የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 6/15 ገጽ 3-5
  • ፕላኔቷ ምድር ዕጣዋ ጥፋት ነውን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ፕላኔቷ ምድር ዕጣዋ ጥፋት ነውን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ግልጽ የሆነ “የጥፋት ቀን” መግለጫ
  • የሰው ልጅ የሚያደርሰው ጥፋት ይቀለበሳል
  • ሊሆን የሚችል ነገር ነው
  • ንዑሳን ፕላኔቶችና ጅራታም ኮከቦች፣ ከምድር ጋር መላተም በመገስገስ ላይ ናቸው?
    ንቁ!—1999
  • የቴምዝ ወንዝ የእንግሊዝ ውድ ቅርስ
    ንቁ!—2006
  • የሰው ልጆች ምድርን ለዘለቄታው ያጠፏት ይሆን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2014
  • አምላክ ፕላኔታችን እንደምትተርፍ ቃል ገብቷል
    ንቁ!—2023
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 6/15 ገጽ 3-5

ፕላኔቷ ምድር ዕጣዋ ጥፋት ነውን?

ሀያኛው መቶ ዘመን አብቅቶ 21ኛው መቶ ዘመን የሚጠባበት ጊዜ ተቃርቧል። ብዙውን ጊዜ የጥፋትን ቀን አስመልክቶ ለተነገሩ ትንቢቶች እምብዛም ግድ የሌላቸው ብዙ ሰዎች በዚህ ወቅት ላይ ዓለምን የሚያናውጥ የሆነ ክስተት ይፈጠር ይሆን የሚል ጥያቄ ተፈጥሮባቸዋል።

ስለዚህ ርዕሰ ጉዳይ የሚያትቱ የጋዜጣና የመጽሔት ርዕሶች አልፎ ተርፎም መጽሐፎች ተመልክተህ ይሆናል። በ21ኛው መቶ ዘመን መባቻ ላይ ምን ነገሮች እንደሚከሰቱ በወቅቱ የምናየው ነገር ይሆናል። አንዳንድ ሰዎች የ2000 ዓመት ማብቂያ መድረስ ከአንድ ዓመት ወደ ሌላ ከመሸጋገር (ወይም ከ2000 የመጨረሻ ደቂቃ ወደ 2001 የመጀመሪያ ደቂቃ ከመሸጋገር) በስተቀር ይህን ያህል ትልቅ ለውጥ እንደማያመጣ ይናገራሉ። ብዙዎችን ይበልጥ የሚያሳስበው ነገር የፕላኔታችን የወደፊት ዕጣ ነው።

በአሁኑ ጊዜ በተደጋጋሚ ሲነገር የሚሰማው አንዱ ትንቢት በአጭርም ይሁን በረጅም ጊዜ ውስጥ በሆነ ወቅት ላይ ፕላኔቷ ምድር ሙሉ በሙሉ መጥፋቷ አይቀርም የሚል ነው። ከእንዲህ ዓይነቶቹ ተስፋ አስቆራጭ ትንቢቶች መካከል ሁለቱን ብቻ ተመልከት።

