አካሄዳችሁን ከአምላክ ጋር አድርጉ
“በመንፈስ ተመላለሱ፣ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ።” —ገላትያ 5:16
1. (ሀ) ሄኖክ አካሄዱን ከአምላክ ጋር አድርጎ የተመላለሰው በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥና ለምን ያህል ጊዜ ነበር? (ለ) ኖኅ አካሄዱን ከአምላክ ጋር አድርጎ የተመላለሰው ለምን ያህል ጊዜ ነው? ምን ከባድ ኃላፊነቶችስ ነበሩበት?
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሄኖክ “አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ” በማለት ይነግረናል። በዙሪያው የነበሩት ሰዎች አሳፋሪ ንግግር የሚናገሩና ለአምላክ አክብሮት የጎደለው አኗኗር ያላቸው ቢሆኑም በ365 ዓመቱ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ አካሄዱን ከአምላክ ጋር በማድረግ ጸንቷል። (ዘፍጥረት 5:23, 24፤ ይሁዳ 14, 15) ኖኅም እንዲሁ ‘አካሄዱን ከእውነተኛው አምላክ ጋር አድርጓል።’ ይህን ሲያደርግ ግን ቤተሰቡን ማስተዳደር፣ ዓመፀኞቹ መላእክትና እብሪተኛ ልጆቻቸው የሚያምሱትን ዓለም ተቋቁሞ መኖር እንዲሁም በጥንቱ ዘመን ከነበሩት በባሕር ላይ የሚንቀሳቀሱ ነገሮች ሁሉ የሚበልጠውን ግዙፍ መርከብ ለመገንባት እያንዳንዱን ዝርዝር መመሪያ ተከታትሎ መሥራት ይጠበቅበት ነበር። ከጥፋት ውኃ በኋላም ይሖዋን በመቃወም የሚፈጸመው ዓመፅ በባቤል እንደገና ባንሠራራበት ጊዜ እርሱ አካሄዱን ከአምላክ ጋር በማድረግ መመላለሱን ቀጥሏል። በእርግጥም ኖኅ በ950 ዓመት ዕድሜው እስከሞተበት ጊዜ ድረስ አካሄዱን ከአምላክ ጋር በማድረግ መመላለሱን ቀጥሏል።—ዘፍጥረት 6:9፤ 9:29
2. ‘አካሄዳችንን ከአምላክ ጋር ማድረግ’ ማለት ምን ማለት ነው?
2 መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ የእምነት ሰዎች ‘አካሄዳቸውን’ ከአምላክ ጋር አድርገዋል ሲል ምሳሌያዊ አነጋገር መጠቀሙ ነው። ሄኖክና ኖኅ በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት እንዳላቸው በሚያሳይ መንገድ ተመላልሰዋል ማለት ነው። ይሖዋ ያዘዛቸውን ከማድረጋቸውም ሌላ እርሱ ከሰው ልጆች ጋር ካደረጋቸው ግንኙነቶች በመማር ከዚያ ጋር በሚስማማ መንገድ ሕይወታቸውን መርተዋል። (ከ2 ዜና መዋዕል 7:17 ጋር አወዳድር።) አምላክ በተናገረውና ባደረገው ነገር መስማማታቸውን በመግለጽ ብቻ ሳይወሰኑ እንዲያደርጉ የሚፈልግባቸውን ሁሉ በከፊል ሳይሆን አለፍጽምናቸው በሚፈቅድላቸው መጠን ሙሉ በሙሉ አከናውነዋል። ለምሳሌ ያህል ኖኅ በዚህ መንገድ አምላክ እንዳዘዘው እንዲሁ አድርጓል። (ዘፍጥረት 6:22) ኖኅ ከተሰጠው መመሪያ ቀድሞም አልሄደም፤ በቸልተኝነትም ወደኋላ አላለም። ከይሖዋ ጋር የቀረበ ዝምድና ያለው ሰው ስለነበር ለመጸለይ ነፃነት የሚሰማውና ለመለኮታዊ መመሪያዎችም ከፍተኛ ግምት የሚሰጥ ሰው በመሆን አካሄዱን ከአምላክ ጋር አድርጓል። እናንተስ እንደዚህ እያደረጋችሁ ነውን?
