እውነተኛውን አምላክ መፍራት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች
“የሚጠቅምህን ሁሉ የማስተምርህና የምትሄድበትን መንገድ የምመራህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ።”—ኢሳይያስ 48:17 የ1980 ትርጉም
1. በአምላካዊ ፍርሃት አማካኝነት የትኞቹ ችግሮች መወገድ ይችሉ ነበር?
አዳም አምላካዊ ፍርሃትን ኮትኩቶ አሳድጎ ቢሆን ኖሮ ለራሱ ዘላለማዊ ሞት ያስከተለበትንና ዘሮቹ ደግሞ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት በሐዘን ተቆራምደው እንዲኖሩ ምክንያት የሆነውን ኃጢአት ከመፈጸም እንዲታቀብ ባስቻለው ነበር። የጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ ይሖዋ እሱን እንዲፈሩና እንዲያፈቅሩት የሰጣቸውን ምክር ተከትለው ቢሆን ኖሮ ወደ ባቢሎን ተማርከው ባልተወሰዱ ነበር፤ እንዲሁም የአምላክን ልጅ አንቀበልም ባላሉና የእሱን ደም በማፍሰስ ተጠያቂ ባልሆኑ ነበር። በዛሬው ጊዜ ያለው ዓለም አምላክን ቢፈራ ኖሮ በአገዛዝም ሆነ በንግዱ ዓለም ምግባረ ብልሹነት አይኖርም ነበር፤ ወንጀልም ሆነ ጦርነት አይኖርም ነበር።—ምሳሌ 3:7
2. በአካባቢያችን ባለው ዓለም ውስጥ ያሉት ሁኔታዎች ምንም ይሁኑ ምን ይሖዋን የመፍራትን ባሕርይ ኮትኩተን ማሳደግ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
2 ይሁን እንጂ በዙሪያችን ያለው ዓለም ምንም ሠራ ምን በግለሰብ ደረጃ፣ በቤተሰብ ደረጃና በጉባኤ ደረጃ የአምላክ አገልጋዮች እንደ መሆናችን መጠን እውነተኛውን አምላክ የመፍራትን ባሕርይ ኮትኩተን በማሳደግ ልንጠቀም እንችላለን። ይህ ሙሴ ለእስራኤል ሕዝብ ከሰጠው ማሳሰቢያ ጋር የሚስማማ ነው፦ “አምላክህን እግዚአብሔርን ትፈራ ዘንድ፣ በመንገዱም ሁሉ ትሄድ ዘንድ፣ አምላክህንም እግዚአብሔርን ትወድድ ዘንድ፣ በፍጹምም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ ታመልከው ዘንድ፣ መልካምም እንዲሆንልህ . . . የእግዚአብሔርን ትእዛዝ . . . ትጠብቅ ዘንድ ነው እንጂ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድር ነው?” (ዘዳግም 10:12, 13) እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን ስንፈራ ከምናገኛቸው ጥቅሞች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
ከወርቅ ይበልጥ ውድ የሆነው ጥበብ
3. (ሀ) ልናገኘው የምንችለው ከሁሉ የላቀ ጥቅም ምንድን ነው? (ለ) የመዝሙር 111:10 ትርጉም ምንድን ነው?