ደራሲውና ፈላስፋው ጆን ሌስሊ በመጀመሪያ በ1996 በታተመው ዚ ኤንድ ኦቭ ዘ ወርልድ​—⁠ዘ ሳይንስ ኤንድ ኤቲክስ ኦቭ ሂውማን ኤክስቲንክሽን በተባለው መጽሐፋቸው ላይ በምድር ላይ ያለው የሰው ሕይወት ሊጠፋ የሚችልባቸውን ሦስት ሁኔታዎች ገልጸዋል። በመጀመሪያ “አጠቃላይ የሆነ የኑክሌር ጦርነት የሰውን ዘር ያጠፋው ይሆን?” የሚል ጥያቄ አቅርበዋል። ከዚያም እንዲህ ሲሉ አክለው ገልጸዋል:- “ለራዲዮ አክቲቭ ጨረር መጋለጥ የሚያስከትላቸው እንደ ካንሰር፣ የተፈጥሮ የሰውነት መከላከያ ኃይል በመዳከሙ ምክንያት የተላላፊ በሽታዎች መዛመት ወይም ደግሞ አካለ ጎዶሎ ሆኖ የመወለድ ችግርን የመሳሰሉ ሁኔታዎች ይበልጥ የሰውን ዘር ከምድር ገጽ ላይ ተጠራርጎ እንዲጠፋ የሚያደርጉት ይመስላል። ለአካባቢ ደህንነት በጣም አስፈላጊ የሆኑ ደቂቅ ዘአካላት ሊሞቱ የሚችሉበት ሁኔታም አለ።” ሚስተር ሌስሊ ያስቀመጡት ሦስተኛው ሁኔታ ደግሞ ምድር በጅራታም ኮከብ ወይም ደግሞ በንዑስ ፕላኔት (asteroid) ልትመታ ትችላለች የሚል ነው:- “አንድ ቀን ምድርን ሊመቱ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ ዲያሜትራቸው ከ1 እስከ 10 ኪሎ ሜትር የሚሆን ወደ ሁለት ሺህ የሚጠጉ ጅራታም ኮከቦችና ንዑስ ፕላኔቶች ሳይኖሩ አይቀሩም። ከእነዚህ በብዛት አነስ ያሉ (ቁጥራቸውን መገመት አዳጋች ነው) ሆኖም ይበልጥ ግዙፍ የሆኑ ጅራታም ኮከቦችና ንዑስ ፕላኔቶች ያሉ ከመሆናቸውም በላይ ከዚህ ይበልጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በመጠን ግን አነስተኛ የሆኑም አሉ።”

ግልጽ የሆነ “የጥፋት ቀን” መግለጫ

አውስትራሊያ ውስጥ በሚገኘው የአዴሌድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ፖል ዴቪስ የተባሉ ሌላ ሳይንቲስት የተናገሩትን ደግሞ ተመልከት። ዋሽንግተን ታይምስ እኚህን ሰው “በዓለም አቀፍ ደረጃ አቻ የማይገኝላቸው የሳይንስ ጸሐፊ” ሲል ጠርቷቸዋል። በ1994 “ስለ ጥፋት ቀን የተጻፉት መጻሕፍት ሁሉ እናት” ተብሎ የተሰየመውን ዘ ላስት ስሪ ሚኒትስ የተባለውን መጽሐፍ ለንባብ አብቅተዋል። የዚህ መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፍ “የጥፋት ቀን” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን አንድ ጅራታም ኮከብ ፕላኔቷን ምድር ቢመታ ምን ሊከሰት እንደሚችል የሚገልጽ ምናባዊ ሐሳብ ይዟል። እኚህ ሰው ከጻፉት እጅግ አስፈሪ የሆነ መግለጫ መካከል ጥቂቱን ተመልከት:-

“ፕላኔቷ ከአሥር ሺህ የምድር ነውጦች ጋር በሚወዳደር ኃይል ትናወጣለች። በኃይል ተገፍትሮ የሚወጣው አየር የሚፈጥረው ክውታዊ ሞገድ (shock wave) ሕንፃዎችን ሁሉ እያፈራረሰና በምድር ገጽ ላይ ያገኘውን ነገር ሁሉ እየጠራረገ ይሄዳል። ጅራታም ኮከቡ በተጋጨበት ቦታ ዙሪያ ያለው ዝርግ መሬት ወደ ላይ ተነስቶ በርካታ ኪሎ ሜትሮች ከፍታ ያላቸው የቀለጡ ተራሮች በመፍጠር የምድርን ከርስ 150 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ገሞራ ቆሬ (crater) ያደርገዋል። . . . ከመሬት ላይ የሚገመሱ ግዙፍ አቧራማ ዓምዶች ከከባቢው አየር ጋር በመቀላቀል መላዋን ፕላኔት ከፀሐይ ብርሃን ይጋርዷታል። ቦታቸውን የለቀቁ ቁሶች እንደገና ከሕዋ ወደ ከባቢ አየር ሲወድቁ የፀሐይ ብርሃን በቢልዮን ከሚቆጠሩ ተወርዋሪ ኮከቦች በሚወጣው ብልጭ ድርግም የሚል ጨረር ይተካና ከበታቹ ያለው መሬት በከፍተኛ የሙቀት ኃይል ይቃጠላል።”