ወጥ የሆነ የሕይወት ጎዳና
3. ራሳቸውን ወስነው የተጠመቁ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ ምን ማድረጋቸው የግድ አስፈላጊ ነው?
3 ሰዎች አካሄዳቸውን ከአምላክ ጋር ማድረግ ሲጀምሩ ማየት ልብን ደስ ያሰኛል። ከይሖዋ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ አዎንታዊ እርምጃዎችን ሲወስዱ እምነት እንዳላቸው ያሳያሉ፤ ያለ እምነት ደግሞ ማንም ሰው አምላክን ደስ ማሰኘት አይችልም። (ዕብራውያን 11:6) ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በየዓመቱ በአማካይ ከ320,000 በላይ የሆኑ ሰዎች ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውንና ይህንንም በውኃ በመጠመቅ ለማሳየት መብቃታቸውን ስንመለከት ምንኛ ደስ ይለናል! ይሁን እንጂ እነርሱም ሆኑ እኛ አካሄዳችንን ከአምላክ ጋር አስማምተን መቀጠላችን በጣም አስፈላጊ ነው።—ማቴዎስ 24:13፤ ራእይ 2:10
4. ከግብጽ የወጡት አብዛኞቹ እስራኤላውያን የተወሰነ እምነት አሳይተው የነበረ ቢሆንም ወደ ተስፋይቱ ምድር ሳይገቡ የቀሩት ለምንድን ነው?
4 በሙሴ ዘመን ለአንድ እስራኤላዊ ቤተሰብ በግብጽ ምድር የማለፍ በዓልን ማክበርና ደሙን በበራቸው መቃንና ጉበን ላይ መቀባት እምነት የሚጠይቅ ነገር ነበር። (ዘጸአት 12:1-28) ሆኖም ወደ ቀይ ባሕር ሲደርሱ የፈርዖን ሠራዊት ከኋላቸው እንደተጠጋቸው ባዩ ጊዜ የብዙዎቹ እምነት ዋዥቆ ነበር። (ዘጸአት 14:9-12) መዝሙር 106:12 እንደሚገልጸው በባሕሩ መሐል በደረቅ የብስ ሲሻገሩና ሞገደኛው ውኃ የግብጻውያኑን ሠራዊት ጠራርጎ ሲያጠፋ ሲመለከቱ እንደገና ‘በይሖዋ ቃል አመኑ።’ ይሁን እንጂ ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በምድረበዳ ሳሉ የመጠጥ ውኃና ምግብን እንዲሁም አመራሩን በተመለከተ ማጉረምረም ጀመሩ። ወደ ተስፋይቱ ምድር ሄደው ከነበሩት 12 ሰላዮች መካከል አሥሩ ይዘውት የተመለሱት አፍራሽ ዘገባ አስፈርቷቸዋል። መዝሙር 106:24 እንደሚለው በእነዚህ ሁኔታዎች ‘በአምላክ ቃል አልታመኑም’ ነበር። ወደ ግብጽ ለመመለስ ፈለጉ። (ዘኁልቁ 14:1-4) ያላቸውም እምነት እንኳ ብልጭ ብሎ ይታይ የነበረው አንዳንድ አስገራሚ የሆኑ የመለኮታዊ ኃይል መግለጫዎችን ሲያዩ ብቻ ነበር። አካሄዳቸውን ከአምላክ ጋር አድርገው አልቀጠሉም። በመሆኑም እነዚያ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሳይገቡ ቀርተዋል።—መዝሙር 95:10, 11
5. በ2 ቆሮንቶስ 13:5 እና ምሳሌ 3:5, 6 የተገለጹት ማሳሰቢያዎች አካሄዳችንን ከአምላክ ጋር ከማድረግ ጋር የሚዛመዱት እንዴት ነው?
