በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ደስተኛ ሆኖ መቀጠል የሚቻልበት መንገድ
አምላክ የለሽ በሆነው በዚህ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች ላይ እንደምንኖር የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ በግልጽ ያሳያል። የይሖዋ አምላክ አገልጋዮች ይህን በመገንዘባቸው አቅማቸው የፈቀደላቸውን ያህል የመንግሥቱን ምሥራች በማሰራጨት ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ። ከ600,000 በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል እንዲችሉ ሁኔታዎቻቸውን አመቻችተዋል። ከእነዚህም መካከል የተወሰኑት አቅኚ ተብለው የሚጠሩ የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ናቸው። ሌሎች ደግሞ በቤቴል ፈቃደኛ አገልጋዮች በመሆን በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት ወይም በቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ ይሠራሉ። ሚስዮናውያንና ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሆነው የሚያገለግሉም አሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው ቀን ‘የሚያስጨንቅ ዘመን’ እንደሚሆን ይናገራል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) የግሪክኛው መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥቅስ “ክፉ የሆኑ የተወሰኑ ዘመናት” የሚል አገላለጽ ይጠቀማል። ስለዚህ ዛሬ ማንም ሰው ከችግር ነፃ የሆነ ሕይወት እንዲኖረው መጠበቅ አይኖርበትም። አንዳንድ ክርስቲያን አገልጋዮች እነዚህ ችግሮች በጣም ከባድ ሆነው ስለሚታዩአቸው ‘በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ልቀጥል እችላለሁ ወይስ ባቆም ይሻላል?’ በማለት ራሳቸውን ይጠይቃሉ።
አንድ ሰው አቅኚ፣ በቤቴል የሚያገለግል ፈቃደኛ ሠራተኛ፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ወይም ሚስዮናዊ ሆኖ በማገልገል ለመቀጠል ይችል ወይም አይችል እንደሆነ ሁኔታውን እንደገና እንዲመረምር የሚያደርጉት ምክንያቶች ምንድን ናቸው? ምናልባት ከባድ የሆነ የጤና መታወክ ያጋጥመው ይሆናል። የማያቋርጥ እንክብካቤ የሚፈልግ በዕድሜ የገፋ ወይም አቅመ ደካማ የሆነ ዘመድ ይኖር ይሆናል። ባልና ሚስት የሆኑ ደግሞ ልጅ ወልደው ይሆናል። አንድ ሰው በእነዚህና በሌሎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታዎች ምክንያት የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ለማቋረጥ ቢወስን ይህን የመሰለ እርምጃ በመውሰዱ ሊያፍርበት አይገባም።
