የይሖዋን ፈቃድ ፈጽመዋል
ወላጆች ያሳዩት እምነት ወሮታ አስገኘ
እስራኤላውያን ወንድ ልጅ ሲወለድላቸው በጣም ይደሰቱ ነበር። ወንድ ልጅ መወለዱ የዘር መስመሩ እንዲቀጥልና ርስቱ ለቤተሰቡ እንዲጸና ያስችላል። ይሁን እንጂ በ1593 ከዘአበ ገደማ ወንድ ልጅ መውለድ በዕብራውያን ዘንድ እንደ በረከት ሳይሆን እንደ እርግማን የሚቆጠርበት ዓመት የነበረ ይመስላል። ግን ለምን? የግብፁ ፈርዖን በግዛቱ ውስጥ ያሉት አይሁዳውያን ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ መሄዱ ስላሰጋው አዲስ የተወለዱ ወንድ ልጆቻቸው ሁሉ እንዲገደሉ ትእዛዝ በማስተላለፉ ነው።— ዘጸአት 1:12, 15-22
ዓምራምና ዮኬቤድ የሚባሉ ዕብራውያን ባልና ሚስት አንድ የሚያምር ልጅ የወለዱት ዘግናኝ ዘር የማጥፋት ሙከራ በተደረገበት ጊዜ ነበር። የፈርዖንን ድንጋጌ ሲያስታውሱ ከመደሰት ይልቅ ምን ያህል በፍርሃት ተውጠው እንደነበረ መገመት አያዳግትም። ሆኖም ዓምራምና ዮኬቤድ ሕፃን ልጃቸውን ሲመለከቱ የመጣው ቢመጣ እሱን አሳልፎ ላለመስጠት ቆረጡ።— ዘጸአት 2:1, 2፤ 6:20 የ1980 ትርጉም
የእምነት እርምጃ
ዓምራምና ዮኬቤድ ሕፃን ልጃቸውን ለሦስት ወር ሸሸጉት። (ዘጸአት 2:2) ሆኖም ዕብራውያን በግብፃውያን አቅራቢያ ይኖሩ ስለ ነበር ይህ አደገኛ ነበር። የፈርዖንን ድንጋጌ ለመጣስ ሲሞክር የተገኘ ማንኛውም ሰው በሞት ሊቀጣ ይችላል። ልጁም መገደሉ አይቀርም። ታዲያ እነዚህ ለአምላክ ያደሩ ወላጆች የራሳቸውንም ሆነ የልጃቸውን ሕይወት ለማዳን ምን ያደርጉ ይሆን?
ዮኬቤድ ጥቂት የደንገል ዝንጣፊዎች ሰበሰበች። ደንገል በረግረግ አካባቢ የሚበቅል ጠንካራ ተክል ሲሆን ከቀርከሃ ጋር ይመሳሰላል፤ የጣት ያህል ውፍረት ያለው ባለ ሦስት ማዕዘን አገዳ አለው። እስከ 6 ሜትር ከፍታ ያህል ሊያድግ ይችላል። ግብፃውያን ይህን ተክል ወረቀት፣ ምንጣፍ፣ የመርከብ ሸራ፣ ነጠላ ጫማዎችና ቀላል ክብደት ያላቸው ጀልባዎች ለመሥራት ይጠቀሙበት ነበር።
ዮኬቤድ ልጅዋን ለመያዝ የሚችል ቅርጫት ከደንገል ሠራች። ከዚያም አገዳውን አንድ ላይ ለማያያዝና ውኃ እንዳያስገባ ቅርጫቱን ዝፈትና ቅጥራን ለቀለቀችው። ቀጥላም ልጅዋን ቅርጫቱ ውስጥ ከተተችውና ቅርጫቱን በአባይ ወንዝ ዳር በበቀለ መቃ መሃል አስቀመጠችው።— ዘጸአት 2:3
ሕፃኑ ተገኘ
ሚርያም የምትባለው የዮኬቤድ ልጅ የሚፈጸመውን ነገር ለማየት በአቅራቢያው ቆማ ነበር። ከዚያ የፈርዖን ልጅ ገላዋን ለመታጠብ ወደ አባይ ወንዝ መጣች።a ምናልባት ዮኬቤድ ልዕልቷ በዚህ አካባቢ እንደምታዘወትር ስለምታውቅ ቅርጫቱን በቀላሉ መታየት በሚችልበት ቦታ አስቀምጣው ይሆናል። ያም ሆነ ይህ የፈርዖን ልጅ በመቃው መካከል ተመቻችቶ የተቀመጠውን ቅርጫት ተመለከተችና አገልጋይዋን ጠርታ አስመጣችው። በቅርጫቱ ውስጥ አንድ የሚያለቅስ ልጅ ስታይ አዘነችለት። የዕብራውያን ልጅ መሆኑን ተገነዘበች። ሆኖም ይህን ውብ ሕፃን እንዴት ልታስገድለው ትችላለች? ከሰብዓዊ ደግነት በተጨማሪ በወቅቱ የነበረው አንድ ሰው ወደ ሰማይ ለመግባት በሕይወቱ የደግነት ተግባር መፈጸም አለበት የሚለው የግብፃውያን እምነት በፈርዖን ልጅ ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ ሊሆን ይችላል።b— ዘጸአት 2:5, 6
