በገና በዓል ላይ ክርስቶስ ተረስቷል!
“የገና በዓል አከባበር ፈጽሞ ሊዋጥልኝ ያልቻለ ነገር ነው። ክብረ በዓሉ ከኢየሱስ ሕይወትና ትምህርት ጋር ጭራሽ የማይጣጣም ሆኖ ነው ያገኘሁት።”—ሞሃንዳስ ኬ ጋንዲ
ብዙዎች በጋንዲ አባባል አይስማሙ ይሆናል። ‘ደግሞ አንድ ሂንዱ የአገር መሪ ስለ ክርስትና በዓል ምን ያውቃልና ነው?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። ሆኖም የገና በዓል በሁሉም ዓይነት ባሕል ላይ ተጽዕኖ በማሳደር በዓለም ዙሪያ መሰራጨቱን አምኖ መቀበል ያስፈልጋል። በየዓመቱ በታኅሣሥ ወር የገና በዓል በሁሉም ባሕሎች ውስጥ የሚገኝ ይመስላል።
ለምሳሌ ያህል ወደ 145 ሚልዮን የሚጠጉ እስያውያን ገናን ያከብራሉ። ይህ ቁጥር የዛሬ አሥር ዓመት ከነበረው በ40 ሚልዮን ጨምሯል። ጋንዲ የበዓሉ “አከባበር” ብለው ሲናገሩ ዘመናዊው የገና በዓል ያለውን ዓለማዊ ገጽታ ማለትም በበዓሉ ሰሞን በገበያ ቦታዎች ስለሚታየው ትርምስ መናገራቸው ከነበረ ይህ የበዓሉ ገጽታ በአመዛኙ ጎላ ብሎ የሚታይ መሆኑን መካድ በጣም ያዳግታል። ኤዥያዊክ የተባለው መጽሔት እንዲህ ይላል:- “ሆንግ ኮንግ ውስጥ በዓሉን ለማድመቅ የሚበሩትን መብራቶች፣ በቤጂንግ ሆቴሎች ውስጥ የሚቆሙትን የገና ዛፎችና በሲንጋፖር መሃል ከተማ የሚገኙትን የኢየሱስን ልደት የሚያሳዩትን ምስሎች ጨምሮ በእስያ የሚከበረው የገና በዓል ባመዛኙ ሃይማኖታዊ ያልሆነ (አብዛኛውን ጊዜ ንግድ የሚጧጧፍበት) ወቅት ነው።”
በዘመናዊው የገና በዓል አከባበር ክርስቶስ እየተረሳ ነውን? የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ኢየሱስ የተወለደበት ቀን ሃይማኖታዊ በዓል ተደርጎ እንዲከበር ከወሰነችበት ከአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ አንስቶ ታኅሣሥ 25 በይፋ ሲከበር ቆይቷል። ይሁን እንጂ በቅርቡ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የተሰበሰበ የሕዝብ አስተያየት እንደሚያመለክተው የገና በዓል ዋና ገጽታ የክርስቶስ ልደት እንደሆነ የሚሰማቸው 33 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው።
አንተስ ምን ትላለህ? የማያባሩ የንግድ ማስታወቂያዎች፣ ናላ በሚያዞረው የስጦታዎች ግዢ፣ ዛፎችን ማስጌጥ፣ ግብዣዎችን ማዘጋጀትና በግብዣዎች ላይ መገኘት፣ የእንኳን አደረስዎ ካርዶች መላላክ፤ በዚህ ሁሉ መሃል አንዳንድ ጊዜ በሆነ መንገድ ኢየሱስ ከጉዳዩ እንደተረሳ ተሰምቶህ ያውቃል?