ይሁን እንጂ አንድ ሰው ደስታ ስላጣበት ብቻ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ለማቆም ቢያስብስ? ምናልባት አንድ አቅኚ ከአገልግሎቱ የሚያገኘው ምላሽ አነስተኛ በመሆኑ ‘ለመልእክቱ ጆሯቸውን የሚሰጡ ሰዎች ጥቂት ሆነው ሳለ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ ሕይወት የምመራው ለምንድን ነው?’ በማለት ሊጠይቅ ይችላል። ምናልባት በቤቴል የሚያገለግል አንድ ወንድም በተሰጠው የሥራ ምድብ ደስተኛ ላይሆን ይችላል። ወይም የሚነዘንዝ ሕመም አንድን ሰው አቅኚ ሆኖ እንዳያገለግል ባያግደውም ደስታውን ግን ሊያሳጣው ይችላል። እንደነዚህ ያሉ ግለሰቦች ደስታቸውን ጠብቀው ለመቆየት የሚችሉት እንዴት ነው? ተሞክሮ ያላቸው አንዳንድ አገልጋዮች የሰጡትን ሐሳብ እስቲ እንመልከት።
ቅር የሚያሰኙ ሁኔታዎችን መቋቋም
ከስዊዘርላንድ የመጣችው አኒ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ ጊልያድ ትምህርት ቤት ገብታ ሥልጠና የወሰደችው በ1950 ነበር። ከአውሮፓ ውጪ በሚገኝ አንድ አገር ተመድባ በሚስዮናዊነት ለማገልገል ጓጉታ ነበር። አኒ በአውሮፓ በሚገኝ ቤቴል ውስጥ እንድትሠራ ስትመደብ ቅር ተሰኘች። ይሁን እንጂ እንድትሠራ የተሰጣትን ምድብ በመቀበል እስካሁን ድረስ በዚያው በትርጉም ክፍል ውስጥ በመሥራት ላይ ትገኛለች። ቅር የተሰኘችበትን ሁኔታ ልትቋቋም የቻለችው እንዴት ነው? አኒ ስትመልስ “ብዙ የሚሠራ ሥራ ነበረ፣ አሁንም አለ። የእኔ ስሜቶችና ምርጫዎች የሥራውን ያህል አስፈላጊ አይደሉም” ብላለች።
በተሰጠን የሥራ ምድብ ደስተኞች ካልሆንን ምናልባት የአኒን ዓይነት አመለካከት ልናዳብር እንችላለን። የግል ምርጫችን ከሁሉ ይበልጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር አይደለም። ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ከመንግሥቱ መልእክት መሰራጨት ጋር የተያያዙ የተለያዩ ኃላፊነቶችን ሁሉ በሚገባ መወጣት ነው። ምሳሌ 14:23 “በድካም ሁሉ ልምላሜ ይገኛል” በማለት ይናገራል። በየትኛውም የሥራ መስክ ላይ ብንመደብ ታማኝ በመሆን ሥራውን መፈጸማችን ለመንግሥቱ ሥራ መከናወን አስተዋጽኦ ያበረክታል። እንዲሁም አምላክ ከሰጠን ከእንዲህ ዓይነቱ ሥራ ትልቅ እርካታ ልናገኝ እንችላለን። አዎን፣ ደስታ ማግኘት እንችላለን።—ከ1 ቆሮንቶስ 12:18, 27, 28 ጋር አወዳድር።
ከሌሎች ጋር ተስማምቶ መኖር
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ማለትም በመስክ፣ በቤቴል፣ በሚስዮናውያን መኖሪያ ቤት ወይም ተጓዥ የበላይ ተመልካች በመሆን ከአንድ ጉባኤ ወደ ሌላ ጉባኤ በመዘዋወር በምንጎበኝበት ወቅት ከሁሉም ዓይነት ሰዎች ጋር በቅርብ እንገናኛለን። ስለዚህ ደስታ ከሌሎች ጋር ተስማምተን በመኖራችን ላይ በእጅጉ የተመካ ነው። ይሁን እንጂ ስለ እነዚህ የመጨረሻ ቀኖች የተነገሩት ‘ክፉ ዘመናት’ በሰዎች ግንኙነት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ አሳድረዋል። አንድ የአምላክ አገልጋይ አንድ ሰው የሚያበሳጭ ነገር ቢያደርግበትም እንኳ ደስታውን ላለማጣት ምን ሊያደርግ ይችላል? ምናልባት ከቪልሄልም አንድ ነገር ልንማር እንችላለን።
