ዓለምን የለወጠ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም
የአምላክ ነቢይ የነበረው ሙሴ ከዛሬ 3,500 ዓመታት በፊት መጽሐፍ ቅዱስን መጻፍ ሲጀምር የተጻፈውን ነገር ሊያነብ ይችል የነበረው አንድ አናሳ ብሔር ብቻ ነበር። (ዘዳግም 7:7) ይህም የሆነበት ምክንያት ቅዱሳን ጽሑፎች ይገኙ የነበረው በዚያ ብሔር የመጀመሪያ መነጋገሪያ ቋንቋ በሆነው በዕብራይስጥ ብቻ ስለነበር ነው። ከጊዜ በኋላ ግን ይህ ተለውጧል።
ለብዙ ዘመናት የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ሊስፋፋና በሰዎች ላይ በጎ ተጽእኖ ሊያሳድር የቻለው በአብዛኛው የመጀመሪያ ትርጉሙ በሆነው በሴፕቱጀንት አማካኝነት ነው። ይህ ትርጉም የተዘጋጀው ለምንድን ነው? ደግሞስ ዓለምን የለወጠ መጽሐፍ ቅዱስ ነው ሊባልለት ይችላልን?
በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈ ትርጉም ነው?
ብዙ አይሁዳውያን በሰባተኛውና በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ወደ ባቢሎን በምርኮ ከተወሰዱ በኋላ ከጥንቷ እስራኤልና ይሁዳ ምድር ውጭ መኖራቸውን ቀጥለው ነበር። በግዞት ለተወለዱ አይሁዳውያን ዕብራይስጥ ሁለተኛ ቋንቋቸው ሆነ። በሦስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የግሪክ መንግሥት ዓቢይ የባህል ማዕከል በነበረው በግብጹ እስክንድርያ አንድ የአይሁድ ማኅበረሰብ ይገኝ ነበረ። እነዚህ አይሁዳውያን ቅዱሳን ጽሑፎችን በዚያን ጊዜ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ወደሆነው ወደ ግሪክኛ መተርጎሙ አስፈላጊ መሆኑን ተገነዘቡ።
እስከዚያን ጊዜ ድረስ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ተመዝግቦ ይገኝ የነበረው በዕብራይስጥ ሲሆን የተወሰነ ክፍሉ ደግሞ ከዕብራይስጥ ጋር ተቀራራቢነት ባለው በአረማይክ ቋንቋ የተጻፈ ነበረ። የአምላክን ቃል በተለየ ቋንቋ መግለጹ በመለኮታዊ መንፈስ አነሣሽነት የተጻፈው ቃል ያለውን ኃይል የሚቀንስ ምናልባትም ወደ ተሳሳቱ ፍቺዎች የሚመራ ይሆን? አይሁዳውያን በአደራ የተሰጣቸውን በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈ ቃል በሚተረጉሙበት ጊዜ መልእክቱን ለመለወጥ ሙከራ አድርገው ይሆን?—መዝሙር 147:19, 20፤ ሮሜ 3:1, 2
እነዚህ ጥያቄዎች ስጋት ፈጥረው ነበር። በመጨረሻ ግን ይበልጥ አሳሳቢ ሆኖ የተገኘው አይሁዳውያን የአምላክን ቃል ሊረዱ አይችሉም የሚለው ጉዳይ ነው። የቶራህን ማለትም በሙሴ የተጻፉትን አምስቱን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የያዘ አንድ የግሪክኛ ትርጉም ለማዘጋጀት ተወሰነ። ትክክለኛው የትርጉም ሂደት በአፈ ታሪኮች የተሸፋፈነ ነው። ሌተር ኦቭ አሪስተስ በተባለው ጽሑፍ መሠረት ቶልሚ 2ኛ (285–246 ከዘአበ) የሚባለው ግብጻዊ ገዥ በቤተ መንግሥቱ ቤተ መጻሕፍት የሚቀመጥ አምስቱን የሙሴ መጻሕፍት (ወይም፣ ቶራህ) የያዘ አንድ ቅጂ ፈልጎ ነበር። ሰውየው ከእስራኤል ወደ ግብጽ የመጡ 72 የአይሁድ ምሁራን የትርጉም ሥራውን እንዲሠሩ ያደረገ ሲሆን እነሱም በ72 ቀናት ውስጥ ትርጉሙን አጠናቀቁ። ከዚያም ትርጉሙ ለአይሁድ ማኅበረሰብ ተነበበ፤ ሕዝቡም ውብና ትክክለኛ ትርጉም ነው በማለት ተናገረ። በዚህ ታሪክ ላይ ከጊዜ በኋላ የተጨመሩ ሌሎች ሐሳቦች ተርጓሚዎቹ በተለያየ ክፍል ውስጥ ተቀምጠው እንዲሠሩ የተደረገ ቢሆንም የትርጉም ሥራቸው ቃል በቃል አንድ ዓይነት እንደነበር ይናገራሉ። በትርጉሙ ሥራ የተካፈሉት 72 ተርጓሚዎች በመሆናቸው ይህ ግሪክኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በላቲን ቋንቋ “ሰባ” የሚል ፍቺ ባለው ቃል ላይ የተመሠረተ ሴፕቱጀንት የሚል ስያሜ ተሰጠው።
