ታስታውሳለህን?
በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ተግባራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ሆነው አግኝተሃቸዋል? ከሆነ ቀጥሎ ባሉት ጥያቄዎች ተጠቅመህ ምን ያህሉን እንደምታስታውስ ለምን ራስህን አትፈትንም:-
◻ ሁለት ክርስቲያኖች ለመተጫጨት ከማሰባቸው በፊት ራሳቸውን ሊጠይቁ የሚገባቸው አንዳንድ ጥያቄዎች ምንድን ናቸው?
‘ስለ እርሱ ወይም ስለ እርሷ መንፈሳዊነትና ለአምላክ ያደረ ለመሆኑ ወይም ለመሆኗ እርግጠኛ ነኝን? ከእርሱ ወይም ከእርሷ ጋር አምላክን ለዘላለም ሳገለግል በዓይነ ሕሊናዬ ይታየኛል? አንዳችን የሌላውን የግል ባሕርይና ጠባይ በሚገባ አጥንተናል? እስከ ዘለቄታው ተስማምተን እንደምንቀጥል እርግጠኛ ነኝን? አንዳችን የሌላውን ያለፈ ድርጊትና አሁን ያለበትን ሁኔታ በሚገባ አውቀናል?’—8/15 ገጽ 31
◻ ኢየሱስ ለተከታዮቹ “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ” ብሎ ሲናገር ምን ማለቱ ነበር? (ማቴዎስ 5:13 1980 ትርጉም)
ተከታዮቹ ለሌሎች ሰዎች የሚያዳርሱት ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸው ስብከት የሚሰሙትን ሰዎች ጠብቆ እንደሚያቆይ በሌላ አባባል ሕይወት ሰጪ እንደሚሆንላቸው ማመልከቱ ነበር። በእርግጥም፣ የኢየሱስን ቃላት በተግባር የሚያውሉ ሰዎች በዓለም ካለው ሥነ ምግባራዊም ሆነ መንፈሳዊ ብልሽት ይጠበቃሉ።—8/15 ገጽ 32
◻ የሚጠናኑ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ከፆታ ብልግና ወጥመድ ሊርቁ የሚችሉት እንዴት ነው?
ከተቃራኒ ፆታ ጋር ተቀጣጥራችሁ የምትጫወቱ ከሆነ ከወደፊቱ የትዳር ጓደኛችሁ ጋር በአንዳንድ አጉል ሁኔታዎች ውስጥ ብቻችሁን ከመሆን መራቃችሁ ጥበብ ነው። ከሌሎች ጋር በቡድን ሆናችሁ ወይም ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ሆናችሁ መጫወቱ የተሻለ ይሆናል። አንዱ የሌላውን ስሜትና ሕሊና በማክበር በፍቅር መግለጫዎች ላይ ገደብ አብጁ።—9/1 ገጽ 17, 18
◻ ማስተዋል ምንድን ነው?
ማስተዋል አንድን ነገር በጥልቀት የመመልከትና የነገሩን ምንነት ለማወቅ የተለያዩ ክፍሎቹ እርስ በርስ ያላቸውን ግንኙነትና አጠቃላዩን ይዘት በማወቅ መዋቅሩን የመረዳት ችሎታ ነው። (ምሳሌ 4:1)—9/15 ገጽ 13
◻ ዛሬ ይሖዋ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?
በመሠረቱ ይሖዋ ከእኛ የሚፈልገው ነገር ልጁን እድንሰማ እንዲሁም ምሳሌውንና ትምህርቱን እንድንከተል ነው። (ማቴዎስ 16:24፤ 1 ጴጥሮስ 2:21)—9/15 ገጽ 22
◻ ሰላም ሊኖራቸው የሚችሉት እነማን ብቻ ናቸው?
“ሰላምን የሚሰጥ” አምላክ ይሖዋ ስለሆነ ሰላም የሚኖራቸው ለአምላክ ፍቅርና ለጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶቹ የጠለቀ አክብሮት ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው። (ሮሜ 15:33)—10/1 ገጽ 11
◻ ዮሴፍ የጲጥፋራ ሚስት ነጋ ጠባ ስትነዘንዘው አይሆንም ለማለት ያስቻለውን የሥነ ምግባር ጥንካሬ ያገኘው ከየት ነበር?
ዮሴፍ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ከጊዜያዊ ደስታ አስበልጦ ተመልክቶታል። ከዚህም ሌላ ዮሴፍ የሚመራበት መለኮታዊ ሕግ የተሰጠው ሰው ባይሆንም የሥነ ምግባር መሠረታዊ ሥርዓቶችን ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። (ዘፍጥረት 39:9)—10/1 ገጽ 29
◻ ወንድሞቻችንን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ መሆናችን ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
የአምላክን ያልተቋረጠ ይቅርታ ማግኘታችን በእጅጉ የተመካው ወንድሞቻችንን ይቅር ለማለት ባለን ፈቃደኝነት ላይ ነው። (ማቴዎስ 6:12, 14፤ ሉቃስ 11:4)—10/15 ገጽ 17
◻ ማቴዎስ 18:15-17 ላይ የሠፈረው መግለጫ የሚያመለክተው ምን ዓይነት ኃጢአትን ነው? ይህስ ምን ያመለክታል?