ቪልሄልም አውሮፓ በሚገኝ በአንድ የቤቴል ቤተሰብ ውስጥ አባል የሆነው በ1947 ነበር። ከዚያ በኋላ በአቅኚነት ሥራና ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ በማገልገል ብዙ ጊዜ አሳልፏል። “እኔና ባለቤቴ ትክክል አይደሉም ብለን የምናስባቸው ወይም የሚያበሳጩ ነገሮች ሲያጋጥሙን ስለ ጉዳዩ እንዴት እንደሚሰማን ለይሖዋ እንነግረውና መፍትሔ እንዲሰጥ ለእሱ እንተውለታለን” በማለት ቪልሄልም ተናግሯል።—መዝሙር 37:5
ምናልባት አንተንም አንድ መሰል ክርስቲያን አክብሮት ወይም አሳቢነት የጎደለው ቃል በመናገር አስቀይሞህ ያውቅ ይሆናል። ሁላችንም በአንደበታችን ብዙ ጊዜ እንደምንሳሳት አስታውስ። (ያዕቆብ 3:2) ስለዚህ ይህን ሁኔታ ‘ጸሎት ሰሚ’ ወደሆነው አምላክ ይበልጥ ለመቅረብ ለምን አትጠቀምበትም? (መዝሙር 65:2) ለይሖዋ ስለጉዳዩ ከነገርከው በኋላ በእሱ ላይ ጣለው። አምላክ ለውጥ እንዲደረግ ከፈለገ ያደርገዋል። በሚስዮናውያን መኖሪያ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ወንድሞች ይህን አመለካከት በአእምሯቸው ማኖራቸው ተመሳሳይ የሆኑ ችግሮች ቢነሱ በይሖዋ አገልግሎት ደስተኞች ሆነው እንዲቀጥሉ ይረዳቸዋል።
ጤንነት በሚታወክበት ጊዜ
የጤንነት ችግር የሌለባቸው ሰዎች የሉም ለማለት ይቻላል። ሌላው ቀርቶ ገና በወጣትነት ዕድሜ ላይ አሉ የሚባሉት እንኳ በመንፈስ ጭንቀት ወይም በበሽታ ሊሰቃዩ ይችላሉ። አንዳንዶች ጤናቸው በመታወኩ ምክንያት የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ቢያቆሙም ከዚያ በኋላ የመንግሥቱ አስፋፊዎች በመሆን በጣም ጥሩ ሥራ ያከናውናሉ። ይሁን እንጂ ሌሎች ጤንነታቸው የተቃወሰ ቢሆንም እንኳ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመቀጠል ችለዋል። ለምሳሌ ሃርትሙትንና ጂስሊንድን ተመልከት።
ሃርትሙትና ጂስሊንድ ባልና ሚስት ሲሆኑ በአቅኚነት፣ በሚስዮናዊነትና በተጓዥነት ሥራ 30 ዓመታት ያህል አሳልፈዋል። ሁለቱም አልፎ አልፎ በአካልም ሆነ በስሜት ጉዳት ላይ የጣሏቸው ከባድ ሕመሞች ተፈራርቀውባቸዋል። የሆኖ ሆኖ በጣም ጥሩ የሆነ ሥራ ለመሥራትና ተመሳሳይ በሆነ ፈተና ሥር ያሉትን ለማበረታታት ችለዋል። ምን ምክር ይሰጡ ይሆን? “የወደፊቱን እንጂ ያለፈውን አትመልከቱ። እያንዳንዱን አጋጣሚ ከሁሉ በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት። እያንዳንዱ ቀን ይሖዋን ለማወደስ የሚያስችል አንድ አጋጣሚ ሊያመጣ ይችላል። ያንን አጋጣሚ ተጠቀሙበት፤ እንዲሁም አጋጣሚውን በማግኘታችሁ ደስ ይበላችሁ።”
የሀንለርን ሁኔታ ተመልከት። በአቅኚነት፣ በሚስዮናዊነት፣ ከባሏ ጋር በመሆን በተጓዥነት ሥራና በቤቴል አገልግሎት ባሳለፈቻቸው 30 ዓመታት በየጊዜው በሚቀሰቀስባት ሕመም ምክንያት ትቸገር ነበር። ሀንለር እንዲህ ብላለች:- “ሰይጣን የሰው ልጆች ይሖዋን የሚያገለግሉት ሲመቻቸው ብቻ ነው በማለት ያስነሳውን ክርክር ሁልጊዜ አስታውሳለሁ። ፈተናዎችን በመቋቋም ሰይጣን ሐሰተኛ መሆኑን በማጋለጥ በኩል የድርሻዬን ላበረክት እችላለሁ።” ይህ ጠንካራ ምክንያት ሊሆነን ይችላል። በፈተና ሥር በምትሆኑበት ጊዜ ይሖዋ በግላችሁ ታማኝነታችሁን እንድታሳዩት እንደሚፈልግ አትዘንጉ።—ኢዮብ 1:8-12፤ ምሳሌ 27:11
