የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w19 ግንቦት ገጽ 14-20
  • ጥቃት የደረሰባቸውን ማጽናናት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጥቃት የደረሰባቸውን ማጽናናት
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2019
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ማጽናኛ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
  • እነማን ሊያጽናኗቸው ይችላሉ?
  • ማጽናናት የምንችለው እንዴት ነው?
  • ‘ያዘኑትን አጽናኑ’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
  • ያዘኑትን አጽናኑ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • ማጽናኛና ማበረታቻ ብዙ ገጽታዎች ያሏቸው ዕንቁዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ‘ከመጽናናት ሁሉ አምላክ’ የሚገኝ መጽናኛ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2019
w19 ግንቦት ገጽ 14-20

የጥናት ርዕስ 20

ጥቃት የደረሰባቸውን ማጽናናት (ከአራት ተከታታይ ክፍሎች አራተኛው)

“የመጽናናት ሁሉ አምላክ . . . በሚደርስብን መከራ ሁሉ ያጽናናናል።”—2 ቆሮ. 1:3, 4

መዝሙር 134 ልጆች ከአምላክ በአደራ የተሰጡ ናቸው

የትምህርቱ ዓላማa

1-2. (ሀ) ሰዎች በተፈጥሯቸው ማጽናኛ እንደሚሹና ሌሎችን የማጽናናት ችሎታ እንዳላቸው የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ። (ለ) አንዳንድ ልጆች ምን ዓይነት ጉዳት ይደርስባቸዋል?

ሰዎች በተፈጥሯቸው ማጽናኛ ይሻሉ፤ ሌሎችን የማጽናናት አስደናቂ ችሎታም አላቸው። ለምሳሌ አንድ ትንሽ ልጅ ሲጫወት ቢወድቅና ጉልበቱ ቢደማ እያለቀሰ ወደ እናቱ ወይም ወደ አባቱ መሄዱ አይቀርም። ወላጆቹ ቁስሉን ሊፈውሱለት ባይችሉም ሊያጽናኑት ይችላሉ። ምን እንደደረሰበት ሊጠይቁት፣ እንባውን ሊጠራርጉለት፣ እቅፍ አድርገው ሊያባብሉት፣ መድኃኒት ሊያደርጉለት ወይም ቁስሉን በጨርቅ ሊያስሩለት ይችላሉ። ብዙም ሳይቆይ ልጁ ማልቀሱን ሊያቆም አልፎ ተርፎም ጨዋታውን ሊቀጥል ይችላል። በጊዜ ሂደት ቁስሉም ይድናል።

2 አንዳንድ ጊዜ ግን ልጆች ከዚህ የከፋ ጉዳት ይደርስባቸዋል። አንዳንዶቹ ፆታዊ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል። ጥቃቱ አንድ ጊዜ ብቻ የተፈጸመ ወይም ለዓመታት የዘለቀ ሊሆን ይችላል። ጥቃቱ የተፈጸመው አንዴም ሆነ በተደጋጋሚ፣ በግለሰቡ ላይ ከባድ የስሜት ቁስል ማስከተሉ አይቀርም። ጥቃቱን የፈጸመው ሰው ተገቢውን ቅጣት የሚያገኝበት ጊዜ አለ፤ አንዳንድ ጊዜ ግን ከቅጣት ሊያመልጥ ይችላል። ሆኖም በጥፋተኛው ላይ አፋጣኝ የፍርድ እርምጃ ቢወሰድም እንኳ ጥቃት በተፈጸመበት ሰው ላይ የደረሰው ስሜታዊ ቁስል ለበርካታ ዓመታት ላይሽር ይችላል።

3. በ2 ቆሮንቶስ 1:3, 4 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ በጎቹ ምን እንዲያገኙ ይፈልጋል? የትኞቹን ጥያቄዎችስ እንመረምራለን?

3 በልጅነቱ ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመበት አንድ ክርስቲያን፣ አዋቂ ከሆነ በኋላም ጥቃቱ ካስከተለበት የስሜት ሥቃይ ጋር የሚታገል ከሆነ ምን ሊረዳው ይችላል? (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4⁠ን አንብብ።) ይሖዋ በጎቹ ተገቢውን ፍቅርና ማጽናኛ እንዲያገኙ እንደሚፈልግ ግልጽ ነው። ከዚህ አንጻር የሚከተሉትን ሦስት ጥያቄዎች እንመርምር፦ (1) በልጅነታቸው ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው ሰዎች ማጽናኛ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? (2) እነዚህን ሰዎች እነማን ሊያጽናኗቸው ይችላሉ? (3) ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸውን ሰዎች ውጤታማ በሆነ መንገድ ማጽናናት የምንችለው እንዴት ነው?

