ኤርምያስ በኩል እንዲህ ብሎ ሊናገር ችሏል:- “ምሕረትንና ፍርድን፣ ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር [ነኝ] . . . ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና።” (ኤርምያስ 9:​24) ይሖዋ የፍትሕና የጽድቅ ሥራ ይሠራል። በምድር ላይ በሚያመጣው ሰላምም ደስ ይለዋል።

የሰላሙ ገዢ አስተዳደር

15, 16. (ሀ) ይሖዋ ንጉሥ ሆኖ እንዲገዛ የመረጠው ማንን ነው? (ለ) ይህ አገዛዝ እንዴት ተደርጎ ተገልጿል? በአገዛዙ እነማን ይካፈላሉ?

15 በመንግሥቱ ግዛት ሥር ለሚኖሩት ሁሉ እውነተኛ ሰላም ለማምጣት ይሖዋ የመግዛቱን ሥልጣን ለእውነተኛው የሰላም ገዢ ለኢየሱስ ክርስቶስ አስረክቦታል፤ ይህም በኢሳይያስ 9:​6, 7 ላይ በትንቢት ተነግሯል:- “ሕፃን ተወልዶልናልና፣ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል። ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። . . . አለቅነቱ ይበዛል፣ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም። የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል።” መዝሙራዊውም ትንቢታዊ በሆነ መንገድ ስለ መሲሑ ሰላማዊ ግዛት ሲጽፍ “በዘመኑም ጽድቅ ያብባል፤ ጨረቃም እስኪያልፍ ድረስ ሰላም ብዙ ነው” ብሏል።​— መዝሙር 72:​7

16 በተጨማሪም 144,000ዎቹ በመንፈስ የተቀቡ የክርስቶስ ወንድሞች በሰማይ አብረውት ይገዛሉ። ጳውሎስ “የሰላምም አምላክ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን” ሲል የጻፈላቸው የክርስቶስ ተባባሪ ወራሾች እነዚህ ናቸው። (ሮሜ 16:​20) አዎን፣ በሰማያት ሆነው ክርስቶስ ጦርነት ናፋቂ በሆነው በሰይጣን ዲያብሎስ ላይ በሚቀዳጀው ድል ተካፋዮች ይሆናሉ!

17. እውነተኛ ሰላም ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

17 እንግዲያው አሁን የሚነሣው ጥያቄ እውነተኛ ሰላም ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርባችኋል? የሚል ነው። እውነተኛ ሰላም ሊመጣ የሚችለው በአምላክ መንገድ ብቻ ሲሆን ይህንንም ለማግኘት አዎንታዊ እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርባችኋል። የሰላሙን ገዢ መቀበልና በእርሱ ማመን ይገባናል። ይህ ማለት ክርስቶስ ኃጢአተኛውን የሰው ዘር የተቤዠና ነፃ ያወጣ መሆኑን መቀበል አለብን ማለት ነው። ኢየሱስ ራሱ በሰፊው የታወቁትን ቃላት እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአል።” (ዮሐንስ 3:​16) ክርስቶስ ኢየሱስ እውነተኛ ሰላምና ደህንነት የሚያሰፍን የአምላክ ወኪል መሆኑን ለማመን ፈቃደኛ ናችሁን? ሰላም እንደሚያመጣና የሚያመጣውም ሰላም የጸና እንደሚሆን ዋስትና ሊሰጥ የሚችል ሌላ ስም ከሰማይ በታች የለም። (ፊልጵስዩስ 2:​8-11) ለምን ቢባል? በአምላክ የተመረጠው ኢየሱስ ስለሆነ ነው። በምድር ላይ ከተመላለሱት ሁሉ የሚበልጠው የሰላም መልእክተኛ እርሱ ነው። ኢየሱስን ታዳምጣላችሁ? አርዓያውንስ ትከተላላችሁ?

18. ኢየሱስ በዮሐንስ 17:​3 ላይ በተናገረው መሠረት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

18 ኢየሱስ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:​3) በመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉት የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ አዘውትራችሁ በመገኘት ትክክለኛውን እውቀት መቅሰም ያለባችሁ ዛሬ ነው። እነዚህ ትምህርታዊ ስብሰባዎች ያገኛችሁትን እውቀትና ተስፋ ለሌሎች እንድታካፍሉ ያነሳሱአችኋል። እናንተም የአምላክ ሰላም መልእክተኞች ለመሆን ትችላላችሁ። በይሖዋ አምላክ ከታመናችሁ ኢሳይያስ 26:​3 (የ1980 ትርጉም) “በአንተ በመታመናቸው በዓላማቸው ለጸኑ ሁሉ ፍጹም የሆነውን ሰላምህን ትሰጣቸዋለህ” ባለው መሠረት በአሁኑ ዘመን እንኳን ሰላም ማግኘት ትችላላችሁ። መታመን የሚኖርባችሁ በማን ነው? “እናንት ሕዝቦች በዘመናት ሁሉ በይሖዋ ታመኑ፤ ያህ ይሖዋ የዘላለም አለት ነውና።”​— ኢሳይያስ 26:​4 NW

19, 20. ዛሬ ሰላምን የሚፈልጉና የሚከተሉ ሰዎች ወደፊት ምን ያገኛሉ?

19 በአምላክ ሰላማዊ አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም ለመኖር አሁን ቁርጥ ያለ እርምጃ ውሰዱ። የአምላክ ቃል በራእይ 21:​3, 4 ላይ የሚከተለውን ዋስትና ይሰጠናል:- “እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።” እናንተስ የምትናፍቁት እንዲህ ባለ ሰላማዊ ሁኔታ ለመኖር አይደለምን?

20 እንግዲያው አምላክ የሰጠውን ተስፋ አስታውሱ። “ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል። ቅንነትን ጠብቅ፣ ጽድቅንም እይ፤ ለሰላም ሰው ቅሬታ አለውና።” (መዝሙር 37:​11, 37) ይህ አስደሳች ቀን ሲመጣ ልባችን በአመስጋኝነት ተሞልቶ “በመጨረሻ እውነተኛ ሰላም አገኘን! የእውነተኛ ሰላም ምንጭ የሆነው ይሖዋ አምላክ ምስጋና ይድረሰው!” ለማለት ያብቃን።

ልታብራራ ትችላለህን?

◻ አንድ ሰው በአስተሳሰብና በድርጊት በኩል ለውጥ እንዲያደርግ የሚረዳው ምንድን ነው?

◻ የይሖዋ ምሥክሮች በግለሰብና በቡድን ደረጃ ለእውነተኛ ሰላም ያላቸውን ፍቅር ያሳዩት እንዴት ነው?

◻ ይሖዋ ጥላቻንና ጦርነትን በሚያራምዱት ሰዎች ላይ ምን እርምጃ ይወስዳል?

◻ የሰላሙ ገዢ አስተዳደር ለሰው ልጆች ምን ያመጣላቸዋል?

[በገጽ 14 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የኢሳይያስ ቃላት ፍጻሜያቸውን ያገኙት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሳይሆን ለይሖዋ ትምህርት አዎንታዊ ምላሽ በሰጡት ሰዎች አማካኝነት ነው

[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

እነዚህ ሁለት ሰዎች ሰላምን ለመከተል ሲሉ ለውጥ አድርገዋል

ራሚ ኦቬድ

ገኦርግ ሮይተር

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሰላሙ ገዢ አስተዳደር ሥር እውነተኛ ሰላም ይሰፍናል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