ጤንነትህን በተመለከተ ሚዛናዊ ውሳኔ ለማድረግ እንዲያስችልህ ኢየሱስ ክርስቶስ የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያን አስመልክቶ የተናገረውን የሚከተለውን ሁለት ገጽታ ያለውን ትንቢት ተመልከት። ኢየሱስ በልዩ ልዩ ሥፍራ ቸነፈር ይሆናል በማለት ተናግሯል። በተጨማሪም “ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:3, 14፤ ሉቃስ 21:11) ኢየሱስ በመጨረሻው ዘመን ተከታዮቹ ከበሽታ ጋር እንደሚታገሉ ያውቅ ነበር። ይሁን እንጂ የስብከቱ ሥራ የተሻለ ጤንነት ባላቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆን በከባድ ሕመም በሚሰቃዩ ግለሰቦችም ጭምር እንደሚሠራ ተገንዝቦ ነበር። የጤና መታወክ ቢኖርብንም እንኳ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመቀጠል ከቻልን ይሖዋ ለስሙ ያሳየነውን ፍቅር አይረሳም።—ዕብራውያን 6:10
ሰዎች ግድየለሽ ቢሆኑም ደስታን ጠብቆ መኖር
ሰዎች ለመንግሥቱ ስብከት ሥራ የሚሰጡት ምላሽ አመለካከታችንን ሊነካ ይችላል። ተሞክሮ ያለው አንድ አገልጋይ “ሌላው ቀርቶ አቅኚዎች እንኳ ከአንድ የቤት ባለቤት ጋር ውይይት ለመክፈት ይቸገራሉ” ሲል ተናግሯል። “ሁላችንም ደስታችንን ጠብቀን ለመቀጠል መታገል ይኖርብናል።” አዎን፣ ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት ግድየለሽ መሆናቸው በመስክ አገልግሎት ላይ የምናገኘውን ደስታ ሊቀንስብን ይችላል። ስለዚህ ብዙውን ጊዜ ለመልእክቱ ግድየለሽ የሆኑ ሰዎች የሚያጋጥሙት አንድ አቅኚ ደስታውን ጠብቆ ለመቀጠል የሚችለው እንዴት ነው? ተሞክሮ ያላቸው አገልጋዮች የሚከተሉትን የተሞከሩና በተግባር የተፈተኑ ሐሳቦች ያቀርባሉ።
የሰዎች ግድየለሽነት ራሱን የቻለ ፈተና ቢሆንም እጅ መስጠት አይኖርብንም። የሰዎች ግድየለሽነት እየጨመረ መሄዱ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ለማቆም ምክንያት አይሆንም። ቅዱሳን ጽሑፎችን በጥልቀት ለማጥናት በቂ ጊዜ የምንመድብ ከሆነ ሰዎች ግድየለሽ ቢሆኑም ደስታችንን ጠብቀን ለመቆየት እንችላለን። ቅዱሳን ጽሑፎች ‘ለበጎ ሥራ ሁሉ ያስታጥቁናል።’ ይህ ደግሞ ለምሥራቹ ጆሮ አንሰጥም ለሚሉ ሰዎች መናገርን ይጨምራል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ሰዎች ለመስማት አለመፈለጋቸው ነቢዩ ኤርምያስን እንዳይናገር አልገታውም። (ኤርምያስ 7:27) መጽሐፍ ቅዱስን በክርስቲያናዊ ጽሑፎች ረዳትነት በምናጠናበት ጊዜ እምነታችንን ሊያጠነክሩልንና ግድየለሽነትን እንድንቋቋም ሊረዱን የሚችሉ ነጥቦችን ካስተዋልን በእጅጉ ልንጠቀም እንችላለን።
የሰዎች ግድየለሽነት አንድ ራሱን የቻለ ፈተና መሆኑን ተቀብለን እስቲ ለምንሰብክላቸው ሰዎች ያለንን አመለካከት እንመርምር። ግድየለሾች የሆኑት ለምንድን ነው? በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች ውስጥ ለተስፋፋው ግድየለሽነት አንዱ ምክንያት የሐሰት ሃይማኖት ያስመዘገበው አሳዛኝ የሆነ ታሪክ በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው። ሰዎች ሃይማኖት በሕይወት ውስጥ ቦታ ሊኖረው የሚገባ ነገር እንደሆነ አድርገው ማሰብ ከማቆማቸውም በላይ ከሃይማኖት ጋር ምንም ግንኙነት እንዲኖራቸው አይፈልጉም። እንደ ሁኔታው ለውጥ በማድረግ ሰዎችን ስለሚያሳስቧቸው ነገሮች ማለትም ስለ ሥራ ማጣት፣ ስለ ጤንነት፣ ስለ ወንጀል፣ መቻቻል ስለመጥፋቱ፣ ስለ ከባቢ ሁኔታ ስለ ጦርነት ስጋት ልናነጋግራቸው ይገባል።