ማጽናኛ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

4-5. (ሀ) ልጆች ከአዋቂዎች የተለዩ እንደሆኑ መገንዘባችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ፆታዊ ጥቃት፣ አንድ ልጅ ለሌሎች ባለው አመለካከት ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል?

4 በልጅነታቸው ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው አንዳንድ ሰዎች አዋቂ ከሆኑ በኋላም እንኳ ማጽናኛ ማግኘት ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ለምን? ይህን ለመረዳት በቅድሚያ ልጆች ከአዋቂዎች በጣም የተለዩ እንደሆኑ መገንዘብ ይኖርብናል። አብዛኛውን ጊዜ፣ አንድ በደል በልጆች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ በአዋቂዎች ላይ ከሚያሳድረው ተጽዕኖ የተለየ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

5 ልጆች ከሚያሳድጓቸውና ከሚንከባከቧቸው ሰዎች ጋር የቀረበ ዝምድና መመሥረትና በእነሱ ላይ እምነት መጣል ያስፈልጋቸዋል። እንዲህ ያለው ዝምድና፣ ልጆች የደህንነት ስሜት እንዲሰማቸውና ፍቅር የሚያሳያቸውን ሰው ማመን ቀላል እንዲሆንላቸው ያደርጋል። (መዝ. 22:9) የሚያሳዝነው ግን አብዛኛውን ጊዜ ፆታዊ ጥቃት የሚፈጸመው በቤት ውስጥ ሲሆን ጥቃቱን የሚፈጽሙት፣ የቤተሰብ አባላት ወይም ለቤተሰቡ ቅርብ የሆኑ ሌሎች ሰዎች ናቸው። በሚያምነው ሰው እንዲህ ያለ በደል የተፈጸመበት ልጅ፣ ዓመታት ካለፉ በኋላም እንኳ ሌሎችን ለማመን ሊቸገር ይችላል።

6. ፆታዊ ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል የጭካኔ ድርጊት ነው የምንለው ለምንድን ነው?

6 ልጆች ራሳቸውን ከጥቃት መከላከል አይችሉም። ፆታዊ ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል የጭካኔ ድርጊት ነው። ልጆች በጋብቻ ውስጥ ለሚደረገው የፆታ ግንኙነት በአካል፣ በስሜት ወይም በአእምሮ ዝግጁ ከመሆናቸው ከብዙ ዓመታት በፊት ፆታዊ ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ መደረጋቸው ከባድ ጉዳት ያስከትላል። ፆታዊ ጥቃት ልጆች ለፆታ ግንኙነት፣ ለራሳቸው እንዲሁም ሊቀርባቸው ለሚፈልግ ማንኛውም ሰው ያላቸውን አመለካከት ክፉኛ ሊያዛባው ይችላል።

7. (ሀ) ሕፃናትን የሚያስነውር መሠሪ ሰው ልጆችን በቀላሉ ማታለል የሚችለው ለምንድን ነው? ምን በማለትስ ሊያታልላቸው ይችላል? (ለ) እንዲህ ያሉት ውሸቶች ምን ውጤት ሊያስከትሉ ይችላሉ?

7 ልጆች የማሰብ፣ የማመዛዘን ወይም አደጋ የሚፈጥሩ ሁኔታዎችን አውቆ ከእነዚህ የመራቅ ችሎታቸው ሙሉ በሙሉ አልጎለበተም። (1 ቆሮ. 13:11) በመሆኑም ሕፃናትን የሚያስነውሩ መሠሪ ሰዎች በቀላሉ ሊያታልሏቸው ይችላሉ። እነዚህ ሰዎች ለልጆቹ አደገኛ ውሸቶችን በመንገር ሊያታልሏቸው ይሞክራሉ፤ ለምሳሌ ጥፋተኞቹ ልጆቹ ራሳቸው እንደሆኑ፣ የተፈጠረውን ነገር ለማንም መናገር እንደሌለባቸው፣ ቢናገሩም እንኳ የሚሰማቸው ወይም ግድ የሚሰጠው አንድም ሰው እንደማይኖር አሊያም በአንድ ልጅና በአንድ አዋቂ መካከል የሚፈጸመው እንዲህ ያለው ድርጊት ምንም ስህተት እንደሌለውና ተገቢ የፍቅር መግለጫ እንደሆነ ይነግሯቸው ይሆናል። ልጆቹ የተነገራቸው ነገር ውሸት እንደሆነ የሚያውቁት ከበርካታ ዓመታት በኋላ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያሉ ውሸቶች የተነገሯቸው ልጆች ንጽሕናቸው እንደጎደፈ፣ ምንም እንደማይጠቅሙ፣ የሚወዳቸው ሰው እንደሌለ ወይም ማጽናኛ ማግኘት እንደማይገባቸው ሊሰማቸው ይችላል።

