የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w97 12/1 ገጽ 10-14
  • ይሖዋ፣ “ይቅር ለማለት ዝግጁ” የሆነ አምላክ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋ፣ “ይቅር ለማለት ዝግጁ” የሆነ አምላክ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ይሖዋ “ይቅር ለማለት ዝግጁ” የሆነው ለምንድን ነው?
  • የይሖዋ ይቅር ባይነት ምን ያህል ፍጹም ነው?
  • “ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብም”
  • የሠራነው ኃጢአት ስለሚያስከትለው ውጤት ምን ማለት ይቻላል?
  • ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ የሆነ አምላክ
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
  • ይሖዋ ይቅር እንዳለህ አምነህ ተቀበል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ይቅር ማለትና መርሳት የሚቻለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—1995
  • የይሖዋ ይቅርታ ለአንተ ምን ትርጉም አለው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
w97 12/1 ገጽ 10-14

ይሖዋ፣ “ይቅር ለማለት ዝግጁ” የሆነ አምላክ

“አቤቱ አንተ መሓሪና ይቅር ባይ [“ይቅር ለማለት ዝግጁ፣” NW] ነህ።”​—⁠መዝሙር 86:​5

1. ንጉሥ ዳዊት ምን ከባድ ሸክም ተሸክሞ ነበር? የታወከው ልቡ የተጽናናው እንዴት ነበር?

በጥንቷ እስራኤል ዘመን የኖረው ንጉሥ ዳዊት የጥፋተኛነት ስሜት ምን ያህል ከባድ ሸክም ሊሆን እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ኃጢአቴ በራሴ ላይ ከፍ ከፍ ብሎአልና፣ እንደ ከባድ ሸክምም በላዬ ከብዶአልና። ታመምሁ እጅግም ተቸገርሁ፣ ከልቤ ውዝዋዜም የተነሣ ጮኽሁ።” (መዝሙር 38:​4, 8) ይሁን እንጂ የታወከውን የዳዊት ልብ ያጽናናለት ነገር ነበር። ይሖዋ ኃጢአትን ቢጠላም ኃጢአተኛው ከልቡ ንስሐ እስከገባና የኃጢአት ጎዳናውን እስከተወ ድረስ እርሱን እንደማይጠላ ያውቅ ነበር። (መዝሙር 32:​5፤ 103:​3) ዳዊት፣ ይሖዋ ንስሐ ለሚገቡ ሰዎች ምሕረት ለማሳየት ፈቃደኛ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ ያምን ስለነበር “አቤቱ አንተ መሐሪና ይቅር ባይ [“ይቅር ለማለት ዝግጁ፣” NW] ነህ” ብሏል።​—⁠መዝሙር 86:​5

2, 3. (ሀ) ኃጢአት በመሥራታችን ምክንያት ምን ዓይነት ሸክም ሊጫነን ይችላል? ይህስ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በጥፋተኛነት ስሜት “መዋጥ” ምን አደገኛ ሁኔታ ሊያስከትል ይችላል? (ሐ) ይሖዋ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ስለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ማረጋገጫ ይሰጠናል?