3 ከሁሉ የላቀው ጥቅም እውነተኛ ጥበብ ነው። መዝሙር 111:10 “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” ሲል ይገልጻል። ይህ ምን ማለት ነው? ጥበብ ችግሮችን ለመፍታት፣ ከአደጋ ለማምለጥና የተወሰኑ ግቦችን ዳር ለማድረስ እውቀትን በተቃና ሁኔታ የመጠቀም ችሎታ ነው። ጥሩ የማመዛዘን ችሎታንም ይጨምራል። የእንዲህ ዓይነቱ ጥበብ መጀመሪያውና አንደኛው መሠረት ይሖዋን መፍራት ነው። ለምን? ምክንያቱም ፍጥረታት በሙሉ የእጁ ሥራ ናቸው። ያለ እርሱ መኖር አይችሉም። ይሖዋ ለሰው ዘር ነፃ ፈቃድ ሰጥቶታል፤ ሆኖም ያለ እርሱ አመራር አካሄዱን ማቅናት የሚችልበትን ችሎታ ግን አልሰጠውም። (ኢያሱ 24:15፤ ኤርምያስ 10:23) ዘላቂ ስኬትን ማግኘት የምንችለው እነዚህን መሠረታዊ የሆኑ የሕይወት እውነታዎች ስንገነዘብና ከእነርሱ ጋር በሚስማማ መንገድ ስንኖር ብቻ ነው። ስለ ይሖዋ ያለን እውቀት የአምላክ ፈቃድ በእርግጥ ግቡን የሚመታ እንደሆነ እንዲሁም ለታማኝነት ዋጋ እንደሚከፍል የገባው ቃልና ይህን ለማድረግ ያለው ችሎታ አስተማማኝ እንደሆነ ያለ አንዳች ጥርጥር እንድናምን ካደረገን አምላካዊ ፍርሃት በጥበብ እንድንመላለስ ይገፋፋናል።—ምሳሌ 3:21–26፤ ዕብራውያን 11:6
4, 5. (ሀ) አንድ ወጣት የተከታተለው የዩኒቨርሲቲ ትምህርት እውነተኛ ጥበብን ሊያስገኝለት ያልቻለው ለምንድን ነው? (ለ) ከጊዜ በኋላ ይህ ሰውና ሚስቱ እውነተኛ ጥበብን ያገኙት እንዴት ነው? ይህስ ሕይወታቸውን የለወጠላቸው በምን መንገድ ነው?
4 አንድ ምሳሌ እንመልከት። ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በፊት አንድ ወጣት ሰው ካናዳ በሚገኘው በሳስከችዋን ዩኒቨርሲቲ ይማር ነበር። ከሚማራቸው ትምህርቶች አንዱ ባዮሎጂ ሲሆን ስለ ዝግመተ ለውጥ ተማረ። ይህ ወጣት ከተመረቀ በኋላ በቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ ነፃ የትምህርት ዕድል በማግኘት በአቶሚክ ፊዚክስ ልዩ ሥልጠና ወሰደ። ትምህርቱን በሚከታተልበት ጊዜ በአተሞች አሠራር ውስጥ አስደናቂ የሆነ ሥርዓትና ንድፍ መኖሩን ተገንዝቦ ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ ንድፍ ያወጣው ማን ነው? መቼና ለምንስ አወጣው? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ አላገኘም ነበር። ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ሳያገኝ በጊዜው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ውስጥ ተዘፍቆ በነበረው ዓለም ከዩኒቨርሲቲ ያገኘውን እውቀት በጥበብ ሊጠቀምበት ይችላልን? ለሕይወቱ መመሪያ የሚሆነው ምንድን ነው? ብሔራዊ ስሜት? ቁሳዊ ሀብት የማግኘት ምኞት? በእርግጥ እውነተኛ ጥበብ አግኝቶ ነበርን?
5 ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ብዙም ሳይቆይ ይህ ወጣትና ሚስቱ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመሩ። ከዚህ በፊት ሊያገኙ ያልቻሏቸውን መልሶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት ጀመሩ። ፈጣሪ የሆነውን ይሖዋ አምላክን ለማወቅ ቻሉ። ሙሴ በቀይ ባሕር ያደረገውን፣ ዳንኤልና ባልንጀሮቹ በባቢሎን ያደረጉትን ሲያውቁ ሰዎችን ሳይሆን አምላክን መፍራት በጣም አስፈላጊ መሆኑን ተገነዘቡ። (ዘጸአት 14:10–31፤ ዳንኤል 3:8–30) ይህ ዓይነቱ አምላካዊ ፍርሃት ለይሖዋ እውነተኛ ፍቅር ማሳየት ታክሎበት ሕይወታቸውን የሚመራ ኃይል ሆነላቸው። ብዙም ሳይቆይ ጠቅላላ አኗኗራቸው ተለወጠ። በመጨረሻም ይህ ወጣት በባዮሎጂ ትምህርቱ የእጁን ሥራዎች ሲያጠና የነበረውን አምላክ አወቀ። በፊዚክስ ጥናቱ ላይ ጥበቡ ተንጸባርቆ የተመለከተውን አምላክ ዓላማዎች መረዳት ጀመረ። እውቀቱን መሰሎቹ የሆኑትን የሰው ልጆች የሚያጠፋ መሣሪያ ለመሥራት ከመጠቀም ይልቅ እሱና ሚስቱ ሌሎች ሰዎች አምላክንና መሰሎቻቸው የሆኑትን የሰው ልጆች እንዲወዱ ለመርዳት ፈለጉ። የሙሉ ጊዜ የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች ሆነው ማገልገል ጀመሩ። ከዚያም በኋላ በመጠበቂያ ግንብ የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ሠልጥነው ለሚስዮናዊ አገልግሎት ተላኩ።
6. ይሖዋን በመፍራት ላይ የተመሠረተ ጥበብ ካለን ምን ጊዜያዊ የሆኑ ነገሮችን ከማሳደድ እንቆጠባለን? በእሱ ፋንታስ ምን እናደርጋለን?
