የይሖዋን ፈቃድ ፈጽመዋል
ኢዮብ ንጹህ አቋሙን በመጠበቁ ወሮታ ተከፍሎታል
ኢዮብ ለመበለቶች፣ ወላጆቻቸው ለሞቱባቸው ልጆችና ለተጨቆኑ ሰዎች የሚቆም ርኅሩኅ ሰው ነበር። (ኢዮብ 29:12-17፤ 31:16-21) ሆኖም ንብረቱን፣ ልጆቹንና ጤናውን በማጣት በቅጽበት ውድቀት ደረሰበት። የሚያሳዝነው ግን ይህ ለሰው ችግር ደራሽ የነበረ ለጋስ ሰው እሱ እርዳታ ባስፈለገው ጊዜ ማንም አልደረሰለትም። የገዛ ሚስቱ እንኳ “እግዚአብሔርን ስደብና ሙት” አለችው። ኤልፋዝ፣ በልዳዶስና ሶፋር የተባሉ “ወዳጆቹ” ምንም ዓይነት መጽናኛ አልሰጡትም። ከዚህ ይልቅ ኢዮብ ኃጢያት እንደሠራና የእጁን እያገኘ እንዳለ በተዘዋዋሪ ነገሩት።—ኢዮብ 2:9፤ 4:7, 8፤ 8:5, 6፤ 11:13-15
ምንም እንኳ ኢዮብ ይህ ሁሉ ስቃይ ቢደርስበትም እስከ መጨረሻው ታማኝ ሆኗል። በዚህ ምክንያት ይሖዋ በመጨረሻ ባርኮታል። ይህ የኢዮብ ታሪክ አምላክ ንጹህ አቋማቸውን ለሚጠብቁ ሁሉ በጊዜው ወሮታቸውን እንደሚከፍላቸው ማረጋገጫ ይሰጣል።
ከክስ ነፃ መሆንና እንደገና መባረክ
በመጀመሪያ ይሖዋ ኤልፋዝን በልዳዶስንና ሶፋርን ገሰጻቸው። ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ከሁሉ በእድሜ የሚበልጠውን ኤልፋዝን ይሖዋ እንዲህ ብሎታል:- “እንደ ባሪያዬ እንደ ኢዮብ ቅንን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና ቁጣዬ በአንተና በሁለቱ ባልንጀሮችህ ላይ ነድዶአል። አሁን እንግዲህ ሰባት ወይፈኖችና ሰባት አውራ በጎች ይዛችሁ ወደ ባሪያዬ ኢዮብ ዘንድ ሂዱ፣ የሚቃጠልንም መሥዋዕት ስለ ራሳችሁ አሳርጉ፤ ባሪያዬም ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልያል።” (ኢዮብ 42:7, 8) ይህ ምን ሊያመለክት እንደሚችል እስቲ አስብ!
ይሖዋ የሠሩትን ኃጢያት ክብደት ለመግለጽ ኤልፋዝ፣ በልዳዶስና ሶፋር ከፍ ያለ መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ፈለገ። ኤልፋዝ፣ በልዳዶስና ሶፋር ሆን ብለውም ይሁን ሳያውቁ አምላክ ‘በአገልጋዮቹ አይታመንም’ እንዲሁም ኢዮብ ጻድቅ ሆነም አልሆነ ለይሖዋ ምንም ለውጥ አያመጣም በማለት አምላክን ተሳድበዋል። እንዲያውም ኢዮብ በአምላክ ዓይን ከብል የማይበልጥ ተደርጎ እንደሚታይ ኤልፋዝ ተናግሯል! (ኢዮብ 4:18, 19፤ 22:2, 3) ስለዚህ ይሖዋ “ቅንን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና” ብሎ መናገሩ አይገርምም!
ይሁን እንጂ ይህ ብቻ አይደለም። ኤልፋዝ፣ በልዳዶስና ሶፋር ኢዮብ ይህ ሁሉ ችግር የደረሰበት በራሱ ጥፋት እንደሆነ በመናገራቸው ኃጢያት ሠርተዋል። ይህ መሠረተ ቢስ ክስና ፍጹም አሳቢነት የጎደለው ንግግር ኢዮብን እንዲማረርና እንዲያዝን ከማድረጉም በላይ “ነፍሴን የምትነዘንዙ፣ በቃልስ የምታደቅቁኝ እስከ መቼ ነው?” በማለት በሐዘን እንዲያንጎራጉር አድርጎታል። (ኢዮብ 10:1፤ 19:2) እነዚህ ሦስት ሰዎች ለኃጢአታቸው መሥዋዕት እንዲያቀርብላቸው ወደ ኢዮብ ሲመጡ ምን ዓይነት ኀፍረት እንደተሰማቸው መገመት ትችላለህ!