ፕሮፌሰር ዴቪስ በመቀጠል ይህን ምናባዊ ሐሳብ ስዊፍት-ተትል የተባለችው ጅራታም ኮከብ ምድርን ልትመታ ትችላለች ከሚለው ትንበያ ጋር አያይዘውታል። አክለውም ምንም እንኳ እንዲህ ዓይነቱ ክስተት በቅርቡ ላይከሰት ቢችልም “ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ ስዊፍት-ተትል ወይም ሌላ ግዑዝ አካል ምድርን ይመታል” የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሱት በምድር መሳበሪያ ምህዋሮች ላይ የሚዞሩ ግማሽ ኪሎ ሜትር የሚሆን ዲያሜትር ያላቸው 10,000 ግዑዝ አካላት አሉ በሚለው ግምታዊ ሐሳብ ላይ ተመርኩዘው ነው።

እንዲህ ዓይነቱ አስፈሪ ሁኔታ እውን ይሆናል የሚል እምነት አለህ? በጣም ብዙ ሰዎች ይህ ይፈጸማል ብለው ያምናሉ። ሆኖም ይህ ሁኔታ በእኛ ዕድሜ አይከሰትም ብለው ራሳቸውን በማጽናናት ከጭንቀት ነፃ ለመሆን ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ ፕላኔቷ ምድር በቅርቡም ይሁን ከብዙ ሺህ ዓመታት በኋላ ሙሉ በሙሉ የምትጠፋበት ምክንያት ምንድን ነው? በውስጧ ላሉ ነዋሪዎች ማለትም ለሰዎችም ሆነ ለእንስሳት ችግር ዋነኛ መንስኤ ምድር እንዳልሆነች የተረጋገጠ ነው። ይልቁንም ‘የምድርን ሙሉ በሙሉ የመጥፋት’ አደጋ ጨምሮ በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ላሉት ለአብዛኞቹ ችግሮች ተጠያቂው ሰው ራሱ አይደለምን?​—⁠ራእይ 11:​18

የሰው ልጅ የሚያደርሰው ጥፋት ይቀለበሳል

የሰው ልጅ አግባብነት በሌለውና ስግብግብነት በተሞላበት ድርጊት ምድርን ሙሉ በሙሉ ሊያጠፋ ወይም ሊያወድም ስለሚችልበት ሁኔታስ ምን ማለት ይቻላል? ገደብ በሌለው የደን ምንጠራ፣ ከቁጥጥር ውጪ በሆነ የከባቢ አየር ብክለትና በውኃ መስመሮች ላይ በሚደርስ ብክለት ሳቢያ በአንዳንድ የምድር ክፍሎች ከፍተኛ ጥፋት እንደደረሰ ምንም አያጠያይቅም። ይህን ሁኔታ ከዛሬ 25 ዓመት ገደማ በፊት ባርብራ ዋርድና ረኔ ዱቦ የተባሉ ደራሲዎች ኦንሊ ዋን ኧርዝ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ጠቅለል አድርገው ገልጸውታል:- “ልንመረምራቸው የሚገቡ ሦስቱ ሰፊ የብክለት መስኮች ማለትም አየር፣ ውኃና አፈር በፕላኔታችን ላይ ላለው ሕይወት እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ሦስት ዋና ዋና ንጥረ ነገሮች ናቸው።” ሁኔታው አሁንም ቢሆን እንዳልተሻሻለ ግልጽ ነው።

የሰው ልጅ በራሱ አላዋቂነት ምድርን ሊያጠፋ ወይም ሊያወድም የሚችልበትን ሁኔታ ስንመረምር ፕላኔቷ ምድር ያላትን ወደ ቀድሞ ሁኔታዋ የመመለስና ራሷን የማደስ አስደናቂ ችሎታ በማሰብ ልንጽናና እንችላለን። ረኔ ዱቦ ዘ ሬዚሊያንስ ኦቭ ኤኮሲስተምስ በተባለ ሌላ መጽሐፍ ላይ ምድር ያላትን ይህን አስደናቂ የሆነ ራስን የማደስ ችሎታ አስመልክተው ሲገልጹ የሚከተሉትን ግንዛቤዎች ጠቅሰዋል:-