6 እርግጥ፣ ሁሉም ሰው ሚስዮናዊ ሊሆን አይችልም። ቢሆንም ሁላችንም ይሖዋን በመፍራት ላይ ከተመሠረተው ጥበብ ተጠቃሚዎች ልንሆን እንችላለን። ይህን ጥበብ ኮትኩተን ካሳደግን ስለ ሕይወት ምንነት የግምት አስተያየት ከመስጠት የማያልፉትን የሰዎች ፍልስፍናዎች በጉጉት አንቀስምም። የዘላለም ሕይወት ሊሰጠን በሚችለውና የሕይወት ምንጭ በሆነው በይሖዋ አምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት እናጠናለን። (መዝሙር 36:9፤ ቆላስይስ 2:8) ራሱ በጥፋት አፋፍ ላይ ሆኖ የሚፍገመገመው የንግድ ሥርዓት ባሪያዎች ከመሆን ይልቅ ከአምላክ ጋር ላለን ዝምድና አንደኛውን ደረጃ እየሰጠን ምግብና ልብስ በማግኘት ረክተን እንድንኖር ይሖዋ የሰጠንን ምክር እንከተላለን። (1 ጢሞቴዎስ 6:8–12) የወደፊት ኑሯችን የተመካው ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ በመድረሳችን ላይ የሆነ ይመስል ይህን ከማሳደድ ይልቅ ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል ሲል የይሖዋ ቃል የሚነግረንን እናምናለን።—1 ዮሐንስ 2:17
7. (ሀ) ምሳሌ 16:16 ከፍ ያለ ዋጋ ያለውን ነገር ለይተን በማወቅ ረገድ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረን የሚረዳን እንዴት ነው? (ለ) ሕይወታችን ሙሉ በሙሉ የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ላይ ያተኮረ እንዲሆን በማድረግ የምናገኛቸው ወሮታዎች ምንድን ናቸው?
7 ምሳሌ 16:16 “ጥበብን [ይሖዋን በመፍራት የሚጀምረውን ጥበብ] ማግኘት ምንኛ ከወርቅ ይሻላል! ማስተዋልንም ማግኘት ከብር ይልቅ የሚመረጥ ነው” ብሎ እውነቱን በመግለጽ ያበረታታናል። እንዲህ ዓይነቶቹ ጥበብና ማስተዋል ሕይወታችን ሙሉ በሙሉ የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ላይ እንዲያተኩር እንድናደርግ ይገፋፉናል። አምላክ በዚህኛው የሰው ልጅ ታሪክ ዘመን ውስጥ ምሥክሮቹ እንዲያከናውኑት የሰጣቸው ሥራ ምንድን ነው? ሥራው ስለ መንግሥቱ መስበክና ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እውነተኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ መርዳት ነው። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) እውነተኛ እርካታንና ይህ ነው የማይባል ደስታ የሚያስገኝ ሥራ ነው። እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስ “ጥበብን የሚያገኝ ሰው ምስጉን [“ደስተኛ” አዓት] ነው” በማለት የተናገረበት ጥሩ ምክንያት አለው።—ምሳሌ 3:13
መጥፎ ድርጊት ከመፈጸም ይጠብቃል
8. (ሀ) አምላክን በመፍራት የሚገኘውን ሁለተኛ ጥቅም ጥቀስ። (ለ) ጥበቃ ያገኘነው ከምን መጥፎ ነገር ነው? (ሐ) አምላካዊ ፍርሃት ከፍተኛ ግፊት የሚያሳድር ኃይል የሚሆነው እንዴት ነው?