8. ይሖዋ የተጎዱትን እንደሚያጽናና እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

8 እስካሁን ከተመለከትናቸው ነጥቦች አንጻር ፆታዊ ጥቃት ዘላቂ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑ ምንም አያስገርምም። ይህ ድርጊት ምንኛ ጭካኔ የሚንጸባረቅበት ነው! በልጆች ላይ የሚፈጸመው ፆታዊ ጥቃት እንደ ወረርሽኝ መስፋፋቱ በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ እንደምንኖር የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ነው፤ በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ ሰዎች “ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው” እንደሚሆኑ እንዲሁም “ክፉ ሰዎችና አስመሳዮች . . . በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ” እንደሚሄዱ አስቀድሞ ተነግሯል። (2 ጢሞ. 3:1-5, 13) ሰይጣን የሚጠቀምባቸው ዘዴዎች በክፋት የተሞሉ ናቸው፤ ሰዎች ዲያብሎስን የሚያስደስት ድርጊት መፈጸማቸው እንዴት የሚያሳዝን ነው! ሆኖም ይሖዋ ከሰይጣንም ሆነ ከእሱ አገልጋዮች ይበልጥ ኃያል ነው። ደግሞም ሰይጣን የሚጠቀምባቸውን ዘዴዎች ጠንቅቆ ያውቃል። በመሆኑም ይሖዋ የሚደርስብንን ሥቃይ በሚገባ እንደሚረዳና አስፈላጊውን ማጽናኛ እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” የሆነውን ይሖዋን በማምለካችን በጣም ታድለናል፤ “በማንኛውም ዓይነት መከራ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ማጽናናት እንድንችል እሱ በሚደርስብን መከራ ሁሉ ያጽናናናል።” (2 ቆሮ. 1:3, 4) ይሁንና ይሖዋ እኛን ለማጽናናት በእነማን ሊጠቀም ይችላል?

እነማን ሊያጽናኗቸው ይችላሉ?

9. በመዝሙር 27:10 ላይ እንደተገለጸው፣ ወላጆቻቸው ተገቢውን እንክብካቤ ላላደረጉላቸው ሰዎች ይሖዋ ምን ያደርግላቸዋል?

9 በተለይም ፆታዊ ጥቃት ተፈጽሞባቸው ወላጆቻቸው ችላ ያሏቸው ወይም በሚቀርቧቸው ሰዎች ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው ልጆች ማጽናኛ ያስፈልጋቸዋል። መዝሙራዊው ዳዊት፣ ከሁሉ የላቀው የመጽናኛ ምንጭ ይሖዋ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። (መዝሙር 27:10⁠ን አንብብ።) ይሖዋ በሚወዷቸው ሰዎች በደል የተፈጸመባቸውን ሁሉ እንደሚቀበል ዳዊት እምነት ነበረው። ይሖዋ እንዲህ የሚያደርገው እንዴት ነው? በታማኝ አገልጋዮቹ አማካኝነት ነው። ከእኛ ጋር አብረው ይሖዋን የሚያገለግሉ የእምነት ባልንጀሮቻችን፣ መንፈሳዊ ቤተሰቦቻችን ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ አብረውት ይሖዋን የሚያገለግሉ ሰዎችን ወንድሞቼ፣ እህቶቼና እናቶቼ በማለት ጠርቷቸዋል።—ማቴ. 12:48-50

10. ሐዋርያው ጳውሎስ ሽማግሌ በመሆን የሚያከናውነውን አገልግሎት በተመለከተ ምን ብሏል?

10 የክርስቲያን ጉባኤ ልክ እንደ ቤተሰብ እንደሆነ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ እንመልከት። ሐዋርያው ጳውሎስ ትጉና ታማኝ ሽማግሌ ነበር። ለሌሎች ግሩም ምሳሌ የነበረ ከመሆኑም በላይ እሱ የክርስቶስን አርዓያ እንደተከተለ ሁሉ ሌሎችም የእሱን አርዓያ እንዲከተሉ በመንፈስ መሪነት ማበረታቻ ሰጥቷል። (1 ቆሮ. 11:1) ጳውሎስ ሽማግሌ በመሆን የሚያከናውነውን አገልግሎት በተመለከተ በአንድ ወቅት እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “የምታጠባ እናት ልጆቿን በፍቅር እንደምትንከባከብ እኛም በመካከላችሁ በነበርንበት ጊዜ በገርነት ተንከባከብናችሁ።” (1 ተሰ. 2:7) በዛሬው ጊዜ ያሉ ታማኝ ሽማግሌዎችም ለተጎዱት ቅዱስ ጽሑፋዊ ማጽናኛ ለመስጠት ደግነትና ገርነት የተንጸባረቀባቸው ቃላት ይጠቀማሉ።

