ከፍተኛ እንቅስቃሴ ወደሚደረግበት መስክ መግባት
“ምንም የፉክክር መንፈስ አልነበረም። ሁሉም ሌላው ተሳክቶለት ለማየት ይፈልግ ነበር” በማለት ራይካርድና ሉሲያ አብረዋቸው ይማሩ ስለነበሩት የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የ105ኛው ክፍል ተማሪዎች ተናግረዋል። “ሁላችንም በጣም የተለያየን ነን፤ ሆኖም ለእኛ እያንዳንዱ ተማሪ ብርቅ ነው።” አብሯቸው ይማር የነበረው ሎዌል በዚህ ሐሳብ በመስማማት “ልዩነቶቻችን እርስ በርስ አቀራርበውናል” በማለት አክሎ ተናግሯል።
መስከረም 12, 1998 የተመረቀው ክፍል በእርግጥም የተለያዩ ተማሪዎችን ያቀፈ ነበር። አንዳንዶቹ ተማሪዎች የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች በአቅኚነት አገልግለዋል፤ ሌሎቹ በአገራቸው ውስጥ በታማኝነት ሲያገለግሉ ነበር። እንደ ማትስና ሮዝ-ማሪ ያሉ ጥቂት ተማሪዎች ደግሞ ወደ ትምህርት ቤት ከመምጣታቸው በፊት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታቸውን ለማሻሻል ለረዥም ጊዜያት ጠንክረው መሥራት አስፈልጓቸዋል። ብዙዎቹ ተማሪዎች ስለ ሚስዮናዊነት አገልግሎት ማሰብ የጀመሩት ልጆች እያሉ ነበር። አንድ ባልና ሚስት 12 ጊዜ አመልክተዋል፤ በ105ኛው ክፍል ገብተው እንዲማሩ ጥሪ ሲደርሳቸው ምንኛ ተደስተው ነበር!
ሃያ ሳምንታት የፈጀው ጥልቅ ጥናት የተደረገበት ሥልጠና ባንዴ ተጠናቀቀ። ተማሪዎቹ የምረቃው ቀን መቅረቡን ያስተዋሉት በጽሑፍ የሚሠሩትን የመጨረሻ ፈተናና የመጨረሻውን የቃል ሪፖርት ሲያቀርቡ ነበር።
የፕሮግራሙ ሊቀ መንበር የነበረው የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል የሆነው አልበርት ሽሮደር የክፍሉ ተማሪዎች ቀደም ሲል ከጊልያድ ተመርቀው የወጡትን ከ7,000 የሚበልጡ ሌሎች ተማሪዎች በመከተል “የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለመስጠት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ወደሚደረግበት መስክ” ሊገቡ መሆኑን አስታውሷቸዋል። በዚህ የበጋ ወቅት በብሔራት አቀፍ የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት የመጡት ለረዥም ዓመታት ያገለገሉ ሚስዮናውያን የዓለም አቀፉን ዋና መሥሪያ ቤት በጎበኙበት ወቅት ተማሪዎቹ ከእነርሱ ጋር የመተዋወቅ ልዩ አጋጣሚ ማግኘታቸውን ገልጿል።