8 አምላክን ከመፍራት የምናገኘው ሁለተኛው ጥቅም መጥፎ የሆነ ነገር ከማድረግ ሊጠብቀን መቻሉ ነው። አምላክን እጅግ የሚያከብሩ ሰዎች ይህ ጥሩ ነው ይህ ደግሞ መጥፎ ነው ብለው ራሳቸው ለራሳቸው አይወስኑም። አምላክ ጥሩ ነው ያለውን ነገር መጥፎ እንደሆነ አድርገው አይመለከቱም፤ አምላክ መጥፎ ነው ያለውን ነገር ደግሞ ጥሩ እንደሆነ አድርገው አይመለከቱም። (መዝሙር 37:1, 27፤ ኢሳይያስ 5:20, 21) ከዚህም በላይ አምላካዊ ፍርሃት ያደረበት ሰው ይሖዋ መጥፎ ነው የሚለውንና ጥሩ ነው የሚለውን በማወቅ ብቻ አያቆምም። እንዲህ ያለው ሰው ይሖዋ የሚወደውን ይወዳል፣ ይሖዋ የሚጠላውን ይጠላል። በዚህ ምክንያት የሚያደርጋቸው ነገሮች ከአምላክ የአቋም ደረጃዎች ጋር የሚስማሙ ይሆናሉ። በመሆኑም በምሳሌ 16:6 ላይ እንደተገለጸው “እግዚአብሔርንም በመፍራት ሰው ከክፋት ይመለሳል።” እንዲህ ዓይነቱ አምላካዊ ፍርሃት አንድ ሰው በራሱ ኃይል ሊያደርግ የማይችለውን ነገር እንዲያደርግ የሚያስችል ኃይል ይሆንለታል።
9. አንዲት በሜክሲኮ የምትኖር ሴት አምላክን ላለማሳዘን ያደረባት ብርቱ ፍላጎት በውሳኔዋ ላይ ተጽእኖ ያሳደረው እንዴት ነው? ውጤቱስ ምን ሆነ?
9 አንድ ሰው አምላካዊ ፍርሃትን ገና እያዳበረ ቢሆንም እንኳ በቀረው የሕይወቱ ዘመን በሙሉ የሚጸጸትበትን ነገር ከማድረግ እንዲቆጠብ ሊያደርገው ይችላል። ለምሳሌ፣ አንዲት በሜክሲኮ የምትኖር ነፍሰ ጡር የሆነች ሴት የይሖዋ ምሥክር የሆነችን ሌላ ሴት ጽንስ ስለ ማስወረድ ትጠይቃለች። ምሥክሯ ብዙ ጥቅሶችን ካነበበችላት በኋላ “ፈጣሪ ለሕይወት፣ ገና ላልተወለደ ሕፃን ሕይወት እንኳን ከፍተኛ ግምት” እንደሚሰጥ አስረዳቻት። (ዘጸአት 21:22, 23፤ መዝሙር 139:13–16) በጽንሱ ላይ ምርመራ ተደርጎ ጤነኛ ሕፃን ላትወልድ እንደምትችል ተነግሯት ነበር። በዚህ ጊዜ ሴቲቱ በአምላክ ቃል ውስጥ በተመለከተችው ነገር ልቧ በጣም ስለተነካ ልጁ እንዲወለድ ወሰነች። ሐኪምዋ ሁለተኛ እርሷን ለማነጋገር ፈቃደኛ አልሆነም። ባልዋም ጥሏት እንደሚሄድ ዛተባት። እርሷ ግን በውሳኔዋ ጸናች። ከጊዜ በኋላ ጤናማና የምታምር ሴት ልጅ ወለደች። ልቧ በምስጋና ተሞልቶ የይሖዋ ምሥክሮችን ፈልጋ አገኘችና የአምላክን ቃል ከእነርሱ ጋር ማጥናት ጀመረች። በአንድ ዓመት ውስጥ እሷና ባልዋ ተጠመቁ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ በአንድ የወረዳ ስብሰባ ላይ መጀመሪያ ያነጋገረቻትን እህት ሲያገኙ በጣም ተደሰቱ፤ አራት ዓመት የሆናትን ደስ የምትል ልጃቸውንም አስተዋወቋት። አንድ ሰው ለአምላክ ያለው ተገቢ አክብሮትና እርሱን ላለማሳዘን የሚያድርበት ጠንካራ ምኞት ሕይወቱን ሊለውጠው ይችላል።
10. አምላካዊ ፍርሃት ሰዎች ከምን ዓይነት መጥፎ ድርጊቶች እንዲላቀቁ ሊያጠነክራቸው ይችላል?
