የአንባብያን ጥያቄዎች
በ14ኛው መቶ ዘመን ይኖር በነበረው ሼም-ቶብ ቤን አይሲክ ኢበን ሻፕሩት ተብሎ በሚጠራው አይሁዳዊ ሐኪም በተገለበጠው በዕብራይስጡ የማቴዎስ ጽሑፍ ውስጥ ቴትራግራማተን (የአምላክን ስም የሚወክሉት አራት የዕብራይስጥ ፊደላት) ይገኛሉን?
አይገኙም። ይሁን እንጂ በነሐሴ 15, 1996 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 13 ላይ በተገለጸው መሠረት ይህ የማቴዎስ ጽሑፍ ሃሽ.ሼም የተባለውን (በቀጥታ የተጻፈ ወይም በምህፃረ ቃል የተቀመጠ) ቃል 19 ጊዜ ይጠቀማል።
ሃሽ.ሼም የተባለው የዕብራይስጥ ቃል “ስሙ” ማለት ሲሆን መለኮታዊውን ስም ለማመልከት የገባ ነው። ለምሳሌ ያህል በሼም-ቶብ ጽሑፍ ውስጥ ማቴዎስ ከኢሳይያስ 40:3 ላይ የጠቀሰው ምንባብ በሚገኝበት በማቴዎስ 3:3 ላይ ሃሽ.ሼም የሚለው ቃል በምህፃረ ቃል ተቀምጧል። ማቴዎስ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ቴትራግራማተን የሚገኙበትን ጥቅስ በሚጠቅስበት ጊዜ መለኮታዊውንም ስም በወንጌሉ ውስጥ አስፍሯል ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው። ስለዚህ በሼም-ቶብ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው የዕብራይስጥ ጽሑፍ ቴትራግራማተንን የማይጠቀም ቢሆንም እንኳ በማቴዎስ 3:3 ላይ “ስሙ” የሚለውን ቃል መጠቀሙ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “ይሖዋ” የሚለውን ስም መጠቀምን የሚደግፍ ነው።
ሼም-ቶብ የዕብራይስጡን ጽሑፍ የገለበጠው አንድን እምነት በመተቸት በጻፈው ኢቨን ቦቻን ተብሎ በሚጠራው መጽሐፉ ውስጥ ነው። ይሁን እንጂ የዚህ የዕብራይስጥ ጽሑፍ ምንጭ ምንድን ነው? በዚህ ጉዳይ ላይ ጥልቅ ምርምር ያደረጉት ፕሮፌሰር ጆርጅ ሀዋርድ “ሼም-ቶብ የገለበጠው የዕብራይስጡ የማቴዎስ ጽሑፍ የተጻፈው በክርስትና ታሪክ የመጀመሪያ አራት መቶ ዘመናት መካከል በሆነ ወቅት ላይ ነው” ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።a በዚህ ላይ ሌሎች ከፕሮፌሰሩ አስተያየት ጋር አይስማሙ ይሆናል።
ሀዋርድ “በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው የዕብራይስጡ የማቴዎስ ጽሑፍ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ታቅፎ ከሚገኘው በግሪክኛ ከተጻፈው የማቴዎስ ጽሑፍ ጋር ብዙ ልዩነት አለው” ሲሉ ተናግረዋል። ለምሳሌ ያህል በሼም-ቶብ ጽሑፍ መሠረት ኢየሱስ ስለ ዮሐንስ ሲናገር “እውነት እላችኋለሁ፣ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም” ብሏል። ኢየሱስ በመቀጠል የተናገራቸውን የሚከተሉትን ቃላት ግን አውጥቷቸዋል:- “በመንግሥተ ሰማያት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል።” (ማቴዎስ 11:11) ሆኖም ልክ እንደዚሁ በአሁኑ ጊዜ በእጅ የሚገኙትን የጥንቶቹን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችና የግሪክኛውን የሰፕቱጀንት ትርጉም ስናነጻጽር ብዙ የአገላለጽ ልዩነቶች እናገኛለን። እንዲህ ዓይነት ልዩነቶች እንዳሉ ብናምንም እንኳ እነዚህ ጥንታዊ ጽሑፎች የተለያዩ መጻሕፍትን እርስ በርስ ለማነጻጸር መሣሪያ ሆነው ያገለግላሉ።
ከላይ እንደተገለጸው ሼም-ቶብ የገለበጠው የማቴዎስ ጽሑፍ ማቴዎስ ቴትራግራማተንን ተጠቅሟል ብሎ ለማመን የሚያስችል በቂ ምክንያት ባላቸው ቦታዎች ላይ “ስሙ” የሚለውን ቃል አስገብቷል። በዚህም ምክንያት ከ1950 አንስቶ የሼም-ቶብ ጽሑፍ መለኮታዊውን ስም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ለመጠቀም የሚያስችል ድጋፍ ሆኖ ሲሠራበት ቆይቷል፤ አሁንም ቢሆን በባለ ማጣቀሻው የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ውስጥ ተጠቅሶ ይገኛል።b
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በተጨማሪም ጥር 1997 የታተመውን ኒው ቴስታመንት ስተዲስ የተባለውን መጽሔት ጥራዝ 43 ቁጥር 1 ገጽ 58-71 ተመልከት።
b በ1984 ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።