2 እኛም ብንሆን ኃጢአት ስንሠራ የሚሰማን የሕሊና ስቃይ የሚደቁስ ሸክም ሊሆንብን ይችላል። ይህ የጸጸት ስሜት እንግዳ ነገር አይደለም፤ እንዲያውም አስፈላጊ ነው። ስህተቶቻችንን ለማረም አዎንታዊ እርምጃዎች እንድንወስድ ያንቀሳቅሰናል። ይሁንና አንዳንድ ክርስቲያኖች ከልክ በላይ በጥፋተኝነት ስሜት ተውጠዋል። ራሱን የሚኮንነው ልባቸው ምንም ያህል ንስሐ ብትገባ አምላክ ሙሉ በሙሉ ይቅር አይልህም እያለ ይወተውታቸው ይሆናል። አንዲት እህት የፈጸመችውን ስህተት መለስ ብላ በማስታወስ “ይሖዋ ከእንግዲህ ላይወደኝ ይችላል የሚለው ሐሳብ የሚያሳድርባችሁ ስሜት በጣም የሚረብሽ ነው” ብላለች። ንስሐ ከገባችና ከጉባኤ ሽማግሌዎች ጠቃሚ ምክር ካገኘችም በኋላ እንኳ አምላክ ይቅር ሊለኝ የሚገባኝ ሰው አይደለሁም የሚል ስሜት ነበራት። “ይሖዋ ይቅር እንዲለኝ ሳልጸልይ የቀረሁበት አንድም ቀን የለም” ስትል ተናግራለች። በጥፋተኛነት ስሜት ‘ከተዋጥን’ ሰይጣን ይሖዋን ለማገልገል እንደማንበቃ በማሰብ ተስፋ ቆርጠን እጃችንን እንድንሰጥ ሊያደርገን ይሞክር ይሆናል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 2:​5-7, 11

3 ይሁን እንጂ የይሖዋ አመለካከት ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው! ከልባችን እውነተኛ ንስሐ ከገባን እርሱ ይቅር ሊለን ፈቃደኛ እንደሆነ ቃሉ ማረጋገጫ ይሰጠናል። አዎን፣ ይሖዋ እኛን ይቅር ለማለት ዝግጁ ነው። (ምሳሌ 28:​13) በመሆኑም የአምላክን ይቅርታ ማግኘት እንደማትችል ሆኖ ከተሰማህ ምናልባት ይሖዋ ይቅር የሚለው ለምንና እንዴት እንደሆነ የተሻለ ግንዛቤ ማግኘት ያስፈልግህ ይሆናል።

ይሖዋ “ይቅር ለማለት ዝግጁ” የሆነው ለምንድን ነው?

4. ይሖዋ ስለ ተፈጥሮአችን ምን ነገር ያስታውሳል? ይህስ ከእኛ ጋር ባለው ግንኙነት ረገድ ምን ውጤት ይኖረዋል?

4 እንዲህ እናነባለን:- “ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ እንዲሁ ኃጢአታችንን ከእኛ አራቀ። አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራል።” ይሖዋ ምሕረት ወደማሳየት የሚያዘነብለው ለምንድን ነው? የሚቀጥለው ቁጥር “ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና፤ አቤቱ፣ እኛ አፈር እንደ ሆንን አስብ” በማለት መልሱን ይሰጠናል። (መዝሙር 103:​12-14) አዎን፣ ይሖዋ ከአፈር የተሠራን ፍጥረታት መሆናችንንና በአለፍጽምና ምክንያት ድካምና ጉድለት እንደወረስን አይዘነጋም። “ፍጥረታችንን” እርሱ ያውቃል የሚለው አነጋገር መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን ከሸክላ ሠሪ ጋር እኛን ደግሞ እርሱ ከሚሠራቸው የሸክላ ዕቃዎች ጋር በማመሳሰል የሚሰጠውን መግለጫ ያስታውሰናል።a (ኤርምያስ 18:​2-6) አንድ ሸክላ ሠሪ የሸክላ ባሕርይ ምን እንደሆነ ስለሚያውቅ የሸክላ ዕቃዎቹን ጥብቅ አድርጎ ግን በጥንቃቄ ይይዛቸዋል። በመሆኑም ታላቁ ሸክላ ሠሪ ይሖዋም ኃጢአተኛ የሆነው ተፈጥሮአችን ያለበትን ድክመት ግምት ውስጥ በማስገባት እንደ አቅማችን ይይዘናል።​—⁠ከ2 ቆሮንቶስ 4:​7 ጋር አወዳድር።

5. የሮሜ መጽሐፍ ኃጢአት በውዳቂው ሥጋችን ላይ ያለውን ብርቱ ኃይል እንዴት አድርጎ ይገልጸዋል?