በዘመናችን የሚገኙ አብዛኞቹ ምሁራን ሌተር ኦቭ አሪስተስ የተባለው ጽሑፍ አዋልድ መጽሐፍ በመሆኑ ይስማማሉ። በተጨማሪም የትርጉም ሥራው ሐሳብ የመነጨው ከቶልሚ 2ኛ ሳይሆን በእስክንድርያ ከሚገኘው የአይሁድ ማኅበረሰብ እንደሆነ ያምናሉ። ሆኖም የእስክንድርያ ተወላጅ የሆነው አይሁዳዊው ፈላስፋ ፊሎና አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ የጻፏቸው ጽሑፎች እንዲሁም ታልሙድ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አይሁዶች የሴፕቱጀንት ትርጉም ከመጀመሪያዎቹ ቅዱሳን ጽሑፎች ጋር በእኩል ደረጃ በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈ ነው የሚል አጠቃላይ የሆነ እምነት እንደነበራቸው ያሳያሉ። የሴፕቱጀንት ትርጉም በዓለም ዙሪያ በሚገኝ የአይሁድ ማኅበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ የተደረገው ጥረት እንዲህ ያለውን እምነት እንዳስገኘ ምንም አያጠራጥርም።
ሥራው ገና ሲጀመር አምስቱን የሙሴ መጻሕፍት ብቻ የያዘ ቢሆንም ሴፕቱጀንት የሚለው ስም ወደ ግሪክኛ የተተረጎመውን አጠቃላዩን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም የሚያመለክት ሆኗል። ቀሪዎቹ መጻሕፍት በቀጣዮቹ መቶ ዓመታት ወይም ከዚያ በሚበልጥ ጊዜ ውስጥ ተተርጉመዋል። አጠቃላዩ የሴፕቱጀንት ትርጉም የጣምራ ጥረት ውጤት ከመሆን ይልቅ የተናጥል ጥረት ውጤት ነው። ተርጓሚዎቹ በችሎታቸውና በዕብራይስጥ ቋንቋ እውቀታቸው ይለያዩ ነበር። አብዛኞቹ መጻሕፍት የተተረጎሙት ቃል በቃል ነው፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ከመጠን በላይ ደረቅ ትርጉሞች ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ነፃ የአተረጓጎም ስልት ይታይባቸዋል። ጥቂት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች በረዣዥምም በአጫጭርም ጥቅሶች ተተርጉመው ይገኛሉ። በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ማብቂያ ላይ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች መጻሕፍት በሙሉ በግሪክኛ ሊነበቡ ይችሉ ነበር። እርስ በርሳቸው የማይስማሙ ሐሳቦች ቢኖሩትም የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ወደ ግሪክኛ መተርጎማቸው ያስገኘው ውጤት ተርጓሚዎቹ ሊጠብቁ ከሚችሉት እጅግ የበለጠ ነበር።
ያፌት በሴም ድንኳን ውስጥ?
ታልሙድ ስለ ሴፕቱጀንት ሲናገር ዘፍጥረት 9:27ን ይጠቅሳል:- ‘ያፌት በሴም ድንኳን ይደር።’ (መጊላህ 9ለ፣ የባቢሎን ታልሙድ) ታልሙድ የሴፕቱጀንት ትርጉም የተጻፈበት የግሪክኛ ቋንቋ ባለው ውበት አማካኝነት ያፌት (የግሪካውያን ዘር መገኛ የሆነው የያዋን አባት) በሴም (በእስራኤላውያን አያት) ድንኳን እንዳረፈ በምሳሌያዊ መንገድ ያሳያል። ይሁን እንጂ የሴፕቱጀንት ትርጉም ሴም በያፌት ድንኳን ውስጥ አረፈ የሚል ሐሳብም ሊያስተላልፍ ይችላል። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
ከታላቁ እስክንድር ድል በኋላ በአራተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የኋለኛ ዓመታት ላይ ድል በተደረጉት አገሮች ውስጥ የግሪክን ቋንቋና ባህል ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት ተደርጎ ነበር። ይህ ፖሊሲ የግሪክን ባህል ማስፋፋት (ሄለናይዜሽን) በመባል ይታወቃል። አይሁዳውያን የማያቋርጥ የባህል ጥቃት እየተፈጸመባቸው እንዳለ ሆኖ ይሰማቸው ነበር። የግሪክ ባህልና ፍልስፍና ከተስፋፋ የአይሁዳውያን ሃይማኖት ይዳከማል። የዚህን ጥቃት መስፋፋት ሊያስቆም የሚችለው ምንድን ነው?
