ጊልያድ ሚስዮናውያንን ‘እስከ ምድር ዳር ድረስ’ ይልካል
የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት ከግማሽ ምዕተ ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ሚስዮናውያንን እያሰለጠነ ሲልክ ቆይቷል። መስከረም 11, 1999 የጊልያድ 107ኛው ክፍል ተማሪዎች ተመርቀዋል። ክፍሉ ከ11 አገሮች የመጡ 48 ተማሪዎች የነበሩት ሲሆን እነርሱም በ24 የተለያዩ አገሮች እንዲያገለግሉ ተመድበዋል። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት የተናገራቸውን የመጨረሻ ቃላት በመፈጸም ረገድ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ከሚገኙት በሺህ ከሚቆጠሩ ሌሎች ሚስዮናውያን ጋር ተቀላቅለዋል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ‘እስከ ምድር ዳር ድረስ ምስክሮቹ’ እንደሚሆኑ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር።—ሥራ 1:8
ዙሪያው ማራኪ በሆኑ መስህቦች በተከበበው ኒው ዮርክ ፓተርሰን በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ትምህርት ማዕከል የተደረገው ይህ የምረቃ ሥነ ሥርዓት በእርግጥም ታላቅ ወቅት ነበር። ተመራቂዎቹ ተማሪዎች ዘመዶቻቸው፣ የቅርብ ጓደኞቻቸውና እንግዶች በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ በመገኘታቸው በጣም ተደስተው ነበር። ብሩክሊን እና ዎል ኪል በሚገኘው ሕንፃ ውስጥ ሆነው ፕሮግራሙን በምስልና በድምፅ የተከታተሉትን ጨምሮ በጠቅላላው 4,992 የሚሆኑ ሰዎች ፕሮግራሙን ተከታትለዋል።
ይሖዋንና ሰዎችን በታማኝነት ማገልገል
“የይሖዋ ወገን የሆነ ማን ነው?” የአስተዳደር አካል አባልና የምረቃው ሥነ ሥርዓት ሊቀ መንበር የነበረው ካሪ ባርበር ያቀረበው የመክፈቻ ንግግር ጭብጥ ይህ ነበር። በሙሴ ዘመን በነበሩት እስራኤላውያን ፊት ይህ ጥያቄ ተደቅኖ እንደነበር አብራራ። ብዙዎቹ እስራኤላውያን በታማኝነት ከይሖዋ ጎን ባለመቆማቸው ምክንያት እዚያው ምድረ በዳ እንዳሉ ሕይወታቸውን እንዳጡ ለተመራቂ ተማሪዎቹና በሥነ ሥርዓቱ ላይ ለተገኙት ሁሉ አስገነዘበ። ለጣዖት አምልኮ ከተንበረከኩ በኋላ “ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፣ ሊዘፍኑም ተነሡ።” (ዘጸአት 32:1-29) ኢየሱስ ክርስቲያኖች ተመሳሳይ አደጋ ሊደርስባቸው እንደሚችል ሲያስጠነቅቅ እንዲህ ብሏል:- “ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ፣ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋልና።”—ሉቃስ 21:34-36
