“የአምላክ የሕይወት መንገድ” የተባለው ከ1998-1999 የሚደረግ የአውራጃ ስብሰባ በቅርቡ ይጀምራል!
በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብቻ ከግንቦት እስከ መስከረም ባለው ጊዜ ውስጥ 198 ስብሰባዎች ለማድረግ ዕቅድ ተይዟል። ከእነዚህ የሦስት ቀን ስብሰባዎች አንዱ ከቤትህ ብዙም በማይርቅ ከተማ ውስጥ ይደረግ ይሆናል። በአብዛኛዎቹ ቦታዎች ከአርብ እስከ እሁድ ባሉት ቀናት ስብሰባው ከጠዋቱ 3:30 ላይ በሙዚቃ ይጀመራል።
በአርብ ዕለት ጠዋቱ ፕሮግራም በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ቦታዎች የመንግሥቱ ስብከት ባሳየው እድገት ላይ የሚያተኩር ሪፖርት ይቀርባል። በተጨማሪም “የክርስቶስ ቤዛ—አምላክ ያዘጋጀው የመዳን መንገድ” የተሰኘው ቁልፍ ንግግር የስብሰባውን ጭብጥ ያጎላል።
ከሰዓት በኋላ የሚቀርበው “ወላጆች—በልጆቻችሁ አእምሮ ውስጥ የአምላክ መንገድ እንዲቀረጽ አድርጉ” የተባለው ሲምፖዚየም ልጆች ይሖዋን እንዲወዱና እንዲያገለግሉ እንዴት ማነቃቃት እንደሚቻል ሐሳቦች ያቀርባል። የከሰዓት በኋላው ፕሮግራም የሚደመደመው “ከሞት በኋላ ሕይወት አለን?” በሚል ንግግር ይሆናል።
የቅዳሜ ጠዋቱ ፕሮግራም “ሕይወት በሚያስገኘው መንገድ ላይ እንዲጓዙ ሰዎችን መርዳት፣” “ሰዎችን ለማግኘት ያለው ተፈታታኝ ሁኔታ” እና “ክርስቶስ ያዘዘውን ሁሉ ለደቀ መዛሙርት ማስተማር” በሚሉ ሦስት ተከታታይ ንግግሮች የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑትን ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ ያጎላል። የጠዋቱ ፕሮግራም ማብቂያ ላይ ለአዳዲስ ደቀ መዛሙርት የጥምቀት ዝግጅት ይኖራል።
የቅዳሜ የከሰዓት በኋላው ፕሮግራም የሚጀመረው አምላክን ለማገልገል ያነሳሱንን የግል ምክንያቶቻችንን በጥሞና እንድናስብባቸው በሚያደርገን “ማብቂያ የሌለውን ሕይወት ተስፋ በማድረግ ማገልገል” በተባለው ንግግር ይሆናል። “የአምላክን መንገድ የሚያስተምሩትን ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ በአድናቆት መመልከት” እና “አሮጌውን ሰውነት አውልቆ አዲሱን ሰውነት መልበስ” የተባሉት ንግግሮች ኤፌሶን ምዕራፍ 4ን ጥቅስ በጥቅስ በመመርመር እውቀት ሰጪ ትምህርት ያቀርባሉ። ከዚያ በመቀጠል “ከዓለም እድፍ ምንጊዜም ራሳችሁን ጠብቁ” እና ሦስት ክፍሎች ያሉት “ወጣቶች—የአምላክን መንገድ ተከተሉ” በሚለው ሲምፖዚየም በሚቀርቡት ንግግሮች ላይ ጥሩ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ይቀርባል። የከሰዓት በኋላው ፕሮግራም የሚደመደመው “የፈጣሪ ባሕርያትና መንገዶች” በተባለው ንግግር ይሆናል።
የእሁድ ጠዋት ፕሮግራም ሦስት ክፍሎች ባሉት ሲምፖዚየም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን የሕዝቅኤል መጽሐፍ የመጨረሻ ምዕራፎች ከማብራራቱም በላይ ትንቢታዊ ፍጻሜያቸውንም ያጎላል። የጠዋቱ ፕሮግራም የሚጠናቀቀው በሦስቱ አይሁዳውያን ወጣቶች ታማኝነት ላይ ተመስርቶ በዚያ ዘመን የነበረውን አለባበስና ሁኔታ በሚያንጸባርቅ ድራማ ይሆናል። በከሰዓት በኋላው ክፍለ ጊዜ ጎላ የሚለው የስብሰባው ክፍል “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ብቸኛው መንገድ” በሚል ጭብጥ የሚቀርበው የሕዝብ ንግግር ነው።
በሦስቱም ቀናት በመገኘት በመንፈሳዊ እንደምትበለጽጉ እርግጠኞች ነን። ምንም ክፍያ በማትጠየቁበት በዚህ ስብሰባ ላይ በማንኛውም ክፍለ ጊዜ ብትመጡ በደስታ እንቀበላችኋላን። በአቅራቢያችሁ የሚደረገውን የስብሰባ ቦታ ለማወቅ በአካባቢያችሁ ወዳለው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ሄዳችሁ ጠይቁ ወይም ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች ጻፉ።