አንዲት የጎለመሰች እህት፣ ስሜታዊ ሥቃይ የደረሰባትን እህት ስታጽናና

የጎለመሱ እህቶች ሌሎችን በማጽናናት ረገድ አብዛኛውን ጊዜ በጣም ውጤታማ ናቸው (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት)c

11. ሌሎችን የማጽናናት ኃላፊነት ያለባቸው ሽማግሌዎች ብቻ እንዳልሆኑ የሚያሳየው ምንድን ነው?

11 ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸውን ሰዎች የማጽናናት ኃላፊነት ያለባቸው ሽማግሌዎች ብቻ ናቸው? አይደሉም። እያንዳንዱ ክርስቲያን “ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጽናኑ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ የማድረግ ኃላፊነት አለበት። (1 ተሰ. 4:18) በተለይም በመንፈሳዊ የጎለመሱ እህቶች፣ ማጽናኛ የሚያስፈልጋቸውን እህቶች ሊያጽናኗቸው ይችላሉ። ይሖዋ አምላክ ራሱን ልጇን ከምታጽናና እናት ጋር ማመሳሰሉ የተገባ ነው። (ኢሳ. 66:13) መጽሐፍ ቅዱስ በጭንቀት የተዋጡ ሰዎችን ስላጽናኑ ሴቶች ይናገራል። (ኢዮብ 42:11) በዛሬው ጊዜም ይሖዋ ስሜታዊ ሥቃይ ያለባቸውን እህቶቻቸውን ለማጽናናት የሚሞክሩ ክርስቲያን ሴቶችን ሲያይ ምንኛ ይደሰት ይሆን! አንዳንድ ጊዜ ሽማግሌዎች በመንፈሳዊ የጎለመሰችን አንዲት እህት ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባትን እህት እንድታጽናና በጥበብ ሊጠይቋት ይችላሉ።b

ማጽናናት የምንችለው እንዴት ነው?

12. ምን ከማድረግ መቆጠብ ይኖርብናል?

12 እርግጥ ነው፣ የእምነት ባልንጀራችን ሚስጥር አድርጎ መያዝ የሚፈልጋቸውን ነገሮች ለማውጣጣት እንዳንሞክር መጠንቀቅ አለብን። (1 ተሰ. 4:11) ታዲያ እርዳታና ማጽናኛ የሚያስፈልጋቸውን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? ሌሎችን ማጽናናት የምንችልባቸውን አምስት ቅዱስ ጽሑፋዊ መንገዶች እስቲ እንመልከት።

13. በ1 ነገሥት 19:5-8 ላይ እንደተገለጸው፣ የይሖዋ መልአክ ለኤልያስ ምን አድርጎለታል? እኛስ የእሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

13 ተግባራዊ እርዳታ ስጡ። ነቢዩ ኤልያስ ሕይወቱን ለማትረፍ እየሸሸ በነበረበት ወቅት በጣም ተስፋ ከመቁረጡ የተነሳ ሞቱን ተመኝቶ ነበር። በዚህ ጊዜ ይሖዋ በሐዘን የተደቆሰውን አገልጋዩን ለማበረታታት አንድ ኃያል መልአክ ላከ። መልአኩም ለኤልያስ ተግባራዊ የሆነ እርዳታ ሰጠው። ትኩስ ምግብ ካቀረበለት በኋላ እንዲበላ አበረታታው። (1 ነገሥት 19:5-8⁠ን አንብብ።) ይህ ዘገባ አንድ ጠቃሚ እውነት ያስተምረናል፦ አንዳንድ ጊዜ፣ ቀላል የሚመስል የደግነት ተግባር ማከናወናችን ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ሻይ ቡና እንደማለት፣ ምግብ እንደመጋበዝ እንዲሁም አነስ ያለ ስጦታ ወይም አሳቢነታችንን የሚገልጽ ካርድ እንደመስጠት ያሉ ቀላል የሚመስሉ ነገሮች ተስፋ የቆረጠ ወንድማችንን ሊያበረታቱት ብሎም እንደምንወደውና እንደምናስብለት ሊያረጋግጡለት ይችላሉ። ያጋጠሙትን አሳዛኝ ሁኔታዎች አንስተን ከእሱ ጋር ማውራት ቢከብደን እንኳ እንዲህ ባሉ መንገዶች ተግባራዊ እርዳታ ልንሰጠው እንችላለን።

14. ስለ ኤልያስ ከሚናገረው ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን?