10 አምላካዊ ፍርሃት ከብዙ ዓይነት መጥፎ ድርጊቶች ይጠብቀናል። (2 ቆሮንቶስ 7:1) አንድ ሰው በውስጡ አምላክን መፍራትን በሚገባ ኮትኩቶ ካሳደገ እርሱና ይሖዋ ብቻ የሚያውቋቸውን ስውር ኃጢአቶች እንዲያቆም ሊረዳው ይችላል። ከአልኮልና ከአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነት እንዲላቀቅ ሊረዳው ይችላል። ከዚህ በፊት የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኛ የነበረ አንድ ደቡብ አፍሪካዊ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “ስለ አምላክ ያለኝ እውቀት እየጨመረ ሲሄድ እርሱን እንዳላሳዝን ወይም እንዳላስከፋ መፍራት ጀመርኩ። ሁልጊዜ እንደሚመለከተኝ ስለማውቅ ዘወትር የአምላክን ሞገስ የማግኘት ጉጉት ነበረኝ። ይህም በእጄ የነበሩትን አደንዛዥ ዕፆች በሙሉ ሽንት ቤት እንድጨምር ገፋፋኝ።” አምላካዊ ፍርሃት በሺህ የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎቸም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ አስችሏቸዋል።—ምሳሌ 5:21፤ 15:3
ሰዎችን ከመፍራት ይጠብቃል
11. ለይሖዋ የምናሳየው ጤናማ ፍርሃት ከምን የተለመደ ወጥመድ ሊጠብቀን ይችላል?
11 ለአምላክ የምናሳየው ጤናማ ፍርሃት ሰውን ከመፍራትም ይጠብቀናል። አብዛኞቹ ሰዎች ይብዛም ይነስ ሰውን የመፍራት ችግር አለባቸው። ሌላው ቀርቶ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት እንኳ እሱ በጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ በወታደሮች በተያዘበት ጊዜ ጥለውት ሸሽተዋል። ከዚያም በኋላ በሊቀ ካህኑ አጥር ግቢ ጴጥሮስ ሚዛኑን መጠበቅ ተስኖትና በፍርሃት ተውጦ ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዱ መሆኑን በመካድ እንዲያውም እንደማያውቀው ተናግሯል። (ማርቆስ 14:48–50, 66–72፤ ዮሐንስ 18:15–27) ይሁን እንጂ ሐዋርያቱ መንፈሳዊ ሚዛናቸውን መልሰው ማግኘት የሚችሉበት እርዳታ አግኝተዋል። በሌላ በኩል ደግሞ በንጉሥ ኢዮአቄም ዘመን የሸማያ ልጅ የነበረው ኦርዮ በፍርሃት ተውጦ ስለነበር የይሖዋ ነቢይ ሆኖ ያከናውነው የነበረውን አገልግሎት ትቶ አገሪቱን ለቆ ሸሸ፤ ተይዞ ከመገደል ግን አላመለጠም ነበር።—ኤርምያስ 26:20–23
12. (ሀ) ምሳሌ 29:25 ሰውን ከመፍራት መጠበቅ የምንችልበት ነገር ምንድን ነው ይላል? (ለ) በአምላክ መታመን እየጎለበተ የሚሄደው እንዴት ነው?
