ትልቅ ግምት የሚሰጠውን ሺህ ዓመት ለመቀበል ተዘጋጁ!
የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ለሰብዓዊው ቤተሰብ በቃላት ተዘርዝረው የማያልቁ በረከቶችን ያመጣል። በኢየሱስ ፍቅራዊ አመራር የሰው ልጅ አሁን ካለበት አሳዛኝ ሁኔታ ተላቅቆ ክብራማ ወደሆነ የፍጽምና ደረጃ ይደርሳል። ይህ ለአንተ ምን ማለት እንደሚሆን አስበው። ፍጹም ጤንነት! በእያንዳንዱ ዕለት ጧት ከእንቅልፍ ስትነቃ ከፊተኛው ቀን የተሻለ ጤንነት ይሰማሃል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃነት በዚያ አስደሳች ጊዜ ለመኖር በጉጉት ይጠባበቃሉ። በትምክህት ይጠባበቁታል፤ ስለዚያ ጊዜም ይጸልያሉ። እነዚህን በረከቶች አግኝተው ሊደሰቱ እንደሚችሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸው ተረድተዋል።
ይሁን እንጂ ኢየሱስ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛቱን ከመጀመሩ በፊት አገዛዙን የሚቃወሙትን በሙሉ ከምድር ላይ ማጥፋት አለበት። ይህን የሚያደርገው መጽሐፍ ቅዱስ አርማጌዶን በማለት በሚጠራው ጦርነት ነው። (ራእይ 16:16) በምድር ላይ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች በዚህ ጦርነት አይዋጉም። ይህ የአምላክ ጦርነት ነው። እንዲሁም በአንድ የምድር ክፍል የሚወሰን አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ከምድር ዳር ጀምሮ እስከ ምድር ዳር ድረስ እንደሚሆን ይናገራል። የክርስቶስን አገዛዝ የሚቃወሙ ሁሉ ይጠፋሉ። አንዳቸውም አያመልጡም!—ኤርምያስ 25:33
ከዚያም ኢየሱስ ትኩረቱን ወደ ሰይጣን ዲያብሎስና አጋንንቱ ያዞራል። የራእይ መጽሐፍ ጸሐፊ የተመለከተውን ነገር በዓይነ ሕሊናህ ለመመልከት ሞክር:- “የጥልቁንም መክፈቻና ታላቁን ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ [ኢየሱስ ክርስቶስ] ከሰማይ ሲወርድ አየሁ። የቀደመውንም እባብ ዘንዶውን እርሱም ዲያብሎስና ሰይጣን የተባለውን ያዘው፣ ሺህ ዓመትም አሰረው።” (ራእይ 20:1, 2) በኋላም ሰይጣንና አጋንንቱ ለዘላለም ይጠፋሉ።—ማቴዎስ 25:41
“አንድ እንኳ ሊቈጥራቸው የማይችል . . . እጅግ ብዙ ሰዎች” ከአርማጌዶን በሕይወት ያልፋሉ። (ራእይ 7:9) አንድ እረኛ በጎቹን ሕይወት አድን ወደሆነው ውኃ እንደሚመራቸው ሁሉ ክርስቶስም እነዚህን ሰዎች ‘ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭ’ በመምራት ሙሉ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። (ራእይ 7:17) እነዚህ የአርማጌዶን ተራፊዎች ሰይጣንና አጋንንቱ መንፈሳዊ እድገት እንዳያደርጉ ስለማያግዷቸው ቀስ በቀስ ኃጢአተኛ ዝንባሌዎቻቸውን አስወግደው በመጨረሻ ፍጽምና ላይ እንዲደርሱ የሚያስችላቸውን እርዳታ ያገኛሉ!
በክርስቶስ ፍቅራዊ አገዛዝ ሥር የኑሮ ሁኔታዎች እየተሻሻሉ መሄዳቸውን ይቀጥላሉ። ይሖዋ አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ሥቃይና ሐዘን የሚያመጡ ነገሮችን በሙሉ ያስወግዳል። “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም።” (ራእይ 21:4) ነቢዩ ኢሳይያስ ሁኔታውን ጠቅለል አድርጎ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “በዚያን ጊዜም የዕውሮች ዓይን ይገለጣል የደንቆሮችም ጆሮ ይከፈታል። በዚያን ጊዜ አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘልላል፣ የድዳም ምላስ ይዘምራል።” (ኢሳይያስ 35:5, 6) እንዲሁም ‘ታናናሾችና ታላላቆች’ ሙታን ዳግም ያለመሞትን ተስፋ ይዘው ሕያው ይሆናሉ!—ራእይ 20:12
ዛሬም ቢሆን ከአርማጌዶን በሕይወት የሚተርፉት “እጅግ ብዙ ሰዎች” እየተሰበሰቡ ናቸው። ለክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት በመዘጋጀት ላይ ናቸው። ይህ አገዛዝ መቼ እንደሚጀምር ባያውቁም አምላክ በወሰነው ጊዜ እንደሚመጣ እርግጠኞች ናቸው። ከእነሱ መካከል ልትሆን ትችላለህ፤ ሆኖም መዘጋጀት አለብህ። ዝግጅቱ ግን ንብረትህን ሸጠህ ወደ አንድ ቦታ መሄድ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ያለ ምንም ክፍያ ወይም ግዴታ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህ አንተንም ሆነ ቤተሰብህን እንዴት ሊጠቅም እንደሚችል ሊያሳዩህ ፈቃደኞች ናቸው። የዚህ መጽሔት አሳታሚዎችም ተጨማሪ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኞች ናቸው።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሺህ ዓመት ሲባል ቃል በቃል ነው ወይስ በምሳሌያዊ መንገድ?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የራእይ መጽሐፍ በአብዛኛው የተጻፈው በምሳሌያዊ መግለጫ ስለሆነ አንድ ጥያቄ ይነሳል። በራእይ ውስጥ ስለተገለጸው የክርስቶስ የሺህ ዓመት አገዛዝስ ምን ማለት ይቻላል? ይህን የምንረዳው ቃል በቃል ነው ወይስ በምሳሌያዊ መንገድ?
ቃል በቃል የሺህ ዓመት ጊዜን እንደሚያመለክት የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች አሉ። ለምሳሌ:- ሐዋርያው ጳውሎስ የሰው ልጆች የሚፈረዱበትን የክርስቶስ የሺህ ዓመት አገዛዝ እንደ አንድ ቀን አድርጎ ገልጾታል። (ሥራ 17:31፤ ራእይ 20:4) ሐዋርያው ጴጥሮስ አንድ ሺህ ዓመት በይሖዋ ዘንድ እንደ አንድ ቀን (24 ሰዓታት) መሆኑን ጽፏል። (2 ጴጥሮስ 3:8) ይህም ያ የፍርድ “ቀን” ቃል በቃል የአንድ ሺህ ዓመት ጊዜን መሆኑን ያስረዳል። ከዚህም በተጨማሪ በራእይ 20:3, 5-7 ላይ በሦስት የተለያዩ ቦታዎች ላይ “ሺህ ዓመት” ሳይሆን ‘ይህ ሺህ ዓመት’ ተብሎ ተጠቅሶ እናገኛለን። ይህም የተወሰነ መጠን ርዝማኔ ያለውን ጊዜ የሚያመለክት ይመስላል።