‘ሃይማኖታቸው ከሚሰጣቸው ማሠልጠኛ ጋር ተስማምተው ይኖራሉ’
በሚያሚ፣ ፍሎሪዳ ዩ ኤስ ኤ የምትኖር አንዲት ሴት በከተማው እየታተመ ለሚወጣ አንድ ጋዜጣ የሚከተለውን ደብዳቤ ላከች:- “ታኅሣሥ 10 ቀን ልጄ ገበያ ላይ ሳለ የገንዘብ ቦርሳውን ሌባ ሰረቀው። በቦርሳው ውስጥ የመንጃ ፈቃድ፣ ከመንግሥት የገንዘብ ድጎማ የሚያገኝበት መታወቂያ ካርድና ሌሎች ነገሮች እንዲሁም 260 የአሜሪካ ዶላር ነበር።
“የጠፋበትን ንብረት ለሥራ አስኪያጁ ካመለከተ በኋላ ወደ ቤት መጣ። አመሻሹ ላይ የስፓንኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነች አንዲት ሴት ስልክ ደወለችለት። የገንዘብ ቦርሳውን እንዳገኘችው በስልክ ኦፕሬተር አስተርጓሚነት ነገረችው።
“አድራሻዋን ሰጠችው። . . . 260 የአሜሪካ ዶላሩን ጨምሮ ምንም ሳይጎድል የገንዘብ ቦርሳውን እንዳለ ሰጠችው።
“ሌባው የገንዘብ ቦርሳውን ከኪሱ ሲሰርቅ አይታው ጮኸች። ሌባው የገንዘብ ቦርሳውን ጥሎ ሮጠ። በዚህ ጊዜ ልጄን ማግኘት ስላልቻለች ቦርሳውን ወደ ቤቷ ወሰደችና ስልክ ደወለች።
“እርሷና ቤተሰቦቿ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። ሃይማኖታቸው ከሚሰጣቸው ማሠልጠኛ ጋር ተስማምተው እንደሚኖሩ ግልጽ ነው።”
የይሖዋ ምሥክሮች ሐቀኝነትን የሚያሳዩት ከሰዎች ውዳሴ ለማግኘት ሲሉ አይደለም። (ኤፌሶን 6:7) ከዚህ ይልቅ ለሰማዩ አባታቸው ለይሖዋ ውዳሴ ለማምጣት ከልብ ይጥራሉ። (1 ቆሮንቶስ 10:31) ለአምላክና ለጎረቤቶቻቸው ያላቸው ፍቅር ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን ‘ምሥራች’ እንዲያውጁ ይገፋፋቸዋል። (ማቴዎስ 24:14) አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት ምድርን ውብ ገነት እንደሚያደርጋት ቃል ገብቷል። በዚያን ጊዜ ምድር ውበትን ከመላበሷም በላይ ሐቀኝነት ለዘላለም የሚሰፍንባትና ጥሩ ሥነ ምግባር የሚንጸባረቅባት ቦታ ትሆናለች።— ዕብራውያን 13:18፤ 2 ጴጥሮስ 3:13