12 አንድ ሰው ሰውን የመፍራትን ባሕርይ ለማሸነፍ እንዲችል ምን ሊረዳው ይችላል? “ሰውን መፍራት ወጥመድ” እንደሆነ ካስጠነቀቀ በኋላ ምሳሌ 29:25 “በእግዚአብሔር የሚታመን ግን እርሱ ይጠበቃል” በማለት ጨምሮ ይናገራል። ቁልፉ በይሖዋ መታመን ነው። እንዲህ ዓይነቱ እምነት በእውቀትና በተሞክሮ ላይ የተመሠረተ ነው። ቃሉን በማጥናት የይሖዋ መንገዶች ትክክል እንደሆኑ የሚያሳዩ ማስረጃዎችን እናገኛለን። እምነት ሊጣልበት የሚችል መሆኑን፣ (የትንሣኤ ተስፋን ጨምሮ) ቃል የገባቸው ተስፋዎች አስተማማኝ እንደሆኑ፣ ፍቅሩንና ሁሉን ቻይ የሆነውን ኃይሉን የሚያሳዩ ክስተቶችን በደንብ እንመለከታለን። ከዚያም ይሖዋ የሰጣቸውን መመሪያዎች በመፈጸምና እንድንርቃቸው ያስጠነቀቀንን ነገሮች በጽኑ በመጥላት ካገኘነው እውቀት ጋር የሚስማማ ነገር ስናደርግ ፍቅራዊ እንክብካቤውንና እምነት ሊጣልበት የሚችል መሆኑን በራሳችን ላይ ከሚደርሰው ሁኔታ መመልከት እንጀምራለን። ኃይሉ ፈቃዱን ለመፈጸም ሲሠራ የሚያሳይ ማስረጃ በግላችን እንመለከታለን። በእሱ ላይ ያለን ትምክህት ይጨምራል፤ በዚህም ላይ ደግሞ ለእርሱ ያለን ፍቅርና እሱን ላለማሳዘን ያለን ፍላጎት ይጨምራል። እንዲህ ዓይነቱ እምነት በጠንካራ መሠረት ላይ የተመሠረተ ነው። ሰውን የመፍራት ባሕርይን የምንከላከልበት መሣሪያ ሆኖ ያገለግለናል።
13. አምላካዊ ፍርሃት በሰብዓዊ ሥራ ቦታችን፣ በቤትና በትምህርት ቤት ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
13 አንድ አሠሪ በንግድ ዓለም የሚፈጸሙ የማታለያ ድርጊቶችን ካልሠራህ ከሥራ አስወጣሃለሁ ብሎ ቢያስፈራራን በይሖዋ ላይ ያለን እምነት ከአምላካዊ ፍርሃት ጋር ተዳምሮ ትክክል የሆነውን ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ እንዳንል ያደርገናል። (ከሚክያስ 6:11, 12 ጋር አወዳድር።) እንዲህ ዓይነቱ አምላካዊ ፍርሃት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ከማያምኑ የቤተሰብ አባሎች ተቃውሞ ቢደርስባቸውም እውነተኛ አምልኮን እንደያዙ ጸንተው እንዲኖሩ አስችሏቸዋል። በተጨማሪም በትምህርት ቤት የሚማሩ ወጣቶች የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን ለይተው እንዲያሳውቁ የሚያስችላቸውን ድፍረት ይሰጣቸዋል፤ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ የአቋም ደረጃዎች የሚያላግጡ የክፍል ጓደኞቻቸው የሚሰነዝሩባቸውን ትችቶች ለመቋቋም እንዲችሉ ያጠነክራቸዋል። በመሆኑም አንዲት በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ ምሥክር “የእነርሱ አመለካከት የሚያመጣው ለውጥ የለም። ዋናው ነገር ይሖዋ ለእኛ ያለው አመለካከት ነው” በማለት ተናግራለች።
14. የይሖዋ አገልጋዮች ሕይወታቸው አደጋ ላይ በሚወድ ቅበት ጊዜም እንኳ ድል አድራጊዎች መሆን የሚችሉት እንዴት ነው?