ቀጥሎ ንግግሩን ያቀረበው በጽሑፍ ክፍል የሚሠራው ጀን ስማሊ ሲሆን እርሱም “ፓርጎሪክ መሆናችሁን ታስመሰክራላችሁን?” በማለት ለተመራቂ ተማሪዎቹ ጥያቄ አቀረበ። ሕመምን ለማስታገስ የሚሰጡ መድኃኒቶችን ለማመልከት ፓራጎሪያ የሚለው የግሪክኛ ቃል በእንግሊዝኛ ጥቅም ላይ መዋል እንደጀመረ ተናገረ። ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ የሥራ ባልደረቦቹን ለማመልከት በቆላስይስ 4:11 ላይ ይህን ገላጭ ግሪክኛ ቃል ተጠቅሟል። በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ይህ ቃል “የብርታት ምንጭ” ተብሎ ተተርጉሟል።
ተመራቂዎቹ ሚስዮናውያን ተመድበው በሚሄዱበት ቦታ ለሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች የብርታት ምንጭ በመሆንና ከሌሎች ሚስዮናዊ ባልደረቦቻቸው ጋር በትብብርና በፍቅር በመሥራት ዘመናዊዎቹ ፓርጎሪክስ መሆን ይችላሉ።
የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ዳንኤል ሲድሊክ “ልንፈጽመው የሚገባን ወርቃማው ሕግ” በሚል ርዕስ ቀጣዩን ንግግር አቀረበ። ኢየሱስ “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው” በማለት በማቴዎስ 7:12 ላይ የተናገረው ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው መሠረታዊ ሥርዓት የሚያመለክተው በሌሎች ላይ ጎጂ ነገሮችን ከማድረግ መቆጠብን ብቻ ሳይሆን በጎ የሆኑ ነገሮችን ማድረግን የሚያበረታታ ነው።
ይህንንም በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን ሦስት ነገሮች ያስፈልጋሉ። የሚያይ ዓይን፣ ርኅሩኅ ልብና የእርዳታ እጅ። በመደምደሚያውም ላይ “የመርዳት ፍላጎት ሲሰማን ወዲያው የእርዳታ እጃችንን መዘርጋት ይኖርብናል። ሰዎች እንዲያደርጉልን የምንፈልጋቸውን ነገሮች ለሌሎች ለማድረግ ተጨማሪ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል” በማለት ተናግሯል። በተለይ ደግሞ ይህ ሰዎች እውነተኛውን ክርስትና በተግባር እንዲያሳዩ ለመርዳት ወደ ሌሎች አገሮች ለሚሄዱ ሚስዮናውያን በትክክል የሚሠራ ነው።
አስተማሪዎቹ የሰጡት ቀስቃሽ ማሳሰቢያ
የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ካርል አዳምስ ተመራቂ ሚስዮናውያኑ “ማደጋቸውን እንዲቀጥሉ” ማበረታቻ ሰጣቸው። በምን አቅጣጫ? በመጀመሪያ በእውቀትና ይህንንም እውቀት ጥሩ አድርጎ በመጠቀም ረገድ እንዲያድጉ አበረታታቸው። ተማሪዎቹ ጊልያድ በነበሩበት ወቅት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ታሪኮችን ሁኔታና መቼት ለማግኘት እንዴት ምርምር ማድረግ እንደሚቻል ተምረዋል። እያንዳንዱ ታሪክ ሕይወታቸውን እንዴት እንደሚነካ እንዲያስቡ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። ይህንንም ያለማቋረጥ እንዲያደርጉ ማበረታቻ ተሰጣቸው።