ይሁን እንጂ ኢዮብ የእነሱ በኀፍረት መሸማቀቅ አላስፈነደቀውም። እንዲያውም ኢዮብ ስለ ከሳሾቹ እንዲጸልይ ይሖዋ ጠይቆታል። ኢዮብ እንደተባለው በማድረጉ ተባርኳል። በመጀመሪያ ይሖዋ ኢዮብን ከያዘው ዘግናኝ በሽታ እንዲፈወስ አደረገ። ከዚያም ወንድሞቹ፣ እህቶቹና ቀድሞ የሚያውቁት ሁሉ ሊያጽናኑት መጡ፤ በተጨማሪም “እያንዳንዳቸውም የገንዘብና የወርቅ ቀለበት ስጦታ አደረጉለት።”a ከዚህም በላይ ኢዮብ “አሥራ አራት ሺህም በጎች፣ ስድስት ሺህም ግመሎች፣ አንድ ሺህም ጥማድ በሬዎች፣ አንድ ሺህም እንስት አህዮች ነበሩት።”b አንዲሁም የኢዮብ ሚስት እንደተታረቀችው ማስረጃዎች ያሳያሉ። በጊዜው ኢዮብ ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆች በመውለድ ሲባረክ የልጅ ልጆቹን እስከ አራት ትውልድ ድረስ አይቷል።—ኢዮብ 42:10-17
ለእኛ የሚሆኑ ትምህርቶች
ኢዮብ ዛሬ ላሉ የአምላክ አገልጋዮች የላቀ ምሳሌ ነው። ኢዮብ “እንከን የሌለበትና ጻድቅ” ሰው ሲሆን ይሖዋ “ባሪያዬ” ብሎ ሲጠራው አያፍርበትም። (ኢዮብ 1:8 NW፤ 42:7, 8) ይሁን እንጂ ኢዮብ ፍጹም ሰው ነበር ማለት አይደለም። በመከራው ወቅት በአንድ ጉዳይ አምላክን ለመጣበት መከራ ተጠያቂ አድርጎታል። እንዲያውም አምላክን ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ወቅሶታል። (ኢዮብ 27:2፤ 30:20, 21) በተጨማሪም ከአምላክ ይልቅ ራሱን ጻድቅ አድርጓል። (ኢዮብ 32:2) ይሁን እንጂ ኢዮብ በፈጣሪው ላይ ጀርባውን ለማዞር እምቢ በማለት በትህትና ከአምላክ እርማት ተቀብሏል። “የማላውቀውን ድንቅ ነገር ተናግሬአለሁ። ስለዚህ ራሴን እንቃለሁ፤ በአፈርና በአመድ ላይ ተቀምጬ እጸጸታለሁ” በማለት ስህተቱን አምኗል።—ኢዮብ 42:3, 6
እኛም ብንሆን በመከራ ጊዜ ተገቢ ያልሆነ ነገር ልናስብ፣ ልንናገር ወይም ልንሠራ እንችላለን። (ከመክብብ 7:7 ጋር አወዳድር።) ቢሆንም ለአምላክ ጥልቅ የሆነ ፍቅር ካለን በእሱ ላይ አናምፅም ወይም አንዳንድ ከበድ ያሉ ችግሮች እንዲደርሱብን ስለ ፈቀደ አናማርርም። ከዚህ ይልቅ ንጹህ አቋማችንን በመጠበቅ በመጨረሻ ብዙ በረከቶችን እናጭዳለን። መዝሙራዊው ዳዊት “ከታማኝ ጋር ታማኝ ትሆናለህ” በማለት ስለ ይሖዋ ተናግሯል።—መዝሙር 18:25 NW
ኢዮብ እሱን በመቃወም ኃጢያት ለሠሩት አጽናኞች እንዲጸልይላቸው ይሖዋ የጠየቀው ገና ጤንነቱ ሳይመለስለት በፊት ነው። ይህ ለእኛ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! ይሖዋ ኃጢያታችንን ይቅር እንዲልልን እኛ በቅድሚያ የበደሉንን ይቅር እንድንል ይጠብቅብናል። (ማቴዎስ 6:12፤ ኤፌሶን 4:32) ሌሎች ሰዎችን ይቅር ለማለት የሚያስችል በቂ ምክንያት እያለ ፈቃደኛ ካልሆንን ይሖዋ ለእኛ ምሕረት እንዲያሳይ ልንጠብቅ እንችላለንን?—ማቴዎስ 18:21-35
ሁላችንም በተለያየ ጊዜ መከራ ይደርስብናል። (2 ጢሞቲዎስ 3:12) ይሁን እንጂ ልክ እንደ ኢዮብ ንጹህ አቋማችንን ልንጠብቅ እንችላለን። ይህን በማድረጋችን ታላቅ በረከት እናጭዳለን። ያዕቆብ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “እነሆ፣ በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን እንላቸዋለን፤ ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታችኋል፣ ጌታም እንደፈጸመለት አይታችኋል፤ ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና።”—ያዕቆብ 5:11
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a እያንዳንዳቸው ያመጡለት “ገንዘብ” (በዕብራይስጥ ቀሳይታህ) መጠኑ ምን ያክል እንደሆነ መገመት አይቻልም። ይሁን እንጂ በያዕቆብ ዘመን “አንድ መቶ ጥሬ ብር” መጠነኛ የሆነ መሬት ይገዛ ነበር። (ኢያሱ 24:32 የ1980 ትርጉም) ስለዚህ እያንዳንዱ ጠያቂ ያመጣለት “ገንዘብ” ቀላል አልነበረም ማለት ነው።
b አህዮቹ እንስት መሆናቸው ተለይቶ የተጠቀሰው ለርቢ ካላቸው ጠቀሜታ አንፃር ሳይሆን አይቀርም።