ከዚያም ወንድም ሽሮደር የቤቴል ሥራዎች አስተባባሪ ኮሚቴ አባል የሆነውን ማክስ ላርሰንን አስተዋወቀ። ወንድም ላርሰን “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትምህርት” የሚል ጭብጥ ያለው ንግግር አቀረበ። “ጠቢብ እነዚህን ከመስማት ጥበብን ይጨምራል፣ አስተዋይም መልካም ምክርን [“ጥበብ ያለበት መመሪያን፣” NW] ገንዘቡ ያደርጋል” የሚለውን ምሳሌ 1:5ን ጠቀሰ። ውጤታማ ሚስዮናዊ ለመሆን ጥበብ የግድ አስፈላጊ ነው። ጠቢብ የሆኑ ሰዎች በነገሥታት ፊት ይቆማሉ። (ምሳሌ 22:29) ከአምስት ወራት ሥልጠና በኋላ ተማሪዎቹ ታላላቅ ነገሥታት የሆኑትን ይሖዋ አምላክንና ክርስቶስ ኢየሱስን ለመወከል በሚገባ የታጠቁ ሆነዋል።
በአገልግሎት ክፍል ውስጥ የሚሠራው ዴቪድ ኦልሰን “የይሖዋን ልብ ደስ ለማሰኘት የበኩላችሁን አድርጉ” በሚል ርዕስ ቀጥሎ ተናገረ። እንዲህ ብሎ ጠየቀ:- “ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች የአምላክን ልብ ደስ ለማሰኘት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?” መልሱ? በጽናት፣ በታማኝነትና በደስታ ሊያገለግሉት ይችላሉ። ይሖዋ ሕዝቦቹ በሚያቀርቡለት አገልግሎት እንዲደሰቱ ይፈልጋል። የአምላክን ፈቃድ በደስታ የምናደርግ ከሆነ ልቡን ደስ እናሰኛለን። (ምሳሌ 27:11) ወንድም ኦልሰን ከጊልያድ 104ኛው ክፍል የተመረቁ ሚስዮናውያን ባልና ሚስት የጻፉትን ደብዳቤ አነበበ። በአዲሱ ምድባቸው ተደስተው ይሆን? ጉባኤያቸውን በተመለከተ የጻፉት እንዲህ ይላል:- “140 የሚያክሉ አስፋፊዎች ሲኖሩን በአማካይ ከ250 እስከ 300 የሚሆን የተሰብሳቢዎች ቁጥር አለን። ይበልጥ የሚያስደስተው የመስክ አገልግሎት ነው። እያንዳንዳችን አራት ጥናቶች አሉን፤ አንዳንዶቹም ወደ ስብሰባዎች መምጣት ጀምረዋል።”
የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ላይመን ስዊንግል “ቆም ብላችሁ በረከቶቻችሁን የምታስቡበት ጊዜ” በሚል ርዕስ ንግግር አቀረበ። በጊልያድ የተሰጣቸው ሥልጠና ብዙ በረከቶች አስገኝቶላቸዋል። ተማሪዎቹ እውቀታቸው እንዲጨምር፣ ለይሖዋ ድርጅት ያላቸው አድናቆት እንዲያድግና እንደ ትሕትና ያሉትን ተፈላጊ ባሕርያት እንዲኮተኩቱ ረድቷቸዋል። ወንድም ስዊንግል “እዚህ መምጣትና የሚሰጠውን ትምህርት ለማዳመጥ ጊዜን መሠዋት ትሕትናን የሚጠይቅ ነው” ካለ በኋላ “ከዚህ የምትሄዱት ይሖዋን ከፍ ከፍ ለማድረግ በተሻለ ሁኔታ ታጥቃችሁ ነው” ሲል አክሏል።
“ደስታችሁ እንዴት ታላቅ ነው—ታዲያ ለምን ትጨነቃላችሁ?” የሚለው ደግሞ የአስተዳደር አካል በሆነው በዳንኤል ሲድሊክ የቀረበው ንግግር ጭብጥ ነበር። ችግሮች ሲከሰቱ መመሪያ ለማግኘት ቅዱሳን ጽሑፎችን አገላብጡ ሲል አጥብቆ አሳሰበ። ወንድም ሲድሊክ ከማቴዎስ 6ኛ ምዕራፍ የተመረጡ ጥቅሶችን በመጠቀም ይህን እንዴት ማድረግ እንደሚቻል አሳየ። የእምነት ማጣት እንደ ምግብና