5 ይሖዋ ኃጢአት ምን ያህል ኃይል እንዳለው ያውቃል። ቅዱሳን ጽሑፎች ኃጢአት ሰውን ገዳይ በሆነ ማነቆው ተብትቦ የያዘ ብርቱ ኃይል መሆኑን ይገልጻሉ። የኃጢአት ማነቆ ምን ያክል ብርቱ ነው? በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈው ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ መጽሐፍ ውስጥ ይህን ጉዳይ ሕያው በሆነ መንገድ ገልጾታል:- ወታደሮች ከአለቆቻቸው በታች እንደሆኑ ሁሉ እኛም “ከኃጢአት በታች” ነን (ሮሜ 3:​9)፤ በሰው ልጅ ላይ ‘ነግሷል’ (ሮሜ 5:​21)፤ በውስጣችን ‘ያድራል’ ወይም ደግሞ ‘ይኖራል’ (ሮሜ 7:​17, 20)፤ ‘ሕጉ’ ሁልጊዜ በውስጣችን የሚሠራ ሲሆን አካሄዳችንንም ሁሉ ሊቆጣጠር ይሞክራል። (ሮሜ 7:​23, 25) በውዳቂው ሥጋችን ላይ ብርቱ ኃይል ያለውን ኃጢአት ለመቋቋም የምናደርገው ትግል ምንኛ አስቸጋሪ ነው!​—⁠ሮሜ 7:​21, 24

6. ይሖዋ የተሰበረ ልብ ይዘው ምሕረቱን ለማግኘት የሚጥሩ ሰዎችን እንዴት ይመለከታቸዋል?

6 በመሆኑም መሐሪ የሆነው አምላካችን ልባችን የቱንም ያህል ቢናፍቅ ፍጹም በሆነ መንገድ ታዛዥነት ማሳየት እንደማንችል ያውቃል። (1 ነገሥት 8:​46) በተሰበረ ልብ ቀርበን አባታዊ ምሕረቱን ለማግኘት የምንጥር ከሆነ ይቅር እንደሚለን ፍቅራዊ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። መዝሙራዊው ዳዊት እንዲህ ብሏል:- “የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፣ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም።” (መዝሙር 51:​17) ይሖዋ የጥፋተኛነት ስሜት ተጭኖት የተሰበረንና የተዋረደን ልብ አይንቅም ወይም ፊት አይነሣም። ይሖዋ ይቅር ለማለት ዝግጁ መሆኑን የሚያሳይ እንዴት ግሩም መግለጫ ነው!

7. የአምላክን ምሕረት አቃልለን ልንመለከተው የማንችለው ለምንድን ነው?

7 ይሁንና ይህ ማለት አለፍጽምናችንን ለኃጢአት ድርጊት ማሳበቢያ አድርገን በመጠቀም የአምላክን ምሕረት አቅልለን ልናየው ይገባል ማለት ነውን? በፍጹም! ይሖዋ እንዲሁ በስሜት የሚመራ አምላክ አይደለም። ምሕረቱ ወሰን አለው። ልባቸውን አደንድነው ንስሐ ሳይገቡ ሆነ ብለው ተንኮል ያዘለ ኃጢአት የሚሠሩትን ሰዎች በፍጹም ይቅር አይላቸውም። (ዕብራውያን 10:​26-31) በአንጻሩ ‘የተሰበረና የተዋረደ ልብ’ ሲመለከት “ይቅር ለማለት ዝግጁ” ነው። (ምሳሌ 17:​3) እስቲ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአምላክ ይቅር ባይነት ምን ያህል ፍጹም እንደሆነ ለመግለጽ የተሠራባቸውን አንዳንድ ሕያው አገላለጾች እንመልከት።

የይሖዋ ይቅር ባይነት ምን ያህል ፍጹም ነው?

8. ይሖዋ ኃጢአታችንን ሲተውልን ምን ያደረገ ያህል ነው? ይህስ በእኛ ላይ ምን ውጤት ሊኖረው ይገባል?