“ብዙ ሰዎች በሥርዓተ ምህዳር ላይ የደረሰው አብዛኛው ጥፋት ሊስተካከል የማይችል በመሆኑ አካባቢያዊ ሁኔታዎች ይበልጥ እየከፉ መሄዳቸው የታወቀው በጣም ዘግይቶ እንደሆነ ይሰማቸዋል። እንደ እኔ እንደ እኔ ከሆነ ግን ይህ አፍራሽ አስተሳሰብ ትክክል አይደለም፤ ምክንያቱም ሥርዓተ ምህዳሮች ከደረሰባቸው አስከፊ ሁኔታ አንሠራርተው ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው የመመለስ ከፍተኛ ኃይል አላቸው።

“ሥርዓተ ምህዳሮች ራሳቸውን በራሳቸው የሚፈውሱባቸው በርካታ መንገዶች አሏቸው። . . . እነዚህ መንገዶች ሥርዓተ ምህዳሮች ቀስ በቀስ ራሳቸውን አድሰው ወደ ቀድሞው ምህዳረ ተማዝኖ (equilibrium) በመመለስ ያጋጠማቸውን እክል እንዲቋቋሙ ያስችሏቸዋል።”

ሊሆን የሚችል ነገር ነው

ለዚህ አንዱ ግሩም ምሳሌ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ቴምዝ እየተባለ በሚጠራው በታወቀው የለንደን ወንዝ ላይ ቀስ በቀስ የተካሄደው የማጥራት ሥራ ነው። በጄፍሪ ሃሪሰንና በፒተር ግራንት የተዘጋጀው ዘ ቴምዝ ትራንስፎርምድ የተባለው መጽሐፍ ሰዎች ለጋራ ጥቅም ተባብረው ሲሠሩ ምን ሊከናወን እንደሚችል የሚያሳየውን ይህን አስደናቂ ክንውን ይገልጻል። የብሪታንያ የኢድንበርግ መስፍን በመጽሐፉ መቅድም ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የቀረበው ታሪክ ከረጅም ጊዜ በኋላ የተገኘ ታላቅ ስኬት ነው፤ በመሆኑም ምንም እንኳ ታሪኩ አንዳንድ ሰዎች የአካባቢ ጥበቃ ችግሮች በፊት ያምኑበት የነበረውን ያህል ከባድ መስሎ እንዳይታያቸው ሊያደርግ ቢችልም መጽሐፉ ታትሞ መውጣቱ ተገቢ ነው። . . . በቴምዝ ወንዝ ላይ የተከናወነው ነገር ትምክህት ሊያሳድርባቸው ይችላል። ሥርዓተ ምህዳር ራሱን ሊያድስ መቻሉና የእነሱም ዕቅድ ሊሰምር የሚችል መሆኑ አስደሳች ዜና ነው።”

ሃሪሰንና ግራንት “ዘ ግሬት ክሊን-አፕ” በሚለው ምዕራፍ ውስጥ ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ ስለተከናወነው ነገር በጋለ ስሜት እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በጣም ተበክሎና በኢንዱስትሪ ዝቃጮች ተመርዞ የነበረ ወንዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቀድሞ ሁኔታው ተመልሶ ዳግመኛ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ወፎችና ዓሦች መኖሪያ ሊሆን ችሏል። መጀመሪያ ላይ ምንም ተስፋ የሌለው ይመስል የነበረው ይህ ለውጥ በፍጥነት ሊከናወን መቻሉ እጅግ ተስፋ ለቆረጠ የዱር አራዊት ጥበቃ ባለሙያ እንኳ አበረታች ነው።”