14 በጭንቀት የተዋጡ ሰዎች የደህንነት ስሜት እንዲሰማቸውና ዘና እንዲሉ አድርጉ። ስለ ኤልያስ ከሚናገረው ዘገባ ሌላም የምናገኘው ትምህርት አለ። ይሖዋ ይህ ነቢይ እስከ ኮሬብ ተራራ ድረስ መሄድ እንዲችል ተአምራዊ በሆነ መንገድ ረድቶታል። ይሖዋ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን የገባው በዚህ ስፍራ ነበር፤ በመሆኑም ኤልያስ ወደዚህ ገለልተኛ ስፍራ መሄዱ የደህንነት ስሜት እንዲሰማው አድርጎት ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ሊጎዱት የሚፈልጉ ሰዎች ጨርሶ ሊያገኙት እንደማይችሉ ተሰምቶት ይሆናል። ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸውን ሰዎች ለማጽናናት በቅድሚያ የደህንነት ስሜት እንዲሰማቸው ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ሽማግሌዎች ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባት አንዲት እህት ከስብሰባ አዳራሽ ይልቅ ቤት ውስጥ ሻይ ቡና እያለች ማውራት ልትመርጥ እንደምትችል ማስታወስ ይኖርባቸዋል። ሌሎች ደግሞ ስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ቢሆኑ ይበልጥ ዘና ሊሉ ይችላሉ።

ሁለት ሽማግሌዎች ስሜታዊ ሥቃይ የደረሰባትን እህት ሲያጽናኑ፤ ይህች እህት በመንፈሳዊ የጎለመሰች ሌላ እህት አብራት እንድትገኝ አድርጋለች

በትዕግሥት በማዳመጥ፣ ልባዊ ጸሎት በማቅረብና የሚያጽናኑ ቃላትን መርጠን በመናገር ሌሎችን መፈወስ እንችላለን (ከአንቀጽ 15-20⁠ን ተመልከት)d

15-16. ጥሩ አድማጭ መሆን ምን ነገሮችን ይጨምራል?

15 ጥሩ አድማጭ ሁኑ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየ . . . መሆን አለበት” የሚል ቀጥተኛ ምክር ይሰጣል። (ያዕ. 1:19) ጥሩ አድማጭ ናችሁ? አንዳንዶች ጥሩ አድማጭ መሆን ሲባል ምንም ነገር ሳይናገሩ ግለሰቡን ዓይን ዓይኑን እያዩ ከማዳመጥ ያለፈ ነገርን እንደማይጠይቅ ሊሰማቸው ይችላል። እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው። ለምሳሌ ኤልያስ መጨረሻ ላይ ጭንቀቱን ሁሉ አውጥቶ ሲናገር ይሖዋ በጥሞና አዳምጦታል። ኤልያስ እንደፈራ፣ ብቸኝነት እንደተሰማውና ልፋቱ መና እንደቀረ አድርጎ እንዳሰበ ይሖዋ አስተውሏል። በመሆኑም እነዚህን አሉታዊ ስሜቶች አንድ በአንድ እንዲያሸንፍ ረድቶታል። በዚህ መንገድ ኤልያስን በጥሞና እንዳዳመጠው አሳይቷል።—1 ነገ. 19:9-11, 15-18

16 ሌሎችን በምናዳምጥበት ጊዜ፣ አዘኔታና ርኅራኄ በማሳየት ፍቅራችንን መግለጽ የምንችለው እንዴት ነው? አንዳንድ ጊዜ፣ አሳቢነት የሚንጸባረቅባቸው ጥቂት የተመረጡ ቃላትን መናገራችን ብቻ ስሜታችንን ሊገልጽ ይችላል። ለምሳሌ እንዲህ ልትሉ ትችላላችሁ፦ “የደረሰብህ ነገር በጣም ያሳዝናል! በየትኛውም ልጅ ላይ እንዲህ ያለ ግፍ ሊፈጸም አይገባም!” ምናልባትም በጭንቀት የተዋጠው ወንድማችሁ የተናገረውን ነገር እንደተረዳችሁለት ለማረጋገጥ አንድ ወይም ሁለት ጥያቄዎችን ልትጠይቁት ትችላላችሁ። ለምሳሌ “ምን ማለትህ እንደሆነ ልታስረዳኝ ትችላለህ?” አሊያም “እንዲህ ስትል እኔ የገባኝ እንደዚህ ነው። በትክክል ተረድቼሃለሁ?” በማለት ልትጠይቁት ትችላላችሁ። እንዲህ ያሉት ፍቅር የሚንጸባረቅባቸው አገላለጾች ግለሰቡ በጥሞና እያዳመጣችሁት እንዳላችሁና ስሜቱን መረዳት እንደምትፈልጉ እንዲገነዘብ ሊያደርጉት ይችላሉ።—1 ቆሮ. 13:4, 7

