የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ የሚገኙ ወጣቶች አምላክን ያወድሳሉ
ከብዙ ምዕተ ዓመታት በፊት መዝሙራዊው “ጐልማሶችና ልጃገረዶች፣ ሽማግሌዎችና ልጆች . . . የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑ፣ የእርሱ ስም ከሌሎች ስሞች ይበልጣል” በማለት ወጣቶች የዘላለሙን ንጉሥ በማወደስ እንዲተባበሩ ሞቅ ያለ ግብዣ አቅርቦላቸው ነበር። (መዝሙር 148:12, 13 የ1980 ትርጉም) ከኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ የተገኙት ቀጥሎ ያሉት ተሞክሮዎች ይህንን ወደር የለሽ መብት ጎላ አድርገው ይገልጻሉ።
• ለአንድ ልዩ አቅኚ ቤት ያከራየ ግለሰብ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያሳዩት ጠባይ አድናቆት አሳደረበት። ከዚህም የተነሳ ፊፊ የተባለችው የአምስት ዓመት ሴት ልጁ ከምሥክሮቹ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ እንድታጠና ፈቃደኛ ሆነ። ፊፊ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌa የተባለውን መጽሐፍ በማጥናት ያደረገችውን እድገት ካስተዋለ በኋላ በመንግሥት አዳራሽ በሚካሄደው ስብሰባ እንድትገኝ ፈቀደላት። እዚያም ሕፃንዋ ፊፊ ምሥክሮቹ ከሚጠቀሙበት የመዝሙር መጽሐፍ የመንግሥቱን መዝሙሮች መዘመር ተማረች። በተለይ “አምላክ የሰጠው የገነት ተስፋ” የሚል ርዕስ ያለውን መዝሙር ቁጥር 4ን በጣም ወደደችው።
አንድ ቀን የፊፊ አባት እርሱ አባል ወደ ሆነበት ቤተ ክርስቲያን ይዟት ሄደ። እዚያም የቤተ ክርስቲያኑን መዝሙሮች አልዘምርም ማለቷ ሁሉንም ሰዎች አስገረማቸው። ለምን አልዘመረችም? ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያኑ መዝሙሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቷ ካገኘችው ትምህርት ጋር እንደማይስማሙ ስለተሰማት ነው። ከዚህ ይልቅ የምትወደውን የመንግሥት መዝሙር በድፍረት ዘመረች።
አስተሳሰቧን ለማስቀየር ያደረጉት ተደጋጋሚ ጥረት ከከሸፈባቸው በኋላ የቤተ ክርስቲያኑ መሪዎች የአምስት ዓመቷን ፊፊ ከአባልነት ለመሰረዝ ወሰኑ! ምንም እንኳን ቢያመናጭቋትም አባቷ ነገሩን በዝምታ አለፈው። ፊፊ ላመነችበት ነገር ጽኑ አቋም በመያዟ አባቷ ኩራት ተሰምቶት ነበር። ፊፊ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያላትን ግንኙነት እንድትቀጥል የአባቷም ሆነ የእናቷ ፍላጎት ነው።
• በአሥራዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኘው ሉኮዲ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሲጀምር አባቱ አጥብቆ ተቃወመው። አንድ ቀን ለስብሰባ ወደ መንግሥት አዳራሽ ለመሄድ እየተዘጋጀ ሳለ አባትየው በቆንጨራ አስፈራራው። በሌላ ጊዜ አባትየው በዱላ ጀርባውን መትቶ ክፉኛ አቆሰለው። ምንም እንኳን ይህን የመሰለ ከፍተኛ ተቃውሞ ቢደርስበትም ሉኮዲ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ባደረገው ቁርጥ ውሳኔ ጸና። እድገት ማድረጉን ቀጥሎ በመጨረሻ ተጠመቀ። ባሁኑ ጊዜ የዘወትር አቅኚ ሆኖ እያገለገለ ነው።
ሶና የተባለችው የሉኮዲ ታናሽ እህት ወንድሟ በወሰደው አቋም ከመደነቋ የተነሳ እርሷም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች። ሆኖም ጥናቷን እንድታቆም ለማድረግ አባታቸው የይሖዋ ምሥክሮች በሌሉበት ሌላ መንደር ውስጥ በሚገኝ ትምህርት ቤት አስገባት። የሆነ ሆኖ ሶና ስለተማረቻቸው ነገሮች ለሌሎች መናገርን ልማድዋ አደረገችው። ከዚህም የተነሳ የአክስቷ ልጅ ፍላጎት አሳየች።
በአቅራቢያው ባለ መንደር የነበሩ ምሥክሮች ስለ ሶና የስብከት እንቅስቃሴ በሰሙ ጊዜ ሄደው ከመጠየቃቸውም በላይ ቋሚ የሆነ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲመራላት ዝግጅት አደረጉ። እድገት ማድረጓን ቀጠለችና ብዙም ሳይቆይ ራስዋን ወስና የተጠመቀች የይሖዋ ምሥክር በመሆን እሷም የወንድሟን ፈለግ ተከተለች። ከዚህም በተጨማሪ የአክስቷ ልጅ ባሁኑ ጊዜ ያልተጠመቀች አስፋፊ ስትሆን በዚያ መንደር ውስጥ ደግሞ የመጽሐፍ ጥናት መካሄድ ጀምሯል።
የይሖዋን ስም በማወደሱ ሥራ ወጣቶች ሲተባበሩ ማየት እንዴት አስደሳችና መንፈስን የሚያነቃቃ ነው!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።