8 ንስሐ የገባው ንጉሥ ዳዊት እንዲህ ብሏል:- “ኃጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ፣ በደሌንም አልሸፈንሁም፤ ለእግዚአብሔር መተላለፌን እነግራለሁ አልሁ፤ አንተም የልቤን ኃጢአት ተውህልኝ።” (መዝሙር 32:​5፤ ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።) “ተውህልኝ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል መሠረታዊ ትርጉሙ “ማንሳት” “መሸከም” ማለት ነው። እዚህ ጥቅስ ውስጥ ያለው አገባብ ‘ጥፋትን፣ በደልን እና መተላለፍን ማራቅን’ ያመለክታል። በመሆኑም ይሖዋ የዳዊትን ኃጢአቶች ከላዩ በማንሳት ያራቀለት ያክል ነበር። (ከዘሌዋውያን 16:​20-22 ጋር አወዳድር።) ይህ ዳዊት ተሸክሞት የነበረውን የጥፋተኛነት ስሜት እንዳቃለለለት ምንም ጥርጥር የለውም። (ከመዝሙር 32:​3 ጋር አወዳድር።) እኛም በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ባላቸው እምነት መሠረት ይቅር እንዲላቸው ለሚጥሩ ሰዎች ኃጢአታቸውን በሚተውላቸው አምላክ ላይ ሙሉ ትምክህት ሊኖረን ይችላል። (ማቴዎስ 20:​28፤ ከኢሳይያስ 53:​12 ጋር አወዳድር።) ይሖዋ ኃጢአታቸውን አንስቶ ያራቀላቸው ሰዎች ቀደም ሲል በሠሩት ኃጢአት ምክንያት የተፈጠረባቸውን የጥፋተኛነት ስሜት ተሸክመው መቀጠል አያስፈልጋቸውም።

9. ኢየሱስ የተናገራቸው “ዕዳችንን ማረን” የሚሉት ቃላት ትርጉም ምንድን ነው?

9 ኢየሱስ ይሖዋ እንዴት ይቅር እንደሚል በምሳሌ ለማስረዳት በአበዳሪዎችና በባለ ዕዳዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ጠቅሷል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ “ዕዳችንን ማረን” እያልን እንድንጸልይ አሳስቦናል። (ማቴዎስ 6:​12 NW) በዚህ መንገድ ኢየሱስ ‘ኃጢአትን’ ‘ከዕዳ’ ጋር አመሳስሎታል። (ሉቃስ 11:​4) ኃጢአት ስንሠራ በይሖዋ ፊት ‘ባለ ዕዳ’ እንሆናለን። ‘ይቅር ማለት’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “አንድን ዕዳ መተው፣ ሁለተኛ አለመሻት” ማለት ሊሆን ይችላል። ይሖዋ ይቅር ሲል ከሒሳባችን ላይ ሊቀነስ ይገባ የነበረውን ዕዳ የሰረዘልን ያህል ነው። በመሆኑም ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞች በዚህ ሊጽናኑ ይችላሉ። ይሖዋ ለሰረዘው ዕዳ ዳግመኛ ክፍያ አይጠይቅም!​—⁠መዝሙር 32:​1, 2፤ ከማቴዎስ 18:​23-35 ጋር አወዳድር።

10, 11. (ሀ) በሥራ 3:​19 ላይ የሚገኘው ‘መደምሰስ’ የሚለው ቃል የሚያስተላልፈው መልእክት ምንድን ነው? (ለ) የይሖዋ ይቅር ባይነት ፍጹም መሆኑ እንዴት ተደርጎ ተገልጿል?

10 መጽሐፍ ቅዱስ በሥራ 3:​19 ላይ ስለ አምላክ ይቅር ባይነት ለማስረዳት ሌላም ግልጽ የሆነ ምሳሌያዊ አነጋገር ይጠቀማል:- “ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም።” ‘መደምሰስ’ የሚለው ቃል የተተረጎመው በዘይቤያዊ አገባቡ “ሙልጭ አድርጎ መጥረግ፣ ማስወገድ፣ መሰረዝ ወይም ማጥፋት” የሚል ሐሳብ ሊያስተላልፍ ከሚችል የግሪክኛ ግሥ ነው። አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት አንድን የእጅ ጽሑፍ ማጥፋት የሚል መልእክት ያስተላልፋል። ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነበር? ጥንት በአብዛኛው ይጠቀሙበት የነበረው ቀለም ጥቀርሻ፣ ከዕጽዋት የሚገኝ የማጣበቅ ባሕርይ ያለው ፈሳሽና ውኃ ተቀላቅሎ የሚዘጋጅ ነበር። አንድ ሰው እንዲህ ዓይነቱን ቀለም ተጠቅሞ ከጻፈ በኋላ ወዲያው በእርጥብ ስፖንጅ ጽሑፉን ሊያጠፋው ይችል ነበር።

11 ይህ የይሖዋ ይቅር ባይነት ምን ያህል ፍጹም እንደሆነ የሚያሳይ ግሩም መግለጫ ነው። ኃጢአታችንን ይቅር ሲለን በስፖንጅ ሙልጭ አድርጎ እንዳጠፋው ያክል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ምሕረት የሚነግረን ሌላም ተጨማሪ ድንቅ ነገር ስላለ ወደፊት ይህን ኃጢአት አስታውሶ ይጠይቀናል ብለን ልንሰጋ አይገባንም። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ይቅር ሲል ጨርሶ የሚረሳው መሆኑን ይገልጻል!

“ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብም”

12. መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ኃጢአታችንን እንደሚረሳ ሲናገር ፈጽሞ ስለዚያ ነገር ማስታወስ አይችልም ማለቱ ነውን? እንደዚያ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?

12 ይሖዋ በአዲሱ ቃል ኪዳን ሥር የሚታቀፉትን ሰዎች በሚመለከት በነቢዩ ኤርምያስ በኩል ሲናገር “በደላቸውን እምራቸዋለሁና፣ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብም” ብሎ ነበር። (ኤርምያስ 31:​34) ይህ ማለት ይሖዋ ይቅር ሲል የተፈጸመውን ኃጢአት ዳግመኛ ማስታወስ አይችልም ማለት ነውን? ፈጽሞ እንደዚያ ሊሆን አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ ዳዊትን ጨምሮ ይሖዋ ይቅር ስላላቸው ብዙ ሰዎች ኃጢአት ይነግረናል። (2 ሳሙኤል 11:​1-17፤ 12:​1-13) ይሖዋ ስለፈጸሙት ስህተት እስከ ዛሬም ድረስ እንደሚያውቅ ግልጽ ነው፤ እኛም እናውቃለን። ስለ ኃጢአታቸው እንዲሁም ንስሐ ስለ መግባታቸውና ከአምላክ ስላገኙት ይቅርታ የሚተርከው ዘገባ ለእኛ ጥቅም ሲባል እስከ ዛሬ ድረስ ተጠብቆ ቆይቷል። (ሮሜ 15:​4) ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ይቅር ያላቸውን ሰዎች ኃጢአት ‘አያስብም’ ሲል ምን ማለቱ ነው?

13. (ሀ) ‘ማሰብ’ የሚል ፍቺ ያለው የዕብራይስጡ ግሥ ምን ተጨማሪ ትርጉም ያዘለ ነው? (ለ) ይሖዋ “ኃጢአታቸውን ከእንግዲህ ወዲህ አላስብም” ሲል ስለ ምን ነገር ማረጋገጫ መስጠቱ ነው?