5 መጽሐፍ ቅዱስ “በሃይማኖት [“በእምነት፣” NW] ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ” በማለት ያሳስበናል። (2 ቆሮንቶስ 13:5) ‘በእምነት መኖር’ ማለት የክርስትናን እምነቶች በሙሉ አጥብቆ መያዝ ማለት ነው። በሕይወታችን ዘመን ሁሉ አካሄዳችንን ከአምላክ ጋር በማድረግ ረገድ እንዲሳካልን ከፈለግን ይህን ማድረጋችን የግድ አስፈላጊ ነው። አካሄዳችንን ከአምላክ ጋር ለማድረግ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ለመመካት የሚያስችል እምነት ሊኖረን ይገባል። (ምሳሌ 3:5, 6) እንዲህ ማድረግ የተሳናቸውን ሰዎች ሊያጠምዱ የሚችሉ በርካታ ወጥመዶችና እንቅፋቶች አሉ። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
በራስ ከመታመን ወጥመድ ራቁ
6. ሁሉም ክርስቲያኖች ስለ ዝሙትና ምንዝር ምን የሚያውቁት ነገር አለ? ስለ እነዚህ ኃጢአቶችስ ምን ይሰማቸዋል?
6 መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነው የተጠመቁ ሁሉ የአምላክ ቃል ዝሙትንና ምንዝርን እንደሚያወግዝ ያውቃሉ። (1 ተሰሎንቄ 4:1-3፤ ዕብራውያን 13:4) ይህ ነገር ትክክል እንደሆነም ይስማማሉ። ዓላማቸውም ከዚህ ጋር ተስማምቶ መኖር ነው። ይሁንና የጾታ ብልግና እስከ ዛሬም ድረስ ሰይጣን ከሚጠቀምባቸው በጣም ውጤታማ ወጥመዶች መካከል አንዱ ሆኗል። ለምን?
7. እስራኤላውያን ወንዶች በሞዓብ ሜዳ ስህተት እንደሆነ የሚያውቁትን ድርጊት ወደመፈጸም የደረሱት እንዴት ነው?
7 እንዲህ በመሰለው የብልግና ድርጊት ውስጥ የወደቁ ሰዎች መጀመሪያ ላይ ይህን ነገር እንፈጽማለን ብለው አላሰቡ ይሆናል። በሞዓብ ሜዳ የነበሩት እስራኤላውያንም እንዲሁ አስቀድመው አስበውበት ላይሆን ይችላል። በበረሃ ኑሮ የተሰላቹት እስራኤላውያን ወንዶች ልባቸውን የሰረቁትን የሞዓባውያንና የምድያማውያን ሴቶች ሲያገኙ ወዳጃዊ መንፈስ ካላቸውና እንግዳ ተቀባይ ከሆኑ ሰዎች ጋር እንደተገናኙ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ እስራኤላውያኑ ይሖዋን ሳይሆን በኣልን ከሚያመልኩ እንዲሁም ልጃገረዶቻቸው (ከትላልቅ ቤተሰብ የመጡት ሳይቀሩ) ካላገቡት ሰው ጋር የጾታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ ከሚፈቅዱ ሕዝቦች ጋር ወዳጅነት እንዲመሠርቱ የቀረበላቸውን ግብዣ በመቀበላቸው ውጤቱ ምን ሆነ? በእስራኤል ሰፈሮች ያሉት ወንዶች እንዲህ ባለው ወዳጅነት በመማረካቸው ስህተት እንደሆኑ የሚያውቋቸውን ነገሮች ሊፈጽሙ ችለዋል፤ ይህም ሕይወታቸውን አሳጥቷቸዋል።—ዘኁልቁ 22:1፤ 25:1-15፤ 31:16፤ ራእይ 2:14
8. በዛሬው ጊዜ አንድን ክርስቲያን ወደ ጾታ ብልግና ሊመራው የሚችለው ምንድን ነው?