“ሁለተኛ፣ በፍቅር ማደጋቸውን እንዲቀጥሉ ማበረታቻ ተሰጣቸው። ፍቅር ገንቢ የሆነ ነገር ሲያገኝ እያደገ ይሄዳል። ቸል ከተባለ ደግሞ እየሞተ ይሄዳል” በማለት ወንድም አዳምስ ተናግሯል። (ፊልጵስዩስ 1:9) አሁን ሚስዮናውያን እንደመሆናቸው መጠን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው በፍቅር ማደግ ይኖርባቸዋል። እንዲሁም በሦስተኛ ደረጃ “በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እደጉ።” (2 ጴጥሮስ 3:18) “ይህም ይሖዋ በልጁ በኩል ያሳየን እጅግ ግሩም የሆነ የደግነት መግለጫ ነው” በማለት ተናጋሪው ገለጸ። “ለዚህ ይገባናል ለማንለው ደግነት ያለን አድናቆት እያደገ ሲሄድ የአምላክን ፈቃድ በማድረግና የተሰጠንን የሥራ ምድብ በመፈጸም የምናገኘውን ደስታ ከፍ ያደርግልናል።”
ማርክ ኒውመር የተባለ ሌላ የጊልያድ አስተማሪ “ተፈታታኝ ሁኔታዎችን በፍቅር ከተወጣችኋቸው መጽናት ትችላላችሁ” በሚል ጭብጥ ንግግር አቀረበ። እንዲህ በማለት ምክሩን ለገሰ:- “በሚስዮናዊ ሕይወታችሁ የሚያጋጥሟችሁን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በፍቅር ማለፍ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ከተገነዘባችሁ መጽናት ትችላላችሁ። ይሖዋ የሚገሥጸው የሚወደውን ብቻ ነው። አንዳንድ ጊዜ የሚሰጣችሁ ተግሣጽ ጥበብ በጎደለው መንገድ፣ ጥቃቅን በሆኑ ነገሮች ወይም ተገቢ ባልሆነ መንገድ እንደሆነ ሆኖ ቢሰማችሁም እንኳ ለይሖዋ ያላችሁ ፍቅርና ከእርሱ ጋር ያላችሁ ዝምድና ምክሩን እንድትቀበሉ ይረዳችኋል።”
ወንድም ኒውመር ሚስዮናዊ አገልግሎት በርካታ ተግባር ማከናወንን የሚያጠቃልል እንደሆነም ጠቁሟል። “ይሁን እንጂ አንድ ተግባር በፍቅር ካልተሠራ እርካታ ያሳጣል። ፍቅር ካጣችሁ እንደ ምግብ ማብሰል፣ መገብየት፣ ፍራፍሬ ማጠብ፣ ውኃ ማፍላትን የመሳሰሉ የቤት ውስጥ ሥራዎች አሰልቺ ሊሆኑባችሁ ይችላሉ። ለአንድ አፍታ ቆም ብላችሁ ‘እነዚህን ሥራዎች የማከናውነው ለምንድን ነው?’ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። ‘የማደርገው ጥረት ሚስዮናዊ ባልደረቦቼ ጤነኞችና ደስተኞች እንዲሆኑ አስተዋጽዖ የሚያበረክት ነው’ የሚል መልስ ለራሳችሁ ከሰጣችሁ ሥራውን ለማከናወን አትቸገሩም።” ሲያጠቃልልም የሚከተለውን ምክር ለገሰ:- “ምክር መቀበልም ይሁን በሚስዮናዊነት የገባችሁትን ቃል መጠበቅ ወይም አለመግባባቶችን መፍታት ሁሉንም በፍቅር ማድረጋችሁ በተሰማራችሁበት የሥራ ምድብ መጽናት እንድትችሉ ይረዳችኋል። ‘ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም።’”—1 ቆሮንቶስ 13:8
ቀጥሎ ተማሪዎቹ በአካባቢው ከነበሩ ጉባኤዎች ጋር ባገለገሉበት ወቅት ያገኟቸውን የሚያስደስቱ በርካታ ተሞክሮዎች በሠርቶ ማሳያ ሲያቀርቡ ውይይቱን የመራው የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ዋለስ ሊቨራንስ ነበር። በሚስዮናዊነት ያገኙትን ሥልጠና ከቤት ወደ ቤት ሲሄዱ ብቻ ሳይሆን ትልልቅ መኪናዎች በሚቆሙባቸው ቦታዎች፣ በልብስ ንጽሕና መስጫዎች፣ በባቡር ጣቢያዎችና በሌሎች ቦታዎች ሰዎችን አግኝተው ለማነጋገር ተጠቅመውበታል።
ተሞክሮ ያካበቱ ሚስዮናውያን የሰጡት ማረጋገጫ