14 ይኸው እምነት እውነተኛ ክርስቲያኖች ሕይወታቸው ፈተና ላይ በሚወድቅበት ጊዜም እንኳ የይሖዋን መንገዶች አጥብቀው እንዲይዙ ያጠነክራቸዋል። ከዓለም ስደት ይደርስብናል ብለው መጠበቅ እንዳለባቸው ያውቃሉ። ሐዋርያት ክፉኛ እንደተደበደቡ ኢየሱስ ክርስቶስም ራሱ በክፉ ሰዎች እንደተመታና እንደተገደለ ይገነዘባሉ። (ማርቆስ 14:65፤ 15:15–39፤ ሥራ 5:40፤ ከዳንኤል 3:16–18 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ የይሖዋ አገልጋዮች ይሖዋ እንዲጸኑ ሊያጠነክራቸው እንደሚችል፣ በአምላክ እርዳታ ድል አድራጊዎች ሊሆኑ እንደሚችሉና ይሖዋ ያላንዳች ጥርጥር አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም እርሱ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ በትንሣኤ ወደ ሕይወት በመመለስ ታማኝነታቸውን የጠበቁትን ሰዎች እንደሚክሳቸው ሙሉ እምነት አላቸው። ለአምላክ ያላቸው ፍቅር ከአምላካዊ ፍርሃት ጋር ተዳምሮ እርሱን የሚያሳዝን ማንኛውም ነገር እንዳያደርጉ ኃይለኛ ግፊት ያሳድርባቸዋል።
15. የይሖዋ ምሥክሮች በናዚ ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ንጹሕ አቋማቸውን ሳያጎድፉ መኖር ያስቻላቸው ምንድን ነው?
15 ይህ ኃይለኛ ግፊት የሚያሳድርባቸው ውስጣዊ ስሜት የይሖዋ ምሥክሮች በ1930ዎቹና በ1940ዎቹ ዓመታት በናዚ ማጎሪያ ካምፖች የደረሰባቸውን አሠቃቂ መከራ መቋቋም አስችሏቸዋል። በሉቃስ 12:4, 5 ላይ የሚገኘውን የኢየሱስ ምክር ልብ ብለው ነበር፦ “ለእናንተም ለወዳጆቼ እላችኋለሁ፣ ሥጋን የሚገድሉትን በኋላም አንድ ስንኳ የሚበልጥ ሊያደርጉ የማይችሉትን አትፍሩ። እኔ ግን የምትፈሩትን አሳያችኋለሁ፤ ከገደለ በኋላ ወደ ገሃነም ለመጣል ሥልጣን ያለውን ፍሩ። አዎን እላችኋለሁ፣ እርሱን ፍሩ።” በመሆኑም በዛክሰንሃውዘን የማጎሪያ ካምፕ ውስጥ የነበረ ጉስታቭ ኦሽነር የተባለ አንድ ምሥክር ከጊዜ በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የኤስ ኤስ ወታደሮች ኦገስት ዲክማንን ተኩሰው ከገደሉት በኋላ የተቀረነውንም እምነታችንን ክደናል ብላችሁ በሰነድ ላይ ካልፈረማችሁ እንገድላችኋለን ብለው አስፈራሩን። አንዳችንም አልፈረምንም። ከእነርሱ ጥይት ይልቅ በጣም እንፈራ የነበረው ይሖዋን እንዳናሳዝን ነበር።” ሰውን መፍራት አቋምን እንድንለውጥ ያደርጋል፤ አምላክን መፍራት ግን ትክክል ለሆነው ነገር የጸና አቋም እንድንይዝ ያደርጋል።
ሕይወትን ከጥፋት የሚያድን ነው
16. ኖኅ እስከ ጥፋት ውኃ ድረስ ዓመታት አልፈው ዓመታት በተተኩ ቁጥር ትክክል የሆነውን ነገር በማድረግ እንዲቀጥል ያስቻለው ነገር ምንድን ነው? እሱም ሆነ ቤተሰቡ ያገኙት ውጤትስ ምን ነበር?