13 ‘ማሰብ’ የሚል ፍቺ ያለው የዕብራይስጡ ግሥ የጥንቱን ነገር ከማስታወስ የበለጠ ነገር ይጨምራል። ቲኦሎጂካል ዎርድቡክ ኦቭ ዚ ኦልድ ቴስታመንት የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው ከሆነ “ተገቢውን እርምጃ መውሰድ የሚል ተጨማሪ አንድምታም” አለው። በመሆኑም ከዚህ አንጻር አንድን ኃጢአት “ማሰብ” በኃጢአተኞቹ ላይ እርምጃ መውሰድን ይጨምራል። ነቢዩ ሆሴዕ ያመፁትን እስራኤላውያን በሚመለከት “እርሱም [ይሖዋ] በደላቸውን ያስባል” በማለት ሲናገር ንስሐ ባለመግባታቸው ምክንያት ይሖዋ እርምጃ ይወስድባቸዋል ማለቱ ነበር። በመሆኑም የቀረው የጥቅሱ ክፍል “ኃጢአታቸውንም ይበቀላል” በማለት አክሎ ይናገራል። (ሆሴዕ 9:​9) በአንጻሩ ይሖዋ “ኃጢአታቸውን ከእንግዲህ ወዲህ አላስብም” ሲል ንስሐ የገባውን ኃጢአተኛ አንድ ጊዜ ይቅር ካለው በኋላ ወደፊት ያንን ኃጢአት አስቦ እንደማይቀጣው ማረጋገጫ መስጠቱ ነው። (ሕዝቅኤል 18:​21, 22) በመሆኑም ይረሳል ሲባል በተደጋጋሚ እኛን ለመክሰስ ወይም ለመቅጣት ሲል ኃጢአታችንን አሁንም አሁንም አያነሳብንም ማለት ነው። በዚህ መንገድ ይሖዋ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ልንኮርጀው የሚገባ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። አለመግባባት በሚነሣበት ጊዜ ቀደም ሲል ይቅር ለማለት ተስማምተንበት የነበረውን ያለፈ ስህተት አለመጥቀስ ከሁሉ የተሻለ ይሆናል።

የሠራነው ኃጢአት ስለሚያስከትለው ውጤት ምን ማለት ይቻላል?

14. አንድ ንስሐ የገባ ኃጢአተኛ ይቅር ተብሏል ማለት የሠራው ስህተት ከሚያስከትላቸው ውጤቶች ሁሉ ነፃ ይሆናል ማለት አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

14 ይሖዋ ይቅር ለማለት ዝግጁ ነው ማለት ንስሐ የገባ ኃጢአተኛ የሠራው ክፉ ድርጊት ከሚያመጣበት ውጤት ሁሉ ነጻ ይሆናል ማለት ነው? በፍጹም አይደለም። ኃጢአት ፈጽመን ምንም ጉዳት ሳያገኘን እናመልጣለን ማለት አንችልም። ጳውሎስ “ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳል” ሲል ጽፏል። (ገላትያ 6:​7) የሠራነው ሥራ አንዳንድ ውጤቶችን ወይም ችግሮችን ያሳጭደን ይሆናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ይቅር ካለን በኋላ መከራ እንዲደርስብን አያደርግም። አንድ ክርስቲያን ችግር ሲያጋጥመው ‘ምናልባት ይሖዋ ቀደም ሲል በሠራሁት ኃጢአት ምክንያት እየቀጣኝ ይሆናል’ ብሎ ሊያስብ አይገባም። (ከያዕቆብ 1:​13 ጋር አወዳድር።) በአንጻሩ ግን ይሖዋ የፈጸምነው ክፉ ድርጊት ከሚያስከትለው ውጤት ሁሉ ይጠብቀናል ማለት አይደለም። እንደ ፍቺ፣ ያልተፈለገ እርግዝና፣ በጾታ ምክንያት የሚተላለፉ በሽታዎች፣ በሰዎች ዘንድ አመኔታ ወይም አክብሮት ማጣት የመሳሰሉት ነገሮች ሁሉ ኃጢአት ከሚያስከትላቸው መጥፎ ውጤቶች መካከል ሊሆኑ ይችላሉ። ይሖዋ እነዚህ ነገሮች እንዳይደርሱብን አይከላከልልንም። ዳዊት ከቤርሳቤህና ከኦሪዮን ጋር በተያያዘ የሠራውን ኃጢአት ይሖዋ ይቅር ቢለውም ከዚያ በኋላ ከመጡት አስከፊ ውጤቶች ግን እንዳላዳነው አስታውስ።​—⁠2 ሳሙኤል 12:​9-14

15, 16. በዘሌዋውያን 6:​1-7 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ሕግ ተበዳዩንም ሆነ በዳዩን የሚጠቅማቸው እንዴት ነበር?