ልብስ ባሉ ተራ ነገሮች እንድንጨነቅ ሊያደርገን ይችላል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ምን እንደሚያስፈልገን ያውቃል። (ማቴዎስ 6:25, 30) መጨነቅ እያንዳንዱ ቀን በሚያመጣው ችግር ላይ ሌላ ችግር ከመጨመር በስተቀር ምንም የሚፈይደው ነገር የለም። (ማቴዎስ 6:34) በሌላ በኩል ግን እቅድ ማውጣት አስፈላጊ ነው። (ከሉቃስ 14:28 ጋር አወዳድር።) “ኢየሱስ የከለከለው ስለ ወደፊቱ ጊዜ ጥበብ ባለበት መንገድ ማሰብን ሳይሆን ተገቢ ያልሆነ ጭንቀትን ነው” በማለት ወንድም ሲድሊክ አብራራ። “ጭንቀትን ለማስወገድ ከሁሉ የተሻለው ፈውስ ድርጊት ነው። በምንጨነቅበት ጊዜ ስለ እውነት መናገር ብንጀምር ይጠቅመናል።”
አስተማሪዎቻቸው የሰጧቸው የመሰነባበቻ ምክር
ቀጥሎ ሦስት የጊልያድ ትምህርት ቤት አስተዳደር አባላት ንግግር አቀረቡ። ካርል አዳምስ “ለይሖዋ ምን ትመልሱለታላችሁ?” በሚል ርዕስ በመጀመሪያ ተናገረ። ንግግሩ የተመሠረተው በ116ኛው መዝሙር ላይ ሲሆን ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ የዘመረው መዝሙር ሳይሆን አይቀርም። (ማቴዎስ 26:30፣ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) ኢየሱስ “ስላደረገልኝ ሁሉ ለእግዚአብሔር ምንን እመልሳለሁ?” የሚሉትን ቃላት ሲዘምር እያሰበው የነበረው ነገር ምንድን ነው? (መዝሙር 116:12) ይሖዋ ስላዘጋጀለት ፍጹም አካል አስቦ ይሆናል። (ዕብራውያን 10:5) በሚቀጥለው ቀን የፍቅሩን ጥልቀት ለማሳየት ያን አካሉን መሥዋዕት አድርጎ ሊያቀርብ ነበር። የ105ኛው ክፍል ተማሪዎች የይሖዋን ጥሩነት ባለፉት አምስት ወራት አጣጥመዋል። አሁን በሚስዮናዊ ምድባቸው ጠንክረው በመሥራት ለአምላክ ያላቸውን ፍቅር ሊያሳዩ ነው።
ቀጥሎ ንግግር የሰጠው የጊልያድ አስተማሪ ማርክ ኑሜር “ትክክል የሆነውን ማድረጋችሁን ቀጥሉ” በማለት ተማሪዎቹን መክሯል። ዮሴፍ በግብጽ ባሪያ እንዲሆን ከተሸጠ በኋላ ለ13 ዓመታት ያህል የደረሰበትን ግፍ በጽናት ተቋቁሟል። ሌሎች የፈጸሟቸው ስህተቶች አምላክን ከማገልገል እንዲታቀብ አድርገውታልን? አላደረጉትም፤ ትክክል የሆነውን ማድረጉን ቀጥሎ ነበር። ከዚያም አምላክ በወሰነው ጊዜ ዮሴፍ ከመከራው ነፃ ወጣ። በአንድ ጊዜ ከእስር ቤት ወደ ቤተ መንግሥት ኑሮ ተሸጋገረ። (ዘፍጥረት ምዕራፍ 37–50) አስተማሪው ተማሪዎቹን እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው:- “የሚስዮናዊ ምድባችሁ እንደጠበቃችሁት ሆኖ ባታገኙት የሚስዮናዊነት አገልግሎታችሁን ታቆማላችሁ? ለተስፋ መቁረጥ ስሜት እጃችሁን ትሰጣላችሁ? ወይስ ዮሴፍ እንዳደረገው ትጸናላችሁ?”