ብዙዎች በገና በዓል ላይ ክርስቶስ እንዲታወስ ማድረግ የሚቻልበት አንዱ መንገድ የልደቱን ሁኔታ የሚያሳዩ ምስሎችን በመደርደር እንደሆነ የሚሰማቸው ይመስላል። ሕፃኑ ኢየሱስ በግርግም ውስጥ ሆኖ ማርያም፣ ዮሴፍ፣ እረኞች፣ “ሦስት ጠቢባን” ወይም “ሦስት ነገሥታት፣” የተወሰኑ ከብቶችና ተመልካቾች ከበውት የሚያሳይ ምስል ሳትመለከት አትቀርም። እነዚህ ምስሎች ስለ ትክክለኛው የገና በዓል ትርጉም ሰዎችን ለማስታወስ ይረዳሉ የሚል የተለመደ አስተሳሰብ አለ። ዩ ኤስ ካተሊክ የተባለው መጽሔት “ስለ ክርስቶስ ልደት የሚያሳየው ምስል የወንጌል ታሪኮችን ተረት ተረት ገጽታ ቢያጎላም እንኳ ከየትኛውም ወንጌል በተሻለ ሁኔታ ሰፋ ያለ ግንዛቤ ያስጨብጣል” ሲል ገልጿል።
ይሁን እንጂ የክርስቶስን ልደት የሚያሳየው ምስል የመጽሐፍ ቅዱስን የወንጌል ታሪኮች ተረት ተረት የሚያስመስለው እንዴት ነው? በሚያምር ሁኔታ የተቀቡ ትንንሽ ምስሎች የክርስቶስን ልደት የአፈ ታሪክነት ወይም የተረትነት መንፈስ እንዲኖረው እንደሚያደርጉ አይካድም። በ13ኛው መቶ ዘመን በአንድ መነኩሴ የተዘጋጀው የክርስቶስን ልደት የሚያሳየው የመጀመሪያ ምስል ብዙ የተንዛዛ አልነበረም። ከዚህ በዓል ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ሌሎች በርካታ ነገሮች ሁሉ የክርስቶስን ልደት የሚያሳይ ምስልም ዛሬ ትልቅ ንግድ ሆኗል። በኢጣሊያ ኔፕልስ ውስጥ ዓመቱን በሙሉ የክርስቶስን ልደት ለማመልከት የሚያገለግሉ ምስሎችን ወይም ፕሬዤፒ የሚሸጡ በርካታ ሱቆች አሉ። አንዳንዶቹ ይበልጥ ታዋቂ የሆኑት ምስሎች በወንጌል ትረካዎች ውስጥ የሚገኙ ገጸ ባሕርያትን ሳይሆን እንደ ልዕልት ዳያና፣ ማዘር ተሬሳ እና የልብስ ፋሽን አዘጋጅ የሆነው ጂያኒ ቬርሳቼ የመሳሰሉትን የወቅቱን እውቅ ግለሰቦች የሚወክሉ ናቸው። በሌሎች ቦታዎች ደግሞ ፕሬዤፒ ከቼኮሌት፣ ከፓስታ ሌላው ቀርቶ ከባሕር ሼሎች ይሠራል። ይህን በመሰሉ መግለጫዎች ታሪክን መገንዘብ ለምን አስቸጋሪ እንደሚሆን መረዳት ትችላለህ።
ታዲያ የኢየሱስን ልደት የሚያሳዩ ምስሎች “ከየትኛውም ወንጌል ይበልጥ ሰፋ ያለ ግንዛቤ ሊያስጨብጡ የሚችሉት” እንዴት ነው? የወንጌል ዘገባዎች እውነተኛ ታሪኮች አይደሉምን? ሌላው ቀርቶ በጣም ተጠራጣሪ የሆኑ ሰዎች እንኳ ኢየሱስ በገሃዱ ዓለም የነበረ በታሪክ የሚታወቅ ሰው መሆኑን ሊክዱ አይችሉም። በመሆኑም በአንድ ወቅት በተጨባጭ በሚታወቅ ቦታ የተወለደ ሕፃን መሆን አለበት። በክርስቶስ ልደት አካባቢ ስለተከናወኑ ነገሮች ሰፋ ያለ ግንዛቤ ለማግኘት የልደቱን ገጽታ ያሳያል በሚባል ምስል ብቻ ከመወሰን የተሻለ መንገድ መኖር አለበት!
ደግሞም አለ። ሁለት ታሪክ ጸሐፊዎች የኢየሱስን ልደት አስመልክቶ በተናጥል ጽፈዋል። አንዳንድ ጊዜ በገና በዓል ወቅት ክርስቶስ እየተረሳ እንዳለ ከተሰማህ እነዚህን ዘገባዎች ለምን አትመረምራቸውም? በውስጣቸው የምታገኘው ተረት ወይም አፈ ታሪክ ሳይሆን አስደናቂ የሆነውን ትክክለኛ የክርስቶስን ልደት ታሪክ ነው።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ከገጽ 3–6, 8 እና 9 በሕዳጉ ላይ የሚገኙት ሥዕሎች:- Fifty Years of Soviet Art