17. ትዕግሥተኞችና ‘ለመናገር የዘገየን’ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

17 ሆኖም ምንጊዜም ‘ለመናገር የዘገያችሁ’ መሆን እንዳለባችሁ አስታውሱ። ግለሰቡ ሲናገር አቋርጣችሁ ምክር ለመስጠት ወይም አመለካከቱን ለማስተካከል አትሞክሩ። እንዲሁም ትዕግሥተኞች ሁኑ! ኤልያስ የተሰማውን ሁሉ አውጥቶ ለይሖዋ በተናገረበት ወቅት ምሬቱን የሚገልጹ ጠንካራ ቃላት ተጠቅሟል። ይሖዋ እምነቱ እንዲጠናከር ሊረዳው ከሞከረ በኋላም ኤልያስ እነዚያኑ ቃላት ተጠቅሞ ስሜቱን ገልጿል። (1 ነገ. 19:9, 10, 13, 14) ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? አንዳንድ ጊዜ፣ በጭንቀት የተዋጡ ሰዎች ስሜታቸውን ደጋግመው መግለጽ ሊፈልጉ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ ልክ እንደ ይሖዋ በትዕግሥት ልናዳምጣቸው ይገባል። የመፍትሔ ሐሳብ ለማቅረብ ከመሞከር ይልቅ አዘኔታና ርኅራኄ ለማሳየት ጥረት እናደርጋለን።—1 ጴጥ. 3:8

አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ስሜታዊ ሥቃይ ከደረሰባት እህት ጋር አብሮ ሲጸልይ፤ ሌላ ሽማግሌና የጎለመሰች እህት አብረው ተገኝተዋል

18. የምናቀርበው ጸሎት በጭንቀት የተዋጡ ሰዎችን ሊያጽናና የሚችለው እንዴት ነው?

18 በጭንቀት ከተዋጠው ግለሰብ ጋር አብራችሁ ልባዊ ጸሎት አቅርቡ። መንፈሱ የተደቆሰ ሰው መጸለይ ሊከብደው ይችላል። ምናልባትም ወደ ይሖዋ ለመጸለይ ብቁ እንዳልሆነ ይሰማው ይሆናል። እንዲህ ያለውን ሰው ለማጽናናት አብረነው በመሆን ስሙን ጠቅሰን ልንጸልይ እንችላለን። በጸሎታችን ላይ፣ እኛም ሆንን ጉባኤው ይህን ግለሰብ ምን ያህል እንደምንወደው ልንገልጽ እንዲሁም ይሖዋ ውድ የሆነውን በጉን እንዲያረጋጋውና እንዲያጽናናው ልንለምን እንችላለን። እንዲህ ያሉት ጸሎቶች ግለሰቡን በእጅጉ ሊያጽናኑት ይችላሉ።—ያዕ. 5:16

19. ሌሎችን የሚያጽናኑ ቃላትን ለመምረጥ ምን ሊረዳን ይችላል?

19 ሊፈውሱና ሊያጽናኑ የሚችሉ ቃላትን ምረጡ። ከመናገራችሁ በፊት አስቡ። ሳይታሰብባቸው የሚነገሩ ቃላት ሊጎዱ ይችላሉ። ደግነት የተንጸባረቀባቸው ቃላት ደግሞ የመፈወስ ኃይል አላቸው። (ምሳሌ 12:18) በመሆኑም ሊያጽናኑ፣ ሊያበረታቱና ሊያረጋጉ የሚችሉ ቃላትን መምረጥ እንድትችሉ ይረዳችሁ ዘንድ ወደ ይሖዋ ጸልዩ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት ይሖዋ ራሱ ከተናገራቸው ቃላት የበለጠ ኃይል ያላቸው ቃላት ሊኖሩ እንደማይችሉ አስታውሱ።—ዕብ. 4:12

20. አንዳንዶች በተፈጸመባቸው ጥቃት የተነሳ ምን ብለው ሊያስቡ ይችላሉ? እኛስ የትኛውን እውነታ ልናስታውሳቸው ይገባል?