በመጨረሻ የጊልያድ ትምህርት ቤት ሬጂስትራር የሆነው ዋላስ ሊቭረንስ “ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ” በሚለው ጭብጥ ላይ ከክፍሉ አባላት ጋር ደስ የሚል ውይይት አደረገ። አንዳንዶቹ ተማሪዎች ከቤት ወደ ቤት፣ ከሱቅ ወደ ሱቅና በመንገድ ላይ ሲሰብኩ ያጋጠማቸውን ተሞክሮ ተናገሩ። ሌሎች የተለየ ቋንቋ ለሚናገሩ ሰዎች ለመመሥከር ስላደረጉት ጥረት ተናገሩ። ሌሎች ደግሞ የተለያየ ሃይማኖት ላላቸው ሰዎች እንዴት መመሥከር እንደሚቻል አሳይተዋል። ሁሉም ምሩቃን በሚስዮናዊ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተካፋይ ለመሆን ጓጉተው ነበር።
ለረዥም ጊዜ ያገለገሉ ደስተኛ ሚስዮናውያን
“ከሚስዮናዊ አገልግሎት የተገኙ አስደሳች ውጤቶች” የሚለው የሚቀጥለው ክፍል በሮበርት ዎለን የቀረበ ሲሆን በቅርቡ የብዙ ዓመታት ተሞክሮ ካካበቱ ሚስዮናውያን ጋር ገንቢ የሆነ ቅርርብ ፈጥረው ከነበሩ በዋናው መሥሪያ ቤት ውስጥ ከሚገኙ አራት ወንድሞች ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስን የያዘ ነው። ሚስዮናውያኑ አዲስ ቋንቋ መማሩና ከሌላ ባህል ወይም ከተለየ የአየር ሁኔታ ጋር መላመዱ ቀላል ሆኖ እንዳላገኙት በግልጽ ተናግረዋል። የቤተሰብ ናፍቆትንም መቻል ነበረባቸው። አንዳንድ ጊዜ የጤና እክል ያጋጥማቸው ነበር። ያም ሆኖ ግን ሚስዮናውያኑ ምንጊዜም አዎንታዊ አመለካከት ነበራቸው፤ ጥረታቸውም ተባርኳል። አንዳንዶቹ ብዙ ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁ ረድተዋል። ሌሎች ባሉባቸው አገሮች ውስጥ የሚካሄደው የመንግሥቱ ሥራ ጭማሪ እንዲያገኝ በተለያዩ መስኮች እርዳታ አበርክተዋል።
የመጨረሻው ተናጋሪ የአስተዳደር አባል የሆነው ኬሪ ባርበር ነበር። “የአምላክ የሕይወት መንገድ” የተሰኘውን የአውራጃ ስብሰባ ፕሮግራም ጎላ ጎላ ያሉ ነጥቦች ከለሰ። “የአውራጃ ስብሰባው ፕሮግራም ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ዝምድና እንዴት ነክቶታል?” ሲል አድማጮቹን ጠየቀ። ተናጋሪው የአምላክን መንገድ መከተል የሚያስገኛቸውን በረከቶች የዓለምን መንገድ የሚከተሉ ሰዎች ከሚደርስባቸው አሰቃቂ ጥፋት ጋር አነጻጸረ። ሙሴ በመሪባ የሠራውን ስህተት በማውሳት እንዲህ ሲል አስጠነቀቀ:- “ሌላው ቀርቶ አንድ ሰው ለብዙ ዓመታት በታማኝነት ሲያገለግል የቆየ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ ትክክለኛ ሕጎቹ በትንሹም ቢሆን ሲጣሱ ዝም ብሎ አይመለከትም።” (ዘኁልቁ 20:2–13) በየትም ቦታ የሚገኙ የአምላክ አገልጋዮች ያሏቸውን ውድ የአገልግሎት መብቶች አጥብቀው ይያዙ!