አንድን የቤት ባለቤት ለማነጋገር በምንጠቀምባቸው የመክፈቻ ቃላት ላይ በአካባቢው ስለሚገኝ አንድ የሚስብ ነገር መጥቀስ እንችላለን። ዲትማር የተባለ አንድ ወንድም እምብዛም ውጤት ባላገኘበት አንድ መንደር ውስጥ በሚሰብክበት ጊዜ ለማድረግ የሞከረው ይህንን ነበር። በአካባቢው የሚኖር አንድ ሰው በመንደሩ ውስጥ ከአንድ ቀን በፊት አንድ አሳዛኝ ነገር ተፈጽሞ እንደነበር ገለጸ። ዲትማር ከዚያ ቀጥሎ በሄደባቸው ቤቶች ውስጥ ላገኛቸው ሰዎች በሙሉ ተከስቶ በነበረው አሳዛኝ ሁኔታ የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገለጸ። “ሰዎቹ ወዲያውኑ መወያየት ጀመሩ” በማለት ተናገረ። “የተከሰተው አሳዛኝ ሁኔታ በእያንዳንዱ ሰው አእምሮ ውስጥ ነበር። ሕይወታቸውን በሚነኩ ጉዳዮች ላይ ፍላጎት በማሳየቴ ምክንያት በዚያን ዕለት ብዙ አስደሳች የሆነ ውይይት ለማድረግ ችያለሁ።”
ሰዎችን በምናገኝበት በማንኛውም ቦታ ስለ መንግሥቱ ልንመሰክርላቸው ይገባል። መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ፍሬያማ ሊሆን ስለሚችል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች በሚሰጧቸው ሐሳቦች ራሳችንን ለዚህ ሥራ ልናሰለጥን እንችላለን። ለአንድ የቤት ባለቤት ጥቂት ወዳጃዊ ቃላትን መናገር ወይም የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት ቅጂዎችን ማበርከት ደስታ ሊያመጣ ይችላል። ፍላጎት ላሳየ አንድ ሰው ተመላልሶ መጠየቅ አድርገን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት ከጀመርን የምናስጠናውን ሰው “መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የሚፈልግ ሌላ ሰው ታውቃለህ?” ብለን ልንጠይቀው እንችላለን። ይህ ሌላ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሊያስገኝልን ይችላል። በማንኛውም ሁኔታ አዎንታዊ አመለካከት እንያዝ፣ በጸሎት በይሖዋ ላይ እንደገፍ፣ የሰዎች ግድየለሽነት ተስፋ እንዲያስቆርጠን አንፍቀድ።
ከሌሎች የሚገኝ ማበረታቻ
ዮርገን እና ክርስቲያን ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት በአቅኚነትና በተጓዥነት ሥራ አገልግለዋል። አንድ ወቅት አብዛኞቹ ሰዎች ግድየለሾችና ግትሮች በሆኑበት አንድ አካባቢ እንዲሰብኩ ተመድበው ነበር። ዮርገንና ሚስቱ ማበረታቻ ማግኘት በጣም አስፈልጓቸው ነበር! ሆኖም በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ወንድሞች እንደጠበቁት አላበረታቷቸውም።