15 የምንሠራቸው ኃጢአቶች ሌላም ውጤት ሊያስከትሉ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል በዘሌዋውያን ምዕራፍ 6 ላይ የሚገኘውን ዘገባ ተመልከት። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተገለጸው የሙሴ ሕግ አንድ ሰው በዝርፊያ፣ በንጥቂያ ወይም በማጭበርበር የሌላውን እስራኤላዊ ንብረት በመውሰድ ስለሚፈጽመው ከባድ ኃጢአት ይናገራል። ኃጢአተኛው ጥፋተኛነቱን ከመካድም አልፎ ዓይኑን አፍጥጦ በሐሰት ይምላል። ምንም ማስረጃ ባለመኖሩ እገሌ ከገሌ ብሎ ለመፍረድ ያስቸግራል። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ በዳዩ ሕሊናው ይወቅሰውና ኃጢአቱን ይናዘዛል። የአምላክን ይቅርታ ለማግኘት ከፈለገ ሦስት ተጨማሪ ነገሮችን ማድረግ ይኸውም የወሰደውን መመለስ፣ ለተበዳዩ የ20 በመቶ ቅጣት መክፈልና ለበደል መሥዋዕት አንድ አውራ በግ ማቅረብ ነበረበት። ከዚያ በኋላ ስላለው ነገር ሲገልጽ ሕጉ እንዲህ ይላል:- ‘ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል፣ ስለዚህም ይቅር ይባላል።’​—⁠ዘሌዋውያን 6:​1-7፤ ከማቴዎስ 5:​23, 24 ጋር አወዳድር።

16 ይህ ሕግ የአምላክ የምሕረት ዝግጅት ነበር። ንብረቱ የተመለሰለትን ተበዳይ የሚጠቅም ነበር። ከዚህም ሌላ የበደለው ሰው በመጨረሻ ኃጢአቱን ማመኑ ለተበዳዩ ግለሰብ ትልቅ እፎይታ እንደሚያመጣለት ምንም ጥርጥር የለውም። በተመሳሳይም ሕጉ ሕሊናው ቆርቁሮት በመጨረሻ ጥፋቱን በማመን ስህተቱን የሚያስተካክለውንም ግለሰብ የሚጠቅም ነበር። ይህን ባያደርግ አምላክ ይቅር እንደማይለው የታወቀ ነው።

17. እኛ የሠራነው ኃጢአት ሌሎችን በሚጎዳበት ጊዜ ይሖዋ ምን እንድናደርግ ይጠብቅብናል?

17 በሙሴ ሕግ ሥር ባንሆንም ይሖዋ ይቅር ስለ ማለት ያለውን አመለካከት ጨምሮ የእርሱን አሳብ በጥልቀት እንድናስተውል ይረዳናል። (ቆላስይስ 2:​13, 14) ሌሎች ሰዎች እኛ በፈጸምነው ኃጢአት በሚጎዱበት ወይም ቀጥተኛ ተጠቂ በሚሆኑበት ጊዜ የሠራውን ‘ጥፋት ለማረም’ የምንችለውን ሁሉ ስናደርግ ይሖዋ ደስ ይለዋል። (2 ቆሮንቶስ 7:​11 NW) ይህም ኃጢአታችንን ማሳወቅ፣ ጥፋታችንን ማመንና የጎዳነውን ሰው ይቅርታ መጠየቅን ይጨምራል። ከዚያ በኋላ በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት ይሖዋን በመለመን ንጹሕ ሕሊና የምናገኝ ከመሆኑም በላይ አምላክ ይቅር እንዳለን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።​—⁠ዕብራውያን 10:​21, 22

18. ይሖዋ የሚያደርግልን ይቅርታ ምን ቅጣት የታከለበት ሊሆን ይችላል?