አዳዲስ ሚስዮናውያን ወደ ባዕድ አገር በሚሄዱበት ጊዜ ምን እንሆን ይሆን ብለው መጨነቅ ይኖርባቸዋልን? በተመደቡበት አገር የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ችግሮች መወጣት ይችሉ ይሆን? ለሚሄዱባቸው አገሮች ባዕድ የሆኑት እነዚህ ሚስዮናውያን ስኬታማ ይሆኑ ዘንድ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ምን እርዳታ ያበረክቱላቸዋል? ለእነዚህና ለሌሎች ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት በአገልግሎት ክፍል ውስጥ የሚሠራው ስቲቨን ሌት እና በጽሑፍ ክፍል የሚሠራው ዴቪድ ስፕሌን በመጠበቂያ ግንብ ትምህርት ማዕከሉ ውስጥ በሚገኘው የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት ትምህርት ቤት ይካፈሉ ለነበሩ ወንድሞች ቃለ መጠይቅ አደረጉላቸው። ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው እነዚህ ወንድሞች በስፔይን፣ በሆንግ ኮንግ፣ በላይቤሪያ፣ በቤኒን፣ በማዳጋስካር፣ በብራዚልና በጃፓን የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው።
ከእነዚህ ተሞክሮ ያካበቱ የይሖዋ አገልጋዮች መካከል ብዙዎቹ ለአሥርተ ዓመታት ሚስዮናዊ ሆነው ያገለገሉ ሲሆኑ ለተመራቂ ተማሪዎቹም ሆነ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ለተገኙት ወላጆቻቸውና ዘመዶቻቸው መንፈስን የሚያረጋጉ ቃላት ሰንዝረዋል። ከራሳቸውና ከሌሎች ሚስዮናዊ ባልደረቦቻቸው ተሞክሮ በመነሳት ችግሮችና የሚያስጨንቁ ሁኔታዎችን ስኬታማ በሆነ መንገድ መወጣት እንደሚቻል ገልጸዋል። የገጠሟቸው ችግሮች ተራራ መሰል ሊሆኑ ቢችሉም “ሊፈቱ የሚችሉ ናቸው፤ ማኅበሩም ከጎናችን ነው” በማለት በማዳጋስካር ሚስዮናዊ ሆኖ የሚያገለግለው ራይሞ ኮውካኔን አስተያየቱን ሰጥቷል። በአሁኑ ወቅት በብራዚል እያገለገለ ያለው ኦስተን ገስታቭሶን “የሚሰጠንን የሥራ ምድብ የምንመርጠው ራሳችን አይደለንም” በማለት ተናግሯል። “ስለዚህ የተሰጠንን የሥራ ምድብ የሙጥኝ ብለን ለመያዝ ወሰንን።” በጃፓን የሚያገለግለው ጄምስ ሊንተን “ቀደም ሲል ሚስዮናዊ ሆነው እንዲያገለግሉ ተመድበው ከነበሩት ወንድሞች ጋር መገናኘቱ” እንደረዳው ተናግሯል። የሚስዮናዊነት አገልግሎት በደስታና በተሟላ መንገድ ይሖዋን ለማገልገልና በጎቹን ለመንከባከብ የሚያስችል ዝግጅት ነው።
መንፈሳዊነትን ከሚገድል መቅሰፍት ራስን መጠበቅ
በ1946 ከጊልያድ ሰባተኛው ክፍል የተመረቀውና የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ቴዎዶር ጃራዝ “በመንፈሳዊ ሕያው ሆኖ ለመኖር የሚደረግ ፍልሚያ” በሚል ጭብጥ የመደምደሚያውን ንግግር አቀረበ። በመጀመሪያ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች እየተከሰቱ ያሉትን ሰቅጣጭ ሁኔታዎች ከጠቀሰ በኋላ በሰው ዘር ላይ አስከፊ መቅሰፍቶች እየደረሱ መሆኑን አመለከተ።