8 ዛሬስ አንድ ሰው በተመሳሳይ ወጥመድ እንዲወድቅ የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል? የጾታ ብልግና ምን ያህል መጥፎ እንደሆነ የሚያውቅ ቢሆንም በራስ የመተማመንን አደገኛነት ካልተገነዘበ አስተሳሰቡን የሚያጨልምና ኃጢአት እንዲሠራ የሚገፋፋ ሁኔታ ውስጥ ሊገባ ይችላል።—ምሳሌ 7:6-9, 21, 22፤ 14:16
9. ከጾታ ብልግና ሊጠብቁን የሚችሉት ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስጠንቀቂያዎች የትኞቹ ናቸው?
9 ባጭር አነጋገር እኔ ጠንካራ ስለሆንኩ በመጥፎ ባልንጀርነት ልሸነፍ አልችልም ብለን በማሰብ ራሳችንን እንዳናታልል የአምላክ ቃል ያስጠነቅቀናል። ይህ ዓይነቱ ባልንጀርነት የብልግና ኑሮ ያላቸውን ሰዎች ታሪክ የሚያሳዩ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን መከታተልን እንዲሁም የብልግና ፍላጎት የሚቀሰቅሱ መጽሔቶችን ማየትን ይጨምራል። (1 ቆሮንቶስ 10:11, 12፤ 15:33) ከመሰል አማኞች ጋር እንኳን ሳይቀር አጉል ወዳጅነት መፍጠር ወደ ከባድ ችግር ሊመራ ይችላል። በተቃራኒ ጾታዎች መካከል ያለው የመሳሳብ ኃይል ጠንካራ ነው። በመሆኑም የይሖዋ ድርጅት ከፍቅራዊ አሳቢነት በመነሣት የትዳር ጓደኛችን ወይም የቤተሰባችን አባል ካልሆነ ተቃራኒ ጾታ ጋር ብቻችንንና ከእይታ ውጭ እንዳንሆን ያስጠነቅቀናል። አካሄዳችንን ከአምላክ ጋር አድርገን ለመቀጠል በራስ ከመተማመን ወጥመድ ርቀን አምላክ የሚሰጠንን የማስጠንቀቂያ ምክር መከተል ይኖርብናል።—መዝሙር 85:8
ሰውን የመፍራት ዝንባሌ እንዲቆጣጠራችሁ አትፍቀዱ
10. “ሰውን መፍራት” ወጥመድ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
10 ሌላው አደገኛ ሁኔታ ደግሞ በምሳሌ 29:25 ላይ ተገልጿል፤ ጥቅሱ “ሰውን መፍራት መጥመድ ያመጣል” ይላል። ብዙውን ጊዜ የአንድ አዳኝ ወጥመድ አንገትን እንቅ አድርጎ የሚይዝ ሸምቀቆ ወይም ደግሞ የእንስሳውን እግር የሚጠልፍ ገመድ ይኖረዋል። (ኢዮብ 18:8-11) በተመሳሳይም ሰውን መፍራት አንድ ሰው በነጻነት የመናገርና አምላክን የሚያስደስት ነገር የማድረግ ችሎታውን እንዳይጠቀም ማነቆ ሊሆንበት ይችላል። ሌሎችን ለማስደሰት መፈለግ ያለ ነገር ነው፤ ስለ ሌሎች ሰዎች ሐሳብ ጨርሶ ደንታ ቢስ መሆንም ክርስቲያናዊ ባሕርይ አይደለም። ነገር ግን ሚዛናዊነት ያስፈልጋል። አንድ ሰው ሌሎች ምን ይሉ ይሆን በሚል ጭንቀት አምላክ የከለከለውን ነገር የሚያደርግ ወይም የአምላክ ቃል የሚያዝዘውን ከማድረግ የሚታቀብ ከሆነ ይህ ሰው ወጥመድ ውስጥ ገብቷል ማለት ነው።
11. (ሀ) የሰው ፍርሃት እንዲቆጣጠረን ከመፍቀድ የሚጠብቀን ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ሰውን የመፍራት ችግር የነበረባቸውን አገልጋዮቹን የረዳቸው እንዴት ነው?