ሩቅ ሆና ሁኔታውን ትከታተል የነበረችው ሚርያም የፈርዖንን ልጅ ቀርባ አነጋገረቻት። “ሕፃኑን ታጠባልሽ ዘንድ ሄጄ የምታጠባ ሴት ከዕብራውያን ሴቶች ልጥራልሽን?” ስትል ጠየቀቻት። ልዕልቷ “ሂጂ” አለቻት። ሚርያም ሮጣ ወደ እናቷ ሄደች። ብዙም ሳይቆይ ዮኬቤድ በፈርዖን ልጅ ፊት ቀረበች። ልዕልቲቱ “ይህን ሕፃን ወስደሽ አጥቢልኝ፣ ዋጋሽንም እሰጥሻለሁ” አለቻት። በዚህ ጊዜ የፈርዖን ልጅ፣ ዮኬቤድ የሕፃኑ እናት መሆኗን ሳትገነዘብ አልቀረችም።— ዘጸአት 2:7-9
ዮኬቤድ ልጅዋን ጡት እስኪጥል ድረስ አሳደገችው።c ይህም እውነተኛ አምላክ ስለ ሆነው ስለ ይሖዋ እንድታስተምረው ጥሩ አጋጣሚዎችን ፈጥሮላታል። ከዚያም ዮኬቤድ ልጅዋን ወስዳ ለፈርዖን ልጅ ሰጠቻት፤ እሷም “ከውኃ አውጥቼዋለሁ” ብላ ሙሴ የሚል ስም አወጣችለት።— ዘጸአት 2:10
ለእኛ የሚሆን ትምህርት
ዓምራምና ዮኬቤድ ለልጃቸው የንጹሑን አምልኮ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማስተማር ባገኙት ጥቂት አጋጣሚ ሙሉ በሙሉ ተጠቅመዋል። በዛሬው ጊዜ ያሉ ወላጆች እንዲህ ማድረግ ይኖርባቸዋል። እንዲያውም ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩ ታዘዋል። ሰይጣን ዲያብሎስ “የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራል።” (1 ጴጥሮስ 5:8) ወደፊት የይሖዋ አገልጋዮች ለመሆን የሚችሉት ውድ ወጣት ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በእጁ ቢወድቁ ደስ ይለዋል። ሰይጣን ለለጋ ወጣቶች ፈጽሞ ርኅራኄ አያሳይም! ከዚህ አንፃር ብልህ ወላጆች ሕፃን ልጆቻቸውን እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን እንዲፈሩ ያስተምሯቸዋል።— ምሳሌ 22:6፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15
ዓምራምና ዮኬቤድ በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ልጃቸውን ለመሸሸግ ያደረጉት ሙከራ የእምነት እርምጃ እንደሆነ በዕብራውያን 11:23 ላይ ተገልጿል። እነዚህ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆች ልጃቸውን አሳልፈው ባለመስጠት በይሖዋ የማዳን ኃይል እንደሚተማመኑ አሳይተዋል። በዚህም ተባርከዋል። እኛም የይሖዋን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥብቅ መከተልና ይሖዋ በእኛ ላይ እንዲደርስ የሚፈቅደው ነገር ሁሉ ከጊዜ በኋላ ለዘላለማዊ ደህንነታችንና ደስታችን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ እርግጠኞች ልንሆን ይገባል።— ሮሜ 8:28
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ግብፃውያን የመራባት አምላክ ነው በማለት የአባይ ወንዝን ያመልኩ ነበር። ውኃው ፍሬያማ የሚያደርግ እንዲያውም ዕድሜ የሚያራዝም የመፈወስ ኃይል አለው ብለው ያምኑ ነበር።
b ግብፃውያን አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ መንፈሱ በኦሲረስ ፊት ቀርባ “አንድም ሰው አላሠቃየሁም፣” “ሕፃኑን የእናቱን ጡት አልከለከልኩም” እና “ለተራበ እንጀራ፣ ለተጠማ ደግሞ ውኃ ሰጥቻለሁ” ትላለች ብለው ያምኑ ነበር።
c በጥንት ዘመን ብዙ ልጆች በአሁኑ ጊዜ ከተለመደው በላይ ለብዙ ዓመታት ጡት ይጠቡ ነበር። ሳሙኤል ጡት ሲጥል ቢያንስ ሦስት ዓመት ሳይሆነው አይቀርም፤ ይስሐቅ ደግሞ ጡት የጣለው በአምስት ዓመቱ ገደማ ነበር።