አይሁዳውያን የሴፕቱጀንት ትርጉምን ለማዘጋጀት የተነሳሱበት አንደኛው ምክንያት ምን ሊሆን እንዲሚችል ሲናገሩ አይሁዳዊው የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ ማክስ ማርጎሊስ እንዲህ ብለዋል:- “እቅዱን ያመነጨው የአይሁድ ማኅበረሰብ ነው ካልን ከበስተጀርባው አንድ የተለየ ዓላማ አለው ማለት ነው፤ ይኸውም የአይሁድን ሕግ ለአሕዛብ ማዳረስና አይሁዳውያን ከሄላስ [ከግሪክ] ጋር የሚወዳደር ጥበብ እንዳላቸው የዓለምን ሕዝብ ማሳመን ነው።” በመሆኑም የግሪክኛ ተናጋሪ ሕዝብ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን እንዲያገኝ ማድረጉ በአንድ በኩል ራስን መከላከል ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ መልሶ የማጥቃት ዘመቻ ነበር።
የእስክንድር የግሪክን ባህል የማስፋፋት ፖሊሲ ግሪክኛን ዓለም አቀፋዊ ቋንቋ እንዲሆን አስችሎታል። ሌላው ቀርቶ ግዛቱ በሮማውያን ድል ከተመታ በኋላ እንኳ ተራው ግሪክ (ወይም ኮይነ) በንግድ ልውውጥ ወቅትና በብሔራት መካከል በሚደረግ ግንኙነት የመግባቢያ ቋንቋ ሆኖ ማገልገሉን ቀጥሏል። ይህ ሆን ተብሎ የተደረገ የጥረት ውጤት ይሁን ወይም በራሱ የመጣ፣ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የሴፕቱጀንት ትርጉም በጥቂት ጊዜ ውስጥ ቀደም ሲል ከአምላክና ከአይሁድ ሕግ ጋር ትውውቅ ባልነበራቸው ብዙ አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች ቤትና ልብ ውስጥ ተቀባይነት ሊያገኝ ችሏል። ያስገኛቸውም ውጤቶች አስደናቂ ነበሩ።
እምነታቸውን የለወጡና አምላክን የሚፈሩ
በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ላይ ፊሎ “የሙሴ ሕግ ያለው ውበትና ክብር በአይሁዳውያን ብቻ ሳይሆን በሌሎች ብሔራት ጭምር ከፍተኛ አድናቆት የተቸረው ነበር” በማለት ሊጽፍ ችሏል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከፍልስጤም ውጪ ይኖሩ የነበሩትን አይሁዳውያን በተመለከተ አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ዮሴፍ ክሎስነር እንዲህ ብለዋል:- “እነዚህ በሚልዮን የሚቆጠሩ አይሁዳውያን ከትንሿ የፍልስጤም ምድር ፈልሰው በመምጣት የተሰባሰቡ ናቸው ብሎ ለማመን አስቸጋሪ ነው። ይህ ታላቅ እድገት ሊገኝ የቻለው ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ብዙ ቁጥር ያላቸው ወንዶችና ሴቶች በመኖራቸው ጭምር መሆኑ አይካድም።”
ይሁን እንጂ እነዚህ ማራኪ ሐሳቦች የሁኔታውን ዝርዝር ታሪክ አይገልጹም። የአይሁድ ታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ደራሲው ሼይ ጄ ዲ ኮኸን እንዲህ ብለው ነበር:- “ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ብዙ ወንዶችና ሴቶች ወደ ይሁዲነት የተለወጡት በመጨረሻዎቹ መቶ ዘመናት ከዘአበ እና በመጀመሪያዎቹ ሁለት መቶ ዘመናት እዘአ ላይ ነበር። ይሁን እንጂ ከአይሁድ እምነት የተወሰኑ ትምህርቶችን ቢቀበሉም ሙሉ በሙሉ ወደ ይሁዲነት ያልተለወጡ ከዚያ የሚበልጥ ቁጥር ያላቸው አሕዛብ ነበሩ።” ክሎስነርም ሆነ ኮኸን እነዚህን ያልተለወጡ ሰዎች ለማመልከት አምላክን የሚፈሩ ሰዎች የሚለውን መግለጫ ይጠቀሙ የነበረ ሲሆን መግለጫውም በዚያን ጊዜ በነበረው የግሪክ ስነ ጽሑፍ ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜ ይጠቀስ ነበር።