16 ኖኅ ከጥፋት ውኃ በፊት በነበረው ዓለም የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ ኖሯል። ይሖዋ በሰው ክፋት የተነሣ በዚያን ጊዜ የነበረውን ክፉ ዓለም ለማጥፋት ወስኖ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ በእንዲህ እንዳለ ኖኅ በዓመፅና ይህ ነው በማይባል የጾታ ብልግና በተሞላ፣ እንዲሁም ለመለኮታዊ ፈቃድ ግድየለሽ በሆነው በዚህ ዓለም ውስጥ ይኖር ነበር። ምንም እንኳ ኖኅ ስለ ጽድቅ ቢሰብክም ‘የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ ትኩረት ሰጥቶ ያስተዋለ አልነበረም።’ (ማቴዎስ 24:39) ሆኖም ኖኅ አምላክ የሰጠውን ሥራ ተስፋ ቆርጦ አልተወውም። ኖኅ “እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ።” (ዘፍጥረት 6:22) ኖኅ እስከ ጥፋት ውኃ ድረስ ዓመት አልፎ ዓመት በተተካ ቁጥር ትክክል የሆነውን ነገር እያደረገ እንዲቀጥል ያስቻለው ምንድን ነው? ዕብራውያን 11:7 (አዓት) “ኖኅ ገና ስላልታየው ነገር መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ ከተሰጠው በኋላ በእምነት አምላካዊ ፍርሃት አሳየ” በማለት መልሱን ይሰጠናል። በዚህም ምክንያት እሱና ሚስቱ እንዲሁም ልጆቹና ሚስቶቻቸው ከጥፋቱ ውኃ ዳኑ።
17. (ሀ) ሌሎች ሰዎች ምንም አደረጉ ምን እኛ ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ለ) ይሖዋን የሚፈሩ ሰዎች እውነተኛ ደስታ ያላቸው ሕዝቦች የሆኑት ለምንድን ነው?
17 እኛም በብዙ መልኩ ከኖኅ ዘመን ጋር በሚመሳሰል ጊዜ ላይ እንኖራለን። (ሉቃስ 17:26, 27) አሁንም ማስጠንቀቂያ እየተሰጠ ነው። ራእይ 14:6, 7 አንድ መልአክ በሰማይ መካከል እየበረረ የሁሉም ብሔራትና ነገዶች ሕዝቦች ‘አምላክን እንዲፈሩና እንዲያከብሩ’ እንዳሳሰበ ይናገራል። በአካባቢህ ያለው ዓለም ምንም ያድርግ ምን እነዚህን ቃላት ስማ፤ ከዚያም ይህን ጥሪ ለሌሎች አሰማ። ልክ እንደ ኖኅ በእምነት ተመላለስ፤ እንዲሁም አምላካዊ ፍርሃት አሳይ። እንዲህ ማድረግህ የአንተንም ሆነ የሌሎች የብዙ ሰዎችን ሕይወት እንድታድን ሊያደርግህ ይችላል። እውነተኛውን አምላክ የሚፈሩ ሰዎች የሚያገኟቸውን ጥቅሞች በጥሞና ስናስብ በመንፈስ ተነሳስቶ “እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ ትእዛዙንም እጅግ የሚወድድ ሰው ምስጉን [“ደስተኛ” አዓት] ነው” ብሎ እንደዘመረው መዝሙራዊ ለማለት እንገደዳለን።—መዝሙር 112:1
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ እውነተኛውን አምላክ መፍራት ከሚያስገኛቸው ዋና ዋና ጥቅሞች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
◻ በአምላካዊ ፍርሃት ላይ የተመሠረተ ጥበብ ሊጠብቀን የሚችለው እንዴት ነው?
◻ አምላካዊ ፍርሃት ከመጥፎ ነገር እንድንርቅ የሚያደርገን ለምንድን ነው?
◻ አምላካዊ ፍርሃት ሰውን ከመፍራት የሚጠብቀን እንዴት ነው?
◻ አምላካዊ ፍርሃት በወደፊቱ የሕይወት ተስፋዎቻችን ላይ ምን ተጽእኖ ያሳድራል?
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
“እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ ትእዛዙንም እጅግ የሚወድድ ሰው ምስጉን [“ደስተኛ” አዓት] ነው።”—መዝሙር 112:1