11 አንድ ሰው ከዚህ ዓይነቱ ወጥመድ ሊጠበቅ የሚችለው በራሱ ተፈጥሮአዊ ባሕርይ ሳይሆን ‘በአምላክ በመታመን ነው።’ (ምሳሌ 29:25) በተፈጥሮው ዓይን አፋር የሆነ ሰው እንኳ በአምላክ ላይ በመታመን ደፋርና ጽኑ ሊሆን ይችላል። በዚህ የሰይጣን የነገሮች ሥርዓት ተከበን እስካለን ድረስ ሁልጊዜ ሰውን ከመፍራት ወጥመድ ራሳችንን ልንጠብቅ ይገባናል። ነቢዩ ኤልያስ ድፍረት የተሞላበት ግሩም አገልግሎት በማከናወኑ የሚጠቀስ ቢሆንም ኤልዛቤል እንደምትገለው ስትዝትበት ፈርቶ ሸሽቷል። (1 ነገሥት 19:2-18) ሐዋርያው ጴጥሮስ በተጽዕኖ ሥር ሲወድቅ ፈርቶ ኢየሱስን አላውቀውም ብሎ ከመካዱም ሌላ ከዓመታት በኋላ ፍርሃት ከእምነቱ የሚቃረን ነገር እንዲሠራ አድርጎታል። (ማርቆስ 14:66-71፤ ገላትያ 2:11, 12) ይሁን እንጂ ኤልያስም ሆነ ጴጥሮስ የተሰጣቸውን መንፈሳዊ እርዳታ ተቀብለው በይሖዋ በመታመን ተቀባይነት ባለው መንገድ እርሱን ማገልገላቸውን ቀጥለዋል።
12. አንዳንድ ግለሰቦች ሰውን በመፍራት አምላክን ከማስደሰት ወደኋላ እንዳይሉ እርዳታ እንዳገኙ የሚያሳዩን የትኞቹ ዘመናዊ ምሳሌዎች ናቸው?
12 ዛሬ ያሉት ብዙዎቹ የይሖዋ አገልጋዮች የፍርሃትን ወጥመድ እንዴት ማሸነፍ እንደሚችሉ ተምረዋል። በጉያና የምትገኝ አንዲት በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ያለች የይሖዋ ምሥክር “በትምህርት ቤት የእኩዮችን ተጽእኖ መቋቋም ትልቅ ትግል ይጠይቃል” ስትል ተናግራለች። ይሁን እንጂ በመቀጠል “እኔም በይሖዋ ላይ ያለኝ እምነት የዚያኑ ያክል ጠንካራ ነው” ብላለች። አስተማሪዋ በእምነቷ ምክንያት በክፍሏ ተማሪዎች ሁሉ ፊት ሲያፌዝባት በልቧ ወደ ይሖዋ ትጸልይ ነበር። ከዚያ በኋላ ለአስተማሪዋ ለብቻው በጥበብ መሠከረችለት። ይሖዋ ከእርሱ ምን እንደሚፈልግበት የተማረ አንድ ወጣት በቤኒን ወደሚገኝ የትውልድ ቀዬው ተመልሶ በሄደ ጊዜ አባቱ የሠራለትን የጣዖት ቅርጽ ለማጥፋት ቆርጦ ይነሣል። ወጣቱ ይህ ምስል ሕይወት አልባ እንደሆነ ስለሚያውቅ አልፈራም፤ ይሁን እንጂ ይህ ነገር መንደርተኛውን እንደሚያስቆጣና ሊገድሉትም እንደሚችሉ ተገንዝቦ ነበር። ወደ ይሖዋ ከጸለየ በኋላ ሌሊት ጣዖቱን ወደ ጫካ ወስዶ ጣለው። (ከመሳፍንት 6:27-31 ጋር አወዳድር።) በዶሚኒካን ሪፑብሊክ የምትገኝ አንዲት ሴት ይሖዋን ማገልገል ስትጀምር ባሏ ከእርሱና ከይሖዋ አንዳቸውን እንድትመርጥ ያስጨንቃታል። ሰውዬው አለዚያ እፈታሻለሁ ሲል ዛተባት። ፍርሃት እምነቷን እንድትተው አድርጓት ይሆን? “ለባሌ ታማኝ ሳልሆን ቀርቼ ትዳሬ ቢፈርስ አፍራለሁ፤ ይሖዋን በማገልገሌ ምክንያት ቢፈርስ ግን አላፍርም!” ስትል መልሳለች። አካሄዷን ከአምላክ ጋር በማድረጓ ከጊዜ በኋላ ባሏም የይሖዋን ፈቃድ በማድረግ ከጎኗ ተሰልፏል። እኛም በሰማያዊው አባታችን ላይ ሙሉ በሙሉ መታመናችን ሰውን ፈርተን ይሖዋን እንደሚያስደስተው የምናውቀውን ነገር ከማድረግ ወደኋላ እንዳንል ሊጠብቀን ይችላል።