ወደ ይሁዲነት በተለወጠና አምላክን በሚፈራ ሰው መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ሙሉ በሙሉ የተቀየሩ ነበሩ፤ የእስራኤልን አምላክ በመቀበላቸው (ሌሎችን አማልክት በመተው)፣ የግዝረትን ሥርዓት በመፈጸማቸውና ከእስራኤል ብሔር ጋር በመቀላቀላቸው በማንኛውም መንገድ አይሁዳዊ ተደርገው ይቆጠሩ ነበር። በአንፃሩ ግን ኮኸን አምላክን የሚፈሩ ሰዎች ስለተባሉት ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል:- “እነዚህ አሕዛብ በርካታ የአይሁድ ልማዶችን ቢጠብቁም እንዲሁም በአንድ መልኩም ሆነ በሌላ ለአይሁድ አምላክ ክብር ቢሰጡም ራሳቸውን እንደ አይሁዳዊ አይቆጥሩም ነበር፣ ሌሎችም እንደ አይሁዳዊ አድርገው አይመለከቷቸውም ነበር።” የአይሁድ እምነትን ተቀብለው “የወጉን የተወሰነ ክፍል ቢጠብቁም . . . ሙሉ በሙሉ ወደ ይሁዲነት ስላልተለወጡ” ክሎስነር እነዚህን ሰዎች “መሃል ሰፋሪዎች” ብለዋቸዋል።
አንዳንዶች በሚስዮናዊ እንቅስቃሴ ላይ ከነበሩ አይሁዳውያን ጋር ውይይት ማድረጋቸው ወይም አይሁዳውያን በአኗኗር፣ በባህልና በጠባይ የተለዩ መሆናቸውን መመልከታቸው ስለ አምላክ ለማወቅ ፍላጎት እንዲያድርባቸው አድርጓቸው ሊሆን ይችላል። ሆኖም እነዚህ አምላክን የሚፈሩ ሰዎች ስለ ይሖዋ አምላክ ይበልጥ ለመማር የረዳቸው ዋነኛ መሣሪያ ሴፕቱጀንት ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አምላክን የሚፈሩ ሰዎችን ትክክለኛ አኃዝ ለማወቅ የሚቻልበት መንገድ ባይኖርም ሴፕቱጀንት በመላው የሮማ ግዛት ውስጥ ስለ አምላክ የተወሰነ እውቀት እንዲስፋፋ ምክንያት የነበረ መሆኑ ምንም አያጠያይቅም። በተጨማሪም በሴፕቱጀንት አማካኝነት አንድ አስፈላጊ መሠረት ተጥሏል።
ሴፕቱጀንት መንገድ ጠራጊ በመሆን አገልግሏል
ሴፕቱጀንት የክርስትናን መልእክት በማዳረሱ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ በዓል የክርስቲያን ጉባኤ ሲቋቋም ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑ አይሁዳውያን በብዛት ተገኝተው ነበር። በእነዚያ ቀደምት ጊዜያት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ከሆኑት መካከል ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎችም ይገኙበት ነበር። (ሥራ 2:5–11፤ 6:1–6፤ 8:26–38) የኢየሱስ ሐዋርያትና ሌሎች ቀደምት ደቀ መዛሙርት በመንፈስ አነሣሽነት የጻፏቸው ጽሑፎች ብዙ አንባብያንን ለማትረፍ የታለሙ ስለነበሩ የተጻፉት በግሪክኛ ነበር።a ስለዚህ በግሪክኛ የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተጠቅሰው የሚገኙ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የተወሰዱ በርካታ ጥቅሶች የተመሠረቱት በሴፕቱጀንት ትርጉም ላይ ነበር።