ወንድም ጃራዝ መዝሙር 91ን ጠቅሶ በአካባቢያችን የሚኖሩትን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በመንፈሳዊ በማሳመምና በመግደል ላይ የሚገኙት “ቸነፈር” [NW] እና “አደጋ” ምን እንደሆኑ ለይቶ ጠቀሰ። ዲያብሎስና የእርሱ ክፉ ሥርዓት ለትምህርት ያደሩ በመሆንና በፍቅረ ነዋይ ላይ የተመረኮዙ ቸነፈር መሰል ፕሮፓጋንዳዎቻቸውን መንፈሳዊነትን ለማዳከም ይጠቀሙባቸዋል። ሆኖም ይህ ቸነፈር ‘በልዑል መጠጊያ ውስጥ እየኖረ ወዳለ’ ሰው ዘንድ አይቀርቡም።—መዝሙር 91:1-7
“ፈታኝ የሆነው ነገር በእምነት ጤናማ ሆኖ መቀጠልና ደህንነት ባለበት ቦታ ለዘለቄታው መኖር መቻሉ ነው” በማለት ወንድም ጃራዝ ተናግሯል። “‘መንፈሳዊነት እንደጎደላቸው’ ዘባቾች መሆን አንፈልግም። ሆኖም በአሁኑ ጊዜ ያለው ችግር ይህ ነው። በድርጅቱ ውስጥ ታቅፈን ባለነው ላይ የተጋረጠው አንዱ ችግር ይሄ ነው። ሚስዮናዊ ሆናችሁ በምታገለግሉባቸው ቦታዎችም እንዲህ ያለው ችግር ሊገጥማችሁ ይችላል።” (ይሁዳ 18, 19) ሆኖም ተመራቂዎቹ ሚስዮናውያን በተመደቡበት ቦታ መንፈሳዊነታቸውን ጠብቀው ለማቆየት በሚያደርጉት ፍልሚያ አሸናፊ መሆን እንደሚችሉ ተገልጾላቸዋል። እገዳ፣ ኃይለኛ ተቃውሞ፣ ፌዝ፣ አምላክ የለሽ የሆኑ ሰዎች የሚያሰራጩት ፕሮፓጋንዳና የሃሰት ክሶችን በጽናት እየተቋቋሙ ያሉትን እንደ ሩስያ፣ እስያና አፍሪካ ባሉ አገሮች የሚኖሩ ወንድሞቻችንን እንዲያስቡ ማበረታቻ ተሰጣቸው። እንዲሁም በተደጋጋሚ ጊዜያት የሚነሱ የጎሳ ግጭቶችና መሠረታዊ የሆኑ ነገሮች እጥረት አካላዊ ችግሮች ሊያስከትሉ ይችላሉ።
መንፈሳዊነት እያሽቆለቆለ ሲሄድ “የችግሩን መነሾ ለማወቅ መጣርና ከዚያም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙ ምክሮችን በመጠቀም ችግሮቹን ለማስወገድ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ነው።” መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌዎች ቀርበው ነበር። ኢያሱ የሕግ ቅጂውን በየቀኑ ድምፁን እያሰማ እንዲያነብ ማበረታቻ ተሰጥቶታል። (ኢያሱ 1:8) የሕጉ መጽሐፍ በኢዮስያስ ዘመን በተገኘ ጊዜ ሕዝቡ በሕጉ ውስጥ የሚገኙትን መመሪያዎች በታማኝነት በሥራ ላይ ለማዋል ያደረጉትን ጥረት ይሖዋ ባርኮላቸዋል። (2 ነገሥት 23:2, 3) ጢሞቴዎስ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ቅዱሳን ጽሑፎችን ያውቅ ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15) የቤሪያ ሰዎች በጥሞና በማዳመጥ ብቻ የተወሰኑ አልነበሩም፤ ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ ይመረምሩ ስለነበር “ልበ ሰፊዎች” እንደሆኑ ተደርገው ተቆጥረዋል። (ሥራ 17:10, 11) እንዲሁም የአምላክን ቃል ጠንቅቆ በማወቅና በመጠቀም ረገድ ከሁሉ የላቀው ምሳሌ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።—ማቴዎስ 4:1-11