ኢየሱስ ኃጢአት በማለት የጠቀሰው ኃጢአት ፈጻሚውን “እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ” ሊያስቆጥር የሚችል ክብደት ያለው ስህተት ነው። አይሁዳውያን ከአሕዛብ ጋር ምንም ዓይነት ማኅበራዊ ግንኙነት አያደርጉም ነበር፤ እንዲሁም ቀረጥ ሰብሳቢዎችን ሙሉ በሙሉ ይርቋቸው ነበር። ስለዚህ ማቴዎስ 18:15-17 ላይ የሠፈረው መግለጫ የሚያመለክተው በቀላሉ ይቅር ብለህ ልትረሳው የምትችለውን ቅሬታ ወይም ቅያሜ ሳይሆን ከበድ ያሉ ኃጢአቶችን ነው። (ማቴዎስ 18:21, 22)—10/15 ገጽ 19
◻ የአምላክን ቃል ከልብ መውደድ ምን ነገርን ያጠቃልላል?
አንድ ሰው የአምላክን ቃል መውደዱ በመጽሐፉ ውስጥ ከሰፈሩት ብቃቶች ጋር ተስማምቶ እንዲኖር ይመራዋል። (መዝሙር 119:97, 101, 105) ይህም አንድ ሰው በአስተሳሰቡና በአኗኗሩ ያልተቋረጠ ማስተካከያ እንዲያደርግ ይጠይቅበታል።—11/1 ገጽ 14
◻ ከይሖዋ የተቀበልነው ነገር በጣም ብዙ ከመሆኑ የተነሣ እኛ በተራችን ለታላቁ ንጉሥና ሰጪ ለይሖዋ ምን ልንሰጥ እንችላለን?
መጽሐፍ ቅዱስ ለይሖዋ ልንሰጠው የምንችለው ከሁሉ የተሻለ ስጦታ ‘የምሥጋና መሥዋዕት’ እንደሆነ ይናገራል። (ዕብራውያን 13:15) ለምን? ይህ መሥዋዕት የሰዎችን ሕይወት ከማዳን ጋር በቀጥታ የተያያዘ በመሆኑና ይሖዋም በዚህ የፍጻሜ ዘመን እንዲሠራ የሚፈልገው ትልቅ ሥራ በመሆኑ ነው። (ሕዝቅኤል 18:23)—11/1 ገጽ 21
◻ ሰሎሞን “የጠቢባን ቃል እንደ በሬ መውጊያ ነው” ብሎ ሲጽፍ ምን ማለቱ ነው? (መክብብ 12:11)
አምላካዊ ጥበብ ያላቸው ሰዎች የሚናገሯቸው ቃላት አንባቢዎቻቸውን ወይም አድማጮቻቸውን ባነበቡት ወይም በሰሙት መሠረት እርምጃ እንዲወስዱ የመገፋፋት ኃይል አላቸው።—11/15 ገጽ 21
◻ አምላካዊ ማስተዋል ምንድን ነው?
ትክክል የሆነውን ነገር ስህተት ከሆነው ነገር ለይቶ የማወቅና ከዚያም ትክክለኛውን ጎዳና የመምረጥ ችሎታ ነው። የአምላክን ቃል ማጥናትና በሥራ ላይ ማዋል ማስተዋልን ያስገኛል።—11/15 ገጽ 25
◻ ኃላፊነቶችን ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን ሚዛኑን እንዳይስት ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? (2 ጢሞቴዎስ 3:1)
ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ መጠቀም ያስፈልጋል። ማንኛውም ሰው በይሖዋ አገልግሎት የሚያገኘውን ደስታ እስኪያጣ ድረስ ብዙ ኃላፊነቶች መቀበል የለበትም። የፈቃደኝነት መንፈስ ማሳየት የሚያስመሰግን ነው። ሆኖም የምናሳየው የፈቃደኝነት መንፈስ ልከኝነትንና “ጤናማ አስተሳሰብ”ን ማንጸባረቅ አለበት። (ቲቶ 2:12፤ ራእይ 3:15, 16)—12/1 ገጽ 28
◻ የወላጅነትን ተፈታታኝ ሁኔታ መወጣት የሚቻለው እንዴት ነው?
ወላጆች ለልጆቻቸው አርአያ፣ ጓደኛ፣ ምሥጢረኛና አስተማሪ እንዲሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይመክራል። (ዘዳግም 6:6, 7)—12/1 ገጽ 32