ምክርን አቃልላችሁ ከመመልከት ተቆጠቡ
13. በ1 ጢሞቴዎስ 6:9 ላይ ከየትኛው ወጥመድ እንድንርቅ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶናል?
13 አዳኞች የሚጠቀሙባቸው አንዳንዶቹ ወጥመዶች በአንድ የተወሰነ ቦታ የሚያልፈውን ማንኛውንም እንስሳ ለማጥመድ ተብለው የሚቀመጡ ሲሆኑ ሌሎቹ ወጥመዶች ደግሞ እንስሳቱን የሚስብ ማባበያ ይኖራቸዋል። ሀብት ለብዙዎቹ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ወጥመድ ሆኖባቸዋል። (ማቴዎስ 13:22) መጽሐፍ ቅዱስ በ1 ጢሞቴዎስ 6:8, 9 ላይ ምግብና ልብስ ካለን በዚያ ረክተን እንድኖር ያበረታታናል። ከዚያም እንዲህ በማለት ያስጠነቅቃል:- “ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ።”
14. (ሀ) አንድ ሰው ምግብና ልብስ በማግኘቱ ረክቶ እንዲኖር የተሰጠውን ምክር በቁም ነገር እንዳይመለከት ምን ነገር ሊከለክለው ይችላል? (ለ) ስለ ሃብት የተሳሳተ አመለካከት መያዝ አንድ ሰው በ1 ጢሞቴዎስ 6:9 ላይ የተሰጠውን ምክር አቃልሎ እንዲያይ ሊያደርገው የሚችለው እንዴት ነው? (ሐ) “የዓይን አምሮት” አንዳንዶች ከፊታቸው የሚጠብቃቸውን ወጥመድ እንዳያስተውሉ ሊያሳውራቸው የሚችለው እንዴት ነው?
14 ይህ ማስጠንቀቂያ ቢኖርም ብዙዎች ምክሩን ለራሳቸው ስለማይሠሩበት በዚህ ወጥመድ ይያዛሉ። ለምን? መጽሐፍ ቅዱስ ‘ምግብና ልብስ’ ካላችሁ በዚያ ረክታችሁ ኑሩ እያለ ሲያሳስብ እነርሱ ግን ከዚህ የበለጠ ነገር የሚጠይቅ አኗኗራቸውን የሙጥኝ ብለው እንዲቀጥሉ ያደረጋቸው ነገር ኩራት ይሆን? ለእነርሱ ሃብት ማለት በጣም የበለጸጉ ሰዎች ያላቸውን ንብረት ማግኘት ማለት ስለሆነ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ማስጠንቀቂያ አቃልለው ተመልክተውት ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ሃብታም ለመሆን ቆርጦ መነሳትን ምግብና ልብስ በማግኘት ረክቶ ከመኖር ጋር በማነጻጸር ነው። (ከዕብራውያን 13:5 ጋር አወዳድር።) “የዓይን አምሮት፣” ማለትም መንፈሳዊ ጉዳዮችን ሳይቀር መሥዋዕት አድርጎ ያዩትን ነገር ሁሉ የማግኘት ምኞት ለእውነተኛው አምልኮ ሁለተኛ ቦታ እንዲሰጡት አድርጓቸው ይሆን? (1 ዮሐንስ 2:15-17፤ ሐጌ 1:2-8) የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተከትለው በሕይወታቸው ውስጥ ለይሖዋ አገልግሎት ቀዳሚውን ሥፍራ በመስጠት አካሄዳቸውን ከአምላክ ጋር ያደረጉ ሰዎች ምንኛ ይበልጥ ደስተኞች ይሆኑ!