በመጨረሻም ወንድም ጃራዝ በሚስዮናዊነት ለመሰማራት የተዘጋጁትን ተመራቂዎች እንዲህ በማለት ሞቅ ባለ ስሜት አጥብቆ መከራቸው:- “አሁን የሚስዮናዊነት አገልግሎታችሁን ለማከናወን ተዘጋጅታችኋል። እንዲሁም ወደ ውጭ አገር፣ ቃል በቃል ወደተለያዩ የምድር ክፍሎች ልትሄዱ ነው። በመንፈሳዊ ሕያው ሆነን ለመኖር በምናደርገው ፍልሚያ አሸናፊዎች ከሆን ሐሳባችንን በመከፋፈል በቁርጠኝነት የተነሳንለትን ሥራ ዳር እንዳናደርስ እንቅፋት ሊሆኑብን ለሚችሉ ነገሮች እጃችንን አንሰጥም። በቅንዓት ልትሰብኩ ነው፣ ሌሎች እምነታችሁን እንዲመስሉ ልታነሳሱ ነው። ይሖዋ እኛን ሕያው እንዳደረገን ሁሉ የምትሰብኩላቸውንም ሰዎች ሕያው እንዲያደርግላችሁ አብረናችሁ እንጸልያለን። በዚህ መንገድ በርካታ ተጨማሪ ሰዎች በመላው ዓለም ተስፋፍቶ ከሚገኘው መንፈሳዊ መቅሰፍት ይተርፋሉ። የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ከእኛ ጋር ይተባበራሉ። ይህንን ዳር ለማድረስ በምታደርጉት ጥረት ይሖዋ እንዲባርካችሁ እንመኛለን።”
ሊቀ መንበሩ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ከተለያዩ አገሮች የተላኩ ሰላምታዎችን ካነበበ በኋላ ለምሩቃን ተማሪዎቹ ዲፕሎማ የሚሰጥበት ጊዜ ደረሰ። ከዚያም ተማሪዎቹ ያዘጋጁት ልብን በደስታ የሚያሞቅ የአድናቆት ደብዳቤ ተነበበ። ተማሪዎቹ ልዩ ሥልጠና በማግኘታቸውና ‘እስከ ምድር ዳር ድረስ’ በመሄድ በሚስዮናዊነት የማገልገል መብት በማግኘታቸው ለይሖዋና ለድርጅቱ ጥልቅ የአመስጋኝነት ስሜት አድሮባቸዋል!—ሥራ 1:8
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ስለ ተማሪዎቹ የቀረበ አኃዛዊ መረጃ
ሚስዮናውያኑ የተውጣጡባቸው አገሮች:- 11
የተመደቡባቸው አገሮች ብዛት:- 24
የተማሪዎቹ ብዛት:- 48
ባልና ሚስት የሆኑ:- 24
አማካይ ዕድሜ:- 34
በእውነት ውስጥ የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 17
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 12
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የተመረቁ የ107ኛው ክፍል ተማሪዎች
ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ለእያንዳንዱ ረድፍ ተራ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደ ኋላ ሲሆን ስሞቹ የሰፈሩት ከግራ ወደ ቀኝ ነው።
1. ፔራልታ ሲ፣ ሆለንቤክ ቢ፣ ሾው አር፣ ሃሳን ኤን፣ ማርቲን ዲ፣ ሃቺንሰን ኤ። 2. ኤድዋርድስ ኤል፣ ቪዝር ቲ፣ ሴሩቲ ኪው፣ ኤንትዝሚንገር ጂ፣ ዳሎይዝ ኤል፣ ባልዬሪ ኤል። 3. ናይት ፒ፣ ክራውዝ ኤ፣ ካዛስኪ ዲ፣ ሮዝ ኤም፣ ፍሪድል ኬ፣ ንዬቶ አር። 4. ሮዝ ኢ፣ ባካስ ቲ፣ ታሊ ኤስ፣ ኦንቤር ዲ፣ በርንሃርት ኤ፣ ፔራልታ ኤም። 5. ዳሎይዝ ኤ፣ ኦንቤር ዲ፣ ደን ኤች፣ ጋትሊንግ ጂ፣ ሾው ጄ፣ ሴሩቲ ኤም። 6. ባልዬሪ ኤስ፣ ክራውዝ ጄ፣ ሆለንቤክ ቲ፣ ማርቲን ኤም፣ በርንሃርት ጄ፣ ሃቺንሰን ኤም። 7. ባካስ ኤ፣ ደን ኦ፣ ጋትሊንግ ቲ፣ ቪዝር አር፣ ናይት ፒ፣ ሃሳን ኦ። 8. ንዬቶ ሲ፣ ታሊ ኤም፣ ፍሪድል ዲ፣ ካዛስኪ ኤ፣ ኤድዋርድስ ጄ፣ ኤንትዝሚንገር ኤም።