18 ይሖዋ እንደማንኛውም አፍቃሪ ወላጅ ይቅር የሚለን ከተወሰነ ቅጣት ጋር ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 3:​11, 12) ንስሐ የገባ አንድ ክርስቲያን፣ ሽማግሌ፣ የጉባኤ አገልጋይ ወይም አቅኚ ሆኖ ማገልገሉን ማቆሙ ግድ ሊሆን ይችላል። እንደ ውድ ነገር ይመለከታቸው የነበሩትን መብቶቹን ለተወሰነ ጊዜ ማጣቱ በጣም ሊከብደው ይችላል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ቅጣት የይሖዋን ሞገስ አጥቷል ወይም ይሖዋ ይቅር አላለውም ማለት አይደለም። ከዚህም በላይ ተግሳጽ ይሖዋ ለእኛ ያለው ፍቅር መግለጫ እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። ይህን ተግሳጽ ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ ጥቅሙ ለእኛ ለራሳችን ሲሆን ወደ ዘላለም ሕይወትም ሊመራን ይችላል።​—⁠ዕብራውያን 12:​5-11

19, 20. (ሀ) ኃጢአት ፈጽመህ ከሆነ የይሖዋ ምህረት ሊሸፍነው እንደማይችል ሆኖ ሊሰማህ የማይገባው ለምንድን ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ስለ ምን ነገር እንወያያለን?

19 የምናገለግለው አምላክ “ይቅር ለማለት ዝግጁ” መሆኑን ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው! ይሖዋ የሚመለከተው ኃጢአታችንንና የሠራናቸውን ስህተቶች ብቻ አይደለም። (መዝሙር 130:​3, 4) በልባችን ውስጥ ምን እንዳለም ያውቃል። ቀደም ሲል በሠራኸው ኃጢአት ምክንያት ልብህ እንደተሰበረና እንደተዋረደ የሚሰማህ ከሆነ የይሖዋ ምሕረት ሊሸፍነው የማይችል ሁኔታ ውስጥ እንዳለህ አድርገህ አትደምድም። የፈጸምካቸው ስህተቶች ምንም ይሁኑ ምን ከልብህ ንስሐ ከገባህ፣ ስህተቱን ለማስተካከል እርምጃዎችን ከወሰድህ እንዲሁም በፈሰሰው የኢየሱስ ደም መሠረት ይሖዋ ይቅር እንዲልህ ልባዊ ጸሎት ካቀረብህ በ1 ዮሐንስ 1:​9 ላይ የሚገኙት “በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው” የሚሉት ቃላት ለአንተ እንደሚሠሩ ሙሉ ትምክህት ሊኖርህ ይችላል።

20 መጽሐፍ ቅዱስ አንዳችን ከሌላው ጋር ባለን ግንኙነት የይሖዋን ይቅር ባይነት እንድንኮርጅ ያበረታታናል። ይሁን እንጂ ሌሎች ሲበድሉን ይቅር ማለትና መርሳት ያለብን እስከምን ድረስ ነው? ይህ ጥያቄ በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ይብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የሚያስገርመው “ፍጥረታችንን” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል አንድ ሸክላ ሠሪ ከሚሠራቸው የሸክላ ዕቃዎች ጋር በተያያዘ መንገድ ተሠርቶበታል።​—⁠ኢሳይያስ 29:​16

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

◻ ይሖዋ “ይቅር ለማለት ዝግጁ” የሆነው ለምንድን ነው?

◻ መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ይቅር ባይነት ፍጹም መሆኑን የሚገልጸው እንዴት ነው?

◻ ይሖዋ ይቅር ሲል የሚረሳው በምን መንገድ ነው?

◻ እኛ በፈጸምነው ኃጢአት ሌሎች በሚጎዱበት ጊዜ ይሖዋ ምን እንድናደርግ ይፈልጋል?

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ እኛ በፈጸምነው ኃጢአት ሌሎች በሚጎዱበት ጊዜ ጥፋቱን የሚያካክስ ነገር እንድናደርግ ይፈልጋል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