የኑሮን ጭንቀቶች በተሳካ ሁኔታ ማሸነፍ
15. ብዙዎቹን የይሖዋ ሕዝቦች የትኞቹ ሁኔታዎች እንደሚያስጨንቋቸው ግልጽ ነው? በእንዲህ ዓይነት ተጽዕኖ ሥር በምንሆንበት ጊዜ በየትኛው ወጥመድ ላለመያዝ ንቁ መሆን ይገባናል?
15 ሃብታም ለመሆን ቆርጦ ከመነሳት ይልቅ ይበልጥ በሰፊው የሚታየው ችግር ለሕይወት የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማግኘት መጨነቅ ነው። ብዙዎቹ የይሖዋ አገልጋዮች ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ ነው። እንደ ልብስ፣ ለቤተሰባቸው መጠለያ የሚሆን ቦታ እና ቢያንስ የዕለት ጉርስ ያሉትን መሠረታዊ ነገሮች እንኳ ለማግኘት ለብዙ ሰዓታት ጠንክረው ለመሥራት ይገደዳሉ። ሌሎች ደግሞ በራሳቸው ወይም በቤተሰብ አባሎቻቸው ላይ በደረሰው ሕመም ወይም በእርጅና ምክንያት ከሚመጡት ችግሮች ጋር ይታገላሉ። እንዲህ ያሉት ሁኔታዎች በውስጣችን ያለውን መንፈሳዊ ዝንባሌ በቀላሉ ሊያንቁት ይችላሉ!—ማቴዎስ 13:22
16. ይሖዋ የኑሮ ተጽዕኖዎችን እንድንቋቋም የሚረዳን እንዴት ነው?
16 ይሖዋ በፍቅር ተገፋፍቶ መሲሐዊው መንግሥት የሚያመጣውን እፎይታ ገልጾልናል። (መዝሙር 72:1-4, 16፤ ኢሳይያስ 25:7, 8) ቅድሚያ የምንሰጣቸውን ነገሮች ለመወሰን የሚረዳንን ምክር በመስጠት አሁንም ቢሆን የኑሮን ግፊቶች መቋቋም እንድንችል ይረዳናል። (ማቴዎስ 4:4፤ 6:25-34) ይሖዋ ጥንት የነበሩ አገልጋዮቹን እንዴት እንደረዳቸው በሚገልጸው ታሪክ አማካኝነትም ማረጋገጫ ይሰጠናል። (ኤርምያስ 37:21፤ ያዕቆብ 5:11) ምንም ዓይነት መከራ ቢመጣብን እርሱ ለታማኝ አገልጋዮቹ ያለው ፍቅር ፈጽሞ እንደማይለወጥ እንድናውቅ በማድረግ ያበረታናል። (ሮሜ 8:35-39) ትምክሕታቸውን በይሖዋ ላይ ለሚጥሉ ሰዎች “አልለቅህም ከቶም አልተውህም” ብሏል።—ዕብራውያን 13:5
17. ከባድ መከራ እየደረሰባቸው ያሉ ግለሰቦች አካሄዳቸውን ከአምላክ ጋር አድርገው እንዴት መመላለስ እንደቻሉ የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ጥቀስ።
17 እውነተኛ ክርስቲያኖች ይህን በማወቃቸው ተበረታተው ፊታቸውን ወደ ዓለማዊ መንገድ ከመመለስ ይልቅ አካሄዳቸውን ከአምላክ ጋር እንዳደረጉ ይቀጥላሉ። በብዙ አገሮች ውስጥ ባሉ ድኻ ሰዎች ዘንድ የተለመደ አንድ ፈሊጥ አለ፤ ይኸውም ቤተሰብህን ለመመገብ ስትል ብዙ ካለው ሰው ላይ ብትወስድ ስርቆት አይባልም የሚል ነው። ይሁን እንጂ በእምነት የሚመላለሱ ሰዎች ይህን አባባል አይቀበሉትም። ከሁሉ ነገር በላይ ትልቅ ግምት የሚሰጡት ነገር የአምላክን ሞገስ ማግኘታቸውን ሲሆን አምላክ የሐቀኝነት ጎዳናቸውን እንደሚባርክላቸው ያምናሉ። (ምሳሌ 30:8, 9፤ 1 ቆሮንቶስ 10:13፤ ዕብራውያን 13:18) አንዲት በሕንድ የምትኖር መበለት ራሷን ለሥራ ዝግጁ ማድረጓ ከብልሃተኝነቷ ጋር ተዳምሮ ችግርን ለማሸነፍ እንዳስቻላት ተገንዝባለች። ዕጣ ፈንታዋን ከማማረር ይልቅ በሕይወቷ ውስጥ የአምላክን መንግሥትና ጽድቁን ካስቀደመች ለራሷና ለልጅዋ የሚያስፈልጋቸውን መሠረታዊ ነገሮች ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ይሖዋ እንደሚባርክላት ተገንዝባ ነበር። (ማቴዎስ 6:33, 34) በምድር ዙሪያ የሚገኙ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ምንም ዓይነት መከራ ቢደርስባቸው ይሖዋ መታመኛቸውና አምባቸው መሆኑን አሳይተዋል። (መዝሙር 91:2) አንተስ እንዲህ ታደርጋለህን?
18. ከሰይጣን ዓለም ወጥመዶች ለማምለጥ ቁልፉ ምንድን ነው?
18 በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ እስካለን ድረስ ልንጠነቀቅባቸው የሚገቡ ወጥመዶች አሉ። (1 ዮሐንስ 5:19) መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ወጥመዶች ምን እንደሆኑና እንዴት ልንሸሻቸው እንደምንችል ይገልጽልናል። ይሖዋን ከልባቸው የሚያፈቅሩና እርሱን ላለማሳዘን ጤናማ ፍርሃት ያዳበሩ ሰዎች ሁሉ እነዚህን ወጥመዶች በተሳካ ሁኔታ ሊወጧቸው ይችላሉ። ‘በመንፈስ መመላለሳቸውን ከቀጠሉ’ ለዓለማዊ መንገዶች እጃቸውን አይሰጡም። (ገላትያ 5:16-25) ሕይወታቸው ከይሖዋ ጋር ባላቸው ዝምድና ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ያደረጉ ሰዎች ሁሉ ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዘላለማዊ ዝምድና ኖሯቸው ከእርሱ ጋር የመመላለስ ክብራማ ተስፋ ይጠብቃቸዋል።—መዝሙር 25:14
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ በራስ መተማመን ወጥመድ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
◻ ሰውን የመፍራት ዝንባሌ እንዳይቆጣጠረን ሊጠብቀን የሚችለው ምንድን ነው?
◻ ባለጠግነትን ማሳደድ ያለውን አደጋ በሚመለከት የተሰጠንን ምክር ሳንጠቀምበት እንድንቀር ሊያደርገን የሚችለው ምንድን ነው?
◻ የኑሮ ጭንቀቶች ወጥመድ እንዳይሆኑብን ለመከላከል የሚያስችለን ምንድን ነው?
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብዙዎች በሕይወት ዘመናቸው ሙሉ አካሄዳቸውን ከአምላክ ጋር አድርገው ይመላለሳሉ