20 ከዚህ በፊት ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው አንዳንድ ሰዎች እንደቆሸሹ፣ ዋጋ ቢስ እንደሆኑና ማንም እንደማይወዳቸው ሊሰማቸው ይችላል። ሆኖም ይህ ፈጽሞ ከእውነታው የራቀ ነው! በመሆኑም ቅዱሳን መጻሕፍትን ተጠቅማችሁ በይሖዋ ፊት ምን ያህል ከፍተኛ ዋጋ እንዳላቸው እንዲገነዘቡ እርዷቸው። (“ቅዱሳን መጻሕፍት የሚሰጡት ማጽናኛ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ነቢዩ ዳንኤል አዝኖና ተስፋ ቆርጦ በነበረበት ጊዜ መልአኩ እንዴት በደግነት እንዳበረታታው አስታውሱ። ይሖዋ ይህ አገልጋዩ በእሱ ፊት ምን ያህል ውድ እንደሆነ እንዲገነዘብ ፈልጎ ነበር። (ዳን. 10:2, 11, 19) በደል የተፈጸመባቸው ወንድሞቻችንና እህቶቻችንም በይሖዋ ፊት በጣም ውድ ናቸው!

ቅዱሳን መጻሕፍት የሚሰጡት ማጽናኛ

ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸውን ሰዎች በማጽናናት ረገድ ውጤታማ ሆነው የተገኙት የትኞቹ ጥቅሶች ናቸው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ የሚያጽናኑ ጥቅሶች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ መካከል የተወሰኑት በዚህ ርዕስ ላይ ተጠቅሰዋል። እነዚህን ጥቅሶች ሌሎችን ለመርዳት ልንጠቀምባቸው የምንችለው እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ ሐሳቦች ከእያንዳንዱ ጥቅስ ሥር ቀርበዋል።

አንዲት እህት መጽሐፍ ቅዱስ ስታነብ

ኢዮብ 34:22-28

ፆታዊ ጥቃት የሚፈጽሙ አንዳንድ ሰዎች ከቅጣት የሚያመልጡ ሊመስሉ ይችላል። ሆኖም በደል የተፈጸመባቸው ሰዎች የሚያሰሙትን ጩኸት ከሚያዳምጠው ከይሖዋ ፈጽሞ ሊሰወሩ አይችሉም። የፍትሕ አምላክ በሆነው በይሖዋ መታመናችን ውስጣዊ ሰላም እንዲኖረን ይረዳናል።

መዝሙር 62:8

“ይህ ጥቅስ እንደሚያበረታታው፣ ልቤን በይሖዋ ፊት በማፍሰስ እንዲያጽናናኝ እንዲሁም ውስጤን እንዲያረጋጋልኝ ለመንኩት። አዘውትሬ ወደ ይሖዋ መጸለዬ ቀስ በቀስ እውነተኛ መጽናኛና ውስጣዊ ሰላም እንዳገኝ ረድቶኛል።”—የዘጠኝ ዓመት ገደማ ልጅ ሳለ ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመበት የጉባኤ ሽማግሌ።—መዝሙር 56:8-13⁠ንም ተመልከት።

ኢሳይያስ 41:10, 13

እነዚህ ጥቅሶች ይሖዋ ልጆቹን ከአደጋ እንደሚጠብቅ አፍቃሪ አባት እንደሆነና ለአገልጋዮቹ በችግራቸው ጊዜ እንደሚደርስላቸው ያሳያሉ። ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸውን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ያሉ የአምላክ ሕዝቦች ይህ እውነት መሆኑን በገዛ ሕይወታቸው ተመልክተዋል።

ኢሳይያስ 32:1, 2

“የሽማግሌዎችን እርዳታ ጠየቅኩ። እነሱም ጊዜ ወስደው በተደጋጋሚ አነጋግረውኛል። ከልብ እንደሚያስቡልኝ ያሳዩኝ ከመሆኑም ሌላ በጥሞና አዳምጠውኛል። አብረውኝ ጸልየዋል፤ በግላቸውም ቢሆን ጸልየውልኛል።”—የስድስት ዓመት ገደማ ልጅ ሳለች ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባት እህት