ስለዚህ ዮርገን “አንዳንድ አቅኚዎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዳሉባቸውና ከሽማግሌዎችና ከሌሎች አስፋፊዎች የበለጠ ማበረታቻ እንደሚያስፈልጋቸው” ከተሞክሮው አውቋል። ሙሴ ኢያሱን እንዲያበረታውና እንዲያጠነክረው አምላክ ነግሮት ነበር። (ዘዳግም 3:26-28) እንዲሁም ክርስቲያኖች አንዳቸው ለሌላው የብርታት ምንጭ ሊሆኑ ይገባቸዋል። (ሮሜ 1:11, 12) የመንግሥቱ አስፋፊዎች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ላይ የሚገኙትን ወንድሞች በሚገነቡ ቃላት በመናገርና ከጊዜ ወደ ጊዜ አብረዋቸው በማገልገል ሊያበረታቷቸው ይችላሉ።
የይሖዋ ደስታ ምሽጋችን ነው
አብዛኛውን የሕይወታቸውን ክፍል አቅኚ ወይም ሚስዮናዊ በመሆን፣ በቤቴል ውስጥ በማገልገል ወይም በተጓዥነት ሥራ ጉባኤዎችን በመጎብኘት ያሳለፉ ክርስቲያኖች ብዙዎቹ ችግሮች የሚቆዩት ለአጭር ጊዜ እንደሆነና ጥቂቶቹ ግን ለረዥም ጊዜ እንደሚቆዩ አረጋግጠዋል። ጭራሽ የማይለቁ የሚመስሉት ጥቂት ችግሮች እንኳ ደስታችንን ሊነጥቁን አይገባም። ከ45 ዓመታት በላይ በባዕድ አገር ሲያገለግል የቆየው ራመን ችግሮች በሐዘን እንድንዋጥ ሲያደርጉን “ስላሉን ብዙ በረከቶችና ከዚህ የከፋ ችግር ስለሚደርስባቸው በሺህ የሚቆጠሩ ሌሎች ወንድሞች ማሰብ ይኖርብናል” በማለት ሐሳብ ሰጥቷል። በእርግጥ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የእምነት አጋሮቻችን መከራዎች እየደረሱባቸው ቢሆንም ይሖዋ ስለ ሁላችንም እንደሚያስብ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።—1 ጴጥሮስ 5:6-9
ስለዚህ የግል ሁኔታችን የሚፈቅድልን ከሆነ በሰማዩ አባታችን ላይ በመመካት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመካፈልና የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ሆነን በመቀጠል ደስታችንን ጠብቀን እንኑር። እሱ አገልጋዮቹን ያጠነክራል። እንዲሁም ሁላችንም ‘የይሖዋ ደስታ ምሽጋችን’ እንደሆነ አንዘንጋ።—ነህምያ 8:10
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“የእኔ ስሜቶችና ምርጫዎች የሥራውን ያህል አስፈላጊ አይደሉም”
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“እንዴት እንደሚሰማን ለይሖዋ እንነግረውና መፍትሔ እንዲሰጥ ለእሱ እንተውለታለን”
[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
“እያንዳንዱን አጋጣሚ ከሁሉ በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት። እያንዳንዱ ቀን ይሖዋን ለማወደስ የሚያስችል አንድ አጋጣሚ ሊያመጣ ይችላል”
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ፈተናዎችን በመቋቋም ሰይጣን ሐሰተኛ መሆኑን በማጋለጥ በኩል የድርሻዬን ላበረክት እችላለሁ”
[በገጽ 24 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
“አንዳንድ አቅኚዎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች አሉባቸው። ከሽማግሌዎችና ከሌሎች አስፋፊዎች የበለጠ ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል”
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ስላሉን ብዙ በረከቶች ማሰብ ይኖርብናል”