ተማሪዎቹ ዲፕሎማቸውን የሚረከቡበት ጊዜ ደረሰ። ከዚያም አንድ የክፍሉ ተወካይ ተማሪዎቹ ላገኙት ስልጠና ያላቸውን አድናቆት የሚገልጽ ደብዳቤ አነበበ። የመደምደሚያ መዝሙር ከተዘመረና ልባዊ ጸሎት ከቀረበ በኋላ የምረቃው ፕሮግራም ተጠናቀቀ። ይሁን እንጂ ለ105ኛው ክፍል ተማሪዎች ይህ መጀመሪያቸው ብቻ ነበር፤ ምክንያቱም አዲሶቹ ሚስዮናውያን “ከፍተኛ እንቅስቃሴ ወደሚደረግበት መስክ” ገና መግባታቸው ነው።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ስለ ተማሪዎቹ የቀረበ አኃዛዊ መረጃ
ሚስዮናውያኑ የተውጣጡባቸው አገሮች:- 9
የተመደቡባቸው አገሮች ብዛት:- 17
የተማሪዎቹ ብዛት:- 48
ባልና ሚስት የሆኑ:- 24
አማካይ ዕድሜ:- 33
በእውነት ውስጥ የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 16
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 12
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን መርጠዋል
“ወጣት በነበርኩበት ጊዜ አቅኚ የመሆን ዓላማ አልነበረኝም” ይላል ቤን የተባለው የ105ኛው ክፍል ተመራቂ። “ልዩ ችሎታ ያላቸውና ሁኔታዎች የተመቻቹላቸው ሰዎች ብቻ አቅኚ መሆን ይችላሉ የሚል አመለካከት ነበረኝ” በማለት አክሎ ተናግሯል። “ነገር ግን ለመስክ አገልግሎት ፍቅር እያደረብኝ ሄደ። ከዚያም አንድ ቀን አቅኚ መሆን ማለት እኮ በአገልግሎቱ የበለጠ ተሳትፎ ማድረግ ማለት ነው የሚል ሐሳብ ብልጭ አለልኝ። አቅኚ መሆን እንደምችል ያስተዋልኩት በዚህ ጊዜ ነበር።”
ሉሲያ “በቤታችን የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ከፍ ተደርገው ይታዩ ነበር” በማለት ትናገራለች። ሚስዮናውያን እሷ ያለችበትን ጉባኤ ለመጎብኘት በሚመጡበት ጊዜ ጉባኤው ምን ያህል ይደሰት እንደነበር ታስታውሳለች። “ትልቅ ሰው ስሆን ከእቅዶቼ አንዱ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንደሚሆን የታወቀ ነበረ” ብላለች።
ቲየዲስ እናቱ የሞተችው በ15 ዓመቱ ነበር። “በወቅቱ ጉባኤው በሚገባ ረድቶኝ ነበር” ብሏል። “ስለዚህ ‘አድናቆቴን ለማሳየት ምን ማድረግ እችላለሁ?’ ስል ራሴን ጠየቅሁ።” ይህ በመጀመሪያ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት፣ አሁን ደግሞ ወደ ሚስዮናዊ ሥራ እንዲገባ አድርጎታል።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የተመረቁ የ105ኛው ክፍል ተማሪዎች
ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ለእያንዳንዱ ረድፍ ተራ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደ ኋላ ሲሆን ስሞቹ የሰፈሩት ከግራ ወደ ቀኝ ነው
(1) ሳምፕሰን ኤም፣ ብራውን አይ፣ ሄግሊ ጂ፣ ኤቡየን ኢ፣ ዴብዋ ኤም፣ ፑርቲዬ ፒ (2) ካሳም ጂ፣ ሊንበርግ አር፣ ዳፑዞ ኤ፣ ቴይለር ሲ፣ ለፌቭር ኬ፣ ዎከር ኤስ (3) ቤከር ኤል፣ ፔለስ ኤም፣ ቮገን ኢ፣ ቦዬን ሲ፣ አስፕለንድ ጄ፣ ኃይሌ ጄ (4) ፑርቲዬ ቲ፣ ዊቴከር ጄ፣ ፓልመር ኤል፣ ኖርተን ኤስ፣ ጌሪንግ ኤም፣ ኃይሌ ደብልዩ (5) ዎከር ጄ፣ ቦዬን ኤ፣ ግሩንቬልድ ሲ፣ ዋሺንግተን ኤም፣ ዊቴከር ዲ፣ ኤቡየን ጄ (6) ጌሪንግ ደብልዩ፣ ዋሺንግተን ኬ፣ ፔለስ ኤም፣ ዴብዋ አር፣ ሄግሊ ቲ፣ አስፕለንድ ኤ (7) ቮገን ቢ፣ ለፌቭር አር፣ ቴይለር ኤል፣ ብራውን ቲ፣ ግሩንቬልድ አር፣ ፓልመር አር (8) ኖርተን ፒ፣ ሳምፕሰን ቲ፣ ቤከር ሲ፣ ሊንበርግ ኤም፣ ካሳም ኤም፣ ዳፑዞ ኤም