1 ቆሮንቶስ 13:4, 7

ከዚህ በፊት ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመበት ሰው፣ ስለደረሰበት ነገር ሲነግራችሁ እነዚህን ጥቅሶች ለማስታወስ ሞክሩ። የሚናገረውን ነገር ለማመን እንደተቸገራችሁ ወይም ጥርጣሬ እንዳደረባችሁ የሚያሳዩ አገላለጾችን ከመጠቀም ተቆጠቡ። በልጆች ላይ ፆታዊ ጥቃት የሚፈጽሙ በርካታ ሰዎች፣ ልጆቹ ስለ ጉዳዩ ቢናገሩ ማንም እንደማያምናቸው ይነግሯቸዋል። አብዛኞቹ ልጆች ይህ እውነት እንደሆነ ያስባሉ። በመሆኑም የእምነት ባልንጀራችሁ የደረሰበት ነገር ካስከተለበት የስሜት ሥቃይ ጋር እየታገለ እንደሆነ በመገንዘብ እሱን ለማጽናናት የቻላችሁትን ሁሉ አድርጉ።

2 ቆሮንቶስ 10:4, 5

ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው ልጆች አንዳንድ ውሸቶችን እውነት እንደሆኑ አድርገው ማሰብ ሊጀምሩ ይችላሉ፤ በመንፈስ መሪነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ግን ሥር የሰደዱ ሰይጣናዊ ውሸቶችን እንኳ ነቅሎ ለመጣል ያስችላል።

1 ዮሐንስ 3:19, 20

ልባችን አላግባብ በሚኮንነን ጊዜ ይሖዋ “ከልባችን ይልቅ ታላቅ” እንደሆነና “ሁሉንም ነገር [እንደሚያውቅ]” ማስታወስ ይኖርብናል። ቃሉ በአምላክ ፊት ውድ ዋጋ እንዳለን ያረጋግጥልናል።

ወደ ይሖዋ ቅረብ የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 24 ተመልከት።

21. ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች ሁሉ ምን ይጠብቃቸዋል? እስከዚያው ድረስ ግን ሁላችንም ምን ለማድረግ ቆርጠናል?

21 ሌሎችን ስናጽናና ይሖዋ እንደሚወዳቸው እንዲያስታውሱ እንረዳቸዋለን። ደግሞም ይሖዋ የፍትሕ አምላክ እንደሆነ ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም። ከእሱ ሊሰወር የሚችል ምንም ዓይነት የክፋት ድርጊት የለም። ይሖዋ ሁሉንም ነገር የሚያይ ሲሆን ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች የእጃቸውን እንዲያገኙ ያደርጋል። (ዘኁ. 14:18) እስከዚያው ድረስ ግን፣ ፆታዊ ጥቃት ለተፈጸመባቸው ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ፍቅራችንን ለማሳየት የምንችለውን ሁሉ እናድርግ። ይሖዋ በሰይጣንም ሆነ እሱ በሚገዛው ዓለም በደል የተፈጸመባቸውን ሁሉ ለዘለቄታው እንደሚፈውሳቸው ማወቅ ምንኛ የሚያጽናና ነው! በቅርቡ፣ ሥቃይ የሚያስከትሉብን መጥፎ ትዝታዎች በሙሉ ዳግመኛ የማይታወሱበት ጊዜ ይመጣል።—ኢሳ. 65:17

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • በልጅነታቸው ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው ሰዎች ዓመታት ካለፉ በኋላም ማጽናኛ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

  • ማጽናኛ የሚያስፈልጋቸውን የማጽናናት ኃላፊነት ያለባቸው እነማን ናቸው?

  • ሌሎችን ማጽናናት የምንችልባቸው ውጤታማ ዘዴዎች የትኞቹ ናቸው?

መዝሙር 109 አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ

a በልጅነታቸው ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው ሰዎች፣ ዓመታት ካለፉ በኋላም እንኳ ጥቃቱ ካስከተለባቸው የስሜት ሥቃይ ጋር መታገል ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ይህ የሆነበት ምክንያት በዚህ ርዕስ ውስጥ ይብራራል። በተጨማሪም ይህ ርዕስ እንዲህ ያለ በደል የተፈጸመባቸውን ሰዎች ማጽናናት የሚችሉት እነማን እንደሆኑ ይገልጻል። በመጨረሻም፣ በልጅነታቸው ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሰዎች ማጽናናት የምንችልባቸውን አንዳንድ ውጤታማ መንገዶች እንመለከታለን።

b ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመበት ግለሰብ የባለሙያ እርዳታ ማግኘት ከፈለገ ይህ የግል ውሳኔው ነው።

c የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት የጎለመሰች እህት፣ በጭንቀት የተዋጠችን እህት ስታጽናና።

d የሥዕሉ መግለጫ፦ ሁለት ሽማግሌዎች በጭንቀት የተዋጠችውን እህት ሲያነጋግሩ። ይህች እህት፣ የጎለመሰችውን እህት አብራት እንድትሆን ጠርታታለች።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