የእርዳታ ጥሪ
አንዲት ብራዚላዊት ሴት “አምላክ እኔን ረስቶኛል!” ስትል ጮኸች። ባሏ በድንገት በመሞቱ ከዚያ በኋላ የእርሷ ሕይወት ምንም ትርጉም እንደሌለው ተሰምቷት ነበር። እንዲህ ያለ ጭንቀት የደረሰበትን ምናልባትም የእርዳታ ጥሪ በማሰማት ላይ ያለን ሰው ለማጽናናት ሞክረህ ታውቃለህ?
አንዳንዶች በጣም ተስፋ ከመቁረጣቸው የተነሣ ሕይወታቸውን ያጠፋሉ። እንዲህ ያለውን እርምጃ ከሚወስዱት መካከል ደግሞ በርካታዎቹ ወጣቶች ናቸው። ፎልያ ዲ ሳኦ ፖሎ የተባለው ጋዜጣ በብራዚል የተደረገውን ጥናት አስመልክቶ እንደዘገበው “ራሳቸውን የሚገድሉት ወጣቶች ቁጥር 26 በመቶ ጨምሯል።” ለምሳሌ፣ በሳኦ ፖሎ የሚኖረውን ዎልተርa የተባለ ወጣት ሁኔታ ተመልከት። ዎልተር ወላጆች የሉትም፤ ቤትም ሆነ የራሱ ነጻ ጊዜ አልነበረውም። የእኔ የሚላቸው ጓደኞችም የሉትም። ከዚህ ሁሉ ሥቃይ ለመገላገል ሲል ከድልድይ ላይ ለመዝለል ወሰነ።
ኤድና የተባለች አንዲት ነጠላ እናት ከአንድ ሌላ ሰው ጋር በተዋወቀችበት ወቅት ሁለት ልጆች ነበሯት። ከአንድ ወር በኋላ በሰውዬው እናት ቤት አንድ ላይ መኖር ጀመሩ። እናትየው በመናፍስታዊ ድርጊት ከመካፈሏም በላይ የአልኮል ሱሰኛ ነበረች። ኤድና ሌላ ልጅ ከመውለዷም በተጨማሪ ከመጠን በላይ መጠጣት ጀመረች። ይህም ከባድ ጭንቀት ላይ ስለጣላት ራሷን ለመግደል ሙከራ አደረገች። በመጨረሻ ልጆቿን የማሳደግ መብቷን በፍርድ ቤት ተነጠቀች።
በዕድሜ ስለገፉት ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? ማሪያ መጫወትና ብዙ ማውራት የምትወድ ሴት ነበረች። በዕድሜ እየገፋች ስትሄድ ግን በነርስነት ሞያዋ ስህተት እሠራ ይሆናል የሚል ስጋት አደረባት። ይህም ጭንቀት ላይ ስለጣላት በግሏ የተለያዩ መድኃኒቶችን በመውሰድ እፎይታ ለማግኘት ሞክራ አልሆን ሲላት የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ጥረት አደረገች። ሕክምናው ለውጥ ያመጣላት ይመስል ነበር። ይሁን እንጂ በ57 ዓመቷ ሥራ ስታቆም ጭንቀቱ እንደገና አየለባት። ማሪያ ከዚህ ጭንቀቷ የምትገላገልበት መንገድ ፈጽሞ ስላልታያት ራሷን ስለመግደል ማሰብ ጀመረች።
“ጭንቀት ከያዛቸው ሰዎች መካከል ወደ 10 በመቶ የሚጠጉት ራሳቸውን የመግደል ሙከራ ያደርጋሉ” በማለት በሳኦ ፖሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ሆሴ አልቤርቶ ዴል ፖርቶ ተናግረዋል። “በሌሎች ከሚገደሉት ይልቅ ራሳቸውን የሚገድሉት ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ለማመን የሚያስቸግር አሳዛኝ እውነታ ነው” በማለት የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ የጤና ባለ ሥልጣን የሆኑት ዴቪድ ሳቸር ሪፖርት አድርገዋል።
አንዳንድ ጊዜ ራስን ለመግደል የሚደረገው ሙከራ ለእርዳታ የሚቀርብ ጥሪ ነው ለማለት ይቻላል። የቤተሰብ አባሎችና ጓደኞች የተጨነቀውን ሰው ለመርዳት ትክክለኛውን ነገር ማድረግ እንደሚፈልጉ ግልጽ ነው። እርግጥ “ስለ ራስህ ማዘንህን አቁም፣” “ከአንተ የባሱ ስንት አሉ” ወይም “ሁላችንም እኮ እንጨነቃለን” እንደሚሉ ያሉትን መግለጫዎች ተጠቅሞ ለማጽናናት መሞከር ምንም ፋይዳ የለውም። ከዚህ ይልቅ ለምን እውነተኛ ጓደኛና ጥሩ አድማጭ ለመሆን አትሞክርም? አዎን፣ በተስፋ መቁረጥ የተዋጠው ሰው በሕይወት የመኖርን ጥቅም እንዲገነዘብ ለመርዳት ሞክር።
ፈረንሳዊው ደራሲ ቮልቴር “በጭንቀት ተውጦ ዛሬ ሕይወቱን የሚያጠፋ ሰው አንድ ሳምንት ቢታገስ ኖሮ ለመኖር ይጓጓ ነበር” ሲል ጽፏል። ታዲያ ተስፋ የቆረጡ ሰዎች የሕይወትን ዋጋማነት ሊገነዘቡ የሚችሉት እንዴት ነው?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ወጣቶችና አዋቂዎች ራሳቸውን ይገድላሉ
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ተስፋ የቆረጠን ሰው መርዳት የምትችለው እንዴት ነው?