በተፈጥሮ አይሁዳውያን ከሆኑትና ወደ ይሁዲነት ከተለወጡት ሰዎች በተጨማሪ የመንግሥቱን መልእክት ለመቀበል ዝግጁ የሆኑ ሌሎች ሰዎችም ነበሩ። ከአሕዛብ ወገን የሆነው ቆርኔሌዎስ “ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ለሕዝብም እጅግ ምጽዋት የሚያደርግ ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ የሚጸልይ ነበረ።” በ36 እዘአ ቆርኔሌዎስ፣ ቤተሰቡና በቤቱ የተሰበሰቡ ሌሎች ሰዎች የክርስቶስ ተከታዮች በመሆን የተጠመቁ የመጀመሪያዎቹ አሕዛብ ናቸው። (ሥራ 10:1, 2, 24, 44–48፤ ከሉቃስ 7:2–10 ጋር አወዳድር።) ሐዋርያው ጳውሎስ በትንሿ እስያና በግሪክ በተዘዋወረበት ጊዜ አምላክን ይፈሩ ለነበሩ ብዙ አሕዛብና ‘አምላክን ለሚያመልኩ የግሪክ ሰዎች’ ሰብኳል። (ሥራ 13:16, 26፤ 17:4) ቆርኔሌዎስና ሌሎች አሕዛብ ምሥራቹን ለመቀበል ዝግጁዎች የነበሩት ለምንድን ነው? የሴፕቱጀንት ትርጉም መንገድ ጠራጊ በመሆን አገልግሏል። አንድ ምሁር ሴፕቱጀንት “ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው መጽሐፍ ነው፤ ምክንያቱም ያለዚህ ትርጉም የሕዝበ ክርስትናም ሆነ የምዕራቡ ዓለም ባህል መኖር የማይታሰብ ነገር ይሆን ነበር” ሲሉ ገምተዋል።
ሴፕቱጀንት “በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈ” መባሉ አቆመ
የሴፕቱጀንት ትርጉም በስፋት ጥቅም ላይ መዋሉ በአይሁዳውያን ዘንድ ጠንካራ ተቃውሞ አስነሳ። ለምሳሌ ያህል አይሁዳውያን ከክርስቲያኖች ጋር በሚያደርጉት ውይይት ላይ ሴፕቱጀንት የተሳሳተ ትርጉም ነው ብለው መናገር ጀመሩ። በሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ የአይሁድ ማኅበረሰብ በአንድ ወቅት በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈ ነው ብሎ ላወደሰው ትርጉም ሙሉ በሙሉ ጀርባውን ሰጠ። ረቢዎች ስለ 72ቱ ተርጓሚዎች የሚናገረውን ታሪክ እንዲህ በማለት ውድቅ አደረጉት:- “አንድ ጊዜ አምስት ሽማግሌዎች ለንጉሥ ቶልሚ ቶራህን ጻፉለት፤ ቶራህ በትክክል ሊተረጎም ስለማይችል እነዚህ ሰዎች ቶራህን የተረጎሙበት ቀን የወርቁ ጥጃ እንደተሠራበት ዕለት ለእስራኤል መጥፎ ገድ ያመጣ ቀን ነበረ።” ረቢዎች ከራሳቸው አመለካከት ጋር በጥብቅ የሚስማማ እንዲሆን ሲሉ አዲስ የግሪክኛ ትርጉም እንዲዘጋጅ አደረጉ። የትርጉም ሥራው የተካሄደው በሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ፣ አቂላ በተባለ ወደ ይሁዲነት በተለወጠና የረቢ አኪባ ደቀ መዝሙር በነበረ ሰው ነው።
አይሁዳውያን በሴፕቱጀንት መጠቀም ቢያቆሙም ብቅ ማለት ለጀመረው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ “ብሉይ ኪዳን” ሆኖ ያገለገለ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ግን በጀሮም የተዘጋጀው የላቲን ቨልጌት ይበልጥ ተቀባይነት እያገኘ ሄዷል። ምንም እንኳ አንድ ትርጉም እንደ ዋናው ቅጂ ባይሆንም ሴፕቱጀንት ስለ ይሖዋ አምላክና በኢየሱስ ክርስቶስ ስለምትመራው መንግሥቱ የሚናገረውን እውቀት በማስፋፋት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። በእርግጥም ሴፕቱጀንት ዓለምን የለወጠ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የማቴዎስ ወንጌል በመጀመሪያ የተጻፈው በዕብራይስጥ ሳይሆን አይቀርም። ከዚያ ወዲህ የግሪክኛ ቅጂ ተዘጋጅቷል።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጳውሎስ የሰበከላቸው ብዙ ሰዎች የ“ሴፕቱጀንት” ትርጉምን ይረዱት ነበር
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Courtesy of Israel Antiquities Authority