በመቀጠልም ስለተካሄደው ለውጥ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “የሁለተኛው የዓለም ጦርነት የመጨረሻ መቅሠፍት ሊሆን በሚችለው የፍሳሽ መውረጃዎችና ቱቦዎች መፈራረስ ወይም መውደም ሳቢያ የወንዙ ሁኔታ ቀስ በቀስ ከዓመት ወደ ዓመት እየተበላሸ ሄደ። በ1940ዎቹና በ1950ዎቹ የቴምዝ ሁኔታ እጅግ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። ወንዙ ክፍት ከሆነ የፍሳሽ መውረጃ እምብዛም አይሻልም ነበር፤ ውኃው ከመጥቆሩም በላይ ኦክስጅን አልባ ሆነ፤ በበጋ ወራት ከቴምዝ ወንዝ የሚወጣው መጥፎ ጠረን ከርቀት ይሸታል። . . . ከውኃው በላይ ያለውን አየር በቀጥታ መሳብ ከሚችሉት ኢል ተብለው የሚጠሩ ጥቂት የዓሣ ዘሮች በስተቀር በአንድ ወቅት ወንዙ ውስጥ ይርመሰመሱ የነበሩት ዓሦች ሁሉ ጠፉ። ከለንደን እስከ ዉሊች ያለውን ቦታ ሸፍነው በወንዙ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ወፎች እጅግ ተመናምነው ጥቂት ዳክዬዎችና ነጭ ዝይዎች ብቻ ቀሩ፤ እነርሱም በሕይወት ሊቆዩ የቻሉት ተፈጥሯዊ ምግባቸውን ማግኘት ችለው ሳይሆን በወደቡ መድረክ ላይ የሚፈሱ ጥራጥሬዎችን በመመገብ ነበር። . . . ታዲያ ከዚህ አንጻር ሲታይ ይህ አስደናቂ ለውጥ ይከሰታል ብሎ ማን ሊያምን ይችል ነበር? በአሥር ዓመት ውስጥ የወፍ ዘር ያልነበረበት ይኸው የወንዙ ክልል ተለውጦ በበጋ ወራት በአካባቢው የሚከማቹትን ወደ 10,000 የሚጠጉ ዳክዬዎችና 12,000 የሚሆኑ የውኃ ዳር ወፎች ጨምሮ የብዙ ዓይነት የውኃ ወፎች መጠለያ ሆነ።”

እርግጥ ነው፣ ይህ ሁኔታ በአንድ አነስተኛ የምድር ክፍል ብቻ የተፈጸመውን የለውጥ ሂደት የሚያሳይ ነው። ሆኖም ከዚህ ምሳሌ ብዙ ትምህርት እናገኛለን። ፕላኔቷ ምድር በሰው ልጅ ብልሹ አያያዝ፣ ስግብግብነትና ደንታ ቢስነት የተነሳ ዕጣ ፈንታዋ ጥፋት ብቻ እንደሆነ ተደርጎ መታየት እንደሌለበት ይጠቁመናል። ምድር በስነ ምህዳሯ፣ በከባቢ አየሯና በየብሷ ላይ ይህ ነው የማይባል ጥፋት የደረሰ ቢሆንም ለሰው ዘር የጋራ ጥቅም ሲባል ትክክለኛ ትምህርት መስጠትና ኃይልን አስተባብሮ መሥራት ይህን ጥፋት ለመቀልበስ ሊረዳት ይችላል። ይሁን እንጂ በመዞር ላይ ያለን ጅራታም ኮከብ ወይም ንዑስ ፕላኔት ከመሰሉ ውጫዊ ኃይሎች ሊመጣ ስለሚችል ጥፋት ምን ሊባል ይቻላል?

የሚቀጥለው ርዕስ ለዚህ ግራ የሚያጋባ ጥያቄ አጥጋቢ መልስ ማግኘት የሚቻልበትን ቁልፍ ይዟል።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ምድር ይህ ነው የማይባል ጥፋት የደረሰባት ቢሆንም ትምህርት መስጠትና ኃይልን አስተባብሮ መሥራት ይህን ጥፋት ለመቀልበስ ሊረዳት ይችላል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